ታስታውሳለህን?
ታስታውሳለህን?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተጠቅመሃልን? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ለማስታወስ ሞክር:-
• የገና በዓል በኮርያ በቀላሉ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደረገው ነገር ምንድን ነው?
በኮርያም ሆነ በአንዳንድ አገሮች በታኅሣሥ ወር በጭስ ማውጫው በኩል እንደሚገባና ስጦታዎች እንደሚያመጣ ስለሚታሰብ ስለ አንድ የማዕድ ቤት አምላክ የሚነገር የቆየ እምነት ነበር። በተጨማሪም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካ ወታደሮች በአገሪቱ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ስጦታና እርዳታ ያከፋፍሉ ነበር።—12/15 ገጽ 4, 5
• በኢሳይያስ 21:8 ፍጻሜ መሠረት አምላክ በጊዜያችን የሾመው “ጠባቂ” ማን ነው?
የጠባቂ ክፍል ሆነው የሚያገለግሉት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መፈጸሙን የሚያሳዩ የዓለም ሁኔታዎች ምን ትርጉም እንዳላቸው ለሰዎች አሳውቀዋል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ መሠረተ ትምህርቶችንና ተግባሮችን ለይተው እንዲያውቁና እንዲያስወግዱ ረድተዋቸዋል።—1/1 ገጽ 8, 9
• “የፖላንድ ወንድማማቾች” እነማን ናቸው?
በ16ኛውና በ17ኛው መቶ ዘመን በፖላንድ የነበሩ አናሳ ሃይማኖታዊ ቡድን ሲሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን በጥብቅ መከተልን ያበረታቱ ስለነበር እንደ ሥላሴ፣ የሕፃናት ጥምቀትና እሳታማ ሲኦል የመሳሰሉትን ቤተ ክርስቲያን የምትከተላቸውን መሠረተ ትምህርቶች አይቀበሉም ነበር። ከጊዜ በኋላ ከባድ ስደት የደረሰባቸው ከመሆኑም በላይ ወደ ሌሎች አገሮች ለመሰደድም ተገድደዋል።—1/1 ገጽ 21-3
• ፊውቸረሎጂስትስ እየተባሉ የሚጠሩ የማኅበራዊ ሕይወት ሳይንቲስቶች ወይም ኮከብ ቆጣሪዎች ከሚሰጧቸው ትንበያዎች ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እምነት የሚጣልባቸው የሆኑት ለምንድን ነው?
ነቢይ ተብዬዎች ለይሖዋና ለመጽሐፍ ቅዱስ ምንም ትኩረት ስለማይሰጡ እምነት የሚጣልባቸው ሆነው አለመገኘታቸውን አሳይተዋል። አንዳንድ ክስተቶች አምላክ ለሰዎች ካለው ዓላማ ጋር እንዴት እንደሚስማሙ እንድታውቅ በመርዳት ለራስህም ሆነ ለቤተሰብህ ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ብቻ ነው።—1/15 ገጽ 3
• በመጨረሻው ቀን እንደምንኖር የሚያረጋግጡ አንዳንድ አሳማኝ ማስረጃዎች ምንድን ናቸው?
ሰይጣን ከሰማይ መባረሩ ያስከተለውን ውጤት መመልከት እንችላለን። (ራእይ 12:9) የምንኖረው በራእይ 17:9-11 ላይ የተጠቀሰው የመጨረሻው “ንጉሥ” ሕልውና ባገኘበት ዘመን ውስጥ ነው። ምንም እንኳ ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ አንዳንዶቹ ገና እዚሁ ምድር ላይ እንደሚሆኑ ከሁኔታዎች መረዳት ቢቻልም የታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቁጥር እየቀነሰ በመሄድ ላይ ነው።—1/15 ገጽ 12, 13
• የዕንባቆም መጽሐፍ የተጻፈው መቼ ነው? እኛስ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው?
ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በ628 ከዘአበ ገደማ ነበር። ይሖዋ ጥንት በነበሩት በይሁዳና በባቢሎን ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ ይዟል። በተጨማሪም አሁን ባለው ክፉ ሥርዓት ላይ በቅርቡ የሚመጣውን መለኮታዊ ፍርድ ይናገራል።—2/1 ገጽ 8
• አንዲት እናት ልባም ለሆኑ ሚስቶች የሰጠችውን ጥበብ ያዘለ ምክር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኘው የት ቦታ ላይ ነው?
የምሳሌ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ማለትም ምዕራፍ 31 እንዲህ ዓይነት ምክር የሚገኝበት ግሩም ምንጭ ነው።—2/1 ገጽ 30, 31
• ይሖዋ ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ማወቅ የምንችልበትን አጋጣሚ ስለሰጠን አመስጋኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (1 ቆሮንቶስ 2:16 NW)
ይሖዋ በወንጌሎች ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው ታሪክ አማካኝነት የኢየሱስን አስተሳሰብ፣ ስሜት፣ ያከናወናቸውንና ቅድሚያ የሰጣቸውን ነገሮች እንድናውቅ አስችሎናል። ይህ በተለይ ሕይወት አድን ለሆነው የስብከት ሥራ በምንሰጠው ትኩረት ረገድ ይበልጥ ኢየሱስን እንድንመስል ሊረዳን ይችላል።—2/15 ገጽ 25
• በዛሬው ጊዜ አምላክ ለጸሎት መልስ ይሰጣልን?
አዎን። ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሚቀርብለት ጸሎት ሁሉ መልስ እንደሚሰጥ ባይናገርም የጋብቻ ችግሮችን መፍታትን ለመሳሰሉ ጉዳዮች መጽናኛ እና እርዳታ ለማግኘት ለሚጸልዩ ሰዎች በተደጋጋሚ መልስ መስጠቱን በዘመናችን የተፈጸሙ ተሞክሮዎች ያረጋግጣሉ።—3/1 ገጽ 3-7
• አምላክ የሚሰጠውን ብርታት ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን?
ብርታት እንዲሰጠን በጸሎት መጠየቅ፣ መንፈሳዊ ጥንካሬ ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም እና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አማካኝነት ማበረታቻ ማግኘት እንችላለን።—3/1 ገጽ 15, 16
• ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የተሻለ ጥቅም እንዲያገኙ ወላጆች ልጆቻቸውን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?
ምናልባት አስቀድሞ ጥቂት እንዲተኙ በማድረግ በንቃት እንዲከታተሉ ልጆቻቸውን መርዳት ይችላሉ። ልጆች የሚያውቁት ቃል ወይም ስም በተጠቀሰ ቁጥር በአንድ ወረቀት ላይ ምልክት መጻፍን የመሳሰለ ነገር በማድረግ “ማስታወሻ” እንዲይዙ ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይችላል።—3/15 ገጽ 17, 18
• ኢዮብ ከተወልን ምሳሌ የምንማራቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
ኢዮብ ከአምላክ ጋር የነበረውን ዝምድና በአንደኛ ደረጃ አስቀምጧል፤ እንደ እሱ ካሉ ሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት አድልዎ አላሳየም፤ ለትዳር ጓደኛው ታማኝ ለመሆን ጥሯል፤ ለቤተሰቡም መንፈሳዊነት ትኩረት ሰጥቷል እንዲሁም ፈተና ሲያጋጥመው በታማኝነት ጸንቷል።—3/15 ገጽ 25-7
• በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሥጢር ጽሑፍ የተቀመጠ መልእክት አለን?
የለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ የሚባለውን ዓይነት የምሥጢር ጽሑፍ በሌሎች መጻሕፍት ውስጥም ማግኘት ይቻላል። በዕብራይስጥ ጽሑፎች ቅጂ መካከል ያለው የፊደል ልዩነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ የሚባለውን የምሥጢር ጽሕፈት ትርጉም የሚያሳጣ ነው።—4/1 ገጽ 30, 31