በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አዲሱ ዓለም—አንተም በዚያ ትገኝ ይሆን?

አዲሱ ዓለም—አንተም በዚያ ትገኝ ይሆን?

አዲሱ ዓለም​—⁠አንተም በዚያ ትገኝ ይሆን?

“ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።”​—⁠መክብብ 3:​12, 13

1. ስለ ወደፊቱ ጊዜ ጥሩ አመለካከት ሊኖረን የሚችለው ለምንድን ነው?

 ብዙ ሰዎች ሁሉን የሚችለው አምላክ ፈጽሞ የማያፈናፍን እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ሆኖም ከላይ ያለው ጥቅስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃል ውስጥ የሚገኝ እውነት ነው። ‘ደስተኛ አምላክ’ መሆኑና የመጀመሪያ ወላጆቻችንን በምድራዊ ገነት ላይ ማስቀመጡ ከዚህ ጥቅስ አባባል ጋር የሚስማማ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:​11 NW፤ ዘፍጥረት 2:​7-9) አምላክ ለሕዝቦቹ ቃል ስለገባው ስለ ወደፊቱ ጊዜ በጥልቀት ለመረዳት በምንጥርበት ወቅት ዘላለማዊ ደስታ የሚያስገኝ ሁኔታ እንደሚመጣ ማወቃችን አያስገርመንም።

2. በጉጉት የምትጠባበቃቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

2 በቀደመው ርዕሰ ትምህርት ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ትንቢት ከተናገረባቸው አራት ቦታዎች መካከል ሦስቱን ተመልክተናል። (ኢሳይያስ 65:​17) ከእነዚህ አስተማማኝ ትንቢቶች መካከል አንዱ የተመዘገበው በራእይ 21:​1 ላይ ነው። ቀጥለው ያሉት ቁጥሮች ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በምድር ላይ ያሉትን ሁኔታዎች በተሻለ መንገድ እንደሚለውጣቸው ይነግሩናል። በሐዘን ምክንያት የሚፈስሱ እንባዎችን ያብሳል። በዕድሜ መግፋት፣ በበሽታ ወይም በአደጋ ምክንያት የሚሞት ሰው አይኖርም። ሐዘን፣ ለቅሶና ሥቃይ ይወገዳሉ። እንዴት አስደሳች ተስፋ ነው! ይሁን እንጂ ይህ እንደሚመጣ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን? ይህ ተስፋ በአሁኑ ጊዜ በምንኖረው ላይ ሊያሳድረው የሚችለው ተጽእኖስ ምንድን ነው?

እርግጠኞች እንድንሆን የሚያደርጉን ምክንያቶች

3. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰጠውን ተስፋ ማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

3 ራእይ 21:​5 በመቀጠል ምን እንደሚል ልብ በል። በሰማያዊ ዙፋኑ ላይ የተቀመጠው አምላክ “እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” እንዳለ ይገልጻል። ይህ መለኮታዊ የተስፋ ቃል ከማንኛውም የብሔራዊ ነፃነት አዋጅ፣ ከማንኛውም የዘመናችን የሰብዓዊ መብቶች ማስከበሪያ አዋጅ ወይም ከማንኛውም የሰዎች የወደፊት ጊዜ ምኞት የላቀ ነው። ይህ የተስፋ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሊዋሽ አይችልም’ ብሎ የሚናገርለት አምላክ የተናገረው የማይሻር አዋጅ ነው። (ቲቶ 1:​2) በዚህ አስደሳች ተስፋ መርካትና በአምላክ መታመን ብቻውን በቂ እንደሆነ አድርገህ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከዚህ የበለጠ ማድረግም ያስፈልጋል። ወደፊት ስለሚጠብቀን ሁኔታ የምንማረው ተጨማሪ ነገር አለ።

4, 5. የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድንጠባበቅ የሚያደርጉ ምን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መርምረናል?

4 ቀደም ባለው ርዕሰ ትምህርት ላይ የተጠቀሱትን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የሰጠውን ተስፋ እውነተኝነት የሚያረጋግጡ ነጥቦች መለስ ብለን እናስብ። ኢሳይያስ እንዲህ ዓይነት አዲስ ሥርዓት እንደሚመጣ የተናገረው ትንቢት አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው በተመለሱና እውነተኛውን አምልኮ መልሰው ባቋቋሙ ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ዕዝራ 1:​1-3፤ 2:​1, 2፤ 3:​12, 13) ይሁን እንጂ የኢሳይያስ ትንቢት በዚሁ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ነውን? በፍጹም አይደለም! ኢሳይያስ የተነበያቸው ነገሮች ከረጅም ጊዜ በኋላም በላቀ ሁኔታ የሚፈጸሙ ናቸው። እንዲህ ብለን የምንደመድመው ለምንድን ነው? 2 ጴጥሮስ 3:​13 እና ራእይ 21:​1-5 ላይ ባለው ሐሳብ መሠረት ነው። እነዚህ ጥቅሶች ክርስቲያኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሚ ስለሚሆኑባቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የሚገልጹ ናቸው።

5 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” የሚለውን ሀረግ አራት ጊዜ ይጠቀማል። ከእነዚህ መካከል ሦስቱን የተመለከትን ሲሆን አበረታች መደምደሚያ ላይም ደርሰናል። አምላክ ክፋትና መከራ የሚያስከትሉ ሌሎች ነገሮችን እንደሚያጠፋና ቃል በገባው አዲስ ሥርዓት ውስጥ የሰው ዘሮችን እንደሚባርክ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይተነብያል።

6. ስለ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” የሚጠቅሰው አራተኛው ትንቢት የሚተነብየው ምንድን ነው?

6 አሁን በ⁠ኢሳይያስ 66:​22-24 ላይ የሚገኘውን “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” የሚለው ሐረግ የተጠቀሰበትን አራተኛውን ቦታ እንመርምር። “እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ከፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፣ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፣ ይላል እግዚአብሔር። እንዲህ ይሆናል፤ በየመባቻውና በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በፊቴ ይሰግድ ዘንድ ዘወትር ይመጣል፣ ይላል እግዚአብሔር። ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትምና፣ እሳታቸውም አይጠፋምና፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ።”

7. ኢሳይያስ 66:​22-24 በመጪዎቹ ጊዜያት ፍጻሜውን ያገኛል ብለን የምንደመድመው ለምንድን ነው?

7 ይህ ትንቢት ወደ ትውልድ አገራቸው በተመለሱት አይሁዳውያን ላይ ይሠራ የነበረ ቢሆንም ሌላም ፍጻሜ ያለው ነው። የጴጥሮስ ሁለተኛ መልእክትና የራእይ መጽሐፍ ወደ ፊት ስለሚመጣ ‘አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ የሚናገሩ በመሆናቸው ይህ የሚከናወነው እነዚህ መጻሕፍት ከተጻፉበት ዘመን ብዙ ቆይቶ መሆን ይኖርበታል። በአዲሱ ሥርዓት ታላቅና የተሟላ ፍጻሜውን ያገኛል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። ወደፊት ይፈጸማሉ ብለን ልንጠብቃቸው ከምንችላቸው ሁኔታዎች መካከል አንዳንዶቹን እንመርምር።

8, 9. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች “ጸንተው ይኖራሉ” የተባለላቸው ከምን አንጻር ነው? (ለ) የይሖዋ አገልጋዮች “በየመባቻውና በየሰንበቱ” ያመልካሉ የሚለው ትንቢት ያዘለው ትርጉም ምንድን ነው?

8 ራእይ 21:​4 ሞት እንደማይኖር ያመለክታል። ኢሳይያስ ምዕራፍ 66 ላይ የሚገኘው ምንባብም ከዚህ ጋር ይስማማል። አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚኖሩ እንደማይሆኑ ከኢሳ 66 ቁጥር 22 ላይ ማየት እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ሕዝቦቹ በፊት “ጸንተው ይኖራሉ።” አምላክ ለመረጣቸው ሕዝቦቹ ያደረጋቸው ነገሮች ለዚህ ማረጋገጫ ሊሆኑን ይችላሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖች ከባድ ስደት ደርሶባቸዋል። እነርሱን ከምድር ገጽ ፈጽሞ ለማጥፋት ብዙ ጥረት ተደርጓል። (ዮሐንስ 16:​2፤ ሥራ 8:​1) እንደ ሮማዊው አፄ ኔሮና እንደ አዶልፍ ሂትለር ያሉት ኃያላን የአምላክ ሕዝብ ጠላቶች እንኳን የይሖዋን ስም የተሸከሙትን የአምላክን ታማኞች ለማጥፋት አልቻሉም። ይሖዋ የሕዝቦቹን ጉባኤ እስከ አሁን ድረስ ጠብቆ አቆይቷል፤ ወደፊትም ለዘላለም ጠብቆ እንደሚያኖር እርግጠኞች ነን።

9 በተመሳሳይም የአዲሱ ምድር አባሎች የሆኑት የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ማለትም በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖሩት የእውነተኛ አምላኪዎች ማኅበር አባላት፣ ሁሉን ነገር ለፈጠረው አምላክ ንጹሕ አምልኮ ስለሚያቀርቡ በግለሰብ ደረጃ ጸንተው ይቆማሉ። ይህ አምልኮ አልፎ አልፎ ወይም ሲመች ብቻ የሚከናወን አይሆንም። በሙሴ በኩል ለእስራኤል ሕዝብ የተሰጠው የአምላክ ሕግ በየወሩ አዲስ ጨረቃ በታየ ቁጥር፣ እንዲሁም በየሳምንቱ በሰንበት ቀን መፈጸም የሚገባው የአምልኮ ሥርዓት እንዳለ ይደነግግ ነበር። (ዘሌዋውያን 24:​5-9፤ ዘኁልቁ 10:​10፤ 28:​9, 10፤ 2 ዜና መዋዕል 2:​4) ስለዚህ ኢሳይያስ 66:​23 የእውነተኛው አምላክ አምልኮ ከሳምንት እስከ ሳምንት፣ ከወር እስከ ወር ዘወትር በቋሚነት እንደሚከናወን ያሳያል። አምላክ የለሽነትና ሃይማኖታዊ ግብዝነት በዚያ ጊዜ አይኖርም። ‘ሥጋ ለባሽ ሁሉ በይሖዋ ፊት ይሰግድ ዘንድ ይመጣል።’

10. ክፉ ሰዎች አዲሱን ዓለም እንደማያውኩት እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?

10 ኢሳይያስ 66:​24 በአዲሱ ምድር የሚሰፍነው ሰላምና ጽድቅ ፈጽሞ እንደማይደፈርስ ያረጋግጥልናል። ክፉ ሰዎች ፈጽመው አያበላሹትም። 2 ጴጥሮስ 3:​7 ከፊ​ታችን ‘አምላካዊ አክብሮት የሌላቸው ሰዎች የሚጠፉበት የፍርድ ቀን’ እንደሚጠብቀን የሚናገር መሆኑን አስታውስ። በሚመጣው የጥፋት ቀን የሚወገዱት አምላካዊ አክብሮት የሌላቸው ናቸው። ከወታደሮች ይልቅ ብዙ ሲቪሎች በሚገ​ደሉባቸው ሰብዓዊ ጦርነቶች ላይ እንደሚደርሰው ንጹሐን በሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርስ ጉዳት አይኖርም። ከዚህ ይልቅ ታላቁ ፈራጅ በእርሱ ቀን የሚጠፉት አምላካዊ አክብሮት የሌላቸው እንደሚሆኑ ዋስትና ይሰጠናል።

11. ኢሳይያስ ለአምላክና ለአምልኮው ጀርባቸውን የሚሰጡ ሰዎች የወደፊት እጣቸው ምን እንደሚሆን አመልክቷል?

11 ከጥፋቱ በሕይወት የሚያልፉት ጻድቃን የአምላክ ትንቢታዊ ቃል እውነት መሆኑን ያመለክታሉ። ቁጥር 24 ‘በይሖዋ ላይ ያመፁ ሰዎች ሬሳ ለፍርዱ በማስረጃነት እንደሚታይ ይተነብያል። ኢሳይያስ የተጠቀመበት ሥዕላዊ መግለጫ የሚዘገንን ይመስል ይሆናል። ሆኖም ይህ ከአንድ ታሪካዊ ሐቅ ጋር የሚስማማ ነው። ከኢየሩሳሌም ቅጥር ውጭ ቆሻሻና አንዳንድ ጊዜም ክብር ያለው ቀብር ሊያገኙ የማይገባቸው ወንጀለኞች ሬሳ የሚጣልበት የቆሻሻ መጣያ ቦታ ነበር። a በዚያ የሚጣለው ቆሻሻም ሆነ የወንጀለኞቹ አስከሬን ብዙ ሳይቆይ በእሳትና በትል ተበልቶ ያልቃል። ኢሳይያስ ሕግ በሚተላለፉ ላይ የሚመጣው የይሖዋ ፍርድ የማያዳግምና የመጨረሻ መሆኑን ለመግለጽ ሲል ይህን ሁኔታ በምሳሌነት ተጠቅሟል።

ይሖዋ የገባቸው ተስፋዎች

12. ኢሳይያስ በአዲሱ ዓለም የሚኖረውን ሕይወት በተመለከተ ምን ተጨማሪ መግለጫ ይሰጣል?

12 ራእይ 21:​4 በሚመጣው አዲስ ሥርዓት የማይኖሩ ነገሮችን ይነግረናል። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ የሚኖሩት ነገሮች ምንድን ናቸው? በዚያን ጊዜ ሕይወት ምን ይመስላል? ይህን ልናውቅ የምንችልበት አስተማማኝ ምንጭ ይኖር ይሆን? አዎን። የይሖዋን ሞገስ አግኝተን እርሱ በሚፈጥራቸው በእነዚህ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ላይ የመኖር አጋጣሚ ብናገኝ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደምንኖር ኢሳይያስ ምዕራፍ 65 በትንቢታዊ መልክ ይገልጽልናል። በአዲሱ ምድር ውስጥ ዘላቂ ቦታ አግኝተው የሚባረኩ ሁሉ አርጅተው አይሞቱም። ኢሳይያስ 65:​20 የሚከተለውን ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፣ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጎልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፣ [“ጎልማሳው መቶ ዓመት ቢሆነውም ገና ሕፃን እያለ ይሞታል፣” NW ] ኃጢአተኛውም የመቶ ዓመት ሆኖት የተረገመ ይሆናልና።”

13. ኢሳይያስ 65:​20 የአምላክ ሕዝቦች የሚያገኙትን ደህንነት የሚያረጋግጥልን እንዴት ነው?

13 ይህ ትንቢት በመጀመሪያ በኢሳይያስ ሕዝብ ላይ በተፈጸመበት ጊዜ በምድሪቱ የሚኖሩ ሕፃናት የሚያሰጋቸው ነገር እንደማይኖር የሚያመለክት ነበር። በአንድ ወቅት ባቢሎናውያን እንዳደረጉት ገና በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎችን የሚያስግዝ ወይም በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶችን የሚገድል ጠላት አይመጣባቸውም። (2 ዜና መዋዕል 36:​17, 20) በሚመጣው አዲስ ዓለምም ሰዎች የሚያስፈራቸውና የሚያሰጋቸው ነገር ሳይኖር በደስታ ለመኖር ይችላሉ። በአምላክ ላይ ለማመፅ የሚመርጥ ሰው ቢኖር በሕይወት እንዲኖር አይፈቀድለትም። ይሖዋ ያስወግደዋል። ኃጢአት ለመሥራት የመረጠው ሰው የመቶ ዓመት ዕድሜ ቢኖረውስ? ለዘላለም ከመኖር ጋር ሲነጻጸር ‘ገና ሕፃን’ ሳለ ይሞታል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 1:​19, 20፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:​16-19

14, 15. በ⁠ኢሳይያስ 65:​21, 22 መሠረት ምን አርኪ የሆነ ሥራ ልትጠባበቅ ትችላለህ?

14 ኢሳይያስ ሆን ብሎ ኃጢአት የሚሠራ ሰው እንዴት እንደሚወገድ በመግለጹ ላይ ከማተኮር ይልቅ በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖረው የኑሮ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ይገልጻል። በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንደምትኖር አድርገህ አስብ። በመጀመሪያ በዓይነ ሕሊናህ የሚመጣው በመኖሪያህ ማለትም በቤትህ አካባቢ የሚኖረው ሁኔታ ነው። ኢሳይያስ በኢሳ 65 ቁጥር 21 እና 22 ላይ የሚገልጸው ይህንን ነው:- “ቤቶችንም ይሠራሉ፣ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፣ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና።”

15 ቤት የመሥራት ወይም አትክልት የመንከባከብ ተሞክሮ ካልነበረህ የኢሳይያስ ትንቢት የትምህርት ጊዜ እንደሚጠብቅህ ያመለክታል። ይሁን እንጂ ችሎታና ተሞክሮ ያላቸው አስተማሪዎች ምናልባትም ጎረቤቶችህ በሚሰጡህ እገዛ ለመማር ፈቃደኛ ትሆናለህ? ኢሳይያስ በሞቃታማ አካባቢ በነፋሻው አየር ለመደሰት እንድትችል ቤትህ ሰፋፊ ክፍት መስኮቶችና መጋረጃዎች እንደሚኖሩት ወይም የወቅቶችን መፈራረቅ ለመመልከት የሚያስችልህ ዝግ የመሥተዋት መስኮቶች እንደሚኖሩት አይናገርም። ለመሥራት የምትፈልገው ቤት ዝናብና በረዶ ቁልቁል ለማውረድ የሚያስችል ሰያፍ ጣሪያ ያለው ነው? ወይስ በመካከለኛው ምሥራቅ እንደሚገኙት ቤቶች ከቤተሰብህ ጋር ሰብሰብ ብለህ ምግብ የምትገባበዝበትና የምትጨዋወትበት ጠፍጣፋ ጣሪያ መሥራት የሚያስፈልገው የአየር ሁኔታ ይኖር ይሆን?​—⁠ዘዳግም 22:​8፤ ነህምያ 8:​16

16. አዲሱ ዓለም ዘላቂ እርካታ ያስገኛል ብለህ መጠበቅ የምትችለው ለምንድን ነው?

16 እንደነዚህ የመሰሉትን ዝርዝር ጉዳዮች ከማወቅ ይበልጥ የሚያስፈልገው የራስህ መኖሪያ ቤት እንደሚኖርህ ማወቁ ነው። ብዙ ደክመህ ከሠራህ በኋላ ሌላው ሰው ተጠቃሚ እንደሚሆንበት እንዳሁኑ ጊዜ አይሆንም። በተጨማሪም ኢሳይያስ 65:​21 እንደምትተክልና ፍሬውንም እንደምትበላ ይናገራል። መላው ሁኔታ በዚህ ቃል እንደተጠቃለለ ግልጽ ነው። በራስህ ሥራ ማለትም በድካምህ ፍሬ ከፍተኛ እርካታ ታገኛለህ። “እንደ ዛፍ ዕድሜ” ረጅም በሆነው የሕይወት ዘመን ይህን ማከናወን ትችላለህ። በእርግጥም እንዲህ ያለው ሁኔታ ‘ሁሉ አዲስ ይሆናል’ ከሚለው መግለጫ ጋር የሚስማማ ነው!​—⁠መዝሙር 92:​12-14

17. ወላጆች በተለይ አበረታች ሆኖ የሚያገኙት የትኛው ተስፋ ነው?

17 ወላጅ ከሆንክ የሚከተሉት ቃላት ልብህን ይነኩታል:- “እነርሱ ከነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ብሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም [“ለሁከት፣” NW ] አይወልዱም። እንዲህም ይሆናል፤ ሳይጠሩ እመልስላቸዋለሁ፣ ገናም ሲናገሩ እሰማለሁ።” (ኢሳይያስ 65:​23, 24) ‘ለሁከት መውለድ’ የሚያስከትለውን ሐዘን ቀምሰኸዋል? ወላጆችንም ሆነ ሌሎችን የሚያውኩትን በልጆች ላይ የሚደርሱ ችግሮች በሙሉ መዘርዘር አያስፈልገንም። በተጨማሪም ሁላችንም በሥራቸው፣ በግል ጉዳዮቻቸው፣ ወይም የራሳቸውን ተድላ በማሳደድ ተጠምደው ለልጆቻቸው በቂ ጊዜ ወይም ትኩረት ያልሰጡ ወላጆችንም ተመልክተናል። ይሖዋ ከእነዚህ ወላጆች በተለየ መንገድ እንደሚሰማን እንዲያውም ከመናገራችን አስቀድሞ ምላሽ እንደሚሰጠን ማረጋገጫ ሰጥቶናል።

18. በአዲሱ ዓለም በእንስሶች እደሰታለሁ ብለህ ልትጠብቅ የምትችለው ለምንድን ነው?

18 በአዲሱ ዓለም ምን ነገሮች እንደምታገኝ በምታስብበት ጊዜ የአምላክ ትንቢታዊ ቃል የሚገልጸውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። “ተኩላና ጠቦት በአንድነት ይሰማራሉ፣ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል፣ የእባብም መብል ትቢያ ይሆናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ አይጎዱም፣ አያጠፉምም፣ ይላል እግዚአብሔር።” (ኢሳይያስ 65:​25) የሥነ ጥበብ ሰዎች ይህን ትዕይንት በሥዕል ለማስቀመጥ ሞክረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ሠዓሊ እንደመሰለው የሳለው የሥነ ጥበብ ሥራ አይደለም። በገሃድ የሚፈጸም ትዕይንት ነው። የሰው ልጅ እርስ በርሱም ሆነ ከእንስሳት ጋር ሰላም ይኖረዋል። ባሁኑ ጊዜ ብዙ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎችና እንስሳት ወዳዶች አብዛኛውን እድሜያቸውን ሲያጠኑ ቆይተው የሚያውቁት ስለ ጥቂት ዓይነት እንስሳት ወይም ስለ አንድ ንዑስ ዝርያ ብቻ ነው። እንስሳት ሰዎችን ዓይተው በማይደነብሩበት ጊዜ ግን ምን ያህል ለመማርና ለማወቅ እንደምትችል ገምት። በዚህ ጊዜ ወፎችንና ጥቅጥቅ ባለ ደን የሚኖሩ ትናንሽ ፍጥረታትን ሳይቀር ተጠግተህ ለመመልከትና እንደልብህ ዓይተህ ለመደሰት ትችላለህ። (ኢዮብ 12:​7-9) ከሰው ወይም ከእንስሳት ጉዳት ይደርስብኛል የሚል አንዳችም ስጋት አይኖርብህም። ይሖዋ “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ አይጎዱም፣ አያጠፉምም” በማለት ይናጋራል። ይህ ሁሉ ዛሬ ከምናየውና ከሚያጋጥመን ምንኛ የተለየ ይሆናል!

19, 20. የአምላክ ሕዝቦች በአሁኑ ጊዜ ካሉት ከአብዛኞቹ ሰዎች የተለዩ የሆኑት ለምንድን ነው?

19 ቀደም ሲል እንደተገለጸው አዲሱን ሺህ ዓመት በተመለከተ ብዙዎችን የሚያሳስቡ ጉዳዮች ቢኖሩም የሰው ልጆች ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል ሊተነብዩ አይችሉም። ይህ ደግሞ ብዙዎችን ለብስጭት፣ ለግራ መጋባት ወይም ለተስፋ መቁረጥ ዳርጓቸዋል። የካናዳ ዩኒቨርሲቲ ዲሬክተር የሆኑት ፒተር ኤምበርሊ ብዙ ሰዎች “እኔ ማን ነኝ? እንዲህ የምደክመው ምን ለማግኘት ነው? ለመጪው ትውልድ የማስተላልፈው ነገር ምንድን ነው? ከሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ጋር ተፋጥጠዋል። በዕድሜያቸው አጋማሽ ላይ ሕይወታቸውን ሥርዓታማ በሆነና ትርጉም ባለው መንገድ ለመምራት ይታገላሉ” ሲሉ ጽፈዋል።

20 የብዙዎቹ ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል የሆነበትን ምክንያት መረዳት አያስቸግርህም። በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ወይም አስደሳች በሆኑ መዝናኛዎች ሕይወታቸውን ለማስደሰት ይፈልጉ ይሆናል። ሆኖም የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደያዘላቸው ስለማያውቁ ሕይወት ትርጉም፣ ቁም ነገርና ዓላማ ያለው ሆኖ አይታያቸውም። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በተመለከትነው መሠረት አንተ ለሕይወት ያለህን አመለካከት እነዚህ ሰዎች ካላቸው አመለካከት ጋር አነጻጽር። ይሖዋ ቃል በገባልን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ውስጥ ዙሪያችንን ተመልክተን በሙሉ ልብ ‘በእርግጥም አምላክ ሁሉን አዲስ አድርጓል’ ለማለት የምንችል መሆኑን ተገንዝበናል። ምንኛ የሚያስደስት ነው!

21. ኢሳይያስ 65:​25 እና ኢሳይያስ 11:​9 ላይ ምን ተመሳሳይ የሆነ ሐሳብ እናገኛለን?

21 በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ እንደምንኖር አድርገን መመልከታችን ራሳችንን ማመጻደቃችን አይደለም። አምላክ ራሱ ባሁኑ ጊዜ በእውነት እንድናመልከውና “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ አይጎዱም፣ አያጠፉምም” ሲል ቃል በገባልን ዓለም የመኖር ብቃት እንድናገኝ ይጋብዘናል፤ አልፎ ተርፎም በጥብቅ ያሳስበናል። (ኢሳይያስ 65:​25) ኢሳይያስ ቀደም ሲል ተመሳሳይ መግለጫ ተጠቅሞ እንደነበርና በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለመኖር ወሳኝ የሆነውን ብቃት ጠቅሶ እንደነበረ አስተውለሃል? ኢሳይያስ 11:​9 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW ] በማወቅ ትሞላለችና።”

22. መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት አራት ትንቢቶች ላይ ያደረግነው ምርምር የትኛውን ውሳኔያችንን ሊያጠናክረው ይገባል?

22 ‘ይሖዋን ማወቅ።’ አዎን፣ አምላክ ሁሉን አዲስ በሚያደርግበት ጊዜ የምድር ነዋሪዎች ስለ አምላክና ስለ ፈቃዱ ትክክለኛ እውቀት ይኖራቸዋል። ይህ እውቀት ከእንስሳት አፈጣጠር ትምህርት ከመቅሰም የበለጠ ነገርን የሚያካትት ነው። በመንፈስ አነሳሽነት ያስጻፈው ቃሉ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ለምሳሌ ያህል ‘ስለ አዲስ ሰማይና ስለ አዲስ ምድር’ የሚጠቅሱትን አራት ትንቢቶች መመርመራችን ብቻ እንኳ ያስገኘልንን እውቀት አስብ። (ኢሳይያስ 65:​17፤ 66:​22፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13፤ ራእይ 21:​1) መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እንድታነብ የሚያደርግ ጥሩ ምክንያት አለህ። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብ ልማድ አለህ? ከሌለህ አምላክ ከተናገረው ውስጥ የተወሰነውን በየቀኑ ለማንበብ ትችል ዘንድ ማድረግ የምትችላቸው ማስተካከያዎች ይኖሩ ይሆን? አዲሱን ዓለም በጉጉት ከመጠባበቅ ባሻገር ልክ እንደ መዝሙራዊው በአሁኑ ጊዜም እንኳ ትልቅ ደስታ ታገኛለህ።​—⁠መዝሙር 1:​1, 2

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 906ን ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

ኢሳይያስ 66:​22-24 ወደፊት ስለሚሆን ነገር ይተነብያል ብለን ለመደምደም የምንችለው ለምንድን ነው?

በ⁠ኢሳይያስ 66:​22-24 እና በ⁠ኢሳይያስ 65:​20-25 ላይ ከሚገኙት ትንቢቶች መካከል በተለይ አንተ በጉጉት የምትጠባበቀው የትኛውን ነው?

የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድትጠባበቅ የሚያደርጉ ምን ምክንያቶች አሉህ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢሳይያስ፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ ‘የአዲሱን ሰማይና የአዲሱን ምድር’ ገጽታዎች ተንብየዋል