በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

ሦስቱ ወንጌሎች ኢየሱስ ውድ በሆነ ሽቱ መቀባቱን የተቃወሙ ሰዎች እንደነበሩ ይገልጻሉ። ይህን ተቃውሞ ያሰሙት ብዙ ሐዋርያት ናቸው ወይስ ይሁዳ ብቻ?

ይህንን አጋጣሚ በተመለከተ ማቴዎስ፣ ማርቆስና ዮሐንስ በወንጌሎቻቸው ውስጥ ዘግበው እናገኛለን። ተቃውሞ በማሰማት የመጀመሪያ የነበረው ይሁዳ ሆኖ ሌሎች ጥቂት ሐዋርያትም በሐሳቡ የተስማሙ ይመስላል። ይህ አራቱንም የወንጌል ዘገባዎች በማግኘታችን አመስጋኝ መሆን የሚኖርብን ለምን እንደሆነ የሚጠቁም አጋጣሚ ነው። እያንዳንዱ ጸሐፊ ያሰፈረው ነገር ትክክል ቢሆንም ሁሉም አንድ ዓይነት ዝርዝር ጉዳዮችን ጽፈዋል ማለት አይደለም። ተመሳሳይ የሆኑ ዘገባዎችን በማወዳደር ስለ ብዙዎቹ ክንውኖች ይበልጥ የተሟላና ዝርዝር መረጃ እናገኛለን።

በ⁠ማቴዎስ 26:​6-13 ላይ የተገለጸው ዘገባ ቦታው በቢታንያ የሚገኘው የለምጻሙ የስምዖን ቤት መሆኑን ቢገልጽልንም ያንን ውድ ሽቱ በኢየሱስ ራስ ላይ ያፈሰሰችውን ሴት ስም አይጠቅስም። ማቴዎስ ‘ደቀ መዛሙርቱ ይህን አይተው እንደ ተቆጡና’ ሽቱው ተሽጦ ገንዘቡ ለድሆች ሊሰጥ ይችል እንደ ነበር መናገራቸውን ገልጿል።

የማርቆስ ዘገባ ደግሞ ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹን ዝርዝሮች ይዟል። ሆኖም ብልቃጡን ሰብራ እንደከፈተችው ጨምሮ ገልጿል። ከሕንድ ይመጡ የነበሩትን ዓይነት “ጥሩ ናርዶስ” ሽቱ የያዘ ብልቃጥ ነበር። የተነሳውን ተቃውሞ በተመለከተ ማርቆስ ሲገልጽ “አንዳንዶችም . . . ይቆጡ ነበር” እንዲሁም “እርስዋንም ነቀፉአት” ሲል ዘግቧል። (ማርቆስ 14:​3-9፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በመሆኑም ተቃውሞ ያሰሙት ሐዋርያት ከአንድ በላይ እንደሆኑ ሁለቱ ዘገባዎች ያሳያሉ። ይሁንና ተቃውሞው የጀመረው እንዴት ነው?

የዓይን ምሥክር የነበረው ዮሐንስ በጣም ተስማሚ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን ጠቅሷል። ሴትየዋ የማርታና የአልዓዛር እህት የሆነችው ማርያም መሆኗን ገልጿል። በተጨማሪም ዮሐንስ “የኢየሱስን እግር ቀባች፤ በጠጉርዋም እግሩን አበሰች” በማለት ሌላውን ዘገባ እንደሚቃረን ሳይሆን እንደሚደግፍ ተደርጎ ሊታይ የሚችለውን ጉዳይ ጠቅሷል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ዘገባዎቹን አጣምረን ስንመለከታቸው ዮሐንስ ጭምር ‘ጥሩ ናርዶስ’ እንደሆነ የመሠከረለትን ሽቱ ማርያም በኢየሱስ ራስና እግር ላይ እንዳፈሰሰችው መገንዘብ እንችላለን። ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር በጣም ይቀራረብ ስለነበር ለእርሱ ይቆረቆር ነበር። እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ ሊሰጠው ያለው የስምዖን ልጅ የአስቆሮቱ ይሁዳ:- ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ­ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው? አለ።”​—⁠ዮሐንስ 12:​2-8

እርግጥ ይሁዳ “ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ” ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ቦታ የነበረው ሰው ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ማቀዱ ዮሐንስን ምን ያህል እንዳስቆጣው መገመት ትችላለህ። ተርጓሚው ዶክተር ሲ ሃወርድ ማተኒ ዮሐንስ 12:​4ን በተመለከተ የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝረዋል:- “‘አሳልፎ ሊሰጠው ያለው’ የሚለው አነጋገር ሊፈጸም ያለን ቀጣይ ድርጊት የሚያመለክት ነው። ይህ ደግሞ ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ መስጠቱ ድንገት የመጣለት ሐሳብ ሳይሆን ለበርካታ ቀናት ያሰበበትና አስቀድሞ ያቀደው ነገር መሆኑን ያረጋግጣል።” ይሁዳ የተቃወመበትን ምክንያት በተመለከተ “ሌባ ስለ ነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለ ነበረ ነው” በማለት ዮሐንስ ተጨማሪ ሐሳብ ጠቅሷል።

እንግዲያው ውድ የሆነው ሽቱ ተሽጦ ገንዘቡ ይሁዳ በሚይዘው ከረጢት ውስጥ ቢቀመጥ ኖሮ ይሁዳ ብዙ ገንዘብ መስረቅ ይችል ስለነበር ይህን ተቃውሞ የቆሰቆሰው ሌባ የነበረው ይሁዳ ነው ቢባል ምክንያታዊ ይሆናል። ይሁዳ ይህን ተቃውሞ ካስነሳ በኋላ ግን አንዳንድ ሐዋርያትም ትክክል በሚመስለው በዚህ ነጥብ በመስማማት አጉረምርመዋል። ይሁንና የተቃውሞው ዋነኛ ቆስቋሽ ይሁዳ ነበር።