በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ይሖዋን ማመስገን!
የሕይወት ታሪክ
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ይሖዋን ማመስገን!
ስታንሊ ኢ ሬይኖልድስ እንደተናገረው
በ1910 በለንደን እንግሊዝ ተወለድኩ። ወላጆቼ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዌስትባሪ ሌ ወደምትባል አነስተኛ የዊልትሻየር መንደር ተዛወሩ። ትንሽ ልጅ ሳለሁ ብዙ ጊዜ ‘አምላክ የሚባለው ማን ነው?’ ብዬ ራሴን እጠይቅ ነበር። ማንም ሊነግረኝ አልቻለም። አነስተኛ ሕዝብ ያለው የእኛ ዓይነቱ ማሕበረሰብ አምላክን ለማምለክ ለምን ሁለት የጸሎት ቤቶች እንዲሁም አንድ ቤተ ክርስቲያን እንዳስፈለገው ፍጹም ሊገባኝ አልቻለም።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ ከአራት ዓመት በፊት በ1935 እኔና ታናሽ ወንድሜ ዲክ የእረፍት ጊዜያችንን ለማሳለፍ በደቡባዊው የእንግሊዝ የባሕር ዳርቻ ወደሚገኝ ዌመዝ ወደሚባል ቦታ በብስክሌት ተጓዝን። በድንኳናችን ተቀምጠን የሚጥለውን ዶፍ ዝናብ እያዳመጥን ምን ማድረግ እንደምንችል እያሰብን ሳለ አንድ አረጋዊ መጥተው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ሦስት የእንግሊዝኛ መጽሐፎችን አበረከቱልኝ። እነዚህም የአምላክ በገና እና ብርሃን ጥራዝ አንድ እና ጥራዝ ሁለት ናቸው። ችክ ያለውን ዝናብ ለማስረሳት እንደሚረዱኝ በማሰብ መጽሐፎቹን በደስታ ተቀበልኩ። ባነበብኩት ነገር ወዲያውኑ የተመሰጥኩ ቢሆንም ይህ ነገር የእኔንም ሆነ የወንድሜን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ይለውጣል የሚል ሐሳብ አልነበረኝም።
ወደ ቤት ከተመለስኩ በኋላ እናቴ ካት ፓርሰንስ የምትባል አንዲት የመንደራችን ሴት ተመሳሳይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንዳሠራጨች ነገረችኝ። ሴትየዋ በዕድሜ የገፋች ብትሆንም እንኳ ተራርቀው ለሚኖሩት የመንደራችን ሰዎች ለመመሥከር አነስተኛ ሞተር ብስክሌት ስለምትጠቀም በብዙዎች ዘንድ ትታወቃለች። ላነጋግራት በሄድኩ ጊዜ ፍጥረት እና ሀብት የተባሉ የእንግሊዝኛ መጽሐፎችንና የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ያሳተማቸውን ሌሎች ጽሑፎችን በደስታ ሰጠችኝ። እንዲሁም የይሖዋ ምሥክር እንደሆነች ነገረችኝ።
መጽሐፎቹን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እያገናዘብኩ ካነበብኩ በኋላ ይሖዋ እውነተኛው አምላክ እንደሆነ ስለተረዳሁ እርሱን ማምለክ ፈለግሁ። ስለዚህ ለነበርኩበት ቤተ ክርስቲያን የመልቀቂያ ደብዳቤ ጻፍኩ፤ ከዚያም በጆንና አላስ ሙዲ ቤት በሚደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ መገኘት ጀመርኩ። እነርሱም የሚኖሩት ለእኛ በጣም ቅርብ በሆነችው በዌስትበሪ ከተማ ነበር። በስብሰባዎቹ ላይ የምንገኘው ሰባት ሰዎች ብቻ ነበርን። ከስብሰባ በፊትና በኋላ አብረን የመንግሥቱን መዝሙሮች ድምፃችንን ከፍ አድርገን ስንዘምር ካት ፓርሰንስ ደግሞ የሙዚቃ መሣሪያውን ትጫወትልን ነበር!
የመጀመሪያዎቹ ቀናት
በታሪካዊ ወቅት ላይ እንደምንኖር በመገንዘቤ በማቴዎስ 24:14 ላይ አስቀድሞ በተተነበየው የስብከት ሥራ ለመካፈል በጣም ጓጉቼ ነበር። ስለዚህ ሲጋራ ማጨስ አቆምኩ፣ ቦርሳ ገዛሁና ራሴን ለታላቁ አምላክ ለይሖዋ ወሰንኩ።
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ነሐሴ 1936 “አርማጌዶን” በሚል ርዕስ ንግግር ለማቅረብ ግላስጎው ስኮትላንድን ጎብኝቶ ነበር። ምንም እንኳን ግላስጎው እኛ ካለንበት 600 ኪሎ ሜትር ያክል ቢርቅም በዚያ ስብሰባ ላይ ለመገኘትና ለመጠመቅ ወስኜ ነበር። ያለኝ ገንዘብ በጣም አነስተኛ ስለነበር የስኮትላንድ የድንበር ከተማ እስከሆነችው ካርሊስሌ ድረስ ብስክሌቴን ጭኜ በባቡር ከሄድኩ በኋላ ወደ ሰሜን 160 ኪሎ ሜትር በብስክሌት ተጓዝኩ። ወደ ቤት ስመለስም አብዛኛውን መንገድ በብስክሌት የተጓዝኩ ሲሆን ሰውነቴ ቢዝልም በመንፈሣዊ ግን ብርታት አግኝቼ ነበር።
ከዚያ ወዲህ ቅርብ ባሉ መንደሮች ለሚኖሩ ሰዎች እምነቴን ለማካፈል በፈለግሁ ጊዜ ሁሉ በብስክሌት እጓዝ ነበር። በእነዚያ ጊዜያት እያንዳንዱ ምሥክር የቤቱ ባለቤት የሚያነበው ቅዱስ ጽሑፋዊ መልእክት የተጻፈባቸው የመመሥከሪያ ካርድ ይይዝ ነበር። በክር የተቀዱ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን ለማሰማት ተንቀሳቃሽ የሸክላ ማጫወቻዎችንም እንጠቀም ነበር። እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ለይቶ ያሳውቀን የነበረው የመጽሔት ቦርሳ a አይለየንም ነበር።
በጦርነት ጊዜ አቅኚ መሆን
ወንድሜ በ1940 ተጠመቀ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1939 ጀምሮ ስለነበር ሁለታችንም የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች በጣም እንደሚያስፈልጉ ተገነዘብን። በመሆኑም የአቅኚነት ማመልከቻ አስገባን። ከኢደዝ ፑል፣ በርት ፋርመር፣ ቶምና ዶውረዚ ብሪጅስ፣ በርናርድ ሆውተን እንዲሁም ከረጅም ጊዜ አንስቶ እምነታቸውን ስናደንቅ ከቆየናቸው ከሌሎች አቅኚዎች ጋር ብሪስቶል በሚገኘው የአቅኚዎች ቤት እንድንኖር አብረን በመመደባችን ሁለታችንም አመስጋኞች ነን።
ወዲያው ጎኑ ላይ በደማቅ ፊደላት “የይሖዋ ምሥክሮች” የሚል የተጻፈበት አነስተኛ የጭነት መኪና ሊወስደን መጣ። መኪናውን ይነዳ የነበረው ስታንሊ ጆንስ ከጊዜ በኋላ በቻይና ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን በስብከት እንቅስቃሴው ምክንያት ለሰባት ዓመታት ለብቻው ተገልሎ ታስሮ ነበር።
ጦርነቱ እየቀጠለ ሲመጣ ብዙውን ጊዜ ሙሉ ሌሊት አንተኛም ነበር። በአቅኚ ቤታችን አካባቢ ቦምቦች ይወድቁ ስለነበረ የእሳት አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች ለመከላከል ሳናቋርጥ ነቅተን እንጠብቃለን። አንድ ቀን ማታ 200 ምሥክሮች የተገኙበትን ትልቅ ስብሰባ ካደረግን በኋላ ሕዝብ የሚበዛበት የብሪስተልን እምብርት ለቅቀን የአየር መቃወሚያ ሲተኮስ የሚወጣው ፍንጥርጣሪ በላያችን እየዘነበብን በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ከአደጋ ነጻ ወደሆነው ስፍራ ሸሸን።
በማግሥቱ ጠዋት ዲክና እኔ የተውናቸውን አንዳንድ ዕቃዎች ለመውሰድ ወደ ከተማዋ ተመለስን። እዚያ ስንደርስ በተመለከትነው ነገር ክው ብለን ቀረን። ብሪስቶል ጨርሶ እንዳልነበረች ሆናለች። የከተማው እምብርት ሙሉ በሙሉ ጋይቷል። የመንግሥት አዳራሻችን የሚገኝበት የፓርክ ጎዳና የሚጨስ የፍርስራሽ ክምር ሆኖ ነበር። ነገር ግን የተገደለም ሆነ ጉዳት የደረሰበት ምሥክር አልነበረም። ደስ የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን ከመንግሥት አዳራሽ አውጥተን በጉባኤው አባላት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ አስቀምጠናቸው ነበር። ከምሥክሮች መካከል አንዱም ስላልሞተና ጽሑፎቻችንም ስላልተቃጠሉ ይሖዋን አመሰገንን።
ያልተጠበቀ ነፃነት
ለብሔራዊ ውትድርና መመልመሌን የሚገልጽ ደብዳቤ ሲደርሰኝ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኜ የማገለግልበት የብሪስቶል ጉባኤ አስፋፊዎች ቁጥር 64 ደርሶ ነበር። በገለልተኛ አቋማቸው ምክንያት ሌሎች ብዙ ምሥክሮች ስለ ታሰሩ የእኔም የመስበክ ነፃነት በአጭሩ እንደሚቀጭ ስጠብቅ ነበር። የተከሰስኩበት ጉዳይ በብሪስቶል ፍርድ ቤት ሲሰማ ቀድሞ የእስር ቤት ኃላፊ የነበረው ወንድም አንቶኒ ቡክ እኔን ወክሎ ተናገረ። ልበ ሙሉ፣ ደፋርና ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ቆራጥ አቋም የነበረው ይህ ሰው እኔን ወክሎ በጥሩ ሁኔታ ስለተናገረ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴን መቀጠል እንድችል ሳይታሰብ ከውትድርና አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ነጻ እንድሆን ተፈረደልኝ!
ከውትድርና አገልግሎት ነጻ በመሆኔ በጣም ተደሰትኩ፤ ስለዚህ የቻልኩትን ያህል በስፋት በመስበክ ያገኘሁትን ይህን ነጻነት ልጠቀምበት ወሰንኩ። በለንደን ቅርንጫፍ ቢሮ ተገኝቼ የቅርንጫፍ የበላይ ተመልካቹን አልበርት ዲ ሽሮደርን እንዳነጋግር መልእክት ሲደርሰኝ ለምን ይሆን ብዬ አስቤ ነበር። በየሳምንቱ አንድ ጉባኤ እየጎበኘሁ ወንድሞችን ለመረዳትና ለማበረታታት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ለማገልገል ወደ ዮርክሻየር እንድሄድ ስጋበዝ ምን እንደተሰማኝ ልትገምቱ ትችላላችሁ። ለዚህ ዓይነቱ ሥራ ፈጽሞ ብቃት እንደሌለኝ ተሰማኝ፤ ይሁን እንጂ ከውትድርና አገልግሎት ነጻ ለመሆን በመቻሌ እንዳልሄድ የሚያግደኝ ነገር አልነበረም። በዚህ ምክንያት የይሖዋን መመሪያ ተቀብዬ ለመሄድ ፈቃደኛ ሆንኩ።
አልበርት ሽሮደር በሁደርስፊልድ በተደረገው አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ከወንድሞች ጋር አስተዋወቀኝና ሚያዝያ 1941 አዲሱን ሥራዬን ቀጠልኩ። እነዚያን ተወዳጅ ወንድሞች በቅርብ ማወቅ ምንኛ አስደሳች ነው! ፍቅራቸውንና ደግነታቸውን ስመለከት ይሖዋ እርስ በርሳቸው የሚፋቀሩ ሙሉ በሙሉ ለእርሱ ያደሩ ሕዝቦች እንዳሉት ይበልጥ እንድገነዘብ አደረገኝ።—ዮሐንስ 13:35
ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶች
በ1941 በሌስተሩ ደ ሞንትፎርት አዳራሽ የማይረሳ የአምስት ቀን አገር አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ አደረግን።
ምግብ የሚከፋፈለው በራሽን ቢሆንም በአገር ውስጥ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ቢጣልም እንኳን እሁድ ቀን ከፍተኛው የተሰብሳቢዎች ቁጥር 12, 000 ደርሷል። በዚያን ጊዜ በጠቅላላ በአገሪቱ ውስጥ የነበሩት ምሥክሮች ቁጥር ከ11, 000 ትንሽ በለጥ የሚል ነበር። የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ንግግር የተቀዳባቸውን ክሮች ያዳመጥን ሲሆን ልጆች የተባለው አዲስ መጽሐፍ መውጣቱ በማስታወቂያ ተነገረ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተፋፋመበት በዚያ ጊዜ ያደረግነው ይህ የአውራጃ ስብሰባ በእርግጥም በእንግሊዝ የይሖዋ ምሥክሮች ቲኦክራሲያዊ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነበር።የአውራጃ ስብሰባውን ካደረግን በኋላ ብዙም ሳይቆይ በለንደን ቤቴል ውስጥ እንዳገለግል ተጋበዝኩ። እዚያም በዕቃ መላኪያና ማሸጊያ ክፍል በኋላም ከጉባኤ እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሚያከናውነው ቢሮ ሠርቻለሁ።
የቤቴል ቤተሰብ ለንደን ላይ የሚደረገውን የማያቋርጥ የአየር ድብደባ እንዲሁም ባለሥልጣናት ኃላፊነት ባላቸው ወንድሞች ላይ በተደጋጋሚ የሚያደርጉትን ምርመራ መቋቋም ነበረበት። ፕሪስ ሂዩዝ፣ ዩኧርት ቺቲ እና ፍራንክ ፕላት የተባሉ ወንድሞች በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት ታሰሩ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ አልበርት ሽሮደር ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተባረረ። እነዚህ ሁሉ ተጽእኖዎች ቢኖሩም የጉባኤዎችም ሆነ የመንግሥቱ ጉዳዮች ሥራ አልተስተጓጎለም።
ወደ ጊልያድ መጠራት!
ጦርነቱ በ1945 ሲጠናቀቅ በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በሚስዮናዊነት ለመሰልጠን አመለከትኩና በ1946 ለሚጀምረው ለስምንተኛው ክፍል ተጠራሁ። ማኅበሩ ቶኒ ኦትዉድን፣ ስታንሊ ጆንስን፣ ሐሮልድ ኪንግን፣ ዶን ሬንዴልንና ስታንሊ ዉድበርንን ጨምሮ ለብዙዎቻችን በኮርኒሽ የዓሣ ማጥመጃ ወደብ ከሆነችው ከፎኢ በመርከብ እንድንጓዝ ማኅበሩ ዝግጅት አደረገልን። አንድ የአካባቢው ምሥክር የሸክላ ሰሃን ለመሥሪያ የሚያገለግል አፈር በሚያጓጉዝ አነስተኛ የጭነት መርከብ እንድንጓዝ ትኬት ቆረጠልን። ያለንበት የመርከብ ክፍል በሰዎች የተጨናነቀ ከመሆኑም በላይ ወለሉም በውኃ የተጥለቀለቀ ነበር። በመጨረሻ መድረሻችን ወደሆነው ወደ ፊላደልፍያ ወደብ ስንደርስ ምን ያህል እፎይታ ተሰማን!
በኒው ዮርክ ሰሜናዊ ክልል በሳውዝ ላንሲንግ የሚገኘው የጊልያድ ትምህርት ቤት በሚያምር ቦታ የሚገኝ ሲሆን እዚያ ያገኘሁት ስልጠና ለእኔ ልዩ ትርጉም ነበረው። ተማሪዎቹ የመጡት ከአሥራ ስምንት አገሮች ሲሆን ማኅበሩ አገልጋዮችን ከሌሎች አገሮች በብዛት ሲመዘግብ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር። እርስ በርስ እጅግ የተቀራረበ ወዳጅነት መሥርተን ነበር። ከፊንላንድ ከመጣው ኮልሌ ሶልአቮራ ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ በመኖሬ በጣም ተደስቻለሁ።
ጊዜው በፍጥነት ያለፈ ሲሆን በአምስተኛው ወር መጨረሻ ላይ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ናታን ኤች ኖር ዲፕሎማችንን ሊሰጠንና ምድብ ቦታችንን ሊነግረን ብሩክሊን ከሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት መጣ። በዚያ ወቅት በምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ከመነገሩ በፊት ተማሪዎች ምድብ ቦታቸውን ቀደም ብለው አያውቁም ነበር። እኔም የቀድሞ ሥራዬን እንድቀጥል ለንደን ወደሚገኘው ቤቴል እንደገና ተመደብኩ።
ወደ ለንደን መመለስ
በብሪታኒያ ከጦርነቱ በኋላ የነበሩት ዓመታት ምቹ አልነበሩም። ወረቀትን ጨምሮ ምግብና ሌሎች በርካታ አስፈላጊ ነገሮች የሚታደሉት በራሽን ነበር። ይሁን እንጂ ያ ጊዜ እንደምንም ያለፈ ሲሆን የይሖዋ መንግሥት ፍላጎቶችም በልጽገዋል። ቤቴል ውስጥ ከመሥራት በተጨማሪ በአየርላንድ የሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎችን ጨምሮ በአውራጃና በወረዳ ስብሰባዎች ላይ አገልግያለሁ፤ እንዲሁም ጉባኤዎችን ጎብኝቻለሁ። ከኤሪክ ፍሮስትና ሌሎች የአውሮፓ ወንድሞችንና እህቶችን ማግኘትና በአሠቃቂው የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ስላሳዩት የአቋም ጽናት ከእነርሱ መማር ልዩ መብት ነበር። በእርግጥም የቤቴል አገልግሎት የተባረከ መብት ነበር።
በለንደን በስተሰሜን ዋትፎርድ በምትባል ከተማ ልዩ አቅኚ የነበረችውን ጆአን ዌብን ለአሥር ዓመታት አውቃት ነበር። ከጆአን ጋር በ1952 ተጋባን። ሁለታችንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመቀጠል ፍላጎት ነበረን። በዚህ ምክንያት በቤቴል ማገልገል ካቆምኩ በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ስሾም በጣም ተደሰትን። የመጀመሪያው ወረዳችን ደቡባዊው የእንግሊዝ ወደብ ዳር ሴክሰን እና ሃምፕሻየር ነበር። በእነዚያ ጊዜያት የወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ቀላል አልነበረም። በአብዛኛው በአውቶቡስ፣ በብስክሌትና በእግር እንጓዛለን። ብዙ ጉባኤዎች ለመድረስ አስቸጋሪ የሆኑ ሰፊ የገጠር ክልሎች ያሏቸው ቢሆንም የምሥክሮች ቁጥር ያለማቋረጥ እድገት ያደርጋል።
ኒው ዮርክ ከተማ 1958
በ1957 ለንደን ከሚገኘው ቤቴል “በ1958 በኒው ዮርክ ከተማ በያንኪ ስታዲየምና በፖሎ ግራውንድስ ለሚከናወነው ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ በሚደረጉት የጉዞ ሥራ 2:41
ዝግጅቶች እርዳታ ለማበርከት ወደ ቢሮ መምጣት ትችላለህ?” የሚል ግብዣ ቀረበልኝ። እኔና ጆአን ማኅበሩ በተከራያቸው አውሮፕላኖችና መርከቦች ለመጓዝ ወንድሞች ያቀረቧቸውን ማመልከቻዎች ስናስተናግድ ፋታ አጥተን ነበር። መለኮታዊ ፈቃድ የተሰኘው ይህ ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ 253, 922 የሚያክሉ ብዙ ተሰብሳቢዎችን በማስተናገዱ በሰፊው ይታወቃል። ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ለማሳየት 7, 136 ሰዎች ውኃ ውስጥ በመጥለቅ ተጠምቀዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው በ33 እዘአ በጰንጤቆስጤ ታሪካዊ ዕለት ከተጠመቁት በሁለት እጥፍ ይበልጣል።—እኔና ጆአን በስብሰባው ላይ ተገኝተን ከ123 አገሮች ወደ ኒው ዮርክ ከተማ የሚመጡ እንግዶች እንድናስተናግድ ወንድም ኖር በግል በመጋበዝ ያሳየንን ደግነት ፈጽሞ አንረሳውም። ይህ ለሁለታችንም አስደሳችና የማይረሳ ተሞክሮ ነበር።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በረከቶች
የጤና ችግር እስኪያጋጥመን ጊዜ ድረስ ከስብሰባው ስንመለስ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ቀጠልን። ጆአን ሆስፒታል ስትገባ እኔ ደግሞ ቀላል የደም መርጋት በሽታ አጋጠመኝ። ወደ ልዩ አቅኚነት ደረጃ ተዛወርን፤ ሆኖም ከጊዜ በኋላ ለጊዜው በወረዳ የበላይ ተመልካችነት የማገልገል መብት እንደገና አገኘን። በመጨረሻ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመቀጠል ወደ ብሪስቶል ተመለስን። ወንድሜ ዲክ ከቤተሰቡ ጋር በአቅራቢያችን ስለሚኖር ብዙ ጊዜ ያሳለፍናቸውን ጊዜያት እያስታወስን እናወራለን።
በ1971 በሕክምና ሊስተካከል በማይችል ሁኔታ የማየት ችግር ገጠመኝ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ለማንበብ በጣም እቸገራለሁ። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በቴፕ ክር ማግኘቱ ግሩም የይሖዋ ዝግጅት እንደሆነ ይሰማኛል። እኔና ጆአን አሁንም ቢሆን የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን የምንመራ ሲሆን ሰባት አባላት ያሉትን አንድ ቤተሰብ ጨምሮ በጠቅላላው 40 የሚያክሉ ሰዎች ወደ እውነት እንዲመጡ የመርዳት መብት አግኝተናል።
ከ60 ዓመት በፊት ሕይወታችንን ለይሖዋ ስንወስን ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባትና በዚያው ለመጽናት ፍላጎት ነበረን። ታላቁን ይሖዋን ለማገልገል አሁንም ብርታት ያለን በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን። እሱ ላሳየን የጥሩነት ባሕርይና በአንድነት ላሳለፍናቸው የደስታ ዓመታት እሱን ማመስገን የምንችልበት ብቸኛው መንገድ አገልግሎታችን ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የመጠበቂያ ግንብ እና የኮንሶሌሽን (ከጊዜ በኋላ ንቁ! የተባለውን) መጽሔት ቅጂዎች ለመያዝ የተዘጋጀ በትከሻ ላይ የሚነገት ከጨርቅ የተሠራ ቦርሳ።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከወንድሜ ከዲክ ጋር (በስተግራ ዳር፤ ዲክ ቆሞ) እንዲሁም ሌሎች አቅኚዎች በብሪስቶል የአቅኚዎች መኖሪያ ፊት ለፊት
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1940 በብሪስቶል የነበረው የአቅኚዎች መኖሪያ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስታንሊ እና ጆአን ሬይኖልድስ ጥር 12, 1952 በተጋቡበት ዕለትና በዛሬው ጊዜ