በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እርማት በመቀበል ረገድ ምሳሌ የሚሆን ሰው

እርማት በመቀበል ረገድ ምሳሌ የሚሆን ሰው

እርማት በመቀበል ረገድ ምሳሌ የሚሆን ሰው

“በዛምቢያ በየወሩ 30 ሰዎች በአዞዎች ይበላሉ።” አንድ የአፍሪካ ጋዜጣ ከጥቂት ዓመታት በፊት ይህን ዘግቦ ነበር። ጥናት ለማካሄድ እነዚህን ገበሎ አስተኔዎች የያዙ አንድ የስነ እንስሳ ተመራማሪ እንዳሉት “አንድ አዞ ለመያዝ 12 ሰዎች አስፈልገው ነበር።” ኃይለኛ ጭራውና መንጋጭላው አዞን አስፈሪ እንስሳ አድርገውታል!

ፈጣሪም አዞን ለማመልከት ይመስላል “ሌዋታን” በማለት አገልጋዩ ለሆነው ለኢዮብ አንድ አስፈላጊ የሆነ ትምህርት ለማስተማር ይህን “የአራዊት ሁሉ ንጉሥ” ተጠቅሟል። (ኢዮብ 41:​1, 341980 ትርጉም ) ይህ የሆነው ከዛሬ 3, 500 ዓመት በፊት በኡር ምድር ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በሰሜናዊው የአረብ ምድር አካባቢ ይገኛል። አምላክ ስለዚህ ፍጥረት መግለጫ በሚሰጥበት ጊዜ “ያንቀሳቅሰውም ዘንድ የሚደፍር የለም፤ እንግዲህ በፊቴ መቆም የሚችል ማን ነው?” ሲል ኢዮብን ነግሮታል። (ኢዮብ 41:​10የ1980 ትርጉም ) ይህ ምንኛ እውነት ነው! አዞ ይህን ያህል የሚያስፈራን ከሆነ በአዞ ፈጣሪ ላይ አንዳች የተቃውሞ ቃል እንዳንናገር ምንኛ ልንፈራ ይገባል! ኢዮብ ስህተቱን በማመን ለዚህ ትምህርት ያለውን አድናቆት አሳይቷል።​—⁠ኢዮብ 42:​1-6

ኢዮብ በሚጠቀስበት ጊዜ ፈተናዎችን በጽናት ለማለፍ ያሳየው የታማኝነት ምሳሌ ትዝ ይለን ይሆናል። (ያዕቆብ 5:​11) እንዲያውም በእምነቱ ላይ ከባድ ፈተና ከመድረሱም በፊት ይሖዋ በኢዮብ ተደስቶ ነበር። በአምላክ አመለካከት በዚያን ጊዜ “በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው” አልነበረም። (ኢዮብ 1:​8) ይህ ስለ ኢዮብ ተጨማሪ ትምህርት እንድንቀስም ሊገፋፋን የሚገባ ሲሆን እንዲህ ማድረጋችን እኛም አምላክን እንዴት ማስደሰት እንደምንችል እንድናውቅ ይረዳናል።

ቅድሚያ የሰጠው ከአምላክ ጋር ስላለው ዝምድና ነው

ኢዮብ ባለጸጋ ሰው ነበር። ከነበረው ወርቅ ሌላ 7, 000 በጎች፣ 3, 000 ግመሎች፣ 500 እንስት አህዮች፣ 1, 000 የቀንድ ከብቶችና እጅግ ብዙ አገልጋዮች ነበሩት። (ኢዮብ 1:​3) ይሁን እንጂ ኢዮብ ይታመን የነበረው በሀብት ሳይሆን በይሖዋ ነበር። እንዲህ በማለት አስረድቷል:- “ወርቅን ተስፋ አድርጌ፣ ጥሩውንም ወርቅ:- በአንተ እታመናለሁ ብዬ እንደ ሆነ፤ ሀብቴ ስለ በዛ፣ እጄም ብዙ ስላገኘች ደስ ብሎኝ እንደሆነ፤ . . . ልዑል እግዚአብሔርን በካድሁ ነበርና ይህ ደግሞ ፈራጆች የሚቀጡበት በደል በሆነ ነበር።” (ኢዮብ 31:​24-28) እኛም እንደ ኢዮብ ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ ከይሖዋ አምላክ ጋር ላለን የቅርብ ዝምድና ከፍተኛ ቦታ ልንሰጠው ይገባል።

ሰዎችን ተገቢ በሆነ መንገድ ይይዝ ነበር

ኢዮብ አገልጋዮቹን ይይዝ የነበረው እንዴት ነው? አገልጋዮቹ የማያዳላና የሚቀረብ ዓይነት ሰው ሆኖ እንዳገኙት የሚከተሉት ራሱ ኢዮብ የተናገራቸው ቃላት ይጠቁማሉ:- “ወንድ ባሪያዬ ወይም ሴት ባሪያዬ ከእኔ ጋር በተምዋገቱ ጊዜ፣ ሙግታቸውን ንቄ እንደ ሆነ፣ እግዚአብሔር በተነሣ ጊዜ ምን አደርጋለሁ? በጎበኘኝ ጊዜ ምን እመልስለታለሁ?” (ኢዮብ 31:​13, 14) ኢዮብ የይሖዋን ምሕረት ከፍ አድርጎ ይመለከት ስለነበር አገልጋዮቹንም በምሕረት ይዟቸዋል። በተለይ በጉባኤ ውስጥ በበላይ ተመልካችነት ቦታ ላይ ለሚገኙ ይህ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ይሆናል! እነርሱም ቢሆኑ አንዱን ከአንዱ የማያበላልጡ፣ የማያዳሉና በቀላሉ የሚቀረቡ መሆን አለባቸው።

ኢዮብ ለራሱ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን በውጭ ላሉ ሰዎችም አሳቢነት አሳይቷል። ለሌሎች ያለውን አሳቢነት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ድሀውን ከልመናው ከልክዬ፣ የመበለቲቱን ዓይን አጨልሜ እንደ ሆነ፣ . . . በበሩ ረዳት ስላየሁ፣ በድሀ አደጉ [“አባት በሌላቸው ልጆች፣” NW ] ላይ እጄን አንሥቼ እንደሆነ፣ ትከሻዬ ከመሠረትዋ ትውደቅ፣ ክንዴም ከመገናኛዋ ትሰበር።” (ኢዮብ 31:​16-22) እኛም በጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ ችግር ላይ ለወደቁ ሁሉ አሳቢነት የምናሳይ እንሁን።

ኢዮብ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ለሰዎች የአሳቢነት መንፈስ ስለነበረው የማያውቃቸውን ሰዎች በእንግድነት ይቀበል ነበር። በዚህም የተነሳ “መጻተኛው ግን በሜዳ አያድርም ነበር፣ ደጄንም ለመንገደኛ እከፍት ነበር” ብሎ ለመናገር ችሏል። (ኢዮብ 31:​32) ይህ በዛሬው ጊዜ ላሉ የአምላክ አገልጋዮች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት ያሳደሩ አዳዲስ ሰዎች ወደ መንግሥት አዳራሽ በሚመጡበት ጊዜ በጥሩ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እነርሱን መቀበላችን ለሚያደርጉት መንፈሳዊ እድገት አስተዋጽዖ ሊያበረክት ይችላል። እርግጥ ነው፣ ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾችም ሆነ ለሌሎች ክርስቲያኖች ፍቅራዊ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት ይኖርብናል።​—⁠1 ጴጥሮስ 4:​9፤ 3 ዮሐንስ 5-8

ኢዮብ ጠላቶቹን እንኳ ሳይቀር በጥሩ ፊት ይመለከታቸው ነበር። ለእርሱ ጥላቻ ባለው ሰው ላይ አደጋ ቢደርስ ኢዮብን አያስደስተውም ነበር። (ኢዮብ 31:​29, 30) ከዚያ ይልቅ ለሦስቱ የውሸት አጽናኞች ለመጸለይ ካሳየው የፈቃደኝነት መንፈስ ለማየት እንደሚቻለው እንደዚህ ላሉ ሰዎች መልካም ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር።​—⁠ኢዮብ 16:​2፤ 42:​8, 9፤ ከማቴዎስ 5:​43-48 ጋር አወዳድር።

በፆታ ሥነ ምግባር በኩልም ንጹህ ነበር

ኢዮብ ለትዳር ጓደኛው ታማኝ የነበረ ሲሆን ልቡ ሌላዋን ሴት እንዲከጅል ፈጽሞ አይፈቅድም ነበር። ኢዮብ እንዲህ አለ:- “ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፤ እንግዲህስ ቆንጆይቱን እንዴት እመለከታለሁ? ልቤ ወደ ሌላይቱ ሴት ጎምጅቶ እንደ ሆነ፣ በባልንጀራዬም ደጅ አድብቼ እንደ ሆነ፣ ሚስቴ ለሌላ ሰው ትፍጭ፣ ሌሎችም በእርስዋ ላይ ይጎንበሱ። ይህ ክፉ አበሳ [“ብልግና፣” NW ]፣ ፈራጆችም የሚቀጡበት በደል ነውና።”​—⁠ኢዮብ 31:​1, 9-11

ኢዮብ የብልግና ምኞት አእምሮውን እንዲያቆሽሽበት አልፈቀደም። ከዚያ ይልቅ ቅን ጎዳና ተከትሏል። ይሖዋ አምላክ፣ የብልግና ምኞቶችን አጥብቆ ይዋጋ በነበረው በዚህ ታማኝ ሰው መደሰቱ ምንም አያስደንቅም!​—⁠ማቴዎስ 5:​27-30

ለቤተሰቡ መንፈሳዊነት ያስብ ነበር

አልፎ አልፎ የኢዮብ ወንዶች ልጆች ድግስ ያዘጋጁና ወንዶችም ሴቶችም ልጆቹ አንድ ላይ ተሰባስበው ይበሉ ነበር። የድግሱ ቀናት ካለፉ በኋላ ኢዮብ ልጆቹ በይሖዋ ላይ ምናልባት ኃጢአት ፈጽመው ሊሆን ይችላል ብሎ ያስብ ነበር። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሰፈረው ዘገባ እንደሚገልጸው ኢዮብ አንድ ነገር ያደርግ ነበር:- “የግብዣውም ቀኖች ባለፉ ጊዜ ኢዮብ:- ምናልባት ልጆቼ በድለው፣ እግዚአብሔርንም በልባቸው ሰድበው ይሆናል ብሎ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር፤ ኢዮብም ማልዶ ተነሣ፣ እንደ ቁጥራቸውም ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።” (ኢዮብ 1:​4, 5) ኢዮብ እንዲህ ማድረጉ የቤተሰቡ አባላት ለይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲኖራቸውና በመንገዶቹም እንዲጓዙ ያለውን አሳቢነት የሚያሳይ ነበር!

ዛሬም ክርስቲያን የቤተሰብ ራሶች ቤተሰቦቻቸውን በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መምራት ይኖርባቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​8) ለቤተሰብ አባላትም መጸለይ ተገቢ ነው።​—⁠ሮሜ 12:​12

በታማኝነት በመጽናት ፈተናን አሸንፏል

በኢዮብ ላይ ስለ ደረሱት ከባድ ፈተናዎች አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባብያን ያውቃሉ። ሰይጣን ዲያብሎስ በኢዮብ ላይ ከባድ መከራ ቢደርስ አምላክን ይሰድባል የሚል ክስ አቀረበ። ይሖዋ ይህን ክስ ተቀበለ፤ ሰይጣንም ወዲያው በኢዮብ ላይ መቅሰፍቱን ማውረድ ጀመረ። ኢዮብ ከብቶቹ በሙሉ ሞቱበት። ይህም ሳያንስ ልጆቹን በሞት ማጣቱ ከባድ ሥቃይ አስከተለበት። ከዚያም ብዙም ሳይቆይ ሰይጣን ኢዮብን ከራስ ፀጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ በከባድ ቁስል መታው።​—⁠ኢዮብ ምዕራፍ 1, 2

ውጤቱ ምን ሆነ? ሚስቱ አምላክን እንዲሰድብ ስትወተውተው ኢዮብ “አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፣ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን? አላት።” የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በመጨመር “በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም” በማለት ይናገራል። (ኢዮብ 2:​10) አዎን፣ ኢዮብ በታማኝነት በመጽናት ዲያብሎስ ሃሰተኛ መሆኑን አረጋግጧል። እኛም በተመሳሳይ ፈተናዎችን በጽናት የምንወጣና አምላክን የምናገለግለው ለይሖዋ ባለን ንጹሕ ፍቅር ተገፋፍተን እንደሆነ የምናሳይ እንሁን።​—⁠ማቴዎስ 22:​36-38

የተሰጠውን እርማት በትሕትና ተቀብሏል

ምንም እንኳ ኢዮብ በብዙ መንገዶች ምሳሌ ቢሆንም ፍጹም አልነበረም። “ከርኩስ ነገር ንጹሕን ሊያወጣ ማን ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 14:​4፤ ሮሜ 5:​12) ስለዚህ አምላክ ኢዮብን ነቀፋ የሌለበት ብሎ ሲናገር አምላክ ፍጹማን ያልሆኑና ኃጢአተኛ የሆኑ ሰብዓዊ አገልጋዮቹ እንዲያሟሉ ከሚጠብቅባቸው ነገሮች ጋር ተስማምቶ ኖሯል ለማለት ነው። ይህ እንዴት የሚያበረታታ ነው!

ኢዮብ የደረሰበትን ፈተና በጽናት የተቋቋመ ቢሆንም ፈተናዎቹ ጉድለቱን አውጥተውበታል። ሦስት አጽናኝ ተብዬዎች የደረሰበትን መከራ በሙሉ ከሰሙ በኋላ ሊጠይቁት መጡ። (ኢዮብ 2:​11-13) ኢዮብ በሠራው ከባድ ኃጢአት ይሖዋ እንደቀጣው ተናገሩ። ኢዮብ በእነዚህ የሐሰት ክሶች ስሜቱ እንደተጎዳ ግልጽ ነው። እርሱም ራሱን ለመከላከል የተቻለውን ያህል ጥሯል። ሆኖም ራሱን ንጹሕ ለማድረግ ያደረገው ጥረት ሚዛኑን እንዲስት አደረገው። እንዲያውም እሱ ከአምላክ ይበልጥ ጻድቅ እንደሆነ አድርጎ ተናገረ!​—⁠ኢዮብ 35:​2, 3

አምላክ ኢዮብን ይወደው ስለነበር በአንድ ወጣት አማካኝነት ስህተቱን እንዲገነዘብ አደረገ። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ኢዮብም ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና . . . የኤሊሁ ቁጣ ነደደ፤ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና ኢዮብን ተቆጣው።” ኤሊሁ እንዳስተዋለው “ኢዮብ:- እኔ ጻድቅ ነኝ፣ እግዚአብሔር ግን ፍርዴን አስወገደ” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 32:​2፤ 34:​5) የሆነ ሆኖ ኤሊሁ፣ አምላክ ኢዮብን የቀጣው ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ነው በማለት ሦስቱ “አጽናኞች” በስህተት ከደረሱበት መደምደሚያ ጋር አልተስማማም። ከዚያ ይልቅ ኢዮብ ታማኝ መሆኑን ኤሊሁ በእርግጠኝነት በመናገር “የአንተ ጉዳይ በእርሱ እጅ ስለሆነ፣ በትዕግሥት ብትጠባበቅ ይሻልሃል” በማለት ኢዮብን መከረው። እርግጥ ነው፣ ኢዮብ በችኮላ በመናገር ንጹሕ መሆኑን ለማሳመን ከሚጥር ይልቅ ይሖዋን መጠበቅ ይገባው ነበር። ኤሊሁ “[አምላክ] በፍርድና በጽድቅም አያስጨንቅም” በማለት ለኢዮብ አረጋገጠለት።​—⁠ኢዮብ 35:​14 የ1980 ትርጉም፤ ኢዮብ 37:​23

የኢዮብ አስተሳሰብ መታረም ነበረበት። ስለዚህ ይሖዋ፣ ሰው ከአምላክ ትልቅነት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የማይባል ኢምንት መሆኑን ለማስገንዘብ አንድ ትምህርት ሰጠው። ይሖዋ ምድርን፣ ባሕርን፣ በሰማይ ላይ የሚገኙ ከዋክብትን፣ እንስሳትንና ሌሎች በርካታ አስደናቂ ፍጥረታትን ጠቀሰ። በመጨረሻም አምላክ ስለ ሌዋታን ማለትም ስለ አዞ ተናገረ። ኢዮብ የተሰጠውን እርማት በትህትና ተቀበለ። በዚህ ረገድም ለእኛ ምሳሌ ይሆነናል።

በይሖዋ አገልግሎት ጥሩ ተሳትፎ ለማድረግ ብንችልም ስህተት መሥራታችን ግን የማይቀር ነው። ከባድ ስህተት ስንሠራ ይሖዋ በሆነ መንገድ እርማት ሊሰጠን ይችላል። (ምሳሌ 3:​11, 12) ሕሊናችንን ጠቅ የሚያደርግ አንድ ጥቅስ ወደ አእምሯችን ሊመጣ ይችላል። ምናልባትም መጠበቂያ ግንብ ወይም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ያዘጋጀው አንድ ሌላ ጽሑፍ ስህተታችንን እንድንገነዘብ የሚያደርግ ነገር ሊነግረን ይችላል። ወይም በሥራ ላይ ሳናውል የቀረነው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት መኖሩን አንድ መሰል ክርስቲያን በደግነት ሊነግረን ይችላል። እነዚህን ለመሰሉ እርማቶች የምንሰጠው ምላሽ ምን ዓይነት ነው? ኢዮብ ጸጸት በሞላበት ስሜት “ራሴን እንቃለሁ፣ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ” በማለት ተናግሯል።​—⁠ኢዮብ 42:​6

ይሖዋ ክሶታል

ይሖዋ አገልጋዩ ተጨማሪ 140 ዓመት እንዲኖር በማድረግ ኢዮብን ክሶታል። በእነዚያ ዓመታትም አጥቶት ከነበረው እጅግ የበዛ ሀብት አግኝቷል። መጨረሻ ላይ ኢዮብ ቢሞትም እንኳ በአምላክ አዲስ ዓለም ትንሣኤ አግኝቶ እንደሚነሳ እርግጠኛ ነው።​—⁠ኢዮብ 42:​12-17፤ ሕዝቅኤል 14:​14፤ ዮሐንስ 5:​28, 29፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13

እኛም አምላክን በታማኝነት ብናገለግልና በመንገዳችን ላይ የሚሰጠንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እርማት ብንቀበል የአምላክን ሞገስና በረከት እንደምናገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። በውጤቱም በአምላክ አዲስ ሥርዓት ውስጥ የመኖር የተረጋገጠ ተስፋ ይኖረናል። ከሁሉም የበለጠው ግን ይሖዋን የምናከብር መሆናችን ነው። የታማኝነት አኗኗራችን ዋጋ ያስገኝልናል እንዲሁም ሕዝቦቹ እርሱን የሚያገለግሉት ለጥቅም ሳይሆን ከሙሉ ልብ በመነጨ የፍቅር ስሜት ተገፋፍተው እንደሆነ ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጣል። የተሰጠውን እርማት በትሕትና የተቀበለው ታማኙ ኢዮብ እንዳደረገው የይሖዋን ልብ ደስ የማሰኘት መብት በማግኘታችን ምንኛ የታደልን ነን!​—⁠ምሳሌ 27:​11

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብ ወላጆቻቸው ለሞቱባቸው ልጆች፣ ለመበለቶችና ለሌሎች ፍቅራዊ አሳቢነት አሳይቷል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብ የተሰጠውን እርማት በትሕትና በመቀበሉ ምክንያት በብዙ ተክሷል