በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕንድ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት እምነት መገንባት

ሕንድ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት እምነት መገንባት

ከሚያምኑት ወገን ነን

ሕንድ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት እምነት መገንባት

ሕንድ በሰሜን ከሚገኘውና በበረዶ ከተሸፈነው ባለግርማ የሂማልያ ተራራ አንስቶ በደቡብ እስካሉት ሞቃታማዎቹ የሕንድ ውቅያኖስ የባሕር ዳርቻዎች ድረስ የተለያዩ መልክዓ ምድራዊና ሃይማኖታዊ ገጽታዎች ባለቤት የሆነች አገር ናት። ከአንድ ቢልዮን በላይ ከሆኑት ነዋሪዎቿ መካከል 83 በመቶ የሚሆኑት የሒንዱ እምነት ተከታዮች ናቸው። አሥራ አንድ በመቶ የሚሆኑት ሙስሊሞች ሲሆኑ የተቀሩት የሕዝበ ክርስትና፣ የሲክ፣ የቡድሃ እንዲሁም የጄንስ እምነት ተከታዮች ናቸው። ሁሉም የአምልኮ ነጻነት አላቸው። “ሃይማኖት በሕንዳውያን አኗኗር ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወታል” በማለት ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ገልጿል።

በሕንድ ከክርስቲያናዊ እምነታቸው ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ከ21,200 የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። በሌሎች የዓለም ክፍሎች እንደሚገኙት የእምነት አጋሮቻቸው በሕንድ ያሉትም የይሖዋ ምሥክሮች ጎረቤቶቻቸው የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲገነቡ መርዳቱን እንደ ልዩ መብት ይቆጥሩታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17) እስቲ በደቡብ ሕንድ ቼኒ በተባለ ቦታ የሚኖር አንድ ቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዴት እንደተማረ ተመልከት።

ይህ ቤተሰብ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከመገናኘቱ በፊት ራእይ እናያለን፣ በልሳን እንናገራለን እንዲሁም የታመሙትን እንፈውሳለን በሚል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ነበረው። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥና በሕዝቡ ዘንድ በሰፊው የሚታወቁ ከመሆናቸው የተነሣ የአካባቢው ነዋሪዎች አንዳንዶቹን የቤተሰቡን አባላት “ስዋሚ” ወይም “ጌታ” በማለት ይጠሯቸው ነበር። ሆኖም አንድ ቀን አንድ የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤታቸው ሄዶ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንጂ ብዙውን ጊዜ ሰዎች እንደሚያምኑት ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳልሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳያቸው። በተጨማሪም የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነና ይህችን ምድር ወደ ገነትነት የመለወጥ ዓላማ እንዳለው አስረዳቸው።​—⁠መዝሙር 83:​18 NW ፤ ሉቃስ 23:​43፤ ዮሐንስ 3:​16

የቤተሰቡ አባላት ለአምላክ ቃል አክብሮት ስለነበራቸውና የሰሙትንም ነገር ስለወደዱት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ተስማሙ። ከዚህ የተነሣ በቤተ ክርስቲያናቸው የሚያውቋቸው ሰዎች ቢያላግጡባቸውም የቤተሰቡ አባላት ጥናቱን ለመቀጠል ወሰኑ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው እውቀት እየጨመረና እምነታቸው እየጎለበተ ሲሄድ ከሐሰት ሃይማኖታዊ ልማዶች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋረጡ። ዛሬ ሦስቱ የቤተሰቡ አባላት ቀናተኛ የተጠመቁ አስፋፊዎች ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ አመቺ በሆነላት ጊዜ ሁሉ ረዳት አቅኚ በመሆን ታገለግላለች።

እንቅፋቶችን ለማሸነፍ የሚያስችል እምነት

ፑንጃብ በሚገኝ አንድ መንደር ውስጥ የሚኖር ሱንደር ላል የተባለ ወጣት የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች ማካፈል ትልቅ እምነትና ድፍረት ጠይቆበታል። (ማቴዎስ 24:​14) ይህ ሊሆን የቻለበት አንደኛው ምክንያት ብዙ አማልክት የሚያመልኩ ቤተሰቦቹንና መንደሩን ትቶ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ለማምለክ መወሰኑ ሲሆን ሌላው ደግሞ ሱንደር ላል እግር አልነበረውም።

እስከ 1992 ድረስ የሱንደር ላል ሕይወት ነጋ ጠባ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ብቻ የተወሰነ ነበር። የአንድ ዶክተር ረዳት ሆኖም ይሠራ የነበረ ሲሆን ከዚያ ሲወጣ በተመረጠው ደብተራ አማካኝነት ለተለያዩ አማልክት በሚቀርበው አምልኮ ከቤተሰቡ ጋር ይካፈላል። ሆኖም አንድ ቀን አመሻሹ ላይ የባቡር ሃዲድ ሲያቋርጥ ወደቀና ባቡሩ ሁለቱንም እግሮቹን ከጭኑ ቆረጠው። በሕይወት ቢተርፍም ተስፋው ጨልሞበት ነበር። ሱንደር ላል በከፍተኛ ጭንቀት ከመዋጡ የተነሳ ራሱን ለመግደል ማሰቡ አያስገርምም። ምንም እንኳን ቤተሰቦቹ የድጋፍ ምንጭ ቢሆኑለትም የወደፊት ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ይመስል ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ የይሖዋ ምሥክር አምላክ ምድርን አስደሳች ገነት ለማድረግ እንዲሁም ለሚወዱትና ለሚፈሩት ሰዎች የተሟላ ጤንነት ለመስጠት ዓላማ እንዳለው ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳየው። ሱንደር ላል መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት በመስማማት ለአንድ ዓመት ያህል በትጋት አጠና። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ግብዣ ቀርቦለት ስለነበር በጓደኛው ብስክሌት ላይ ተፈናጥጦ ወደ ስብሰባው ሄደ። ምንም እንኳን ጉዞው አስቸጋሪ ቢሆንም ውጤቱ ግን እጅግ የሚክስ ነበር። በስብሰባው ላይ የአምላክ ቃል የያዘውን ተስፋ ከልብ የሚያምኑ እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች ሲመለከት በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ያገኘው ትምህርት እውነት መሆኑን አረጋገጠ።

ከዚህ በኋላ ሱንደር ላል ምሥራቹን ለጎረቤቶቹ ማካፈል ጀመረና በ1995 ተጠመቀ። ወትሮም የሚሄደው እየተንፏቀቀ በመሆኑ በዚሁ መንገድ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት መካፈል ጀመረ። በአሁኑ ጊዜ ግን በእጅ ለማሽከርከር የሚያመች ባለ ሦስት እግር ብስክሌት ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ በስጦታ አግኝቷል። ለባለ ሦስት እግሩ ብስክሌት ምሥጋና ይግባውና አሁን ብዙም የሰው ድጋፍ ሳያስፈልገው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የ12 ኪሎ ሜትር ጉዞ ማድረግ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ወደ ስብሰባው ሲሄድ ኃይለኛ ንፋስ ያዘለ ዝናብ ያጋጥመዋል። በሌላ ጊዜ ደግሞ የአየሩ ሙቀት ከ43 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ይደርሳል።

ሱንደር ላል በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ ከመገኘቱም በተጨማሪ እውነተኛ አምላክ በሆነው በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ለመገንባት እርዳታ የሚፈልጉ ሌሎች ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናል። እንዲያውም ከቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ መካከል ሰባት የሚያክሉት አሁን የተጠመቁ አስፋፊዎች ሆነዋል። ከዚህም በላይ እሱ የመሰከረላቸው ሦስት ሰዎች ከሌሎች ምሥክሮች ጋር ጥናታቸውን ቀጥለው በአሁኑ ጊዜ ራሳቸውን ወስነው ተጠምቀዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ከሆነ ‘እምነት ለሁሉ አይደለም።’ (2 ተሰሎንቄ 3:​2) ሆኖም ቋሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ‘ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁትን’ ሰዎች እምነት ሊገነባ ይችላል። (ሥራ 13:​48) እንዲህ ያለው ጥናት በሕንድ ውስጥ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሰዎች በአስደናቂው የወደፊት ተስፋ ላይ ሙሉ እምነት በማሳደር መንፈሳዊ ዓይኖቻቸው እንዲበሩ አድርጓል።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አፍጋኒስታን

ፓኪስታን

ኔፓል

ቡታን

ቻይና

ባንግላዴሽ

ማያንማር

ላኦስ

ታይላንድ

ቬትናም

ካምቦዲያ

ስሪ ላንካ

ሕንድ

[ምንጭ]

Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.