“የክርስቶስን አስተሳሰብ” ማወቅ
“የክርስቶስን አስተሳሰብ” ማወቅ
“እንዲያስተምረው የጌታን ልብ [“የይሖዋን አስተሳሰብ፣” NW ] ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልብ [“አስተሳሰብ፣” NW ] አለን።”—1 ቆሮንቶስ 2:16
1, 2. ይሖዋ በቃሉ ውስጥ ኢየሱስን በተመለከተ ስለ ምን ነገር መግለጽን ይበልጥ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል?
ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው ነበር? የፀጉሩ፣ የቆዳው፣ የዓይኑ ቀለም ምን ዓይነት ነበር? ረዥም ነበር ወይስ አጭር? ክብደቱስ ምን ያክል ነበር? ባለፉት መቶ ዘመናት ኢየሱስን በተለያየ መንገድ በሥዕል ለመግለጽ ተሞክሯል። አንዳንዶቹ ሥዕሎች ከእውነታው ብዙም ያልራቁ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ምንም የማይገናኙ ናቸው። አንዳንዶች ፈርጠም ያለ ሰውነት ያለው ወንዳ ወንድ አድርገው ሲሥሉት ሌሎች ደግሞ ከሲታና ልፍስፍስ አድርገው ሥለውታል።
2 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ ቁመና ላይ ትኩረት አያደርግም። ከዚያ ይልቅ ይሖዋ ይበልጥ አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው ኢየሱስ ምን ዓይነት ባሕርይ ያለው ሰው እንደነበር መገለጹ ላይ ነበር። የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ የተናገረውንና ያደረገውን ነገር መዘገብ ብቻ ሳይሆን ከተናገራቸውና ካደረጋቸው ነገሮች በስተጀርባ የነበረውን ጥልቅ ስሜትና አስተሳሰብ ጭምር ገልጠውልናል። እነዚህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ አራት ዘገባዎች ሐዋርያው ጳውሎስ “የክርስቶስ አስተሳሰብ” ብሎ የጠቀሰውን ነገር ቀረብ ብለን እንድንመረምር ያስችሉናል። (1 ቆሮንቶስ 2:16 NW ) ከኢየሱስ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ባሕርይ ጋር መተዋወቃችን አስፈላጊ ነው። ለምን? ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ነው።
3. የክርስቶስን አስተሳሰብ በሚገባ ማወቃችን ምን ማስተዋል ያስገኝልናል?
3 አንደኛ፣ የክርስቶስ አስተሳሰብ የይሖዋ አምላክን አስተሳሰብ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ኢየሱስ ከአባቱ ጋር በጣም የጠበቀ ቅርርብ ስለነበረው እንዲህ ብሎ ለመናገር ችሏል:- “ወልድንም ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፣ አብንም ማን እንደ ሆነ ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር የሚያውቅ የለም።” (ሉቃስ 10:22) እዚህ ላይ ኢየሱስ ‘ይሖዋ ምን እንደሚመስል ለማወቅ ከፈለጋችሁ እኔን ተመልከቱ’ ብሎ የተናገረ ያህል ነበር። (ዮሐንስ 14:9) ስለዚህ ወንጌሎች ስለ ኢየሱስ አስተሳሰብና ስሜት የሚናገሩትን ዘገባ በምናጠናበት ጊዜ እግረ መንገዳችንን የይሖዋን አስተሳሰብና ስሜት እየተማርን ነው ማለት ነው። እንዲህ ያለው እውቀት ወደ አምላካችን ይበልጥ እንድንቀርብ ያስችለናል።—ያዕቆብ 4:8
4. ልክ እንደ ኢየሱስ ለማድረግ በመጀመሪያ ምን ነገር መማር አለብን? ለምንስ?
4 ሁለተኛ፣ የኢየሱስን አስተሳሰብ ማወቃችን ‘ፈለጉን በቅርብ እንድንከተል’ ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስን መከተል ማለት እንዲያው የተናገራቸውን ቃላት ደግሞ መናገርና ድርጊቱን መቅዳት ማለት አይደለም። በንግግርና በድርጊት የሚንጸባረቀው አስተሳሰብና ስሜት ስለሆነ ክርስቶስን መከተል እርሱ የነበረው ዓይነት “አሳብ” ማዳበርን ይጠይቅብናል። (ፊልጵስዩስ 2:5) በሌላ አባባል የኢየሱስን ተግባር መኮረጅ የምንፈልግ ከሆነ በመጀመሪያ ፍጽምና የሌለን ቢሆንም እንኳ አቅማችን በሚፈቅድልን መጠን የኢየሱስን ዓይነት አስተሳሰብና ስሜት ማዳበርን መማር አለብን። ስለዚህ ከወንጌል ጸሐፊዎች በምናገኘው እርዳታ የክርስቶስን አስተሳሰብ ቀረብ ብለን ለመመርመር እንሞክር። ኢየሱስ ያን ዓይነት አስተሳሰብና ስሜት እንዲኖረው ያደረጉትን ነገሮች በመጀመሪያ እንመለከታለን።
ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረው ሕይወት
5, 6. (ሀ) አብረናቸው የምንውላቸው ሰዎች በእኛ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ? (ለ) የአምላክ የበኩር ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ከማን ጋር ይኖር ነበር? ይህስ በእርሱ ላይ ምን ተጽእኖ አሳድሯል?
5 አብረን የምንውለው ሰው በአስተሳሰባችን፣ በስሜታችንና በድርጊታችን ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። a (ምሳሌ 13:20) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ሰማይ እያለ ከማን ጋር እንደነበር አስብ። ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት “ቃል” ወይም የአምላክ ቃል አቀባይ ይባል እንደነበር የዮሐንስ ወንጌል ይገልጽልናል። ዮሐንስ እንዲህ ይላል:- “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሔር [“አምላክ፣” NW ] ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።” (ዮሐንስ 1:1, 2) ይሖዋ መጀመሪያ ስለሌለው ቃል ‘በመጀመሪያ’ ከአምላክ ጋር ነበር የሚለው አባባል የአምላክ የፍጥረት ሥራዎች መጀመሪያ መሆኑን የሚያመለክት መሆን አለበት። (መዝሙር 90:2) ኢየሱስ “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው።” ስለዚህ ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታትና ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በሕይወት ይኖር ነበር ማለት ነው።—ቆላስይስ 1:15፤ ራእይ 3:14
6 አንዳንድ ሳይንሳዊ ግምቶች እንደሚሉት ከሆነ ግዑዙ ጠፈር 12 ቢልዮን ለሚያክል ዓመት ኖሯል። እነዚህ ግምቶች ትንሽ እንኳ ወደ ትክክለኛው የሚቀርቡ ከሆኑ የአምላክ የበኩር ልጅ ከአዳም መፈጠር በፊት ሕልቆ መሳፍርት ለሌለው ዘመን ከአባቱ ጋር ኖሯል ማለት ነው። (ከሚክያስ 5:2 ጋር አወዳደር።) ስለሆነም በሁለቱ መካከል የጠበቀና ጥልቀት ያለው ዝምድና ሊመሠረት ችሏል። ይህ የበኩር ልጅ ሰው ከመሆኑ በፊት በነበረው ሕይወት በጥበብ ተመስሎ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ዕለት ዕለት [ይሖዋን] ደስ አሰኘው ነበርሁ፤ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበር” ብሏል። (ምሳሌ 8:30) በእርግጥም የአምላክ ልጅ የፍቅር ምንጭ ከሆነው አካል ጋር ቁጥር ስፍር ለሌለው ጊዜ ተቀራርቦ መኖሩ ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ጥርጥር የለውም! (1 ዮሐንስ 4:8) ይህ ልጅ የአባቱን አስተሳሰብ፣ ስሜትና መንገድ ከሌላ ከማንም በበለጠ መንገድ ለማወቅና ለማንጸባረቅ ችሏል።—ማቴዎስ 11:27
ምድራዊ ሕይወቱና የገጠሙት ተጽዕኖዎች
7. የአምላክ የበኩር ልጅ የግድ ወደ ምድር እንዲመጣ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ ምንድን ነው?
7 የይሖዋ ዓላማ ልጁ “በድካማችን ሊራራልን” የሚችል ሩኅሩኅ ሊቀ ካህናት ሆኖ እንዲያገለግል ማዘጋጀት ስለነበረ የአምላክ ልጅ ተጨማሪ ትምህርቶችን መቅሰም ነበረበት። (ዕብራውያን 4:15) ይህ ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ምድር የመጣበት አንዱ ምክንያት ለዚህ ቦታ የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ነው። ኢየሱስ እዚህ ምድር ላይ ሥጋና ደም ለብሶ ሲኖር ቀደም ሲል በሰማይ ይመለከታቸው ብቻ የነበሩትን ሁኔታዎችና ተጽዕኖዎች ተጋርቷል። አሁን ሰዎች የሚሰማቸው ስሜት በራሱ ላይ ሊደርስ ነው። በተለያዩ ጊዜያት በድካም ዝሏል፣ ተጠምቷል እንዲሁም ተርቧል። (ማቴዎስ 4:2፤ ዮሐንስ 4:6, 7) ከዚያም በላይ የደረሰበትን ችግርና ሥቃይ በሙሉ ተቋቁሟል። በዚህ መንገድ ‘መታዘዝን ተምሮ’ ሊቀ ካህናት ሆኖ ለሚያከናውነው ሥራ ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆኗል።—ዕብራውያን 5:8-10
8. ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፈው የልጅነት ሕይወት ምን የምናውቀው ነገር አለ?
8 ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው የልጅነት ሕይወትስ ምን ይመስል ነበር? ስለ ልጅነቱ የተዘገበው ታሪክ በጣም አናሳ ነው። እንዲያውም በተወለደበት ወቅት ስለደረሱት ክንውኖች የዘገቡት ማቴዎስና ሉቃስ ብቻ ናቸው። የወንጌል ጸሐፊዎች ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ይኖር እንደነበር ያውቃሉ። ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ አጥጋቢ በሆነ መንገድ ማብራሪያ ሊያስገኝ የሚችለው ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረው ሕይወት ነው። ያም ሆኖ ግን ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሰው ነበር። ፍጹም የነበረ ቢሆንም እንኳ ትምህርት እየቀሰመ ከሕፃንነት ወደ ልጅነት ከዚያም ከጉርምስና ወደ ሙሉ ሰው ማደግ ነበረበት። (ሉቃስ 2:51, 52) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ የልጅነት ሕይወት አንዳንድ ነገሮችን ይገልጻል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ተጽዕኖ እንዳሳደሩበት ምንም ጥርጥር የለውም።
9. (ሀ) ኢየሱስ የተወለደው በድሃ ቤተሰብ ውስጥ እንደሆነ የሚጠቁም ምን ማስረጃ አለ? (ለ) ኢየሱስ ያደገው በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም?
9 ኢየሱስ በአንድ ድሃ ቤተሰብ መካከል እንደተወለደ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ይህም ኢየሱስ ከተወለደ ከ40 ቀናት በኋላ ዮሴፍና ማርያም በቤተ መቅደስ ለመሥዋዕት ካቀረቡት ነገር መረዳት ይቻላል። ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ጠቦት፣ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ የእርግብ ጫጩት ወይም አንድ ዋኖስ ይዘው ከመሄድ ይልቅ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች” ይዘው ሄዱ። (ሉቃስ 2:24 የ1980 ትርጉም ) በሙሴ ሕግ መሠረት እንዲህ ያለውን መሥዋዕት የሚያቀርቡት ደግሞ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች ናቸው። (ዘሌዋውያን 12:6-8) ከጊዜ በኋላ ይህ ዝቅተኛ ኑሮ ያለው ቤተሰብ በቁጥር እያደገ ሄደ። ኢየሱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከተወለደ በኋላ ዮሴፍና ማርያም ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ቢያንስ ስድስት ልጆችን ወልደዋል። (ማቴዎስ 13:55, 56) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ሰፊ በሆነ ምናልባትም መጠነኛ ገቢ ባለው ቤተሰብ ውስጥ አደገ።
10. ማርያም እና ዮሴፍ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች እንደነበሩ የሚያሳየው ምንድን ነው?
10 ኢየሱስን ተንከባክበው ያሳደጉት ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ናቸው። እናቱ ማርያም በጣም ጥሩ ሴት ነበረች። መልአኩ ገብርኤል ሰላምታ ሲሰጥ “ደስ ይበልሽ፣ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” እንዳላት አስታውስ። (ሉቃስ 1:28) ዮሴፍም ቢሆን ለአምላክ ያደረ ሰው ነበር። የማለፍን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም በየዓመቱ 150 ኪሎ ሜትር በእግሩ ይጓዝ ነበር። በዚህ በዓል ላይ እንዲገኙ የሚጠበቅባቸው ወንዶች ብቻ ቢሆኑም ማርያምም አብራው ትሄድ ነበር። (ዘጸአት 23:17፤ ሉቃስ 2:41) እንዲህ ባለው አንድ አጋጣሚ ዮሴፍና ማርያም የጠፋባቸውን ኢየሱስን ለማግኘት ከፍተኛ ፍለጋ ካደረጉ በኋላ የ12 ዓመቱ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ውስጥ በመምህራን መካከል ተቀምጦ አገኙት። ኢየሱስ በጣም ተጨንቀው ለነበሩት ወላጆቹ “በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። (ሉቃስ 2:49) “አባቴ” የሚለው ቃል ልጅ ለነበረው ለኢየሱስ ሞቅ ያለ የመውደድ ስሜት የሚያስተላልፍና አዎንታዊ አንድምታ የነበረው መሆን አለበት። አንደኛው ነገር፣ እውነተኛ አባቱ ይሖዋ መሆኑን ተነግሮት መሆን አለበት። ከዚህም በተጨማሪ ዮሴፍ ለእርሱ ጥሩ አሳዳጊ አባት ነበር። መቼም ይሖዋ ውድ ልጁን እንዲያሳድግለት ኃይለኛ ወይም ጨካኝ የሆነ ሰው እንደማይመርጥ የታወቀ ነው!
11. ኢየሱስ ምን ዓይነት የእጅ ሙያ ተምሮ ነበር? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በዚህ ሙያ መሥራት ምን ይጠይቅ ነበር?
11 ኢየሱስ ናዝሬት በኖረበት ዓመታት ከአሳዳጊው አባቱ ከዮሴፍ ሳይሆን አይቀርም የአናፂነትን ሙያ ተምሯል። ኢየሱስ ይህን የእጅ ሙያ ተክኖት ስለነበር እሱ ራሱ “ጸራቢው” ተብሎ ተጠርቷል። (ማርቆስ 6:3) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አናፂዎች ቤቶችን፣ (ጠረጴዛ፣ በርጩማና አግዳሚ ወንበሮችን ጨምሮ) የቤት ዕቃዎችንና የግብርና መሣሪያዎችን ይሠሩ ነበር። በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ ይኖር የነበረው ሰማዕቱ ጀስቲን ዲያሎግ ዊዝ ትራይፎ በተባለው መጽሐፉ ላይ ስለ ኢየሱስ ሲጽፍ “በአናፂነት ሙያው ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆኖ ሞፈርና ቀንበሮችን የመሥራት ልማድ ነበረው” ብሏል። በዚያ ዘመን አንድ አናፂ ለሥራው የሚጠቀምባቸውን እንጨቶች በግዢ ማግኘት ስለማይችል እንዲህ ዓይነቱ ሥራ አድካሚ ነበር። ወደ ጫካ ሄዶ ዛፍ መርጦ ከቆረጠ በኋላ ተሸክሞ ወደ ቤት የሚያመጣው ራሱ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ መተዳደሪያ ማግኘት፣ ደንበኞችን ማግባባትና ቤተሰብን በገንዘብ መደጎም ያለውን ተፈታታኝ ሁኔታ ሳይገነዘብ አይቀርም።
12. ዮሴፍ ከኢየሱስ ቀድሞ እንደ ሞተ የሚጠቁሙ አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ይህስ ኢየሱስ ምን እንዲያደርግ ይጠይቅበታል?
12 ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ እንደ መሆኑ መጠንና በተለይ ደግሞ ዮሴፍ የሞተው ከእርሱ ቀድሞ ሳይሆን ስለማይቀር ቤተሰቡን የማስተዳደሩ ኃላፊነት በእርሱ ጫንቃ ላይ ሳይወድቅ አልቀረም። b የጥር 1, 1900 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) እንዲህ ብሎ ነበር:- “ዮሴፍ የሞተው ኢየሱስ ገና ወጣት በነበረበት ጊዜ እንደሆነና በዚህም የተነሳ ኢየሱስ የአናፂነቱን ሥራ ተረክቦ ቤተሰቡን ማስተዳደር እንደጀመረ በአፈ ታሪክ ይነገራል። ይህም ኢየሱስ አናፂ እንደሆነ ተደርጎ መጠራቱ እንዲሁም እናቱና ወንድሞቹ ሲጠቀሱ ዮሴፍ ግን አለመጠቀሱ ይህን አፈ ታሪክ ቅዱሳን ጽሑፎችም በጥቂቱ የሚደግፉት ይመስላል። (ማርቆስ 6:3) . . . ይህ ሁኔታ ከተከሰተበት [በሉቃስ 2:41-49 ተመዝግቦ የሚገኘው ማለት ነው] ጊዜ አንስቶ እስከ ተጠመቀበት ጊዜ ድረስ ያለውን ማለትም ጌታችን ረዥሙን አሥራ ስምንት ዓመት ያሳለፈው የዕለት ተዕለት የኑሮ ተግባሮችን በማከናወን ሳይሆን አይቀርም።” ኢየሱስን ጨምሮ ማርያምና ልጆቿ ተወዳጅ የሆነን ባልና አባት በሞት ማጣት ምን ያህል አሳዛኝ መሆኑን እንደሚያውቁ ግልጽ ነው።
13. ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲጀምር ሌላ ማንም ሰው ያልነበረው እውቀት፣ ማስተዋልና የአዛኝነት ስሜት ነበረው የምንለው ለምንድን ነው?
13 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ የተመቻቸ ኑሮ ባለው ቤተሰብ ውስጥ አልተወለደም። ከዚያ ይልቅ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች ሕይወት ምን እንደሚመስል ቀምሷል። ከዚያም በ29 እዘአ ኢየሱስ የተሰጠውን መለኮታዊ ሥራ የሚጀምርበት ጊዜ ደረሰ። ልክ በዚያ ዓመት በውኃ ተጠመቀና የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ሆኖ እንደገና ተወለደ። በዚህ ወቅት ‘ሰማይ መከፈቱ’ አሁን ቀደም ሲል የነበረውን አስተሳሰብና ስሜት ጨምሮ ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይ የነበረውን ሕይወት ማስታወስ የሚችል መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። (ሉቃስ 3:21, 22) ስለዚህ ኢየሱስ አገልግሎቱን የጀመረው ሌላ ማንም ሰው የሌለውን እውቀት፣ ማስተዋልና ጥልቅ ስሜት ይዞ ነው። የወንጌል ጸሐፊዎች በአብዛኛው ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት ባከናወናቸው ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ያለ ምክንያት አልነበረም። እንደዚያም ሆኖ እንኳ በአገልግሎቱ ወቅት የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች በሙሉ መጻፍም አልቻሉም። (ዮሐንስ 21:25) ሆኖም እነዚህ የወንጌል ጸሐፊዎች በመንፈስ አነሳሽነት የመዘገቧቸው ነገሮች እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የነበረውን አስተሳሰብ በሚገባ እንድናውቅ ያስችሉናል።
ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው ነበር?
14. ወንጌሎች ኢየሱስ ጥልቅ የሆነ የመራራትና የአዛኝነት ስሜት እንደነበረው የገለጹት እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ ጥልቅ የሆነ የመራራትና የአዛኝነት ስሜት እንደነበረው ከወንጌል ዘገባዎች ለመረዳት ይቻላል። ለአንድ ለምጻም የርኅራኄ ስሜት በማሳየት (ማርቆስ 1:40, 41)፣ ጥሩ ምላሽ ላልሰጡ ሰዎች ከልቡ በማዘን (ሉቃስ 19:41, 42)፣ ስግብግብ በሆኑ የገንዘብ ለዋጮች ላይ የጽድቅ ቁጣ በመቆጣት የተለያየ ዓይነት ስሜት አንጸባርቋል። (ዮሐንስ 2:13-17) ኢየሱስ የሌሎችን ችግር እንደራሱ አድርጎ ይመለከት ስለነበር የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን በእንባው እንኳን ለመግለጽ ወደኋላ አይልም ነበር። በጣም አድርጎ ይወደው የነበረው አልአዛር በሞተ ጊዜ የአልአዛር እህት ማርያም ስቅስቅ ብላ ስታለቅስ ሲያያት ስሜቱ በጥልቅ ከመነካቱ የተነሳ በሰዎች ፊት እንባውን አፍስሷል።—ዮሐንስ 11:32-36
15. ኢየሱስ ሰዎችን የተመለከተበትና የያዘበት መንገድ ጥልቅ የሆነ የመራራት ስሜት እንደነበረው ያንጸባረቀው እንዴት ነበር?
15 ኢየሱስ የነበረው ከአንጀት የመራራት ስሜት በተለይ ለሰዎች በነበረው አመለካከት እንዲሁም ለእነርሱ ባደረገው አያያዝ ግልጽ ሆኖ ታይቷል። ድሆችና የተጨቆኑ ሰዎች ‘ለነፍሳቸው ዕረፍት እንዲያገኙ’ ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። (ማቴዎስ 11:4, 5, 28-30) አንዲት ደም የሚፈስሳት ሴት ልብሱን በነካች ጊዜም ይሁን አንድ ዓይነ ስውር በጩኸት ልመናውን ባበዛ ጊዜ ባደረገው ነገር እንደታየው መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማድረግ ሥራ እንደበዛበት ሆኖ አልተሰማውም። (ማቴዎስ 9:20-22፤ ማርቆስ 10:46-52) ኢየሱስ ሌሎች የሚያደርጉትን መልካም ነገር በመመልከት ያመሰግናቸው የነበረ ሲሆን አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም ተግሣጽ ለመስጠት ወደኋላ አይልም ነበር። (ማቴዎስ 16:23፤ ዮሐንስ 1:47፤ 8:44) ሴቶች ብዙ መብታቸውን በተነፈጉበት በዚያ ዘመን ኢየሱስ ሚዛናዊ የሆነ አክብሮት ይሰጣቸው ነበር። (ዮሐንስ 4:9, 27) የተወሰኑ ሴቶች በራሳቸው ወጪ እርሱን ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑት አለምክንያት አይደለም።—ሉቃስ 8:3
16. ኢየሱስ ለኑሮ ጉዳዮችና ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት እንደነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው?
16 ኢየሱስ ለኑሮ ጉዳዮች ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው። ቁሳዊ ነገሮችን በአንደኛ ቦታ አላስቀመጠም። ቁሳዊ ነገር እንዲያው ምንም አልነበረውም ለማለት ይቻላል። “ራሱን የሚያስጠጋበት” እንኳ እንደሌለው ተናግሯል። (ማቴዎስ 8:20) ሆኖም ኢየሱስ ሌሎች የሚደሰቱበትን ነገር አድርጓል። ሙዚቃ፣ ዘፈን፣ ሣቅና ጨዋታ በነበረበት በአንድ የሠርግ ድግስ ላይ የተገኘው ለመደሰት እንደሆነ ግልጽ ነው። እንዲያውም የመጀመሪያውን ተዓምር የፈጸመው በዚህ ወቅት ነበር። የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ ውኃውን “የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል” ወደተባለለት መጠጥ ማለትም ወደ ጥሩ ወይን ጠጅ ቀይሯል። (መዝሙር 104:15፤ ዮሐንስ 2:1-11) በዚህ መንገድ ዝግጅቱ ሳይቋረጥ ሊቀጥል ችሏል፤ ሙሽሮቹም ከኃፍረት ድነዋል። ኢየሱስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ብዙ ጊዜውን በአገልግሎቱ ያጠፋ እንደነበር በተደጋጋሚ ጊዜ መገለጹ ሚዛናዊነቱን የሚያሳይ ሌላ ማስረጃ ነው።—ዮሐንስ 4:34
17. ኢየሱስ የተዋጣለት አስተማሪ መሆኑ የማያስገርመን ለምንድን ነው? ትምህርቶቹስ ምን ነገር የሚያንጸባርቁ ነበሩ?
17 ኢየሱስ የተዋጣለት አስተማሪ ነበር። አብዛኞቹ ትምህርቶቹ ዕለት ተዕለት በሚያጋጥሙ እውነታዎች ላይ የተመሠረቱ ሲሆኑ እርሱም በሚገባ የሚያውቃቸው ነበሩ። (ማቴዎስ 13:33፤ ሉቃስ 15:8) በጣም ግልጽ፣ ቀላልና ተግባራዊ የሆነ የማስተማር ዘዴው አቻ የማይገኝለት ነበር። ከሁሉም ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው ግን ያስተማረው ነገር ነው። የኢየሱስ ትምህርቶች አድማጮቹ ከይሖዋ አስተሳሰብ፣ ስሜትና መንገዶች ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግ ያለውን ውስጣዊ ምኞት የሚያንጸባርቁ ነበሩ።—ዮሐንስ 17:6-8
18, 19. (ሀ) ኢየሱስ አባቱን የገለጸው በየትኞቹ ሕያው የሆኑ ቃላት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ ምን ነገር ይብራራል?
18 ኢየሱስ ምሳሌዎችን ደጋግሞ በመጠቀም አባቱን ሊረሳ በማይችል መንገድ ሕያው አድርጎ ገልጾታል። ስለ አምላክ መሐሪነት በደፈናው መናገር አንድ ነገር ነው። ሆኖም ጠፍቶ የነበረው ልጁ ተመልሶ በመጣ ጊዜ ገና ከሩቅ ሳለ ተመልክቶ ‘ሮጦ ሄዶ አንገቱ ላይ ጥምጥም ብሎ በሳመው’ ይቅር ባይ አባት ይሖዋን መመሰል ግን ሌላ ነገር ነው። (ሉቃስ 15:11-24) ኢየሱስ የሃይማኖታዊ መሪዎች ተራውን ሕዝብ በንቀት እንዲመለከቱ የሚያደርገውን አጉል ልማድ በማስወገድ አባቱ የሚሰማው በጉራ ለታይታ ጸሎት የሚያቀርበውን ፈሪሳዊ ሳይሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ ልመና የሚያቀርብን ቀረጥ ሰብሳቢ እንደሆነ በመግለጽ አባቱ በቀላሉ የሚቀረብ አምላክ መሆኑን አብራርቷል። (ሉቃስ 18:9-14) ይሖዋ ትንሿ ድንቢጥ መሬት ብትወድቅ የሚያውቅ አሳቢ አምላክ መሆኑን ኢየሱስ ሕያው በሆነ መንገድ ገልጾታል። ኢየሱስ “አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 10:29, 31) ሰዎች በኢየሱስ ‘የማስተማር ዘዴ’ የተደነቁበትና የተሳቡበት ምክንያት ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 7:28, 29) እንዲያውም በአንድ ወቅት “ብዙ ሕዝብ” ምግብ በአፋቸው ሳይዞር ለሦስት ቀናት አብረውት ቆይተዋል!—ማርቆስ 8:1, 2
19 ይሖዋ በቃሉ ውስጥ የክርስቶስን አስተሳሰብ ስለገለጠልን አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን! ታዲያ እኛስ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ የክርስቶስን አስተሳሰብ ማዳበርና ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ይህ በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መንፈሳዊ ፍጥረታት አብረዋቸው ባሉ ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታት ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ራእይ 12:3, 4 ላይ ተመልክቷል። እዚህ ጥቅስ ላይ ሰይጣን ሌሎች “ከዋክብት”ን ወይም መንፈሳዊ ልጆችን የእርሱ የዓመፅ ድርጊት ተባባሪ እንዲሆኑ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችል “ዘንዶ” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል።—ከኢዮብ 38:7 ጋር አወዳድር።
b ዮሴፍ ለመጨረሻ ጊዜ በቀጥታ የተጠቀሰው የ12 ዓመት ልጅ የነበረው ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በተገኘበት ወቅት ነው። ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት በቃና ተደርጎ በነበረው የሠርግ ግብዣ ላይ ዮሴፍ እንደተገኘ የሚገልጽ ማስረጃ የለም። (ዮሐንስ 2:1-3) በ33 እዘአ ኢየሱስ ተሰቅሎ ሳለ ማርያምን አደራ የሰጠው ለተወደደው ለሐዋርያው ዮሐንስ ነበር። ዮሴፍ በሕይወት የነበረ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ እንዲህ አያደርግም ነበር።—ዮሐንስ 19:26, 27
ታስታውሳለህን?
• ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ከማን ጋር አብሮ ይኖር ነበር?
• ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ወቅት ምን ሁኔታዎችና ተጽዕኖዎች ደርሰውበታል?
• ወንጌሎች ስለ ኢየሱስ ባሕርያት ምን ነገሮችን ገልጠውልናል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ያደገው ዝቅተኛ ኑሮ ባለው አንድ ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የ12 ዓመቱ ኢየሱስ በነበረው የማስተዋል ችሎታና በሚሰጣቸው መልሶች መምህራኑ ተገርመዋል