በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት ሌሎችን ወደ አምላክ ይመራል

ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት ሌሎችን ወደ አምላክ ይመራል

የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት

ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት ሌሎችን ወደ አምላክ ይመራል

ይሖዋ ታላቅ ጥበብና ማስተዋል በመስጠት ዮሴፍን ባርኮታል። (ሥራ 7:​10) ከዚህም የተነሳ የዮሴፍ ማስተዋል ‘በፈርዖንና በሎሌዎቹ ፊት መልካም ሆኖ ታይቷል።’​—⁠ዘፍጥረት 41:​37

ይሖዋ ዛሬም በተመሳሳይ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ሕዝቦቹ ጥበብና ማስተዋል እንዲያገኙ ያደርጋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17) የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ሥራ ላይ ሲያውሉ እንዲህ ያለው ጥበብና ማስተዋል መልካም ፍሬ ያስገኛል። ከዚምባብዌ የተገኙት የሚከተሉት ተሞክሮዎች እንደሚያረጋግጡት አብዛኛውን ጊዜ ምሥክሮቹ የሚያሳዩት ጥሩ ባሕርይ ‘በሚመለከቷቸው ሰዎች ዘንድ መልካም ሆኖ’ ይገኛል።

• አንዲት ሴት የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ጎረቤቶች ነበሯት። ምንም እንኳን ምሥክሮቹን ባትወዳቸውም አኗኗራቸውን በተለይ ደግሞ የቤተሰብ ሕይወታቸውን ታደንቅ ነበር። ባልና ሚስቱ ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸውና ልጆቻቸውም ታዛዦች እንደሆኑ ተገነዘበች። በተለይ ባልየው ሚስቱን በጣም እንደሚወዳት አስተውላ ነበር።

በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች አንድ ባል ሚስቱን የሚያፈቅራት ከሆነ “ውጭ ውጭ እንዳይል” ሚስቱ መድኃኒት አድርጋበት መሆን አለበት ብሎ ማመን የተለመደ ነው። ስለዚህ ሴትየዋ ወደ ምሥክሯ ቀርባ “ያንቺ ባል የሚወድሽን ያህል ባሌ እንዲወደኝ እባክሽ የተጠቀምሽበትን መስተፋቅር ስጭኝ” በማለት ጠየቀቻት። ምሥክሯም “እሺ፣ ነገ ከሰዓት በኋላ ይዤልሽ እመጣለሁ” አለቻት።

በሚቀጥለው ቀን እህት “መስተፋቅሩን” ይዛ ወደ ጎረቤቷ አመራች። “መስተፋቅሩ” ምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍ ነበር። እህት ከእውቀት መጽሐፍ “አምላክን የሚያስከብር ቤተሰብ መመሥረት” በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን ሀሳብ ካወያየቻት በኋላ እንዲህ አለቻት:- “እኔና ባለቤቴ ‘ውጭ ውጭ እንዳንል’ የተጠቀምንበት ‘መስተፋቅር’ ይህ ነው። በጣም የምንዋደደውም ለዚህ ነው።” ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረና ሴትዮዋ ፈጣን እድገት በማድረግ ራሷን ለይሖዋ መወሰኗን በውኃ ጥምቀት አሳየች።

• ዚምባብዌን ከሞዛምቢክ በሚያዋስናት ሰሜናዊ ምሥራቅ ጠረፍ አካባቢ በሚገኝ አንድ ትንሽ ጉባኤ ውስጥ የተመደቡ ሁለት ልዩ አቅኚዎች ለሁለት ሳምንት ያህል ከቤት ወደ ቤት አላገለገሉም ነበር። ለምን? ምክንያቱም ሰዎች እነርሱ የሚሉትን ለመስማት ወደ ቤታቸው ይጎርፉ ነበር። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ አንደኛው አቅኚ ሲያብራራ እንዲህ ብሏል:- “ፍላጎት ላሳየ አንድ ሰው ሳምንታዊ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት የአሥራ አምስት ኪሎ ሜትር ጉዞ እናደርግ ነበር። ሰውዬው ያለበት ቦታ መድረስ ቀላል አልነበረም። በጭቃ ውስጥ እየዳከርን መሄድና እስከ አንገታችን የሚደርስ ውኃ ያላቸውን ሞገደኛ ወንዞች መሻገር ነበረብን። ልብሶቻችንንና ጫማዎቻችንን በጭንቅላታችን ላይ አስተካክለን በማስቀመጥ ወንዙን ከተሻገርን በኋላ እንደገና ለባብሰን እንሄድ ነበር።

“የምናስጠናው ሰው ጎረቤቶች ባሳየነው ቅንአት በጣም ተደነቁ። ሁኔታውን ካስተዋሉት ሰዎች መካከል አንዱ የአካባቢው ሃይማኖታዊ ድርጅት መሪ ነበር። ለተከታዮቹ እንዲህ አላቸው:- ‘እንደ ሁለቱ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ቀናተኞች መሆን አትፈልጉም?’ በሚቀጥለው ቀን ይህን ያህል ጽናት ያሳየንበትን ምክንያት ለማወቅ ሲሉ ብዙ ተከታዮቹ ወደ ቤታችን መጡ። በተጨማሪም በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ወደ እኛ የመጡት ሰዎች በጣም ብዙ ከመሆናቸው የተነሣ ምግባችንን እንኳን ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ አልነበረንም!”

በእነዚህ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ወደ አቅኚዎቹ ቤት ከመጡት ሰዎች መካከል የሃይማኖት መሪውም ይገኝበት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና የቀረበለትን ግብዣ ሲቀበል አቅኚዎቹ ምን ያህል እንደተደሰቱ ገምቱ!