በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ክርስቶስ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር በነበረበት ወቅት ሰዎችን ለመርዳት ያከናወነው ነገር በጣም የሚያስደንቅ ነው። ይህ ነገር እውነት ከመሆኑ የተነሳ አንድ የዓይን ምሥክር ኢየሱስ በሕይወት ዘመኑ ያደረጋቸውን ነገሮች ከዘረዘረ በኋላ የሚከተለውን ተናገረ:- “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል።” (ዮሐንስ 21:​25) ኢየሱስ ብዙ ነገሮችን ያደረገው በምድር ላይ እያለ ስለነበረ እንዲህ ብለን እንጠይቅ ይሆናል:- ‘በሰማይ ሆኖ እንዴት ሊረዳን ይችላል? ኢየሱስ ከሚያሳየው ከአንጀት የመራራት ስሜት በአሁኑ ጊዜ ጥቅም ማግኘት እንችላለን?’

ለእነዚህ ጥያቄዎች የምናገኘው መልስ አስደሳችና አስተማማኝ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ “በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ . . . ወደ ሰማይ ገባ” በማለት ይነግረናል። (ዕብራውያን 9:​24) ለእኛ ምን አደረገልን? “[ክርስቶስ] የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት [“ወደ ሰማይ”] በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም” በማለት ጳውሎስ ያብራራል።​—⁠ዕብራውያን 9:​12፤ 1 ዮሐንስ 2:​2

ይህ እንዴት ያለ ምሥራች ነው! ኢየሱስ ወደ ሰማይ በሄደ ጊዜ ለሰዎች ያደርግላቸው የነበረው አስደናቂ ሥራ አላበቃም። ከዚህ ይልቅ ለሰው ዘሮች የበለጡ ነገሮችን ማከናወን እንዲችል በር ከፍቶለታል። ይህ የሆነበት ምክንያት አምላክ ይገባናል በማንለው ደግነቱ ተገፋፍቶ ኢየሱስን “የሕዝብ አገልጋይ” ማለትም “በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ” ሆኖ የሚያገለግል ሊቀ ካህናት አድርጎ ስለ ሾመው ነው።​—⁠ዕብራውያን 8:​1, 2 NW

“የሕዝብ አገልጋይ”

ኢየሱስ፣ በሰማይ ለሰው ዘር የሕዝብ አገልጋይ በመሆን ይሠራል። የእስራኤል ሊቀ ካህናት በጥንት ጊዜ ለነበሩት ለአምላክ አገልጋዮች ያደርግ የነበረውን ዓይነት ሥራ ያከናውናል። ያ ሥራ ምን ነበር? ጳውሎስ “ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና፤ ስለዚህም ለዚህ ደግሞ [ወደ ሰማይ የሄደው ኢየሱስ ክርስቶስ] የሚያቀርበው አንዳች ሊኖረው የግድ ነው” በማለት ገልጿል።​—⁠ዕብራውያን 8:​3

ኢየሱስ የጥንቱ ሊቀ ካህናት ሊያቀርብ ይችል ከነበረው የሚልቅ ነገር ነበረው። “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም” ለጥንቱ እስራኤል በተወሰነ ደረጃ መንፈሳዊ ንጽሕና ማስገኘት ከቻለ ‘የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልናመልክ ከሞተ ሥራ ሕሊናችንን ያነጻ ይሆን?’​—⁠ዕብራውያን 9:​13, 14

በተጨማሪም ኢየሱስ ያለ መሞትን ባሕርይ የተላበሰ በመሆኑ ምክንያት ከሁሉ የላቀ የሕዝብ አገልጋይ ያደርገዋል። በጥንቷ እስራኤል “እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው።” ኢየሱስስ? “ለዘላለም የሚኖር ስለ ሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” በማለት ጳውሎስ ጽፏል። (ዕብራውያን 7:​23-25፤ ሮሜ 6:​9) አዎን፣ በሰማይ በአምላክ ቀኝ ‘ስለ እኛ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት የሚኖር’ የሕዝብ አገልጋይ አለን! ይህ በአሁኑ ጊዜ ለምንኖረው ምን ትርጉም እንዳለው አስብ!

ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ ሰዎች ለእርዳታ ወደ እርሱ ይጎርፉ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜም ከእርሱ እርዳታ ለማግኘት ረዥም ርቀት ተጉዘው ወደ እሱ ይመጡ ነበር። (ማቴዎስ 4:​24, 25) አሁን ግን ኢየሱስ ያለው በሰማይ በመሆኑ በየትኛውም የምድር ክፍል ለሚገኙ ሰዎች ቅርብ ነው። በዚያው ባለበት በሰማይ ሁልጊዜ የሕዝብ አገልጋይ ሆኖ መሥራት ይችላል።

ኢየሱስ ምን ዓይነት ሊቀ ካህናት ነው?

በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰፈረው መግለጫ ለመርዳት ዝግጁና ከአንጀቱ የሚራራ መሆኑን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ ድንቅ መንፈስ ያለው መሆኑን አሳይቷል! እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ሆነው ለማረፍ የነበራቸው ፍላጎት ከአንድ ጊዜ በላይ ተስተጓጉሏል። ሰላማዊና ፀጥ ያለ ጊዜ ሊያገኝ የሚችልበትን አጋጣሚ እንዳስተጓጎሉበት አድርጎ ከማሰብ ይልቅ የእርሱን እርዳታ ለማግኘት ለመጡት ሰዎች ‘አዝኖላቸዋል።’ ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ ድክም ብሎት፣ እርቦትና ጠምቶት ሳለ እነርሱን ‘በደግነት ተቀብሎ’ ለመርዳት ሲል ጦሙን ለመዋል ፈቃደኛ ነበር።​—⁠ማርቆስ 6:​31-34፤ ሉቃስ 9:​11-17፤ ዮሐንስ 4:​4-6, 31-34

ኢየሱስ በሃዘኔታ ስሜት ተገፋፍቶ የሰዎችን አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ተግባራዊ እርምጃዎችን ወስዷል። (ማቴዎስ 9:​35-38፤ ማርቆስ 6:​35-44) ከዚያም በላይ ዘላቂ የሆነ እፎይታና ማጽናኛ እንዲያገኙ አስተምሯቸዋል። (ዮሐንስ 4:​7-30, 39-42) ለምሳሌ ያህል “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” በማለት ለሕዝቡ ያቀረበው ግብዣ ምንኛ ማራኪ ነው!​—⁠ማቴዎስ 11:​28, 29

ኢየሱስ ለሰዎች የነበረው ፍቅር ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ለኃጢአተኛው የሰው ዘር ሕይወቱን አሳልፎ እንዲሰጥ አድርጎታል። (ሮሜ 5:​6-8) ከዚህ በመነሳት ጳውሎስ የሚከተለውን ምክንያታዊ ማብራሪያ ሰጥቷል:- “[ይሖዋ አምላክ] ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? . . . የሞተው፣ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፣ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።”​—⁠ሮሜ 8:​32-34

ሊራራ የሚችል ሊቀ ካህናት

ኢየሱስ ሰው በነበረበት ወቅት ረሃብን፣ ጥማትን፣ ድካምን፣ ጭንቀትን፣ ሕመምንና ሞትን ቀምሷል። የደረሰበትን ውጥረትና ጭንቀት በጽናት ማለፉ በሥቃይ ላይ ለሚገኙት የሰው ዘሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ ለማገልገል ልዩ በሆነ መንገድ ብቁ አድርጎታል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[ኢየሱስ] የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፣ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፣ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።”​—⁠ዕብራውያን 2:​17, 18፤ 13:​8

ኢየሱስ ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ለመርዳት ብቃትም ሆነ ፈቃደኝነት ያለው መሆኑን አስመስክሯል። ታዲያ ይህ ማለት ኢየሱስ ይቅር ለማለት ፍላጎት የሌለውን ኃይለኛና ምሕረት የለሽ የሆነ አምላክ ማግባባት አለበት ማለት ነው? በጭራሽ። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “መሓሪና ይቅር ባይ” እንደሆነ ማረጋገጫ ይሰጠናል። በተጨማሪም እንዲህ ይላል:- “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።” (መዝሙር 86:​5፤ 1 ዮሐንስ 1:​9) በእርግጥም ርኅራኄ የተንጸባረቀበት የኢየሱስ አነጋገርና ድርጊት የአባቱን ርኅራኄ፣ ምሕረትና ፍቅር የሚያሳይ ነው።​—⁠ዮሐንስ 5:​19፤ 8:​28፤ 14:​9, 10

ኢየሱስ ንሥሐ ለሚገቡ ኃጢአተኞች እፎይታን የሚሰጣቸው እንዴት ነው? አምላክን ለማስደሰት በሚያደርጉት ልባዊ ጥረት ደስታና እርካታ እንዲያገኙ በመርዳት ነው። ጳውሎስ ለቅቡዓን ክርስቲያን ባልደረቦቹ የሚከተለውን በጻፈ ጊዜ ሁኔታውን ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል:- “እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፣ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፣ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።”​—⁠ዕብራውያን 4:​14-16

‘በሚያስፈልገን ጊዜ የሚረዳን’

ሥር የሰደደ ሕመም፣ የጥፋተኝነት ስሜት የሚያሳድረው የስሜት መደቆስ፣ ከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜትና ጭንቀት ወይም ሌሎች ከአቅማችን በላይ እንደሆኑ አድርገን የምናስባቸው ችግሮች በሚገጥሙን ጊዜ ምን ልናደርግ እንችላለን? ኢየሱስ ራሱ ዘወትር የድጋፍ ምንጭ አድርጎ ይመለከተው በነበረው ዝግጅት ማለትም ውድ በሆነው የጸሎት መብት እኛም ልንጠቀም እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ለእኛ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት በነበረው ምሽት “አጽንቶ ይጸልይ ነበር፤ ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ።” (ሉቃስ 22:​44) አዎን፣ ኢየሱስ፣ አምላክን በጸሎት መማጸን የሚያሳድረውን ስሜት ያውቃል። ኢየሱስ “በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፣ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት።”​—⁠ዕብራውያን 5:​7

ሰዎች የሚያቀርቡት ጸሎት ‘ተሰሚነት’ አግኝቶ የሚያጠነክራቸው ነገር ሲያገኙ የሚሰማቸውን ስሜት ኢየሱስ ያውቃል። (ሉቃስ 22:​43) ከዚያም በላይ እንዲህ በማለት ቃል ገብቷል:- “አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። . . . ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ።” (ዮሐንስ 16:​23, 24) በዚህም የተነሳ አምላክ ልጁ ያለውን ሥልጣንና ለእኛ ያቀረበውን የቤዛዊ መሥዋዕቱን ዋጋ እንዲጠቀምበት ያደርጋል የሚል ትምክህት ይዘን አምላክን ልንለምን እንችላለን።​—⁠ማቴዎስ 28:​18

ኢየሱስ በሰማይ ያገኘውን ሥልጣን በመጠቀም በተገቢው ጊዜ ትክክለኛውን እርዳታ እንደሚሰጠን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ለምሳሌ ያህል አንድ ዓይነት ኃጢአት ብንፈጽምና ከልባችን ብንጸጸት “ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ከሚለው የማረጋገጫ ቃል ማጽናኛ ልናገኝ እንችላለን። (1 ዮሐንስ 2:​1, 2) በሰማይ የሚገኘው ረዳታችንና አጽናኛችን ለእኛ ስለሚማልድ በስሙና ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር በሚስማማ መንገድ የምናቀርበው ጸሎት መልስ ያገኛል።​—⁠ዮሐንስ 14:​13, 14፤ 1 ዮሐንስ 5:​14, 15

ክርስቶስ ለሚያደርግልን እርዳታ አድናቆት ማሳየት

አምላክን በልጁ በኩል መለመን ብቻ በቂ አይደለም። በቤዛዊ መሥዋዕቱ ዋጋ አማካኝነት ክርስቶስ የሰውን ዘር ‘ዋጅቷል’፤ በሌላ አነጋገር የራሱ እንዲሆኑ ‘ገዝቷቸዋል።’ (ገላትያ 3:​13፤ 4:​5፤ 2 ጴጥሮስ 2:​1 NW ) ክርስቶስ በእኛ ላይ ያለውን ሥልጣን በመቀበልና “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ያቀረበልን ግብዣ በደስታ በመቀበል ክርስቶስ ላደረገልን ነገር ሁሉ ያለንን አመስጋኝነት ልናሳይ እንችላለን። (ሉቃስ 9:​23) ‘ራስን መካድ’ ማለት የራሳችን ንብረት አለመሆናችንን ከመናገር የሚበልጥ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። እንዲያውም “በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ [ክርስቶስ] ስለ ሁሉ ሞተ።” (2 ቆሮንቶስ 5:​14, 15) ስለዚህ ለቤዛው ያለን አድናቆት በአመለካከታችን፣ በግባችንና በአኗኗር ዘይቤአችን ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይኖርበታል። ‘ስለ እኛ ነፍሱን ለሰጠው ለክርስቶስ ኢየሱስ’ ባለ ዕዳ መሆናችን ስለ እርሱና አፍቃሪ ስለሆነው አባቱ ስለ ይሖዋ አምላክ ተጨማሪ ትምህርት እንድንቀስም ሊገፋፋን ይገባል። በተጨማሪም በእምነት ለማደግ፣ አምላክ ካወጣቸው ጠቃሚ መስፈርቶች ጋር ተስማምተን ለመኖርና ‘ለመልካም ሥራ ለመቅናት’ መፈለግ አለብን።​—⁠ቲቶ 2:​13, 14፤ ዮሐንስ 17:​3

የክርስቲያን ጉባኤ ወቅታዊ መንፈሳዊ ምግብ፣ ማበረታቻና መመሪያ የምናገኝበት ቦታ ነው። (ማቴዎስ 24:​45-47፤ ዕብራውያን 10:​21-25) ለምሳሌ ያህል ከመካከላችን አንዱ በመንፈሳዊ ቢታመም “የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች [የተሾሙ ሽማግሌዎችን] ወደ እርሱ ይጥራ።” ያዕቆብ በማከል “የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል” ሲል ማረጋገጫ ይሰጣል።​—⁠ያዕቆብ 5:​13-15

ይህን በምሳሌ ለማስረዳት:- በደቡብ አፍሪካ በእስር ቤት የሚገኝ አንድ ሰው “ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት እንዲቀርቡ በመርዳት ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስ የጀመረውን መልካም ሥራ በመፈጸም ላይ ለሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች” ያለውን አድናቆት የሚገልጽ ደብዳቤ ለአንድ የጉባኤ ሽማግሌ ጽፎ ነበር። ከዚያም እንዲህ በማለት ጻፈ:- “የላካችሁልኝ ደብዳቤ በደረሰኝ ጊዜ የተሰማኝ ደስታ ወሰን አልነበረውም። በመንፈሳዊ እኔን ለመታደግ ያሳያችሁት አሳቢነት ልቤን በጥልቅ ነክቶታል። ይህም ይሖዋ አምላክ ንሥሐ እንድገባ ያደረገልኝን ጥሪ እንድቀበል አድርጎኛል። ላለፉት 27 ዓመታት በኃጢአት፣ በአታላይነት፣ በሕግ አፍራሽነት፣ ከሥነ ምግባር ውጭ በሆነ አኗኗርና በሐሰት ሃይማኖት ጨለማ ውስጥ ስዳክርና መንገዴን ስቼ ስባዝን ኖሬያለሁ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከተገናኘሁ በኋላ እውነትን ማለትም ትክክለኛውን ጎዳና እንዳገኘሁ ሆኖ ይሰማኛል! አሁን የቀረኝ ነገር ቢኖር መንገዱን ተከትዬ መጓዝ ብቻ ነው።”

በቅርቡ የሚገኝ ከፍተኛ እርዳታ

እየተበላሸ በመሄድ ላይ የሚገኘው የዓለም ሁኔታ “ታላቁ መከራ” ከመፈንዳቱ በፊት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ዘመን ላይ እንደምንኖር በግልጽ የሚያሳይ ነው። በአሁኑ ጊዜ ከብሔር፣ ከነገድ፣ ከሕዝብና ከቋንቋ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ‘ልብሳቸውን አጥበው በበጉ ደም አንጽተዋል።’ (ራእይ 7:​9, 13, 14፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ በማመን ለኃጢአታቸው ይቅርታ እያገኙ ሲሆን ከአምላክ ጋርም የተቀራረበ ዝምድና እንዲመሠርቱና ከዚያም አልፎ የእርሱ ወዳጆች እንዲሆኑ እርዳታ በማግኘት ላይ ይገኛሉ።​—⁠ያዕቆብ 2:​23

በጉ ኢየሱስ ክርስቶስ “[ከታላቁ መከራ በሕይወት ለተረፉት] እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔር እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።” (ራእይ 7:​17) ከዚያም ክርስቶስ የሊቀ ካህንነቱን ሥራ ዳር ያደርሳል። ከዚያም ክርስቶስ ሁሉም የአምላክ ወዳጆች ‘ከሕይወት ውኃ ምንጭ’ የተሟላ መንፈሳዊ፣ አካላዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ ጥቅም እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። ኢየሱስ በ33 እዘአ የጀመረውና ከዚያም በሰማይ ሆኖ የቀጠለው ሥራ ፍጽምናን ያላብሳል።

ስለዚህ አምላክና ክርስቶስ ስላደረጉልንና እያደረጉልን ስላሉት ነገሮች ያለህን ጥልቅ አድናቆት ከመግለጽ ፈጽሞ ወደኋላ አትበል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይመክራል:- “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ . . . በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።”​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​4, 6, 7

በሰማይ ለሚገኘው ረዳታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለህን አድናቆት ልትገልጽ የምትችልበት አንድ ለየት ያለ መንገድ አለ። ረቡዕ፣ ሚያዝያ 19, 2000 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቶስን የሞት መታሰቢያ ለማክበር አንድ ላይ ይሰበሰባሉ። (ሉቃስ 22:​19) ለክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ያለህን አድናቆት ከፍ ማድረግ እንድትችል ይህ ጥሩ አጋጣሚ ይሰጥሃል። በዚህ ስብሰባ ላይ ተገኝተህ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት ያዘጋጀው መዳን ዘላለማዊ ጥቅም ሊያስገኝልህ የሚችለው እንዴት እንደሆነ ሲገለጽ እንድታዳምጥ ሞቅ ባለ ስሜት እንጋብዝሃለን። ይህ ልዩ ስብሰባ የሚደረግበትን ሰዓትና ቦታ ማወቅ ትችል ዘንድ እባክህ አካባቢህ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች አነጋግር።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ፣ አምላክን በጸሎት መማጸን የሚያሳድረውን ስሜት ያውቃል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቶስ ብቻችንን ልንወጣቸው የማንችላቸውን ችግሮች እንድንቋቋም ይረዳናል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቶስ አፍቃሪ በሆኑ ሽማግሌዎች አማካኝነት ይረዳናል