በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በኢይዝራኤል ምን አግኝተዋል?

በኢይዝራኤል ምን አግኝተዋል?

በኢይዝራኤል ምን አግኝተዋል?

የጥንቷ የኢይዝራኤል ከተማ የነበረችበት አካባቢ ለብዙ መቶ ዓመታት ባድማ ሆኖ ቆይቷል። በአንድ ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ነበራት። የቀድሞ ክብሯን የተገፈፈችውና በምድር ንብር የተሸፈነችው ኢይዝራኤል ዛሬ እንዲሁ አንድ ጉብታ ወይም ኮረብታ ብቻ ሆናለች። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አርኪኦሎጂስቶች የኢይዝራኤልን ፍርስራሽ መመርመር ጀምረዋል። እነዚህ ፍርስራሾች ስለ መጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ ምን የሚሉት ነገር ይኖራል?

የመጽሐፍ ቅዱስዋ ኢይዝራኤል

በኢይዝራኤል ሸለቆ ምሥራቃዊ ክፍል የምትገኘው ኢይዝራኤል ከጥንቷ እስራኤል እጅግ ለም አካባቢዎች አንዷ ነበረች። ከሸለቆው ባሻገር በስተ ሰሜን በኩል ምድያማውያን መስፍኑን ጌዴዎንን ለማጥቃት ሲዘጋጁ የሠፈሩበት የሞሬ ኮረብታ ይገኛል። ትንሽ ወደ ምሥራቅ ፈቀቅ ብሎ ደግሞ በጊልቦዓ ተራራ ግርጌ ያለው የሐሮድ ምንጭ ይገኛል። ይሖዋ ብርቱ ወታደራዊ ኃይል ሳያስፈልግ ሕዝቡን የማዳን ችሎታ እንዳለው ለማሳየት በሺዎች የሚቆጠረውን የጌዴዎን ሠራዊት ወደ 300 የቀነሰው በዚህ ምንጭ አጠገብ ነበር። (መሳፍንት 7:​1-25፤ ዘካርያስ 4:​6) የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል ከፍልስጤማውያን ጋር ባደረገው ታሪካዊ ውጊያ ድል ተነሥቶ ዮናታንና ሁለቱ ሌሎች የሳኦል ልጆች የተገደሉትና ሳኦል ራሱም የገዛ ሕይወቱን ያጠፋው እዚሁ አካባቢ በሚገኘው የጊልቦዓ ተራራ ነው።​—⁠1 ሳሙኤል 31:​1-5

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥንቷ የኢይዝራኤል ከተማ የሚሰጠው መግለጫ የተለያዩ ገጽታዎች የተንጸባረቀበት ነው። የእስራኤል ገዥዎችን የሥልጣን ብልግናና ክህደት እንዲሁም የይሖዋ አገልጋዮችን ታማኝነትና ቅንዓት ይገልጻል። በአሥረኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ የሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት ያስተዳድር የነበረው ንጉሥ አክዓብ ኦፊሴላዊ መዲናው ሰማርያ ብትሆንም ንጉሣዊ መኖሪያውን ያደረገው በኢይዝራኤል ነበር። (1 ነገሥት 20:​1) የይሖዋ ነቢይ የነበረው ኤልያስ የባዕድ አገር ሰው ከሆነችው ከአክዓብ ሚስት ከኤልዛቤል የግድያ ዛቻ የተሰነዘረበት ከኢይዝራኤል ነበር። ኤልያስ የእውነተኛውን አምላክ ማንነት በተመለከተ በቀርሜሎስ ተራራ ካቀረበው ፈተና በኋላ ያለ አንዳች ፍርሃት የበኣልን ነቢያት አስገድሎ ስለነበር ኤልዛቤል በጣም ተቆጥታ ነበር።​—⁠1 ነገሥት 18:​36–19:​2

ከዚያም በኢይዝራኤል አንድ ወንጀል ተፈጸመ። የኢይዝራኤሉ ነዋሪ ናቡቴ ተገደለ። ንጉሡ አክዓብ የናቡቴን የወይን እርሻ ተመኝቶት ነበር። ንጉሡ የእርሻ ቦታውን እንዲሰጠው በጠየቀ ጊዜ ናቡቴ በታማኝነት “የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ” ሲል መለሰ። ይህ በመሠረታዊ ሥርዓት የተደገፈ ምላሽ አክዓብን አስከፋው። የንጉሡን መቆዘም ያየችው ንግሥት ኤልዛቤል የይስሙላ ሸንጎ አቋቋመችና ናቡቴ አምላክን ተሳድቧል ተብሎ ተከሰሰ። ምስኪኑ ናቡቴ በጥፋተኝነት ተወነጀለና በድንጋይ ተወግሮ ተገደለ። ንጉሡም የወይን እርሻውን ወሰደ።​—⁠1 ነገሥት 20:​1-16

ከዚህ ክፉ ሥራ የተነሣ ኤልያስ “በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ ኤልዛቤልን ውሾች ይበሉአታል” ብሎ ትንቢት ተናገረ። ነቢዩ በመቀጠልም እንዲህ ብሏል:- “ከአክዓብም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል . . . በእግዚአብሔር ፊት ክፋት ለመሥራት ራሱን እንደ ሸጠ፣ ሚስቱም ኤልዛቤል እንደ ነዳችው፣ እንደ አክዓብ ያለ ሰው አልነበረም።” ይሁን እንጂ ኤልያስ የይሖዋን ፍርድ በነገረው ጊዜ አክዓብ ራሱን በማዋረዱ ይሖዋ ቅጣቱ በእርሱ ዘመን እንደማይፈጸም ተናግሯል። (1 ነገሥት 20:​23-29) የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ በመቀጠል በኤልያስ እግር በተተካው በኤልሳዕ ዘመን ኢዩ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ይገልጻል። ኢዩ ወደ ኢይዝራኤል እየጋለበ ከሄደ በኋላ ኤልዛቤል በቤተ መንግሥቷ መስኮት በኩል እንድትወረወር ትእዛዝ ሰጠ። እርሷም ከፈረሶቹ እግር አጠገብ ተፈጠፈጠች። ከዚያ በኋላ ቆሻሻ የሚለቃቅሙ ውሾች በልተዋት ከጭንቅላቷ አጥንት፣ ከእግርዋና ከእጆቿ መዳፍ በቀር ሌላ ነገር አልተገኘም። (2 ነገሥት 9:​30-37) ከኢይዝራኤል ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው የመጨረሻው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክንውን ከአክዓብ 70 ልጆች መገደል በኋላ የሆነው ነገር ነው። ኢዩ ራሶቻቸውን በኢይዝራኤል ከተማ መግቢያ ላይ በሁለት ክምር ቆለለው። ከዚያም ከአክዓብ ከሃዲ ንጉሣዊ ግዛት ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ታላላቆችና ካህናት ገድሏል።​—⁠2 ነገሥት 10:​6-11

አርኪኦሎጂስቶች ምን አግኝተዋል?

ኢይዝራኤል በነበረችበት ቦታ ላይ የጋራ የቁፋሮ ምርምር ፕሮጄክት በ1990 ተጀመረ። በዚህ ምርምር የተሳተፉት (በዴቪድ ኡሲሽኪን የተወከለው) የቴልአቪቭ ዩኒቨርሲቲ አርኪኦሎጂ ተቋም እና (በጂን ዉድሄድ የተወከለው) በኢየሩሳሌም የሚገኘው የብሪቲሽ የአርኪኦሎጂ ትምህርት ቤት ናቸው። ከ1990-96 ባሉት ዓመታት ለሰባት ወቅቶች (እያንዳንዱ ወቅት ስድስት ሳምንት ያህል ይኖረዋል) በቁፋሮው ቦታ ላይ ከ80 እስከ 100 የሚደርሱ ፈቃደኛ ሠራተኞች ተሰማርተው ቆይተዋል።

ዘመናዊው የአርኪኦሎጂ ምርምር የሚካሄደው ቀደም ሲሉ ከነበሩት አመለካከቶችና ቲዮሪዎች ነፃ በሆነ መልኩ በቁፋሮው ቦታ ላይ የተገኙትን ማስረጃዎች ብቻ በማስመርኮዝ ነው። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ ተጠቀሰው ምድር የሚያጠኑት አርኪኦሎጂስቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ የመጨረሻው ዳኛ እንደሆነ አድርገው አይመለከቱትም። ሌሎቹን ምንጮችና ግዑዝ ማስረጃዎች ሁሉ ይመረምራሉ በጥንቃቄም ይመዝናሉ። ይሁን እንጂ ጆን ዉድሄድ እንደተናገሩት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ጥቂት ምዕራፎች ውጭ የኢይዝራኤልን ከተማ በተመለከተ ምንም ዓይነት ጥንታዊ የጽሑፍ ማስረጃ የለም። በመሆኑም የትኛውም ምርምር ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱሱን ዘገባና የዘመን ስሌት ከግምት ውስጥ ማስገባቱ ግድ ነው። የአርኪኦሎጂስቶቹ ጥረት ምን ውጤት አስገኝቷል?

ቅጥሮቿና የሸክላ ሥራዎቿ ተቆፍረው እንደወጡ ፍርስራሾቹ የብረት ዘመን በሚባለው ጊዜ የነበሩ መሆናቸው ከወዲሁ ተረጋገጠ። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰችው ኢይዝራኤል የነበረችበት ትክክለኛ ዘመን ነው። ይሁን እንጂ ቁፋሮው ሲቀጥል በርካታ አስገራሚ ነገሮች ተገኝተዋል። የመጀመሪያው ነገር የቦታው ስፋትና ግዙፍ የሆኑት ቅጥሮቹ ናቸው። አርኪኦሎጂስቶቹ የጠበቁት የእስራኤል መንግሥት ዋና ከተማ ከነበረችው ከጥንቷ ሰማርያ ቅጥሮች ጋር የሚመጣጠን ቅጥር ያለው ቦታ ነበር። ይሁን እንጂ ቁፋሮአቸውን ሲቀጥሉ ኢይዝራኤል ከዚያ ይበልጥ ትልቅ መሆኗን ተገነዘቡ። 300 ሜትር በ150 ሜትር የሚያክል ስፋት ያለው የተቀጠረው የከተማዋ ክልል በዘመኑ ከነበሩትና በእስራኤል በቁፋሮ ከተገኙት ከተሞች ሁሉ ሦስት እጥፍ ያህል የሚበልጥ ነበር። በደረቅ ቦይ የተከበበች ሲሆን ከቅጥሩ ሰባት ሜትር የሚደርስ ጥልቀት ነበረው። እንደ ፕሮፌሰር ኡሲሽኪን አባባል ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንዲህ ያለው ቦይ የተለመደ ነገር አልነበረም። “እስከ መስቀል ጦርነት ተፋላሚዎች ድረስ በእስራኤል ውስጥ በየትኛውም ቦታ ይህን የመሰለ ነገር አናገኝም” ብለዋል።

ሌላው እንግዳ የሆነው ገጽታ ደግሞ በከተማዋ መካከል ግዙፍ ግንባታዎች አለመኖራቸው ነው። ከተማዋ በተሠራችበት ወቅት የመጣውን ከፍተኛ መጠን ያለው ቡናማ ቀይ አፈር በቅጥሩ ውስጥ በመደልደል ከመሬት ከፍ ያለ እንደ መድረክ ያለ ነገር ገንብተዋል። በቴል ኢይዝራኤል የተከናወነውን ቁፋሮ በተመለከተ የወጣው ሁለተኛው መቅድም ሪፖርት እንደጠቆመው ከሆነ ይህ ከሩቅ የሚታይ ጉብታ ኢይዝራኤል ከንጉሣዊ መኖሪያነትም ሌላ ዓላማ እንደነበራት የሚጠቁም ማስረጃ ሊሆን ይችላል። ሪፖርቱ እንዲህ ብሏል:- “በዘንበራውያን [በዘንበሪና በልጆቹ] ነገሥታት ዘመን ለእስራኤል ንጉሣዊ ሠራዊት እንደ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ሆና የምታገለግል . . . የንጉሡ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የሚቀመጡባትና የሚሰለጥኑባት ማዕከል ልትሆን የምትችልበትም አጋጣሚ እንዳለ መጠቆም እንወዳለን።” ዉድሄድ ከፍ ካለው ጉብታ መጠንና ዙሪያውን ካለው ቅጥር በመነሳት ይህ በወቅቱ በመካከለኛው ምሥራቅ ከሁሉ ይበልጥ ግዙፍ የነበረውን የሠረገላ ሠራዊት ጡንቻ ለማሳየት ሲባል ወታደራዊ ሰልፍ ይካሄድበት የነበረ ቦታ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ሰንዝረዋል።

ተቆፍረው የወጡት የከተማዋ በር ቅሪቶችም የአርኪኦሎጂስቶቹን ትኩረት የሳቡ ልዩ ገጽታዎች ናቸው። ቢያንስ አራት የዘበኛ ጓዳ የነበራቸው መግቢያዎች እንደነበሩ ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ ባለፉት መቶ ዘመናት በቦታው የነበሩ ብዙ ድንጋዮች በመወሰዳቸው አሁን ያለው ሁኔታ እንዲህ ነበር ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር አይደለም። ዉድሄድ በመጊዶ፣ በአሶርና በጌዝር ከነበሩት ጋር ተመሳሳይ መጠን ያላቸው ባለ ስድስት ጓዳ መግቢያዎች እንደነበሩ ከቅሪቶቹ መረዳት ይቻላል የሚል ሐሳብ አላቸው። a

የአርኪኦሎጂ ግኝቶቹ በሙሉ የሚጠቁሙት ከወታደራዊም ሆነ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር በጣም አመቺ ቦታ ላይ ትገኝ የነበረችው ከተማ የቆየችው በጣም አጭር ለሆነ ጊዜ ብቻ እንደነበር ነው። ዉድሄድ ኢይዝራኤል በቅጥር የተከበበች ታላቅ ከተማ ብትሆንም በአንድ የተወሰነ ዘመን ብቻ የነበረችና ለጥቂት አሥርተ ዓመታት ያገለገለች ከተማ መሆኗን አጽንዖት ሰጥተውታል። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቁልፍ ቦታ ከነበራቸውና እንደ መጊዶ፣ አሶር እና እንደ ዋና ከተማዋ ሰማርያ ካሉት ከተሞች ፍጹም የተለየ ነው። እነዚህ ከተሞች በተደጋጋሚ ተገንብተዋል፣ ተስፋፍተው ተሠርተዋል እንዲሁም በተለያዩ ዘመናት ሰዎች ኖረውባቸዋል። ታዲያ ይህች ቁልፍ ቦታ ላይ የተቀመጠች ከተማ በአጭር ጊዜ ውስጥ የከሰመችው ለምንድን ነው? እንደ ዉድሄድ ግምታዊ አስተያየት ከሆነ አክዓብና ሥርወ መንግሥቱ የብሔሩን ጥሪት በማባከናቸው ኢኮኖሚያዊ ውድቀት አስከትለው ነበር። የኢይዝራኤልም ስፋትና ጥንካሬ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። አዲሱ የኢዩ አገዛዝ አክዓብ ያከናወነው ነገር ሁሉ ፈጽሞ እንዲረሳ ስለፈለገ ከተማዋን ሆን ብሎ ትቷት ሊሆን ይችላል።

እስከዚህ ጊዜ ድረስ የተገኙት የቁፋሮ ማስረጃዎች በሙሉ ኢይዝራኤል የብረት ዘመን በመባል በሚታወቀው ጊዜ ከፍ ያለ ቦታ የነበራት የእስራኤላውያን ማዕከል እንደነበረች ይጠቁማሉ። ስፋቷና ቅጥሮቿ የአክዓብና የኤልዛቤል መኖሪያ የነበረች ጎላ ያለ ስፍራ የነበራት ቦታ ስለመሆኗ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው መግለጫ ጋር ይስማማል። በዚህ ዘመን ይኖርባት የነበረው የሕዝብ ብዛት በጣም ውስን መሆኑን የሚጠቁሙት ምልክቶች ከተማዋን በሚመለከት በመጽሐፍ ቅዱስ ከሚገኘው ዘገባ ጋር ይስማማሉ:- በአክዓብ ዘመን በአጭር ጊዜ ውስጥ የላቀ ስፍራ ተሰጥቷት ከቆየ በኋላ በይሖዋ ትእዛዝ ኢዩ “ከአክዓብ ቤት የቀረውን ሁሉ፣ ታላላቆቹንም ሁሉ፣ ወዳጆቹንና ካህናቱን ማንም ሳይቀር በኢይዝራኤል” በገደላቸው ጊዜ ከተማዋ የነበራት ክብር ጠፍቷል።​—⁠2 ነገሥት 10:​11

የኢይዝራኤል ዕድሜ ሲሰላ

ጆን ዉድሄድ “በአርኪኦሎጂ ትክክለኛውን ዘመን ለመናገር የሚያስችል ተጨባጭ መሠረት ማግኘት አስቸጋሪ ነው” ሲሉ ሐቁን ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። በመሆኑም አርኪኦሎጂስቶቹ በሰባቱ ዓመታት ቁፋሮአቸው ያገኙትን ውጤት ሲያጠኑ በሌሎች የአርኪኦሎጂ ቁፋሮ ቦታዎች ከተገኙት ውጤቶች ጋር አወዳድረውታል። ይህም አንዳንዶቹ ነገሮች እንደገና እንዲጤኑ ወይም ክርክር እንዲነሣ ምክንያት ሆኗል። ለምን? ምክንያቱም እስራኤላዊው አርኪኦሎጂስት ዪጌል ያዴን በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በመጊዶ ካከናወኗቸው ቁፈራዎች በኋላ በአርኪኦሎጂው ዓለም ያሉ ብዙዎች ዪጌል በሰሎሞን ዘመን የተሠሩ ቅጥሮችንና የከተማዎችን በሮች እንዳገኙ አድርገው ያምኑ ነበር። በኢይዝራኤል የተገኙት ቅጥሮች፣ የሸክላ ሥራዎችና በሮች ግን አንዳንዶች እነዚህን መደምደሚያዎች እንዲጠራጠሩ እያደረጓቸው ነው።

ለምሳሌ ያህል በኢይዝራኤል የተገኘው የሸክላ ሥራ ያዴን ከሰሎሞን ዘመን ጋር ካያያዙት የመጊዶ ንብብር ጋር ተመሳሳይ ነው። የሁለቱም ቦታዎች የበሮቹ አሠራርና ስፋት ፍጹም አንድ ዓይነት ነው ባይባልም ተመሳሳይ ነው። ዉድሄድ እንዲህ ብለዋል:- “እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች አንድም ኢይዝራኤል በሰሎሞን ዘመን እንደነበረች ያረጋግጣሉ፤ አለዚያም ደግሞ ሌሎቹን ቦታዎች [መጊዶና አሶር] በአክዓብ ዘመን እንደነበሩ የሚያረጋግጡ ናቸው።” መጽሐፍ ቅዱስ ኢይዝራኤል በአክዓብ ዘመን የነበረች መሆኗን በግልጽ ስለሚናገር ይህ ንብብር የሚያመለክተው የአክዓብን የግዛት ዘመን ነው ብሎ ማመኑን ምክንያታዊ ሆኖ አግኝተውታል። ዴቪድ ኡሲሽኪን እንዲህ ሲሉ ተስማምተዋል:- “መጽሐፍ ቅዱስ ሰሎሞን መጊዶን እንደገነባ ይናገር እንጂ እነዚያን በሮች ስለመገንባቱ ምንም የሚገልጸው ነገር የለም።”

የኢይዝራኤል ታሪክ ሊታወቅ ይችላልን?

እነዚህ የአርኪኦሎጂ ግኝቶችና እነርሱን ተከትለው የተነሡት ክርክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢይዝራኤልም ሆነ ስለ ሰሎሞን የሚናገረውን ዘገባ ጥያቄ ላይ የሚጥል ነውን? እርግጥ አርኪኦሎጂያዊ ውዝግቡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር በቀጥታ የሚያገናኘው ነገር የለም ለማለት ይቻላል። አርኪኦሎጂ ታሪክን የሚያጠናበት መሠረቱ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው ትረካ የተለየ ነው። የሚያነሳው ጥያቄም ሆነ አጽንዖት የሚሰጥበት ነገር ፈጽሞ የተለየ ነው። አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪና አርኪኦሎጂስት ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ ትይዩ በሆኑ ሁለት አቅጣጫዎች እንደሚጓዙ መንገደኞች አድርጎ መቁጠር ይቻላል። አንደኛው ተጓዥ በአውራ ጎዳናው ላይ ሲያሽከረክር ሌላኛው ደግሞ በእግረኛው መንገድ ላይ በእግሩ ይሄዳል። የትኩረት አቅጣጫቸውና የሚያሳስባቸው ነገር የተለያየ ነው። ይሁንና እይታቸው ብዙውን ጊዜ የሚቃረን ሳይሆን የሚደጋገፍ ነው። የሁለቱን ተጓዦች አስተያየት ማገናዘብ ተጨማሪ ማስተዋል ለማግኘት ሊረዳ ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ጥንት ስለተከናወኑ ነገሮችና በዚያን ጊዜ ስለነበሩ ሰዎች በጽሑፍ የሰፈረ ዘገባ ይዟል። አርኪኦሎጂ ደግሞ በአፈር ውስጥ ተቀብሮ የሚገኘውን ማንኛውንም ዓይነት መረጃ በማሰባሰብ ስለ እነዚህ ክንውኖችና ሕዝቦች የሚታወቀውን መረጃ ለማግኘት ይሞክራል። ይሁን እንጂ ባብዛኛው እንደዚህ ያሉት ቅሪቶች ያልተሟሉና የተለያየ ዓይነት ትርጓሜ ሊሰጣቸው የሚችሉ ናቸው። በዚህ ረገድ አርኪኦሎጂ ኦቭ ዘ ላንድ ኦቭ ዘ ባይብል​—⁠10, 000-​586 ቢ ሲ ኢ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ አሜሃይ ማዛር እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “የአርኪኦሎጂ የመስክ ሥራ . . . ባብዛኛው የግል ጥበብ እንዲሁም የሥልጠናና የሙያዊ ክህሎት ጥምረት ነው። ስኬት ለማግኘት የሚያስችል ድርቅ ያለ ፎርሙላ የሌለ ሲሆን የመስክ ዲሬክተሮች ከሁኔታው ጋር ተስማምተው መሥራታቸውና የፈጠራ ችሎታቸውን መጠቀማቸው የግድ አስፈላጊ ነው። አንድ አርኪኦሎጂስት ያለው ባሕርይ፣ ተሰጥዎና ተፈጥሮአዊ የማመዛዘን ችሎታ የሚኖረው ጠቀሜታ ካገኘው ሥልጠናና ከቀረቡለት መረጃዎች ያልተናነሰ ነው።”

አርኪኦሎጂ በኢይዝራኤል ከፍተኛ የንጉሡ ወታደራዊ ተቋም እንደነበርና መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው ጋር በሚስማማ መንገድ በአክዓብ ዘመን በጣም አጭር ለሆነ ጊዜ ብቻ እንደቆየች አረጋግጧል። አርኪኦሎጂስቶች ገና በመጪዎቹ ዓመታት ሊያጠኗቸው የሚችሉ ብዙ አመራማሪ ጥያቄዎች ተነሥተዋል። ይሁን አንጂ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ አርኪኦሎጂ ፍጹም ሊወዳደረው በማይችል መንገድ የተሟላውን ታሪክ በማስቀመጥ በግልጽ መናገሩን ይቀጥላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በነሐሴ 15, 1988 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ የሚገኘውን “የበሮቹ ምሥጢር” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢይዝራኤል የተደረጉ አርኪኦሎጂያዊ ቁፋሮዎች

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢይዝራኤል የተገኘ የከነዓናውያን ጣዖት