በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ—ኃይሉ እጅግ ታላቅ ነው

ይሖዋ—ኃይሉ እጅግ ታላቅ ነው

ይሖዋ​—⁠ኃይሉ እጅግ ታላቅ ነው

“በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።”​—⁠ኢሳይያስ 40:​26

1, 2. (ሀ) የሁላችንም ሕይወት የተመካው በየትኛዋ ግዑዝ የኃይል ምንጭ ላይ ነው? (ለ) የመጨረሻው የኃይል ሁሉ ምንጭ ይሖዋ ነው የምንልበት ምክንያት ምን እንደሆነ አብራራ።

 ብዙዎቻችን ስለ ኃይል ሥራዬ ብለን አናስብም። ለምሳሌ ያህል ብርሃንና ሙቀት እንድናገኝ ወይም ደግሞ ያሉንን የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ለማሠራት ስለሚያስችለን የኤሌክትሪክ ኃይል እምብዛም አናስብም። ኃይል ባይኖር ኖሮ እኮ የሰው ልጅ ከተሞች እንቅስቃሴ አልባ ይሆኑ ነበር ብለንም የምናስበው ድንገት የኤሌክትሪክ ኃይል የተቋረጠ እንደሆነ ብቻ ነው። ዛሬ አብዛኛውን ነገር ለመሥራት የምንገለገልበት የኤሌክትሪክ ኃይል በተዘዋዋሪ መንገድ የሚገኘው ለምድር እጅግ አስተማማኝ የኃይል ምንጭ ከሆነችው ከፀሐይ ነው። a የዚህ ኃይል አፀግባሪ የሆነችው ፀሐይ በእያንዳንዱ ሰኮንድ አምስት ሚልዮን ቶን የሚመዝን የኑክሌር ነዳጅ በማቃጠል ሕይወትን ለማቆየት የሚያስፈልገውን ኃይል ወደ ምድር ትልካለች።

2 ይህ ሁሉ የፀሐይ ኃይል የመጣው ከየት ነው? ይህን ሰማያዊ የኃይል ማመንጫ የተከለው ማን ነው? ይሖዋ አምላክ ነው። መዝሙር 74:​16 ስለ እርሱ ሲናገር “አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ” ይላል። አዎን፣ ይሖዋ የሕይወት ሁሉ ምንጭ እንደሆነ ሁሉ የመጨረሻው የኃይል ምንጭም እርሱ ነው። (መዝሙር 36:​9) የእርሱን ኃይል በፍጹም አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል እንደ ፀሐይና ከዋክብት ያሉትን የሰማይ አካላት ቀና ብለን እንድንመለከትና እንዴት ወደ ሕልውና እንደመጡ እንድናስብ ይመክረናል። “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።”​—⁠ኢሳይያስ 40:​26፤ ኤርምያስ 32:​17

3. ይሖዋ ኃይሉን የሚገልጥበት መንገድ ለእኛ ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

3 የይሖዋ ኃይል እጅግ ታላቅ በመሆኑ ፀሐይ ለሕልውናችን መሠረት የሆነውን ብርሃንና ሙቀት መስጠቷን እንደምትቀጥል እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ይሁን እንጂ የይሖዋ ኃይል የሚያስፈልገን መሠረታዊ የሆነውን ቁሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት ብቻ አይደለም። ከኃጢአትና ከሞት መቤዠታችን፣ የወደፊቱ ተስፋችን እንዲሁም በይሖዋ ላይ ያለን ትምክህት ሁሉ ከእርሱ ኃይል ተነጥለው የማይታዩ ነገሮች ናቸው። (መዝሙር 28:​6-9፤ ኢሳይያስ 50:​2) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ለመፍጠርና ለመቤዠት፣ ሕዝቡን ለማዳንና ጠላቶቹን ለማጥፋት ያለውን ኃይል በሚያረጋግጡ ምሳሌዎች የተሞላ ነው።

የአምላክ ኃይል በፍጥረት ሥራዎቹ ተንጸባርቋል

4.(ሀ) ዳዊት የሌሊቱን ሰማይ በመመልከቱ የተነካው እንዴት ነው? (ለ) የሰማይ አካላት ስለ መለኮታዊው ኃይል ምን ይመሠክራሉ?

4 ሐዋርያው ጳውሎስ የፈጣሪያችን ‘ዘላለማዊ ኃይል ከተሠሩት ነገሮች ግልጥ ሆኖ እንደሚታይ’ አስረድቷል። (ሮሜ 1:​20) ከዚያ ብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ደግሞ፣ እረኛ እንደመሆኑ የሌሊቱን ሰማይ በተደጋጋሚ ጊዜ የማየት አጋጣሚ ያገኘው መዝሙራዊው ዳዊት የአጽናፈ ዓለሙን ታላቅነትና የሠሪውን ኃይል ተገንዝቦ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፣ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?” (መዝሙር 8:​3, 4) ዳዊት ስለ ሰማይ አካላት የነበረው እውቀት በጣም ውስን ቢሆንም በጣም ሰፊ የሆነውን አጽናፈ ዓለማችንን ከፈጠረው አምላክ ጋር ሲወዳደር እርሱ ከቁጥርም እንደማይገባ ተገንዝቦ ነበር። ዛሬ የጠፈር ተመራማሪዎች ስለ አጽናፈ ዓለሙ ግዝፈትም ሆነ ስለሚንቀሳቀስበት ኃይል ሰፊ እውቀት አካብተዋል። ለምሳሌ ያህል የእኛ ፀሐይ በእያንዳንዱ ሰኮንድ ከ100, 000 ሜጋ ቶን ቲ ኤን ቲ ፍንዳታዎች ጋር የሚመጣጠን ኃይል እንደምታመነጭ ይነግሩናል። b ከዚህ የኃይል መጠን መካከል ወደ ምድር የሚመጣው እጅግ በጣም ትንሹ ቢሆንም በፕላኔታችን ላይ ያለውን ሕይወት ለማቆየት በቂ ነው። ያም ሆኖ ግን ከሌሎች የሰማይ ከዋክብት ሁሉ የበለጠ ኃይል ያላት የእኛ ፀሐይ ነች ማለት አይደለም። ፀሐይ ቀኑን ሙሉ የምታመነጨውን የሚያህል የኃይል መጠን በአንድ ሰኮንድ ውስጥ ብቻ የሚያመነጩ ከዋክብት አሉ። እንዲህ ዓይነቶቹን የሰማይ አካላት የፈጠረው አምላክ ያለው ኃይል ምን ያህል እንደሆነ መገመት ትችላለህ! ኤሊሁ “ሁሉን የሚችል አምላክን እናገኝ ዘንድ አንችልም፤ በኃይል ታላቅ ነውና” ብሎ መናገሩ ተገቢ ነበር።​—⁠ኢዮብ 37:​23

5. የይሖዋ ብርታት በሥራዎቹ ላይ ተንጸባርቆ የምናየው እንዴት ነው?

5 እኛም እንደ ዳዊት ‘የአምላክን ሥራዎች ብንፈልግ’ በነፋሱና በሞገዱ፣ በነጎድጓዱና በመብረቁ፣ በሚያስገመግሙት ወንዞችና ግዙፍ በሆኑት ተራራዎች ላይ የተንጸባረቀውን ኃይሉን መመልከት እንችላለን። (መዝሙር 111:​2፤ ኢዮብ 26:​12-14) ከዚህም በላይ ይሖዋ ኢዮብን እንዳሳሰበው እንስሳትም ቢሆኑ የእርሱን ኃይል ይገልጣሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ቤህሞት ወይም ጉማሬ ነው። ይሖዋ ኢዮብን “እነሆ፣ ብርታቱ በወገቡ ውስጥ ነው፤ . . . አጥንቱ እንደ ናስ አገዳ ነው” ብሎታል። (ኢዮብ 40:​15-18) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ያልተገራ በሬ ያለው አስፈሪ ኃይልም በሰፊው የታወቀ ነበር። ዳዊት ‘ከአንበሳ አፍና ከዱር በሬ ቀንድ አድነኝ’ ሲል ጸልዮአል።​—⁠መዝሙር 22:​21 NW ፤ ኢዮብ 39:​9-11

6. በሬ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ምን ያመለክታል? ለምንስ? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

6 በሬ ካለው ጥንካሬ የተነሣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የይሖዋን ኃይል ለማመልከት ተሠርቶበታል። c ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ይሖዋ ዙፋን የተመለከተው ራእይ አራት ሕያዋን ፍጥረታት የታዩበት ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዱ እንደ በሬ ያለ መልክ ነበረው። (ራእይ 4:​6, 7) በዚህ ኪሩብ የተወከለው ከይሖዋ አራት ዋና ዋና ባሕርያት አንዱ ኃይል እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ሌሎቹ ፍቅር፣ ጥበብና ፍትሕ ናቸው። ኃይል በአምላክ ስብዕና ውስጥ ይህን ያህል ጎላ ያለ ስፍራ ያለው በመሆኑ ስለ ኃይሉና ይህን ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀምበት የጠራ ግንዛቤ ማግኘታችን ወደ እርሱ እንድንቀርብና ያለንን ማንኛውንም ኃይል በአግባቡ በመጠቀም ረገድ የእርሱን ምሳሌ እንድንኮርጅ ይረዳናል።​—⁠ኤፌሶን 5:​1

‘ኃያሉ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ’

7. ክፋት በበጎነት ድል እንደሚደረግ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

7 ይሖዋ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ‘ሁሉን የሚችል አምላክ’ ተብሎ የተጠራ ሲሆን ይህ የማዕረግ ስያሜ እርሱ ያለውን ኃይል አቅልለን እንዳንመለከት ወይም ደግሞ ጠላቶቹን ለመደምሰስ ያለውን ችሎታ እንዳንጠራጠር ማሳሰቢያ ይሆነናል። (ዘፍጥረት 17:​11980 ትርጉም ፤ ዘጸአት 6:​3) የሰይጣን የነገሮች ሥርዓት የተደላደለ ይመስል ይሆናል። በይሖዋ ዓይን ግን “አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፣ በሚዛንም እንዳለ ትንሽ ትቢያ ተቆጥረዋል።” (ኢሳይያስ 40:​15) እንዲህ ላለው መለኮታዊ ኃይል ምሥጋና ይግባውና ክፋት በበጎነት ድል መነሳቱ የማይቀር ነው። ክፋት በጣም በተስፋፋበት በአሁኑ ጊዜ “የእስራኤል ኃያል የሠራዊት ጌታ” የሆነው ይሖዋ ክፋትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያጠፋ ማወቃችን ያጽናናናል።​—⁠ኢሳይያስ 1:​24፤ መዝሙር 37:​9, 10

8. ይሖዋ የሚያዝዘው ሰማያዊ ሠራዊት የትኛው ነው? ምን ያህል ኃይል እንዳላቸው የሚጠቁምስ ምን ማስረጃ አለን?

8 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 285 ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኘው “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” የሚለው መግለጫ ይሖዋ አምላክ ስላለው ኃይል እንድናስብ የሚያደርገን ሌላው ነገር ነው። “ሠራዊት” የሚለው ይህ መግለጫ ይሖዋ የሚያዝዛቸውን እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መንፈሳዊ ፍጥረታት የሚያመለክት ነው። (መዝሙር 103:​20, 21፤ 148:​2) ከእነዚህ መላእክት አንዱ ብቻውን ኢየሩሳሌምን ያስፈራሩ የነበሩትን 185, 000 አሦራውያን በአንድ ሌሊት ፈጅቷቸዋል። (2 ነገሥት 19:​35) የይሖዋ ሰማያዊ ሠራዊት ያለውን ኃይል ከተገነዘብን ለተቃዋሚዎች ማስፈራሪያ በቀላሉ አንንበረከክም። ነቢዩ ኤልሳዕ እርሱን ፍለጋ የመጣው ሠራዊት እንደከበበው ቢያውቅም ከእርሱ ጎን የነበረውን ሰማያዊ ኃይል በእምነት ዓይኑ መመልከት ስለቻለ እንደ አገልጋዩ አልተጨነቀም።​—⁠2 ነገሥት 6:​15-17

9. እንደ ኢየሱስ በመለኮታዊ ጥበቃ ላይ ትምክህት ሊኖረን የሚችለው ለምንድን ነው?

9 ኢየሱስም ሰይፍና ቆመጥ የታጠቁ ሰዎች በጌተሰማኔ የአትክልት ሥፍራ በመጡበት ጊዜ የመላእክት ድጋፍ እንዳለው ተገንዝቦ ነበር። ሰይፉን ወደ ቦታው እንዲመልስ ለጴጥሮስ ከነገረው በኋላ ቢያስፈልግ ኖሮ ‘ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት’ እንዲሰድለት አባቱን መጠየቅ ይችል እንደነበር ነገረው። (ማቴዎስ 26:​47, 52, 53) እኛም የአምላክን ሰማያዊ ሠራዊት በተመለከተ ተመሳሳይ ግንዛቤ ካለን መለኮታዊ ድጋፍ እንደምናገኝ ሙሉ ትምክህት ይኖረናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?” ሲል ጽፏል።​—⁠ሮሜ 8:​31

10. ይሖዋ ለእነማን ሲል ኃይሉን ይጠቀማል?

10 እንግዲያውስ በይሖዋ ጥበቃ የምንታመንበት በቂ ምክንያት አለን። ኃይሉን የሚጠቀምበት ሁልጊዜ ለመልካም ነገርና እንደ ፍትሕ፣ ጥበብና ፍቅር ካሉት ሌሎች ባሕርያቱ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። (ኢዮብ 37:​23፤ ኤርምያስ 10:​12) ብዙውን ጊዜ ኃያላን ሰዎች ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ድሆችንና ምስኪኖችን የሚጨቁኑ ቢሆኑም ይሖዋ ግን ‘ችግረኛውን ከመሬት የሚያነሣና ለማዳን የሚበረታ’ አምላክ ነው። (መዝሙር 113:​5-7፤ ኢሳይያስ 63:​1) ‘ብርቱ የሆነው’ አምላክ እርሱን ለሚፈሩት ሰዎች ሲል ትዕቢተኞችን በማዋረድና የተዋረዱትን ከፍ ከፍ በማድረግ ኃይሉን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ እንደሚጠቀምበት ስለ ራሷ ልከኛ አመለካከት የነበራትና ትሑት የነበረችው የኢየሱስ እናት ማርያም ተገንዝባ ነበር።​—⁠ሉቃስ 1:​46-53

ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ኃይሉን ይገልጥላቸዋል

11. እስራኤላውያን በ1513 ከዘአበ የአምላክን ኃይል በሚመለከት ምን ነገር ሲከናወን ተመልክተዋል?

11 ይሖዋ በተለያዩ አጋጣሚዎች ኃያልነቱን ለአገልጋዮቹ አሳይቷል። ከእነዚህ አጋጣሚዎች አንዱ በ1513 ከዘአበ በሲና ተራራ የተከናወነው ሁኔታ ነው። በዚያው ዓመት እስራኤላውያን የአምላክን ኃይል አስገራሚ ማረጋገጫ ተመልክተው ነበር። አሥሩ አውዳሚ መቅሰፍቶች የይሖዋን ክንድ ታላቅነትና የግብጻውያን አማልክትን አቅመ ቢስነት ያረጋገጡ ነበሩ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ቀይ ባሕርን በተዓምራዊ ሁኔታ መሻገራቸውና በፈርዖን ሠራዊት ላይ የደረሰው ጥፋት ተጨማሪ የመለኮታዊ ኃይል ማረጋገጫ ሆኖላቸው ነበር። ከሦስት ወራት በኋላ በሲና ተራራ ግርጌ ይሖዋ “ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት” እንዲሆኑለት እስራኤላውያንን ጋበዛቸው። እነርሱም በበኩላቸው “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” በማለት ቃል ገቡ። (ዘጸአት 19:​5, 8) ከዚያም ይሖዋ ኃይሉን በግልጽ የሚያሳይ ነገር አከናወነ። የሲና ተራራ በነጎድጓድና መብረቅ እንዲሁም በከፍተኛ የመለከት ድምፅ ታጅቦ መጨስና መንቀጥቀጥ ጀመረ። በርቀት ቆመው ይመለከቱ የነበሩት እስራኤላውያን በፍርሃት ተንቀጠቀጡ። ይሁን እንጂ ሙሴ ይህ ያዩት ነገር አምላካዊ ፍርሃትን ሊያስተምራቸው እንደሚገባ አሳሰባቸው። ይህ ዓይነቱ ፍርሃት ከሁሉ በላይ ኃያልና ብቸኛ የሆነውን እውነተኛ አምላክ ይሖዋን እንዲታዘዙ የሚያነሳሳቸው ዓይነት ፍርሃት ነበር።​—⁠ዘጸአት 19:​16-19፤ 20:​18-20

12, 13. ኤልያስ ምድብ ሥራውን ትቶ እንዲሸሽ ያደረገው ነገር ምን ነበር? ይሁንና ይሖዋ ያበረታው እንዴት ነው?

12 ከጥቂት መቶ ዓመታት በኋላ ደግሞ በኤልያስ ዘመን በሲና ተራራ ላይ ሌላ የመለኮታዊ ኃይል መግለጫ ታየ። ነቢዩ ከዚያ ቀደምም ቢሆን የአምላክን ኃይል አሠራር ተመልክቷል። የእስራኤላውያኑ ብሔር ከሃዲ ሆኖ በመገኘቱ አምላክ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል ‘ሰማይን ዘግቶ ነበር።’ (2 ዜና መዋዕል 7:​13) ይህ ሁኔታ ድርቅ ባስከተለ ጊዜም ኤልያስ በኮራት ፈፋ ተቀምጦ ቁራዎች ሲመግቡት ቆይቷል። በኋላም አንዲት መበለት የነበራት ሙጣጭ ዱቄትና ዘይት በተዓምራዊ መንገድ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ ተደርጎ እርሱን ለመመገብ አገልግሏል። ይሖዋ የዚህችን መበለት ልጅ ከሞት እንኳ ሳይቀር የማስነሣት ኃይል ለኤልያስ ሰጥቶታል። በመጨረሻ በቀርሜሎስ ተራራ በተካሄደው የአምላክነት ግድድር ላይ እሳት ከሰማይ ወርዳ ኤልያስ ያቀረበውን መሥዋዕት በልታለች። (1 ነገሥት 17:​4-24፤ 18:​36-40) ሆኖም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኤልያስ የኤልዛቤልን የግድያ ዛቻ ሲሰማ በፍርሃትና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተዋጠ። (1 ነገሥት 19:​1-4) በነቢይነት የሚያከናውነው ሥራ እንዳበቃ በማሰብ አገሪቱን ትቶ ሸሸ። ይሖዋ እርሱን ለማጽናናትና ለማበርታት ሲል በደግነት ለብቻው የመለኮታዊ ኃይል መግለጫ አሳይቶታል።

13 ኤልያስ በዋሻ ተደብቆ ሳለ ይሖዋ የሚቆጣጠራቸው ሦስት አስፈሪ ኃይሎችን ተመለከተ። እነዚህም ኃይለኛ ነፋስ፣ የምድር መንቀጥቀጥ እና በመጨረሻም እሳት ናቸው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ኤልያስን ያነጋገረው ‘ዝግ ባለ ለስላሳ ድምፅ’ ነበር። ተጨማሪ ሥራ ሰጠውና በምድሪቱ 7, 000 ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች እንዳሉ አሳወቀው። (1 ነገሥት 19:​9-18) እኛም አንዳንድ ጊዜ በአገልግሎታችን ውጤት ባለማግኘታችን ምክንያት እንደ ኤልያስ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ቢያድርብን ይሖዋ ‘ከወትሮው የበለጠ ኃይል’ ይሰጠን ዘንድ ልንለምነው እንችላለን። ይህም ኃይል ምሥራቹን ያለመታከት መስበ​ካችንን እንድንቀጥል ብርታት ይሰጠናል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:​7

የይሖዋ ኃይል ተስፋዎቹ እንደሚፈጸሙ ዋስትና ይሆነናል

14. ከይሖዋ የግል መጠሪያ ምን መረዳት ይቻላል? ኃይሉስ ከስሙ ጋር የተዛመደው እንዴት ነው?

14 የይሖዋ ኃይል ከስሙና ከዓላማው መፈጸም ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው። “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጓሜ ያለው ይሖዋ የሚለው ልዩ ስም ዓላማውን አስፈጻሚ አድርጎ ራሱን እንደሚያቀርብ የሚጠቁም ነው። ተጠራጣሪ የሆኑ ሰዎች የቱንም ያህል የማይጨበጡ አድርገው ይመልከቷቸው እንጂ አምላክ ዓላማዎቹን ዳር እንዳያደርስ ሊያግደው የሚችል አንዳች ነገር አይኖርም። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እንደነገራቸው “በእግዚአብሔር ዘንድ . . . ሁሉ ይቻላል።”​—⁠ማቴዎስ 19:26

15. ለይሖዋ የሚሳነው ነገር እንደሌለ ለአብርሃምና ለሣራ ማሳሰቢያ የተሰጣቸው እንዴት ነው?

15 ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በአንድ ወቅት ይሖዋ ለአብርሃምና ለሣራ ዘራቸውን ትልቅ ብሔር እንደሚያደርገው ቃል ገብቶላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ለብዙ ዓመታት ልጅ ሳይወልዱ ኖረዋል። ተስፋው ፍጻሜውን የሚያገኝበት ጊዜ መቃረቡን ይሖዋ ሲነግራቸው ሁለቱም በጣም አርጅተው ስለነበር ሣራ ሳቀች። መልአኩ ግን “በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?” ሲል መለሰላት። (ዘፍጥረት 12:​1-3፤ 17:​4-8፤ 18:​10-14) በመጨረሻ ከአራት መቶ ዓመታት በኋላ ሙሴ ታላቅ ብሔር የሆኑትን የአብርሃም ዘሮች በሞዓብ ሜዳ በሰበሰበ ጊዜ አምላክ የገባውን ቃል እንደፈጸመ አስታውሷቸዋል። ሙሴ እንዲህ ብሏል:- “[ይሖዋ] አባቶችህን ወድዶአልና ከእነርሱ በኋላ ዘራቸውን መረጠ፣ ዛሬ እንደሆነው ሁሉ ከአንተ የጸኑትን ታላላቆችን አሕዛብ በፊትህ እንዲያወጣ፣ አንተንም እንዲያገባህ፣ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ እንዲሰጥህ፣ ከአንተ ጋር ሆኖ በታላቅ ኃይሉ ከግብፅ አወጣህ።”​—⁠ዘዳግም 4:​37, 38

16. ሰዱቃውያን የሙታን ትንሣኤን እስከ መካድ ያደረሳቸው ነገር ምን ነበር?

16 ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ በትንሣኤ የማያምኑትን ሰዱቃውያን አውግዟቸዋል። አምላክ ሙታንን እንደሚያስነሳ የገባውን ቃል ለማመን ያዳገታቸው ለምን ነበር? ኢየሱስ “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁም” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 22:​29) ቅዱሳን ጽሑፎች ‘በመቃብር ያሉቱ ሁሉ የሰውን ልጅ ድምፅ ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት እንደሚመጣ’ ማረጋገጫ ይሰጡናል። (ዮሐንስ 5:​27-29) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ የሚናገረውን ነገር ካወቅን በአምላክ ኃይል ላይ ያለን ትምክህት ሙታን እንደሚነሡ በጽኑ እንድናምን ያደርገናል። አምላክ “ሞትን ለዘላለም ይውጣል . . . እግዚአብሔር ተናግሮአልና።”​—⁠ኢሳይያስ 25:​8

17. በይሖዋ ላይ ያለን ትምክህት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አንገብጋቢ የሚሆንበት ቀን የትኛው ነው?

17 በቅርቡ እያንዳንዳችን በአምላክ የማዳን ኃይል ላይ ለየት ባለ መንገድ እንድንታመን የሚጠይቅ ጊዜ ይመጣል። ሰይጣን ዲያብሎስ ያለ ምንም ከለላ የተቀመጡ በሚመስሉት የአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። (ሕዝቅኤል 38:​14-16) በዚህ ጊዜ አምላክ እኛን ለመጠበቅ ሲል እርምጃ ይወስዳል። ሰው ሁሉ ደግሞ እርሱ ይሖዋ እንደሆነ ማወቅ ይኖርበታል። (ሕዝቅኤል 38:​21-23) በዚያ ቀውጢ ጊዜ እንዳንወላውል ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ላይ ያለንን እምነት መገንባት ያለብን ዛሬ ነው።

18. (ሀ) በይሖዋ ኃይል ላይ ማሰላሰላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? (ለ) የሚቀጥለው ርዕስ ለየትኛው ጥያቄ ማብራሪያ ይሰጣል?

18 በእርግጥም ስለ ይሖዋ ኃይል የምናሰላስልባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉን። በሥራዎቹ ላይ ባሰላሰልን መጠን ታላቁን ፈጣሪያችንን እንድናወድስና ኃይሉን እንደዚህ በመሰለ የጥበብና የፍቅር መንገድ ስለሚጠቀምበት እንድናመሰግነው እንገፋፋለን። በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ከታመንን ፈጽሞ አንፈራም። እርሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ጠንካራ ይሆናል። ይሁን እንጂ በአምላክ አምሳል የተፈጠርን መሆናችንን እናስታውስ። በተወሰነ መጠንም ቢሆን እኛም ኃይል አለን። ኃይላችንን በምንጠቀምበት መንገድ ፈጣሪያችንን መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ መልስ ያገኛል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ዛሬ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ለማንቀሳቀስ በዋነኛነት የሚያገለግሉት እንደ ነዳጅ ዘይትና የድንጋይ ከሰል ያሉት ከቅሪተ አካል የሚገኙ ነዳጆች ኃይላቸውን ያገኙት ከፀሐይ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል።

b ከዚህ በተቃራኒው እስካሁን ከተሞከሩት የኑክሌር ቦምቦች መካከል ከፍተኛ የፍንዳታ ኃይል አለው የተባለለት 57 ሜጋ ቶን ቲ ኤን ቲ ነው።

c በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት በሬ የሚለው ቃል (በላቲን ዩረስ ) አዉራከስ የሚለው እንደሆነ ግልጽ ነው። ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት እነዚህ እንስሳት በጋውል (በዛሬዋ ፈረንሳይ) ይገኙ የነበረ ሲሆን ጁሊየስ ቄሣር እነርሱን በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እነዚህ ዩራይ ከዝሆን የማይተናነሱ ሲሆን ተፈጥሯቸው፣ ቀለማቸውና መልካቸው ግን የበሬ ነው። ያላቸው ጉልበትም ሆነ ፍጥነታቸው እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ዓይናቸው የገባውን ሁሉ ሰውም ሆነ እንስሳ አይምሩም።”

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ትችላለህ?

ፍጥረት ስለ ይሖዋ ኃይል ምን ይመሠክራል?

ይሖዋ ሕዝቡን ለማገዝ የትኛውን ሠራዊት ሊጠቀም ይችላል?

ይሖዋ ኃይሉን ያሳየባቸው አንዳንዶቹ አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው?

ይሖዋ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ምን ዋስትና አለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው?”

[ምንጭ]

Photo by Malin, © IAC/RGO 1991

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ኃይሉን ስላሳየባቸው አጋጣሚዎች ማሰላሰል እርሱ በሰጠው ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ይገነባልናል