በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአምላክ ቤት ውስጥ የሚገኝ የለመለመ የወይራ ዛፍ

በአምላክ ቤት ውስጥ የሚገኝ የለመለመ የወይራ ዛፍ

በአምላክ ቤት ውስጥ የሚገኝ የለመለመ የወይራ ዛፍ

በእስራኤል ምድር የሚበቅል ዘላለማዊ ሊባል የሚችል አንድ ዛፍ አለ። ከተቆረጠ በኋላ እንኳ ጉቶው ወዲያውኑ ያቆጠቁጣል። እንዲሁም ፍሬው በሚሰበሰብበት ጊዜ ለምግብ፣ ለመብራት፣ ለንጽሕናና ለቅባት የሚሆን የተትረፈረፈ ዘይት በመስጠት ባለቤቱን በብዙ ይክሰዋል።

“አንድ ጊዜ ዛፎች በላያቸው ንጉሥ ሊያነግሡ ሄዱ” የሚል አንድ ጥንታዊ ምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በመሳፍንት መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። በአንደኛ ደረጃ የመረጡት የትኛውን የጫካ ዛፍ ነው? አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም ከሚችለውና ምርት በገፍ ከሚሰጠው ከወይራ ዛፍ ሌላ ሊመርጡ እንደማይችሉ የታወቀ ነው።​—⁠መሳፍንት 9:​8

ከ3, 500 ዓመታት በፊት ነቢዩ ሙሴ እስራኤልን ‘ወይራ የሞላበት መልካም ምድር’ በማለት ገልጾታል። (ዘዳግም 8:​7, 8) ዛሬም ቢሆን በስተ ሰሜን ከሚገኘው የሄርሞን ተራራ ግርጌ አንስቶ በስተ ደቡብ እስከሚገኙት የቤርሺባ ዳርቻዎች ድረስ ባለው ገፀምድር ላይ ዕጅብ ብለው የበቀሉ የወይራ ዛፎች ይታያሉ። አሁንም ድረስ የሻሮን ሜዳማ የባሕር ዳርቻ፣ ዓለታማ የሆኑት የሰማርያ ኮረብታዎችና ለሙ የገሊላ ሸለቆ በወይራ ዛፎች አጊጠው ይታያሉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የወይራ ዛፍን በተደጋጋሚ ጊዜያት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተጠቅመውበታል። ይህ ዛፍ ያሉት የተለያዩ ገፅታዎች የአምላክን ምሕረት፣ የትንሣኤ ተስፋንና ደስተኛ የቤተሰብ ኑሮን በምሳሌያዊ መንገድ ለመግለጽ አገልግለዋል። የወይራ ዛፍን ቀረብ ብሎ መመርመራችን እነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅሶች ያላቸውን ትርጉም እንድንረዳና ከሌሎች ፍጥረታት ጋር ሆኖ ለሠሪው ውዳሴ ለሚያቀርበው ለዚህ ልዩ ዛፍ ያለንን አድናቆት እንድናሳድግ ይረዳናል።​—⁠መዝሙር 148:​7, 9

ውልግድግድ ያለ ቅርጽ ያለው የወይራ ዛፍ

የወይራ ዛፍ እንዲሁ ሲያዩት ያን ያህል የሚስብ አይደለም። ታላቅ ግርማ እንደተላበሱት እንደ አንዳንዶቹ የሊባኖስ ዝግባ ዛፎች ሰማይ ጠቀስ አይደለም። እንጨቱ የጥድ ዛፍን ያህል ተወዳጅ አይደለም፤ አበቦቹ እንደ ለውዝ ዛፍ አበባ ለዓይን ማራኪ አይደሉም። (መኃልየ መኃልይ 1:​17፤ አሞጽ 2:​9) የወይራ ዛፍ ምሥጢር ያለው ለዓይን በማይታየው ከመሬት በታች ባለው ክፍሉ ላይ ነው። ለዛፉ ምርታማነትና ረዥም ዕድሜ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ከመሬት በታች እስከ 6 ሜትር የሚያድገውና ወደ ጎን ከዚህ የበለጠ ሰፊ አካባቢ የሚሸፍነው ሥሩ ነው።

በድርቅ ጊዜ ከሸለቆው በታች ያሉት ሌሎች ዛፎች በውኃ እጦት ሲደርቁ ኮረብታው አካባቢ ያሉት የወይራ ዛፎች ግን ሥሮቻቸው ድርቁን ተቋቁመው እንዲያልፉ ይረዷቸዋል። ውልግድግድ ያለ ቅርጽ ያለው የዛፉ ግንድ እንዲሁ ሲታይ ከማገዶነት ሌላ ጥቅም ያለው ባይመስልም ሥሮቹ ለበርካታ መቶ ዘመናት ፍሬ መስጠቱን እንዲቀጥል ያስችሉታል። ይህ ውልግድግድ ያለ ዛፍ የሚፈልገው ነገር ከአረም ወይም ጎጂ ነፍሳትን ከሚስቡ ሌሎች እጽዋት ነፃ የሆነ ለመብቀል የሚያስችለው ሰፋ ያለ ቦታና በቀላሉ አየር የሚያስገባ አፈር ብቻ ነው። እነዚህ ቀላል የሆኑ ነገሮች ከተሟሉለት አንዱ ዛፍ በአንድ ዓመት ውስጥ እስከ 57 ሊትር የሚደርስ ዘይት ይሰጣል።

የወይራ ዛፍን በእስራኤላውያን ዘንድ ተወዳጅ ያደረገው ነገር ውድ የሆነው ዘይቱ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ለቤታቸው ብርሃን እንዲሰጥላቸው የወይራ ዘይትን መጥጠው ወደ ላይ የሚስቡ ክሮች ያሉት ኩራዝ ይጠቀሙ ነበር። (ዘሌዋውያን 24:​2) የወይራ ዘይት ምግብ ለማብሰልም እጅግ አስፈላጊ ነበር። ቆዳን ከፀሐይ የሚከላከል ከመሆኑም በላይ እስራኤላውያን ልብሳቸውን ለማጠብ እንደ ሳሙና አድርገው ይጠቀሙበት ነበር። ጥራ ጥሬ፣ ወይንና ወይራ ምድሪቱ በዋነኛነት የምታበቅላቸው ሰብሎች ነበሩ። በመሆኑም የወይራ ዛፍ ሳያፈራ መቅረቱ በአንድ እስራኤላዊ ቤተሰብ ትልቅ ችግር ያስከትል ነበር።​—⁠ዘዳግም 7:​13፤ ዕንባቆም 3:​17

ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ የወይራ ዘይት እጥረት አይኖርም ነበር። ሙሴ የተስፋይቱን ምድር በተመለከተ ‘የወይራ ምድር’ በማለት የተናገረው በአካባቢው በአብዛኛው የሚለማው የወይራ ዛፍ ስለሆነ ሊሆን ይችላል። የአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ሊቀ ተፈጥሮ የሆኑት ኤች ትሪስትራም የወይራ ዛፍን “የአገሪቱ ዓይነተኛ መለያ” በማለት ገልጸውታል። የወይራ ዘይት ትልቅ ዋጋ ያለውና በገፍ የሚገኝ በመሆኑ በሜዲትራኒያን አካባቢ ተቀባይነት ያለው ገንዘብ ሆኖ አገልግሏል። ኢየሱስ ክርስቶስም ‘በመቶ ማድጋ ዘይት’ ተሰልቶ ስለተገለጸ ዕዳ ተናግሯል።​—⁠ሉቃስ 16:​5, 6

“እንደ ወይራ ቡቃያ”

ጠቃሚ የሆነው የወይራ ዛፍ መለኮታዊ በረከቶችን ለመግለጽ ተስማሚ ነው። ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው የሚባረከው እንዴት ነው? መዝሙራዊው “ሚስትህ በቤትህ እልፍኝ ውስጥ እንደሚያፈራ ወይን ናት” ካለ በኋላ “ልጆችህ በማዕድህ ዙሪያ እንደ ወይራ ቡቃያ ናቸው” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 128:​3) እዚህ ላይ የ“ወይራ ቡቃያ” የተባሉት ምንድን ናቸው? መዝሙራዊው ከልጆች ጋር ያመሳሰላቸውስ ለምንድን ነው?

የወይራ ዛፍ ያለማቋረጥ ከግንዱ ሥር አዳዲስ ችግኞች የሚበቅሉ መሆናቸው ከሌሎች ዛፎች የተለየ ያደርገዋል። a ዋነኛው ግንድ ረጅም ዘመን በማስቆጠሩ የተነሳ እንደ ቀድሞው ፍሬ መስጠቱን በሚያቆምበት ጊዜ አራሾቹ የተወሰኑት ቡቃያዎች ወይም ችግኞች አድገው የዛፉ ዋና አካል እንዲሆኑ ሳይነኳቸው ይተዋቸዋል። ከጊዜ በኋላ ዋነኛው ዛፍ በማዕድ ዙሪያ እንዳሉ ልጆች አዲስና ጠንካራ በሆኑ ሦስት ወይም አራት ግንዶች ይከበባል። የእነዚህ ቡቃያዎች ሥር ከዋነኛው ግንድ ጋር አንድ ሲሆን እነርሱም ጥሩ የወይራ ፍሬ ያፈራሉ።

ይህ የወይራ ዛፍ ጉልህ ባሕርይ ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆች በወላጆቻቸው ጠንካራ መንፈሳዊ ሥር በመጠቀም በእምነት እንዴት ጠንካራ ሆነው ሊያድጉ እንደሚችሉ ጥሩ አድርጎ ያሳያል። ልጆች እያደጉ ሲሄዱ ፍሬ በማፍራቱና ወላጆቻቸውን በመርዳቱ ሥራ ተካፋይ ይሆናሉ። ወላጆች ልጆቻቸው ከጎናቸው ሆነው ይሖዋን ሲያገለግሉ ሲመለከቱ ደስ ይላቸዋል።​—⁠ምሳሌ 15:​20

“ዛፍ . . . ተስፋ አለው”

ይሖዋን የሚያገለግል አንድ በእድሜ የገፋ አባት ለአምላክ ባደሩ ልጆቹ ይደሰታል። ይሁን እንጂ እነዚህ ልጆች ከጊዜ በኋላ አባታቸው ‘የምድሩን ሁሉ መንገድ ሲሄድ’ ያዝናሉ። (1 ነገሥት 2:​2) በቤተሰብ ላይ የሚደርሰውን እንዲህ ያለውን ሃዘን ለመቋቋም እንድንችል ለመርዳት መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ትንሣኤ እንዳለ ማረጋገጫ ይሰጣል።​—⁠ዮሐንስ 5:​28, 29፤ 11:​25

በርካታ ልጆች የነበሩት ኢዮብ የሰው ልጅ ዕድሜ አጭር እንደሆነ በሚገባ ያውቅ ነበር። የሰው ልጅን እድሜ ቶሎ ከሚረግፍ አበባ ጋር አመሳስሎታል። (ኢዮብ 1:​2፤ 14:​1, 2) ኢዮብ መቃብርን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለቅቆት ሊወጣ እንደሚችል መሸሸጊያ አድርጎ በመመልከት ከደረሰበት ሥቃይ ለመገላገል ሲል ሞትን ተመኝቶ ነበር። “በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን?” በማለት ኢዮብ ጠየቀ። ከዚያም በእርግጠኝነት “መለወጤ እስኪመጣ ድረስ፣ የሰልፌን ዘመን ሁሉ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር። በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፤ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር” በማለት መልሷል።​—⁠ኢዮብ 14:​13-15

ኢዮብ፣ አምላክ ከመቃብር እንደሚጠራው ያለውን የጸና እምነት በምሳሌ የገለጸው እንዴት ነው? በአንድ ዛፍ ሲሆን ከሰጠው መግለጫ ለመረዳት እንደሚቻለው የጠቀሰው የወይራ ዛፍን ሳይሆን አይቀርም። ኢዮብ “ዛፍ ቢቆረጥ ደግሞ ያቆጠቁጥ ዘንድ፣ . . . ተስፋ አለው” በማለት ተናገረ። (ኢዮብ 14:​7) አንድ የወይራ ዛፍ ሊቆረጥ ይችላል፤ ሆኖም ስለተቆረጠ ብቻ ሙሉ በሙሉ አይጠፋም። ከሥሩ ካልተነቀለ በስተቀር አይሞትም። ሥሩ ምንም እስካልሆነ ድረስ ዛፉ እንደገና በአዲስ ጉልበት ሊያቆጠቁጥ ይችላል።

ለረዥም ጊዜ የቆየ ድርቅ አን​ድን ብዙ ዘመን ያስቆጠረ የወይራ ዛፍ ሊያደርቀው ቢችልም የደረቀው ዛፍ ተመልሶ ሊለመልም ይችላል። “ሥሩም በምድር ውስጥ ቢያረጅ፣ ግንዱም በመሬት ውስጥ ቢሞት፣ ከውኃ ሽታ የተነሣ ያቆጠቁጣል፤ እንደ [“አዲስ፣” NW ] አትክልት ቅርንጫፍ ያወጣል።” (ኢዮብ 14:​8, 9) ኢዮብ ይኖር የነበረው አቧራ በበዛበት ደረቅ ምድር ስለነበር የደረቁና የሞቱ የሚመስሉ በርካታ ያረጁ የወይራ ዛፍ ጉቶዎች ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ዝናብ መዝነብ ሲጀምር “የሞተው” ዛፍ ሕይወት ሊዘራና ልክ እንደ አንድ “አዲስ አትክልት” አዲስ ግንድ ከሥሩ ሊያወጣ ይችላል። እንዲህ ያለው አስደናቂ የተሃድሶ ሂደት አንድን ቱኒዝያዊ ጓሬ ተክል አጥኚ “የወይራ ዛፎች ዘላለማውያን ናቸው ቢባል ይቀላል” እንዲሉ አድርጓቸዋል።

የደረቀበት የወይራ ዛፍ እንደገና የሚያብብበትን ጊዜ ለማየት እንደሚጓጓ ገበሬ ይሖዋም የታመኑ አገልጋዮቹን ከሞት ለማስነሳት ከፍተኛ ጉጉት አለው። አብርሃም እና ሣራ፣ ይስሐቅ እና ርብቃ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ታማኝ አገልጋዮቹ ወደ ሕይወት የሚመለሱበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃል። (ማቴዎስ 22:​31, 32) ሙታን ሲነሱ መቀበልና እንደገና የተሟላና ፍሬያማ የሆነ ሕይወት ሲመሩ መመልከቱ ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል!

ምሳሌያዊው የወይራ ዛፍ

ይሖዋ የማያዳላ መሆኑና የትንሣኤ ዝግጅት ማድረጉ ምሕረቱን የሚያንጸባርቅ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎች ዘራቸው ወይም አስተዳደጋቸው ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ምሕረቱን እንዴት እንደዘረጋላቸው ለማስረዳት የወይራ ዛፍን እንደ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሟል። አይሁዳውያን ለብዙ መቶ ዘመናት ‘የአብርሃም ዘር’ ማለትም አምላክ የመረጣቸው ሕዝቦች በመሆናቸው ይኩራሩ ነበር።​—⁠ዮሐንስ 8:​33፤ ሉቃስ 3:​8

በአይሁድ ብሔር ውስጥ መወለድ ብቻውን መለኮታዊ ሞገስ አያስገኝም። ሆኖም የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሁሉም አይሁዳውያን ነበሩ። በዚህም ምክንያት ተስፋ የተደረገበት የአብርሃም ዘር አባላት እንዲሆኑ በአምላክ ከተመረጡት ሰዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ መሆን ችለዋል። (ዘፍጥረት 22:​18፤ ገላትያ 3:​29) ጳውሎስ እነዚህን አይሁዳውያን ደቀ መዛሙርት ከምሳሌያዊ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፍ ጋር አመሳስሏቸዋል።

በትውልድ አይሁዳውያን የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ኢየሱስን አንቀበልም በማለታቸው የ“ታናሽ መንጋ” ወይም ‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ አባላት መሆን የሚችሉበት መብት አጡ። (ሉቃስ 12:​32፤ ገላትያ 6:​16) በዚህም ምክንያት ተቆርጠው እንደተጣሉ ምሳሌያዊ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች ሆኑ። በእነርሱ ቦታ ማን ተተካ? በ36 እዘአ አሕዛብ የአብርሃም ዘር ክፍል እንዲሆኑ ተመረጡ። ይሖዋ የበረሃ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎችን ቆርጦ በጓሮ የወይራ ዛፍ ላይ ያጣበቀ ያህል ነበር። ከአሕዛብ የመጡ ሰዎችም ተስፋ በተደረገበት የአብርሃም ዘር አባላት ውስጥ ተካትተዋል። ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች “የወይራ ዘይት ከሚወጣው ሥር ተካፋይ” መሆን ችለዋል።​—⁠ሮሜ 11:​17

አንድ ገበሬ ዱር ከሚገኝ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፍ ቆርጦ በጓሮ በሚገኝ የወይራ ዛፍ ላይ ማጣበቅ ፈጽሞ የማያስበው ነገር ከመሆኑም በላይ ‘ከተፈጥሮ ውጪ’ ነው። (ሮሜ 11:​24) “ጥሩውን ቅርንጫፍ ወስዶ በዱሩ ላይ በማጣበቅ አረቦቹ እንደሚሉት የዱሩን ማሸነፍ ይቻላል። ሆኖም ተቃራኒውን በማድረግ ጥሩ ውጤት ማግኘት አይቻልም” በማለት ዘ ላንድ ኤንድ ዘ ቡክ የተባለ ጽሑፍ ያብራራል። በተመሳሳይ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ይሖዋ ‘ለስሙ የሚሆንን ወገን ለመውሰድ ለመጀመሪያ ጊዜ ትኩረቱን ወደ አሕዛብ ሲያዞር’ ተገርመው ነበር። (ሥራ 10:​44-48፤ 15:​14) ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ የአምላክ ዓላማ አፈጻጸም በአንድ ብሔር ላይ የተመካ እንዳልሆነ በግልጽ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። “በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ” ነው።​—⁠ሥራ 10:​35

ታማኝ ያልሆኑት የአይሁድ የወይራ ዛፍ “ቅርንጫፎች” ተቆርጠው እንደተጣሉ ሁሉ የኩራት መንፈስ በማሳየትና ባለመታዘዝ በይሖዋ ሞገስ ታቅፎ ለመኖር አሻፈረኝ የሚል ሰው ተመሳሳይ ሁኔታ ሊደርስበት እንደሚችል ጳውሎስ አመልክቷል። (ሮሜ 11:​19, 20) ይገባናል የማንለውን የአምላክን ፍቅራዊ ደግነት አቅልለን መመልከት እንደማይገባን ይህ ጥሩ አድርጎ ያሳያል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 6:​1

ዘይት መቀባት

ቅዱሳን ጽሑፎች የወይራ ዘይትን ቃል በቃልም ሆነ በምሳሌያዊ ሁኔታ ስለመጠቀም ይናገራሉ። በጥንት ጊዜ ቁስልና ሰንበር ቶሎ እንዲድን ‘በዘይት እንዲለዝብ’ ይደረግ ነበር። (ኢሳይያስ 1:​6) ኢየሱስ በተናገረው በአንዱ ምሳሌው ላይ ደጉ ሳምራዊ ወደ ኢያሪኮ እየተጓዘ ሳለ መንገድ ላይ ባገኘው ሰው ቁስል ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶለታል።​—⁠ሉቃስ 10:​34

የወይራ ዘይት በአንድ ሰው ራስ ላይ ማፍሰስ መንፈስን የሚያድስና የሚያረጋጋ ነበር። (መዝሙር 141:​5 NW ) እንዲሁም ክርስቲያን ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ የታመመን ሰው በሚረዱበት ጊዜ ‘በይሖዋ ስም ዘይት ሊቀቡት’ ይችላሉ። (ያዕቆብ 5:​14) ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ ለታመመው የእምነት ባልደረባቸው የሚሰጡት በፍቅር ላይ የተመሠረተ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክርና የሚያቀርቡት ልባዊ ጸሎት መንፈስን ከሚያረጋጋ የወይራ ዘይት ጋር ተመሳስሎ ተገልጿል። በዕብራውያን የአነጋገር ዘይቤ ጥሩ የሆነ ሰው አንዳንድ ጊዜ “ንጹሕ የወይራ ዘይት” ተብሎ የሚገለጽ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።

“በእግዚአብሔር ቤት እንደ ለመለመ እንደ ወይራ ዛፍ”

ከላይ ከተዘረዘሩት ነጥቦች አንጻር የአምላክ አገልጋዮች ከወይራ ዛፍ ጋር ተመሳስለው መገለጻቸው የሚያስገርም አይሆንም። ዳዊት “በእግዚአብሔር ቤት እንደ ለመለመ እንደ ወይራ ዛፍ” ለመሆን ተመኝቶ ነበር። (መዝሙር 52:​8) ብዙውን ጊዜ እስራኤላውያን ቤተሰቦች በቤቶቻቸው ዙሪያ የወይራ ዛፎች ይኖሯቸው እንደነበረ ሁሉ ዳዊትም ወደ ይሖዋ ለመቅረብና ለአምላክ የምስጋና ፍሬ ለማፍራት ተመኝቷል።​—⁠መዝሙር 52:​9

ሁለት ነገዶችን ያቀፈው የይሁዳ መንግሥት ለይሖዋ ታማኝ በነበረበት ወቅት ‘በመልካም ፍሬ እንደተዋበ የለመለመ የወይራ ዛፍ’ ነበር። (ኤርምያስ 11:​15, 16) ይሁን እንጂ የይሁዳ ሕዝብ ‘የይሖዋን ቃል ለመስማት አሻፈረኝ ባለ ጊዜና ሌሎች አማልክትን በተከተለ ጊዜ’ የነበረውን ልዩ ቦታ አጣ።​—⁠ኤርምያስ 11:​10

በአምላክ ቤት ውስጥ እንደለመለመ የወይራ ዛፍ ለመሆን ይሖዋን መታዘዝና ተጨማሪ ክርስቲያናዊ ፍሬዎችን ማፍራት እንችል ዘንድ እኛን “ለመግረዝ” የሚጠቀምበትን ተግሣጽ ለመቀበል ፈቃደኞች ሆነን መገኘት አለብን። (ዕብራውያን 12:​5, 6) ከዚህም በላይ አንድ የወይራ ዛፍ የድርቅ ወቅትን ተቋቁሞ ማለፍ እንዲችል ረዣዥም ሥሮች እንደሚያስፈልጉት ሁሉ እኛም የሚገጥሙንን ፈተናዎችና ስደቶች በጽናት ማለፍ እንድንችል መንፈሳዊ ሥሮቻችንን ማጠናከር ይኖርብናል።​—⁠ማቴዎስ 13:​21፤ ቆላስይስ 2:​6, 7

የወይራ ዛፍ በዓለም ዘንድ ላይታወቅ ቢችልም እንኳ አምላክ በሚገባ የሚያውቀውን የታመነ ክርስቲያን ጥሩ አድርጎ ያመለክታል። እንዲህ ያለው ሰው በዚህ ሥርዓት ቢሞት እንኳ በሚመጣው አዲስ ዓለም ሕያው ይሆናል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 6:​9፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13

ከዓመት ዓመት ፍሬ የሚያፈራውና ዘላለማዊ ሊባል የሚችለው የወይራ ዛፍ “የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፣ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል” በማለት አምላክ የገባውን የወደፊት ተስፋ ያስታውሰናል። (ኢሳይያስ 65:​22) ይህ ትንቢታዊ ቃል በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ፍጻሜውን ያገኛል።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​13

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ብዙውን ጊዜ እነዚህ አዳዲስ ችግኞች የዋነኛውን ዛፍ ጥንካሬ እንዳያዳክሙ ሲባል በየዓመቱ ይገረዛሉ።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስፔይን በአሊካንቲ ወረዳ፣ ሃሴያ ውስጥ የሚገኘው በጉጥ የተሞላ ጥንታዊ ግንድ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስፔይን፣ ግራናዳ ወረዳ የበቀሉ የወይራ ዛፎች

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከኢየሩሳሌም ቅጥር ውጭ የሚገኝ አንድ ጥንታዊ የወይራ ዛፍ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ ከሌላ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፍ ቆርጦ ሌላ ዛፍ ላይ ስለማጣበቅ ይናገራል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይህ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ የወይራ ዛፍ ለጋ በሆኑ ቅርንጫፍ ቡቃያዎች ተከብቧል