ለአንድ መሠረታዊ ሥርዓት ሲል ሞተ
ለአንድ መሠረታዊ ሥርዓት ሲል ሞተ
በቀድሞው የዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በቅርቡ ለሕዝብ እይታ ይፋ በሆነ አንድ ሰሌዳ ላይ (እዚህ ላይ የሚታየው) የተቀረጸው ጽሑፍ ሲጀምር እንደሚከተለው ይላል:- “ኦጎስት ዲክማን (በ1910 ተወለደ) የተባለውን የይሖዋ ምሥክር ፈጽሞ አንዘነጋውም።” ይህ ሰሌዳ በአንድ የይሖዋ ምሥክር ስም ሊዘጋጅ የቻለው ለምንድን ነው? ጽሑፉ ታሪኩን ሲቀጥል “በኅሊናው ምክንያት አልዋጋም በማለቱ መስከረም 15, 1939 በኤስ ኤስ ወታደሮች ባደባባይ ተገደለ።”
ኦጎስት ዲክማን በዛክሰንሃውዘን የማጎሪያ ካምፕ የታሰረው በ1937 ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1939 ከጀመረ ከሦስት ቀን በኋላ በጦር ኃይሉ ውስጥ ለወታደራዊ አገልግሎት እንደተመለመለ የሚገልጸውን ቅጽ እንዲፈርም ታዘዘ። ፈቃደኛ ስላልሆነ የካምፑ አዛዥ የኤስ ኤስ ኃላፊ (ሹትስሽታፈል የሂትለር ልዩ ጠባቂ) ወደነበረው ወደ ሂንሪሽ ሂምለር በመሄድ ዲክማን በሁሉም የካምፑ እስረኞች ፊት እንዲገደል ፈቃድ ጠየቀ። ኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው መጽሔት መስከረም 17, 1939 ከጀርመን እንዲህ ሲል ዘግቦ ነበር:- “የ29 ዓመቱ ኦጎስት ዲክማን . . . በረሻኝ ጓድ አማካኝነት በጥይት ተደብድቦ ተገድሏል።” ጋዜጣው ዲክማን በኅሊናው ምክንያት አልዋጋም ያለ የመጀመሪያው ጀርመናዊ እንደሆነም ዘግቧል።
መስከረም 18, 1999 ከስልሳ ዓመት በኋላ በብራንደንበርግ መታሰቢያ ድርጅት አማካኝነት የዲክማን መታሰቢያ የተከበረ ሲሆን ጎብኚዎች ለመታሰቢያነት የተዘጋጀውን ይህን ሰሌዳ ሲመለከቱ ዲክማን ያሳየውን ድፍረትና የነበረውን ጠንካራ እምነት ያስታውሳቸዋል። በቀድሞው ማጎሪያ ካምፕ የውጭ ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ የሚታየውን ሌላ ሰሌዳ ጎብኚዎች ሲመለከቱ ከዲክማን ሌላ የይሖዋ ምሥክር በመሆናቸው ምክንያት በዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ ስቃይ የደረሰባቸው 900 የሚያክሉ ምሥክሮች እንደነበሩ ይገነዘባሉ። ከዚህ የበለጠ ቁጥር ያላቸው ምሥክሮች በሌሎች ካምፖች ውስጥ ታስረው ስቃይ ደርሶባቸዋል። አዎን፣ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ አስከፊ ስቃይ ቢደርስባቸውም ብዙዎቹ አምላክ ላወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ታማኞች ሆነዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች ‘በበላይ ላሉት የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች መገዛት’ ክርስቲያናዊ ግዴታቸው እንደሆነ ይገነዘባሉ። (ሮሜ 13:1) ይሁን እንጂ የአምላክን ሕግ እንዲተላለፉ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ሲያስገድዷቸው “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ያሉትን የክርስቶስን ሐዋርያት ምሳሌ ይከተላሉ። (ሥራ 5:29) በዚህ ምክንያት የጎሳና የዘር ጥላቻዎች ዘግናኝ የጭካኔ ድርጊቶችን እያስከተሉ ባለበት ዓለም ውስጥ በየትኛውም ስፍራ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ልክ እንደ ኦጎስት ዲክማን ሁሉ ሰላምን ይከታተላሉ። “ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥብቅ ምክር ይመራሉ።—ሮሜ 12:21