ይሖዋ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው
ይሖዋ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው
መዝሙራዊው “እግዚአብሔር በሚፈሩት . . . ይደሰታል” ሲል ጽፏል። በእርግጥም ፈጣሪ የእሱን የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች ለማክበር ጥረት በሚያደርግ በእያንዳንዱ ሰብዓዊ አገልጋዩ ደስ ይለዋል። አምላክ ታማኞቹን ይባርካቸዋል፣ ያበረታታቸዋል እንዲሁም ተስፋ በሚቆርጡበት ጊዜ ያጽናናቸዋል። አምላኪዎቹ ፍጹማን እንዳልሆኑ ስለሚያውቅ ከእነሱ በሚፈልገው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነው።—መዝሙር 147:11
ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በአጠቃላይ ታላቅ ፍቅር እንዳለው ማመን አይከብደን ይሆናል። ነገር ግን አንዳንዶች ባለባቸው ጉድለት ላይ ከመጠን በላይ ትኩረት ስለሚያደርጉ ይመስላል፣ ይሖዋ በፍጹም ሊወዳቸው እንደማይችል ሆኖ ይሰማቸዋል። “ይሖዋ እኔን ሊወደኝ አይችልም” ብለው ይደመድሙ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ሁላችንም አልፎ አልፎ ስለ ራሳችን አሉታዊ ስሜት ይሰማን ይሆናል። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ከሚሰማቸው ጥልቅ የሆነ የዋጋ ቢስነት ስሜት ጋር የማያቋርጥ ትግል ያደርጋሉ።
በሐዘን ስሜት መዋጥ
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የታመኑ ሰዎች በከባድ የሐዘን ስሜት ተውጠው ነበር። ኢዮብ ሕይወቱን ከመጥላቱም በላይ አምላክ እንደተወው ተሰምቶት ነበር። የሳሙኤል እናት የነበረችው ሐናም በአንድ ወቅት ልጅ መውለድ ባለመቻሏ ምክንያት በጣም ተጨንቃ በምሬት አልቅሳለች። ዳዊት “ልቤም ተሰበረ” ብሎ ነበር። እንዲሁም አፍሮዲጡ የሕመሙ ዜና ወንድሞቹን ስላሳዘናቸው መዝሙር 38:6 NW ፤ 1 ሳሙኤል 1:7, 10፤ ኢዮብ 29:2, 4, 5፤ ፊልጵስዩስ 2:25, 26
ተጨንቆ ነበር።—በዛሬው ጊዜ ስለሚገኙት ክርስቲያኖችስ ምን ለማለት ይቻላል? ምናልባት ህመም፣ የዕድሜ መግፋት ወይም ሌሎች የግል ሁኔታዎች አንዳንዶች የሚፈልጉትን ያህል ቅዱስ አገልግሎት ከማቅረብ ያግዳቸው ይሆናል። ይህም ይሖዋና መሰል አማኞች እንደሚጠብቁብን ሆነን አልተገኘንም ብለው እንዲደመድሙ ሊያደርጋቸው ይችላል። ወይም አንዳንዶች ባለፉት ጊዜያት ለሠሯቸው ስህተቶች ይሖዋ ይቅር አላለኝ ይሆናል ብለው ስለሚያስቡ ዘወትር ራሳቸውን ይወቅሳሉ። ሌሎች ደግሞ ምናልባትም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ያደጉ ይሆኑና ሊወደዱ የማይገባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
አንዳንዶች የፍቅር መንፈስ ጎልቶ በሚታይበት ቤተሰብ ውስጥ ሳይሆን ራስ ወዳድነት፣ የአሽሙር ንግግር እንዲሁም ፍርሃት በሰፈነበት ቤተሰብ ውስጥ ያድጋሉ። በጥልቅ የሚወዳቸው፣ እነሱን ለማመስገንና ለማበረታታት አጋጣሚ የሚፈልግ፣ ጥቃቅን ስህተቶችን የሚያልፍና ከበድ ያሉትን ስህተቶች እንኳን ሳይቀር ይቅር ለማለት ዝግጁ የሆነ እንዲሁም የሚያሳየው ፍቅራዊ ስሜት መላውን ቤተሰብ የሚያረጋጋ አባት የማግኘትን ጣዕም አያውቁት ይሆናል። ስለዚህ አፍቃሪ የሆነ ምድራዊ አባት ኖሯቸው ስላላደጉ አፍቃሪ የሆነ ሰማያዊ አባት ማግኘት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ይከብዳቸው ይሆናል።
ለምሳሌ ፍሪትስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አባቴ የሚያሳየው ፍቅር የጎደለው ባሕርይ በልጅነትና በወጣትነት ዕድሜዬ በእጅጉ ተጽእኖ አሳድሮብኝ ነበር። a አንድም ቀን የምስጋና ቃል ከአፉ ወጥቶ አያውቅም። እኔም እንደቀረብኩት ሆኖ ተሰምቶኝ አያውቅም። እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ እፈራው ነበር።” ከዚህም የተነሳ ዛሬ በ50ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ፍሪትስ አሁንም የሚጎድለው ነገር እንዳለ ሆኖ ይሰማዋል። ማርጋሬትም እንዲህ በማለት ትገልጻለች:- “ወላጆቼ ደንታ ቢስና ፍቅር የጎደላቸው ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስጀምር አፍቃሪ አባት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ከብዶኝ ነበር።”
እንዲህ ዓይነት ስሜቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆነው ነገር ምንም ይሁን ምን ይህ ስሜት ካለ አምላክን እንድናገለግል በዋነኛነት ያነሳሳን ነገር ፍቅር መሆኑ ቀርቶ የበደለኛነት ስሜት ወይም ፍርሃት ሊሆን ይችላል። ምርጣችንንም ሰጥተን በፍጹም በቂ መስሎ አይታየንም። ይሖዋንና ክርስቲያን ወንድሞቻችንን ለማስደሰት ያለን ምኞት ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር ለማድረግ እየጣርን እንዳለ እንዲሰማን ሊያደርገን ይችላል። በዚህም ምክንያት ያወጣናቸው ግቦች ላይ መድረስ ያቅተንና፣ ራሳችንን ልንወቅስ እንዲሁም በሐዘን ልንዋጥ እንችላለን።
እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲገጥመን ምን ልናደርግ እንችላለን? ምናልባት ይሖዋ ምን ያህል አሳቢ እንደሆነ ማስታወስ ያስፈልገን ይሆናል። እንዲህ ያለውን የአምላክ ፍቅራዊ ባሕርይ ከተገነዘቡት ሰዎች መካከል አንዱ ሐዋርያው ዮሐንስ ነበር።
“እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው”
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ ለክርስቲያን ወንድሞቹ እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል:- “ልባችንም በእኛ ላይ በሚፈርድበት ሁሉ፣ ከእውነት እንደ ሆንን በዚህ እናውቃለን በፊቱም ልባችንን እናሳርፋለን፣ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል።” ዮሐንስ እንደዚህ ብሎ የጻፈው ለምንድን ነው?—1 ዮሐንስ 3:19, 20
ዮሐንስ አንድ የይሖዋ አገልጋይ ልቡ ሊፈርድበት እንደሚችል አሳምሮ ያውቅ ነበር። ምናልባትም ዮሐንስ ራሱ እንዲህ ያለ ስሜት ተሰምቶት ያውቅ ይሆናል። ወጣት ሳለ ቶሎ የመቆጣት ባሕርይ ስለነበረው ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ መፍረድ ይቀናው ነበር። በአንድ ወቅትም ኢየሱስ ክርስቶስ እርማት ሰጥቶታል። እንዲያውም ኢየሱስ ዮሐንስንና ያዕቆብ የተባለ ወንድሙን ‘ቦአኔርጌስ ብሎ ሰይሟቸዋል፣ ትርጉሙ የነጐድጓድ ልጆች ማለት ነው።’—ማርቆስ 3:17፤ ሉቃስ 9:49-56
በሚቀጥሉት 60 ዓመታት ውስጥ ዮሐንስ በዕድሜ እየበሰለ ሲሄድ ሚዛናዊ፣ አፍቃሪና መሐሪ ክርስቲያን መሆን ችሏል። በሕይወት የቀረ የመጨረሻ ሐዋርያ ሆኖ የመጀመሪያውን ደብዳቤ በመንፈስ አነሳሽነት በጻፈ ጊዜ ይሖዋ አገልጋዮቹን ለእያንዳንዱ ጥቃቅን ስህተት ተጠያቂ እንደማያደርጋቸው ተረድቶ ነበር። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ፍቅራዊ ስሜት ያለው፣ አሳቢ፣ ቸርና ርኅሩኅ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሚወዱትና በእውነት ለሚያመልኩት ሁሉ የጠለቀ ፍቅር ያለው አባት እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት ጽፏል።—1 ዮሐንስ 4:8
ይሖዋ ለእርሱ በምናቀርበው አገልግሎት ደስ ይለዋል
አምላክ ስንወለድ ጀምሮ ያሉብንን ድክመቶችና ጉድለቶች ስለሚያውቅ እነዚህን ነገሮች ግምት ውስጥ ያስገባል። ዳዊት “ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፣ መዝሙር 103:14
እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ” ሲል ጽፏል። አስተዳደጋችን በስብዕናችን ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ ይገነዘባል። እንዲያውም እኛ ራሳችንን ከምናውቀው የበለጠ ያውቀናል።—ብዙዎቻችን ከአሁኑ የተለየን ሰዎች መሆን እንደምንፈልግ ነገር ግን ያሉብንን ጉድለቶች ሙሉ በሙሉ ታግለን ማሸነፍ እንደማንችል ያውቃል። ያለንበት ሁኔታ ሐዋርያው ጳውሎስ ከነበረበት ሁኔታ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ጳውሎስ “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም” በማለት ጽፏል። ሁላችንም በተመሳሳይ ትግል አለብን። አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ያለው አመለካከት የሚኮንን ልብ እንዲኖረን ሊያደርግ ይችላል።—ሮሜ 7:19
አንድ ነገር ፈጽሞ አትዘንጋ:- ዋናው ነገር እኛ ለራሳችን ያለን አመለካከት ሳይሆን ይሖዋ ለእኛ ያለው አመለካከት ነው። ምንጊዜም እሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ጥረት የሚመለከተው እንዲሁ በይሁንታ ስሜት ሳይሆን ከልብ በመነጨ ደስታ ነው። (ምሳሌ 27:11) ምንም እንኳን ያከናወንነው ነገር በራሳችን ዓይን ሲታይ እዚህ ግባ የማይባል ቢመስልም ያሳየነው የፈቃደኝነት መንፈስና ያንን ለማድረግ የተነሳሳንበት ጤናማ የሆነ ዝንባሌ ያስደስተዋል። ይሖዋ የሚያየው የምናከናውነውን ነገር ብቻ አይደለም። ምን ማድረግ እንደምንፈልግ ይረዳልናል፣ ምኞታችንንና ፍላጎታችንን ያውቃል። ይሖዋ ልባችንን ሊያነብ ይችላል።—ኤርምያስ 12:3፤ 17:10
ለምሳሌ ያህል ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በተፈጥሮአቸው ዓይን አፋርና ቁጥብ ስለሆኑ ብዙም የሌሎችን ትኩረት መሳብ አይፈልጉም። እንዲህ ያሉት ሰዎች ምስራቹን ከቤት ወደ ቤት መስበክ ተፈታታኝ ሊሆንባቸው ይችላል። ሆኖም አምላክን ለማገልገልና ጎረቤቶቻቸውን ለመርዳት ስለሚፈልጉ ዓይን አፋር የሆኑት ሳይቀሩ ለጎረቤቶቻቸው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራሉ። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ በአገልግሎታቸው ያከናወኑት ጥቂት እንደሆነ ሊሰማቸውና ይህም ደስታቸውን ሊነጥቃቸው ይችላል። ልባቸው ለሕዝብ የሚያቀርቡት አገልግሎት ዋጋ የሚሰጠው እንዳልሆነ ይነግራቸው ይሆናል። ነገር ግን ይሖዋ እነዚህ ሰዎች በአገልግሎታቸው የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጥረት ሲመለከት ከልብ ይደሰታል። ከዚህም በላይ የተዘራው የእውነት ዘር መቼና የት እንደሚበቅል፣ እንደሚያድግና ፍሬ እንደሚያፈራ እርግጠኞች ሊሆኑ አይችሉም።—መክብብ 11:6፤ ማርቆስ 12:41-44፤ 2 ቆሮንቶስ 8:12
ሌሎች ምሥክሮች ደግሞ ለረጅም ጊዜ በሚቆይ ህመም እየተሰቃዩ ወይም ደግሞ ዕድሜያቸው ገፍቶ ይሆናል። አዘውትረው ስብሰባ የሚገኙት ከከባድ ስቃይና ጭንቀት ጋር ሊሆን ይችላል። ስለ ስብከቱ ሥራ የሚቀርቡ ንግግሮችን ሲሰሙ በፊት ያደርጉት የነበረውንና አቅማቸው ቢፈቅድላቸው ኖሮ አሁንም ሊሠሩት የሚፈልጉትን ነገር ሊያስታውሳቸው ይችላል። የሚፈልጉትን ያህል ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ ስለማይችሉ ይህ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲያድርባቸው ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም ይሖዋ ታማኝነታቸውንና ጽናታቸውን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው የተረጋገጠ ነው። እስከ መጨረሻው ታማኝ ሆነው እስከተገኙ ድረስ ሥራቸውን በፍጹም አይረሳም።—መዝሙር 18:25 NW ፤ 37:28
‘ልባችንን ማሳረፍ’
ዮሐንስ በእርጅና ዘመኑ የአምላክን አሳቢነት በጥልቅ ሳይገነዘብ አይቀርም። “እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል” ብሎ እንደጻፈ አስታውስ። ከዚህም በላይ ዮሐንስ ‘ልባችንን እንድናሳርፍ’ አበረታቶናል። ዮሐንስ ‘ልባችንን ማሳረፍ’ ሲል ምን ማለቱ ነው?
ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ “ማሳረፍ” የሚል ፍቺ የተሰጠው የግሪክኛ ግስ ትርጉም “የማሳመን ችሎታን መጠቀም፣ ማሸነፍ ወይም መርታት፣ ማሳመን” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። በሌላ አባባል ልባችንን ማሳረፍ ሲባል ልባችንን መርታት እንዲሁም ይሖዋ እንደሚወደን ልባችንን ማሳመን ማለት ነው። እንዴት?
ቀደም ሲል በዚህ ርዕስ የተጠቀሰው ፍሪትስ ሽማግሌ በመሆን በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ከ25 ለሚበልጡ ዓመታት አገልግሏል። የግል ጥናት ማድረጉ ይሖዋ እንደሚወድደው ልቡን ለማሳመን አስችሎታል። “ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስንና የተለያዩ ጽሑፎችን በጥንቃቄ አጠናለሁ። እንዲህ ማድረጌ ስላለፈው ነገር ከማብሰልሰል ይልቅ አስደናቂ ስለሆነው የወደፊት ተስፋችን የጠራ አመለካከት እንድይዝ ረድቶኛል። አልፎ አልፎ ያለፈውን ጊዜ እያሰብሁ በሐዘን እዋጥና ይሖዋ ፈጽሞ ሊወደኝ እንደማይችል ሆኖ ይሰማኛል። ይሁን እንጂ በአጠቃላይ
ሲታይ ዘወትር የማደርገው የግል ጥናት ልቤን እንዳጠነከረልኝ፣ እምነቴን እንደጨመረልኝ እንዲሁም ደስተኛና ሚዛናዊ ሰው ሆኜ እንድቀጥል እንደረዳኝ ተገንዝቤአለሁ።”መጽሐፍ ቅዱስ ማንበባችን እንዲሁም ባነበብነው ነገር ላይ ጊዜ ወስደን ማሰላሰላችን ብቻውን ያለንበትን ሁኔታ ላይለውጠው እንደሚችል አይካድም። ነገር ግን ስለ ራሳችን ሁኔታ ያለንን አመለካከት ሊለውጠው ይችላል። ቃሉን በማንበብ የአምላክ አስተሳሰብ ወደ ልባችን ጠልቆ እንዲገባ ማድረጋችን ልክ እንደ እርሱ እንድናስብ ይረዳናል። ከዚህም በላይ ጥናት የአምላክን አሳቢነት በይበልጥ እንድንገነዘብ ያስችለናል። ስለዚህ ይሖዋ በልጅነታችን በነበረን ሁኔታም ሆነ ዛሬ ባለብን የአቅም ገደብ ምክንያት እንደ ጥፋተኛ እንደማይቆጥረን ቀስ በቀስ እየገባን ሊመጣ ይችላል። ይሖዋ ብዙዎቻችን የተሸከምናቸውን ስሜታዊም ሆኑ አካላዊ ሸክሞች ራሳችን ፈልገን ያመጣናቸው እንዳልሆኑ ስለሚያውቅ በፍቅር ሁኔታውን ከግምት ውስጥ ያስገባልናል።
ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ማርጋሬትስ? ይሖዋን ይበልጥ እያወቀችው ስትሄድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷ እርሷንም በጣም ጠቅሟታል። እሷም እንደ ፍሪትስ ስለ አባት ያላትን አመለካከት እንደገና ማጤን አስፈልጓታል። ማርጋሬት በጥናቷ ያገኘችውን እውቀት ለማዋሃድ የረዳት ጸሎት ነው። “መጀመሪያ ላይ ይሖዋን እንደ ቅርብ ጓደኛዬ አድርጌ እመለከተው ነበር። ምክንያቱም አፍቃሪ ከሆነ አባት ይልቅ አፍቃሪ የሆኑ ጓደኞች ስለነበሩኝ እንዲህ ማድረጉ አልከበደኝም። ቀስ በቀስ ግን ስሜቴን፣ ጥርጣሬዬን፣ ስጋቴን፣ እንዲሁም ጭንቀቴን ግልጥልጥ አድርጌ ለይሖዋ መንገርን ተማርኩ። ስለ እርሱ የተማርኳቸውን አዳዲስ ነገሮች አንድ ላይ እያገናዘብኩ በተደጋጋሚ በጸሎት አነጋግረው ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለይሖዋ ያለኝ ስሜት እያደገ በመሄዱ አሁን እሱን እንደ አፍቃሪ አባቴ አድርጌ ለመመልከት እምብዛም አይከብደኝም።”
ከሁሉም ዓይነት ጭንቀት ነፃ መሆን
ይህ ክፉና አሮጌ ሥርዓት እስካለ ድረስ ማንኛችንም ብንሆን ከጭንቀት ነፃ የሆነ ሕይወት ይኖረናል ብለን መጠበቅ አንችልም። ይህም ማለት አንዳንድ ክርስቲያኖች የጭንቀት ወይም የጥርጣሬ ስሜት እንደገና ሊቀሰቀስባቸውና ይህም ሊያስጨንቃቸው ይችላል ማለት ነው። ሆኖም ይሖዋ ጤናማ የሆነውን ውስጣዊ ዝንባሌያችንና በአገልግሎቱ የምናከናውነውን ትጋት የተሞላበት ሥራ እንደሚያውቅ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር ፈጽሞ አይረሳም።—ዕብራውያን 6:10
በመሲሐዊው መንግሥት ሥር በሚተዳደረው መጪው አዲስ ምድር ውስጥ የታመኑ የሰው ልጆች በሙሉ የሰይጣን ሥርዓት ከሚያመጣው ማንኛውም ሸክም ነፃ እንደሚሆኑ በትምክህት ሊጠባበቁ ይችላሉ። እንዴት ያለ ግልግል ይሆናል! በዚያን ጊዜ ይሖዋ ምን ያህል አሳቢ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ እናገኛለን። እስከዚያው ድረስ ግን ሁላችንም ‘እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ እንደሆነና ሁሉንም እንደሚያውቅ’ እርግጠኞች እንሁን።—1 ዮሐንስ 3:20
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሞቹ ተለውጠዋል።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ይሖዋ ጨካኝ ገዥ ሳይሆን ፍቅራዊ ስሜት ያለው፣ አሳቢና ርኅሩኅ አባት ነው
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክን ቃል ማጥናት ልክ እንደ እርሱ እንድናስብ ይረዳናል