በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ እምነት ይኑራችሁ!

በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ እምነት ይኑራችሁ!

በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ እምነት ይኑራችሁ!

“እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን።”​—⁠2 ጴጥሮስ 1:​19

1, 2. በታሪክ በመጀመሪያ የተነገረው ትንቢት የትኛው ነው? ይህ ትንቢት ከሚያስነሳቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ ምንድን ነው?

 በታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ትንቢት ምንጭ ይሖዋ ነው። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ አምላክ ለእባቡ እንደሚከተለው ሲል ነገረው:- “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍጥረት 3:​1-7, 14, 15) የእነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ትርጉም ሙሉ በሙሉ ግልጽ ከመሆኑ በፊት ብዙ መቶ ዘመናት ማለፍ ነበረባቸው።

2 ይህ የመጀመሪያው ትንቢት ለኃጢአተኛው የሰው ዘር እውነተኛ ተስፋ የያዘ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች ያ “የቀደመው እባብ” ሰይጣን ዲያብሎስ መሆኑን ከጊዜ በኋላ ግልጽ አድርገዋል። (ራእይ 12:​9) ሆኖም አምላክ ተስፋ የሰጠበት ዘር ማን ነው?

የዘሩን ማንነት መመርመር

3.አቤል በመጀመሪያው ትንቢት ላይ እምነት እንደነበረው ያሳየው እንዴት ነው?

3 ምንም እንኳ አባቱ እምነት ሳያሳይ ቢቀርም አምላካዊ ፍርሃት የነበረው አቤል በመጀመሪያው ትንቢት ላይ እምነት እንዳለው አሳይቷል። አቤል ኃጢአትን ለመሸፈን ደም መፍሰስ የሚያስፈልግ መሆኑን ተገንዝቦ እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ስለዚህ በአምላክ ዘንድም ተቀባይነት ያገኘውን የእንስሳት መሥዋዕት እንዲያቀርብ ያነሳሳው እምነት ነው። (ዘፍጥረት 4:​2-4) ሆኖም ተስፋ የተሰጠበት ዘር ማንነት ገና ምሥጢር እንደሆነ ቆይቷል።

4.አምላክ ለአብርሃም ምን ተስፋ ሰጠው? ይህስ ስለ ተስፋው ዘር ምን የሚጠቁመው ነገር አለ?

4 አቤል ከኖረበት ዘመን 2, 000 ዓመታት ገደማ በኋላ ይሖዋ ለፓትሪያርኩ አብርሃም የሚከተለውን ትንቢታዊ ተስፋ ሰጠው:- “በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፣ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት . . . አበዛዋለሁ፤ . . . የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ።” (ዘፍጥረት 22:​17, 18) እነዚህ ቃላት አብርሃም ከመጀመሪያው ትንቢት ፍጻሜ ጋር ግንኙነት እንዲኖረው ከማድረጋቸውም በላይ የሰይጣንን ሥራዎች የሚያፈርሰው ዘር በአብርሃም የዘር ሐረግ በኩል እንደሚመጣ አመልክተዋል። (1 ዮሐንስ 3:​8) “[አብርሃም] በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም።” ‘የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያላገኙ’ በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮችም አልተጠራጠሩም። (ሮሜ 4:​20, 21፤ ዕብራውያን 11:​39) ከዚህ ይልቅ በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ ያላቸውን እምነት እስከ መጨረሻው ጠብቀዋል።

5.አምላክ ስለ ዘሩ የሰጠው ተስፋ ፍጻሜውን የሚያገኘው በማን በኩል ነው? እንዲህ ብለህ የመለስከውስ ለምንድን ነው?

5 ሐዋርያው ጳውሎስ “ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር ለዘሮቹም አይልም፣ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን:- ለዘርህም ይላል፣ እርሱም ክርስቶስ” ብሎ ሲጽፍ አምላክ ተስፋ የሰጠበትን ዘር ማንነት አመልክቷል። (ገላትያ 3:​16) አሕዛብ ራሳቸውን የሚባርኩበት ዘር የአብርሃምን ልጆች በሙሉ ይመለከታል ማለት አይደለም። የልጁ የእስማኤል ዝርያዎችም ሆኑ አብርሃም ከኬጡራ የወለዳቸው ልጆች የሰው ዘር የሚባረክበት ዘር መስመር በመሆን አላገለገሉም። የሰው ዘር የሚባረክበት ዘር የመጣው በልጁ በይስሐቅና በልጅ ልጁ በያዕቆብ በኩል ነበር። (ዘፍጥረት 21:​12፤ 25:​23, 31-34፤ 27:​18-29, 37፤ 28:​14) ያዕቆብ “ሰዎች” የይሁዳ ነገድ ለሆነው ሴሎ እንደሚታዘዙ አመልክቶ ነበር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ዘሩ በዳዊት መሥመር ብቻ ተወሰነ። (ዘፍጥረት 49:​10፤ 2 ሳሙኤል 7:​12-16) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዶች አንድ ሰው መሲሕ ወይም ክርስቶስ ሆኖ እንደሚመጣ ይጠብቁ ነበር። (ዮሐንስ 7:​41, 42) አምላክ ስለ ዘሩ የተናገረው ትንቢት በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ፍጻሜውን አግኝቷል።

መሲሑ ተገለጠ!

6.(ሀ) ስለ 70 ሳምንታት የሚናገረውን ትንቢት የምንረዳው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ‘ኃጢአትን ወደ ፍጻሜው ያመጣው’ እንዴትና መቼ ነው?

6 ነቢዩ ዳንኤል አ⁠ንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ መሲሐዊ ትንቢት ዘግቧል። በሜዶናዊው ዳርዮስ ንግሥና የመጀመሪያ ዓመት ኢየሩሳሌም ባድማ ሆና የቆየችበት 70 ዓመት ፍጻሜው እንደተቃረበ ተገንዝቦ ነበር። (ኤርምያስ 29:​10፤ ዳንኤል 9:​1-4) ዳንኤል እየጸለየ ሳለ መልአኩ ገብርኤል መጥቶ ‘ኃጢአትን ወደ ፍጻሜው ለማምጣት ሰባ ሳምንት’ እንደተቀጠረ ገለጸለት። መሲሑ በሰባኛው ሳምንት አጋማሽ ላይ ይገደላል። እነዚህ ‘ሰባ የዓመታት ሳምንታት’ የጀመሩት የፋርሱ ንጉሥ አርጤክስስ ቀዳማዊ ኢየሩሳሌም ዳግም እንድትገነባ ‘ትእዛዝ ባወጣበት’ በ455 ከዘአበ ነው። (ዳንኤል 9:​20-27ሞፋት፤ ነህምያ 2:​1-8) ከሰባት ሳምንት ሲደመር 62 ሳምንት በኋላ መሲሑ ይመጣል። እነዚህ 483 ዓመታት ከ455 ከዘአበ ጀምረው 29 እዘአ ኢየሱስ የተጠመቀበትና መሲህ ወይም ክርስቶስ ሆኖ በአምላክ የተቀባበት ጊዜ ላይ ያደርሱናል። (ሉቃስ 3:​21, 22) ኢየሱስ በ33 እዘአ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ‘ኃጢአትን ወደ ፍጻሜው አምጥቷል።’ (ማርቆስ 10:​45) በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ እምነት እንዲኖረን የሚያደርግ እንዴት ያለ ጠንካራ ማስረጃ ነው! a

7.ቅዱሳን ጽሑፎችን በመጠቀም ኢየሱስ መሲሐዊ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ያደረገው በምን መንገድ እንደሆነ አስረዳ።

7 በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ ያለን እምነት መሲሑን ለይተን እንድናውቅ ያስችለናል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን የጻፉት ጸሐፊዎች በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት ብዙዎቹ መሲሐዊ ትንቢቶች በቀጥታ ኢየሱስን እንደሚመለከቱ ዘግበዋል። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ኢየሱስ የተወለደው በኢየሩሳሌም ከምትገኝ አንዲት ድንግል ነው። (ኢሳይያስ 7:​14፤ ሚክያስ 5:​2፤ ማቴዎስ 1:​18-23፤ ሉቃስ 2:​4-11) ከተወለደ በኋላ ከግብፅ የተጠራ ሲሆን ከእርሱ መወለድ በኋላ ሕፃናት ተጨፈጨፉ። (ኤርምያስ 31:​15፤ ሆሴዕ 11:​1፤ ማቴዎስ 2:​13-18) ኢየሱስ ሕመማችንን ተሸክሟል። (ኢሳይያስ 53:​4፤ ማቴዎስ 8:​16, 17) አስቀድሞ በተነገረው መሠረት በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገብቷል። (ዘካርያስ 9:​9፤ ዮሐንስ 12:​12-15) ኢየሱስ ከተሰቀለ በኋላ ወታደሮቹ ልብሶቹን በተከፋፈሉበትና በእጀ ጠባቡ ላይ ዕጣ በተጣጣሉበት ጊዜ መዝሙራዊው የተናገራቸው ቃላት ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። (መዝሙር 22:​18፤ ዮሐንስ 19:​23, 24) በተጨማሪም አጥንቶቹ እንደማይሰበሩና ጎኑን እንደሚወጉት የተነገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። (መዝሙር 34:​20፤ ዘካርያስ 12:​10፤ ዮሐንስ 19:​33-37) በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በቀጥታ ኢየሱስን እንደሚያመለክቱ ከጠቀሷቸው መሲሐዊ ትንቢቶች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። b

መሲሐዊውን መንግሥት አወድሱ

8.በዘመናት የሸመገለው ማን ነው? በ⁠ዳንኤል 7:​9-14 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ትንቢትስ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

8 በባቢሎናዊው ንጉሥ በብልጣሶር የመጀመሪያ ዓመት ይሖዋ ለነቢዩ ዳንኤል ሕልምና አስደናቂ ራእይ አሳየው። ነቢዩ በመጀመሪያ አራት ግዙፍ አራዊት ተመለከተ። የአምላክ መልአክ እነዚህ አራዊት “አራት ነገሥታት” መሆናቸውን በመግለጽ በተከታታይ የሚነሱ የዓለም ኃያላን መንግሥታት ምሳሌ እንደሆኑ አመለከተ። (ዳንኤል 7:​1-8, 17) ቀጥሎ ዳንኤል ‘በዘመናት የሸመገለው’ ይሖዋ በክብራማ ሁኔታ በዙፋን ላይ ተቀምጦ ተመለከተ። ይሖዋ በእነዚህ አራዊት ላይ ከፈረደባቸውና ሥልጣናቸውን ከወሰደባቸው በኋላ አራተኛውን አውሬ አጠፋው። “ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ” ‘የሰው ልጅ ለሚመስለው’ የዘላለም ግዛት ተሰጠው። (ዳንኤል 7:​9-14) ‘የሰው ልጅ’ የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በዙፋን ላይ ከመቀመጡ ጋር ግንኙነት ያለው እንዴት ያለ አስደናቂ ትንቢት ነው!​—⁠ማቴዎስ 16:​13

9, 10. (ሀ) የሕልሙ ምስል የተለያዩ ክፍሎች ምን ያመለክታሉ? (ለ) የ⁠ዳንኤል 2:​44ን ፍጻሜ እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?

9 አምላክ ‘ነገሥታትን እንደሚያፈልስና ነገሥታትን እንደሚያስነሳ’ ዳንኤል ያውቅ ነበር። (ዳንኤል 2:​21) ነቢዩ ‘ምሥጢርን ገላጭ’ በሆነው በይሖዋ በማመን ባቢሎናዊው ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕልም ያየው ግዙፍ ምስል ምን ትርጉም እንዳለው አስታወቀ። የምስሉ የተለያዩ ክፍሎች እንደ ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስ፣ ግሪክና ሮም ያሉት የዓለም ኃያላን መንግሥታትን መነሳትና መውደቅ ያመለክታሉ። በተጨማሪም አምላክ እስከ ዘመናችን ድረስና ከዚያም በኋላ ስለሚኖረው የዓለም ሁኔታ እንዲጽፍ ዳንኤልን ተጠቅሞበታል።​—⁠ዳንኤል 2:​24-30

10 “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን” ይላል ትንቢቱ “የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።” (ዳንኤል 2:​44) ‘የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት’ በ1914 ሲያበቁ አምላክ በክርስቶስ የሚመራ ሰማያዊ መንግሥት አቋቋመ። (ሉቃስ 21:​24፤ ራእይ 12:​1-5) ከአምላክ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት “ተራራ” የመሲሐዊው መንግሥት “ድንጋይ” በመለኮታዊ ኃይል ተፈንቅሎ ወጣ። በአርማጌዶን ይህ ድንጋይ ምስሉን በመምታት አመድ ያደርገዋል። መሲሐዊው መንግሥት ‘በመላው ምድር’ ላይ ለውጥ የሚያመጣ ተራራ መሰል መስተዳድር እንደመሆኑ መጠን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።​—⁠ዳንኤል 2:​35, 45፤ ራእይ 16:​14, 16 c

11. የኢየሱስ ተአምራዊ መለወጥ የምን ነገር መቅድም ነው? ይህስ ራእይ በጴጥሮስ ላይ ምን ተጽእኖ አሳድሯል?

11 ኢየሱስ መንግሥታዊ አገዛዙን በአእምሮው በመያዝ ለደቀ መዛሙርቱ “የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ” ሲል ነገራቸው። (ማቴዎስ 16:​28) ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ወደ አንድ ትልቅ ተራራ ይዟቸው ወጣና በተአምራዊ ሁኔታ በፊታቸው ተለወጠ። ከዚያም ደማቅ ደመና ሐዋርያቱን ከሸፈናቸው በኋላ አምላክ “የምወደው ልጄ ይህ ነው፣ እርሱን ስሙት” ሲል ተናገረ። (ማቴዎስ 17:​1-9፤ ማርቆስ 9:​1-9) ክርስቶስ ወደፊት የሚኖረውን መንግሥታዊ ክብር የሚያሳይ እንዴት ያለ አስደናቂ መግለጫ ነው! ጴጥሮስ ይህን እጅግ የሚያንጸባርቅ ራእይ በመጥቀስ “ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን” ሲል መናገሩ ምንም አያስገርምም።​—⁠2 ጴጥሮስ 1:​16-19 d

12. በተለይ ይህ ያለንበት ጊዜ በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ እምነት እንዳለን የምናሳይበት ጊዜ የሆነው ለምንድን ነው?

12 “ትንቢታዊው ቃል” ስለ መሲሑ የሚናገሩትን በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙ ትንቢቶች ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ “በኃይልና በብዙ ክብር” እንደሚመጣ የተናገረውንም እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም። (ማቴዎስ 24:​30) በተአምራዊ ሁኔታ መለወጡ ክርስቶስ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ በክብር እንደሚመጣ የሚያረጋግጥ ነበር። በቅርቡ የክርስቶስ በክብር መገለጥ እምነት የለሽ ለሆኑ ሰዎች ጥፋት የሚያስከትል ሲሆን እምነት እንዳላቸው ላስመሰከሩ ሰዎች ደግሞ በረከት ያስገኝላቸዋል። (2 ተሰሎንቄ 1:​6-10) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን ማግኘቱ “በመጨረሻው ቀን” እንደምንኖር ያረጋግጣል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5, 16, 17፤ ማቴዎስ 24:​3-14) ሚካኤል ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ በይሖዋ የተሾመ ዋና ቅጣት አስፈጻሚ እንደመሆኑ መጠን ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍጻሜው ለማምጣት ዝግጁ ሆኖ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። (ማቴዎስ 24:​21፤ ዳንኤል 12:​1) ይህ በእርግጥም በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ እምነት እንዳለን የምናሳይበት ጊዜ ነው።

በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ ያላችሁን እምነት ጠብቁ

13. ለአምላክ ያለንን ፍቅር ለመጠበቅና በቃሉ ላይ ያለን እምነት ሕያው እንደሆነ እንዲቀጥል ለማድረግ ምን ነገር ሊረዳን ይችላል?

13 ስለ አምላክ ትንቢታዊ ቃል ፍጻሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንሰማ መቼም በጣም እንደተደሰትን የታወቀ ነው። ሆኖም ከዚያ በኋላ እምነታችን ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሄዷል? ፍቅራችንስ ቀዝቅዟል? ‘የቀድሞ ፍቅራቸውን እንደተዉት’ እንደ ኤፌሶን ክርስቲያኖች በፍጹም መሆን የለብንም። (ራእይ 2:​1-4) በሰማይ መዝገብ ለማከማቸት ምንጊዜም ‘የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን ማስቀደማችንን ካልቀጠልን’ በስተቀር የቱንም ያህል ረጅም ዓመት ይሖዋን ያገለገልን ብንሆን እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ሊደርስብን ይችላል። (ማቴዎስ 6:​19-21, 31-33) መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር መሳተፍና በመንግሥቱ የስብከት እንቅስቃሴ በቅንዓት መካፈል ለይሖዋ፣ ለልጁና ለቅዱሳን ጽሑፎች ያለንን ፍቅር ጠብቀን እንድንኖር ይረዱናል። (መዝሙር 119:​105፤ ማርቆስ 13:​10፤ ዕብራውያን 10:​24, 25) ይህ ደግሞ በአጸፋው በአምላክ ቃል ላይ ያለን እምነት ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋል።​—⁠መዝሙር 106:​12

14. ቅቡዓን ክርስቲያኖች በይሖዋ ትንቢታዊ ቃል ላይ ባላቸው እምነት የተባረኩት እንዴት ነው?

14 የአምላክ ትንቢታዊ ቃል ከዚህ ቀደም እንደተፈጸመ ሁሉ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚናገረውም እንደሚፈጸም እምነት ልናሳድር እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ክርስቶስ በመንግሥቱ ክብር ስለመገኘቱ የሚናገረው ትንቢት አሁን እውን ሆኗል፤ እንዲሁም እስከ ሞት ድረስ ታማኝነታቸውን ያረጋገጡ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ድል ለነሳው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ” የሚለው ትንቢታዊ ተስፋ ተፈጽሞላቸዋል። (ራእይ 2:​7, 10፤ 1 ተሰሎንቄ 4:​14-17) ኢየሱስ ድል ለነሱት ቅቡዓን ‘በአምላክ ሰማያዊ ገነት’ ‘ከሕይወት ዛፍ እንዲበሉ’ መብት ይሰጣቸዋል። ‘ብቻውን አምላክ የሆነው የማይጠፋው፣ የማይታየውና የዘመናት ንጉሥ’ የሆነው ይሖዋ ከትንሣኤያቸው በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የማይሞትና የማይጠፋ ሕይወት ይሰጣቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:​17፤ 1 ቆሮንቶስ 15:​50-54፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:​10) ለአምላክ ያላቸው የማይቀዘቅዝ ፍቅርና በትንቢታዊ ቃሉ ላይ ያላቸው የማይናወጥ እምነት የሚያስገኝላቸው እንዴት ያለ ታላቅ ወሮታ ነው!

15. ‘የአዲሱ ምድር’ መሠረት የተጣለው በእነማን ላይ ነው? የእነሱ ጓደኞችስ እነማን ናቸው?

15 ታማኝነታቸውን እንደጠበቁ ሞተው የነበሩ ቅቡዓን በሰማያዊ ‘የእግዚአብሔር ገነት’ ትንሣኤ ካገኙ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በምድር ላይ የነበሩ የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ነፃ ወጡ። (ራእይ 14:​8፤ ገላትያ 6:​16) ‘የአዲሱ ምድር’ መሠረት የተጣለው በእነዚህ ቅቡዓን ላይ ነው። (ራእይ 21:​1) በዚህ መንገድ “አገር” የተወለደ ሲሆን ይህም አገር በዛሬው ጊዜ ምድር አቀፍ መንፈሳዊ ገነት ሊሆን በቅቷል። (ኢሳይያስ 66:​8) በግ መሰል የሆኑት የመንፈሳዊ እስራኤል ጓደኞች በዚህ “በዘመኑ ፍጻሜ” ወደዚህ መንፈሳዊ ገነት በመጉረፍ ላይ ናቸው።​—⁠ኢሳይያስ 2:​2-4፤ ዘካርያስ 8:​23፤ ዮሐንስ 10:​16፤ ራእይ 7:​9

የሰው ዘር የወደፊት ዕጣ በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ውስጥ ተገልጿል

16. የቅቡዓን ታማኝ ደጋፊዎች ተስፋ ምንድን ነው?

16 የቅቡዓን ታማኝ ደጋፊዎች የወደፊት ተስፋ ምንድን ነው? እነሱም በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ እምነት አላቸው፤ ምድራዊ ወደሆነች ገነት እንገባለን ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። (ሉቃስ 23:​39-43) በዚያም ሕይወትን ጠብቆ ከሚያቆይ ‘የሕይወት ውኃ ወንዝ’ ይጠጣሉ እንዲሁም በወንዙ ዳርና ዳር በተተከለው ‘ዛፍ ቅጠሎች’ አማካኝነት ፈውስ ያገኛሉ። (ራእይ 22:​1, 2) እንዲህ ዓይነት አስደናቂ ተስፋ ካለህ ለይሖዋ የጠለቀ ፍቅርና በትንቢታዊ ቃሉ ላይ እምነት እንዳለህ ማሳየትህን ቀጥል። በምድራዊ ገነት ውስጥ ዘላለማዊ ሕይወት መጨበጥ የሚያስገኘውን ወሰን የሌለው ደስታ ከሚቀምሱ ሰዎች መካከል ለመሆን ያብቃህ።

17. በምድራዊ ገነት ውስጥ የሚኖረው ሕይወት ምን በረከቶችን ይጨምራል?

17 ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በመጪው ምድራዊ ገነት ውስጥ የሚኖረውን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ሊገልጹት አይችሉም። ሆኖም ታዛዥ የሆኑ የሰው ዘሮች በዚያን ጊዜ የሚያገኟቸውን በረከቶች በተመለከተ የአምላክ ትንቢታዊ ቃል ጥልቅ ማስተዋል ይሰጠናል። የአምላክ መንግሥት ያለ አንዳች ተቀናቃኝ በሚያስተዳድርበትና ፈቃዱ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም በሚሆንበት ጊዜ ጨካኝ የሆኑ ሰዎች በፍጹም አይኖሩም፤ ሌላው ቀርቶ እንስሳት እንኳ “አይጎዱም አያጠፉምም።” (ኢሳይያስ 11:​9፤ ማቴዎስ 6:​9, 10) ገሮች ምድርን ይወርሳሉ “በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:​11) ‘በምድር ላይ በቂ እህል ስለሚኖርና ተራሮች በሰብል ስለሚሸፈኑ’ በረሀብ የሚሠቃዩ ሰዎች አይኖሩም። (መዝሙር 72:​16) የሐዘን እንባ አይኖርም። በሽታ ሌላው ቀርቶ ሞት እንኳ ይወገዳል። (ኢሳይያስ 33:​24፤ ራእይ 21:​4) ዶክተሮች፣ መድኃኒቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የአእምሮ ሕክምና ተቋሞች ወይም የቀብር ሥነ ሥርዓት የማይኖሩበት ጊዜ ምን ሊመስል እንደሚችል ልትገምት ትችላለህ? እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው!

18. (ሀ) ዳንኤል ምን ዋስትና ተሰጥቶታል? (ለ) የዳንኤል ‘ዕጣ ክፍል’ ምን ይሆናል?

18 ሙታን በትንሣኤ ስለሚነሱ የሰዎች ተራ መቃብር እንኳ ባዶ ይሆናል። ጻድቁ ሰው ኢዮብ እንዲህ ዓይነት ተስፋ ነበረው። (ኢዮብ 14:​14, 15) የይሖዋ መልአክ “አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ፤ አንተም ታርፋለህ፣ በቀኑም መጨረሻ በዕጣ ክፍልህ ትቆማለህ” የሚል የሚያጽናና ዋስትና ሰጥቶት ስለነበር ነቢዩ ዳንኤልም እንዲህ ዓይነት ተስፋ ነበረው። (ዳንኤል 12:​13) ዳንኤል እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ አምላክን በታማኝነት አገልግሏል። ምንም እንኳ ዳንኤል አሁን በሞት አንቀላፍቶ ቢገኝም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት “በጻድቃን ትንሣኤ” ‘ይቆማል።’ (ሉቃስ 14:​14) የዳንኤል ‘ዕጣ ክፍል’ ምን ይሆናል? ስለ ገነት ተስፋ ፍጻሜ የሕዝቅኤል ትንቢት በሚሰጠው ጥቆማ መሠረት ሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች ቦታ ይኖራቸዋል። ሌላው ቀርቶ መሬት ያለ አድልዎና በሥርዓት ይከፋፈላል። (ሕዝቅኤል 47:​13 እስከ 48:​35) ስለዚህ ዳንኤል በገነት ውስጥ ቦታ ይኖረዋል፤ ሆኖም በዚያ የሚኖረው ዕጣ ክፍል መሬት ማግኘት ብቻ አይደለም። በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የሚኖረውን ቦታም ይጨምራል።

19. በምድራዊ ገነት ውስጥ ለመኖር ምን ነገር ማሟላት ያስፈልጋል?

19 ስለ አንተና ስለ ዕጣ ክፍልህስ ምን ለማለት ይቻላል? በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት ካለህ በምድራዊ ገነት ውስጥ ለመኖር እንደምትጓጓ የታወቀ ነው። እንዲያውም በዚያ ተገኝተህ በበረከቶቹ ስትደሰት፣ ምድርን ስትንከባከብና ሙታንን ስትቀበል በዓይነ ሕሊናህ ልትመለከት ትችላለህ። ደግሞም ሰው መኖር ያለበት በገነት ውስጥ ነው። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ጥንድ የፈጠራቸው እንዲህ በመሰለ ቦታ እንዲኖሩ ነበር። (ዘፍጥረት 2:​7-9) ታዛዥ የሆኑ ሰዎችም በገነት ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል። በመጨረሻ ገነት በሆነች ምድር ላይ ከሚኖሩ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ለመሆን ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር በሚስማማ መንገድ ትኖራለህ? ለሰማያዊው አባታችን ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር ካለህና በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ የጸና እምነት ካለህ በዚያ ልትገኝ ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 እና ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው መጽሐፍ “ሰቨንቲ ዊክስ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት። እነዚህን መጻሕፍት ያሳተመው ኒው ዮርክ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ነው።

b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን “ቅዱሳን ጽሑፎች በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉና ጠቃሚ ናቸው” (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 343-4 ተመልከት።

d በሚያዝያ 1, 2000 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት ተከታተል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?

• በመጀመሪያ የተነገረው ትንቢት ምንድን ነው? ተስፋ የተሰጠበት ዘርስ ማን ነው?

• በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን ያገኙ አንዳንድ መሲሐዊ ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው?

ዳንኤል 2:​44, 45 ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?

• የአምላክ ትንቢታዊ ቃል ታዛዥ የሰው ዘሮች ወደፊት ምን እንደሚያገኙ ይናገራል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በምድራዊ ገነት ውስጥ ለመኖር በተስፋ ትጠባበቃለህ?