በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አቤቱ ይሖዋ ሆይ፣ መሠዊያህን እዞራለሁ”

“አቤቱ ይሖዋ ሆይ፣ መሠዊያህን እዞራለሁ”

“አቤቱ ይሖዋ ሆይ፣ መሠዊያህን እዞራለሁ”

“እጆቼን በንጽሕና አጥባለሁ፤ አቤቱ፣ [“ይሖዋ ሆይ፣” NW  ] መሠዊያህን እዞራለሁ።” (መዝሙር 26:​6) በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ዳዊት በእነዚህ ቃላት አማካኝነት ለይሖዋ ያደረ መሆኑን ገልጿል። ይሁንና ዳዊት የይሖዋን ‘መሠዊያ የሚዞረው’ ለምንድን ነው? ደግሞስ እንዴት?

ለዳዊት የይሖዋ አምልኮ ማዕከል የነበረው በናስ የተለበጠ መሠዊያ የሚገኝበት የመገናኛው ድንኳን ነበር። ይህ የመገናኛ ድንኳን በእርሱ የግዛት ዘመን የተተከለው ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን በምትገኘው ገባኦን ነበር። (1 ነገሥት 3:​4) ወደ 2.2 ካሬ ሜትር የሚጠጋው መሠዊያ በሰሎሞን ቤተ መቅደስ አደባባይ ላይ ከተሠራው ዕጹብ ድንቅ መሠዊያ አንጻር ሲታይ በጣም ትንሽ ነው። a ያም ሆኖ ዳዊት በእስራኤል ውስጥ የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል ሆኖ ያገለግል በነበረውና መሠዊያው በሚገኝበት የመገናኛ ድንኳን እጅግ ደስ ይለው ነበር።​—⁠መዝሙር 26:​8

በመሠዊያው ላይ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች፣ የደህንነት መሥዋዕቶች እንዲሁም የኃጢአት መሥዋዕቶች ይቀርቡ ነበር። ከዚህም በላይ በዓመታዊው የስርየት ቀን የሕዝቡን ኃጢአት ለመሸፈን የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ነበሩ። መሠዊያውና የሚቀርቡት መሥዋዕቶች በአሁኑ ጊዜ ለሚገኙት ክርስቲያኖች የሚያስተላልፉት ትርጉም አለ። መሠዊያው የሰው ልጆች ከኃጢአት የሚቤዡበትን ተመጣጣኝ መሥዋዕት ለመቀበል አምላክ ያለውን ፈቃድ እንደሚያመለክት ሐዋርያው ጳውሎስ ገልጿል። “በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል።”​—⁠ዕብራውያን 10:​5-10

ካህናት በመሠዊያው ላይ መሥዋዕቶችን ከማቅረባቸው በፊት እጃቸውን በውኃ የሚታጠቡበት ልማድ ነበር። ከዚህ አንጻር ንጉሥ ዳዊት ‘መሠዊያውን ከመዞሩ’ በፊት እጆቹን “በንጽሕና” መታጠቡ ተገቢ ነበር። ዳዊት “በየዋህ ልብና [“የአቋም ጽናት ባለው ልብ፣” NW  ] በቅንነት” ተመላልሷል። (1 ነገሥት 9:​4) በዚህ መንገድ እጆቹን ባያጥብ ኖሮ አምልኮቱ ማለትም ‘መሠዊያውን መዞሩ’ በአምላክ ፊት ተቀባይነት አይኖረውም ነበር። እርግጥ ነው፣ ዳዊት ሌዋዊ ስላልነበረ የክህነት አገልግሎት የማከናወን ልዩ መብት አልነበረውም። እንዲሁም ንጉሥ ቢሆንም ወደ መገናኛው ድንኳን አደባባይ የመግባት መብት አልነበረውም። ሆኖም ዳዊት ታማኝ እስራኤላዊ እንደመሆኑ መጠን የሙሴን ሕግ በመታዘዝ መሠዊያው ላይ የሚቀርቡ መሥዋዕቶችን ዘወትር ያመጣ ነበር። ሕይወቱን በእውነተኛው አምልኮ ላይ በመገንባቱ የአምላክን መሠዊያ የዞረ ያህል ነበር።

እኛስ ዛሬ የዳዊትን ምሳሌ ልንኮርጅ እንችላለን? አዎን። እኛም በኢየሱስ መሥዋዕት የምናምን ከሆነ ‘እጆቻችንን ልናጥብና የይሖዋን መሠዊያ ልንዞር’ እንዲሁም ‘እጃችንና ልባችን ንጹህ ሆኖ’ ይሖዋን በሙሉ ልባችን ልናገለግለው እንችላለን።​—⁠መዝሙር 24:​4

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይህ መሠዊያ ወደ 9 ካሬ ሜትር የሚጠጋ ነበር።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መሠዊያው የሰው ልጆች ከኃጢአት የሚቤዡበትን ተገቢ መሥዋዕት ለመቀበል ይሖዋ ያለውን ፈቃድ ያመለክታል