ከኒው ዮርክ ከተማ የሚናፍቃት ነገር
ከኒው ዮርክ ከተማ የሚናፍቃት ነገር
እዚህ ላይ የሚታየው ጽሑፍ ከ1950 ጀምሮ ብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፋብሪካ ሕንጻዎች በአንዱ ላይ በጉልህ ይታያል። ይህ ጽሑፍ ለሥራ ወደ ከተማ የሚመላለሱትን፣ ጎብኚዎችንና በዚያ የሚያልፉ የሚያገድሙትን ሌሎች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እንዲያነቡ ሲያሳስባቸው ቆይቷል። ከአንዲት ወጣት ምሥክር የተላከው የሚከተለው ደብዳቤ ይህ ማሳሰቢያ ውጤታማ እንደነበረ ያሳያል።
“የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስጨርስ ምን መሥራት እንደምፈልግ ለክፍል ጓደኛዬ እየነገርኳት ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ስለሆነው ስለ ቤቴል ማውራት ስጀምር ደስ አላት። እርሷም ዕድሜ ልኳን በኒው ዮርክ ከተማ እንደኖረች ነገረችኝ። ቤተሰቦቿ ብዙም ሃይማኖተኞች አይደሉም፤ ይሁን እንጂ ሁልጊዜ ጧት በመስኮት ስትመለከት ‘የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ በየዕለቱ አንብቡ’ የሚለውን ጽሑፍ ታያለች። ስለዚህ በየቀኑ ትምህርት ቤት ከመሄዷ በፊት መጽሐፍ ቅዱሷን ታነባለች።
“የመኖሪያ ቦታ ከቀየረች በኋላ ከኒው ዮርክ ከተማ የሚናፍቃት ነገር ቢኖር ከእንቅልፏ ስትነቃ መጽሐፍ ቅዱሷን እንድታነብ ያሳስባት የነበረው ጽሑፍ እንደሆነ ተናግራለች። ይሁን እንጂ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሕንፃ ላይ በሚገኘው ጽሑፍ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ልማድ አድርጋው ስለነበር በየዕለቱ ማንበቧን አላቋረጠችም!”
የአምላክን ቃል የተወሰነ ክፍል በማንበብ ዕለቱን ከመጀመር የተሻለ ምን ነገር ሊኖር ይችላል? እንዲህ በማድረግ “ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፣ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል” የሚሉትን የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ልብ እንደምትል ምንም ጥርጥር የለውም።—2 ጢሞቴዎስ 3:15-17