በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማጽናኛ በጣም አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ!

ማጽናኛ በጣም አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ!

ማጽናኛ በጣም አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ!

“እነሆም፣ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፣ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም።”​—⁠መክብብ 4:​1

ማጽናኛ ማግኘት ትፈልጋለህ? ያጠላብህን የተስፋ መቁረጥ ደመና ለመግፈፍ የሚያስችሉ ጥቂት የማጽናኛ ቃላት መስማት ትፈልጋለህ? በከባድ ሥቃይና በመጥፎ ገጠመኞች የተበላሸውን ሕይወትህን የሚጠግን ትንሽ ማጽናኛ ለማግኘት ትጓጓለህ?

ሁላችንም ማጽናኛና ማበረታቻ ማግኘት የሚያስፈልገን ወቅት አለ። ይህ የሆነው በሕይወታችን ሃዘን ሊያስከትሉ የሚችሉ በርካታ ችግሮች ስለሚከሰቱ ነው። ሁላችንም መጠጊያ፣ ሞቅ ያለ ስሜትና ፍቅር ማግኘት እንፈልጋለን። አንዳንዶቻችን በዕድሜ የገፋን መሆናችን ቅር ያሰኘናል። ሌሎች ደግሞ ሕይወታቸውን እንዳሰቡት መምራት ባለመቻላቸው ለብስጭት ተዳርገዋል። ሌሎች ደግሞ ባደረጉት የጤና ምርመራ ውጤቶች ቅስማቸው ተሰብሯል።

ከዚህም በላይ በጊዜያችን ያሉት ሁኔታዎች ማጽናኛና ተስፋ የማግኘትን አስፈላጊነት አንገብጋቢ እንዳደረጉት ብዙዎች የሚስማሙበት ነገር ነው። ባለፈው መቶ ዘመን ብቻ ከመቶ ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች በጦርነት አልቀዋል። a ሁሉም ለማለት ይቻላል ቤተሰቦቻቸውን ማለትም እናቶቻቸውንና አባቶቻቸውን፣ እህቶቻቸውንና ወንድሞቻቸውን፣ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን በከፍተኛ ሃዘን ላይ ጥለው ያለፉ ሲሆን ሁሉም ከፍተኛ ማጽናኛ የሚያሻቸው ሆነዋል። ዛሬ ከአንድ ቢልዮን የሚበልጡ ሰዎች በከፋ የድህነት ማጥ ውስጥ ይገኛሉ። ግማሹ የዓለም ሕዝብ ሕክምናና መሠረታዊ የሆኑ መድኃኒቶች በቀላሉ አያገኝም። አሳዳጊ ያጡ ልጆች በተበከሉ ትልልቅ ከተሞች ጎዳናዎች ላይ ሲቅበዘበዙ ይታያሉ። ብዙዎቹም ሱስ የሚያሲዙ አደገኛ መድኃኒቶችን የሚወስዱና ዝሙት አዳሪዎች ናቸው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች አስከፊ በሆኑ ካምፖች ውስጥ ይማቅቃሉ።

ይሁን እንጂ አኃዝ የሰዎችን ትኩረት ሊስብ የሚችል ቢሆንም አንዳንዶች በግል ሕይወታቸው የደረሰባቸውን ሥቃይና መከራ አያሳይም። ለምሳሌ ያህል በድሃ ቤተሰብ ውስጥ የተወለደችውንና በባልካን የምትኖረውን ስቬትላና የተባለች ወጣት ሁኔታ ተመልከት። b እንዲህ ትላለች:- “ለምኜ ወይም ሰርቄ ገንዘብ እንዳመጣ ወላጆቼ ይልኩኝ ነበር። የቤተሰቤ አኗኗር በጣም የተበላሽ ከመሆኑ የተነሳ አንዱ የቅርብ ዘመዴ ወሲባዊ ጥቃት ፈጽሞብኛል። በቡና ቤት ውስጥ የአስተናጋጅነት ሥራ አገኘሁ። ያገኘሁትን ገንዘብ በሙሉ የምሰጠው ለእናቴ ሲሆን ሥራውን ብለቅ ራሷን የምትገድል መሆኗን ነገረችኝ። ይህ ሁሉ ተደራርቦ የዝሙት አዳሪነት ሕይወት ውስጥ እንድገባ አደረገኝ። ይህ ሁሉ ሲሆን ገና የ13 ዓመት ልጅ ነበርኩ። ከጊዜ በኋላ አረገዝኩና ፅንሱን አስወረድኩ። የ15 ዓመት ልጅ ሳለሁ ለሚያየኝ ሰው ሁሉ የ30 ዓመት ሴት ነበር የምመስለው።”

በላትቪያ የሚኖረው ላይመንስ ማጽናኛ ማግኘት ያስፈለገው ለምን እንደሆነና ጭንቀት ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ነገር ምን እንደነበረ መለስ ብሎ በማስታወስ ተናግሯል። በ29 ዓመቱ የመኪና አደጋ ደረሰበትና ከወገቡ በታች ሽባ ሆነ። እጅግ ተስፋ ስለቆረጠ የአልኮል መጠጥ መጠጣት ጀመረ። ከአምስት ዓመት በኋላ የወደፊቱ ተስፋው ሁሉ የጨለመበት የለየለት የአልኮል ሱሰኛ ሆነ። ማጽናኛ ከየት ሊያገኝ ይችላል?

ወይም አንጂ የገጠማትን ሁኔታ ተመልከት። ባሏ ሦስት ጊዜ የጭንቅላት ቀዶ ሕክምና የተደረገለት ሲሆን የመጀመሪያው ቀዶ ሕክምና ግማሽ አካሉን ሽባ አድርጎት ነበር። ከዚያም የመጨረሻው ቀዶ ሕክምና ከተደረገለት ከአምስት ዓመት በኋላ ለሞት ሊዳርግ የሚችል ከባድ አደጋ ደረሰበት። ሚስቱ ወደ ድንገተኛ ክፍል ስትገባ ባለቤቷ በጭንቅላቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ራሱን ስቶ ተኝቶ በተመለከተችው ጊዜ አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚጠብቃት ታወቃት። በእርሷና በቤተሰቧ የወደፊት ሕይወት ላይ ሊደርስ የሚችለው ችግር ወለል ብሎ ታያት። ድጋፍና ማበረታቻ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

ፓት ከጥቂት ዓመታት በፊት በቀዝቃዛው የክረምት ወቅት አንድ ቀን ጠዋት የነበራት ስሜት ከወትሮው የተለየ አልነበረም። ይሁን እንጂ በቀጣዮቹ ሦስት ቀናት የሆነውን ሁሉ አታውቅም። ከጊዜ በኋላ ባለቤቷ እንደነገራት ደረቷ ላይ ከፍተኛ ሕመም ከተሰማት በኋላ ልቧ መምታቱን አቆመ። ልቧ ከተለመደው የልብ አመታት ሥርዓት ለየት ባለ መንገድ በከፍተኛ ፍጥነት መምታት ጀመረና ወዲያው ደግሞ ጸጥ አለ። መተንፈስ አቆመች። “የሞትኩኝ ያህል ነበር” ትላለች ፓት። የሆነ ሆኖ ከሞት ተረፈች። በሐኪም ቤት ስለቆየችባቸው ረዥም ጊዜያት ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “በርካታ ምርመራዎች ያደርጉልኝ በነበረ ጊዜ በተለይ ደግሞ መጀመሪያ ላይ ተከስቶ እንደነበረው ልቤ በከፍተኛ ፍጥነት እንዲመታና ምቱን እንዲያቆም ለማድረግ በሚሞክሩበት ጊዜ ከፍተኛ ፍርሃት አድሮብኝ ነበር።” ወሳኝ በሆነው በዚህ ወቅት የሚያስፈልጋትን ማጽናኛና እፎይታ ሊሰጣት የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

ጆ እና ሪቤካ የ19 ዓመት ልጃቸው በደረሰበት የመኪና አደጋ ሞተ። “እንደዚህ አድርጎ ከፍተኛ ሃዘን ውስጥ የከተተን ነገር አጋጥሞን አያውቅም” በማለት ይናገራሉ። “ከዚህ ቀደም የሚወዱትን ሰው በሞት ካጡ ሰዎች ጋር አብረን ያዘንን ቢሆንም እንኳ እንደ አሁኑ ልባችን በከፍተኛ ሃዘን የተመታበት ወቅት የለም።” የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን “ከፍተኛ ሃዘን” ለማስታገስ የሚችል ነገር ይኖር ይሆን?

እነዚህም ሆኑ ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተወዳዳሪ የሌለው የማጽናኛ ምንጭ አግኝተዋል። አንተም ከዚህ የማጽናኛ ምንጭ መጠቀም የምትችለው እንዴት እንደሆነ መረዳት ትችል ዘንድ እባክህ የጀመርከውን ንባብ ሳታቋርጥ ማንበብህን ቀጥል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የሞቱት ወታደሮችና ሲቪሎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በትክክል አይታወቅም። ለምሳሌ ያህል በ1998 የታተመው ፋክትስ አባውት ዚ አሜሪካን ዎርስ የተባለው መጽሐፍ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት በማስመልከት ሲናገር “በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት 50 ሚልዮን የሚያክሉ (ወታደሮችና ሰላማዊ ሰዎች) እንደሞቱ አብዛኞቹ ምንጮች ይገልጻሉ። ሆኖም ጉዳዩን በቅርብ ያጠኑ በርካታ ምንጮች ትክክለኛው አኃዝ ከፍተኛ እንደሆነና ከዚህ ቁጥር በእጥፍ እንደሚበልጥ ያምናሉ።”

b ስሟ ተቀይሯል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

UNITED NATIONS/PHOTO BY J. K. ISAAC

UN PHOTO 146150 BY O. MONSEN