አምላክ ለዘመናችን ያስነገረውን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት ተከታተል
አምላክ ለዘመናችን ያስነገረውን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት ተከታተል
“የሰው ልጅ ሆይ፣ ራእዩ ለፍጻሜ ዘመን እንደ ሆነ አስተውል።”—ዳንኤል 8:17
1. ይሖዋ ያለንበትን ዘመን በተመለከተ የሰው ዘር በሙሉ ምን እንዲያውቅ ይፈልጋል?
ይሖዋ ስለመጪው ጊዜ ያለውን እውቀት ለራሱ ብቻ ምሥጢር አድርጎ አይዝም። ይልቁንም ምሥጢር ገላጭ አምላክ ነው። እንዲያውም ‘ወደ ፍጻሜው ዘመን’ በጣም ጠልቀን የገባን መሆናችንን ሁላችንም እንድናውቅ ይፈልጋል። በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ለሚኖሩ ከስድስት ቢልዮን ለሚበልጡ ሰዎች ይህ ምንኛ ጠቃሚ ዜና ነው!
2. ሰዎች ስለ ሰው ዘር የወደፊት ዕጣ የሚጨነቁት ለምንድን ነው?
2 ይህ ዓለም ወደ ፍጻሜው የቀረበ መሆኑ ሊያስደንቀን ይገባልን? የሰው ልጅ በጨረቃ ላይ መሄድ ችሏል፣ በዚህች ምድር ላይ በሚገኙ ብዙ ጎዳናዎች ላይ ግን ያለ ፍርሃት መንሸራሸር አልቻለም። ቤቱን በተለያዩ ዘመናዊ ዕቃዎች መሙላት ችሏል፣ እየተባባሰ የሚሄደውን የቤተሰብ መፈራረስ ግን ሊገታ አልቻለም። እንደ ልብ የኢንፎርሜሽን ልውውጥ ማድረግ የሚቻልበት ዘመን ላይ ደርሷል፤ ሰዎች እርስ በርሳቸው ተስማምተው በሰላም እንዲኖሩ ማስተማር ግን አልሆነለትም። እነዚህ ያልተሳኩ ጥረቶች በሙሉ በፍጻሜው ዘመን እንደምንኖር ለሚያረጋግጡት በርካታ የቅዱሳን ጽሑፎች ማስረጃዎች ድጋፍ የሚሰጡ ናቸው።
3. ‘የፍጻሜ ዘመን’ የሚሉት ቃላት ለመጀመሪያ ጊዜ በምድር ላይ የተነገሩት መቼ ነው?
3 “የፍጻሜው ዘመን” የሚሉትን እነዚህን አስደንጋጭ ቃላት ከ2, 600 ዓመታት ገደማ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመባቸው መልአኩ ገብርኤል ነው። በፍርሃት ተውጦ የነበረ አንድ የአምላክ ነቢይ፣ ገብርኤል “የሰው ልጅ ሆይ፣ ራእዩ ለፍጻሜ ዘመን እንደሆነ አስተውል” ሲል ሰምቷል።—ዳንኤል 8:17
“የፍጻሜው ዘመን” ይህ ነው
4. መጽሐፍ ቅዱስ በምን ሌሎች መንገዶችም ስለ ፍጻሜው ዘመን ይጠቅሳል?
4 ‘የፍጻሜ ዘመን’ እና ‘የተወሰነው የፍጻሜ ዘመን’ የሚሉት ሐረጎች በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ስድስት ጊዜ ተጠቅሰው ይገኛሉ። (ዳንኤል 8:17, 19፤ 11:35, 40፤ 12:4, 9) ሐዋርያው ጳውሎስ የተነበየለትን “የመጨረሻ ቀን” የሚያመለክቱ ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ኢየሱስ ክርስቶስም ይህ ዘመን እርሱ በሰማይ በዙፋን የተቀመጠ ንጉሥ ሆኖ ‘የሚገኝበትን’ ጊዜ እንደሚያመለክት ገልጿል።—ማቴዎስ 24:37-39
5, 6. በፍጻሜው ዘመን ‘የመረመሩት’ እነማን ናቸው? ከምንስ ውጤት ጋር?
5 ዳንኤል 12:4 እንዲህ ይላል:- “ዳንኤል ሆይ፣ አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፣ መጽሐፉንም አትም ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፣ እውቀትም ይበዛል።” ዳንኤል የጻፈው ነገር በአብዛኛው ለብዙ መቶ ዘመናት ለሰው ልጆች ማስተዋል ምሥጢር ሆኖና ታትሞ ቆይቷል። ዛሬስ?
6 በዚህ የፍጻሜ ዘመን ብዙ ታማኝ ክርስቲያኖች የአምላክን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን አገላብጠው ‘መርምረዋል።’ ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? በጥረታቸው ላይ የይሖዋ በረከት ስለታከለበት እውነተኛ እውቀት በጣም ሊበዛ ችሏል። ለምሳሌ ያህል ቅቡዓን የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 ሰማያዊ ንጉሥ እንደሆነ እንዲያስተውሉ ያስቻላቸውን እውቀት አግኝተዋል። እነዚህ ቅቡዓንና ታማኝ ባልንጀሮቻቸው በ2 ጴጥሮስ 1:19-21 ላይ በሚገኙት የሐዋርያው ቃላት መሠረት ‘ትንቢታዊውን ቃል በትኩረት ከመከታተላቸውም’ በላይ ይህ የአሁኑ ዘመን በእርግጥ የፍጻሜ ዘመን ስለመሆኑ እርግጠኞች ሆነዋል።
7. የዳንኤልን መጽሐፍ ልዩ የሚያደርጉት አንዳንድ ዘገባዎች ምንድን ናቸው?
7 የዳንኤል መጽሐፍ በበርካታ መንገዶች በዓይነቱ ልዩ ነው። በመጽሐፉ ገጾች ውስጥ አንድ ንጉሥ ግራ የተጋባበትን የራሱን ሕልም ጠቢባን ሰዎቹ ሊነግሩትና ፍቺውን ሊገልጡለት ባለመቻላቸው እንደሚገድላቸው ሲዝትባቸው የይሖዋ ነቢይ ግን ሊገልጥለት እንደቻለ ይተርካል። ንጉሡ ያቆመውን ታላቅ ምስል ለማምለክ እምቢተኛ የሆኑ ሦስት ወጣት ወንዶች በሚንቀለቀል እቶን እሳት ውስጥ ተጥለው የእሳት ሽታ እንኳን ሳይነካቸው ወጥተዋል። ከፍተኛ ፈንጠዝያ በነበረበት በዓል ላይ አንድ እጅ በቤተ መንግሥቱ ግድግዳ ላይ ምሥጢራዊ የሆኑ ቃላት ሲጽፍ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ተመልክተዋል። ክፋት የተጠናወታቸው ሴረኞች አንድ አረጋዊ ሰው ወደ አንበሶች ጉድጓድ እንዲጣል አድርገው ነበር፤ ሆኖም ትንሽ ጭረት እንኳን ሳይነካው ወጣ። በአንድ ራእይ ውስጥ አራት አራዊት ይታዩና እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ የሚዘልቅ ትንቢታዊ ትርጉም እንደሚኖራቸው ይገልጻል።
8, 9. የዳንኤል መጽሐፍ በተለይ በዚህ በፍጻሜው ዘመን ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው?
8 የዳንኤል መጽሐፍ ሁለት የተለያዩ ክፍሎች እንዳሉት በግልጽ ማየት ይቻላል። አንደኛው ክፍል ታሪካዊ ሲሆን ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ትንቢታዊ ነው። ሁለቱም ቢሆኑ እምነታችንን ሊገነቡልን ይችላሉ። ታሪካዊው ዘገባ ይሖዋ አምላክ በእርሱ ፊት የአቋም ጽናታቸውን የሚያስመሰክሩትን ሰዎች እንደሚባርክ ያሳያል። ትንቢታዊው ክፍል ደግሞ ይሖዋ ከመቶ ዓመታት፣ እንዲያውም ከሺህ ዓመታት በፊት የታሪክን አካሄድ በቅድሚያ እንደሚያውቅ በማሳየት እምነታችንን ይገነባልናል።
9 በዳንኤል የተመዘገቡ የተለያዩ ትንቢቶች በቀጥታ ወደ አምላክ መንግሥት የሚያመለክቱ ናቸው። እንደነዚህ ያሉትን ትንቢቶች አፈጻጸም ስንመለከት እምነታችንም ሆነ በፍጻሜው ዘመን የምንኖር ስለመሆናችን ያለን እርግጠኝነት ይጠናከራል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ተቺዎች ዳንኤል በስሙ በሚጠራው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች የጻፈው ሁኔታዎቹ ከተፈጸሙ በኋላ ነው ይላሉ። እንደነዚህ ያሉት አባባሎች እውነት ከሆኑ የዳንኤል መጽሐፍ የፍጻሜውን ዘመን አስመልክቶ በሚናገራቸው ትንቢቶች ላይ ከባድ ጥያቄዎች ያስነሳሉ። በተጨማሪም ተጠራጣሪዎች በመጽሐፉ ውስጥ ስለተገለጹት ታሪኮች እውነተኛነት ይጠራጠራሉ። እንግዲያው እስቲ ሁኔታውን እንመርምር።
በችሎት ፊት!
10. የዳንኤል መጽሐፍ ምን ክስ ቀርቦበታል?
10 በአንድ ፍርድ ቤት ችሎት ላይ እንደተገኘህ አድርገህ አስብ። አቃቤ ሕጉ ተከሳሽ የማጭበርበር ድርጊት ፈጽሟል ብሎ ይሟገታል። የዳንኤል መጽሐፍም በአንድ ዕብራዊ ነቢይ በሰባተኛውና በስድስተኛው መቶ ዓመት ከዘአበ የተጻፈ እውነተኛ መጽሐፍ አድርጎ ራሱን አቅርቧል። ተቺዎች ግን የተጭበረበረ መጽሐፍ ነው ይላሉ። ስለዚህ እስቲ በመጀመሪያ የትረካው ክፍል ከታሪክ ጭብጦች ጋር ይስማማ እንደሆነና እንዳልሆነ እንመልከት።
11, 12. ብልጣሶር ልብ ወለድ ገጸ ባሕርይ ነው የሚለው ክስ መጨረሻው ምን ሆነ?
11 በዚያ ዘመን አልነበረም የሚባልለትን ንጉሥ ጉዳይ እንመልከት። ዳንኤል ምዕራፍ 5 የባቢሎን ከተማ በ539 ከዘአበ በወደቀችበት ጊዜ አገሪቱን ይገዛ የነበረው ንጉሥ ብልጣሶር እንደሆነ ያመለክታል። ተቺዎች የብልጣሶር ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በየትኛውም የታሪክ ሰነድ ላይ ተጠቅሶ አይገኝም በማለት ይህ ታሪክ ትክክል አይደለም ብለው ይከራከራሉ። ከዚህ ይልቅ የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች የመጨረሻው የባቢሎን ንጉሥ ናቦኒደስ እንደነበረ ይተርካሉ።
12 ይሁን እንጂ በ1854 በዛሬዋ ኢራቅ በምትገኘው በጥንቷ የባቢሎን ከተማ በኡር ፍርስራሽ ውስጥ ትናንሽ ሞላላ ሸክላዎች ተገኙ። የሽብልቅ ቅርፅ ባላቸው ፊደላት የተጻፈባቸው እነዚህ ሰነዶች ንጉሥ ናቦኒደስ “ታላቁ ልጄ ብልሳርሱር” ሲል የጠቀሰበትን ጸሎት ጭምር ይዘው ተገኝተዋል። ተቺዎች እንኳ ሳይቀሩ ይህ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው ብልጣሶር መሆኑን ተስማምተዋል። ስለዚህ በዚያ ዘመን አልነበረም የሚባለው ንጉሥ በዓለማዊ የታሪክ ሰነዶች ውስጥ ጭምር ሊገኝ ችሏል ማለት ነው። ይህ ዳንኤል የጻፋቸው ታሪኮች በእርግጥ እውነተኛ መሆናቸውን ከሚያረጋግጡት በርካታ ማስረጃዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ማስረጃ የዳንኤል መጽሐፍ በእርግጥም የአምላክ ቃል ክፍልና በዚህ በፍጻሜ ዘመን በጥንቃቄ ልንከታተለው የሚገባ መጽሐፍ መሆኑን ያሳያል።
13, 14. ናቡከደነፆር ማን ነው? በተለይ የትኛውን የሃሰት አምላክ ያመልክ ነበር?
13 በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የዓለም ኃያላን መንግሥታትን መፈራረቅና የአንዳንዶቹን ገዥዎች ተግባራት የሚገልጹ ትንቢቶች በብዛት ተካትተዋል። ከእነዚህ ገዥዎች አንዱ ሰፊ ግዛት የመሠረተ ጦረኛ ገዥ ሊባል ይችላል። የባቢሎን አልጋ ወራሽ በነበረበት ጊዜ የግብጹን ፈርኦን ኒካኡ ጦር በካርኬሚሽ ድምጥማጡን አጥፍቷል። ይሁን እንጂ ይህ ድል አድራጊ መስፍን በደረሰው መልእክት ምክንያት ቀሪውን የማጣሪያ ውጊያ ለጄኔራሎቹ ትቶ ለመመለስ ተገደደ። አባቱ ናቦፖላሳር መሞቱን ከሰማ በኋላ ወጣቱ ናቡከደነፆር በ624 ከዘአበ ዘውድ ጫነ። ለ43 ዓመት በቆየው የግዛት ዘመኑ በአሦር መንግሥት ሥር የነበረውን ግዛትና ከሶርያ አንስቶ የፓለስቲናን ምድር ጨምሮ እስከ ግብጽ ድንበር ይደርስ የነበረውን አገር ያካተተ ሰፊ ግዛት አቋቋመ።
14 ናቡከደነፆር በተለይ ያከብርና ያመልክ የነበረው የባቢሎን ዋነኛ አምላክ የነበረውን ማርዱክን ነበር። ንጉሡ ድል ያቀዳጀው ማርዱክ እንደሆነ ያምን ነበር። ናቡከደነፆር በባቢሎን ውስጥ የነበሩትን የማርዱክ አብያተ መቅደሶችን ከማስዋቡና አዳዲሶችንም ከመሥራቱ በተጨማሪ ለሌሎች በርካታ የባቢሎን አማልክትም መቅደስ ሠርቷል። ይህ ባቢሎናዊ ንጉሥ በዱራ ሜዳ ያቆመው የወርቅ ምስል ለማርዱክ የተሠራ ሳይሆን አይቀርም። (ዳንኤል 3:1, 2) በተጨማሪም ናቡከደነፆር ወታደራዊ እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ጊዜ በምዋርትና በጥንቆላ በጣም ይታመን ነበር።
15, 16. ናቡከደነፆር ለባቢሎን ምን አሠራ? ስለ ባቢሎን ትልቅነት በጉራ ሲናገር ምን ደረሰበት?
15 ናቡከደነፆር አባቱ አስጀምሮት የነበረውን ግዙፍና ድርብ ቅጥር በማስጨረስ ዋና ከተማይቱን በማንም ጠላት ልትደፈር የማትችል አስመስሏት ነበር። የአገሯን ኮረብቶችና ደኖች ትናፍቅ የነበረችውን ሜዶናዊት ንግሥት ለማስደሰት ሲል ከጥንቱ ዓለም ሰባት አስደናቂ ነገሮች አንዱ የሆነውን ገደል ላይ እንዳለ ሆኖ የተገነባ የአትክልት ቦታ እንዳሠራም ይነገርለታል። ባቢሎንን በዘመናት ሁሉ ተወዳዳሪ ካልተገኘላቸው በግንብ የታጠሩ ከተሞች አንዷ ለመሆን እንድትበቃ አድርጓታል። የሐሰት አምልኮ መናኸሪያ በሆነች በዚያች ከተማ ከመጠን በላይ ይኩራራ ነበር!
16 ከዕለታት አንድ ቀን ናቡከደነፆር “ይህች እኔ በጉልበቴ ብርታት ያሠራኋት . . . ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?” ሲል በጉራ ተናገረ። ይሁን እንጂ ዳንኤል 4:30-36 እንደሚለው “ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ” አእምሮው ተለወጠ። ለሰባት ዓመታት አገሩን ማስተዳደር ተስኖት ልክ ዳንኤል እንደተናገረው ሣር ሲበላ ቆየ። ከዚያ በኋላ መንግሥቱ ተመለሰለት። ይህ ሁሉ ምን ትንቢታዊ ትርጉም እንዳለው ታውቃለህ? የትንቢቱ ዋነኛ ፍጻሜ እንዴት ወደ መጨረሻው ዘመን እንደሚያመጣን ማስረዳት ትችላለህ?
ምሳሌ የሚሆኑ አንዳንድ ትንቢቶች
17. ናቡከደነፆር የዓለም ገዢ ሆኖ በነገሠበት ሁለተኛ ዓመት ላይ ይሖዋ ያሳየውን ሕልም እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?
17 እስቲ አሁን በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ትንቢቶችን እንመልከት። ናቡከደነፆር የዓለም ኃያል ገዥ በሆነበት ሁለተኛ ዓመት ላይ (606/605 ከዘአበ) አምላክ አንድ አስደንጋጭ ሕልም አሳየው። ዳንኤል ምዕራፍ 2 እንደሚገልጸው ራሱ ወርቅ፣ ደረቱና ክንዶቹ ብር፣ ሆዱና ጭኖቹ ነሐስ፣ ቅልጥሞቹ ብር፣ እግሮቹ ደግሞ የብረትና የሸክላ ድብልቅ የሆነ ግዙፍ ምስል ተመለከተ። የዚህ ምስል የተለያዩ ክፍሎች ምን ያመለክታሉ?
18. የሕልሙ ምስል የወርቅ ራስ፣ የብር ደረትና ክንዶች፣ እንዲሁም የነሐስ ሆድና ጭኖች ምን ይወክላሉ?
18 የይሖዋ ነቢይ ለናቡከደነፆር “አንተ ንጉሥ ሆይ፣ . . . አንተ የወርቁ ራስ ነህ” ብሎታል። (ዳንኤል 2:37, 38) ናቡከደነፆር የባቢሎንን ግዛት ያስተዳድር የነበረው ሥርወ መንግሥት ራስ ነበር። ይህ ሥርወ መንግሥት በምስሉ የብር ደረትና ክንዶች በተመሰለው የሜዶ ፋርስ መንግሥት ተገለበጠ። ከዚያ ቀጥሎ በነሐሱ ሆድና ጭኖች የተመሰለው የግሪክ መንግሥት ተነሳ። የዚህ የዓለም ኃያል መንግሥት አነሳስ እንዴት ነበር?
19, 20. ታላቁ እስክንድር ማን ነው? ግሪክ የዓለም ኃያል መንግሥት እንድትሆን በማድረግ ረገድስ ምን ሚና ተጫውቷል?
19 በዚህኛው የዳንኤል ትንቢት አፈጻጸም ረገድ ቁልፍ ሚና የተጫወተው በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተነሣ አንድ ወጣት ሰው ነበር። የተወለደው በ356 ከዘአበ ሲሆን ዓለም ታላቁ እስክንድር የሚል ስያሜ ሰጥቶታል። አባቱ ፊሊፕ በ336 ከዘአበ ሲገደል የ20 ዓመቱ እስክንድር የመቄዶንያን ዙፋን ወረሰ።
20 እስክንድር በ334 ከዘአበ ግንቦት መጀመሪያ ላይ የወረራ ዘመቻውን ጀመረ። ሠላሳ ሺ እግረኞችንና 5, 000 ፈረሰኞችን ያካተተ ጥሩ የውጊያ ብቃት የነበረው፣ ግን በቁጥር አነስተኛ የሆነ ጦር ነበረው። በትንሿ እስያ (በአሁኗ ቱርክ) ሰሜናዊ ምዕራብ በሚገኘው በግረናይከስ ወንዝ በ334 ከዘአበ በፋርሳውያን ላይ የመጀመሪያውን ድል ተቀዳጀ። እስከ 326 ከዘአበ ድረስ ይህ ግንባሩን የማያጥፍ ጦረኛ ፋርሳውያንን ከማስገበሩም በላይ ግዛቱን የዛሬዋ ፓኪስታን እስከምትገኝበት እስከ ኢንደስ ወንዝ አስፋፋ። ይሁን እንጂ እስክንድር በባቢሎን እንዳለ በመጨረሻ ውጊያው ድል ተነሳ። ሰኔ 13 ቀን 323 ከዘአበ 32 ዓመት ከስምንት ወር ብቻ በሕይወት ኖሮ ኃያል ጠላት ለሆነው ለሞት እጁን ሰጠ። (1 ቆሮንቶስ 15:55) ሆኖም በዳንኤል ትንቢት እንደተተነበየው ግሪክ በእስክንድር ወረራ የዓለም ኃያል መንግሥት ልትሆን ችላለች።
21. ከሮም መንግሥት በተጨማሪ በሕልሙ ምስል የብረት እግሮች የተመሰለው ሌላው የዓለም ኃያል መንግሥት ማን ነው?
21 የግዙፉ ምስል የብረት ቅልጥሞች ምን ያመለክታሉ? የግሪክን መንግሥት የሰባበረውና ያደቀቀው ብረት መሰሉ ሮም ነበር። ሮማ ኢየሱስ ክርስቶስ ላወጀው የአምላክ መንግሥት ምንም ዓይነት አክብሮት ባለማሳየቷ ኢየሱስን በ33 እዘአ በመከራ እንጨት ላይ አስገድላለች። ሮም እውነተኛ ክርስትናን ለማጥፋት ባደረገችው ሙከራ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት አሳድዳለች። ይሁን እንጂ በናቡከደነፆር ሕልም የታየው ምስል የብረት እግር የሮማን መንግሥት ብቻ ሳይሆን ከሮማ መንግሥት የወጣውን ፖለቲካዊ ቅጥያ ማለትም የአንግሎ አሜሪካን የዓለም ኃያል መንግሥት ጭምር ያመለክታል።
22. የሕልሙ ምስል ወደ ፍጻሜው ዘመን ጠልቀን መግባታችንን እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው?
22 በጥንቃቄ የሚደረግ ጥናት ወደ ፍጻሜው ዘመን ጠልቀን መግባታችንን ያረጋግጣል። ምክንያቱም በሕልሙ ምስል ላይ በታየው የብረትና የሸክላ ጣቶች ባሉበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንዶቹ መንግሥታት ብረት መሰል ወይም አምባገነን ሲሆኑ አንዳንዶቹ ግን ሸክላ መሰል ናቸው። ምንም እንኳን የሰው ልጅ የተሠራበት የሸክላ አፈር በቀላሉ የመሰባበር ባሕርይ ቢኖረውም ብረት መሰል የሆነው የገዢው ክፍል ተራው ሕዝብ አገዛዝን በተመለከተ ሐሳቡን እንዲገልጽ ለመፍቀድ ተገድዷል። (ዳንኤል 2:43፤ ኢዮብ 10:9) እርግጥ ነው ፈላጭ ቆራጭ የሆነው የገዢው መደብና ተራው ሕዝብ አንድ ላይ ሊጣበቁ የሚችሉት የብረትና የሸክላ ያክል ብቻ ነው። ይሁንና የአምላክ መንግሥት ይህን በፖለቲካ የተፈረካከሰ ዓለም በቅርቡ ድምጥማጡን ያጠፋዋል።—ዳንኤል 2:44
23. በብልጣሶር የግዛት ዘመን የመጀመሪያ ዓመት ላይ ዳንኤል ያየውን ሕልምና ራእይ እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?
23 አእምሮ የሚመስጠው የዳንኤል ትንቢት 7ኛ ምዕራፍም ወደ ፍጻሜው ዘመን ያመጣናል። ይህ ምዕራፍ በባቢሎናዊው ንጉሥ ብልጣሶር የመጀመሪያ ዘመነ መንግሥት የተፈጸመውን ሁኔታ ይተርካል። በሰባዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ ይገኝ የነበረው ዳንኤል “በአልጋው ላይ ሕልምንና የራሱን ራእይ አየ።” ይህ ራእይ እጅግ አስፈርቶት ነበር! “እነሆም” በማለት በአድናቆት ይጀምራል። “አራቱ የሰማይ ነፋሳት በታላቁ ባሕር ላይ ይጋጩ ነበር። አራትም ታላላቅ አራዊት ከባሕር ወጡ፣ እያንዳንዲቱም ልዩ ልዩ ነበረች።” (ዳንኤል 7:1-8, 15) እንዴት ያሉ የሚያስገርሙ አራዊት ናቸው! የመጀመሪያው ክንፍ ያለው አንበሳ ሲሆን ሁለተኛው ድብ የሚመስል ነበር። ከዚያም አራት ክንፎችና አራት ራሶች ያሉት ነብር ቀጠለ! በጣም ብርቱ የነበረው አራተኛ አውሬ ትላልቅ የብረት ጥርሶችና አሥር ቀንዶች ነበሩት። ከአሥር ቀንዶቹ መካከል “እንደ ሰው ዓይኖች የነበሩ ዓይኖች፣ በትዕቢትም የሚናገር አፍ” ያለው ትንሽ ቀንድ ወጣ። እንዴት ያለ እንግዳ ፍጡር ነው!
24. በዳንኤል 7:9-14 መሠረት ዳንኤል በሰማይ ምን ነገር ተመለከተ? ይህስ ራእይ ምን ያመለክታል?
24 ቀጥሎ የዳንኤል ራእይ በሰማይ ወደ ተፈጸሙ ሁኔታዎች ዞር ይላል። (ዳንኤል 7:9-14) ‘በዘመናት የሸመገለው’ ይሖዋ አምላክ በገናና ዙፋኑ ላይ ለዳኝነት ተቀምጦ ይታያል። ‘ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍ በፊቱ ቆመዋል።’ በአራዊቱ ላይ ይፈርድና ግዛታቸውን ነጥቆ ከወሰደ በኋላ አራተኛውን አውሬ ያጠፋዋል። “ወገኖች አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ” ይገዙለት ዘንድ ዘላለማዊ ሥልጣን ‘የሰው ልጅ ለሚመስል’ ተሰጠ። ይህ የሚያመለክተው የፍጻሜውን ዘመን እና የሰው ልጅ የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 መንገሡን ነው።
25, 26. የዳንኤልን መጽሐፍ በምናነብበት ጊዜ ምን ጥያቄዎች ሊነሱብን ይችላሉ? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የትኛው መጽሐፍ ሊረዳን ይችላል?
25 የዳንኤልን መጽሐፍ የሚያነብ ማንኛውም ሰው በርካታ ጥያቄዎች እንደሚመጡበት የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይ የተገለጹት አራት አራዊት ምን ያመለክታሉ? በዳንኤል 9:24-27 ላይ የተገለጹት የትንቢታዊዎቹ ‘ሰባ ሳምንታት’ ትርጉም ምንድን ነው? ስለ ዳንኤል ምዕራፍ 11 እንዲሁም በዚያ ላይ ስለተጠቀሱት ስለ ‘ሰሜኑ’ እና ስለ ‘ደቡቡ’ ንጉሥ ትንቢታዊ ግጭትስ ምን ለማለት ይቻላል? በዚህ የፍጻሜ ዘመን ስለ እነዚህ ነገሥታት ምን መጠበቅ እንችላለን?
26 ይሖዋ በዳንኤል 7:18 ላይ “የልዑሉ ቅዱሳን” ተብለው ለተጠሩት በዚህ ምድር ላይ ለሚገኙት ቅቡዓን አገልጋዮቹ እንደነዚህ ስላሉት ጉዳዮች የሚያስፈልገውን ማስተዋል ሰጥቷቸዋል። ከዚህም በላይ “ታማኝና ልባም ባሪያ” በመንፈስ የተጻፈውን የነቢዩ ዳንኤል ትንቢት ሁላችንም በይበልጥ እንድናስተውል የሚያስችለንን ዝግጅት አድርጓል። (ማቴዎስ 24:45) ይህም በቅርቡ ታትሞ በወጣው የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! በተባለው መጽሐፍ ላይ ይገኛል። ይህ በተዋቡ ሥዕላዊ መግለጫዎች ያሸበረቀው ባለ 320 ገጽ ጽሑፍ እያንዳንዱን የዳንኤል መጽሐፍ ክፍል ይሸፍናል። የተወደደው ነቢይ ዳንኤል የመዘገባቸውን እምነት የሚገነቡ ትንቢቶችና ትረካዎች በሙሉ አንድ በአንድ ያብራራል።
ለዘመናችን ትልቅ ትርጉም ያለው
27, 28. (ሀ) በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች ፍጻሜ በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል? (ለ) የምንኖረው በየትኛው ዘመን ላይ ነው? ምንስ ማድረግ አለብን?
27 አሁን፣ የሚከተለውን ቁም ነገር ልብ በል። ከጥቂት ዝርዝር ጉዳዮች በስተቀር በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶች በሙሉ ተፈጽመዋል። ለምሳሌ ያህል በዳንኤል ምዕራፍ 2 ላይ በተገለጸው የሕልም ምስል እግሮች የተተነበየውን የዓለም ሁኔታ አሁን እያየን ነው። በዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ የተጠቀሰው የዛፉ ጉቶ መሲሐዊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 በዙፋን ላይ በተቀመጠበት ጊዜ ተፈትቷል። አዎን፣ በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይ በተተነበየው መሠረት በዘመናት የሸመገለው ለሰው ልጅ ግዛት ሰጥቶታል።—ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 16:27 እስከ 17:9
28 በዳንኤል ምዕራፍ 8 ላይ የተጠቀሱት 2, 300 ቀናትና 1, 290 ቀናት እንዲሁም በምዕራፍ 12 ላይ የተጠቀሱት 1, 335 ቀናት ሁሉም አልፈዋል። የዳንኤል ምዕራፍ 11 ጥናት እንደሚያሳየው ‘በሰሜኑ ንጉሥ’ እና ‘በደቡቡ ንጉሥ’ መካከል ሲታይ የኖረው ግጭት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ይህ ሁሉ ወደ ፍጻሜው ዘመን ጠልቀን የገባን መሆናችንን የሚያሳዩትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች ያጠናክራል። በዘመናት ሂደት ውስጥ በጣም ልዩ በሆነ ዘመን የምንኖር መሆናችንን በመገንዘብ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ለማድረግ መሆን ይኖርበታል? የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት መከታተል እንዳለብን ምንም ጥርጥር የለውም።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
• አምላክ ያለንበትን ዘመን በተመለከተ የሰው ዘር በሙሉ ምን እንዲያውቅ ይፈልጋል?
• የዳንኤል መጽሐፍ እምነታችንን የሚገነባው እንዴት ነው?
• ናቡከደነፆር በሕልም ያየው ምስል ምን ገጽታዎች አሉት? እነዚህስ ምን ያመለክታሉ?
• በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ትንቢቶች ፍጻሜ በተመለከተ ምን ነገር ሊስተዋል ይገባዋል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]