በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በናዚ የጭቆና ቀንበር ሥር ታማኝነትና ድፍረት ማሳየት

በናዚ የጭቆና ቀንበር ሥር ታማኝነትና ድፍረት ማሳየት

በናዚ የጭቆና ቀንበር ሥር ታማኝነትና ድፍረት ማሳየት

ሰኔ 17, 1946 ላይ የኔዘርላንድ ንግሥት ዊልሄልሚና በአምስተርዳም ለሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ የሐዘን መግለጫ መልእክት ላኩ። የመልእክቱ ዓላማ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚዎች ለተገደለው ለቤተሰቡ ልጅ ለያቆፕ ቫን ቤነኮም ያላቸውን አድናቆት ለመግለጽ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በፊት በምሥራቃዊ ኔዘርላንድ የምትገኘው የዲውቲከም ከተማ ምክር ቤት አንድን ጎዳና በቤርናርት ፖልማን ስም ለመሰየም ወስኗል። እሱም ቢሆን በጦርነቱ ወቅት የተገደለ የይሖዋ ምሥክር ነው።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚዎች በያቆፕ፣ በቤርናርትና በኔዘርላንድ ይኖሩ በነበሩ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተነሱት ለምን ነበር? እንዲሁም እነዚህ ምሥክሮች ለዓመታት ጭካኔ የተሞላበት ስደት እየደረሰባቸው በታማኝነት እንዲጸኑና በመጨረሻም የሀገራቸውን ሰዎች ጨምሮ የንግሥቲቱን አክብሮትና አድናቆት እንዲያተርፉ ያስቻላቸው ምንድን ነው? መልሱን ለማግኘት አናሳ በሆነው የይሖዋ ምሥክሮች ቡድንና በግዙፉ የናዚ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ድርጅት መካከል የዳዊትና የጎልያድ ዓይነት ፍጥጫ ላይ ያደረሷቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች እስቲ እንመልከት።

በእገዳ ሥር ቢሆኑም ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ይንቀሳቀሱ ነበር

ግንቦት 10, 1940 የናዚ ሠራዊት በኔዘርላንድ ላይ ድንገተኛ ወረራ አካሄደ። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሰራጩት ጽሑፍ የናዚዝምን እኩይ ተግባር ከማጋለጡም በላይ የአምላክን መንግሥት ስለሚደግፍ ናዚዎች የምሥክሮቹን እንቅስቃሴ ለማስቆም ወዲያውኑ ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ናዚዎች ኔዘርላንድን ከወረሩ ሦስት ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚያሳግድ አዋጅ በምሥጢር አወጡ። በመጋቢት 10, 1941 የወጣ ጋዜጣዊ መግለጫ ምሥክሮቹ “በሁሉም የመንግሥትና የቤተ ክርስቲያን ተቋማት” ላይ ዘመቻ አውጀዋል ብሎ በመወንጀል እገዳውን ይፋ አደረገው። ከዚህ የተነሳ ምሥክሮቹን እያደኑ መያዙ ተጧጧፈ።

ምንም እንኳ በአረመኔነቱ የሚታወቀው ጌስታፖ ማለትም የምሥጢር ፖሊስ በሁሉም ቤተ ክርስቲያኖች ላይ ክትትል ያደርግ የነበረ ቢሆንም ከባድ ስደት ያደርስ የነበረው ግን በአንድ የክርስቲያን ድርጅት ላይ ብቻ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። የደች ተወላጅ የሆኑት የታሪክ ምሁር ዶክተር ሉዊ ደ ዮንግ “እስከ ሞት ድረስ ስደት የገጠመው አንድ የሃይማኖት ቡድን ብቻ ሲሆን ይህም የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ቡድን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።​—⁠ሂት ኮኒንክሪክ ደር ነደርላንደን ኢን ደ ትዋደ ቫረልዶርሎክ (በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበረው የኔዘርላንድ ንጉሣዊ መንግሥት)።

ምሥክሮቹን አድኖ በመያዝ ረገድ ጌስታፖ የደች ፖሊሶች ትብብር አልተለየውም። በተጨማሪም ባደረበት ፍርሃት የተነሳ ከሃዲ የሆነ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች የቀድሞ የእምነት ጓደኞቹን የሚመለከት መረጃ ለናዚዎች ይሰጥ ነበር። በ1941 በሚያዝያ ወር መጨረሻ 113 ምሥክሮች በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር። ይህ ከባድ ጥቃት የስብከቱን እንቅስቃሴ አስቁሟልን?

የዚህ ጥያቄ መልስ በሚያዝያ 1941 በጀርመን ዚከሪትስፖሌትሲ (የሕዝብ ደኅንነት) በተዘጋጀው ሜልደንገን ኦውስ ዴን ኔይደርላንደን (ከኔዘርላንድ የተገኘ ሪፖርት) በተባለው በምሥጢር የተያዘ ሰነድ ላይ ይገኛል። ሪፖርቱ የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “ይህ የተወገዘ ኑፋቄ ሕገ ወጥ ስብሰባዎች በማካሄድ እንዲሁም ‘የአምላክን ምሥክሮች ማሳደድ ወንጀል ነው’ እና ‘ይሖዋ አሳዳጆችን በዘላለማዊ ጥፋት ይቀጣቸዋል’ የሚሉ መፈክሮች የተጻፉባቸውን ወረቀቶች በመለጠፍ በመላ አገሪቱ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።” ከሁለት ሳምንት በኋላ ይኸው ምንጭ “የሕዝብ ደኅንነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርገውን ጥብቅ ቁጥጥር እያጠናከረ ቢመጣም እንቅስቃሴያቸው እያደገ መሄዱን ቀጥሏል” ሲል ሪፖርት አድርጓል። አዎን፣ የመታሰር አደጋ ቢኖርም እንኳ ምሥክሮቹ ሥራቸውን በመቀጠል በ1941 ብቻ ከ350, 000 በላይ ጽሑፎች ለሕዝብ አበርክተዋል!

አነስተኛ በነበረው ሆኖም በቁጥር እየጨመረ በሚሄደው ቡድን ውስጥ የታቀፉት በጥቂት መቶ የሚቆጠሩ ምሥክሮች ኃያል የነበሩትን ጠላቶቻቸውን ለመጋፈጥ የሚያስችል ድፍረት ያገኙት እንዴት ነው? ልክ እንደ ጥንቱ ታማኝ ነቢይ እንደ ኢሳይያስ ሁሉ እነዚህ ምሥክሮች ይፈሩ የነበሩት ሰውን ሳይሆን አምላክን ነበር። ለምን? ይሖዋ ለኢሳይያስ በተናገረው የማጽናኛ ቃል ላይ ጠንካራ ትምክህት በመጣላቸው ምክንያት ነው:- “የማጽናናችሁ እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ፤ የሚሞተውን ሰው . . . ትፈራ ዘንድ አንተ ማን ነህ?”​—⁠ኢሳይያስ 51:​12

አክብሮት ያስገኘ ድፍረት

በ1941 ማብቂያ ላይ ታስረው የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር 241 ደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ ጥቂት የሚሆኑት በሰው ፍርሃት ተሸንፈዋል። የጀርመን የምሥጢር ፖሊስ አባል የሆነው በጭካኔው የሚታወቀው ቪሊ ላገስ “90 በመቶ የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች አንድም ምሥጢር ለማውጣት ፈቃደኞች አልሆኑም። በአንጻሩ ግን ምሥጢር ለመደበቅ ጥንካሬ የነበራቸው የሌሎች ሃይማኖት ቡድን አባላት ቁጥር በጣም ውስን ነበር” ብሎ ሲናገር ተሰምቷል። ከአንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ታስረው የነበሩት የደች ቄስ ዮሐንስ ጄ ቦስከስ የሰጡት አስተያየት የላገስን አባባል ያጠናክራል። በ1951 ቦስከስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:-

“በዚያን ጊዜ፣ በአምላክ ላይ ያላቸው ትምክህትና የእምነታቸው ጥንካሬ ለእነሱ ከፍተኛ አክብሮት እንዲያድርብኝ አድርጎኝ ነበር። የሂትለርንና የሦስተኛውን ራይክ ውድቀት የሚጠቁም በራሪ ወረቀት ያሰራጭ የነበረውን ወጣት ፈጽሞ አልረሳውም። በግምት እድሜው ከ19 ዓመት የሚያልፍ አይመስለኝም። . . . እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ እንደማያደርግ ቃል ቢገባ ኖሮ በግማሽ ዓመት ውስጥ ሊፈታ ይችል ነበር። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኑን በጥብቅ ገለጸ። በመሆኑም በጀርመን የጉልበት ሥራ በሚሠራበት ካምፕ ውስጥ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲታሰር ተፈረደበት። ሁላችንም ይህ ምን ሊያስከትልበት እንደሚችል አሳምረን እናውቅ ነበር። በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ሊወስዱት መጥተው ስንሰናበተው ሁሌ እንደምናስታውሰውና በጸሎት እንደምናስበውም ነገርኩት። የሰጠው መልስ ቢኖር ‘ስለ እኔ አትጨነቁ። የአምላክ መንግሥት መምጣቱ የተረጋገጠ ነው’ የሚል ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች በሚያስተምሯቸው ትምህርቶች ላይ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ሊኖራችሁ ቢችልም እንዲህ ዓይነቱ ነገር ፈጽሞ አይረሳችሁም።”

ጭካኔ የተሞላበት ተቃውሞ ቢገጥማቸውም እንኳ የምሥክሮቹ ቁጥር እያደገ ይሄድ ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ ትንሽ ቀደም ብሎ ወደ 300 ገደማ ይደርስ የነበረው የምሥክሮቹ ቁጥር በ1943 ወደ 1, 379 ደርሶ ነበር። የሚያሳዝነው ነገር በዚያው ዓመት መጨረሻ ላይ ታስረው ከነበሩት ከ350 በላይ ከሚሆኑ ምሥክሮች መካከል 54ቱ በተለያዩ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ መሞታቸው ነው። በ1944፣ ከኔዘርላንድ የመጡ በተለያዩ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ገና በእስር ላይ ያሉ 141 የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ።

የናዚ ስደት የመጨረሻ ዓመት

ድንገተኛ ጥቃት ከተሰነዘረበት ከሰኔ 6, 1944 በኋላ በምሥክሮቹ ላይ የሚደርሰው ስደት ወደ መጨረሻው ዓመት ገባ። ከወታደራዊ ሁኔታ አንጻር ናዚዎችና ተባባሪዎቻቸው አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ነበር። አንድ ሰው በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሥር ናዚዎች ክፋት የሌለባቸውን ክርስቲያኖች ማሳደዳቸውን ያቆማሉ ብሎ ያስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ በዚህ ዓመት ሌሎች 48 ምሥክሮች የታሰሩ ሲሆን ከታሰሩት መካከል ደግሞ ተጨማሪ 68 ምሥክሮች አልቀዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ያቆፕ ቫን ቤነኮም ነው።

የአሥራ ስምንት ዓመቱ ያቆፕ በ1941 የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን ከተጠመቁት 580 ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነቱን የሚያስጥስ ስለሆነበት ጥሩ ገቢ የሚያስገኝለትን ሥራ ለቀቀ። በተላላኪነት ሥራ ተቀጠረና የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከቦታ ቦታ ሲያጓጉዝ ተይዞ ታሰረ። ነሐሴ 1944 ላይ የ21 ዓመቱ ያቆፕ በሮተርዳም ከሚገኝ እስር ቤት ለቤተሰቦቹ ደብዳቤ ጻፈ:-

“እኔ በጣም ደህና ነኝ እንዲሁም ደስተኛ ነኝ። . . . እስካሁን ድረስ አራት ጊዜ ምርመራ ተደርጎብኛል። የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በጣም አሰቃቂ ነበሩ፤ ክፉኛም ደብድበውኛል። ሆኖም ጌታ በሰጠኝ ጥንካሬና ባሳየኝ ይገባኛል የማልለው ደግነት እስካሁን ምሥጢር መጠበቅ ችያለሁ። . . . እዚህ እስካሁን ድረስ ባጠቃላይ ስድስት ንግግሮች የመስጠት አጋጣሚ ያገኘሁ ሲሆን በድምሩ 102 አድማጮች ተገኝተው ነበር። አንዳንዶቹ ጥሩ ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን ከእስር እንደተፈቱ ወዲያው መጽሐፍ ቅዱስን መከታተላቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።”

መስከረም 14, 1944 ያቆፕ የደች ከተማ በሆነችው በአመርስፉርት ወደሚገኝ ማጎሪያ ካምፕ ተወሰደ። እዚያም መስበኩን ቀጥሏል። እንዴት? አብሮት ታስሮ የነበረ ሰው እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “እስረኞች ጠባቂዎቹ የጣሏቸውን የሲጋራ ቁርጥራጮች በመሰብሰብ ከመጽሐፍ ቅዱስ የቀደዱትን ገጽ ሲጋራ መጠቅለያ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር። አንዳንድ ጊዜ ያቆፕ ሲጋራ ለመጠቅለል ከተቀደደ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጽ ላይ ጥቂት ቃላት የማንበብ አጋጣሚ ያገኝ ነበር። ወዲያውኑ፣ ያነበባቸውን ቃላት መነሻ አድርጎ በመጠቀም ይሰብክልን ነበር። ብዙም ሳይቆይ ለያቆፕ ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ሰው’ የሚል ቅጽል ስም አወጣንለት።”

ጥቅምት 1944 ያቆፕ የታንኮችን እንቅስቃሴ ለመግታት ጉድጓድ እንዲቆፍሩ ከታዘዙ በርካታ እስረኞች መካከል ነበር። ያቆፕ ጦርነቱን ለመደገፍ በሚደረግ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ሕሊናው ስላልፈቀደለት በሥራው ለመካፈል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ምንም እንኳ ጠባቂዎቹ በተደጋጋሚ ቢዝቱበትም ለዛቻው አልተሸነፈም። ጥቅምት 13 ላይ አንድ የጦር መኮንን ለብቻው ታስሮ ከነበረበት ክፍል ጉድጓድ ወደሚቆፈርበት ቦታ ወሰደው። አሁንም ያቆፕ ከአቋሙ ፍንክች አላለም። በመጨረሻ ያቆፕ የራሱን መቀበሪያ እንዲቆፍር ታዘዘና በጥይት ተገደለ።

ምሥክሮቹን እያደኑ መያዙ ቀጠለ

የያቆፕም ሆነ የሌሎች ምሥክሮች ድፍረት የተሞላበት አቋም ናዚዎችን ያስቆጣ ሲሆን ምሥክሮቹን እያደኑ ለመያዝ ተጨማሪ ጥረት እንዲያደርጉም አነሳስቷቸዋል። ዒላማ ካደረጓቸው ሰዎች አንዱ የ18 ዓመቱ ኤቨርት ኪተላሪ ነበር። መጀመሪያ ላይ ኤቨርት ሳይያዝ ቀርቶ መደበቅ ቢችልም ከጊዜ በኋላ ግን ተያዘና ሌሎች ምሥክሮችን የሚመለከት መረጃ እንዲያወጣ ለማድረግ ክፉኛ ተደበደበ። ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ የጉልበት ሥራ እንዲሠራ ወደ ጀርመን ተላከ።

በዚያው ወር ማለትም ጥቅምት 1944 ፖሊሶች የኤቨርትን እህት ባል ቤርናርት ሎይመስን ፍለጋ ጀመሩ። ፈልገው ሲያገኙት አንቶኒ ራማየር እና አልቤርተስ ቦዝ ከሚባሉ ሌሎች ሁለት ምሥክሮች ጋር ነበር። ቀደም ሲል አልቤርተስ በአንድ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ለ14 ወራት ታስሮ ነበር። ሆኖም ከእስር ከተፈታ በኋላ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መካፈሉን ቀጠለ። በመጀመሪያ ናዚዎች እነዚህን ሦስት ሰዎች ያላንዳች ርኅራኄ ከደበደቧቸው በኋላ በጥይት ገደሏቸው። አስከሬናቸው የተገኘውና እንደ አዲስ ተቆፍሮ የተቀበረው ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በአገሪቱ የሚታተሙ በርካታ ጋዜጦች ይህን ግድያ በተመለከተ ዘግበዋል። አንደኛው ጋዜጣ እነዚህ ሦስት ምሥክሮች ከአምላክ ቃል ጋር የሚቃረን ማንኛውንም አገልግሎት ለናዚዎች ለመስጠት እንቢ ማለታቸውን ካተተ በኋላ በማከል “ለዚህም ሕይወታቸውን ከፍለዋል” ብሏል።

በዚህ መሀል ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቤርናርት ፖልማን ኅዳር 10, 1944 ላይ ተይዞ በአንድ ወታደራዊ ፕሮጄክት ውስጥ እንዲሠራ ተላከ። በግዳጅ እንዲሠሩ ከታዘዙት ሰዎች መካከል የይሖዋ ምሥክር የነበረውና ይህን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ሳይሆን የቀረው እሱ ብቻ ነበር። ጠባቂዎቹ አቋሙን ለማስቀየር የተለያዩ ዘዴዎች ሞከሩ። ምግብ አልተሰጠውም ነበር። እንዲሁም ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በዱላ፣ በአካፋና በሰደፍ ደበደቡት። በተጨማሪም እስከ ጉልበቱ በሚደርስ ቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ እየተንቦጫረቀ እንዲሄድ አስገደዱት። ከዚያም በውኃ የበሰበሰ ልብሱን ሳይቀይር የታፈገ ምድር ቤት ውስጥ አሳደሩት። አሁንም ቢሆን ቤርናርት አልተሸነፈም።

በዚህ ወቅት፣ የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሁለት የቤርናርት እህቶች እንዲጠይቁት ተፈቀደላቸው። ሐሳቡን እንዲቀይር ቢወተውቱትም በምንም መንገድ ከአቋሙ ፍንክች አላለም። ምን እንዲያደርጉለት እንደሚፈልግ ሲጠይቁት ወደ ቤት ተመልሰው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ሐሳብ አቀረበላቸው። ከዚያም ስቃይ የሚያደርሱበት ሰዎች ጽኑ አቋሙን እንዲያላላ ታደርገዋለች ብለው በማሰብ ጸንሳ የነበረችው ባለቤቱ እንድትጠይቀው ፈቀዱላት። ይሁን እንጂ የእሷ መምጣትና የተናገረችው የማበረታቻ ቃላት ቤርናርት ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ለመቀጠል ያደረገውን ቁርጥ ውሳኔ አጠናከረለት እንጂ ያሰቡት አልተሳካላቸውም። ኅዳር 17, 1944 ቤርናርት በግዳጅ እንዲሠሩ በተደረጉ ሌሎች ሠራተኞች ፊት ያሰቃዩት በነበሩ አምስት ሰዎች በጥይት ተገደለ። ቤርናርት ሰውነቱ በጥይት ተበሳስቶ ከሞተ በኋላም ኃላፊ የነበረው መኮንን በጣም ከመናደዱ የተነሳ ሽጉጡን መዝዞ በሁለቱም የቤርናርት ዓይኖች ላይ ተኮሰ።

ምንም እንኳ ይህን ጭካኔ የተሞላበት ግድያ በተመለከተ ወሬው የደረሳቸው ምሥክሮች ድንጋጤ ቢሰማቸውም ታማኝነታቸውንና ድፍረታቸውን የጠበቁ ከመሆናቸውም በላይ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያቸው ቀጥለዋል። ቤርናርት በተገደለበት አቅራቢያ የሚገኝ አንድ ትንሽ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ግድያው ከተፈጸመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሚከተለውን ሪፖርት ልኳል:- “በዚህ ወር ምንም እንኳ መጥፎ የአየር ሁኔታና ሰይጣን በመንገዳችን ላይ የሚያስቀምጣቸው እንቅፋቶች ቢኖሩም እንቅስቃሴያችንን ማሳደግ ችለናል። በመስክ አገልግሎት ያሳለፍነው ሰዓት ከ429 ወደ 765 ከፍ ብሏል። . . . አንድ ወንድም በስብከቱ ሥራ ላይ ሳለ ምሥክርነቱን ጥሩ አድርጎ የሚያዳምጠው ሰው አገኘ። ሰውየው፣ ወንድም የሚከተለው እምነት በጥይት የተገደለው ሰው ከነበረው እምነት ጋር አንድ ዓይነት እንደሆነ ጠየቀው። አንድ ዓይነት መሆኑን ሲሰማ ‘እንዴት ያለ የእምነት ሰው ነው! ለእምነቱ ያደረ ማለት እንዲህ ያለውን ነው!’ ሲል አድናቆቱን ገልጿል።”

ይሖዋ አይረሳቸውም

ግንቦት 1945 ናዚዎች ተሸንፈው ከኔዘርላንድ ተባረሩ። በጦርነቱ ወቅት የማያባራ ስደት ቢደርስባቸውም የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከጥቂት መቶዎች ተነስቶ ከ2, 000 በላይ ደርሷል። የታሪክ ምሁር የሆኑት ዶክተር ደ ዮንግ በጦርነቱ ወቅት ስለነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “አብዛኞቹ ዛቻና ድብደባ ቢደርስባቸውም እምነታቸውን ለመካድ እምቢተኞች ሆነዋል።”

በመሆኑም አንዳንድ ዓለማዊ ባለሥልጣኖች የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ አገዛዝ ሥር ባሳዩት ድፍረት የተሞላበት አቋም የሚያስታውሷቸው አለምክንያት አልነበረም። ሆኖም ከሁሉም በላይ በጦርነቱ ወቅት የነበሩት እነዚህ ምሥክሮች ያሳዩት ጠንካራ እምነት በይሖዋና በኢየሱስ ዘንድ ይታወሳል። (ዕብራውያን 6:​10) በይሖዋ አገልግሎት ሕይወታቸውን የሰዉ እነዚህ ታማኝና ደፋር ምሥክሮች እየቀረበ ባለው የኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት የግዛት ዘመን በምድራዊ ገነት ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይዘው ከመታሰቢያ መቃብር ይወጣሉ!​—⁠ዮሐንስ 5:​28, 29

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ያቆፕ ቫን ቤነኮም

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮችን መታገድ የሚገልጸውን ዐዋጅ የያዘ የጋዜጣ ቁራጭ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስተ ቀኝ:- ቤርናርት ሉይመስ፤ ከታች:- አልቤርቶስ ቦዝ (በስተ ግራ) እና አንቶኒ ራማየር፤ ከታች:- በሄምስቲዲ የሚገኘው የማኅበሩ ቢሮ