በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

● የማያምን ባል ያላት አንዲት ክርስቲያን ሚስት ሃይማኖታዊ በዓል በሚከበርበት ዕለት የእርሱ ቤተሰቦች ባዘጋጁት ግብዣ ላይ አብራው እንድትገኝ ቢጠይቃት ምን ማድረግ ይኖርባታል?

ይህ ጉዳይ የተለያዩ ነገሮችን ወደ አእምሮዋ እንዲመጡ ስለሚያደርግ አንዲትን ክርስቲያን ሚስት አጣብቂኝ ውስጥ ሊከታት ይችላል። ተገዢነትን የሚመለከቱ ሁለት ነገሮች ወዲያው ወደ አእምሮዋ ሊመጡ ይችላሉ። ለባሏ የመገዛት ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ አለባት። (ቲቶ 2:4, 5) በሌላ በኩል ደግሞ ከማንም በላይ የእርሷ ራስ የሆነውን ይሖዋን የመታዘዝ ኃላፊነት አለባት።—ዕብራውያን 12:9

እንደ ገና ያሉትን ዓለማዊ በዓላት በተመለከተ ክርስቲያኖች ያላቸው አቋም ግልጽ ነው። ክርስቲያኖች የሚያከብሩት ልዩ በዓል ቢኖር የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ብቻ ነው። (ሉቃስ 22:19, 20) ቅዱስ ጽሑፋዊ ከሆኑ ክንውኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው እንኳ ቢሆኑ በአረማዊ አምልኮ በተበከሉ እንደ ገናና ፋሲካ በመሳሰሉ ሃይማኖታዊ በዓላት መካፈል ስህተት ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:14-18) ሆኖም የምንኖረው በዚህ አሮጌ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ እስከሆነ ድረስ በአረማዊ አምልኮ ላይ የተመሠረቱ በዓላትን ከሚያከብሩ ግለሰቦች ጋር የሚያገናኘን ሁኔታ ይኖር ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 5:10) ይህም ከዘመዶቻችን ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ሊጨምር ይችላል።

አንዲት ክርስቲያን ሚስት በባሏ ጥያቄ ዓለማዊ በዓል በሚከበርበት ዕለት ዘመድ ለመጠየቅ አብራው ብትሄድ እዚያ የምታደርገው ነገር በዓሉን እያከበረች እንዳልሆነ በግልጽ የሚያሳይ እንደሚሆን አያጠራጥርም። በበዓል ጊዜ የሚነገሩ የተለመዱ የመልካም ምኞት መግለጫዎችን ሊገልጹላት ይችላሉ፤ ሆኖም እሷ ተመሳሳይ ምላሽ አትሰጥም። በዚህ አጋጣሚ ስጦታ ሊለዋወጡ ይችላሉ፤ እሷ ግን ስጦታ አትሰጥም። እንዲያውም በበዓሉ ሰሞን የበዓሉን መንፈስ የሚያንጸባርቅ ነገር ከማድረግ ትቆጠባለች። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ በግብዣው ላይ የተገኘችው በዓሉን ምክንያት በማድረግ እንዳልሆነ በግልጽ እንዲታይ ማድረግ ትችላለች።

በዓሉን በማስመልከት የሚያደርጉት አምልኮታዊ ነገር ካለ እርሷ ተካፋይ አለመሆኗ ቤተሰቦቹን ቅር ሊያሰኛቸው እንደሚችል በዘዴና በአክብሮት ቀደም ብላ ለባሏ መንገሯ ጥየቃውን ለሌላ ቀን ለማድረግ እንዲወስን ሊያደርገው ይችላል። (1 ጴጥሮስ 3:15) ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋሟን አንዴ ሙሉ በሙሉ ከተረዳ ለእሷም ሆነ ለእሱ ይበልጥ ተስማሚ የሆነ ውሳኔ ወደማድረግ ሊያዘነብል ይችላል።

ጉዳዩን ካስረዳችው በኋላም እንኳ አብራው መሄድ እንዳለባት ቢነግራት መሄድ ወይም አለመሄድ የግል ውሳኔዋ ይሆናል። የቤቱ ራስ እንደመሆኑ መጠን ለቤተሰቡ ምግብ የማቅረብ ኃላፊነት አለበት ብላ ልትደመድም ትችላለች። (ቆላስይስ 3:18) በዚህ ዕለት ግን ራሷ የሆነው ባሏ ሁለቱም ቤተሰቦች እረፍት ስለሆኑና መጠየቅ የሚቻልበት አጋጣሚ ስላለ እርሱ ቤተሰቦች ዘንድ ሄደው እንዲመገቡ አስቦ ሊሆን ይችላል። ቀኑ ዓለማዊ በዓል የሚከበርበት ስለሆነ ብቻ አንድ ሰው ከዘመዶቹ ጋር ምግብ መብላቱ ስህተት ይሆናል ማለት አይደለም። ይህን አጋጣሚ ተጠቅማ ልትመሰክርላቸው ትችላለች።

በአንደኛ ቆሮንቶስ 8:8 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት ልብ በል:- “መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጐድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም።” ምግቡ በዓለማዊ በዓል ቀን ስለተበላ ብቻ ይረክሳል ማለት አይደለም። አንዲት ክርስቲያን በየዕለቱ ከምትመገበው ምግብ ምንም የተለየ ነገር እንደሌለው አድርጋ ልትመለከተው ትችላለች። ሃይማኖታዊ ሰላምታዎችን አትለዋወጥም፣ በመዝሙሮች አትካፈልም፣ ለመልካም ምኞት መግለጫ ተብሎ ብርጭቆ አታጋጭም። ስለዚህ ምግቡን መመገቧ ብቻ እንደ ኃጢአት ሊታይ አይችልም።

ሆኖም በእንዲህ ዓይነቱ ግብዣ ላይ መገኘት በሌሎች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽእኖ ማጤኑም ተገቢ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 8:9 ላይ “ይህ መብታችሁ ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆንባቸው ተጠንቀቁ” ሲል አክሎ ተናግሯል። እዚህ ላይ ሐዋርያው ለጣዖት ስለተሠዋ ምግብ እየተናገረ ስለሆነ ዓለማዊ በዓል በሚከበርበት ዕለት ዓለማዊ ዘመዶችን ለመጠየቅ መሄዷን የሚያውቁ ሊሰናከሉ የሚችሉ መሆናቸውን የሚያጎላ ነው።—1 ቆሮንቶስ 10:23, 24

በተጨማሪም አቋሟን እንድታላላ ግፊት የሚያደርጉባት ከሆነ የጸና ክርስቲያናዊ አቋሟን እንደያዘች መቀጠል ልትቸገር ትችላለች። እነሱን ቅር ላለማሰኘት ስትል በተሳሳቱ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ድርጊቶች ለመሳተፍ ልትፈተን ትችላለች። ይሖዋን የሚያሳዝን አንድ ነገር ብትፈጽም ትልቅ ጸጸት ውስጥ እንደሚከታት የታወቀ ነው። ስለዚህ ውሳኔ ከማድረጓ በፊት እነዚህን ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት ቀደም ብሎ ጉዳዩን በጥሞና ማጤኗ አስፈላጊ ነው።

ስለዚህ ወደ ማጠቃለያው ስንመጣ ሁኔታውን በሚገባ ካጤነች በኋላ የግል ውሳኔዋን ማድረግ ትችላለች። (ገላትያ 6:5) ጳውሎስ “እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ” ሲል እንደተናገረው ለማለት የሚያስችል ንጹህ ክርስቲያናዊ ኅሊና እንዲኖራት በሚያደርግ መንገድ ብትወስን ጥሩ ይሆናል።—ሥራ 24:16