በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰው ዘር ረዳት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

የሰው ዘር ረዳት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

የሰው ዘር ረዳት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

ቀደም ሲል ኩሩና ኃይለኛ የነበረ አንድ ሰው ‘ክፉና አሳዳጅ ነበርኩ’ ሲል አምኗል። ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ያለ ርኅራኄ ያንገላታና ይደበድብ የነበረ ተሳዳቢ ሰው ነበር። “ነገር ግን . . . ምሕረትን አገኘሁ” በማለት በአመስጋኝነት ስሜት ተናግሯል። ለማመን የሚያዳግት ቢመስልም እንኳ ይህ ኃይለኛ አሳዳጅ የነበረ ሰው ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ የሚታወቅ ታማኝ ክርስቲያን ሆኗል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 1:​12-16፤ ሥራ 9:​1-19

ሁሉም ሰው ጳውሎስ የፈጸመው ዓይነት ድርጊት አልፈጸመም። ሆኖም ሁላችንም አምላክ ያወጣቸውን የአቋም ደረጃዎች አናሟላም። ለምን? ምክንያቱም “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል።” (ሮሜ 3:​23) ከዚህም በላይ የአምላክን ምሕረት ማግኘት የማይገባኝ መጥፎ ሰው ነኝ ብለን በማሰብ በቀላሉ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ልንዋጥ እንችላለን። ጳውሎስ ራሱ ያለበትን የኃጢአተኝነት ዝንባሌ ካሰላሰለ በኋላ “እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል” በማለት ተናግሯል። ላቀረበው ጥያቄ ራሱ መልስ ሲሰጥ:- “በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” በማለት ጽፏል።​—⁠ሮሜ 7:​24, 25

ጻድቅ የሆነ ፈጣሪ ኃጢአተኞችን እንዴት ሊቀበል ይችላል? (መዝሙር 5:​4) ጳውሎስ ምን ብሎ እንደተናገረ ልብ በል “በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) የአምላክን ምሕረት ያገኘ ሌላ ሰው ደግሞ “ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ [“ረዳት፣” NW ] አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፣ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።”​—⁠1 ዮሐንስ 2:​1, 2

ኢየሱስ “ከአብ ዘንድ ጠበቃ [“ረዳት፣” NW ]” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? እንዲሁም ኢየሱስ “የኃጢአታችን ማስተስሪያ” የሆነው እንዴት ነው?

ረዳት ያስፈለገን ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው “ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ” ነው። (ማቴዎስ 20:​28) ቤዛ መልሶ ለመግዛት ወይም አንድን ሰው ወይም ነገር ለማስለቀቅ የሚከፈል ዋጋ ነው። “ቤዛ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ግስ ኃጢአት የመሸፈንን ወይም የማስተሰረይን ሐሳብ ያስተላልፋል። (መዝሙር 78:​38 NW ) ማቴዎስ 20:​28 ላይ እንደሚገኘው ግሪክኛው ቃል በተለይ ይሠራበት የነበረው የጦር እስረኞችን ለመቤዠት ወይም ባሪያዎችን ነፃ ለማውጣት የሚከፈለውን ዋጋ ለማመልከት ነበር። ፍትሕ የሚጠይቀውን ነገር ለማሟላት ለአንድ ነገር ልዋጭ ሆኖ የሚከፈል ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ነገር ይሰጣል።

የመጀመሪያው ሰው በአምላክ ላይ በማመፁ ምክንያት የሰው ዘር በባርነት ቀንበር ውስጥ ገባ። በ⁠ዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ላይ እንደተገለጸው ፍጹም የነበረው ሰው አዳም፣ ይሖዋ አምላክን ባለመታዘዝ የዓመፀኝነት ጎዳና መከተልን መረጠ። እንዲህ በማድረግ እርሱንም ሆነ ወደፊት የሚወልዳቸውን ዘሮቹን ለኃጢአትና ለሞት ባርነት ሸጧል። በዚህ መንገድ አዳም ራሱንም ሆነ ዘሮቹን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት አሳጥቷል።​—⁠ሮሜ 5:​12, 18, 19፤ 7:​14

በጥንቷ እስራኤል አምላክ መሥዋዕት ሆነው በሚቀርቡ እንስሳት አማካኝነት የሰዎችን ኃጢአት የማስተሰረይ ወይም የመሸፈን ዝግጅት አድርጎ ነበር። (ዘሌዋውያን 1:​4፤ 4:​20, 35) መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበው እንስሳ ሕይወት በኃጢአተኛው ሰው ምትክ የሚቀርብ ነበር። (ዘሌዋውያን 17:​11) በዚህም የተነሳ “የማስተሰረያ ቀን” “የቤዛ ቀን” እንደሆነ ተደርጎ ሊነገርም ይችላል።​—⁠ዘሌዋውያን 23:​26-28

ይሁን እንጂ እንስሳት ከሰው ያነሱ እንደመሆናቸው መጠን ‘የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ሊያስወግድ አይችልም።’ (ዕብራውያን 10:​1-4) አንድ መሥዋዕት ኃጢአትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስተሰረይ ወይም ለማንጻት የሚያስችል የተሟላ ዋጋ እንዲኖረው ካስፈለገ አዳም ካሳጣው ነገር ጋር የሚመጣጠን ዋጋ ሊኖረው ይገባል። የፍትሕ ሚዛን የተስተካከለ መሆን ይችል ዘንድ ፍጹም ሰው የነበረው (ኢየሱስ ክርስቶስ) ፍጹም ሰው የነበረው (አዳም) ያጣውን ነገር መልሶ ማስገኘት ይኖርበታል። የአዳም ዘሮችን በመጀመሪያ አባታቸው አማካኝነት ለባርነት ከተሸጡበት መልሶ ለመግዛት አንድ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሰው የቤዛውን ዋጋ መክፈል አለበት። እውነተኛ ፍትሕ የሚጠይቀው ነገር የሚሟላው ‘ነፍስ ለነፍስ’ ሲከፈል ነው።​—⁠ዘጸአት 21:​23-35

አዳም ኃጢአት ሠርቶ ሞት በተፈረደበት ጊዜ ወደፊት የሚወለዱት ዘሮቹ ገና በወገቡ ውስጥ ነበሩ። በዚህም የተነሳ አብረውት ሞተዋል። “ኋለኛው አዳም” ተብሎ የተጠራው ፍጹም የነበረው ኢየሱስ በራሱ ፈቃድ ቤተሰብ ሳያፈራ ቀርቷል። (1 ቆሮንቶስ 15:​45) ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ መሥዋዕት ሆኖ በሞተበት ወቅት ያልተወለዱ ዘሮች በወገቡ ውስጥ ነበሩ። ስለዚህ በወገቡ ውስጥ ያለው የወደፊት የሰው ዘር ከእርሱ ጋር አብሮ እንደ ሞተ ተደርጎ ሊነገር ይችላል። ኢየሱስ ኃጢአተኛና ሟች የሆነውን የአዳም ቤተሰብ የራሱ ንብረት ያደረገው ያህል ነበር። የራሱን ቤተሰብ ለመመሥረት የሚያስችለውን መብት ሠውቷል። ኢየሱስ የራሱን ፍጹም ሰብዓዊ አካል መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ መላውን የአዳም ዘር መልሶ ገዝቷል። በዚህም የተነሳ የራሱ ቤተሰብ በማድረግ ‘የዘላለም አባታቸው’ ሆኗል።​—⁠ኢሳይያስ 9:​6, 7

የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ታዛዥ የሰው ልጆች የአምላክን ምሕረት እንዲቀበሉና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ በር ከፍቷል። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 6:​23) ይሖዋ ለራሱም ሆነ በጣም ለሚወደው ልጁ ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትል ቢሆንም እንኳ ከቤዛው ጋር በተያያዘ ላሳየን ፍቅርና ርኅራኄ እርሱን እንድናወድስ ይገፋፋናል። (ዮሐንስ 3:​16) እንዲሁም ኢየሱስ ለሰማያዊ ሕይወት ትንሣኤ አግኝቶ የቤዛዊ መሥዋዕቱን ዋጋ በሰማይ በአምላኩ ፊት ባቀረበ ጊዜ “ከአብ ዘንድ ጠበቃ” መሆኑን አረጋግጧል። a (ዕብራውያን 9:​11, 12, 24፤ 1 ጴጥሮስ 3:​18) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ በአሁኑ ጊዜ በሰማይ ሆኖ ረዳታችን ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 4ንና 7ን ተመልከት።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአዳምን ዘሮች ለመቤዥት የኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ቤዛ ሆኖ ተከፍሏል