በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያኖች ትሕትናን ማዳበር ያለባቸው ለምንድን ነው?

ክርስቲያኖች ትሕትናን ማዳበር ያለባቸው ለምንድን ነው?

ክርስቲያኖች ትሕትናን ማዳበር ያለባቸው ለምንድን ነው?

ትሕትና ኩራተኛ ወይም ዕብሪተኛ አለመሆን ማለት ነው። ትሕትና ድክመት ሳይሆን ይሖዋ ደስ የሚሰኝበት ባሕርይ  ነው።

አንድ ሰው ከአምላክና ከሰዎች ጋር ያለውን ዝምድና በመጽሐፍ ቅዱስ በሠፈረው መሠረት በመመዘንና የተማራቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ የትሕትናን ባሕርይ ሊላበስ ይችላል። “ራስህን ዝቅ አድርግ” ተብሎ የተተረጎመው ሂዝራፕፔስ የተሰኘው የዕብራይስጥ ቃል ቀጥተኛ ፍቺ “ራስህን ወደታች እርገጥ” የሚል ነው። ይህም ጠቢቡ የምሳሌ ጸሐፊ የጠቀሰውን ድርጊት ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው:- “ልጄ ሆይ፣ ለጎረቤትህ ዋስ ብትሆን፣ . . . በአፍህ ቃል ተጠመድህ፤ . . . በጎረቤትህ እጅ ወድቀሃልና፤ ፈጥነህ ሂድ [ራስህን ወደታች እርገጥ]፣ ጎረቤትህንም ነዝንዘው። . . . ትድን ዘንድ።” (ምሳሌ 6:1-5) በሌላ አባባል ኩራትህን አስወግድ፣ ስተትህን እመን፣ ነገሮችን አስተካክልና ይቅርታ ጠይቅ ማለቱ ነው። ኢየሱስ አንድ ሰው ልክ እንደ ሕፃን ልጅ በአምላክ ፊት ራሱን ዝቅ እንዲያደርግና ከሌሎች ልቆ ለመታየት ከመሞከር ይልቅ የወንድሞቹ አገልጋይ እንዲሆን መክሯል።—ማቴዎስ 18:4፤ 23:12

ክርስቲያኖች ትሕትናን ማዳበር አለባቸው

ሐዋርያው ጳውሎስ “የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው” እንዲለብሱ ለክርስቲያን ባልደረቦቹ ምክር በለገሰ ጊዜ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ።” (ቆላስይስ 3:10, 12፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ክርስቶስ ያሳየውን ግሩም ምሳሌ ከጠቀሰ በኋላ “[የአምላክ አገልጋይ የሆነ] ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቊጠር” በማለት አሳስቧል። (ፊልጵስዩስ 2:3) እንዲህ በማለትም ተማጽኗል:- “እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፣ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ።”—ሮሜ 12:16

ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከተማ ለሚገኙ ክርስቲያኖች የሚከተለውን የጻፈው ተመሳሳይ ነገር በአእምሮው ይዞ ነበር:- “ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ። አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፣ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፣ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፤ ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፣ ያለ እግዚአብሔር ሕግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፣ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደ ሌለኝ ሆንሁ፤ ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ።” (1 ቆሮንቶስ 9:19-22) ይህን ለማድረግ ከልብ ትሑት መሆን ያስፈልጋል።

ሰላምን ያሰፍናል። ትሕትና ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል። ትሑት የሆነ ሰው “መብቴ ነው” የሚለውን ነገር ለማስጠበቅ ሲል ከክርስቲያን ወንድሞቹ ጋር አይጣላም። ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉን ለማድረግ ነፃነት የነበረው ቢሆንም እንኳን ሌሎችን የሚያንጽ ነገር ብቻ ያደርግ ነበር። የሚያከናውነው ነገር የአንድን ወንድም ሕሊና የሚረብሽ ሆኖ ካገኘው ያንን ድርጊት እርግፍ አድርጎ ይተወው ነበር።—ሮሜ 14:19-21፤ 1 ቆሮንቶስ 8:9-13፤ 10:23-33

በተጨማሪም ሌሎች በእኛ ላይ የሠሩትን ኃጢአት ይቅር እንድንል ኢየሱስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ሰላምን ለመጠበቅ ትሕትና ትልቅ ድርሻ ያበረክታል። (ማቴዎስ 6:12-15፤ 18:21, 22) እንዲሁም አንድ ሰው ሌላን በሚበድልበት ጊዜ ወደ በደለው ሰው ዘንድ ሄዶ ስህተቱን እንዲያምንና ይቅርታ እንዲጠይቅ የሚያዘውን ትእዛዝ ተግባራዊ ማድረግ ትሕትናውን ይፈትናል። (ማቴዎስ 5:23, 24) ወይም የተጎዳው ግለሰብ ወደ እርሱ በሚመጣበት ጊዜ ስህተቱን አምኖ የተፈጠረውን ችግር ወዲያው እንዲያስተካክል ሊረዳው የሚችለው በፍቅር የታገዘ ትሕትና ብቻ ነው። (ማቴዎስ 18:15፤ ሉቃስ 17:3፤ ከዘሌዋውያን 6:1-7 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው የትሕትና ባሕርይ ከሚያስከትለው የኃፍረት ስሜት ይልቅ ለግለሰቡም ሆነ ለድርጅቱ የሚያመጣው ሰላም የላቀ ይሆናል። እንዲሁም የወሰደው የትሕትና እርምጃ በግለሰቡ ውስጥ ግሩም የሆነው የትሕትና ባሕርይ ይበልጥ እንዲያድግና እንዲጠነክር ያደርገዋል።

የጉባኤውን አንድነት ለመጠበቅ የግድ አስፈላጊ ነው። ትሕትና አንድ ክርስቲያን ባለው ነገር እንዲረካና ደስታውንና ሚዛኑን ጠብቆ እንዲኖር ይረዳዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በ⁠አንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 12 ላይ በምሳሌ እንዳብራራው የክርስቲያን ጉባኤ እርስ በርሱ ተደጋግፎ እንዲቆም ያደረገው መሠረት ታዛዥነት፣ ትሕትናና ለአምላክ ድርጅታዊ ዝግጅት ተገዥ መሆን ነው። በዚህም የተነሳ በጉባኤው ውስጥ የሚገኙት ወንዶች “ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል” ተብሎ የተነገራቸው ቢሆንም በሥልጣን ጥመኝነት ተነሳስተው ‘የባሰውን ፍርድ እንዳይቀበሉ’ እንደ አስተማሪነት ያሉ የኃላፊነት ቦታዎችን ከመሻት እንዲታቀቡም ተነግሯቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ያዕቆብ 3:1

ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ግንባር ቀደም ሆነው ለሚያገለግሉት ታዛዥ መሆን ያለባቸው ሲሆን ሹመቶችን ወይም ኃላፊነቶችን የሚሰጠው ይሖዋ እንደመሆኑ መጠን እርሱን መጠባበቅ ይኖርባቸዋል። (መዝሙር 75:6, 7) ሌዋውያን የነበሩት አንዳንድ የቆሬ ልጆች “ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኀጥአን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ” በማለት ተናግረዋል። (መዝሙር 84:10) እንዲህ ያለውን እውነተኛ የትሕትና ባሕርይ ለማዳበር ጊዜ ይጠይቃል። ቅዱሳን ጽሑፎች የበላይ ተመልካች ሆነው የሚሾሙ ሁሉ ሊያሟሉት የሚገባቸውን ብቃቶች ሲዘረዝሩ “በትዕቢት ተነፍቶ በዲያብሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ” አዲስ ክርስቲያን መሾም እንደሌለበት በግልጽ አስቀምጠዋል።—1 ጢሞቴዎስ 3:6