በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለዓመፀኞች ያለህ አመለካከት ከአምላክ አመለካከት ጋር ይስማማልን?

ለዓመፀኞች ያለህ አመለካከት ከአምላክ አመለካከት ጋር ይስማማልን?

ለዓመፀኞች ያለህ አመለካከት ከአምላክ አመለካከት ጋር ይስማማልን?

ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጥንካሬና ጀግንነት ያሳዩ ኃያላን ሰዎችን ከጥንት ጀምሮ ሲያደንቁና ሲያከብሩ ኖረዋል። እንዲህ ከመሳሰሉት ሰዎች መካከል አንዱ በአፈ ታሪክ የሚነገርለት የጥንት ግሪክ ጀግና ሄራክለስ ወይም በሮማውያን ዘንድ እንደሚታወቀው ሄርኩለስ ነው።

ሄራክለስ የጀግኖች ጀግናና የኃያላን ኃያል የሚል ታላቅ ዝና አትርፏል። በአፈ ታሪኩ መሠረት ሄራክለስ የግሪክ አምላክ የሆነው የዙስ ሰብዓዊ እናት ከሆነችው ከአልከሚኒ የወለደው ኃያል ሰው ነው። ሄራክለስ ጀብዱ መሥራት የጀመረው ገና ሕፃን ሳለ ነው። በቅናት ያረረች አንዲት እንስት አምላክ ልትገድለው ሁለት ትልልቅ እባቦች በላከችበት ጊዜ ሄራክለስ እባቦቹን አንቆ ገደላቸው። በቀሪ ሕይወቱ ተዋግቷል፣ ጭራቆችን ድል አድርጓል እንዲሁም ጓደኛውን ለማዳን ሲል ከሞት ጋር ታግሏል። ከዚህም በተጨማሪ ከተሞችን አጥፍቷል፣ ሴቶችን አስገድዶ ደፍሯል፣ አንድን ልጅ ከማማ ላይ ወርውሮ ፈጥፍጧል፤ እንዲሁም የገዛ ሚስቱንና ልጁን ገድሏል።

ሄራክለስ በእውን የነበረ ሰው ባይሆንም እንኳ በግሪካውያን ዘንድ በሚታወቁ ጥንታዊ ቦታዎች ይነገሩ በነበሩ ታሪኮች ሁሉ ሲጠቀስ ኖሯል። ሮማውያን እንደ አምላክ አድርገው አምልከውታል፤ ነገዴዎችና መንገደኞች እንዲያበለጽጋቸውና ከአደጋ እንዲጠብቃቸው ወደ እሱ ጸልየዋል። የፈጸማቸው ጀብዱዎች ለብዙ ሺህ ዓመታት ሰዎችን ሲያስገርሙ ኖረዋል።

የአፈ ታሪኩ አመጣጥ

ስለ ሄራክለስ የሚነገሩ ታሪኮችም ሆኑ ገድል ፈጽመዋል ስለሚባሉ ሌሎች ሰዎች የሚነገሩ አፈ ታሪኮች መነሻ የሆናቸው እውነታ አለን? ሊኖራቸው ይችል ይሆናል። በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ አካባቢ “አማልክት” እና “አምላክ አከል” ሰዎች በምድር ላይ የተመላለሱበት ጊዜ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።

ሙሴ ስለዚያ ዘመን ሲገልጽ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንዲህም ሆነ ሰዎች በምድር ላይ መብዛት በጀመሩ ጊዜ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ።”​—⁠ዘፍጥረት 6:​1, 2

እነዚህ “የእግዚአብሔር ልጆች” ሰዎች ሳይሆኑ መላእክታዊ የአምላክ ልጆች ነበሩ። (ከ⁠ኢዮብ 1:​6፤ 2:​1፤ 38:​4, 7 ጋር አወዳድር።) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ይሁዳ ‘መኖሪያቸውን የተዉና የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁ’ አንዳንድ መላእክት እንዳሉ ገልጿል። (ይሁዳ 6) በሌላ አነጋገር ምድር ላይ ካሉ ውብ ሴቶች ጋር ለመኖር ሲሉ በአምላክ ሰማያዊ ድርጅት ውስጥ የነበራቸውን ቦታ ተዉ ማለት ነው። እነዚህ ዓመፀኛ መላእክት ‘ዝሙትን ያደርጉ ከነበሩትና ሌላን ሥጋ ከተከተሉት’ በሰዶምና ገሞራ ከነበሩ ሰዎች ጋር እንደሚመሳሰሉ ይሁዳ አክሎ ገልጿል።​—⁠ይሁዳ 7

መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ዓመፀኛ መላእክት ያደረጓቸውን ነገሮች በሙሉ አይገልጽም። ይሁን እንጂ በግሪክም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚነገሩ ጥንታዊ አፈ ታሪኮች ወንድና ሴት አማልክት በሚታይም ሆነ በማይታይ ሁኔታ በሰዎች መካከል ይኖሩ እንደነበር ይገልጻሉ። ሰብዓዊ አካል ሲለብሱ ውብ ነበሩ። እነዚህ ሰብዓዊ አካል የለበሱ መላእክት ይበሉና ይጠጡ፣ ይተኙ እንዲሁም እርስ በእርሳቸውና ከሰዎች ጋር የጾታ ግንኙነት ይፈጽሙ ነበር። ቅዱስና ያለመሞት ባሕርይ የተላበሱ ቢሆኑም ይዋሻሉ፣ ያታልላሉ፣ ይጣላሉ፣ ይደባደባሉ፣ ሴቶችን አማልለው የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ያደርጋሉ እንዲሁም አስገድደው ይደፍራሉ። ከላይ የተጠቀሰውን የመሰሉ አፈ ታሪኮች ተቀባብተውና ተጣምመው ይቅረቡ እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰውን ከጥፋት ውኃ በፊት የሆነውን ሁኔታ የሚገልጹ ሊሆኑ ይችላሉ።

በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሰዎች

ሥጋ የለበሱት ዓመፀኛ መላእክት ከሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት የፈጸሙ ሲሆን ሴቶቹም ልጆችን ወለዱ። የተወለዱት ልጆች የተለዩ ነበሩ። ከመላእክትና ከሰው የተዳቀሉት እነዚህ ልጆች ኔፊሊሞች ነበሩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚከተለው ይላል:- “በእነዚያም ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው፤ እነርሱም በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ።”​—⁠ዘፍጥረት 6:​4

“ኔፊሊም” የሚለው የዕብራይስጡ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “የሚዘርሩ” ማለትም እያነሱ የሚያፈርጡ ማለት ነው። ስለሆነም የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ “ምድርም ግፍን ተሞላች” ሲል ጨምሮ መናገሩ አያስገርምም። (ዘፍጥረት 6:​11) ሄራክለስንና ባቢሎናዊውን ጀግና ጊልጋሜሽን ስለመሳሰሉት አምላክ አከል ሰዎች የሚነገረው አፈ ታሪክ ከኔፊሊም ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል።

ኔፊሊሞች “ስማቸው የታወቀ” እና “ኃያላን” መባላቸውን ልብ በል። ኔፊሊሞች በዚያው ዘመን ይኖር እንደነበረው እንደ ጻድቁ ኖኅ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ የማድረግ ፍላጎት አልነበራቸውም። ዋነኛ ፍላጎታቸው ለራሳቸው ክብርና ዝናን ማትረፍ ነበር። የኃይል እርምጃ በመውሰድና ደም በማፍሰስ የፈጸሟቸው ጀብዱዎች በዙሪያቸው ከነበረው አምላክ የለሽ ዓለም የቋመጡለትን ዝና አስገኝተውላቸዋል። በማንም በምንም የማይበገሩ በጣም የሚፈሩና የሚከበሩ የዘመኑ ጀብደኞች ነበሩ።

ኔፊሊሞችና ወራዳ የሆኑት መላእክታዊ አባቶቻቸው በዘመኑ በነበሩት ሰዎች ፊት ዝና አትርፈው ይሆናል፤ በአምላክ ዓይን ግን ዝና ያተረፉ እንዳልነበሩ ግልጽ ነው። አኗኗራቸው እጅግ አስጸያፊ ነበር። በመሆኑም አምላክ በእነዚህ ወራዳ መላእክት ላይ እርምጃ ወሰደ። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ከፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው፣ ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ [አ]ወረደ።”​—⁠2 ጴጥሮስ 2:​4, 5

ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በወረደ ጊዜ ዓመፀኞቹ መላእክት ሥጋዊ አካላቸውን በመተው በውርደት ወደ መንፈሳዊው ዓለም ተመለሱ። አምላክ መልሰው ሰብዓዊ አካል የመልበስ ችሎታቸውን በመንሳት ቀጣቸው። ከማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር የላቀ ኃይል የነበራቸው የእነዚህ ዓመፀኛ መላእክት ልጆች ማለትም ኔፊሊሞች በሙሉ ጠፉ። ከጥፋት ውኃው የተረፉት ኖኅና አነስተኛ የሆነው ቤተሰቡ ብቻ ነበር።

በዛሬው ጊዜ እንደ ጀብደኛ ተደርገው የሚታዩ ሰዎች

ዛሬ አማልክትና አምላክ አከል ፍጡራን በምድር ላይ አይመላለሱም። ይሁን እንጂ ዓመፅ ከመጠን በላይ ተስፋፍቷል። በዛሬው ጊዜ ያሉ እንደ ጀብደኛ ተደርገው የሚታዩ ሰዎች በመጻሕፍት፣ በፊልሞች፣ በቴሌቪዥንና በሙዚቃ ይሞገሳሉ። ጠላታቸውን ለመውደድ፣ ሰላምን ለመሻት፣ ይቅር ለማለት ወይም ከኃይል ድርጊት ለመራቅ ሲባል ሌላኛውን ጉንጭ ማዞር በእነሱ ዘንድ ጨርሶ የማይታሰብ ነው። (ማቴዎስ 5:​39, 44፤ ሮሜ 12:​17፤ ኤፌሶን 4:​32፤ 1 ጴጥሮስ 3:​11) በአንጻሩ ግን ዛሬ ያሉት ኃያላን ሰዎች በጥንካሬያቸው፣ በድብድብ ችሎታቸው፣ በሚወስዱት የበቀል እርምጃና ዓመፅን በከፋ ዓመፅ በመመለሳቸው ይሞካሻሉ። a

አምላክ ለእንዲህ ዓይነት ሰዎች ያለው አመለካከት በኖኅ ዘመን ከነበረው አመለካከት አልተለወጠም። ይሖዋ ዓመፅ ወዳዶችን አያደንቅም፤ በሚፈጽሙት ጀብዱም አይደሰትም። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ጻድቅንና ኀጥእን ይመረምራል፤ ዓመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቶአል” ሲል ዘምሯል።​—⁠መዝሙር 11:​5

ለየት ያለ ጥንካሬ

ኃያላን ከሆኑ የዓመፅ ሰዎች ፈጽሞ የተለየና እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ዝነኛ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም ሰው ነበር። ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ “ግፍን አላደረገም።” (ኢሳይያስ 53:​9) በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ሳለ ጠላቶቹ ሊይዙት በመጡበት ጊዜ የእሱ ተከታዮች ሰይፍ ነበራቸው። (ሉቃስ 22:​38, 47-51) ለአይሁዶች አልፎ እንዳይሰጥ ለመከላከል መዋጋት ይችሉ ነበር።​—⁠ዮሐንስ 18:​36

እንዲያውም ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ እንዳይያዝ ለመከላከል ሰይፉን መዝዞ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ” ሲል ተናግሮታል። (ማቴዎስ 26:​51, 52) የሰው ልጅ ታሪክ በተደጋጋሚ እንዳረጋገጠው የኃይል እርምጃ መውሰድ የሚያስከትለው አጸፋ ተመሳሳይ ነው። ኢየሱስ ቢፈልግ ኖሮ ከጦር መሣሪያ ይልቅ ሌላ ራሱን የሚከላከልበት ዘዴ ነበረው። ቀጥሎ ለጴጥሮስ እንዲህ አለው:- “አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን?”​—⁠ማቴዎስ 26:​53

ኢየሱስ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ወይም መላእክታዊ ጥበቃ እንዲደረግለት ከመጠየቅ ይልቅ ለሚገድሉት ሰዎች ራሱን አሳልፎ ሰጠ። ለምን? አንዱ ምክንያት የሰማይ አባቱ ከምድር ላይ ክፋትን የሚያስወግድበት ጊዜ ገና እንደሆነ ያውቅ ስለነበረ ነው። ኢየሱስ ነገሮችን በራሱ መንገድ ለመወጣት ከመሞከር ይልቅ ሙሉ በሙሉ ትምክህቱን በይሖዋ ላይ ጥሏል።

ይህ ደካማነት ሳይሆን ትልቅ ውስጣዊ ጥንካሬን የሚያሳይ ነው። ኢየሱስ፣ ይሖዋ በራሱ ጊዜና መንገድ ነገሮችን እንደሚያስተካክል ጠንካራ እምነት እንዳለው አሳይቷል። ኢየሱስ ባሳየው ታዛዥነት ከራሱ ከይሖዋ ቀጥሎ ያለውን ከፍተኛ ሥልጣን እንዲይዝ ተደርጓል። ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስን በተመለከተ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፣ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።”​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​8-11

አምላክ ዓመፅን ለማስወገድ የገባው ቃል

እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሕይወታቸው መመሪያ አድርገው የሚጠቀሙት የኢየሱስን ምሳሌና ትምህርቶች ነው። የዚህን ዓለም ዝነኛና ዓመፀኛ ሰዎች አያደንቁም ምሳሌያቸውንም አይኮርጁም። በኖኅ ዘመን የነበሩ ክፉዎች እንደጠፉ ሁሉ ዛሬ ያሉ እንዲህ ዓይነት ሰዎችም አምላክ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምድር ገጽ ተጠራርገው እንደሚጠፉ ያውቃሉ።

አምላክ የምድርና የሰው ዘር ፈጣሪ ነው። ሉዓላዊ የመሆን መብት ያለው እሱ ነው። (ራእይ 4:​11) አንድ ሰብዓዊ ዳኛ እንኳ ብይን የመስጠት መብት ካለው፣ አምላክ እንዲህ ለማድረግ የበለጠ ሥልጣን ይኖረዋል። ጻድቅ ለሆኑት መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ያለው አክብሮት እንዲሁም እሱን ለሚወዱት ሰዎች ያለው ፍቅር ክፋትንና ክፉ አድራጊዎችን ጠራርጎ እንዲያጠፋ ግድ ይለዋል።​—⁠ማቴዎስ 13:​41, 42፤ ሉቃስ 17:​26-30

ይህም በፍትሕና በጽድቅ ጽኑ ሆኖ የተመሠረተ ዘላቂ ሰላም በምድር ላይ እንዲሰፍን ያደርጋል። ይህም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚናገር አንድ ታዋቂ ትንቢት ላይ አስቀድሞ ተነግሯል። “ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል።”​—⁠ኢሳይያስ 9:​6, 7

ስለዚህ ክርስቲያኖች ከረጅም ጊዜ በፊት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የሚከተለውን ምክር ልብ ማለታቸው ተገቢ ነው:- “በግፈኛ ሰው አትቅና፣ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ። ጠማማ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነውና፤ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው።”​—⁠ምሳሌ 3:​31, 32.

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በቪዲዮ ጨዋታዎችና በሳይንሳዊ ልብ ወለድ ፊልሞች ላይ የሚቀርቡት ባለ ታሪኮች በአብዛኛው እነዚህን የዓመፀኝነት ባሕርያት የሚያንጸባርቁ ናቸው።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ዛሬ ያሉ ኃያላን ሰዎች በጥንካሬያቸውና ዓመፅን በከፋ ዓመፅ በመመለስ ችሎታቸው ይሞካሻሉ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Alinari/Art Resource, NY