በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአምላክ ጋር የሚዋጉ አያሸንፉም!

ከአምላክ ጋር የሚዋጉ አያሸንፉም!

ከአምላክ ጋር የሚዋጉ አያሸንፉም!

ከአንተ ጋር ይዋጋሉ፣ ነገር ግን . . . ድል አይነሡህም።ኤርምያስ 1:​19

1. ኤርምያስ የተሰጠው ተልዕኮ ምን ነበር? ሥራውስ ለምን ያህል ጊዜ ቀጥሏል?

 ይሖዋ ወጣቱን ኤርምያስን ለአሕዛብ ነቢይ አድርጎ ሾሞት ነበር። (ኤርምያስ 1:​5) ይህ የሆነው በመልካሙ የይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ዘመን ነው። የኤርምያስ ትንቢታዊ አገልግሎት የባቢሎን መንግሥት ኢየሩሳሌምን ድል አድርጎ ከመያዙ በፊት የነበረውን ሁከት የነገሠበት ዘመንና የአምላክ ሕዝቦች ምርኮኞች የነበሩበትን ጊዜ የሚጨምር ነበር።​—⁠ኤርምያስ 1:​1-3

2. ይሖዋ ኤርምያስን ያበረታው እንዴት ነው? ይህን ነቢይ መቃወምስ ምን ማለት ነበር?

2 ኤርምያስ እንዲያውጅ የተነገረው የፍርድ መልእክት ተቃውሞ ማስነሣቱ የማይቀር ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ኤርምያስን ከፊቱ ለሚጠብቀው ነገር አዘጋጅቶታል። (ኤርምያስ 1:​8-10) ለምሳሌ ያህል “ከአንተ ጋር ይዋጋሉ፣ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ድል አይነሡህም፣ ይላል እግዚአብሔር” የሚሉት ቃላት የነቢዩን መንፈስ አጠናክረውለት ነበር። (ኤርምያስ 1:​19) ኤርምያስን መቃወም ማለት አምላክን መቃወም ማለት ነበር። ዛሬም ቢሆን ይሖዋ ከኤርምያስ ጋር የሚመሳሰል የነቢይነት ሥራ የሚሠራ የአገልጋዮች ቡድን አለው። ልክ እንደ እርሱ የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በድፍረት ያውጃሉ። መልእክቱ በበጎም ይሁን በክፉ እያንዳንዱን ግለሰብና ብሔር የሚነካ መልእክት ነው። ይህም በመልእክቱ በሚሰጡት ምላሽ ላይ የተመካ ነው። በኤርምያስ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ዛሬም የአምላክን አገልጋዮችና የተሰጣቸውን መለኮታዊ ሥራ በመቃወም ከአምላክ ጋር ሲጣሉ የሚገኙ ሰዎች አሉ።

የይሖዋ ሕዝቦች ጥቃት ይደርስባቸዋል

3. የይሖዋ አገልጋዮች ጥቃት ሲደርስባቸው የኖረው ለምንድን ነው?

3 ከ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ የይሖዋ ሕዝቦች ጥቃት ሲደርስባቸው ቆይቷል። በብዙ አገሮች በክፋት የተነሳሱ ሰዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች እወጃ ለማስተጓጎል ብሎም ለማስቆም ሞክረዋል። እንዲህ ለማድረግ ያነሳሳቸው ደግሞ “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ [የሚዞረው]” ቀንደኛው ባላጋራችን ዲያብሎስ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:​8) ‘የተቀጠሩት የአሕዛብ ዘመናት’ በ1914 ካበቁ በኋላ አምላክ ልጁን ‘በጠላቶቹ መካከል የመግዛት’ ተልዕኮ ሰጥቶ የምድር አዲስ ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። (ሉቃስ 21:​24 NW ፤ መዝሙር 110:​2) ክርስቶስ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ሰይጣንን ከሰማይ በማባረር በምድር አካባቢ ብቻ እንዲወሰን አድርጎታል። ዲያብሎስ የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን ስለሚያውቅ በቅቡዓኑና በተባባሪዎቻቸው ላይ ንዴቱን ሊወጣባቸው ይሞክራል። (ራእይ 12:​9, 17) እነዚህ ከአምላክ ጋር የሚዋጉ ሰዎች በተደጋጋሚ የሰነዘሩት ጥቃት ውጤት ምንድን ነው?

4. የይሖዋ ሕዝቦች በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ምን ፈተና ደርሶባቸዋል? ይሁን እንጂ በ1919 እና 1922 ምን ተከናውኗል?

4 በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቅቡዓን የይሖዋ አገልጋዮች ብዙ የእምነት ፈተና ገጥሟቸው ነበር። ማፌዣ ሆነዋል፣ ስማቸው ጠፍቷል፣ የሕዝብ ዓመፅ ተነስቶባቸዋል እንዲሁም ተደብድበዋል። ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው “በአሕዛብ ሁሉ የተጠ[ሉ]” ሆነው ነበር። (ማቴዎስ 24:​9) በዚያ ቀውጢ የጦርነት ወቅት የአምላክ መንግሥት ጠላቶች ቀደም ሲል በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ተሠርቶበት የነበረውን ዘዴ ተጠቅመዋል። ሕዝብን በመንግሥት ላይ ያነሳሳሉ በሚል የሐሰት ክስ የይሖዋን ሕዝቦች በመወንጀል የአምላክን ምድራዊ ድርጅት እምብርት የጥቃታቸው ዒላማ አደረጉ። ግንቦት 1918 የፌደራሉ መንግሥት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጄ ኤፍ ራዘርፎርድና ሰባት የቅርብ ባልደረቦቹ እንዲታሠሩ ፈቃድ ሰጠ። ከዚያም እነዚህ ስምንት ሰዎች የብዙ ዓመት እስር ተፈርዶባቸው በጆርጂያ፣ አትላንታ ወደሚገኘው የፌደራሉ ወህኒ ቤት ወረዱ። ይሁንና ከዘጠኝ ወራት በኋላ ተለቀቁ። በግንቦት 1919 የአካባቢው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በተከሳሾቹ ላይ የፍርድ መድሎ መደረጉን በመግለጽ ውሳኔውን ሻረው። ጉዳዩ እንደ አዲስ እንዲታይ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም መንግሥት ክሱን በማንሳቱ ወንድም ራዘርፎርድና ባልደረቦቹ ሙሉ በሙሉ ነፃ ወጡ። እንደገና ተግባራቸውን ማከናወን የጀመሩ ሲሆን በ1919ና በ1922ም በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ የተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎችም የመንግሥቱ የስብከት ሥራ በአዲስ መልክ ተጠናክሮ እንዲጀመር ኃይል ሰጥተዋቸዋል።

5. በናዚ ጀርመን ሥር የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

5 በ1930ዎቹ አምባገነን አገዛዞች ብቅ በማለታቸው ጀርመን፣ ኢጣሊያና ጃፓን የጋራ አንድ ጥምር ኃይል ፈጠሩ። በዚያ አሥርተ ዓመት መጀመሪያ ላይ የአምላክ ሕዝቦች በተለይ በናዚ ጀርመን አረመኔያዊ ድርጊት ይፈጸምባቸው ነበር። እገዳዎች ተጥለውባቸዋል። ቤቶቻቸው ይፈተሹና የተገኙት ሰዎች ይታሰሩ ነበር። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እምነታቸውን ለመካድ እምቢተኞች በመሆናቸው ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ተጥለዋል። በአምላክና በሕዝቡ ላይ የተከፈተው ውጊያ በእነዚህ ፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት ግዛት ውስጥ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች ጠራርጎ ለማጥፋት የታለመ ነበር። a የይሖዋ ምሥክሮች ለመብታቸው ለመሟገት በጀርመን ችሎት ፊት በቀረቡ ጊዜ የራይኩ የፍትህ ሚንስቴር የይሖዋ ምሥክሮች እንዳይሳካላቸው ለማድረግ ሲል የሚከተለውን ረጅም ሐተታ አዘጋጅቶ ሰጥቶ ነበር:- “ፍርድ ቤቶች እንዲሁ በሕግ አንቀጾች በመመራት ብቻ ስህተት መፈጸም የለባቸውም፤ ከዚያ ይልቅ ሕጉ ሊያስቸግራቸው ቢችልም የበለጠውን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያስችል መንገድ መፍጠር አለባቸው።” ይህ ደግሞ ትክክለኛ ፍትሕ ለማግኘት እንደማይቻል የሚያሳይ ነበር። ናዚዎች የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ አደገኛና አስጊ እንዲሁም ‘ለብሔራዊው ሶሺያሊስታዊ ግንባታ ደንቃራ ነው’ የሚል አመለካከት ነበራቸው።

6. በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅትና ከዚያም በኋላ ሥራችንን ለማስቆም ምን ዓይነት ጥረቶች ተደርገዋል?

6 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአውስትራሊያና በካናዳ እንዲሁም በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በካሪቢያንና በፓስፊክ ደሴቶች በሚገኙ የብሪታንያ የጋራ ብልፅግና አባል አገራት ውስጥ በአምላክ ሕዝቦች ላይ እገዳ ተጥሎ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ ሰፊ ተደማጭነት ያላቸው ጠላቶችና የተዛባ መረጃ የደረሳቸው ሰዎች ‘ሕግን ተንተርሰው ችግር’ ፈጥረዋል። (መዝሙር 94:​20 NW ) ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክን የሚያግድ ሕግ እንዲወጣ በቀረበው ጥያቄ ላይና ለባንዲራ ሰላምታ መስጠትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ችሎት ፊት በተካሄደው ክርክር መርታት የተቻለ ከመሆኑም በላይ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተላለፉት ውሳኔዎች ለአምልኮ ነፃነት ጠንካራ ድጋፍ ሆነዋል። ለይሖዋ ምስጋና ይድረሰውና ጠላት ያደረጋቸው ጥረቶች አልሰመሩም። በአውሮፓ ጦርነቱ ሲያበቃ ተጥለው የነበሩት እገዳዎችም ተነሡ። በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ታስረው የነበሩት በሺህ የሚቆጠሩ ምሥክሮች ተለቀቁ። ሆኖም ውጊያው አብቅቷል ማለት አልነበረም። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ ወዲያው ቀዝቃዛው ጦርነት ተጀመረ። የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ተጨማሪ ተጽእኖ ማሳደር ጀመሩ። የስብከት እንቅስቃሴያችንን ለማስተጓጎል ብሎም ለማስቆም፣ የጽሑፍ ስርጭቱን ለመግታት እንዲሁም ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ለማስቀረት በይፋ አንዳንድ እርምጃዎች ተወሰዱ። ብዙዎች ታሠሩ እንዲሁም የጉልበት ሥራ ቅጣት ወደሚፈጸምባቸው ካምፖች ተላኩ።

በስብከቱ ሥራ መቀጠል

7. የይሖዋ ምሥክሮች በቅርብ ዓመታት በፖላንድ፣ በሩሲያና በሌሎች አገሮች ምን ሁኔታ ገጥሟቸዋል?

7 ብዙ አሥርተ ዓመታት ካለፉ በኋላ የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ለማከናወን በሩ ተከፈተ። ፖላንድ ገና በኮሙኒስት አገዛዝ ሥር በነበረችበት በ1982 የአንድ ቀን የአውራጃ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ፈቀደች። ከዚያም በ1985 ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባዎች ተደረጉ። ቀጥሎም ከሩሲያና ከዩክሬይን የመጡ በሺህ የሚቆጠሩ ተሰብሳቢዎች የተገኙባቸው ትላልቅ ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባዎች በ1989 ተደርገዋል። በዚያው ዓመት ሃንጋሪና ፖላንድ ለይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ሰጥተዋል። በ1989 የመከር ወቅት የበርሊን ግንብ ፈረሰ። ከጥቂት ወራት በኋላ በምሥራቅ ጀርመን ሕጋዊ እውቅና አገኘን። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በበርሊን ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ተዘጋጀ። በ20ኛው መቶ ዘመን የመጨረሻ አሥርተ ዓመት መጀመሪያ ላይ በሩሲያ ከሚገኙ ወንድሞች ጋር በግል ለመገናኘት ጥረት እየተደረገ ነበር። በሞስኮ የሚገኙ አንዳንድ ባለ ሥልጣናትን ቀርቦ ማነጋገር በመቻሉ የይሖዋ ምሥክሮች በ1991 ሕጋዊ እውቅና አግኝተው ለመመዝገብ በቅተዋል። ከዚያ ጊዜ አንስቶ በሩሲያም ሆነ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት አካል በነበሩት ሪፐብሊኮች ሥራው ከፍተኛ እድገት አሳይቷል።

8. ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በነበሩት 45 ዓመታት የይሖዋ ሕዝቦች ምን ገጥሟቸዋል?

8 ስደቱ በአንዳንድ ቦታዎች ጋብ ቢልም በሌሎች ቦታዎች ግን ተጠናክሮ ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በነበሩት 45 ዓመታት ውስጥ ብዙ አገሮች ለይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ለመስጠት ፈቃደኞች አልነበሩም። በተጨማሪም በ23 የአፍሪካ፣ በ9 የእስያ፣ በ8 የአውሮፓ፣ በ3 የላቲን አሜሪካና በ4 የደሴት አገሮች ውስጥ በእኛ ወይም በሥራችን ላይ እገዳ ተጥሎ ነበር።

9. በማላዊ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ምን ዓይነት ሁኔታ አሳልፈዋል?

9 በማላዊ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከ1967 ጀምሮ ጭካኔ የሞላበት ስደት ደርሶባቸዋል። በዚያ አገር የሚገኙ የእምነት ወንድሞቻችን እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን ባላቸው የገለልተኛነት አቋም የፖለቲካ ፓርቲ ካርዶችን ለመግዛት ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። (ዮሐንስ 17:​16) በ1972 ከተደረገው የማላዊ ኮንግረስ ፓርቲ ስብሰባ በኋላ የሚፈጸምባቸው የጭካኔ ድርጊት በአዲስ መልክ ተጠናክሮ ቀጠለ። ወንድሞች ከቤታቸው ተባርረዋል፤ እንዳይሠሩ ታግደዋል። በሺህ የሚቆጠሩት ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ አገሪቷን ለቅቀው ተሰድደዋል። ይሁን እንጂ ከአምላክና ከወንድሞቻችን ጋር ውጊያ የገጠሙት እነዚህ ሰዎች አሸንፈዋልን? በፍጹም! ዛሬ ሁኔታዎቹ ተቀይረው በ1999 በማላዊ 43, 767 የደረሰ ከፍተኛ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ከ120, 000 የሚበልጡ ሰዎች በዚያች አገር በተካሄዱት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተዋል። በዋና ከተማዋም አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ ተገንብቷል።

ሰበብ ይፈላልጋሉ

10. በዳንኤል ሁኔታ እንደታየው ዛሬም ያሉት የአምላክን ሕዝብ የሚቃወሙ ሰዎች ምን አድርገዋል?

10 ከሃዲዎች፣ ቀሳውስትና ሌሎችም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መልእክታችንን መስማት አይሆንላቸውም። በአንዳንድ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ክፍሎች ግፊት ተቃዋሚዎች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚያካሂዱትን ውጊያ ትክክለኛ ነገር አስመስለው ለማቅረብ ሕጋዊ የሚሉትን መንገድ ይፈልጋሉ። አንዳንድ ጊዜ የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ምንድን ናቸው? ሴራ ይጠነስሱ የነበሩት ሰዎች ዳንኤልን ለማጥቃት የተጠቀሙበት ዘዴ ምን ነበር? በዳንኤል 6:​4, 5 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “የዚያን ጊዜም አለቆችና መሳፍንቱ ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ሰበብ ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን የታመነ ነበረና፣ ስሕተትና በደልም አልተገኘበትምና በእርሱ ላይ ሰበብና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም። እነዚያም ሰዎች:- ከአምላኩ ሕግ በቀር በዚህ በዳንኤል ላይ ሌላ ሰበብ አናገኝበትም አሉ።” ዛሬም በተመሳሳይ ተቃዋሚዎች ሰበብ ለማግኘት ይፈልጋሉ። ስለ “አደገኛ ኑፋቄዎች” በየአደባባዩ ይለፍፉና የይሖዋ ምሥክሮችንም ከእነዚህ ቡድኖች መካከል ለመፈረጅ ይሞክራሉ። ያለ ስማቸው ስም በመስጠት፣ በተዘዋዋሪ መንገድ በመዝለፍና ውሸት በመናገር የአምልኮ መንገዳችንንና አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሙጥኝ ማለታችንን ይነቅፋሉ።

11. የይሖዋ ምሥክሮችን የሚቃወሙ አንዳንድ ሰዎች ምን የሐሰት ክስ አቅርበዋል?

11 በአንዳንድ አገሮች ያሉ የተለያዩ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ወገኖች የምናካሂደው ‘አምልኮ በእግዚአብሔር ዘንድ ንጹሕና ነውር የሌለበት’ መሆኑን አምነው መቀበል አይፈልጉም። (ያዕቆብ 1:​27) ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችን በ234 አገሮች ውስጥ እየተካሄደ ያለ ቢሆንም ሃይማኖታችሁ “የታወቀ ሃይማኖት” አይደለም ለማለት ይዳዳቸዋል። በ1998 ከተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ትንሽ ቀደም ብሎ አንድ በአቴንስ የሚታተም ጋዜጣ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቄስ የተናገሩትን “[የይሖዋ ምሥክሮች] ሃይማኖት ‘የታወቀ ሃይማኖት’ አይደለም” የሚለውን ከአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ውሳኔ ጋር የማይጣጣም ሐሳብ ዘግቧል። ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ በዚያው ከተማ የሚታተም አንድ ሌላ ጋዜጣ አንድ የቤተ ክርስቲያን ቃል አቀባይ እንደሚከተለው ማለታቸውን ዘግቦ ነበር:- “[የይሖዋ ምሥክሮች] የኢየሱስ ክርስቶስን ባሕርይ ከሚያንጸባርቀው የክርስቲያን እምነት ጋር የሚጣጣም ነገር የላቸውምና ‘የክርስቲያን ጉባኤ’ ተብለው ሊጠሩ አይችሉም።” የኢየሱስን ፈለግ ስለ መከተል የይሖዋ ምሥክሮችን ያህል የሚጨነቅ አንድም ሃይማኖታዊ ቡድን አለመኖሩ እውነት ሆኖ ሳለ እንዲህ ብለው መናገራቸው በጣም የሚያስገርም ነው!

12. መንፈሳዊ ውጊያችንን ስናካሂድ ማድረግ ያለብን ነገር ምንድን ነው?

12 ምሥራቹ ሕጋዊ ከለላ እንዲያገኝ ለማድረግ እንጥራለን። (ፊልጵስዩስ 1:​7 NW ) ከዚሁ ጋር ደግሞ ለአምላክ የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች ያለንን ጥብቅ አቋም አናላላም ወይም አንተውም። (ቲቶ 2:​10, 12) ልክ እንደ ኤርምያስ እኛም አምላክን የሚቃወሙ ወገኖች በምንም ዓይነት እንዲያስፈራሩን ሳንፈቅድ ‘ወገባችንን ታጥቀን አምላክ ያዘዘንን ሁሉ እንናገራለን።’ (ኤርምያስ 1:​17, 18) የይሖዋ ቅዱስ ቃል ልንመላለስበት የሚገባንን ትክክለኛ ጎዳና በግልጽ አመልክቶናል። ደካማ በሆነው “የሥጋ ክንድ” ለመደገፍ ወይም ‘በግብጽ ጥላ’ ማለትም በዚህ ዓለም ለመታመን አንፈልግም። (2 ዜና መዋዕል 32:​8፤ ኢሳይያስ 30:​3፤ 31:​1-3) ይህንን መንፈሳዊ ውጊያ ስናካሂድ በራሳችን ማስተዋል ከመደገፍ ይልቅ በፍጹም ልባችን በይሖዋ መታመናችንንና እርሱ መንገዳችንን እንዲመራልን መፍቀዳችንን መቀጠል ይኖርብናል። (ምሳሌ 3:​5-7) የይሖዋን ድጋፍ ካላገኘንና እሱ ራሱ ካልጠበቀን ሥራችን ሁሉ ‘ከንቱ’ ይሆናል።​—⁠መዝሙር 127:​1

ስደት ቢደርስባቸውም አቋማቸውን አያላሉም

13. ሰይጣን በኢየሱስ ላይ የሰነዘረው ጥቃት መክኗል ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

13 አላንዳች ማወላወል ለይሖዋ የማደርን ባሕርይ በማሳየት በኩል ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ኢየሱስ ሲሆን ሕዝብን በማነሳሳትና መንግሥትን በማወክ በሐሰት ተወንጅሎ ነበር። ጲላጦስ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ኢየሱስን በነፃ ሊያሰናብተው ፈልጎ ነበር። ኢየሱስ ምንም ጥፋት የሌለበት ሰው ቢሆንም የተሰበሰበው ሕዝብ ግን በሃይማኖት መሪዎቹ ቆስቋሽነት ይሰቀል እያለ ጮኸ። ይልቁንም በኢየሱስ ፋንታ በመንግሥት ላይ ሕዝብን በማነሳሳትና ሰው በመግደል ወንጀል ወኅኒ ወርዶ የነበረው በርባን እንዲፈታላቸው ጠየቁ! ጲላጦስ እነዚህን ምክንያታዊነት የጎደላቸው ተቃዋሚዎች ሐሳባቸውን ለማስቀየር በማሰብ ሌላ ሙከራ አድርጎ ነበር። ይሁንና በመጨረሻ ለሕዝቡ ጩኸትና ጥያቄ እጁን ሰጠ። (ሉቃስ 23:​2, 5, 14, 18-25) ኢየሱስ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ቢሞትም ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት አስነስቶ በቀኙ በክብር ስላስቀመጠው ሰይጣን አንዳች ጥፋት ባልነበረበት የአምላክ ልጅ ላይ የሰነዘረው ይህ አሰቃቂ ጥቃት መክኗል። ክብር በተጎናጸፈው በኢየሱስ አማካኝነት መንፈስ ቅዱስ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን በመፍሰሱ “አዲስ ፍጥረት” የሆነው ክርስቲያን ጉባኤ ተቋቁሟል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 5:​17፤ ሥራ 2:​1-4

14. የአይሁድ ሃይማኖታዊ ወገኖች የኢየሱስን ተከታዮች መቃወማቸው ውጤቱ ምን ነበር?

14 ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሃይማኖታዊ ወገኖች ሐዋርያቱን አስፈራርተዋቸው ነበር። ሆኖም እነዚያ የክርስቶስ ተከታዮች ያዩትንና የሰሙትን ነገር ከመናገር ወደኋላ አላሉም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “አሁንም፣ ጌታ ሆይ፣ ወደ ዛቻቸው ተመልከት፤ . . . ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው” ሲሉ ጸልየዋል። (ሥራ 4:​29) ይሖዋም በመንፈስ ቅዱስ በመሙላትና ቃሉን በድፍረት ማወጃቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችል ብርታት በመስጠት ለልመናቸው ምላሽ ሰጥቷል። ብዙም ሳይቆይ በድጋሚ ሐዋርያቱ መስበካቸውን እንዲያቆሙ በታዘዙ ጊዜ ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ሲሉ መልሰዋል። (ሥራ 5:​29) ዛቻ፣ እስርና ግርፋት የመንግሥቱን ሥራቸውን ከማስፋፋት አልገታቸውም።

15. ገማልያል ማን ነበር? የኢየሱስን ተከታዮች ይቃወሙ ለነበሩት ሃይማኖታዊ ወገኖችስ ምን ምክር ሰጥቷል?

15 የሃይማኖት መሪዎቹ ምላሽ ምን ነበር? “እነርሱም ሲሰሙ በጣም ተቈጡ [ሐዋርያትን] ሊገድሉአቸውም አሰቡ።” ይሁን እንጂ በሁሉም ዘንድ ተሰሚነት የነበረው ገማልያል የሚባል አንድ ፈሪሳዊ የሕግ መምህር በዚያ ነበር። ሐዋርያቱን ከሳንሄድሪን ሸንጎ አዳራሽ ለጥቂት ጊዜ እንዲያስወጧቸው ካደረገ በኋላ እነዚህን ተቃዋሚ ሃይማኖተኞች እንዲህ ሲል መከራቸው:- “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። . . . አሁንም እላችኋለሁ:- ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፣ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።”​—⁠ሥራ 5:​33-39

በእኛ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም

16. ይሖዋ ለሕዝቡ የሰጠውን ዋስትና በራስህ አባባል እንዴት ትገልጸዋለህ?

16 ገማልያል የሰጠው ምክር ግሩም ነበር። ዛሬም አንዳንዶች ስለ እኛ ሆነው የሚናገሩትን ነገር እናደንቃለን። እንዲሁም ፍትሐዊ ዳኞች ያሳለፏቸው የፍርድ ቤት ውሳኔዎች የአምልኮ ነፃነታችን እንዲከበር እንዳደረጉ እንገነዘባለን። እርግጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶችና ትምህርቶች በጥብቅ መከተላችን ለሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትም ሆነ ለሌሎቹ የታላቂቱ ባቢሎን ሃይማኖታዊ መሪዎች አይዋጥላቸውም። (ራእይ 18:​1-3) እነዚህም ሰዎች ሆኑ እነርሱ ተጽዕኖ ያደረጉባቸው ወገኖች ምንም ቢቃወሙን የሚከተለው ዋስትና ተሰጥቶናል:- “በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም፤ በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፣ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው፣ ይላል እግዚአብሔር።”​—⁠ኢሳይያስ 54:​17

17. ተቃዋሚዎች ቢዋጉንም እንኳ ደፋሮች የሆንነው ለምንድን ነው?

17 ጠላቶቻችን ያለ ምክንያት ይቃወሙናል። ሆኖም ተስፋ አንቆርጥም። (መዝሙር 109:​1-3) የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክታችንን የሚጠሉ ሰዎች አስፈራርተው እምነታችንን እንዲያስክዱን በፍጹም አንፈቅድላቸውም። መንፈሳዊ ውጊያችን ይበልጥ እንደሚፋፋም የምንጠብቅ ቢሆንም መጨረሻው ምን እንደሆነ እናውቃለን። ልክ እንደ ኤርምያስ “ከአንተ ጋር ይዋጋሉ፣ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ድል አይነሡህም” የሚሉት ትንቢታዊ ቃላት ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ እንመለከታለን። (ኤርምያስ 1:​19) አዎን፣ ከአምላክ ጋር የሚዋጉ እንደማያሸንፉ እናውቃለን!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “በናዚ የጭቆና ቀንበር ሥር ታማኝነትና ድፍረት ማሳየት” የሚለውን በገጽ 24-28 ላይ የሚገኘውን ርዕስ ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የይሖዋ አገልጋዮች ጥቃት ሲደርስባቸው የኖረው ለምንድን ነው?

• ተቃዋሚዎች ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ሲዋጉ የኖሩት በምን መንገዶች ነው?

• ከአምላክ ጋር የሚዋጉ እንደማያሸንፉ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ከእርሱ ጋር እንደሚሆን ኤርምያስ ማረጋገጫ ተሰጥቶት ነበር

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከማጎሪያ ካምፖች የተረፉ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተነሣ የሕዝብ ዓመፅ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጄ ኤፍ ራዘርፎርድና ባልደረቦቹ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአምላክ ጋር የሚዋጉ ሰዎች በኢየሱስ ላይ በሰነዘሩት ጥቃት አላሸነፉም