በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን ለማገልገል ኑሮን ቀላል ማድረግ

ይሖዋን ለማገልገል ኑሮን ቀላል ማድረግ

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋን ለማገልገል ኑሮን ቀላል ማድረግ

ክላራ ገርበር ሞየር እንደተናገረችው

ዕድሜዬ 92 ዓመት ሲሆን የምራመደው በትግል ነው። ሆኖም ንቁና በደንብ የሚያስታውስ አእምሮ አለኝ። ከልጅነቴ አንስቶ ይሖዋን የማገልገል መብት በማግኘቴ ምንኛ አመስጋኝ ነኝ! ኑሮዬን ቀላል ማድረጌ ይህን ውድ ሀብት እንዳገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ነሐሴ 18, 1907 በአሊያንስ፣ ኦሃዮ፣ ዩ ኤስ ኤ የተወለድኩ ሲሆን ከአምስት ልጆች መካከል የመጀመሪያዋ ነኝ። የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ አንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚታወቁበት ስም ነው) የወተት ላሞችን ወደምናረባበት ቦታ በብስክሌት መጣ። እናቴን ላውራ ገርበርን በር ላይ አገኛትና አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት ታውቅ እንደሆነ ጠየቃት። እማዬ ይህ ጥያቄ ሁልጊዜ በአእምሮዋ ይጉላላ ነበር።

ወደ በረቱ ሄዳ አባዬን ካማከረችው በኋላ በስድስት ጥራዝ የተዘጋጁትን የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት (እንግሊዝኛ) የተባሉትን መጻሕፍት እንዲያመጣላት ጠየቀችው። መጻሕፍቱን በከፍተኛ ጉጉት ከማንበቧም በላይ የተማረችው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በጥልቅ ነካት። አዲስ ፍጥረት የተባለውን ስድስተኛውን ጥራዝ ካጠናች በኋላ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ ክርስቲያናዊ ጥምቀት ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን በግልጽ ተረዳች። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹን እንዴት ማግኘት እንደምትችል ስላላወቀች፣ ምንም እንኳ ወቅቱ የቅዝቃዜ ወር ቢሆንም መጋቢት 1916 ላይ በከብት እርባታው ቦታ በሚገኝ የቦይ ውኃ ውስጥ አባዬ እንዲያጠምቃት ጠየቀችው።

ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ እማዬ አሊያንስ በሚገኘው ዶውተርስ ኦቭ ቬተራንስ በተባለው አዳራሽ ውስጥ ንግግር እንደሚሰጥ የሚገልጽ አንድ ማስታወቂያ ጋዜጣ ላይ አነበበች። የንግግሩ ርዕስ “ዘ ዲቫይን ፕላን ኦቭ ዚ ኤጅስ” የሚል ነበር። የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት ጥራዝ 1 ከንግግሩ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ርዕስ ስለነበረው እማዬ ስብሰባው ላይ ለመገኘት ወዲያውኑ ወሰነች። በፈረስ የሚጎተት ጋሪ ተዘጋጀና መላ ቤተሰቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደተገኘበት ስብሰባ በፈረስና በጋሪ ሄድን። ከዚያን ጊዜ አንስቶ እሁድና ረቡዕ ማታ ወንድሞች ቤት በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርን። ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እማዬን የክርስቲያን ጉባኤ ተወካይ የሆነ ሰው እንደገና አጠመቃት። ሁልጊዜ በግብርና ሥራ ይጠመድ የነበረው አባዬም የኋላ ኋላ መጽሐፍ ቅዱስ የማጥናት ፍላጎት አደረበትና ከጥቂት ዓመታት በኋላ ተጠመቀ።

ኃላፊነት ካላቸው ወንድሞች ጋር ተገናኘን

ሰኔ 10, 1917 በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ “ብሔራት የሚዋጉት ለምንድን ነው?” በሚል ርዕስ ንግግር ለመስጠት ወደ አሊያንስ መጣ። የዘጠኝ ዓመት ልጅ የነበርኩ ሲሆን ከወላጆቼ እንዲሁም ዊሊና ቻርለስ ከሚባሉት ወንድሞቼ ጋር በስብሰባው ተገኘሁ። ስብሰባው ላይ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች የተገኙ ሲሆን ይህም ግሩም የተሰብሳቢዎች ቁጥር ነበር። የወንድም ራዘርፎርድ ንግግር ካበቃ በኋላ ስብሰባው ላይ የተገኙ አብዛኞቹ ሰዎች ንግግሩ በተሰጠበት የኮሎምቢያ ቲያትር በራፍ ላይ ፎቶ ተነሱ። በቀጣዩ ሳምንት በዚሁ አዳራሽ ኤ ኤች ማክሚላን “የሚመጣው የአምላክ መንግሥት” በሚል ርዕስ ንግግር ሰጠ። እነዚህ ወንድሞች ወደ ትንሿ ከተማችን መምጣታቸው ትልቅ መብት ነበር።

ቀደም ባሉት ጊዜያት የተደረጉ የማይረሱ የአውራጃ ስብሰባዎች

ለመጀመሪያ ጊዜ በአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኘሁት በ1918 ሲሆን ከአሊያንስ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኘው በአትዎተር ኦሃዮ ነበር። እማዬ ስብሰባው ላይ የነበረውን የማኅበሩን ተወካይ ዕድሜዬ ለጥምቀት ደርሶ እንደሆነ ጠየቀችው። የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ለእሱ ትርጉም ያለው ውሳኔ እንዳደረግሁ ስለተሰማኝ በአንድ ትልቅ የፖም እርሻ አጠገብ በሚገኝ ጅረት ውስጥ የዚያኑ ዕለት እንድጠመቅ ተፈቀደልኝ። ወንድሞች ለልብስ መቀየሪያ ብለው በተከሉት ድንኳን ውስጥ ልብሴን ቀየርኩና አንድ ያረጀ ወፍራም የሌሊት ልብስ ለብሼ ተጠመቅሁ።

መስከረም 1919 ከወላጆቼ ጋር ሆኜ ኢሪ ሐይቅን አቋርጠን ወደ ሳንደስኪ ኦሃዮ በባቡር ተጓዝን። እዚያ እንደደረስን በጀልባ ተሳፈርንና ፈጽሞ የማይረሳው የአውራጃ ስብሰባ ወደሚደረግበት ወደ ሴዳር ፖይንት በአጭር ጊዜ ውስጥ ደረስን። ከጀልባው ስንወርድ ወደቡ ላይ አንድ ትንሽ የምግብ መሸጫ ነበር። ሀምበርገር ገዛሁ። በዚያ ወቅት ይህ ለእኔ እንደ ቅንጦት ምግብ ነበር። እጅ ያስቆረጥም ነበር! ለስምንት ቀን በቆየው የአውራጃ ስብሰባችን ላይ 7, 000 የደረሰ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ነበረን። የድምፅ መሣሪያ ስላልነበረ በጥንቃቄ ማዳመጥ ነበረብኝ።

በዚህ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የመጠበቂያ ግንብ ተጓዳኝ የሆነው ወርቃማው ዘመን (አሁን ንቁ! ) የሚባለው መጽሔት መውጣቱ ተገለጸ። አውራጃ ስብሰባው ላይ ለመገኘት ስል የመጀመሪያው ሳምንት ትምህርት አምልጦኛል፤ ሆኖም የሚያስቆጭ አልነበረም። ሴዳር ፖይንት ለዕረፍት የሚኬድበት ቦታ ሲሆን እዚያ ባለው ምግብ ቤት ለስብሰባ ለመጡት እንግዶች ምግብ የሚያዘጋጁ የወጥ ቤት ሠራተኞችም ነበሩ። ይሁን እንጂ የወጥ ቤት ሠራተኞቹና አስተናጋጆቹ በሆነ ምክንያት የሥራ ማቆም አድማ መትተው ስለነበር ምግብ የመሥራት ችሎታ የነበራቸው ወንድሞች ለስብሰባ ለመጡት እንግዶች ምግብ የማዘጋጀቱን ሥራ ያቀላጥፉት ጀመር። ከዚህ በኋላ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የይሖዋ ሕዝቦች በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የሚመገቡትን ምግብ ራሳቸው አዘጋጅተዋል።

በተጨማሪም ከ18, 000 በላይ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር በተመዘገበበት መስከረም 1922 በተካሄደው የዘጠኝ ቀን የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እንደገና ወደ ሴዳር ፖይንት የመሄድ መብት አገኘን። ወንድም ራዘርፎርድ “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ” የሚል ማበረታቻ የሰጠን በዚህ ስብሰባ ላይ ነበር። እኔ ግን የተወሰኑ ዓመታት ቀደም ብሎ ትራክት እና ወርቃማው ዘመን የተባለውን መጽሔት በማሰራጨት አገልግሎት ጀምሬ ነበር።

ለአገልግሎቱ የነበረኝ አድናቆት

በ1918 መጀመሪያ ላይ በአቅራቢያችን በሚገኙ የእርሻ ቦታዎች የባቢሎን ውድቀት (እንግሊዝኛ) የተባለውን ትራክት በማሠራጨቱ ሥራ ተካፍያለሁ። ከፍተኛ ቅዝቃዜ ስለነበር ቤት ውስጥ የእንጨት ምድጃው ላይ ድንጋይ እናሞቅና እግራችን ሙቀት እንዲያገኝ ጋሪው ላይ ጭነን እንወስድ ነበር። ጋሪው ከላይና ከጎን መሸፈኛ ይኑረው እንጂ ማሞቂያ ስላልነበረው ወፍራም ካፖርትና ኮፍያ እንለብስ ነበር። ይሁንና እነዚያ ጊዜያት አስደሳች ነበሩ።

በ1920 ያለቀለት ምሥጢር የተባለው መጽሐፍ አንድ ልዩ እትም ዜድ ጂ በሚል ስያሜ በመጽሔት መልክ ተዘጋጀ። a እኔና ወላጆቼ አሊያንስ ውስጥ ይህን ጽሑፍ ይዘን ለአገልግሎት ወጣን። በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ ሰው በር የሚያንኳኳው ብቻውን ነበር። በመሆኑም ብዙ ሰዎች ተቀምጠው ወደነበረበት በረንዳ የሚያደርሰውን ደረጃ የወጣሁት ፈራ ተባ እያልኩ ነበር። መጽሔቱን አስተዋውቄ እንደጨረስኩ አንዲት ሴት “አጠር ያለ ቆንጆ ንግግር መስጠት ትችልበት የለም እንዴ” ብላ ጽሑፉን ወሰደች። ከቤት ወደ ቤት ሳገለግል ለመጀመሪያ ጊዜ ረዘም ያለ መደበኛ አቀራረብ በተጠቀምኩበት በዚያን ዕለት 13 ዜድ ጂ መጽሔቶች አበረከትኩ።

የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ እናቴ የሳንባ ምች ያዛትና ከአንድ ወር ለሚበልጥ የአልጋ ቁራኛ ሆነች። ትንሿ እህቴ ሐዜል ሕፃን ልጅ ስለነበረች በከብት እርባታው ሥራ ለማገዝና ልጆቹን ለመንከባከብ ስል ትምህርቴን አቋረጥኩ። ይህም ሆኖ ቤተሰባችን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በቁም ነገር ከመያዙም በላይ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በቋሚነት እንገኝ ነበር።

በ1928 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ “ዘጠኙ ወዴት ሄዱ?” የሚል ርዕስ ያለው ትራክት በስብሰባው ለተገኙት በሙሉ ታደለ። ትራክቱ በተአምራዊ መንገድ ከተፈወሱት አሥር ለምጻሞች መካከል በትሕትና ኢየሱስን ያመሰገነው አንዱ ብቻ ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ በሉቃስ 17:​11-19 ላይ የሚናገረውን ያብራራ ነበር። ይህ ነጥብ ልቤን ነካው። ‘አድናቆቴ ምን ያህል ነው?’ ስል ራሴን ጠየቅሁ።

ቤታችን ውስጥ ነገሮች መልክ እየያዙ ስለመጡና እኔም ጥሩ ጤንነት ስለነበረኝ እንዲሁም ከባድ ኃላፊነት ስላልነበረብኝ ከቤተሰቦቼ ተለይቼ የአቅኚነት አገልግሎት (የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መጠሪያ ነው) ለመጀመር ወሰንኩ። ወላጆቼም አቅኚ እንድሆን አበረታቱኝ። በመሆኑም እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ ኤግነስ አሌታ ምድብ ቦታችን ተነገረንና ነሐሴ 28, 1928 ከምሽቱ 3:​00 ሰዓት ላይ ባቡር ተሳፈርን። ሁለታችንም የየራሳችን ሻንጣ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን የምንይዝበት አንድ ቦርሳ ነበረን። ባቡር ጣቢያው ላይ እኛም ሆንን እህቶቼና ወላጆቼ ተላቀስን። አርማጌዶን በቅርብ እንደሚመጣ እናምን ስለነበር ጨርሶ እንደገና ላላያቸው እንደምችል ተሰምቶኝ ነበር። በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ምድብ ቦታችን ብሩክስቪል፣ ኬንተኪ ደረስን።

አንዲት ትንሽ ክፍል ተከራየንና የምንበላውን የታሸገ ስፓጌቲ ገዛን፤ ሳንድዊችም አዘጋጀን። በየቀኑ በተለያየ አቅጣጫ ለብቻችን እያገለገልን በቤታቸው የምናገኛቸውን ሰዎች 1.98 የአሜሪካ ዶላር አስተዋጽኦ በማድረግ አምስት የተጠረዙ መጻሕፍት እንዲወስዱ እንጠይቃቸው ነበር። ቀስ በቀስ ከተማውን ያዳረስን ሲሆን ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ፍላጎት ያላቸው በርካታ ሰዎችም አገኘን።

በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ በብሩክስቪልና በአውጉስታ እንዲሁም በአቅራቢያቸው የሚኖሩትን ሰዎች ባጠቃላይ አነጋገርን። ስለዚህ በሜይዝቪል፣ ፓሪስና ሪችሞንድ ለማገልገል አካባቢ ቀየርን። በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት አንድም ጉባኤ ያልነበረባቸውን በኬንተኪ የሚገኙ በርካታ ወረዳዎችን ሸፈንን። አብዛኛውን ጊዜ ጓደኞቻችንና አንዳንድ ቤተሰቦች ከኦሃዮ መጥተው ለሳምንት ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ ከእኛ ጋር በማገልገል ያግዙን ነበር።

ሌሎች የማይረሱ የአውራጃ ስብሰባዎች

ከሐምሌ 24-30, 1931 በኮለምበስ ኦሃዮ የተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ፈጽሞ የማይረሳ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተው የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስም እንደምንጠራ ማስታወቂያ የተነገረው በዚህ ስብሰባ ላይ ነበር። (ኢሳይያስ 43:​12) ከዚህ በፊት ሰዎች ሃይማኖታችንን ሲጠይቁን “ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች” ብለን እንነግራቸው ነበር። ሆኖም ከተለያዩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ጋር የቅርብ ትስስር ያላቸው ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስለነበሩ ይህ ስም በትክክል ለይቶ አያሳውቀንም ነበር።

የአገልግሎት ጓደኛዬ ኤግነስ ስታገባ ብቻዬን ቀርቼ ነበር። ስለዚህ አብሯቸው የሚያገለግል አቅኚ የሚፈልጉ ሁሉ አንድ ቦታ መጥተው እንዲያሳውቁ በማስታወቂያ ሲነገር በጣም ተደሰትኩ። እዚያ ሄጄ ከቤርታና ከኤልሲ ጋርቲ እንዲሁም ከቤሲ ኢንስሚንገር ጋር ተገናኘሁ። ሁለት መኪናዎች የነበሯቸው ሲሆን አብራቸው የምታገለግል አራተኛ አቅኚ እህት ይፈልጉ ነበር። ምንም እንኳ ከዚህ ቀደም ጭራሽ የማንተዋወቅ ብንሆንም ከስብሰባው በኋላ አብረን ሄድን።

በበጋው የፔንሲልቬኒያን ክልል ከዳር እስከ ዳር አዳረስን። ከዚያም ክረምት ከመግባቱ በፊት ሞቃታማ በሆኑት ደቡባዊ ክፍሎች ማለትም በሰሜን ካሮላይና፣ ቨርጂኒያና ሜሪላንድ የአገልግሎት ምድብ እንዲሰጠን ጠየቅን። ጸደይ ሲገባ ወደ ሰሜናዊ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስን። በዚያን ጊዜ አቅኚዎች እንዲህ የማድረግ ልማድ ነበራቸው። ይህን ልማድ ይከተሉ የነበሩት ጆን ቡዝ እና ሩዶልፍ አቡል በ1934 ራልፍ ሞየርንና ታናሽ ወንድሙ ዊላርድን ይዘው ወደ ሐዛርድ፣ ኬንተኪ ተጓዙ።

በተለያዩ አጋጣሚዎች ከራልፍ ጋር ተገናኝተን የነበረ ሲሆን ዋሽንግተን ዲ ሲ ውስጥ ከግንቦት 30​—⁠ሰኔ 3, 1935 ተደርጎ በነበረው ትልቅ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ትውውቃችን ከበፊቱ የበለጠ ጎለበተ። “እጅግ ብዙ ሰዎች”ን በተመለከተ ንግግር ሲሰጥ እኔና ራልፍ ሰገነት ላይ ጎን ለጎን ተቀምጠን ነበር። (ራእይ 7:​9-14) እስከዚህ ጊዜ ድረስ እጅግ ብዙ ሰዎች ከ144, 000ዎቹ ያነሰ ታማኝነት ያሳዩ የሰማያዊ ክፍል አባላት እንደሆኑ እናምን ነበር። (ራእይ 14:​1-3) በመሆኑም ከእነሱ መካከል የመሆን ፍላጎት አልነበረኝም!

ወንድም ራዘርፎርድ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ምድራዊ ክፍል የሆኑ አርማጌዶንን በሕይወት የሚያልፉ ታማኝ ሰዎች መሆናቸውን ሲገልጽ ብዙዎች ተገረሙ። ከዚያም የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል የሆኑት በሙሉ ከመቀመጫቸው እንዲነሱ ጠየቀ። ራልፍ ሲቆም እኔ ግን ተቀምጬ ቀረሁ። ከጊዜ በኋላ ነገሮች ይበልጥ ግልጽ ስለሆኑልኝ ለመጨረሻ ጊዜ በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን የተካፈልኩት በ1935 ነበር። እናቴ ግን በኅዳር 1957 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ከቂጣውና ከወይኑ መካፈሏን ቀጠለች።

የዕድሜ ልክ ጓደኛ

እኔና ራልፍ ደብዳቤ መጻጻፋችንን ቀጠልን። እኔ በኒው ዮርክ፣ ሌክ ፕላሲድ አገለግል የነበረ ሲሆን እሱ ደግሞ በፔንሲልቬኒያ ያገለግል ነበር። በ1936 በመኪናው የምትሳብ አንዲት ትንሽ ተጎታች ቤት ሠራ። ከጥቅምት 16-18 በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ተጎታች ቤቱን ይዞ ከፖትስታውን ፔንሲልቬኒያ ወደ ኒዋርክ፣ ኒው ጀርሲ መጣ። አንድ ቀን ከፕሮግራሙ በኋላ አመሻሹ ላይ ጥቂት የምንሆን አቅኚዎች የራልፍን አዲስ ተጎታች ቤት ለማየት ሄድን። እኔና እሱ ቤቱ ውስጥ ዕቃ ማጠቢያው አጠገብ ቆመን ሳለ “ተጎታች ቤቱን ወደድሽው?” ሲል ጠየቀኝ።

ራሴን በመነቅነቅ መስማማቴን ስገልጽ “እዚህ ውስጥ መኖር ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቀኝ።

“አዎን” ብዬ ስመልስለት ሳም አደረገኝ፤ ይህን ፈጽሞ አልረሳውም። ከጥቂት ቀናት በኋላ የጋብቻ ምሥክር ወረቀት አወጣን። በአውራጃ ስብሰባው ማግስት ጥቅምት 19 ወደ ብሩክሊን ሄደን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የማተሚያ ሕንፃን ጎበኘን። ከዚያም የአገልግሎት ክልል እንዲሰጠን ጠየቅን። ግራንት ሱተር የአገልግሎት ክልል ኃላፊ ስለነበር ክልሉን የሚሸፍነው ማን እንደሚሆን ጠየቀን። ራልፍ “የጋብቻችን ጉዳይ የሚጠናቀቅልን ከሆነ ሁለታችን እንሸፍነዋለን” ሲል መለሰ።

ወንድም ሱተር “ከሰዓት በኋላ 11 ሰዓት ላይ ከመጣችሁ አስፈላጊውን ነገር አመቻችተን እንቆያችኋለን” ሲል መለሰ። ስለዚህ የዚያን ዕለት አመሻሹ ላይ በብሩክሊን ሃይትስ በሚገኝ አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤት ተጋባን። ከተወሰኑ ጓደኞቻችን ጋር ሆነን በአቅራቢያው በሚገኝ አንድ ምግብ ቤት እራት ከበላን በኋላ የሕዝብ ትራንስፖርት ይዘን የራልፍ ተጎታች መኪና ወደቆመችበት ወደ ኒዋርክ፣ ኒው ጀርሲ ሄድን።

ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ለመጀመሪያ ጊዜ አብረን በአቅኚነት እንድናገለግል ወደተመደብንበት ወደ ሄትስቪል ቨርጂኒያ አቀናን። በኖርቱምበርላንድ ወረዳ ካገለገልን በኋላ በፔንሲልቬኒያ በሚገኙት የፉልቶንና የፍራንክሊን ወረዳዎች ማገልገላችንን ቀጠልን። በ1939 ራልፍ በዞን አገልጋይነት እንዲሠራ ተጠየቀ። ይህም በርካታ ጉባኤዎችን በዙር መጎብኘት ማለት ነው። በቴኔሲ ክልል የሚገኙትን ጉባኤዎች ጎበኘን። በቀጣዩ ዓመት ወንድ ልጃችን አለን ስለተወለደ በ1941 የዞን ሥራው ተቋረጠ። ከዚያም በማሪዮን ቨርጂኒያ በልዩ አቅኚነት እንድናገለግል ተመደብን። በዚያን ወቅት ልዩ አቅኚ መሆን ማለት በወር 200 ሰዓት በአገልግሎት ማሳለፍ ይጠይቅ ነበር።

ማስተካከያዎች ማድረግ

በ1943 የልዩ አቅኚነት አገልግሎት ማቆም ግድ ሆነብኝ። ማድረግ የምችለው ነገር ቢኖር በአንዲት ትንሽ ተጎታች ቤት ውስጥ መኖር፣ አንድ ትንሽ ልጅ መንከባከብ፣ ምግብ ማዘጋጀት፣ ሁላችንም ንጹሕ ልብስ እንድንለብስ ማድረግና በአገልግሎት በየወሩ ወደ 60 ሰዓት ገደማ ማሳለፍ ብቻ ነበር። ራልፍ ግን በልዩ አቅኚነት ማገልገሉን ቀጠለ።

በ1945 ወደ ኦሃዮ አሊያንስ ተመልሰን ለዘጠኝ ዓመታት መኖሪያ ቤታችን የነበረውን ተጎታች ቤት ሸጥንና ከወላጆቼ ጋር በከብት ማርቢያው ቦታ መኖር ጀመርን። ሴት ልጃችን ሬቤካ የተወለደችው ከፊት ለፊት ባለው በረንዳ ላይ ነበር። ራልፍ ከተማ ውስጥ የግማሽ ቀን ሥራ የተቀጠረ ሲሆን የዘወትር አቅኚ ሆኖ ማገልገሉንም ቀጠለ። እኔ በግብርና ሥራ ከመሰማራቴም በላይ እሱ በአቅኚነት እንዲቀጥል ለመርዳት የቻልኩትን አደርግ ነበር። ምንም እንኳ ቤተሰቦቼ ባዶ መሬትና ቤት ቢሰጡንም ራልፍ ለመውሰድ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። የመንግሥቱን ጥቅሞች ይበልጥ በተሟላ መልኩ መከታተል እንድንችል አንድም የሚያስተጓጉለው ነገር እንዲኖር አልፈለገም ነበር።

በ1950 መኖሪያ ቀይረን ወደ ፖትስታውን ፔንሲልቬኒያ መጣንና በወር 25 የአሜሪካ ዶላር የሚከፈልበት ቤት ተከራየን። በቀጣዮቹ 30 ዓመታት የቤት ኪራዩ ቢጨምርም ከ75 ዶላር አላለፈም። ይሖዋ ኑሮአችንን ቀላል አድርገን እንድንቀጥል እየረዳን እንዳለ ተሰምቶናል። (ማቴዎስ 6:​31-33) ራልፍ በሳምንት ሦስት ቀን በፀጉር አስተካካይነት ይሠራ ነበር። በየሳምንቱ ሁለት ልጆቻችንን መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠና፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንገኝ እንዲሁም በቤተሰብ መልክ የመንግሥቱን ምሥራች እንሰብክ ነበር። ራልፍ በአካባቢያችን በሚገኘው ጉባኤ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኖ አገልግሏል። ኑሮአችንን ቀላል በማድረግ በይሖዋ አገልግሎት ብዙ ማከናወን ችለናል።

ውድ ባለቤቴን አጣሁ

ግንቦት 17, 1981 መንግሥት አዳራሽ ውስጥ ተቀምጠን የሕዝብ ንግግር እያዳመጥን ነበር። ራልፍ የሕመም ስሜት ስለተሰማው ወደ አዳራሹ መጨረሻ ሄዶ ወደ ቤት ሊሄድ መሆኑን ማስታወሻ ጽፎ በአስተናጋጁ በኩል ላከልኝ። ራልፍ እንዲህ ዓይነት ልማድ ፈጽሞ ስላልነበረው አንድ ሰው ወዲያውኑ በመኪና ቤት እንዲያደርሰኝ ጠየቅሁ። ራልፍ በዚያው ሰዓት ውስጥ በከባድ ስትሮክ በሽታ ሞተ። የዚያኑ ዕለት ጠዋት የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እንዳበቃ የራልፍ መሞት ለጉባኤው ተነገረ።

ራልፍ በዚያን ወር ከ50 ሰዓት በላይ በአገልግሎት አሳልፎ ነበር። በአቅኚነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፈው ጊዜ ከ46 ዓመት ይበልጣል። ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ለመሆን የበቁ ከመቶ ለሚበልጡ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርቷል። ባሳለፍናቸው ዓመታት በሙሉ ከከፈልናቸው ከየትኞቹም መሥዋዕቶች ይልቅ ያገኘናቸው መንፈሳዊ በረከቶች ይበልጣሉ።

ላገኘኋቸው መብቶች አመስጋኝ ነኝ

ላለፉት 18 ዓመታት ስብሰባዎች ላይ እየተገኘሁ፣ አቅሜ በሚፈቅድልኝ መጠን ለሌሎች እየሰበኩና የአምላክን ቃል እያጠናሁ የኖርኩት ብቻዬን ነው። አሁን የምኖረው አረጋውያን በሚጦሩበት አፓርትመንት ውስጥ ነው። ጥቂት የቤት ውስጥ እቃዎች ያሉኝ ሲሆን ቴሌቪዥን ግን እንዲኖረኝ አልፈለግሁም። ሆኖም ሕይወቴ የተሟላና በመንፈሳዊ የበለጸገ ነው። ወላጆቼና ሁለቱ ወንድሞቼ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ታማኝነታቸውን ጠብቀዋል። ሁለቱ እህቶቼ ደግሞ በእውነት መንገድ በታማኝነት መጓዛቸውን ቀጥለዋል።

ወንዱ ልጄ አለን የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ። ለበርካታ ዓመታት የመንግሥት አዳራሾችንና የትልልቅ ስብሰባ አዳራሾችን እንዲሁም በበጋ በሚደረጉ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የድምፅ መሣሪያዎች በመትከል ሠርቷል። ሚስቱ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ስትሆን ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌ ሆነው ያገለግላሉ። ሴቷ ልጄ ሬቤካ ካረስ ብሩክሊን በሚገኘው በዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ያገለገለችባቸውን አራት ዓመታት ጨምሮ ከ35 ዓመት በላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አሳልፋለች። እሷና ባለቤቷ ያለፉትን 25 ዓመታት በተለያዩ የዩናይትድ ስቴትስ ክፍሎች በተጓዥ አገልጋይነት በመሥራት አሳልፈዋል።

የአምላክ መንግሥት ተፈልጎ ሊገኝ እንደሚችል እንደተደበቀ ሀብት መሆኑን ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:​44) ቤተሰቦቼ ይህን ሀብት ከብዙ ዓመታት በፊት በማግኘታቸው አመስጋኝ ነኝ። ራሴን ለአምላክ በመወሰን ከ80 ለሚበልጡ ዓመታት ያቀረብኩትን አገልግሎት መለስ ብዬ መመልከት መቻሌ ምንኛ መብት ነው! አንድም የምቆጭበት ነገር የለም! ያሳለፍኩትን ሕይወት መድገም ብችል ኖሮ በዚያው መልክ እኖር ነበር። ምክንያቱም ‘የአምላክ ምሕረት ከሕይወት ይሻላልና።’​—⁠መዝሙር 63:​3

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ያለቀለት ምሥጢር (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት በሚል ርዕስ በተከታታይ ከወጡት ጥራዞች ውስጥ ሰባተኛው ሲሆን የመጀመሪያ ስድስቱ በቻርልስ ቴዝ ራስል የተዘጋጁ ነበሩ። ያለቀለት ምሥጢር የታተመው ራስል ከሞተ በኋላ ነው።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1917 ወንድም ራዘርፎርድ በአሊያንስ ኦሃዮ የሰጠውን ንግግር አዳምጠናል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከራልፍ ጋር፣ እሱ የሠራው ተጎታች ቤት ፊት ቆመን

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ከሁለቱ ልጆቼ ጋር