በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላካዊ ትምህርትን አጥብቀህ ያዝ

አምላካዊ ትምህርትን አጥብቀህ ያዝ

አምላካዊ ትምህርትን አጥብቀህ ያዝ

“በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።”​—⁠ምሳሌ 3:​5, 6

1. ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በአሁኑ ጊዜ ለሰብዓዊ እውቀት የተጋለጥነው እንዴት ነው?

 በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ወደ 9, 000 የሚጠጉ ጋዜጦች በየዕለቱ ይሠራጫሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ 200, 000 የሚደርሱ አዳዲስ መጻሕፍት በየዓመቱ ይታተማሉ። በአንድ ግምታዊ አስተያየት መሠረት በመጋቢት 1998 በኢንተርኔት 275 ሚልዮን የሚሆኑ የዌብ ገጾች ተዘርግተው ነበር። ይህ አኃዝ በየወሩ በ20 ሚልዮን ገጾች እንደሚያድግ ይነገራል። ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ስለፈለጉት ርዕሰ ጉዳይ መረጃ ማግኘት ይችላሉ። ይህ ሁኔታ አዎንታዊ ገጽታ ያለው ቢሆንም እንዲህ ያለው ስፍር ቁጥር የሌለው የመረጃ ብዛት ችግሮች ይፈጥራል።

2. ስፍር ቁጥር ለሌላቸው መረጃዎች ራስን ማጋለጥ ምን ችግሮች ሊያስከትል ይችላል?

2 አንዳንድ ሰዎች በመረጃ ሱስ የተጠመዱ በመሆናቸው መቼም የማይረካውን ከጊዜው ጋር እኩል ለመራመድ ያላቸውን ፍላጎት በማሟላት ላይ ብቻ በማተኮር በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ችላ ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በጣም ውስብስብ ስለሆኑ የእውቀት መስኮች ያልተሟላ መረጃ ይቀስሙና ራሳቸውን ሊቅ እንደሆኑ አድርገው ይመለከታሉ። የቀሰሙትን አነስተኛ እውቀት መሠረት በማድረግ የሚያደርጉት ከባድ ውሳኔ በራሳቸው ወይም በሌሎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም ለሃሰት ወይም ለተሳሳተ መረጃ የመጋለጥ አደጋ አለ። ብዙውን ጊዜ ይህ ስፍር ቁጥር የሌለው መረጃ ትክክልና ሚዛናዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል አስተማማኝ የሆነ መንገድ የለም።

3. ሰብዓዊ ጥበብ መከታተልን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ማስጠንቀቂያ ሰፍሮ ይገኛል?

3 አዳዲስ ነገሮችን የማወቅ ፍላጎት ከጥንት ጀምሮ የነበረ የሰው ልጅ ባሕርይ ነው። ፋይዳ ቢስ አልፎ ተርፎም ጎጂ የሆነ መረጃ በመከታተል ጊዜን ማባከን አደጋ እንዳለው በንጉሥ ሰሎሞን ዘመንም ይታወቅ ነበር። ንጉሥ ሰሎሞን “ተግሣጽን ስማ፤ ብዙ መጻሕፍትን ማድረግ ፍጻሜ የለውም፣ እጅግም ምርምር ሰውነትን ያደክማል” ሲል ተናግሯል። (መክብብ 12:​12) ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሚከተለውን ጽፎለታል:- “በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፣ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤ ይህ እውቀት አለን ብለው፣ አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና።” (1 ጢሞቴዎስ 6:​20, 21) አዎን፣ በዛሬውም ጊዜ ያሉት ክርስቲያኖች ጎጂ ለሆኑ አስተሳሰቦች እንዳይጋለጡ ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

4. በይሖዋና በትምህርቶቹ ላይ የምንታመን መሆናችንን ልናሳይ የምንችልበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?

4 የይሖዋ ሕዝቦች በ⁠ምሳሌ 3:​5, 6 ላይ የሚገኙትንም ቃላት መከተል ይኖርባቸዋል:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።” በይሖዋ መታመን ከራሳችንም ሆነ ከሌላ ሰው የሚመነጨውን ከአምላክ ቃል ጋር የሚጋጭ ማንኛውንም ዓይነት አስተሳሰብ ማስወገድን ይጨምራል። ጎጂ መረጃዎችን ለይተን በማወቅና ከእንዲህ ዓይነቶቹ መረጃዎች በመራቅ መንፈሳዊነታችንን መጠበቅ እንችል ዘንድ የማስተዋል ችሎታችንን ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ዕብራውያን 5:​14) ቀጥለን እንደነዚህ ያሉ መረጃዎች የሚገኙባቸውን አንዳንድ ምንጮች እንመለከታለን።

በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለ ዓለም

5. ጎጂ አስተሳሰብ የሚፈልቅበት አንደኛው ምንጭ ምንድን ነው? ከእርሱስ በስተጀርባ ያለው ማን ነው?

5 ይህ ዓለም ጎጂ አስተሳሰቦች የሚፈልቁበት ቦታ ነው። (1 ቆሮንቶስ 3:​19) ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን በማስመልከት “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም” በማለት ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:​15) ኢየሱስ፣ ሰይጣን በዓለም ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በመገንዘብ አምላክ ደቀ መዛሙርቱን ‘ከክፉ እንዲጠብቃቸው’ መጠየቁ ነበር። ክርስቲያን መሆናችን በራሱ ይህ ዓለም ከሚያሳድራቸው መጥፎ ተጽዕኖዎች ሊጠብቀን አይችልም። ዮሐንስ “ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:​19) በተለይ በዚህ ፍጻሜው በተቃረበበት የመጨረሻ ዘመን ሰይጣንና አጋንንቱ ዓለም ጎጂ በሆኑ መረጃዎች እንድትጥለቀለቅ ማድረጋቸው የሚጠበቅ ነገር ነው።

6. የዓለም መዝናኛ በሥነ ምግባር ስሜታችንን ሊያደነዝዝ የሚችለው እንዴት ነው?

6 በተጨማሪም ከእነዚህ ጎጂ መረጃዎች መካከል አንዳንዶቹ ጉዳት የማያስከትሉ መስለው የሚታዩ መሆናቸው የሚጠበቅ ነገር ነው። (2 ቆሮንቶስ 11:​14) ለምሳሌ ያህል የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን፣ ፊልሞችን፣ ሙዚቃዎችንና እየታተሙ የሚወጡ ጽሑፎችን ጨምሮ የዚህን ዓለም መዝናኛዎች ተመልከት። አንዳንድ የመዝናኛ ዓይነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሚሄድ መጠን እንደ ሥነ ምግባር ብልግና፣ ዓመፅና አደገኛ ዕፆችን መውሰድ የመሰሉ ወራዳ ድርጊቶችን እንደሚያስፋፉ ብዙዎች ይስማማሉ። አንድ ሰው እንደነዚህ ያሉ በሥነ ምግባር በጣም ያዘቀጡ መዝናኛዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመለከት ሊዘገነን ይችል ይሆናል። ሆኖም በተደጋጋሚ መመልከት ከጀመረ እየደነዘዘ ሊሄድ ይችላል። ጎጂ አስተሳሰብ የሚያስፋፉ መዝናኛዎችን ተቀባይነት እንዳላቸው ወይም ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትሉ አድርገን ፈጽሞ መመልከት አይኖርብንም።​—⁠መዝሙር 119:​37

7. በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለንን እምነት ሊሸረሽርብን የሚችለው የትኛው ሰብዓዊ ጥበብ ነው?

7 ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ሌላው አደገኛ የመረጃ ምንጭ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ አንዳንድ ሳይንቲስቶችና ምሁራን በሚያሳትሟቸው ጽሑፎች ላይ የሚወጣው ሐሳብ ነው። (ከ⁠ያዕቆብ 3:​15 ጋር አወዳድር።) እንደነዚህ ያሉ ሐሳቦች በየጊዜው በሚታተሙ መጽሔቶችና በታወቁ መጻሕፍት ላይ የሚወጡ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለንን እምነት ሊሸረሽሩብን ይችላሉ። አንዳንድ ግለሰቦች ማለቂያ የሌለው ግምታዊ አስተሳሰብ በመሰንዘር የአምላክ ቃል ያለውን ሥልጣን ለማዳከም በሚያደርጉት ጥረት ይኩራራሉ። በሐዋርያት ዘመንም ተመሳሳይ አደጋ እንደነበር ሐዋርያው ጳውሎስ ከጻፋቸው ቃላት ለመረዳት ይቻላል:- “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።”​—⁠ቆላስይስ 2:​8

የእውነት ጠላቶች

8, 9. በዛሬው ጊዜ ክህደት ራሱን እየገለጠ ያለው እንዴት ነው?

8 ከሃዲዎችም መንፈሳዊነታችንን አደገኛ ሁኔታ ላይ ሊጥሉት ይችላሉ። ክርስቲያን ነን በሚሉ መካከል ክህደት እንደሚነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ አስቀድሞ ተናግሯል። (ሥራ 20:​29, 30፤ 2 ተሰሎንቄ 2:​3) እርሱ በተናገራቸው ቃላት ፍጻሜ መሠረት ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ የተነሳው ከፍተኛ ክህደት ለሕዝበ ክርስትና መስፋፋት ምክንያት ሆኗል። ዛሬ በአምላክ ሕዝቦች መካከል እየተፈጸመ ያለ ታላቅ ክህደት የለም። ሆኖም ከእኛ መካከል ጥቂት ግለሰቦች ወጥተዋል። ከእነርሱም መካከል አንዳንዶቹ የሃሰት ወሬዎችንና የተሳሳቱ መረጃዎችን በመንዛት የይሖዋ ምሥክሮችን ስም ለማጥፋት ቆርጠው ተነስተዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ከሌሎች ቡድኖች ጋር ሕብረት በመፍጠር እውነተኛውን አምልኮ ይቃወማሉ። እንዲህ በማድረግም ከመጀመሪያው ከሃዲ ከሰይጣን ጎራ ራሳቸውን አሰልፈዋል።

9 አንዳንድ ከሃዲዎች የይሖዋ ምሥክሮችን በሚመለከት የሃሰት ወሬዎችን ለመንዛት ኢንተርኔትን ጨምሮ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በከፍተኛ ሁኔታ በመጠቀም ላይ ናቸው። በዚህም የተነሳ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች እምነታችንን በተመለከተ ምርምር በሚያደርጉበት ጊዜ የከሃዲዎችን ፕሮፓጋንዳ ሊያገኙ ይችላሉ። አንዳንድ ምሥክሮችም ሳያውቁ እንዲህ ላለው ጎጂ ጽሑፍ ራሳቸውን አጋልጠዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከሃዲዎች አልፎ አልፎ በቴሌቪዥን ወይም በራዲዮ ፕሮግራሞች ብቅ ይላሉ። ይህን በተመለከተ ልንከተለው የሚገባን ጥበብ ያለበት አካሄድ ምንድን ነው?

10. ከሃዲዎች ለሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ልናሳየው የሚገባን ጥበብ የተሞላበት ምላሽ ምንድን ነው?

10 ክርስቲያኖች ከሃዲዎችን በቤታቸው እንዳይቀበሉ ሐዋርያው ዮሐንስ መመሪያ ሰጥቷል። እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና።” (2 ዮሐንስ 10, 11) ከእነዚህ ባላጋራዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አለመፍጠራችን ብልሹ ከሆነው አስተሳሰባቸው ይጠብቀናል። በጊዜያችን ባሉ የተለያዩ ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት ለከሃዲ ትምህርቶች ራሳችንን ብናጋልጥ ሊደርስብን የሚችለው ጉዳት ከሃዲውን በቤታችን ብንቀበል ከሚደርስብን ጉዳት የሚተናነስ አይደለም። አዳዲስ ነገሮችን የማወቅ ጉጉት ወደዚህ የጥፋት ጎዳና ስቦ እንዲያስገባን ፈጽሞ አንፍቀድ!​—⁠ምሳሌ 22:​3

በጉባኤ ውስጥ

11, 12. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበረው ጎጂ አስተሳሰብ ምንጩ ምን ነበር? (ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች አምላካዊ ትምህርቶችን አጥብቀው ሳይዙ የቀሩት እንዴት ነው?

11 ጎጂ አስተሳሰቦች ሊመነጩ የሚችሉበትን ሌላ አቅጣጫ ደግሞ እንመልከት። ራሱን ለአምላክ የወሰነ አንድ ክርስቲያን የሃሰት ትምህርቶችን የማስተማር ዓላማ ባይኖረውም እንኳ አሳቢነት በጎደለው ሁኔታ የመናገር ልማድ ሊያዳብር ይችላል። (ምሳሌ 12:​18) ፍጹማን ባለመሆናችን የተነሳ አልፎ አልፎ ሁላችንም በአንደበታችን እንስታለን። (ምሳሌ 10:​19፤ ያዕቆብ 3:​8) በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመንም በጉባኤ ውስጥ አንደበታቸውን መቆጣጠር የተሳናቸውና በከፍተኛ የቃላት ክርክር ውስጥ የገቡ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። (1 ጢሞቴዎስ 2:​8) በራሳቸው አስተያየት ከልክ በላይ የሚመኩና የጳውሎስን ሥልጣን እስከ መቃወም የደረሱ ሰዎችም ነበሩ። (2 ቆሮንቶስ 10:​10-12) እንዲህ ያለው መንፈስ አላስፈላጊ የሆኑ ግጭቶች አስከትሏል።

12 አንዳንድ ጊዜ እነዚህ አለመግባባቶች ተባብሰው በትንሹም በትልቁም “የማያቋርጥ ክርክር” ሊያስከትሉና የጉባኤውን ሰላም ሊያውኩ ይችላሉ። (1 ጢሞቴዎስ 6:​5የ1980 ትርጉም፤ ገላትያ 5:​15) እንዲህ ያለውን ክርክር የሚቆሰቁሱ ሰዎችን በማስመልከት ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፣ በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፣ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም . . . ይወጣሉ።”​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​3, 4

13. በመጀመሪያው መቶ ዘመን አብዛኞቹ ክርስቲያኖች የነበራቸው ምግባር ምን ዓይነት ነበር?

13 ደስ የሚለው ግን በሐዋርያት ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ታማኝ የነበሩ ሲሆን ትኩረታቸውንም የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማወጁ ሥራ ላይ አድርገው ነበር። ‘ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባልቴቶች በመከራቸው’ በመጠየቅ ሥራ ራሳቸውን አስጠምደው የነበረ ከመሆኑም በላይ ጥቃቅን በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመነታረክ ጊዜያቸውን ከማጥፋት ይልቅ ‘ከዓለም እድፍ ራሳቸውን ይጠብቁ’ ነበር። (ያዕቆብ 1:​27) መንፈሳዊነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ በክርስቲያን ጉባኤም ሳይቀር ከ“ክፉ ባልንጀርነት” ይርቁ ነበር።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​33፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:​20, 21

14. ካልተጠነቀቅን ጉዳት ያላቸው የማይመስሉ የተለመዱ ውይይቶች ጎጂ ወደሆነ ክርክር ሊያመሩ የሚችሉት እንዴት ነው?

14 በተመሳሳይም አንቀጽ 11 ላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች በዛሬው ጊዜ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ዓይነተኛ ገጽታዎች አይደሉም። ሆኖም እንዲህ ያለው በጥቃቅን ነገሮች ላይ የሚደረግ ክርክር ሊከሰት እንደሚችል መዘንጋት አይኖርብንም። እርግጥ ነው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ታሪኮች ላይ መወያየት ወይም ገና ባልተገለጡ የአዲሱ ዓለም ተስፋ ገጽታዎች ላይ መነጋገሩ ምንም ስህተት የለበትም። እንዲሁም አለባበስንና አበጣጠርን ወይም የመዝናኛ ምርጫን የመሰሉ የግል ጉዳዮችን በተመለከተም ሐሳቦችን መለዋወጡ ምንም ስህተት የለውም። ይሁን እንጂ የእኛ አስተሳሰብ ብቻ ትክክል እንደሆነ አድርገን በማሰብ ድርቅ ያለ አቋም የምንይዝና ሌሎች የእኛን አሳብ ሳይቀበሉ በሚቀሩበት ጊዜ የምንቀየም ከሆነ ጉባኤው በጥቃቅን ጉዳዮች ሳይቀር ሊከፋፈል ይችላል። ጉዳት የሌለው በሚመስል ተራ ወሬ የተጀመረ ነገር እየሰፋ ሊሄድና ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

የተቀበልነውን አደራ መጠበቅ

15. ‘የአጋንንት ትምህርቶች’ በመንፈሳዊ ምን ያህል ሊጎዱን ይችላሉ? በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ምን ምክር ተሰጥቷል?

15 ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ያስጠነቅቃል:- “መንፈስ ግን በግልጥ:- በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና . . . የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፣ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል።” (1 ጢሞቴዎስ 4:​1) አዎን፣ ጎጂ ሐሳቦች አደገኛ ሁኔታ ሊፈጥሩ ይችላሉ። ጳውሎስ ተወዳጅ የሆነውን ጓደኛውን ጢሞቴዎስን እንደሚከተለው ብሎ ለመለመን ያበቃው በቂ ምክንያት እንደነበረው ግልጽ ነው:- “ጢሞቴዎስ ሆይ፣ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፣ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤ ይህ እውቀት አለን ብለው፣ አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና።”​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​20, 21

16, 17. ከአምላክ የተቀበልነው አደራ ምንድን ነው? ልንጠብቀው የሚገባንስ እንዴት ነው?

16 ዛሬ እኛ ከዚህ ፍቅራዊ ማስጠንቀቂያ ጥቅም ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው? ጢሞቴዎስ በጥንቃቄ ሊይዘውና ሊጠብቀው የሚገባው ከፍተኛ ዋጋ ያለው አንድ አደራ ተሰጥቶት ነበር። ይህ አደራ ምን ነበር? ጳውሎስ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፣ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤ መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ።” (2 ጢሞቴዎስ 1:​13, 14) አዎን፣ ጢሞቴዎስ የተሰጠው አደራ ‘ጤናማውን ቃል’ ማለትም ‘እግዚአብሔርን ከመምሰል [“ለአምላክ ከማደር፣” NW ] ጋር የሚስማማውን ትምህርት’ የሚጨምር ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:​3) በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከእነዚህ ቃላት ጋር በመስማማት እምነታቸውንና በአደራ የተቀበሉትን መላውን እውነት ለመጠበቅ ቆርጠዋል።

17 ይህንን አደራ መጠበቅ “ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም” ከማድረግ ጎን ለጎን ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልማድንና በጸሎት መጽናትን የመሰሉ ነገሮችን ማዳበርን ይጨምራል። (ገላትያ 6:​10፤ ሮሜ 12:​11-17) በመጨመር ጳውሎስ እንዲህ በማለት ምክሩን ይለግሳል:- “ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል። መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፣ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት [“አጥብቀህ፣” NW ] ያዝ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:​11, 12) “መልካሙን የእም​ነት ገድል ተጋደል” እና “አጥብቀህ ያዝ” የሚሉት ጳውሎስ የተጠቀመባቸው ሐረጎች በመንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ተጽዕኖዎችን በንቃት እና በቁርጠኝነት መቋቋም እንዳለብን በግልጽ የሚያስገነዝቡ ናቸው።

አስተዋይ የመሆን አስፈላጊነት

18. ዓለማዊ መረጃዎችን በተመለከተ ክርስቲያናዊ ሚዛናዊነት ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?

18 እርግጥ ነው፣ መልካሙን የእምነት ገድል ለመጋደል ማስተዋል አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 2:​11፤ ፊልጵስዩስ 1:​9) ለምሳሌ ያህል ሁሉንም ዓይነት ዓለማዊ መረጃዎች በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ምክንያታዊ አይሆንም። (ፊልጵስዩስ 4:​5፤ ያዕቆብ 3:​17) ሁሉም ሰብዓዊ አስተሳሰቦች ከአምላክ ቃል ጋር የሚጋጩ ናቸው ማለት አይቻልም። ኢየሱስ የታመሙ ሰዎች ዓለማዊ ሙያ ወዳለው ሐኪም ዘንድ ሄደው መታከም እንደሚያስፈልጋቸው በተዘዋዋሪ መንገድ ተናግሯል። (ሉቃስ 5:​31) በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በኢየሱስ ዘመን የነበረው የሕክምና ዘዴ ኋላ ቀር ቢሆንም ሐኪሞች ከሚሰጡት እርዳታ የተወሰነ ጥቅም ማግኘት እንደሚቻል ያምን ነበር። በዛሬውም ጊዜ ክርስቲያኖች ዓለማዊ መረጃዎችን በተመለከተ ሚዛናዊ መሆን ያለባቸው ቢሆንም በመንፈሳዊነታቸው ላይ ጉዳት ሊያስከትል ከሚችል ከማንኛውም ዓይነት መረጃ ራሳቸውን ይጠብቃሉ።

19, 20. (ሀ) ሽማግሌዎች ጥበብ በጎደለው መንገድ የሚናገሩ ሰዎችን በሚረዱበት ጊዜ ማስተዋል ሊያሳዩ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ጉባኤው የሃሰት ትምህርት የሚያስፋፉ ግለሰቦችን የሚይዛቸው እንዴት ነው?

19 ሽማግሌዎች ጥበብ በጎደለው መንገድ የሚናገሩ ሰዎችን በሚያስተካክሉበት ጊዜም አስተዋይነት ማሳየታቸው አስፈላጊ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 2:​7) አልፎ አልፎ የጉባኤ አባላት ጥቃቅን በሆኑ ጉዳዮችና ግምታዊ በሆኑ አስተሳሰቦች የጦፈ ክርክር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። የጉባኤውን አንድነት ለመጠበቅ ሲሉ ሽማግሌዎች እንዲህ ያለውን ችግር ፈጥነው ማስወገድ ይኖርባቸዋል። ይህን ሲያደርጉም የወንድሞቻቸውን የውስጥ ዝንባሌ በመጥፎ ከመተርጎም ይቆጠባሉ እንዲሁም ከሃዲ እንደሆኑ አድርገው ለመመልከትም አይቸኩሉም።

20 ጳውሎስ እርዳታ በሚሰጥበት ጊዜ ሊኖር ስለሚገባው መንፈስ ግልጽ ማብራሪያ ሰጥቷል። “ወንድሞች ሆይ፣ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት” ብሏል። (ገላትያ 6:​1) ይሁዳ ካደረባቸው የጥርጣሬ መንፈስ ጋር ስለሚታገሉ ክርስቲያኖች ሲናገር “ለሚጠራጠሩ ሰዎች ርኅራኄ አድርጉላቸው፤ . . . ከእሳት አውጥታችሁ አድኑአቸው” በማለት ጽፏል። (ይሁዳ 22, 23የ1980 ትርጉም ) እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ተደጋጋሚ ምክር ተሰጥቶት የሃሰት ትምህርቶችን ማስፋፋቱን ከቀጠለ ሽማግሌዎች ጉባኤውን ለመጠበቅ ሲሉ ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 1:​20፤ ቲቶ 3:​10, 11

አእምሯችንን በመልካም ነገሮች መሙላት

21, 22. በምን ረገድ መራጮች መሆን አለብን? አእምሯችንንስ በምን ነገሮች መሙላት አለብን?

21 ክርስቲያን ጉባኤ “እንደ ጭንቁር” ከሚባሉ ጎጂ ቃላት ይርቃል። (2 ጢሞቴዎስ 2:​16, 17፤ ቲቶ 3:⁠9) ይህ አባባል አሳሳች ለሆነ ዓለማዊ ‘ጥበብ፣’ ከሃዲዎች ለሚነዟቸው ፕሮፓጋንዳዎች ወይም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞች ለሚሰነዝሯቸው አሳቢነት የጎደላቸው ንግግሮች ሁሉ የሚሠራ ነው። አዳዲስ ነገሮችን የማወቅ ጤናማ ፍላጎት ጠቃሚ ሊሆን ቢችልም እንዲህ ዓይነቱ ፍላጎት ገደቡን በሚያልፍበት ጊዜ ጎጂ ለሆኑ አስተሳሰቦች ሊያጋልጠን ይችላል። ሰይጣን የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች እናውቃቸዋለን። (2 ቆሮንቶስ 2:​11) ሐሳባችንን በመከፋፈል ለአምላክ የምናቀርበውን አገልግሎት ለማዳፈን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ እናውቃለን።

22 እንደ መልካም አገልጋዮች መጠን አምላካዊ ትምህርትን አጥብቀን እንያዝ። (1 ጢሞቴዎስ 4:​6) በመረጃ ምርጫችን ረገድ ጠንቃቆች በመሆን ጊዜያችንን በጥበብ የምንጠቀም እንሁን። እንደዚያ ካደረግን ሰይጣን በሚያናፍሰው ፕሮፓጋንዳ በቀላሉ አንናወጥም። አዎን፣ “እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ።” አእምሯችንንና ልባችንን በእነዚህ ነገሮች ከሞላናቸው የሰላም አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​8, 9

ምን ተምረናል?

• ዓለማዊ ጥበብ በመንፈሳዊነታችን ላይ አደገኛ ሁኔታ ሊፈጥር የሚችለው እንዴት ነው?

• ከሃዲዎች ከሚያሰራጯቸው ጎጂ መረጃዎች ራሳችንን ለመጠበቅ ምን ልናደርግ እንችላለን?

• በጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት ንግግር ከመናገር መቆጠብ አለብን?

• በዛሬው ጊዜ ያሉትን ስፍር ቁጥር የሌላቸው መረጃዎች በተመለከተ ክርስቲያናዊ ሚዛናዊነት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሰፊው ተቀባይነት ያገኙ በርካታ መጽሔቶችና መጻሕፍት ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራችን ጋር የሚጣጣሙ አይደሉም

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች የእኔ አስተሳሰብ ብቻ ነው ትክክል የሚል ድርቅ ያለ አቋም ሳይዙ ሐሳቦችን ሊለዋወጡ ይችላሉ