በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙስና ይህን ያህል የተስፋፋው ለምንድን ነው?

ሙስና ይህን ያህል የተስፋፋው ለምንድን ነው?

ሙስና ይህን ያህል የተስፋፋው ለምንድን ነው?

“ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ነገር እንዳያዩ ዐይናቸውን ስለሚያሳውርና የንጹሕ ሰዎችንም ፍርድ ስለሚያጣምም ጉቦ አትቀበል።”​—⁠ዘጸአት 23:​8 የ1980 ትርጉም

ከዛሬ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት በፊት የሙሴ ሕግ ጉቦ መቀበልን አውግዟል። ከዚያ በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት በርካታ ፀረ ሙስና ሕጎች ተረቅቀዋል። ያም ሆኖ ግን የተደነገጉት ሕጎች ሙስናን በመግታት ረገድ ስኬታማ ሊሆኑ አልቻሉም። በየቀኑ በሚልዮን የሚቆጠሩ ጉቦ የመስጠትና የመቀበል ወንጀሎች የሚፈጸሙ ሲሆን በዚህ ጦስ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይሠቃያሉ።

ሙስና እጅግ ከመስፋፋቱና በዓይነቱ በጣም እየረቀቀ ከመምጣቱ የተነሳ ኅብረተሰቡ የተገነባበትን መዋቅር እንዳያሽመደምድ ያሰጋል። በአንዳንድ አገሮች በእጅ ካልተሄደ ምንም ነገር ማስፈጸም አይቻልም ለማለት ያስደፍራል። ለተገቢው ሰው የሚሰጥ ጉቦ አንድ ሰው ፈተና እንዲያልፍ፣ መንጃ ፈቃድ እንዲያወጣ፣ ውል እንዲፈራረምና የፍርድ ቤት ክስ እንዲረታ ያስችለዋል። አርኖ ሞንትበር የተባሉ በፓሪስ የሚኖሩ አንድ ጠበቃ “ሙስና የሰዎችን መንፈስ እንደሚጫጫን መጠነ ሰፊ የአየር ብክለት ሊመሰል ይችላል” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።

በተለይ በንግዱ ዓለም ጉቦኝነት በእጅጉ ተስፋፍቶ ይገኛል። አንዳንድ ኩባንያዎች ከሚያገኙት ትርፍ ውስጥ አንድ ሦስተኛውን ምግባረ ብልሹ ለሆኑ የመንግሥት ቢሮክራቶች ጉቦ ለመስጠት ይመድባሉ። ዚ ኢኮኖሚስት የተባለው የብሪታኒያ መጽሔት እንደዘገበው በየዓመቱ ለዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ ንግድ ከሚውለው 25 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ 10 በመቶ የሚሆነው አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራት በጉቦ መልክ የሚሰጥ ነው። ሙስና እየተስፋፋ በሄደ መጠን የሚያስከትለው መዘዝም የዚያኑ ያህል አደገኛ ሆኗል። ባለፈው አሥርተ ዓመት “ክሮኒ” ካፒታሊዝም ተብሎ በሚታወቀው ሥርዓት ዘመድ ናቸው ለሚባሉ ጥቂት ሰዎች አድልዎ በማሳየት በተፈጸመ ሙስና ሳቢያ የተለያዩ አገሮች ኢኮኖሚ እንደተንኮታኮተ ይነገራል።

በሙስናም ሆነ ሙስና በሚያስከትለው የኢኮኖሚ ውድቀት በጣም የሚጎዱት የትኛውንም ሰው በጉቦ ለመደለል አቅሙ የሌላቸው ድሆች መሆናቸው የታወቀ ነው። ዚ ኢኮኖሚስት በአጭር አነጋገር እንዳስቀመጠው “ሙስና አንድ ዓይነት የጭቆና ዘርፍ ነው።” እንዲህ ዓይነቱ ጭቆና ሊወገድ ይችላልን? ወይስ ሙስና የትም ሊሸሹት የማይቻል ነገር ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ አንዳንዶቹን የሙስና መሠረታዊ መንስዔዎች ማወቅ አለብን።

የሙስና መንስዔዎች ምንድን ናቸው?

ሰዎች በሐቅ ከመሥራት ይልቅ ማጭበርበር የሚመርጡት ለምንድን ነው? አንዳንዶች የሚፈልጉትን ነገር ማግኘት የሚችሉበት አቋራጭ መንገድ ወይም ብቸኛው መንገድ በሙስና መሠማራት ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ጉቦ ከቅጣት ለማምለጥ የሚያስችል አመቺ መንገድ ያስገኝ ይሆናል። የፖለቲካ ሰዎች፣ ፖሊሶችና ዳኞች ሙስናን ችላ ብለው ሲያልፉ አልፎ ተርፎም እነሱ ራሳቸው ሙስና ሲፈጽሙ በማየታቸው ብቻ ብዙዎች የእነሱን አርአያ ይከተላሉ።

ሙስና በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ በሄደ መጠን የኋላ ኋላ በጣም የተለመደ ነገር እስከመሆን ድረስ ይበልጥ ተቀባይነት እያገኘ ይሄዳል። በጣም አነስተኛ ክፍያ የሚያገኙ ሰዎች ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ማሰብ ይጀምራሉ። ትንሽ ሻል ባለ ሁኔታ ኑሮአቸውን ለመደጎም ከፈለጉ ጉቦ መጠየቅ አለባቸው። እንዲሁም ጉቦ የሚቀበሉ ወይም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ጉቦ የሚሰጡ ሰዎች ሳይቀጡ ስለሚታለፉ ብዙዎች ሙስናን ለመዋጋት አይነሳሱም። ንጉሥ ሰሎሞን “በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይፈረድምና ስለዚህ በሰው ልጆች ውስጥ ልባቸው ክፉን ለመሥራት ጠነከረ” ሲል ተናግሯል።​—⁠መክብብ 8:​11

ሙስናን እንዲባባስ እያደረጉ ያሉ ሁለት ብርቱ ኃይሎች አሉ። እነዚህም ራስ ወዳድነትና ስግብግብነት ናቸው። ምግባረ ብልሹ የሆኑ ሰዎች ራስ ወዳድ ከመሆናቸው የተነሳ በሙስና መካፈላቸው በሌሎች ላይ የሚያመጣውን መከራ ችላ ብለው ያልፋሉ። እንዲሁም ከጉቦኝነት ጥቅም ስለሚያገኙ ብቻ ይህ ድርጊት ምንም ክፋት እንደሌለበት ለማስመሰል ይጥራሉ። በሙስና የተዘፈቁ ሰዎች ይበልጥ ቁሳዊ ነገሮች ባካበቱ መጠን ይበልጥ ስግብግብ እየሆኑ ይሄዳሉ። ሰሎሞን እንዲህ ብሏል:- “ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ባለጠግነትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም።” (መክብብ 5:​10) እርግጥ ስግብግብነት ገንዘብ የሚያስገኝ ቢሆንም በአንፃሩ ደግሞ ማንኛውንም ዓይነት ሙስናና ሕገ ወጥነት በጭፍን ያልፋል።

ችላ መባል የሌለበት ሌላው ነጥብ መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ዲያብሎስ ብሎ የሚጠራው በዓይን የማይታየው የዚህ ዓለም ገዥ የሚጫወተው ሚና ነው። (1 ዮሐንስ 5:​19፤ ራእይ 12:​9) ሰይጣን ሙስናን በከፍተኛ ሁኔታ ያስፋፋል። በታሪክ ዘመናት ሁሉ በከፍተኛነቱ አቻ ያልተገኘለት ሰይጣን ለክርስቶስ ያቀረበለት ጉቦ ነው። ‘ወድቀህ ብትሰግድልኝ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ እሰጥሃለሁ።’​—⁠ማቴዎስ 4:​8, 9

ሆኖም ኢየሱስ ምንም አቋሙን አላጎደፈም። ተከታዮቹም ተመሳሳይ አቋም እንዲይዙ አስተምሯቸዋል። በዛሬው ጊዜ የኢየሱስ ትምህርት ሙስናን ለመዋጋት የሚያስችል ውጤታማ መሣሪያ ሊሆን ይችላልን? ቀጥሎ ያለው ርዕስ ይህን ጥያቄ ይመረምራል።