‘ክርስቶስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ’ አላችሁን?
‘ክርስቶስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ’ አላችሁን?
“ጽናትንና መጽናናትን የሚሰጠው አምላክ . . . ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ ይስጣችሁ።”—ሮሜ 15:5 NW
1. በብዙዎቹ የሕዝበ ክርስትና ሥዕሎች ላይ ኢየሱስ በምን መንገድ ተገልጿል? ይህስ ኢየሱስን በትክክል የማይገልጽ የሆነው ለምንድን ነው?
“አንድም ቀን ሲስቅ ታይቶ አያውቅም።” አንድ የጥንት የሮማ ባለ ሥልጣን ጽፎታል ተብሎ በሃሰት በሚነገርለት በአንድ ጽሑፍ ላይ ኢየሱስ የተገለጸው በዚህ መንገድ ነው። አሁን ባለበት ሁኔታ ከ11ኛው መቶ ዘመን አንስቶ ይታወቅ የነበረው ይህ የጽሑፍ ሰነድ በብዙ ሠዓሊያን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ይነገርለታል። a በብዙ ሥዕሎች ላይ ኢየሱስ ፈገግታ የሚባል ነገር የማያውቅ በሐዘን የተደቆሰ እንደሆነ ተደርጎ ተስሏል። ወንጌሎች ሞቅ ያለ መንፈስና የጠለቀ የርኅራኄ ስሜት እንዳለው አድርገው የገለጹትን ኢየሱስን ይህን ዓይነት ገጽታ እንዲላበስ ማድረግ አግባብ አይሆንም።
2. “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረውን ዓይነት አስተሳሰብ” ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ ለምን ነገር ያስታጥቀናል?
2 እውነተኛውን ኢየሱስ በትክክል ለማወቅ ከፈለግን አእምሯችንንና ልባችንን ኢየሱስ ምድር በነበረበት ወቅት ምን ዓይነት ሰው እንደነበር በሚገልጸው ትክክለኛ እውቀት መሙላት አለብን። ስለዚህ ስሜቱን፣ ማስተዋሉን፣ አስተሳሰቡንና ምክንያታዊነቱን ስለሚገልጸው ስለ “ክርስቶስ አስተሳሰብ” የጠለቀ ማስተዋል ማግኘት እንችል ዘንድ አንዳንድ የወንጌል ዘገባዎች የሚሰጡትን መግለጫ እንመርምር። (1 ቆሮንቶስ 2:16 NW ) እግረ መንገዳችንንም “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ” ማዳበር የምንችልበትን መንገድ እንመልከት። (ሮሜ 15:5 NW ) እንዲህ ካደረግን በራሳችን ሕይወትም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ እሱ የተወልንን ምሳሌ ለመከተል በተሻለ ሁኔታ የታጠቅን ልንሆን እንችላለን።—ዮሐንስ 13:15
በቀላሉ የሚቀረብ
3, 4. (ሀ) በማርቆስ 10:13-16 ላይ የተመዘገበው ታሪክ መቼት ምን ይመስላል? (ለ) ደቀ መዛሙርቱ ልጆች ወደ እርሱ እንዳይቀርቡ በከለከሉ ጊዜ ኢየሱስ ምን ብሎ ተናገረ?
3 ሰዎች ከኢየሱስ ጋር መሆን ያስደስታቸው ነበር። በተለያዩ ጊዜያት የተለያየ ዕድሜና አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች ሳይሸማቀቁ ይቀርቡት ነበር። ማርቆስ 10:13-16 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ታሪክ ተመልከት። ታሪኩ የተፈጸመው አሰቃቂ ሞት ለመጋፈጥ ወደ ኢየሩሳሌም ለመጨረሻ ጊዜ እያመራ ባለበት በአገልግሎቱ መደምደሚያ አካባቢ ነበር።—ማርቆስ 10:32-34
4 ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ኢየሱስ እንዲባርክላቸው ሰዎች ልጆቻቸውን፣ ሕፃናትን ጭምር ወደ እሱ ማምጣት ጀመሩ። b ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ ልጆቹ ወደ ኢየሱስ እንዳይቀርቡ ለመከልከል ሞከሩ። ምናልባት ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በዚህ ወሳኝ በሆነ ሳምንት በልጆች መቸገር እንደማይፈልግ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ተሳስተው ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እያደረጉ ያሉትን ነገር ሲያስተውል አልተደሰተም። ኢየሱስ “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው” በማለት ልጆቹን ወደ እሱ ጠራቸው። (ማርቆስ 10:14) ከዚያም ልባዊ ርኅራኄና ፍቅር የሚያንጸባርቅ ነገር አደረገ። ዘገባው “አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው” በማለት ይነግረናል። (ማርቆስ 10:16) ኢየሱስ ባቀፋቸው ጊዜ ልጆቹ ምንም እንዳልተሸማቀቁ ግልጽ ነው።
5. ማርቆስ 10:13-16 ላይ የሰፈረው ዘገባ ስለ ኢየሱስ ማንነት ምን የሚነግረን ነገር አለ?
5 ይህ አጭር ዘገባ ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው እንደነበር ብዙ ነገር ይነግረናል። ኢየሱስ በቀላሉ የሚቀረብ ሰው እንደነበር አስተውል። በሰማይ ከፍተኛ ቦታ የነበረው ቢሆንም ፍጹም ያልሆኑ ሰዎችን የሚያሸማቅቅ ወይም የሚያንኳስስ አልነበረም። (ዮሐንስ 17:5) ልጆች እንኳን እንደ ልባቸው የሚቀርቡት መሆኑ አንድ ነገር የሚጠቁም አይደለም? ኢየሱስ ፈጽሞ ፈገግ ብሎ ወይም ስቆ የማያውቅ ፊቱ የማይፈታ ሰው ቢሆን ኖሮ ልጆች ሊቀርቡት እንደማይችሉ የታወቀ ነው! በተለያየ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ኢየሱስ ሞቅ ያለ መንፈስ ያለውና ለሰዎች የሚያስብ ሰው መሆኑን በማወቅና ፊት ይነሳናል የሚል ስጋት ሳያድርባቸው በቀላሉ ይቀርቡት ነበር።
6. ሽማግሌዎች ራሳቸውን ይበልጥ በቀላሉ የሚቀረቡ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
6 በዚህ ታሪክ ላይ በማሰላሰል ራሳችንን ‘የኢየሱስ ዓይነት አስተሳሰብ አለኝ? በቀላሉ የምቀረብ ሰው ነኝ?’ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። በዚህ አስጨናቂ ዘመን የአምላክ በጎች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ” ሆነው የሚያገለግሉ በቀላሉ የሚቀረቡ እረኞች ይፈልጋሉ። (ኢሳይያስ 32:1, 2፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) እናንት ሽማግሌዎች ለወንድሞቻችሁ ጥልቅ የሆነ የአሳቢነት ስሜት ካዳበራችሁና ራሳችሁን ለእነርሱ ለመስጠት ፈቃደኞች ከሆናችሁ የምትጨነቁላቸው መሆናችሁን በቀላሉ ይረዳሉ። ይህን ስሜታችሁን ከፊታችሁ ላይ ሊያነቡት፣ ከድምፃችሁ ቃና ሊረዱትና ከምታደርጉት የደግነት ድርጊት ሊያስተውሉት ይችላሉ። እንዲህ ያለው ልባዊ ስሜትና አሳቢነት የመተማመን መንፈስ እንዲሰፍን ስለሚያደርግ ልጆችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ወደ እናንተ ለመቅረብ አያዳግታቸውም። አንዲት ክርስቲያን ሴት ለአንድ ሽማግሌ የልቧን ግልጥልጥ አድርጋ የተናገረችው ለምን እንደሆነ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “ያነጋገረኝ በደግነትና በርኅራኄ ነበር። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ አንዲትም ቃል አልተነፍስለትም ነበር። ምንም እንዳልሸማቀቅ አድርጎኛል።”
ለሌሎች አሳቢ ነበር
7.(ሀ) ኢየሱስ ለሌሎች አሳቢ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነበር? (ለ) ኢየሱስ አንድን ዓይነ ሥውር ቀስ በቀስ የፈወሰው ለምን ሊሆን ይችላል?
7 ኢየሱስ አሳቢና ለሌሎች ስሜት የሚጠነቀቅ ነበር። መከራ የደረሰባቸውን ሰዎች በተመለከተ ጊዜ የተሰማው ጥልቅ ሃዘን ከሥቃያቸው እንዲገላግላቸው ገፋፍቶታል። (ማቴዎስ 14:14) የሌሎች ሰዎችን የአቅም ገደብና የሚያስፈልጋቸውን ነገር ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር። (ዮሐንስ 16:12) በአንድ ወቅት ሰዎች አንድ ዓይነ ሥውር ወደ ኢየሱስ አመጡና እንዲፈውሰው ለመኑት። ኢየሱስ ሰውየውን ፈወሰው። ሆኖም የፈወሰው ቀስ በቀስ ነበር። በመጀመሪያ ሰውየው ሰዎችን የተመለከተው በድንግዝግዝታ ነበር። “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ” አለ። ከዚያም ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ እንዲያይ አደረገው። ሰውዬውን ቀስ በቀስ የፈወሰው ለምን ነበር? ብርሃን ሳያይ ለረዥም ጊዜ የኖረን አንድ ሰው ድንገት ለፀሐይ ብርሃንና በአካባቢው ላለው ሁኔታ በማጋለጥ ሊደርስበት የሚችለውን ድንጋጤ ለማስቀረት ብሎ መሆን አለበት።—ማርቆስ 8:22-26
8, 9. (ሀ) ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ዲካፖሊስ እንደደረሱ ምን ነገር ተከሰተ? (ለ) ኢየሱስ መስማት የተሳነውን አንድ ሰው እንዴት እንደፈወሰው ግለጽ።
8 በተጨማሪም በ32 እዘአ ከተከበረው የማለፍ በዓል በኋላ የተከሰተ አንድ ሁኔታ ተመልከት። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከገሊላ ባሕር በስተ ምሥራቅ ወደሚገኘው ዲካፖሊስ ወደተባለ አውራጃ ገና መድረሳቸው ነበር። እዚያም ብዙ ሕዝብ አገኟቸውና የታመሙና የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች እንዲፈውሳቸው ወደ ኢየሱስ አመጧቸው። (ማቴዎስ 15:29, 30) የሚገርመው ኢየሱስ ለየት ያለ ትኩረት የሚያሻውን አንድ ሰው ከሕዝቡ መካከል ለይቶ ለብቻው ወሰደው። ይህን ታሪክ የመዘገበው የወንጌል ጸሐፊ ማርቆስ በዚህ ወቅት የሆነውን ሁኔታ ዘግቧል።—ማርቆስ 7:31-35
9 ሰውዬው መስማት የተሳነውና መናገር የሚቸግረው ሰው ነበር። ኢየሱስ ይህ ሰው የተሰማውን የመረበሽ ወይም የእፍረት ስሜት ተገንዝቦ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ አንድ ያልተለመደ ነገር አደረገ። ሰውዬውን ከሕዝቡ ለይቶ ገለል ወዳለ ስፍራ ወሰደው። ከዚያም ኢየሱስ የሚያደርገውን ነገር ለማስረዳት ለሰውዬው ምልክት አሳየው። “ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ።” (ማርቆስ 7:33) ከዚያም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመለከተና ቃተተ። እነዚህ ድርጊቶች ለሰውዬው ‘አሁን ለአንተ የማደርግልህ ከአምላክ ባገኘሁት ኃይል ነው’ የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ። በመጨረሻም ኢየሱስ “ተከፈት” አለ። (ማርቆስ 7:34) በዚያን ጊዜ ሰውዬው መሥማትና አጥርቶ መናገር ቻለ።
10, 11. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ላሉ ሰዎች ስሜት አሳቢ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በቤተሰብ ውስጥስ?
10 ኢየሱስ ለሰዎች ያሳየው እንዴት ያለ አሳቢነት ነው! ለስሜታቸው ይጠነቀቅ ነበር፤ እንዲህ ያለው የአዛኝነት ባሕርይ ደግሞ የሌሎችን ስሜት የሚጎዳ ነገር እንዳያደርግ ይገፋፋዋል። እኛም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በዚህ ረገድ የኢየሱስ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበርና ማንጸባረቅ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይመክረናል:- “በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፣ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፣ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፣ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ።” (1 ጴጥሮስ 3:8) ይህም የሌሎችን ስሜት ግምት ውስጥ እንዳስገባን በሚያሳይ መንገድ እንድንናገርና እንድናደርግ ይጠይቅብናል።
11 ለእኛ እንዲደረግልን የምንፈልገውን ነገር ለሌሎች በማድረግ ሰብአዊ ክብራቸውን ከጠበቅን ለሌሎች ስሜት አሳቢ መሆናችንን በጉባኤ ውስጥ ማሳየት እንችላለን። (ማቴዎስ 7:12) ይህም ስለምንናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን እንዴት ብለን እንደምንናገር ጠንቃቆች መሆንንም ይጨምራል። (ቆላስይስ 4:6) ‘ሳይታሰብ የሚሰነዘሩ ቃላት እንደ ሰይፍ ሊያቆስሉ እንደሚችሉ’ አስታውስ። (ምሳሌ 12:18) በቤተሰብ መካከልስ? እርስ በርሳቸው ከልብ የሚዋደዱ ባልና ሚስቶች አንዱ ለሌላው ስሜት ያስባሉ። (ኤፌሶን 5:33) ሻካራ ቃላትን ከመናገር፣ የነቀፋ ውርጅብኝ ከማውረድና የሚከነክን የሽሙጥ ቃል ከመናገር ይቆጠባሉ። እነዚህ ሁሉ በቀላሉ የማይሽር የስሜት ቁስል ሊያስከትሉ ይችላሉ። ልጆችም ቢሆኑ ስሜት አላቸው፤ አፍቃሪ ወላጆች ይህን ግምት ውስጥ ያስገባሉ። እርማት መስጠት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ እንደነዚህ ያሉት ወላጆች የልጆቻቸውን ክብር በሚጠብቅ መንገድ እርማት በመስጠት ልጆቻቸውን ከማበሳጨት ይቆጠባሉ። c (ቆላስይስ 3:21) በዚህ መንገድ ለሌሎች ሰዎች አሳቢነት ስናሳይ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ እንዳለን እናንጸባርቃለን።
በሌሎች ላይ እምነት እንደሚጥል አሳይቷል
12. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በተመለከተ የነበረው ሚዛናዊና ከእውነታው ያልራቀ አመለካከት ምን ነበር?
12 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በተመለከተ ሚዛናዊና ከእውነታው ያልራቀ አመለካከት ነበረው። ፍጹማን አለመሆናቸውን በሚገባ ያውቃል። ከዚህም በላይ የሰዎችን ልብ ማንበብ ይችላል። (ዮሐንስ 2:24, 25) ሆኖም የሚመለከተው ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ከመሆናቸው አንጻር ሳይሆን ካላቸው ጥሩ ባሕርይ አንጻር ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ የሳባቸው እነዚህ ሰዎች ያላቸውን ችሎታ ተመልክቷል። (ዮሐንስ 6:44) ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የነበረው ግንኙነትና እነርሱን የያዘበት መንገድ ለእነርሱ አዎንታዊ አመለካከት እንደነበረው የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ ያህል እምነት እንደሚጥልባቸው አሳይቷል።
13. ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ እምነት ይጥል እንደነበር ያሳየው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ እምነት እንደሚጥል ያሳየው እንዴት ነበር? ምድርን ለቅቆ በሄደበት ጊዜ ለተቀቡት ደቀ መዛሙርቱ ከባድ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። በምድር ዙሪያ ያለውን የመንግሥቱን ፍላጎቶች የማካሄዱን ኃላፊነት የተወው ለእነርሱ ነበር። (ማቴዎስ 25:14, 15፤ ሉቃስ 12:42-44) በአገልግሎቱ ወቅት ትናንሽ በሆኑ ጉዳዮችና ቀጥተኛ ባልሆኑ መንገዶች እንኳ እምነት እንደሚጥልባቸው አሳይቷል። ተሰብስበው የነበሩትን ሰዎች ለመመገብ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ ምግቡ እንዲበዛ ባደረገ ጊዜ ምግቡን የማከፋፈሉን ሥራ የሰጠው ለደቀ መዛሙርቱ ነበር።—ማቴዎስ 14:15-21፤ 15:32-37
14. በማርቆስ 4:35-41 ላይ የሚገኘውን ታሪክ ጠቅለል ባለ ሁኔታ እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?
14 በማርቆስ 4:35-41 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ታሪክ ተመልከት። በዚህ ወቅት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በአንዲት ጀልባ ተሳፍረው ከገሊላ ባሕር በስተ ምሥራቅ አቀኑ። መቅዘፍ ከጀመሩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ በጀልባዋ በኋለኛው በኩል ተኛና ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደው። ይሁን እንጂ ወዲያው “ብርቱ ዐውሎ ነፋስ” ተነሳ። እንዲህ ያለው አውሎ ነፋስ ለገሊላ ባሕር እንግዳ አይደለም። ረባዳማ ቦታ (ወደ 200 ሜትር ከባሕር ወለል በታች) በመሆኑ በዚህ አካባቢ የሚኖረው አየር አካባቢው ካለው አየር ይበልጥ ሞቃታማ ነው። ይህም አየሩ እንዲለዋወጥ ያደርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ በስተ ደቡብ ከሚገኘው ከሄርሞን ተራራ ኃይለኛ ነፋስ ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ ይነፍሳል። ጸጥ ያለው አየር ከመቅጽበት ተለውጦ ከፍተኛ አውሎ ነፋስ ሊፈጥር ይችላል። ይህን ደግሞ አስብ:- ኢየሱስ ያደገው በገሊላ ስለሆነ በዚያ አካባቢ አውሎ ነፋስ ሲነሳ በተደጋጋሚ እንደተመለከተ የተረጋገጠ ነው። ሆኖም አንዳንዶቹ ዓሣ አጥማጅ የሆኑት ደቀ መዛሙርቱ ባላቸው ችሎታ ላይ እምነት በመጣል ያለ ስጋት ተኛ።—ማቴዎስ 4:18, 19
15. ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የነበረውን እምነት የመጣል መንፈስ እንዴት መኮረጅ እንችላለን?
15 እኛም ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ያሳየው ዓይነት እምነት የመጣል መንፈስ ልናሳይ እንችላለን? አንዳንዶች ኃላፊነቶችን ለሌሎች መስጠት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። ሁሉንም ነገር ራሳቸው መሥራት ይፈልጋሉ። ‘አንድ ነገር በትክክል እንዲሠራ ከፈለግሁ ራሴ መሥራት አለብኝ!’ ብለው ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሁሉንም ነገር ራሴ ካልሠራሁት የምንል ከሆነ ራሳችንን ልናደክምና ምናልባትም ለቤተሰቦቻችን ልንሰጣቸው የሚገባውን ጊዜ ሳያስፈልግ ልንነፍጋቸው እንችላለን። በተጨማሪም ተገቢ የሆኑ ሥራዎችንና ኃላፊነቶችን ለሌሎች የማንሰጥ ከሆነ ሊያገኙ የሚገባቸውን ተሞክሮና ሥልጠና እንዳያገኙ ልንነፍጋቸው እንችላለን። አንዳንድ ኃላፊነቶችን በማካፈል በሌሎች ላይ እምነት መጣልን መማር ጥበብ ይሆናል። ራሳችንን እንዲህ ብለን በሃቀኝነት መጠየቃችን ጥሩ ነው:- ‘በዚህ ረገድ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ አለኝ? አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል እንደሚሠሩ በማመን አንዳንድ ሥራዎችን ለሌሎች ለማካፈል ፈቃደኛ ነኝን?’
ደቀ መዛሙርቱን እንደሚተማመንባቸው አሳይቷል
16, 17. (ሀ) ኢየሱስ እንደሚተዉት ቢያውቅም በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ምሽት ለሐዋርያቱ ምን ማረጋገጫ ሰጣቸው?
16 ኢየሱስ በሌላ አንድ አስፈላጊ በሆነ መንገድ ለደቀ መዛሙርቱ አዎንታዊ አመለካከት እንዳለው አሳይቷል። እንደሚተማመንባቸው እንዲያውቁ ያደርግ ነበር። ምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ለሐዋርያቱ ከተናገራቸው የማረጋገጫ ቃላት ይህን በግልጽ ለማየት ይቻላል። የሆነውን ነገር ተመልከት።
17 ኢየሱስ የቀረው ጊዜ አንድ ሙሉ ሌሊት ብቻ ነበር። እግራቸውን በማጠብ ለሐዋርያቱ ትሕትናን በሚመለከት አንድ አስፈላጊ የሆነ ትምህርት አስተማረ። ቀጥሎም ለሞቱ መታሰቢያ የሚሆን የእራት ዝግጅት አደረገ። ከዚያም ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሚሆን የጦፈ ክርክር ያዙ። ኢየሱስ በጣም ታጋሽ በመሆን እነርሱን በቁጣ ከመገሰጽ ይልቅ ምክንያት እያቀረበ አስረዳቸው። ከፊታቸው ምን ነገር እንደሚጠብቃቸው ነገራቸው:- “በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና።” (ማቴዎስ 26:31፤ ዘካርያስ 13:7) እርዳታ በሚያስፈልገው ወቅት የቅርብ ወዳጆቹ እንደሚተዉት ያውቅ ነበር። እንዲህም ሆኖ አላወገዛቸውም። ከዚያ ፈጽሞ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የሚከተለውን አላቸው:- “ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው።” (ማቴዎስ 26:32) አዎን፣ እነርሱ ቢተዉትም እርሱ እንደማይተዋቸው አረጋገጠላቸው። ይህ ከባድ የመከራ ጊዜ ካለፈ በኋላ እንደገና ያገኛቸዋል።
18. ኢየሱስ በገሊላ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ከበድ ያለ ተልእኮ ሰጣቸው? ሐዋርያትስ የተሰጣቸውን ተልእኮ ወደ ፍጻሜ ያደረሱት እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ ቃሉን አላጠፈም። ከዚያም ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ፣ ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ከሌሎች በርካታ ሰዎች ጋር ለነበሩት ለአሥራ አንዱ ሐዋርያት ተገለጠላቸው። (ማቴዎስ 28:16, 17፤ 1 ቆሮንቶስ 15:6) እዚያም ኢየሱስ አንድ ከበድ ያለ ተልእኮ ሰጣቸው:- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:19, 20) ሐዋርያት የተሰጣቸውን ይህን ተልእኮ ወደ ፍጻሜ እንዳደረሱት የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በግልጽ ያሳያል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምሥራቹን የመስበኩን ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው በታማኝነት አከናውነዋል።—ሥራ 2:41, 42፤ 4:33፤ 5:27-32
19. ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ያደረገው ነገር ስለ ክርስቶስ አስተሳሰብ ምን ነገር ያስተምረናል?
19 ይህ ግልጽ ዘገባ ስለ ክርስቶስ አስተሳሰብ ምን ነገር ያስተምረናል? ኢየሱስ የሐዋርያቱን ደካማ ጎን አብጠርጥሮ ያውቅ የነበረ ቢሆንም ‘እስከ መጨረሻ ወድዷቸዋል።’ (ዮሐንስ 13:1) ጉድለት ቢኖርባቸውም የሚተማመንባቸው መሆኑን እንዲያውቁ አድርጓል። ኢየሱስ በእነርሱ ላይ እምነት መጣሉ ስህተት እንዳልነበር ልብ በል። በእነርሱ ላይ እምነትና ትምክህት እንዳለው ማሳየቱ ያዘዛቸውን ሥራ ዳር ለማድረስ ከልባቸው ቆርጠው እንዲነሱ እንዳበረታቸው ምንም ጥርጥር የለውም።
20, 21. የእምነት ባልደረቦቻችንን በተመለከተ አዎንታዊ አመለካከት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
20 በዚህ ረገድ የክርስቶስን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው? የእምነት ባልደረቦችህን በተመለከተ አፍራሽ አስተሳሰብ አትያዝ። ስለ ድክመታቸው የምታስብ ከሆነ በምትናገረው ቃላትና በምታደርገው ድርጊት መገለጡ የማይቀር ነው። (ሉቃስ 6:45) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር “ሁሉን ያምናል” በማለት ይነግረናል። (1 ቆሮንቶስ 13:7) ፍቅር አዎንታዊ እንጂ አሉታዊ አይደለም። ይገነባል እንጂ አያፈርስም። ሰዎች ጥሩ ምላሽ የሚሰጡት ለሚያሸማቅቃቸው ሳይሆን ፍቅር ለሚያሳያቸው ሰው ነው። እንደምንተማመንባቸው በመግለጽ ሌሎችን ልንገነባና ልናበረታታ እንችላለን። (1 ተሰሎንቄ 5:11) እንደ ክርስቶስ ለወንድሞቻችን አዎንታዊ አመለካከት ካለን በሚገነባቸውና ያላቸውን መልካም ነገር መጠቀም በሚቻልበት መንገድ እንይዛቸዋለን።
21 የክርስቶስን አስተሳሰብ ማዳበርና ማንጸባረቅ ኢየሱስ ያደረጋቸውን አንዳንድ ነገሮች ከመኮረጅ አልፎ የሚሄድ ነገር ነው። ቀደም ሲል በነበረው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው ኢየሱስ እንዳደረገው ማድረግ የምንፈልግ ከሆነ በመጀመሪያ ነገሮችን እርሱ በተመለከተበት መንገድ መመልከትን መማር ይገባናል። በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንደሚብራራው ወንጌሎች ኢየሱስ የነበረውን ባሕርይ፣ አስተሳሰብና ለተሰጠው ሥራ የነበረውን ስሜት ከሌላ አቅጣጫ እንድንመለከት ይረዱናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህን የሐሰት ሰነድ ያዘጋጀው ሰው የፀጉሩን፣ የፂሙንና የዓይኑን ቀለም ጨምሮ የኢየሱስን ጠቅላላ ቁመና በራሱ ግምት ገልጿል። ኤድገር ጄ ጎድስፒድ የተባሉ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ሲገልጹ ይህ የፈጠራ ሐሳብ “የኢየሱስን ቁመና በሚመለከት ለሠዓሊያን ፍንጭ ለመስጠት ታልሞ የተዘጋጀ ነው” ብለዋል።
b ልጆቹ የተለያየ ዕድሜ ያላቸው እንደሚሆኑ የታወቀ ነው። እዚህ ላይ ‘ልጆች’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል የ12 ዓመቷን የኢያኢሮስ ልጅ ለማመልከትም ይሠራል። (ማርቆስ 5:39, 42 NW ፤ 10:13 NW ) ይሁን እንጂ ሉቃስ ይህንኑ ታሪክ በመዘገበበት ቦታ ላይ ሕፃናትን በሚያመለክት ቃል ተጠቅሟል።—ሉቃስ 1:41 NW ፤ 2:12፤ 18:15
c “ክብራቸውን ትጠብቅላቸዋለህን?” የሚለውን በሚያዝያ 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን ርዕስ ተመልከት።
ልታብራራ ትችላለህ?
• ደቀ መዛሙርቱ ሕፃናት ወደ እሱ እንዳይቀርቡ ለመከልከል በሞከሩ ጊዜ ኢየሱስ ምን አደረገ?
• ኢየሱስ ለሌሎች አሳቢነት ያሳየው በምን መንገዶች ነው?
• ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ እምነት በመጣል ረገድ የተወውን ምሳሌ ልንኮርጅ የምንችለው እንዴት ነው?
• ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የነበረውን መተማመን ልንኮርጅ የምንችለው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕፃናት ወደ ኢየሱስ መቅረብ አይፈሩም ነበር
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ሌሎችን በርኅራኄ ይዟል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቀላሉ የሚቀረቡ ሽማግሌዎች በረከት ናቸው