በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንጌሎች—እውነተኛ ታሪክ ናቸው ወይስ ተረት?

ወንጌሎች—እውነተኛ ታሪክ ናቸው ወይስ ተረት?

ወንጌሎች​—እውነተኛ ታሪክ ናቸው ወይስ ተረት?

በዓለም ዙሪያ የሰው ልጅን ታሪክ አቅጣጫ ስለለወጠው ወጣት ማለትም ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ የሚገልጸው ታሪክ የሰው ልጅ ኅብረተሰብ መሠረታዊ አካል ሆኗል። ሰዎች መደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከሚማሯቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ ነው። ብዙዎች “ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን” እንደሚለው ያሉትን በወንጌል ውስጥ የሚገኙ ዘገባዎች የሚመለከቷቸው ጊዜ እንደማይሽራቸው እውነታዎችና አባባሎች አድርገው ነው። (ማቴዎስ 5:​37፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እንዲያውም፣ ክርስቲያን ሆኑም አልሆኑ ወላጆችህ በወንጌል ውስጥ የሚገኙ ዘገባዎችን ተጠቅመው አስተምረውህ ሊሆን ይችላል።

በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው የክርስቶስ ተከታዮች ወንጌሎችን የሚመለከቷቸው ለእርሱ ሲሉ ሥቃይ ለመቀበልና ለመሞት ፈቃደኛ ስለሆኑለት ሰው የሚናገሩ ዘገባዎች አድርገው ነው። በተጨማሪም ወንጌሎች የድፍረት፣ የጽናት፣ የእምነትና የተስፋ መሠረትና ምንጭ ናቸው። እንግዲያው እነዚህን ዘገባዎች ከተራ ልብ ወለዶች ጎራ ከመፈረጃቸው በፊት ምንም የማያከራክር ማስረጃ መቅረብ አለበት ቢባል አትስማማም? የወንጌል ዘገባዎች በሰው ልጆች አስተሳሰብና ባሕርይ ላይ ካሳደሩት ከፍተኛ ተጽዕኖ አንጻር ስታየው አንድ ሰው በዘገባዎቹ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ለማንሳት ቢፈልግ አሳማኝ ማስረጃ እንዲያቀርብ አትጠብቅበትምን?

ከዚህ ቀጥሎ ወንጌሎችን በሚመለከት ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ በርከት ያሉ ጥያቄዎችን እንድትመረምር እንጋብዝሃለን። ክርስቲያን ያልሆኑትን ጨምሮ በወንጌሎች ላይ ጥናት ያካሄዱ የተወሰኑ ምሁራን እነዚህን ጥያቄዎች በሚመለከት ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንዳላቸው ራስህ ተመልከት። ከዚያም የራስህ የሆነ በእውቀት ላይ የተመሠረተ መደምደሚያ ላይ ልትደርስ ትችላለህ።

ሊጤኑ የሚገባቸው ጥያቄዎች

ወንጌሎች በረቀቀ መንገድ የተዘጋጁ ድንቅ የፈጠራ ሥራ ሊሆኑ ይችላሉን?

የኢየሱስ ሴሚናር መሥራች የሆኑት ሮበርት ፈንክ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ‘መሲሑን’ ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ሕልውና ካገኘው ከክርስትና መሠረተ ትምህርት ጋር ሊጣጣም በሚችልበት መንገድ ‘አቅርበውታል።’” ይሁን እንጂ ወንጌሎች በተጻፉበት ወቅት ኢየሱስ የተናገራቸውን ትምህርቶች ያዳመጡ፣ ያደረጋቸውን በርካታ ሥራዎች የተመለከቱና ከሞት ከተነሳ በኋላ ያዩት በርካታ ሰዎች ገና በሕይወት ነበሩ። የወንጌል ጸሐፊዎች የማጭበርበር ድርጊት እንደፈጸሙ አድርገው አልወነጀሏቸውም።

የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ተመልከት። የኢየሱስን ሞትና ትንሣኤ በሚመለከት አስተማማኝ ዘገባ ያሠፈሩት የወንጌል ጸሐፊዎች ብቻ ሳይሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተካቶ በሚገኘው በጥንቷ ቆሮንቶስ ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖች በላከው በመጀመሪያው ደብዳቤ ላይም ይህንኑ ጉዳይ አስፍሯል። እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ:- መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፣ ተቀበረም፣ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፣ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ።” (1 ቆሮንቶስ 15:​3-8) እነዚህ የዓይን ምሥክሮች ከኢየሱስ ሕይወት ጋር ለተያያዙት የታሪክ እውነታዎች እማኞች ናቸው።

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ዘመናዊ ተቺዎች የሚሉት ዓይነት የፈጠራ ሐሳብ አይንጸባረቅባቸውም። ይልቁንም እንዲህ ዓይነቱ የፈጠራ መንፈስ የተንጸባረቀው በሁለተኛው መቶ ዘመን በተዘጋጁ ሰነዶች ላይ ነው። በመሆኑም ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ አንዳንድ ታሪኮች የተዘጋጁት ክህደት ከሐዋርያዊው ጉባኤ በራቁ ማኅበረሰቦች ውስጥ ከእውነተኛ ክርስትና መካከል ብቅ ባለ ጊዜ ነበር።​—⁠ሥራ 20:​28-30

ወንጌሎች አፈ ታሪክ ሊሆኑ ይችላሉን?

ደራሲና ሃያሲ የሆኑት ሲ ኤስ ሌዊስ ወንጌሎችን እንደ አፈ ታሪክ አድርገው መመልከቱን አስቸጋሪ ሆኖ አግኝተውታል። “የሥነ ጽሑፍና የታሪክ ሰው እንደመሆኔ መጠን ምንም ይሁን ምን ወንጌሎች አፈ ታሪክ አለመሆናቸውን ሙሉ በሙሉ አምኛለሁ” በማለት ጽፈዋል። “አቀራረባቸው አፈ ታሪክ ሊያሰኛቸው የሚችል አይደለም። . . . አብዛኛውን የኢየሱስ የሕይወት ታሪክ አናውቅም። አፈ ታሪክ የሚጽፉ ሰዎች ደግሞ እንዲህ አያደርጉም።” የታወቁት ታሪክ ጸሐፊ ኤች ጂ ዌልስ ክርስቲያን ነኝ የሚሉ ሰው ባይሆኑም እንኳ የተናገሩት ነገር ትኩረት የሚስብ ነው:- “አራቱም [የወንጌል ጸሐፊዎች] ስለ አንድ ሰው እርስ በርሱ የሚስማማ መግለጫ ይሰጡናል። . . . በእውነታው ላይ ጽኑ እምነት እንደነበራቸው ተንጸባርቋል።”

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ የተገለጠበትን አንድ ሁኔታ ተመልከት። አንድ የራሱን ሐሳብ ፈጥሮ የሚጽፍ ሰው ኢየሱስ በሚያስደንቅ መንገድ ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንደተመለሰ፣ ወሳኝ የሆነ ንግግር እንዳቀረበ ወይም አንጸባራቂ ብርሃን እንደተጎናጸፈ አድርጎ ሊገልጸው ይችል ነበር። የወንጌል ጸሐፊዎች ግን የገለጹት እንዲሁ በደቀ መዛሙርቱ ፊት መጥቶ እንደቆመ አድርገው ነው። “ልጆች ሆይ፣ አንዳች የሚበላ አላችሁን?” በማለት ጠየቃቸው። (ዮሐንስ 21:​5) ግሬግ ኢስተርብሩክ የተባሉ ምሁር “እነዚህ መግለጫዎች በእውነተኛ ዘገባ ውስጥ እንጂ በፈጠራ ታሪክ ውስጥ ሊንጸባረቁ የሚችሉ አይደሉም” በማለት የመደምደሚያ ሐሳብ ሰጥተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ወንጌሎች አፈ ታሪክ ናቸው የሚለው ክስ ወንጌሎች በተጻፉበት ወቅት ረቢዎች በስፋት ይጠቀሙበት ከነበረው የማስተማሪያ ዘዴ ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ይሆናል። በዚያን ጊዜ የነበረው የማስተማሪያ ዘዴ በመደጋገም ወይም በመሸምደድ በቃል የሚደረግ ጥናት ነው። ይህም የኢየሱስ ንግግሮችና ድርጊቶች ተፈልስፈው መቅረባቸውን ሳይሆን በትክክልና በጥንቃቄ የሰፈሩ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።

ወንጌሎች አፈ ታሪክ ቢሆኑ ኖሮ ኢየሱስ ከሞተ በኋላ በዚያን ያህል አጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅረው ሊቀርቡ ይችሉ ነበርን?

የተገኙት ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት ወንጌሎቹ የተጻፉት ከ41 እስከ 98 እዘአ ባሉት ዓመታት ውስጥ ነው። ኢየሱስ የሞተው በ33 እዘአ ነው። ይህ ማለት ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚናገሩት ዘገባዎች የተጠናቀሩት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ኢየሱስ አገልግሎቱን ከፈጸመ በኋላ በነበረው አጭር ጊዜ ውስጥ ነው። ይህም በወንጌል ውስጥ የሚገኙት ትረካዎች አፈ ታሪክ ናቸው የሚለውን አስተያየት በእጅጉ የሚቃረን ይሆናል። አፈ ታሪኮች ተፈጥረው መልክ እስኪይዙ ድረስ ጊዜ ይወስዳሉ። የጥንቱ የግሪክ ባለ ቅኔ ሆመር የደረሳቸውን ኢሊያድ እና ኦዲሲ የተባሉትን እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። እነዚህ ስለ ጀግንነት የሚያወሱ ሁለት አፈ ታሪኮች እስኪዳብሩና አንድ ወጥ መልክ እስኪይዙ ድረስ በርካታ መቶ ዓመታት እንደወሰዱ አንዳንዶች ያምናሉ። ስለ ወንጌሎችስ ምን ለማለት ይቻላል?

ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት ቄሣር እና ክርስቶስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ጥቂት ተራ ሰዎች ይህን የመሰለ ከፍተኛ የመለወጥ ኃይልና ተወዳጅነት ያለው ሰው፣ ይህን የመሰለ ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃና ሰብዓዊ ወንድማማችነት ለመፈልሰፍ ከቻሉ በወንጌሎች ውስጥ ከተጻፉት ተአምራት ሁሉ ይበልጥ ለማመን የሚያዳግት ተአምር ይሆናል። ከሁለት ምዕተ ዓመት የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት በኋላ የክርስቶስን ሕይወት፣ ባሕርይና ትምህርት ጨምቆ የሚያቀርበው ታሪክ አሁንም ቢሆን በአመዛኙ ግልጽና በምዕራቡ ዓለም የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስደናቂ የሆነውን ገጽታ ይዟል።”

ወንጌሎች በጥንት ዘመን ከነበረው የክርስትና ማኅበረሰብ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣሙ ሲባል ከጊዜ በኋላ ለውጥ ተደርጎባቸዋልን?

አንዳንድ ተቺዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ማኅበረሰብ ፖለቲካ የወንጌል ጸሐፊዎች በኢየሱስ ታሪክ ላይ አንዳንድ ለውጥ እንዲያደርጉ ወይም በታሪኩ ላይ ተጨማሪ ሐሳብ እንዲያክሉ አድርጓቸዋል በማለት ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ ወንጌሎችን ቀረብ ብለን ከመረመርን እንዲህ ዓይነት ለውጥ እንዳልተደረገባቸው እንረዳለን። በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ የሚገኘው የኢየሱስ ታሪክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በተፈጸመ የማጭበርበር ድርጊት ተለውጦ ከሆነ በጽሑፉ ውስጥ የሚገኙት ስለ አይሁድና ስለ አሕዛብ የተነገሩት አሉታዊ አስተያየቶች እስከ አሁን ድረስ እንዴት ተጠብቀው ሊቆዩ ቻሉ?

ኢየሱስ የሰጠው ሐሳብ በቀጥታ የተጠቀሰበትን በ⁠ማቴዎስ 6:​5-7 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። “ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኵራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፣ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።” ይህ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎችን ለማውገዝ ተብሎ የተነገረ ቃል እንደሆነ ግልጽ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ “አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ” በማለት ተናግሯል። የወንጌል ጸሐፊዎች ኢየሱስ የተናገረውን በዚህ መንገድ በመጥቀስ አዳዲስ ሰዎችን እምነት ለማስለወጥ እየሞከሩ አልነበረም። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የተናገራቸውን ነገሮች መመዝገባቸው ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ወደ ተቀበረበት መቃብር ስለሄዱትና ባዶ ሆኖ ስላገኙት ሴቶች የሚናገረውን የወንጌል ዘገባ ተመልከት። (ማርቆስ 16:​1-8) ግሬግ ኢስተርብሩክ እንዳሉት ከሆነ “በጥንቱ የመካከለኛው ምሥራቅ ኅብረተሰብ ዘንድ ሴቶች የሚሰጡት ምሥክርነት ተአማኒነት አያገኝም ነበር። ለምሳሌ ያህል ሁለት ወንዶች በሚሰጡት ምሥክርነት አንዲት ሴት ዝሙት እንደፈጸመች ተደርጋ ልትወነጀል ትችል ነበር፤ በሌላው በኩል ግን የትኛዋም ሴት በምትሰጠው ምሥክርነት አንድ ወንድ በጥፋተኝነት መወንጀል አይቻልም ነበር።” የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ቢሆኑ ሴቶቹ የሰጡትን ምሥክርነት አላመኑም! (ሉቃስ 24:​11) ስለዚህ እንዲህ ያለው ታሪክ በፈጠራ የተጻፈ ነው ብሎ ለማመን በጣም ያስቸግራል።

በመልእክቶችና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ምሳሌዎች አለመኖራቸው በወንጌሎች ውስጥ የሚገኙት ምሳሌዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የጨመሯቸው ሳይሆኑ ኢየሱስ ራሱ የተናገራቸው ለመሆናቸው ጠንካራ ማስረጃ ነው። በተጨማሪም ወንጌሎችን ከመልእክቶች ጋር በጥንቃቄ ማወዳደሩ ጳውሎስ የተናገራቸው ቃላትም ሆኑ ሌሎቹ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሐፊዎች የተናገሯቸው ቃላት ኢየሱስ የተናገራቸውንና የተወሰነ ለውጥ አድርገውባቸው የጻፏቸው እንዳልሆኑ ያረጋግጣሉ። በጥንት ዘመን የነበረው የክርስቲያን ማኅበረሰብ አንዳንድ ሐሳቦችን ኢየሱስ እንደተናገራቸው አድርጎ አቅርቦ ቢሆን ኖሮ በመልእክት ውስጥ የሚገኙ ቢያንስ የተወሰኑ ሐሳቦችን በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ እናገኛለን ብለን መጠበቅ ይኖርብናል። እንዲህ ያለ ነገር ለማግኘት አለመቻላችን የወንጌል ጽሑፎች ከጊዜ በኋላ የተለወጡ ሳይሆኑ ትክክለኛ ናቸው ብለን እንድንደመድም ያደርገናል።

በወንጌሎች ውስጥ ስላሉት እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ስለሚመስሉ ዘገባዎችስ ምን ለማለት ይቻላል?

ተቺዎች ወንጌሎች እርስ በርሳቸው በሚጋጩ ዘገባዎች የተሞሉ እንደሆኑ አድርገው መናገር ከጀመሩ ቆይተዋል። ታሪክ ጸሐፊው ዱራንት የገለልተኝነትን አቋም በመያዝ የወንጌል ዘገባዎችን እንደ ታሪካዊ ሰነዶች አድርገው በመመልከት ለመመርመር ጥረት አድርገዋል። እርስ በርሳቸው የሚጋጩ የሚመስሉ ዘገባዎች መኖራቸውን ከተናገሩ በኋላ የሚከተለውን የመደምደሚያ አስተያየት ሰጥተዋል:- “ይጋጫሉ የተባሉት ሐሳቦች ይሄን ያህል ክብደት የሚሰጣቸው ሳይሆኑ [ተራ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች] ናቸው። ወንጌሎቹ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በሚያስገርም ሁኔታ እርስ በርሱ የሚስማማ ዘገባ ያቀረቡ ሲሆን ክርስቶስን አንድ ወጥ በሆነ መንገድ ስለውታል።”

እርስ በርስ የሚጋጩ የሚመስሉት በወንጌል ውስጥ የሚገኙት ዘገባዎች ብዙውን ጊዜ በቀላሉ መፍትሔ የሚያገኙ ናቸው። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ማቴዎስ 8:​5 ላይ “የመቶ አለቃ ወደ እርሱ [ኢየሱስ] ቀርቦ” አገልጋዩን እንዲፈውስለት “ለመነው” ይላል። ሉቃስ 7:​3 ላይ የመቶ አለቃው “የአይሁድን ሽማግሎች ወደ እርሱ [ኢየሱስ] ላከና መጥቶ ባሪያውን እንዲያድን ለመነው” ይላል። የመቶ አለቃው ሽማግሌዎቹን ወኪሎቹ አድርጎ ልኳቸዋል። ሰውዬው ልመናውን ያቀረበው እንደ ቃል አቀባዮቹ አድርጎ በተጠቀመባቸው ሽማግሌዎች በኩል በመሆኑ ማቴዎስ የመቶ አለቃው ራሱ ኢየሱስን እንደለመነ አድርጎ ጽፏል። ይህ በወንጌል ውስጥ ልዩነት እንዳላቸው ተደርገው የሚታዩ ሐሳቦች በቀላሉ መፍትሔ ሊገኝላቸው እንደሚችል የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ነው።

ወንጌሎች እውነተኛ ታሪክ ሊያሟላ የሚገባውን መስፈርት አያሟሉም ብለው ስለሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎችስ ምን ሊባል ይቻላል? ዱራንት በመቀጠል እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “ተቺዎች የደረሱባቸው ግኝቶች በፈጠሩባቸው ልዩ ስሜት በመነሳሳት የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ትክክለኛነት ለመመዘን የተጠቀሙበትን ድርቅ ያለ መስፈርት እንደ ሃሙራቢ፣ ዳዊትና ሶቅራጥስ ያሉ በጥንት ጊዜ የነበሩ በርካታ ታዋቂ ሰዎች በእርግጥ በሕይወት የነበሩ ሰዎች መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ብንጠቀምበት እነዚህም ሰዎች የአፈ ታሪክ ገጸ ባሕርያት ናቸው ወደሚል መደምደሚያ ልንደርስ እንችላለን። የወንጌል ጸሐፊዎች ወገናዊና ሃይማኖታዊ ጥላቻን ሳይፈሩ ሐዋርያት በመንግሥቱ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ለማግኘት ያደረጉትን ፉክክር፣ ኢየሱስ በተያዘ ጊዜ መሸሻቸውንና ጴጥሮስ ኢየሱስን መካዱን የመሰሉ ፈጥረው የሚጽፉ ሰዎች ሊደብቋቸው የሚችሏቸውን በርካታ ክስተቶች ዘግበዋል። . . . እነዚህን ዘገባዎች የሚያነብ ማንኛውም ሰው ከእነርሱ በስተጀርባ ያለውን ስብዕና ትክክለኛ ሕልውና ሊጠራጠር አይችልም።”

በዘመናችን ያለው ክርስትና በወንጌሎች ውስጥ የተገለጸውን ኢየሱስን ይወክላል?

የኢየሱስ ሴሚናር በወንጌሎች ላይ ያደረገው ምርምር “በቤተ ክርስቲያን የመማክርት ጉባኤ አመ​ራር የተካሄደ እንዳልሆነ” ገልጿል። ይሁን እንጂ ታሪክ ጸሐፊው ዌልስ ወንጌሎች ውስጥ ተመዝግበው በሚገኙት የኢየሱስ ትምህርቶችና በሕዝበ ክርስትና ትምህርቶች መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ ተገንዝበዋል። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የኢየሱስ ሐዋርያት ኢየሱስ ስለ ሥላሴ ሲናገር እንደሰሙ የሚጠቁም ማስረጃ የለም። . . . በተጨማሪም [ኢየሱስ] እናቱ ማርያም የሰማይ ንግሥት ተብላ እንደምትጠራው አይሲስ ትመለክ የሚል ቃል አልወጣውም። በአምልኮም ሆነ በሃይማኖታዊ ልማድ የሕዝበ ክርስትና መለያ ስለሆኑት ትምህርቶች የተናገረው ነገር የለም።” ስለዚህ አንድ ሰው በሕዝበ ክርስትና ትምህርቶች ላይ ተመርኩዞ የወንጌሎችን ዋጋማነት ሊመዝን አይችልም።

ምን መደምደሚያ ላይ ደረስክ?

ከላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦች ከመረመርህ በኋላ ምን መደምደሚያ ላይ ደረስክ? ወንጌሎች ተረት ናቸው ሊያሰኝ የሚችል እውነተኛና አሳማኝ ማስረጃ አለ? በወንጌሎች ትክክለኝነት ላይ የተነሱት ጥያቄዎችና ጥርጣሬዎች ተዓማኒነት የጎደላቸውና አሳማኝ እንዳልሆኑ ብዙዎች ተገንዝበዋል። የራስህን የግል አስተያየት መስጠት እንድትችል አእምሮህን ክፍት አድርገህ ወንጌሎችን ማንበብ ይኖርብሃል። (ሥራ 17:​11) ወንጌሎች ስለ ኢየሱስ የሚሰጡትን እርስ በርሱ የሚስማማ፣ ሃቀኛና ትክክለኛ ሐሳብ ስትመረምር እነዚህ ዘገባዎች የአፈ ታሪክ ስብስብ አለመሆናቸውን ትገነዘባለህ። a

መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ከመረመርክና የሚሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ካዋልክ ሕይወትን በተሻለ መንገድ እንዴት ሊለውጠው እንደሚችል ትመለከታለህ። (ዮሐንስ 6:​68) በተለይ ደግሞ በወንጌል ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት እንዲህ ዓይነት ለውጥ ያስከትላሉ። ከዚህም በላይ ታዛዥ የሆኑ የሰው ዘሮች ወደፊት ስለሚጠብቃቸው አስደናቂ ጊዜም ትምህርት ልታገኝ ትችላለህ።​—⁠ዮሐንስ 3:​16፤ 17:​3, 17

[የግርጌ ማስታወሻ]

a መጽሐፍ ቅዱስ​—⁠የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ከምዕራፍ 5 እስከ 7 ድረስ እንዲሁም ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተባለውን ብሮሹር ተመልከት። ሁለቱም ጽሑፎች ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጁ ናቸው።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የትክክለኛ ዘገባ ማስረጃ

ቀደም ሲል መጽሐፍ ቅዱስን ይተቹ የነበሩ አንድ አውስትራሊያዊ ጸሐፊ ተውኔት ከጥቂት ዓመታት በፊት ስህተታቸውን አምነው በመቀበል እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ዘጋቢ መጀመሪያ ላይ ሊያደርገው የሚገባውን ተግባር በማከናወን ያሰባሰብኳቸውን መረጃዎች መረመርኩ። . . . [በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ] ያነበብኩት ነገር አፈ ታሪክና እውነታን የተላበሰ ልብ ወለድ አለመሆኑን ስገነዘብ በጣም ደነገጥኩ። ትክክለኛ ዘገባ ነው። ዘጋቢዎቹ በቀጥታ በዓይናቸው ያዩአቸውንና በጆሯቸው የሰሟቸውን እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች የሰሟቸውን እጅግ አስደናቂ ክንውኖች የያዘ ዘገባ ነው። . . . ዘገባ የራሱ የሆነ መለያ ባሕርይ ያለው ሲሆን ይህ መለያ ባሕርይ በወንጌሎች ውስጥ ተንጸባርቋል።”

በተመሳሳይም በኦክላንድ ዩኒቨርሲቲ በጥንቶቹ የግሪክና የሮም የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ፕሮፌሰር የሆኑት ኢ ኤም ብላይክሎክ የሚከተለውን ምክንያታዊ አስተያየት ሰንዝረዋል:- “የታሪክ ምሁር እንደ መሆኔ መጠን የጥንቱን የግሪኮችና የሮማውያን የሥነ ጽሑፍ ሥራ የማየው ከታሪክ አንጻር ነው። ስለ ክርስቶስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ የሚቀርቡት ማስረጃዎች የጥንቱን ታሪክ በሚመለከት ካሉት ከአብዛኞቹ መረጃዎች ይበልጥ ትክክለኛ እንደሆኑ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።”

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ፊንቄ

ገሊላ

የዮርዳኖስ ወንዝ

ይሁዳ

[ሥዕሎች]

‘ስለ ክርስቶስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ የሚቀርቡት ማስረጃዎች የጥንቱን ታሪክ በሚመለከት ካሉት ከአብዛኞቹ መረጃዎች ይበልጥ ትክክለኛ ናቸው።’​—ፕሮፌሰር ኢ ኤም ብላይክሎክ

[ምንጭ]

Background maps: Based on a map copyrighted by Pictorial Archive (Near Eastern History) Est. and Survey of Israel.