በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰው ልጅ እንዲያው ሻል ያለ እንስሳ ነውን?

የሰው ልጅ እንዲያው ሻል ያለ እንስሳ ነውን?

የሰው ልጅ እንዲያው ሻል ያለ እንስሳ ነውን?

“ስለ ሕይወት አመጣጥ ያለን እምነት ለውጥ ያመጣል?”

በብራዚል የምትገኝ አንዲት የ16 ዓመት ልጅ “የሰው ልጅ እንዲያው ሻል ያለ እንስሳ ነውን?” በሚል ርዕስ ንግግር ባቀረበችበት ወቅት በመግቢያዋ ላይ ከላይ ያለውን ጥያቄ አቅርባ ነበር። አስተማሪዋ በዚህ ርዕስ ላይ የወጣ የሰኔ 22, 1998 ንቁ! (እንግሊዝኛ) አንብባ ስለነበር በዚህ ጥያቄ ላይ ተመሥርታ ለክፍሏ ተማሪዎች ንግግር እንድታቀርብ ይህችን ተማሪ ጋበዘቻት።

የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ይህች ወጣት በተፈጥሯዊ ምርጦሽ (natural selection) ላይ የተመሠረተው የአዝጋሚ ለውጥ ትምህርት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ጎላ አድርጋ ገልጻለች። ለምሳሌ ያህል የአዝጋሚ ለውጥ ፅንሰ ሐሳብ ብዙዎች ጦርነትን በሕይወት ለመቀጠል የሚደረገው ዘላለማዊ ትግል ክፍል እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል። ይህም ለፋሺዝምና ለናዚዝም መንገድ ጠርጓል።

ተማሪዋ በሰዎችና በእንስሳት መካከል ሰፊ ልዩነት መኖሩን አስገንዝባለች። እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “መንፈሳዊነትን ማዳበር የሚችሉት ሰዎች ብቻ ናቸው። የሕይወትን ትርጉምና ዓላማ መርምረው ለማግኘት የሚጥሩት ሰዎች ብቻ ናቸው። ሞት ክፉኛ የሚረብሻቸው፣ ከየት እንደመጡ የማወቅ ጉጉት ያላቸውና ለዘላለም የመኖር ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። ስለዚህ ስለ አመጣጣችን ለማወቅ ጊዜ ማጥፋታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!”

ተማሪዋ ግሩም አድርጋ ስላቀረበች አስተማሪዋ አመሰገነቻት። አስተማሪዋ ይህች ወጣት ምሥክር እንዲህ ጎበዝ ልትሆን የቻለችው ማንበብ ስለምትወድ እንደሆነም ገልጻለች። ይህች ልጅ እንደ ንቁ! እና መጠበቂያ ግንብ ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ጥሩ አድርጋ እንደምታነብ በትምህርት ቤት ውስጥ ትታወቃለች።

የይሖዋ ምሥክሮች የአዝጋሚ ለውጥ ፅንሰ ሐሳብ በወጣቶች ልብና አእምሮ ላይ እያሳደረ ያለው ተጽእኖ በእጅጉ ያሳስባቸዋል። ይህች ልጅ ያለችበት ጉባኤ የሰኔ 22, 1998 ንቁ! መጽሔትን ለአስተማሪዎቻቸውና ለክፍል ጓደኞቻቸው እንዲሰጡ ወጣት ምሥክሮችን አበረታታ። በከተማው ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች 230 የሚያክሉ መጽሔቶች ተሰራጭተዋል። በአንድ ትምህርት ቤት የሳይንስ ዲፓርትመንት ኃላፊ የሆነ አንድ መምህር የንቁ! መጽሔት ኮንትራት ገብቷል።

አዎን፣ ስለ ሕይወት አመጣጥ ያለን እምነት ልዩነት ያመጣል! በፈጣሪ ማመናቸው በሕይወታቸው ላይ ትልቅ ልዩነት ማምጣቱን ይህች ወጣትና ጓደኞቿ አሳይተዋል።