‘አቤቱ አምላክ፣ ብርሃንህን ላክ’
‘አቤቱ አምላክ፣ ብርሃንህን ላክ’
“ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ።”—መዝሙር 43:3
1. ይሖዋ ዓላማውን የሚገልጠው እንዴት ነው?
ይሖዋ ዓላማውን ለአገልጋዮቹ የሚያሳውቅበት መንገድ አሳቢነቱን ያሳያል። ሁሉንም እውነት በአንድ ጊዜ በመግለጥ ዓይን እንደሚያጥበረብር ብርሃን ከማድረግ ይልቅ የእውነትን ብርሃን ቀስ በቀስ ይገልጥልናል። በሕይወት ጎዳና ላይ የጀመርነው ጉዞ ረጅም የእግር ጉዞ ለማድረግ ከተነሳ ሰው ጋር ሊነጻጸር ይችላል። ሌሊቱ ገና ለዓይን ይዞ ሳለ ጉዞውን ይጀምራል። ቀስ በቀስ ጎህ እየቀደደ ሲሄድ በአቅራቢያው ያሉትን አንዳንድ ነገሮች መለየት ይጀምራል። የተቀሩት ነገሮች የሚታዩት ግን በድንግዝግዝታ ብቻ ነው። ሆኖም ፀሐይዋ እየወጣች ስትሄድ ይበልጥ አርቆ ማየት ይጀምራል። አምላክ መንፈሳዊ ብርሃን የሚሰጥበት መንገድም ተመሳሳይ ነው። በአንድ ጊዜ የሚገልጥልን የተወሰኑ ነገሮችን ብቻ ነው። የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስም መንፈሳዊ ብርሃን ይገልጥ የነበረው በተመሳሳይ መንገድ ነው። ይሖዋ ጥንት ለነበሩት ሕዝቦቹ የእውቀት ብርሃን ያበራላቸው እንዴት እንደነበረና በጊዜያችንም ይህን የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
2. ይሖዋ በቅድመ ክርስትና ዘመን የእውቀት ብርሃን ይሰጥ የነበረው እንዴት ነው?
2 አርባ ሦስተኛውን መዝሙር 43 ያጠናቀሩት የቆሬ ልጆች ሳይሆኑ አይቀሩም። ሌዋውያን እንደ መሆናቸው መጠን ለሕዝቡ የአምላክን ሕግ የማስተማር መብት ነበራቸው። (ሚልክያስ 2:7) እርግጥ ነው፣ ታላቁ አስተማሪያቸው ይሖዋ ነበር፤ የጥበብ ሁሉ ምንጭ እርሱ ስለሆነ ፊታቸውን የሚያዞሩት ወደ እሱ ነበር። (ኢሳይያስ 30:20) መዝሙራዊው “አቤቱ [አምላክ]፣ . . . ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ” ሲል ጸልዮአል። (መዝሙር 43:1, 3) እስራኤላውያን ለእሱ ታማኝ እስከ ሆኑ ድረስ ይሖዋ መንገዱን ያስተምራቸው ነበር። የተወሰኑ መቶ ዘመናት ካለፉ በኋላ ይሖዋ በጣም ድንቅ የሆነ ብርሃንና እውነት በመላክ ሞገሱን አሳይቷቸዋል። አምላክ ይህን ያደረገው ልጁን ወደ ምድር በላከበት ጊዜ ነው።
3. አይሁዶች በኢየሱስ ትምህርት የተፈተኑት እንዴት ነበር?
3 የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው በነበረበት ጊዜ “የዓለም ብርሃን” ነበር። (ዮሐንስ 8:12) ለሕዝቡም “ብዙ ነገሮችን በምሳሌ” አስተምሯቸዋል። ማለትም አዳዲስ ነገሮችን አሳውቋቸዋል። (ማርቆስ 4:2፣ የ1980 ትርጉም ) ለጴንጤናዊው ጲላጦስ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” ሲል ነግሮታል። (ዮሐንስ 18:36) ይህ ሐሳብ ለአንድ ሮማዊም ሆነ መሲሑ የሮማውያንን አገዛዝ አንበርክኮ እስራኤልን ወደ ቀድሞ ክብሯ ይመልሳታል ብለው ይጠብቁ ለነበሩ ብሔራዊ ስሜት ለሚያንገበግባቸው አይሁዳውያን አዲስ ነበር። ኢየሱስ ከይሖዋ ያገኘውን ብርሃን እያንጸባረቀ ነበር፤ ሆኖም የተናገረው ነገር ‘ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ይወዱ የነበሩትን’ የአይሁድ መሪዎች አላስደሰተም። (ዮሐንስ 12:42, 43) ብዙዎቹ አምላክ የሚሰጠውን መንፈሳዊ ብርሃንና እውነት ከመቀበል ይልቅ ሰው ሰራሽ ወጎችን የሙጥኝ እንዳሉ መቀጠል መርጠዋል።—መዝሙር 43:3፤ ማቴዎስ 13:15
4. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያላቸው ግንዛቤ እያደገ መሄዱን እንደሚቀጥል እንዴት እናውቃለን?
4 ይሁን እንጂ ቅን ልብ ያላቸው ጥቂት ወንዶችና ሴቶች ኢየሱስ ያስተማረውን እውነት በደስታ ተቀበሉ። ስለ አምላክ ዓላማዎች ያላቸው ግንዛቤ በየጊዜው ማደጉን ቀጠለ። ሆኖም የአስተማሪያቸው ምድራዊ ሕይወት ሊያበቃ በተቃረበበትም ወቅት ገና ብዙ የሚማሩት ነገር ነበር። ኢየሱስ “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፣ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም” ሲል ነገራቸው። (ዮሐንስ 16:12) አዎን፣ ደቀ መዛሙርቱ ስለ አምላክ እውነት ያላቸው ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይሄዳል።
ብርሃኑ መፈንጠቁን ይቀጥላል
5. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምን ጥያቄ ተነስቶ ነበር? ለጥያቄውስ እልባት ማስገኘት የነበረበት ማን ነው?
5 አምላክ የሚሰጠው ብርሃን ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በኋላ ከምንጊዜውም ይበልጥ ብሩህ ሆኗል። ይሖዋ ያልተገረዙ አሕዛብ የክርስቶስ ተከታዮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ለጴጥሮስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ አሳየው። (ሥራ 10:9-17) ጴጥሮስ ያየው ራእይ ነበር! ሆኖም ከጊዜ በኋላ አንድ ጥያቄ ተነሳ:- እነዚህ አሕዛብ ክርስቲያን ከሆኑ በኋላ እንዲገረዙ ይሖዋ ይጠብቅባቸዋል? የዚህ ጥያቄ መልስ በራእዩ ውስጥ አልተገለጠም ነበር። ስለሆነም ጉዳዩ በክርስቲያኖች መካከል የጦፈ ክርክር አስነሳ። ውድ የሆነው አንድነታቸው እንዳይናጋ ይህ ክርክር እልባት ማግኘት ነበረበት። ስለዚህ በኢየሩሳሌም “ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ስለዚህ ነገር ለመማከር ተሰበሰቡ።”—ሥራ 15:1, 2, 6
6. ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ግርዘትን በተመለከተ የተነሳውን ጥያቄ በመረመሩበት ወቅት የተከተሉት የአሠራር ሥርዓት ምን ዓይነት ነበር?
6 በዚያ የተሰበሰቡት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያመኑትን አሕዛብ በተመለከተ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ይሖዋ ውይይቱን እንዲመራ መልአክ አልላከም ወይም በዚያ የተገኙት ራእይ እንዲያዩ አላደረገም። ይሁን እንጂ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያለምንም መመሪያ ተትተዋል ማለት አይደለም። አምላክ ባልተገረዙ አሕዛብ ላይ መንፈስ ቅዱስን በማፍሰስ ከአሕዛብ ጋር ግንኙነት እንደ ጀመረ አንዳንድ አይሁድ ክርስቲያኖች የሰጡትን ምሥክርነት አዳመጡ። በተጨማሪም መመሪያ ለማግኘት ቅዱሳን ጽሑፎችን አገላበጡ። ከዚያም ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ የእውቀት ብርሃን የሚፈነጥቅ አንድ ጥቅስ መሠረት በማድረግ ሐሳብ አቀረበ። በዚህ ማስረጃ ላይ ሲያሰላስሉ የአምላክ ፈቃድ ግልጽ ሆነላቸው። አሕዛብ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት የግድ መገረዝ አያስፈልጋቸውም። ሌሎች ክርስቲያኖች ይመሩበት ዘንድ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ይህን ውሳኔ ወዲያው በጽሑፍ አሰፈሩት።—ሥራ 15:12-29፤ 16:4
7. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እድገት ያደርጉ የነበረው በምን መንገድ ነበር?
7 ምንም እንኳ ይህን ግንዛቤ መቀበል በአጠቃላይ ስለ አሕዛብ የነበራቸውን አመለካከት መለወጥ የሚጠይቅባቸው ቢሆንም አብዛኞቹ አይሁድ ክርስቲያኖች የቀድሞ አባቶቻቸውን ወግ የሙጥኝ ብለው እንደያዙት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ከመሆን ይልቅ አምላክ አሕዛብን በተመለከተ ስላለው ዓላማ የሚገልጸውን ይህን አስደናቂ የሆነ አዲስ ግንዛቤ በደስታ ተቀበሉ። ይሖዋ ያሳዩትን የትሕትና መንፈስ በመባረኩ “አብያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ይበረቱ ነበር፣ በቁጥርም ዕለት ዕለት ይበዙ ነበር።”—ሥራ 15:31፤ 16:5
8. (ሀ) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ካበቃ በኋላም ተጨማሪ የእውቀት ብርሃን ሊፈነጥቅ እንደሚችል እንዴት እናውቃለን? (ለ) የትኞቹን ተገቢ የሆኑ ጥያቄዎች እንመረምራለን?
8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በጠቅላላ መንፈሳዊ ብርሃን መፈንጠቁን ቀጥሏል። ሆኖም ይሖዋ ለጥንት ክርስቲያኖች እያንዳንዱን የዓላማውን ገጽታ አልገለጸላቸውም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለመጀመሪያው መቶ ዘመን የእምነት ባልደረቦቹ “ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን” ሲል ነግሯቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 13:12) እንዲህ ዓይነቱ መስተዋት መልክን ጥርት አድርጎ የሚያሳይ አልነበረም። ስለዚህ መጀመሪያ ላይ የነበረው መንፈሳዊ ብርሃንን የመረዳቱ ሁኔታ ውስን ነበር። ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ መንፈሳዊው ብርሃን ለተወሰነ ጊዜ ደብዝዞ ነበር፤ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት ተትረፍርፏል። (ዳንኤል 12:4) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙት ሕዝቦቹ የእውቀት ብርሃን የሚፈነጥቅላቸው እንዴት ነው? ይሖዋ ለቅዱሳን ጽሑፎች ያለንን ግንዛቤ እያሰፋው ሲሄድ የእኛ ምላሽ ምን መሆን አለበት?
ብርሃኑ ደረጃ በደረጃ እየደመቀ ይሄዳል
9. የቀድሞዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የተጠቀሙበት ልዩ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥኛ ዘዴ ምን ነበር?
9 በዘመናችን እውነተኛው የብርሃን ጭላንጭል ለመጀመሪያ ጊዜ መታየት የጀመረው በ19ኛው መቶ ዘመን የመጨረሻ ሩብ ዓመታት ላይ የተወሰኑ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች በቡድን ሆነው ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥልቀት መመርመር በጀመሩበት ጊዜ ነበር። ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ዘዴ ፈጥረው ነበር። አንድ ሰው ጥያቄ ያነሳል፤ ከዚያም ቡድኑ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጥቅሶች በሙሉ ይመረምራል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ከሌላ ጥቅስ ጋር የሚጋጭ ከመሰለ እነዚህ ልበ ቅን ክርስቲያኖች ሁለቱን ጥቅሶች ለማስታረቅ ይሞክራሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (የይሖዋ ምሥክሮች በዚያን ጊዜ ይጠሩበት የነበረ ስም ነው) በወጎችና በሰው ሠራሽ ቀኖናዎች ሳይሆን በቅዱሳን ጽሑፎች መመራት አለብን የሚል አቋም በመያዝ በዘመኑ ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ልዩ መሆናቸውን አሳይተዋል። ሁሉንም ቅዱስ ጽሑፋዊ መረጃ ከመረመሩ በኋላ የደረሱበትን መደምደሚያ በጽሑፍ ያሰፍሩታል። በዚህ መንገድ መሠረታዊ የሆኑ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ግልጽ እያደረጉ መጡ።
10. ቻርልስ ቴዝ ራስል መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያግዙ ምን መጻሕፍትን አዘጋጅቷል?
10 ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጎልቶ የሚጠቀሰው ቻርልስ ቴዝ ራስል ነው። የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት (እንግሊዝኛ) የሚል ርዕስ ያላቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ስድስት ተከታታይ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል። ወንድም ራስል የሕዝቅኤልንና የራእይን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የሚያብራራ ሰባተኛ ጥራዝ የማዘጋጀት ዕቅድ ነበረው። “ቁልፉን እንዳገኘሁ ሰባተኛውን ጥራዝ እጽፋለሁ” ብሎ ነበር። ሆኖም አክሎ ሲናገር “ጌታ ቁልፉን ለሌላ ሰው ከሰጠው ያ ሰው ሊጽፈው ይችላል” ብሏል።
11. የአምላክን ዓላማ በመረዳትና በጊዜ መካከል ምን ግንኙነት አለ?
11 ከላይ ያለው የሲ ቲ ራስል አነጋገር አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ለመረዳት ባለን ችሎታ ረገድ ጊዜ ወሳኝ ሚና እንዳለው የሚያስረዳ ነው። አንድ ተጓዥ ፀሐይዋን በማስገደድ ያለ ጊዜዋ ቶሎ እንድትወጣለት ማድረግ እንደማይችል ሁሉ ወንድም ራስልም የራእይን መጽሐፍ ለመረዳት የሚያስችለው ብርሃን አለ ጊዜው እንዲበራለት ማድረግ እንደማይችል አውቋል።
አምላክ በወሰነው ጊዜ ተገለጠ
12. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ይበልጥ በግልጽ መረዳት የሚቻለው መቼ ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት የመረዳት ችሎታችን በአምላክ የጊዜ ሰሌዳ ላይ የተመካ መሆኑን የትኛው ምሳሌ ያሳያል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
12 ሐዋርያት ስለ መሲሑ የሚናገሩትን ብዙ ትንቢቶች የተረዱት ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በኋላ እንደሆነ ሁሉ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችም አንድን ትንቢት በማያሻማ መንገድ ሙሉ በሙሉ የሚረዱት ፍጻሜውን ካገኘ በኋላ ነው። (ሉቃስ 24:15, 27፤ ሥራ 1:15-21፤ 4:26, 27) ራእይ የትንቢት መጽሐፍ ነው፤ ስለዚህ የሚጠቅሳቸውን አንዳንድ ነገሮች በግልጽ እንገነዘባቸዋለን ብለን መጠበቅ ያለብን ከተፈጸሙ በኋላ ነው። ለምሳሌ ወንድም ራስል በራእይ 17:9-11 ላይ የተገለጸውን ቀይ አውሬ ትርጉም በትክክል መረዳት አልቻለም ነበር። ምክንያቱም ይህ አውሬ የሚወክላቸው ድርጅቶች ማለትም የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕልውና ያገኙት ወንድም ራስል ከሞተ በኋላ ነው። a
13. በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ላይ የእውቀት ብርሃን በሚፈነጥቅበት ጊዜ አንዳንዴ ምን ይከሰታል?
13 የጥንት ክርስቲያኖች ያልተገረዙ አሕዛብ የእምነት ባልደረቦቻቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ መገንዘባቸው አሕዛብ መገረዝ ያስፈልጋቸዋል ወይስ አያስፈልጋቸውም የሚል አዲስ ጥያቄ አስነስቶ ነበር። ይህም ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ግርዘትን የሚመለከተውን ጉዳይ እንደገና አንድ በአንድ እንዲመረምሩ አደረጋቸው። ዛሬም የሚደረገው ተመሳሳይ ነው። ቀጥሎ ካለው በቅርቡ ከተፈጸመ ምሳሌ መረዳት እንደሚቻለው በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የፈነጠቀ ብሩህ የእውቀት ብርሃን ቅቡዓን የአምላክ አገልጋዮች ማለትም “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች እንደገና እንዲመረምሩ ያደርጋቸዋል።—ማቴዎስ 24:45
14-16. ስለ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ በነበረን አመለካከት ላይ የተደረገው ማስተካከያ በሕዝቅኤል ምዕራፍ 40 እስከ 48 ላይ በነበረን ግንዛቤ ላይ ለውጥ ያስከተለው እንዴት ነው?
14 በ1971 “አሕዛብ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ”—እንዴት? (እንግሊዝኛ) የተባለ የሕዝቅኤልን ትንቢት የሚያብራራ አንድ መጽሐፍ ወጥቶ ነበር። የዚህ መጽሐፍ አንድ ምዕራፍ ሕዝቅኤል በተመለከተው የቤተ መቅደስ ራእይ ላይ አጠር ያለ ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር። (ሕዝቅኤል ምዕራፍ 40-48) በወቅቱ ትኩረት የተሰጠው ሕዝቅኤል ያየው የቤተ መቅደስ ራእይ በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንዴት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ነበር።—2 ጴጥሮስ 3:13
15 ሆኖም በታኅሣሥ 1, 1972 መጠበቂያ ግንብ ላይ ታትመው የወጡ ሁለት ርዕሰ ትምህርቶች ስለ ሕዝቅኤል ራእይ የነበረንን ግንዛቤ የሚነኩ ነበሩ። ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን ምዕራፍ 10 ላይ ስለገለጸው ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አብራርተዋል። መጠበቂያ ግንቡ የመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ቅድስትና የውስጠኛ አደባባይ ቅቡዓን በምድር ላይ ሳሉ የሚኖራቸውን ሁኔታ እንደሚያመለክት አብራርቶ ነበር። ከዓመታት በኋላ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 40 እስከ 48 እንደገና ሲመረመር መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ በዛሬው ጊዜ እየሠራ እንዳለ ሁሉ ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ቤተ መቅደስም በዛሬው ጊዜ በመሥራት ላይ እንደሆነ ተስተዋለ። እንዴት?
16 ሕዝቅኤል በተመለከተው ራእይ ላይ ካህናት በቤተ መቅደሱ አደባባይ ሆነው ካህናት ያልሆኑትን ነገዶች ሲያገለግሉ ታይተዋል። እነዚህ ካህናት የሚወክሉት “የንጉሥ ካህናት” የሆኑትን የይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮች እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። (1 ጴጥሮስ 2:9) ይሁን እንጂ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት በሙሉ በቤተ መቅደሱ ምድራዊ አደባባይ ያገለግላሉ ማለት አይደለም። (ራእይ 20:4) በዚያን ወቅት በአብዛኛው እንዲያውም ሙሉ በሙሉ ለማለት ይቻላል ቅቡዓን አምላክን የሚያገለግሉት በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ማለትም ‘በሰማይ’ ይሆናል። (ዕብራውያን 9:24) ሕዝቅኤል ባየው ቤተ መቅደስ አደባባይ ካህናት ወዲያ ወዲህ ሲሉ መታየታቸው ይህ ራእይ የተወሰኑት ቅቡዓን ገና ምድር ላይ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ ፍጻሜውን በማግኘት ላይ መሆን አለበት። በዚህ መሠረት የመጋቢት 1, 1999 የዚህ መጽሔት እትም ይህን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ የተደረገውን ማስተካከያ ይዞ ወጥቶ ነበር። እስከ 20ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ድረስ በሕዝቅኤል ትንቢት ላይ መንፈሳዊ ብርሃን ሲፈነጥቅ ቆይቷል።
አመለካከትህን ለማስተካከል ፈቃደኛ ሁን
17. ወደ እውነት ከመጣህበት ጊዜ ጀምሮ በግል አመለካከትህ ረገድ ምን ማስተካከያዎችን አድርገሃል? ይህስ የጠቀመህ እንዴት ነው?
17 እውነትን ለማወቅ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ‘አእምሮን ሁሉ እየማረከ ለክርስቶስ እንዲገዛ ለማድረግ’ ፈቃደኛ መሆን አለበት። (2 ቆሮንቶስ 10:5) በተለይ ሥር የሰደደ አመለካከት በሚኖርበት ጊዜ እንዲህ ማድረጉ ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። ለምሳሌ ያህል እውነትን ከማወቅህ በፊት ከቤተሰብህ ጋር ሆነህ አንዳንድ ሃይማኖታዊ በዓላትን ስታከብር ኖረህ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስትጀምር እነዚህ በዓላት አረማዊ አመጣጥ እንዳላቸው ተገነዘብክ። መጀመሪያ ላይ የተማርከውን ተግባራዊ ለማድረግ አንገራግረህ ይሆናል። በመጨረሻ ግን ከሃይማኖታዊ አመለካከትህ ይልቅ ለአምላክ ያለህ ፍቅር እየጠነከረ መጣና አምላክን የማያስደስቱትን በዓላት ማክበርህን አቆምክ። ያደረግከውን ውሳኔ ይሖዋ አልባረከልህም?—ከዕብራውያን 11:25 ጋር አወዳድር።
18. ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት የነበረን ግንዛቤ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ ሲሄድ ምን ምላሽ መስጠት አለብን?
18 ማንኛውንም ነገር በአምላክ መንገድ ማድረጋችን ጥቅሙ ለእኛው ነው። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ስለዚህ ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ያለን ግንዛቤ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ ሲሄድ እያደገ ባለው የእውነት እውቀት እንደሰት! አዎን፣ በየጊዜው አዳዲስ የእውቀት ብርሃን እያገኘን መሄዳችን በትክክለኛው ጎዳና ላይ እየተጓዝን መሆናችንን የሚያረጋግጥ ነው። ‘እንደ ንጋት ብርሃን የሆነውና ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ እየተጨመረ የሚበራው የጻድቃን መንገድ’ ነው። (ምሳሌ 4:18) በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ዓላማ አንዳንድ ገጽታዎች የምናየው ‘በድንግዝግዝ’ መሆኑ እውነት ነው። ሆኖም እግራችን ከዚህ “መንገድ” ሳይወጣ ከጸና አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ እውነት ሙሉ በሙሉ ፍንትው ብሎ ሲበራ እናያለን። ገና በግልጥ ያልተረዳናቸውን እውነቶች በተመለከተ የሚፈነጥቀውን የእውቀት ብርሃን በመጠባበቅ እስከዚያው ድረስ ይሖዋ በገለጠልን እውነቶች እንደሰት።
19. እውነትን እንደምንወድ የምናሳይበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
19 ላገኘነው ብርሃን ያለንን አድናቆት ተግባራዊ በሆነ መንገድ መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ የአምላክን ቃል ዘወትር ከተቻለም በየዕለቱ በማንበብ ነው። ቋሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም አለህ? መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችም ጥሩ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርቡልናል። በተጨማሪም እኛን ለመጥቀም ሲባል የተዘጋጁትን መጻሕፍት፣ ብሮሹሮችና ሌሎች ጽሑፎች አስብ። የመንግሥቱን ስብከት እንቅስቃሴ በተመለከተ በይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ላይ የሚወጡትን አበረታች ሪፖርቶች በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል?
20. ከይሖዋ የምናገኘው ብርሃንና እውነት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘታችን ጋር ያለው ዝምድና ምንድን ነው?
20 አዎን፣ ይሖዋ በመዝሙር 43:3 ላይ ለቀረበው ጸሎት አስደናቂ በሆነ መንገድ መልስ ሰጥቷል። በዚህ ጥቅስ መጨረሻ ላይ “[ብርሃንህና እውነትህ] ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያ ይውሰዱኝ” የሚል እናነባለን። ከሌሎች እጅግ ብዙ ሰዎች ጋር ሆነህ ይሖዋን ለማምለክ ትጓጓለህ? በስብሰባዎቻችን ላይ የሚቀርበው መንፈሳዊ ትምህርት ይሖዋ የእውቀት ብርሃን የሚሰጥበት አንዱ ዋነኛ መንገድ ነው። ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ያለን አድናቆት እንዲጨምር ምን ማድረግ እንችላለን? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የቀረበውን ትምህርት በጸሎት እንድትመረምረው እንጋብዝሃለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሲ ቲ ራስል ከሞተ በኋላ የሕዝቅኤልንና የራእይን መጻሕፍት ለማብራራት የተሞከረበት የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት ሰባተኛ ጥራዝ የሚል ስያሜ የተሰጠው ጽሑፍ ተዘጋጀ። ይህ ጥራዝ የያዘው ማብራሪያ በከፊል የተመሠረተው ራስል እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በተመለከተ በሰጠው ሐሳብ ላይ ነበር። ሆኖም የእነዚህን ትንቢቶች ትርጉም ማብራራት የሚቻልበት ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር። ስለዚህ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት በተባለው ጥራዝ ላይ የተሰጠው ማብራሪያ በአጠቃላይ ሲታይ ድንግዝግዝ ያለ ነበር። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይገባናል የማንለው የይሖዋ ደግነትና በዓለም ላይ የሚከናወኑ ሁኔታዎች ክርስቲያኖች የእነዚህን የትንቢት መጻሕፍት ትርጉም ይበልጥ በትክክል እንዲረዱ አስችለዋቸዋል።
ልትመልስ ትችላለህ?
• ይሖዋ ዓላማውን ደረጃ በደረጃ የሚገልጠው ለምንድን ነው?
• በኢየሩሳሌም የነበሩ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ግርዘትን በተመለከተ ለተነሳው ክርክር እልባት ያስገኙት እንዴት ነበር?
• የቀድሞዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሥራ ላይ ያዋሉት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ዘዴ ምን ዓይነት ነበር? ልዩ ያደረገውስ ምንድን ነው?
• አምላክ በወሰነው ጊዜ መንፈሳዊ ብርሃን የሚገለጠው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቻርልስ ቴዝ ራስል አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በራእይ መጽሐፍ ላይ ብርሃን እንደሚፈነጥቅ ተገንዝቦ ነበር