በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ እየመራን ያለው እንዴት ነው?

ይሖዋ እየመራን ያለው እንዴት ነው?

ይሖዋ እየመራን ያለው እንዴት ነው?

በቀና መንገድ ምራኝ።​—⁠መዝሙር 27:​11

1, 2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሕዝቡን እየመራ ያለው እንዴት ነው? (ለ) ከስብሰባዎች ሙሉ በሙሉ መጠቀም ምን ማድረግን ይጨምራል?

 ከዚህ በፊት በነበረው ርዕስ ላይ እንደተማርነው ይሖዋ የብርሃንና የእውነት ምንጭ ነው። በቀና መንገድ በምንጓዝበት ጊዜ ቃሉ ያበራልናል። ይሖዋ እያስተማረ በመንገዱ ይመራናል። (መዝሙር 119:​105) ልክ እንደ ጥንቱ መዝሙራዊ የይሖዋን መምሪያ በመቀበል አመስጋኝነታችንን እንገልጻለን፤ እንዲሁም “አቤቱ፣ መንገድህን አስተምረኝ፣ ስለ ጠላቶቼም በቀና መንገድ ምራኝ” ብለን እንጸልያለን።​—⁠መዝሙር 27:​11

2 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የሚያስተምርበት አንዱ መንገድ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ናቸው። በስብሰባ ላይ (1) ዘወትር በመገኘት (2) በጥሞና በማዳመጥና (3) አድማጮችን በሚያሳትፉ ክፍሎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ እየተጠቀምን ነውን? ከዚህም በተጨማሪ ‘በቀናው መንገድ’ መጓዛችንን እንድንቀጥል የሚረዱ ምክሮች ሲሰጡን በአድናቆት ተቀብለን አዎንታዊ ምላሽ እንሰጣለን?

በስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ ትገኛለህን?

3. አንዲት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ዘወትር በስብሰባዎች ላይ የመገኘት ልማድ ያዳበረችው እንዴት ነው?

3 አንዳንድ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ዘወትር መገኘት የጀመሩት ገና ከሕፃንነታቸው ጀምረው ነው። አንዲት የይሖዋ ምሥክር የሙሉ ጊዜ አገልጋይ “በ1930ዎቹ እኔና እኅቶቼ ልጆች በነበርንበት ወቅት ካልታመምን በስተቀር ከስብሰባ እንደማንቀር የታወቀ ስለሆነ ወላጆቻችንን ወደ ስብሰባ ስለመሄድ ጠይቀን አናውቅም። ቤተሰባችን ፈጽሞ ከስብሰባ አይቀርም” ስትል ተናግራለች። ልክ እንደ ነቢይቱ ሐና ይህችም እኅት ከይሖዋ የአምልኮ ሥፍራ ‘ጠፍታ አታውቅም።’​—⁠ሉቃስ 2:​36, 37

4-6. (ሀ) አንዳንድ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ከስብሰባዎች የሚቀሩት ለምንድን ነው? (ለ) በስብሰባዎች ላይ መገኘት ወሳኝ ነገር የሆነው ለምንድን ነው?

4 በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ከሚገኙት መካከል ነህ ወይስ አልፎ አልፎ ትቀራለህ? በዚህ ረገድ ብዙም ችግር እንደሌለባቸው ይሰማቸው የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች በስብሰባ ላይ የመገኘት ልማዳቸው ምን ያህል እንደሆነ ለመገምገም ፈለጉ። ለተወሰኑ ሳምንታት ስብሰባ ላይ በተገኙ ቁጥር ስብሰባ ላይ መገኘታቸውን በማስታወሻቸው ላይ ምልክት ያደርጉ ጀመር። ከዚያም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ማስታወሻቸውን ሲመለከቱና ምን ያህል ጊዜ ከስብሰባዎች እንደቀሩ ሲገነዘቡ በጣም ተገርመዋል።

5 ‘ታዲያ ይሄ ምን ያስገርማል። ዛሬ ሰዎች ብዙ ጫና ስላለባቸው በስብሰባዎች ላይ አዘውታሪ መሆን ያዳግታቸዋል’ ብሎ የሚናገር ይኖር ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ውጥረት በበዛበት ዘመን ውስጥ እንደምንኖር አይካድም። ደግሞ ውጥረቱ እየባሰ እንደሚሄድ የታወቀ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​13) ሆኖም ይህ ሁኔታ በስብሰባዎች ላይ ዘወትር የመገኘትን አስፈላጊነት ይበልጥ ወሳኝ አያደርገውምን? ጤናማ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ዘወትር እስካልተመገብን ድረስ ይህ ሥርዓት የሚያሳድርብንን ጫና መቋቋም እንችላለን ብለን ተስፋ ልናደርግ አንችልም። እንዲያውም አዘውትረን ካልተሰበሰብን ‘ከጻድቃን መንገድ’ ከነአካቴው ርቀን ለመሄድ ልንፈተን እንችላለን! (ምሳሌ 4:​18) እውነት ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ቀኑን ሙሉ ስንደክም ውለን ቤት ስንገባ ስብሰባ መሄድ ላይታየን ይችላል። ሆኖም ምንም ቢደክመን እንኳ በስብሰባ ላይ ከተገኘን ራሳችንን እንጠቅማለን በመንግሥት አዳራሽ የምናገኛቸውንም ክርስቲያን ባልንጀሮቻችንን እናበረታታለን።

6 ዕብራውያን 10:​25 በስብሰባ ላይ አዘውትሮ መገኘት በጣም አስፈላጊ የሆነበትን ሌላ ምክንያት ይገልጽልናል። በዚህ ጥቅስ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ቀኑ ሲቀርብ እያዩ አብልጠው’ ይህን እንዲያደርጉ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን አጥብቆ መክሯል። አዎን፣ “የይሖዋ ቀን” እየቀረበ በመምጣት ላይ መሆኑን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። (2 ጴጥሮስ 3:​12 NW ) የዚህ ሥርዓት ማክተሚያ ሩቅ ነው ብለን የምናስብ ከሆነ በስብሰባ ላይ እንደመገኘት ከመሳሰሉት በጣም አስፈላጊ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ይልቅ የግል ጉዳዮቻችንን ማስቀደም ልንጀምር እንችላለን። ከዚያም ልክ ኢየሱስ እንዳስጠነቀቀው ‘ያ ቀን በድንገት ይመጣብናል።’​—⁠ሉቃስ 21:​34

በጥሞና አዳምጡ

7. ልጆች በስብሰባዎች ላይ በትኩረት መከታተላቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

7 በስብሰባ ላይ መገኘት ብቻ በቂ አይደለም። በዚያ እየተነገረ ላለው ነገር ትኩረት መስጠትና በጥሞና ማዳመጥ አለብን። (ምሳሌ 7:​24) ይህ ደግሞ ልጆቻችንንም ይጨምራል። አንድ ልጅ ትምህርት ቤት በሚሄድበት ጊዜ ትምህርቱን ብዙም ባይወደውም ወይም ከእሱ የመረዳት ችሎታ በላይ ቢመስልም እንኳ አስተማሪው የሚናገረውን በጥሞና ማዳመጥ ይጠበቅበታል። ልጁ በጥሞና ለማዳመጥ ከሞከረ ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ ከትምህርቱ እንደሚጠቀም አስተማሪው ያውቃል። ታዲያ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ልጆች ገና ስብሰባው እንደ ጀመረ እንቅልፍ እንዲወስዳቸው ከመፍቀድ ይልቅ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጠውን ትምህርት በትኩረት እንዲከታተሉ ማድረግ ምክንያታዊ አይደለምን? እርግጥ ነው፣ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኙት ውድ እውነቶች መካከል ‘አንዳንዶቹ ለማስተዋል የሚከብዱ’ እንደሆኑ አይካድም። (2 ጴጥሮስ 3:​16) ቢሆንም የአንድን ልጅ የመረዳት ችሎታ አቅልለን መመልከት አይኖርብንም። አምላክ የልጆችን የመረዳት ችሎታ አቅልሎ አይመለከትም። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ‘ይሰሙና ይማሩ ዘንድ፣ አምላካቸውንም ይሖዋን ይፈሩ፣ የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ ጠብቀው ያደርጉ ዘንድ’ ወጣት አገልጋዮቹን አዝዞ ነበር። ከዚህ የሕግ ቃሎች መካከል አንዳንዶቹ ለልጆች አእምሮ የሚከብዱ እንደነበሩ ጥርጥር የለውም። (ዘዳግም 31:​12፤ ከዘሌዋውያን 18:​1-30 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ፣ በዛሬው ጊዜ ካሉት ልጆችስ ከዚህ ያነሰ ይጠብቃልን?

8. አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በስብሰባዎች ላይ በትኩረት እንዲከታተሉ ለመርዳት ምን እርምጃዎችን ወስደዋል?

8 ክርስቲያን ወላጆች የልጆቻቸው መንፈሳዊ ፍላጎት በከፊል የሚሟላው በስብሰባዎች ላይ በሚማሩት ነገር መሆኑን ይገነዘባሉ። ስለሆነም አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ንቁና ለመማር ዝግጁ ሆነው ወደ መንግሥት አዳራሽ እንዲሄዱ ለማድረግ ሲሉ ከስብሰባው በፊት ጥቂት እንዲተኙ ያደርጓቸዋል። አንዳንድ ወላጆች ደግሞ ምሽት ላይ ስብሰባ በሚኖራቸው ዕለት ልጆቻቸው ቴሌቪዥን የሚያዩበትን ሰዓት በተመለከተ ጥብቅ ገደብ ያበጃሉ ወይም በዚያን ዕለት ጭራሽ ቴሌቪዥን እንዳያዩ በመከልከል ጥበብ ያለበት እርምጃ ይወስዳሉ። (ኤፌሶን 5:​15, 16) እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው እንደ ዕድሜያቸውና እንደ አቅማቸው በተቻለ መጠን ሐሳባቸውን ሰብስበው በጥሞና እንዲያዳምጡና እንዲማሩ ያበረታታሉ።​—⁠ምሳሌ 8:​32

9. የማዳመጥ ችሎታችንን ለማዳበር ምን ሊረዳን ይችላል?

9 ኢየሱስ “እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ” ሲል የተናገረው ለአዋቂዎች ነበር። (ሉቃስ 8:​18) ዛሬ ዛሬ ይህን ማድረጉ እንደመናገሩ ቀላል አይደለም። በንቃት ማዳመጥ ከባድ ሥራ ነው፤ ሆኖም የማዳመጥ ችሎታ ሊዳብር ይችላል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ወይም የስብሰባ ክፍል በምታዳምጥበት ጊዜ ዋና ዋናዎቹን ሐሳቦች ለመለያየት ሞክር። ተናጋሪው ቀጥሎ ምን ሊናገር እንደሚችል ለመገመት ሞክር። በአገልግሎትህ ልትጠቀምባቸው ወይም በሕይወትህ ልትሠራባቸው የምትችላቸውን ነጥቦች ፈልግ። እየተብራሩ ያሉትን ነጥቦች በአእምሮህ ከልስ። አጭር ማስታወሻ ያዝ።

10, 11. አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ አድማጮች እንዲሆኑ የረዷቸው እንዴት ነው? አንተስ ጠቃሚ ሆኖ ያገኘኸው ዘዴ የትኛው ነው?

10 በጥሞና የማዳመጥ ልማድ በተሻለ ሁኔታ ሊዳብር የሚችለው በልጅነት ወቅት ነው። ዕድሜያቸው ለትምህርት ያልደረሰ አንዳንድ ልጆች ማንበብና መጻፍ ከመማራቸው በፊት እንኳ በስብሰባዎች ወቅት “ማስታወሻ” እንዲይዙ ወላጆቻቸው ያበረታቷቸዋል። “ይሖዋ፣” “ኢየሱስ” ወይም “መንግሥት” እንደሚሉት ያሉትን በተደጋጋሚ የሚነገሩ ቃላት በሚሰሙበት ጊዜ በወረቀት ላይ ይሞጫጭራሉ። በዚህ መንገድ ልጆች ከመድረክ የሚነገረውን በጥሞና ማዳመጥን ሊማሩ ይችላሉ።

11 ከፍ ያሉ ልጆችም እንኳ በትኩረት እንዲከታተሉ አንዳንዴ ማበረታቻ መስጠት ያስፈልጋል። በአንድ ትልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ አንድ የቤተሰብ ራስ የ11 ዓመት ልጁ ሐሳቡ ወደ ሌላ ቦታ እንደሄደ ሲያስተውል መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠውና ተናጋሪው ጥቅስ በሚጠቅስበት ጊዜ እያወጣ እንዲከታተል ጠየቀው። ማስታወሻ ይይዝ የነበረው አባትዬው ልጁ ጥቅስ የሚያወጣ መሆኑን ይከታተለው ነበር። ከዚያም ልጁ የስብሰባውን ፕሮግራም ይበልጥ በንቃት ተከታተለ።

ድምፃችሁ ይሰማ

12, 13. በጉባኤ በሚዘመሩ መዝሙሮች መሳተፍ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ ይሖዋ ሆይ፣ ምስጋና ከፍ ብሎ ይሰማ ዘንድ መሠዊያህን እዞራለሁ” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 26:​6, 7 NW ) የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች እምነታችንን ከፍ ባለ ድምፅ ለመግለጽ ግሩም አጋጣሚ ይሰጡናል። ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ በጉባኤ የሚዘመሩትን መዝሙሮች አብረን በመዘመር ነው። ይህ አንዱ አስፈላጊ የአምልኮታችን ክፍል ነው። ሆኖም በቀላሉ ቸል ሊባል ይችላል።

13 ማንበብ የማይችሉ አንዳንድ ልጆች በየሳምንቱ ስብሰባ ላይ የሚዘመሩትን መዝሙሮች ግጥም በቃላቸው ይይዙታል። ከትልልቆች ጋር አብረው ሲዘምሩ ደስ ይላቸዋል። ይሁን እንጂ ልጆች እያደጉ ሲሄዱ የመንግሥቱን መዝሙሮች አብረው የመዘመር ዝንባሌያቸው እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል። አንዳንድ አዋቂዎችም በስብሰባዎች ላይ መዘመር ያሳፍራቸዋል። ሆኖም የመስክ አገልግሎት የአምልኮታችን ክፍል እንደሆነ ሁሉ መዘመርም የአምልኮታችን አንዱ ክፍል ነው። (ኤፌሶን 5:​19) በመስክ አገልግሎት ይሖዋን ለማወደስ የተቻለንን እንደምናደርግ ሁሉ ጥሩ ድምፅ ኖረንም አልኖረንም የውዳሴ መዝሙሮችን ድምፃችንን ከፍ አድርገን ከልብ በመዘመር ይሖዋን ከፍ ከፍ ማድረግ አንችልምን?​—⁠ዕብራውያን 13:​15

14. በጉባኤ የምናጠናውን ትምህርት ቀደም ብሎ በጥንቃቄ መዘጋጀት ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

14 በተጨማሪም የአድማጮችን ተሳትፎ በሚጠይቅ የስብሰባ ክፍል ላይ ገንቢ የሆኑ ሐሳቦችን በመስጠት አምላክን ማወደስ እንችላለን። ይህ ደግሞ ዝግጅት ይጠይቃል። ጥልቅ የሆነውን የአምላክን ቃል የተለየ ገጽታ ለመረዳት ጊዜ ይጠይቃል። ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት ያጠና የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ተገንዝቦ ነበር። “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 11:​33) እናንተ የቤተሰብ ራሶች፣ እያንዳንዱ የቤተሰባችሁ አባል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን የአምላክን ጥበብ በጥልቅ እንዲመረምር መርዳታችሁ የግድ አስፈላጊ ነው። ከበድ ያሉ ነጥቦችን ለማብራራትና ቤተሰባችሁ ለስብሰባ እንዲዘጋጅ ለመርዳት በቤተሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት የተወሰነ ጊዜ መድቡ።

15. አንድ ሰው በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ እንዲሰጥ ምን ማድረግ ሊረዳው ይችላል?

15 በስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ ሐሳብ ለመስጠት ከፈለግህ ልትናገር የምትፈልገውን ሐሳብ ለምን አስቀድመህ አትዘጋጅም? ሰፊ ሐተታ መስጠት አያስፈልግም። ተስማሚ ሆኖ ያገኘኸውን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንደምታምንበት በሚያሳይ መንገድ ማንበቡ ወይም የተመረጡ ጥቂት ቃላትን ከልብ በመነጨ ስሜት መናገሩ በቂ ነው። አንዳንድ አስፋፊዎች እምነታቸውን የሚገልጹበት አጋጣሚ እንዳያመልጣቸው ሲሉ የጥናቱ መሪ አንድ የተወሰነ አንቀጽ ላይ ሲደርስ የመጀመሪያውን መልስ ለእነሱ እንዲሰጣቸው አስቀድመው ይነግሩታል።

በቂ ተሞክሮ የሌላቸው ጥበበኛ ይሆናሉ

16, 17. አንድ ሽማግሌ ለአንድ የጉባኤ አገልጋይ ምን ምክር ሰጠው? ውጤቱስ ምን ሆነ?

16 የአምላክን ቃል በየዕለቱ እንድናነብ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ በየጊዜው ማሳሰቢያ ይሰጠናል። በየዕለቱ የአምላክን ቃል ማንበብ መንፈስን ያድሳል። በተጨማሪም ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንድናደርግ፣ ያሉብንን መጥፎ ባሕርያት እንድናስተካክል፣ የሚደርሱብንን ፈተናዎች እንድንቋቋምና አቅጣጫችንን ስተን ከነበረ መልሰን መንፈሳዊ ሚዛናችንን እንድንይዝ ይረዳናል።​—⁠መዝሙር 19:​7

17 ተሞክሮ ያላቸው የጉባኤ ሽማግሌዎች ለእኛ ሁኔታ የሚስማማ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለመስጠት ምንጊዜም ዝግጁ ናቸው። እኛ ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክራቸውን ለማግኘት በመጣር ይህን ምክር ‘መቅዳት’ ነው። (ምሳሌ 20:​5) አንድ ቀን፣ ቅንዓት ያለው አንድ ወጣት የጉባኤ አገልጋይ ጉባኤውን ይበልጥ ሊጠቅም የሚችልበትን መንገድ በተመለከተ ሐሳብ እንዲለግሰው አንድን የጉባኤ ሽማግሌ ጠየቀ። ይህን ወጣት በደንብ የሚያውቀው ሽማግሌም የተሾሙ ወንዶች “ምክንያታዊ” መሆን እንዳለባቸው የሚገልጸውን 1 ጢሞቴዎስ 3:​3ን [NW ] ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥቶ አነበበለት። ይህ ወጣት ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ምክንያታዊነትን ሊያንጸባርቅ የሚችልበትን መንገድ በደግነት ጠቆመው። ይህ ወጣት ወንድም በተሰጠው ቀጥተኛ ምክር ተቀየመ? በፍጹም! “ሽማግሌው የመከረኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ ስለሆነ ምክሩ ከይሖዋ የመጣ እንደሆነ ተገነዘብኩ” ሲል ገልጿል። የጉባኤ አገልጋዩ የተሰጠውን ምክር በደስታ ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረግ ጥሩ እድገት እያሳየ ነው።

18. (ሀ) አንዲት ወጣት ክርስቲያን በትምህርት ቤት ሳለች ይደርሱባት የነበሩትን ፈተናዎች እንድትቋቋም የረዳት ምንድን ነው? (ለ) ፈተናዎች ሲያጋጥሙህ የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ታስታውሳለህ?

18 በተጨማሪም የአምላክ ቃል ወጣቶች “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት” እንዲሸሹ ይረዳቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 2:​22) በቅርቡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀች አንዲት ወጣት የይሖዋ ምሥክር በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ማሰላሰሏና ተግባራዊ ማድረጓ በትምህርት ቤት ባሳለፈቻቸው ዓመታት ይደርሱባት የነበሩትን ፈተናዎች እንድትቋቋም አስችሏታል። “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል” የሚለውን በምሳሌ 13:​20 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ምክር ብዙ ጊዜ ታስታውስ ነበር። ስለሆነም ጓደኝነት የምትመሠርተው ቅዱስ ጽሑፋዊ ለሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥልቅ አክብሮት ካላቸው ሰዎች ጋር ብቻ ነበር። ይህን ያደረገችበትን ምክንያት ስትገልጽ “እኔ ከማንም አልበልጥም። ከመጥፎ ልጆች ጋር ከገጠምኩ እነሱን ለማስደሰት መፈለጌና ችግር ውስጥ መግባቴ አይቀርም” ብላለች። በተጨማሪም በ2 ጢሞቴዎስ 1:​8 ላይ የሚገኘው የጳውሎስ ምክር ረድቷታል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በጌታችን ምስክርነት . . . አትፈር። ነገር ግን . . . ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል።” በዚህ ምክር መሠረት ባገኘችው አመቺ አጋጣሚ ሁሉ ለክፍል ጓደኞቿ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተ እምነቷ በድፍረት ትናገር ነበር። በክፍል ውስጥ የቃል ሪፖርት እንድታቀርብ ስትጠየቅ ስለ አምላክ መንግሥት በዘዴ ለመመስከር የሚያስችላትን ርዕስ ትመርጥ ነበር።

19. አንድ ወጣት የዚህን ዓለም ተጽእኖዎች መቋቋም ተስኖት የነበረው ለምንድን ነው? ሆኖም በኋላ መንፈሳዊ ጥንካሬ የሰጠው ምንድን ነው?

19 ምንጊዜም ቢሆን ‘ከጽድቅ መንገድ’ ወጣ ካልን የአምላክ ቃል እርምጃችንን እንድናስተካክል ሊረዳን ይችላል። (ምሳሌ 4:​18) በአፍሪካ የሚኖር አንድ ወጣት ይህ አባባል እውነት መሆኑን በራሱ ላይ ከደረሰው ሁኔታ ተገንዝቧል። አንድ የይሖዋ ምሥክር ያነጋግረውና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ይጀምራል። የሚማረውን ነገር ወድዶት ነበር፤ ሆኖም በትምህርት ቤት ከመጥፎ ልጆች ጋር ወዲያው ገጠመ። ከዚያም ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት መምራት ጀመረ። “ሕሊናዬ ዘወትር ይወቅሰኝ ስለነበር ስብሰባ ላይ መገኘቴን ለማቆም ተገደድኩ” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ከጊዜ በኋላ እንደገና ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመረ። ይህ ወጣት ሳይሸሽግ የሚከተለውን ተናግሯል:- “ለዚህ ሁሉ የዳረገኝ ዋና ምክንያት ራሴን ለመንፈሳዊ ረሀብ ማጋለጤ እንደሆነ ተገነዘብኩ። የግል ጥናት አልነበረኝም። የደረሰብኝን ፈተና መቋቋም ያቃተኝ ለዚህ ነው። ከዚያም መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ማንበብ ጀመርኩ። ቀስ በቀስ መንፈሳዊ ጥንካሬ እያገኘሁ መጣሁና በኋላ ሕይወቴን አስተካከልኩ። ያደረግኩትን ለውጥ ለሚያስተውሉ ሰዎች ይህ ትልቅ ምሥክርነት ነበር። ተጠመቅሁ፤ እነሆ አሁን ደስተኛ ነኝ።” ይህ ወጣት የሥጋ ድክመቱን እንዲያሸንፍ ብርታት የሰጠው ምንድን ነው? ዘወትር በሚደረግ የግል ጥናት አማካኝነት መንፈሳዊ ጥንካሬውን ማግኘቱ ነው።

20. አንድ ወጣት የሰይጣንን ጥቃት መቋቋም የሚችለው እንዴት ነው?

20 ክርስቲያን ወጣቶች፣ ዛሬ በእናንተ ላይ ከፍተኛ ጥቃት እየተሰነዘረ ነው! የሰይጣንን ጥቃት ለመቋቋም ከፈለጋችሁ ዘወትር መንፈሳዊ ምግብ መመገብ አለባችሁ። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ራሱም ወጣት የነበረው መዝሙራዊ ይህን ተረድቶ ነበር። ‘ጎልማሳ መንገዱን ማንጻት ይችል ዘንድ’ ቃሉን ስለሰጠው ይሖዋን አመስግኗል።​—⁠መዝሙር 119:​9

ይሖዋ በሚመራን መንገድ ሁሉ እንሄዳለን

21, 22. የእውነት መንገድ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ አድርገን መደምደም የሌለብን ለምንድን ነው?

21 ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር መርቷቸዋል። በሰብዓዊ ዓይን ሲታይ ይሖዋ አድካሚ መንገድ በመምረጥ አለአግባብ እንዳንከራተታቸው ሊታሰብ ይችላል። ይሖዋ ሕዝቦቹን ቀላልና ይበልጥ ቀና በሆነው በሜድትራንያን ባሕር በኩል ይዟቸው ከመሄድ ይልቅ አስቸጋሪ በሆነ ምድረ በዳ በኩል እየመራ ወሰዳቸው። ይሁን እንጂ ይህ ለእነሱ ሲል በደግነት ያደረገው ነገር ነበር። በዚህ ባሕር በኩል መሄድ አቋራጭ ቢሆንም እስራኤላውያን ጠላቶቻቸው በሆኑት በፍልስጤማውያን ምድር እንዲሄዱ ያደርጋቸው ነበር። ስለዚህ ይሖዋ በሌላ መንገድ ይዟቸው መሄዱ አለጊዜው ከፍልስጤማውያን ጋር ከመፋጠጥ አድኗቸዋል።

22 ዛሬም በተመሳሳይ አንዳንዴ ይሖዋ አስቸጋሪ በሆነ መንገድ እየመራን እንዳለ ሆኖ ይሰማን ይሆናል። የጉባኤ ስብሰባዎችን፣ የግል ጥናትንና የመስክ አገልግሎትን ጨምሮ እያንዳንዱ ሳምንት በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች የተያዘ ነው። ሌሎች መንገዶች ቀላል መስለው ሊታዩን ይችላሉ። ሆኖም ልንደርስበት እየጣርን ወዳለንበት ቦታ መድረስ የምንችለው ይሖዋ በሚመራን መንገድ ከሄድን ብቻ ነው። ስለዚህ ይሖዋ የሚሰጠንን ወሳኝ የሆኑ መመሪያዎች በመቀበል ‘ቀና በሆነው መንገድ’ ላይ ለዘላለም መመላለሳችንን እንቀጥል።​—⁠መዝሙር 27:​11

ልታብራራ ትችላለህ?

በተለይ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር መገኘታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ወላጆች ልጆቻቸው በስብሰባዎች ላይ በትኩረት እንዲከታተሉ ለመርዳት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

ጥሩ አድማጭ መሆን ምንን ይጨምራል?

በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ለመስጠት ምን ሊረዳን ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን የይሖዋ ቀን ከአእምሮአችን እንዳይጠፋ ይረዳናል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይሖዋን የምናወድስባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ