በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመለወጥ ላይ ያለው “የክርስትና እምነት” ገጽታ—በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለውን?

በመለወጥ ላይ ያለው “የክርስትና እምነት” ገጽታ—በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለውን?

በመለወጥ ላይ ያለው “የክርስትና እምነት” ገጽታ​—በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለውን ?

አንድ ሰዓሊ እንዲሥልህ ጠይቀኸዋል እንበል። ሲጨርስ ጥሩ አድርጎ ስለሳለህ በጣም ትደሰታለህ። ልጆችህ፣ የልጅ ልጆችህ እንዲሁም የእነሱ የልጅ ልጆች ሥዕሉን በታላቅ ኩራት ሲመለከቱት ይታይሃል።

ሆኖም የተወሰኑ ትውልዶች ካለፉ በኋላ ከልጅ ልጆችህ አንዱ ሥዕሉ ላይ የሚታየው የሸሸው ፀጉር ውበት እንደሚቀንስ ስለተሰማው ፀጉር እንዲጨመርበት ያደርጋል። ሌላው ደግሞ የአፍንጫው ቅርጽ ስላላስደሰተው ቅርጹ እንዲለወጥ ያደርጋል። በቀጣዮቹ ትውልዶች ሌሎች “ማሻሻያዎች” ከመደረጋቸው የተነሳ በመጨረሻ ሥዕሉ ከገጽታህ ጋር ያለው ተዛማችነት በጣም ውስን ይሆናል። ይህ ነገር እንደሚደርስ ብታውቅ ምን ይሰማሃል? እንደምትናደድ ምንም ጥርጥር የለውም።

የሚያሳዝነው ነገር፣ በመሠረቱ የዚህ ሥዕል ታሪክ የስመ ክርስትና ቤተ ክርስቲያን ያሳለፈውን ታሪክ የሚያሳይ ነው። ታሪክ እንደሚያሳየው የክርስቶስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በትንቢት በተናገረው መሠረት በይፋ የሚታወቀው “የክርስትና እምነት” ገጽታ መለወጥ ጀመረ።​—⁠ማቴዎስ 13:​24-30, 37-43፤ ሥራ 20:​30 a

እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በተለያዩ ባሕሎችና ዘመናት እንዲሠሩ ማድረግ አግባብነት ያለው ነገር ነው። በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ካለው አስተሳሰብ ጋር እንዲስማሙ ለማድረግ ሲባል የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን መለወጥ ግን ፈጽሞ የተለየ ነገር ነው። ሆኖም በእርግጥ የተፈጸመው ይኸው ነው። ለምሳሌ ያህል በርካታ በሚሆኑ ዓበይት ጉዳዮች ላይ የተደረጉትን ለውጦች ተመልከት።

ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት ጋር ቁርኝት ፈጠረች

ኢየሱስ የእሱ አገዛዝ ወይም መንግሥት ከሰማይ እንደሆነና ጊዜው ሲደርስ ማንኛውንም ሰብዓዊ አገዛዝ ደምስሶ በመላው ምድር ላይ እንደሚገዛ ተናግሯል። (ዳንኤል 2:​44፤ ማቴዎስ 6:​9, 10) የእሱ መንግሥት በሰብዓዊ የፖለቲካ ሥርዓት አማካኝነት አይገዛም። ኢየሱስ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:​16፤ 18:​36) በመሆኑም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሕግ አክባሪዎች ቢሆኑም እንኳ ከፖለቲካ ጉዳዮች ርቀዋል።

ሆኖም የሮማው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ሥልጣን ላይ በነበረበት በአራተኛው መቶ ዘመን በርካታ ክርስቲያን ነን ባዮች የክርስቶስን መመለስና የአምላክ መንግሥትን መቋቋም በትዕግሥት መጠበቅ ተስኗቸው ነበር። ቀስ በቀስ ለፖለቲካ የነበራቸው አመለካከት ተለወጠ። ዩሮፕ​—⁠ኤ ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ከቆስጠንጢኖስ በፊት ክርስቲያኖች ዓላማቸውን ለማራመድ የሚያገለግል መሣሪያ በማድረግ [የፖለቲካ] ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት አልነበራቸውም። ከቆስጠንጢኖስ በኋላ የክርስትና እምነትና ፖለቲካ እጅና ጓንት ሆኑ።” በአዲስ መልክ የተዋቀረው የክርስትና እምነት የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ኦፊሴላዊ “ሁሉን አቀፍ” ወይም “ካቶሊክ” ሃይማኖት ሆነ።

ግሬት ኤጅስ ኦቭ ማን የተባለው ኢንሳይክሎፒዲያ በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ከተፈጠረው ጥብቅ ትስስር የተነሳ “ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ385 ማለትም በክርስቲያኖች ላይ የደረሰው የመጨረሻው የስደት ማዕበል ካበቃ ከ80 ዓመት በኋላ ቤተ ክርስቲያን ራሷ ያፈነገጡትን መግደል የጀመረች ሲሆን የቀሳውስቱ ክፍል ደግሞ ከንጉሠ ነገሥታቱ የማይተናነስ ሥልጣን ይዞ ነበር” ሲል ገልጿል። በመሆኑም የሰዎችን እምነት ለመለወጥ በማሳመን ችሎታ ከመጠቀም ይልቅ ሰይፍ የተተካበት እንዲሁም የማዕረግ ስም ያላቸው የሥልጣን ጥመኛ የሆኑ ቀሳውስት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ትሑት ሰባኪያን ተክተው የመጡበት ዘመን ጠባ። (ማቴዎስ 23:​9, 10፤ 28:​19, 20) ታሪክ ጸሐፊው ኤች ጂ ዌልስ በአራተኛው መቶ ዘመን በነበረው የክርስትና እምነትና “የናዝሬቱ ኢየሱስ ባስተማረው ትምህርት” “መካከል ስላሉት ከፍተኛ ልዩነቶች” ጽፈዋል። እነዚህ “ከፍተኛ ልዩነቶች” ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ በሚሰጡት መሠረታዊ ትምህርቶች ላይ እንኳ ሳይቀር ተጽእኖ አሳድረዋል።

አምላክን በአዲስ መልክ ማቅረብ

ክርስቶስ እና ደቀ መዛሙርቱ ጥንታዊ በሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅልሎች ላይ ወደ 7, 000 ጊዜ ያህል በሚገኘው ይሖዋ በሚለው የግል ስሙ ተለይቶ የሚታወቅ “አንድ አምላክ አብ” ብቻ መኖሩን አስተምረዋል። (1 ቆሮንቶስ 8:​6፤ መዝሙር 83:​18 NW ) ኢየሱስ የአምላክ ፍጡር ነው። የካቶሊኩ ዱዌይ ቨርሽን መጽሐፍ ቅዱስ በቆላስይስ 1:​15 ላይ ኢየሱስ “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር” መሆኑን ይናገራል። በመሆኑም ኢየሱስ ፍጡር እንደመሆኑ መጠን “ከእኔ አብ ይበልጣል” ሲል በግልጽ ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 14:​28

ሆኖም በሦስተኛው መቶ ዘመን፣ ተደማጭነት የነበራቸው አንዳንድ ቀሳውስት አረማዊው የግሪክ ፈላስፋ ፕላቶ ባስተማረው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ከመማረካቸው የተነሳ አምላክን ከሥላሴ ትምህርት አንጻር ለመግለጽ በአዲስ መልክ ማዋቀር ጀመሩ። በቀጣዮቹ መቶ ዘመናት ይህ መሠረተ ትምህርት ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆነ መንገድ ኢየሱስን ከፍ በማድረግ ከይሖዋ ጋር እኩል ያደረገው ሲሆን የአምላክን መንፈስ ቅዱስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል ደግሞ አካል እንደሆነ አድርጎ ገልጾታል።

ቤተ ክርስቲያን አረማዊ የሆነውን የሥላሴ ትምህርት መቀበሏን በተመለከተ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “‘አንድ አምላክ በሦስት አካላት’ የሚለው ድንጋጌ ጠንካራ መሠረት ያገኘውና በክርስትና ሕይወትና የእምነት መግለጫ ውስጥ ሙሉ ተቀባይነት ያገኘው ከ4ኛው መቶ ዘመን በኋላ ነበር። ይሁን እንጂ የሥላሴ ቀኖና የሚለው ስያሜ የተሰጠው ለዚህ ድንጋጌ ነው። ሐዋርያዊ አባቶች እንዲህ ያለ አመለካከት ወይም ከዚህ እምነት ጋር የሩቅ ዝምድና እንኳን ያለው አስተሳሰብ እንደነበራቸው የሚያመለክት አንድም ማስረጃ አናገኝም።”

በተመሳሳይ ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና እንዲህ ይላል:- “የአራተኛው መቶ ዘመኑ የሥላሴ እምነት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ስለ አምላክ ማንነት የነበራቸውን እምነት በትክክል አያንጸባርቅም። እንዲያውም እነሱ ከነበራቸው እምነት ፈጽሞ የራቀ ነው።” ዚ ኦክስፎርድ ኮምፓኒየን ቱ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ ሥላሴ “ከጊዜ በኋላ ከተደነገጉት ሃይማኖታዊ ቀኖናዎች” መካከል አንዱ እንደሆነ ገልጿል። ሆኖም ቤተ ክርስቲያን የተቀበለችው አረማዊ ትምህርት የሥላሴ እምነት ብቻ አይደለም።

ነፍስን በአዲስ መልክ ማቅረብ

በዛሬው ጊዜ ሰዎች አካላቸው ከሞተ በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነፍስ አለቻቸው ተብሎ በሰፊው ይታመናል። ሆኖም ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ይህ ትምህርትም ከጊዜ በኋላ የተጨመረ መሆኑን ታውቅ ነበርን? ኢየሱስ ሙታን ‘አንዳች እንደማያውቁ’ እና በምሳሌያዊ አነጋገር አንቀላፍተው እንዳሉ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አጠናክሮታል። (መክብብ 9:​5፤ ዮሐንስ 11:​11-13) እንደገና ሕይወት ማግኘት የሚቻለው በትንሣኤ አማካኝነት ሲሆን ይህም በሞት ከማንቀላፋት ‘እንደገና መነሳት’ ማለት ነው። (ዮሐንስ 5:​28, 29) ያለመሞት ባሕርይ ካለ ሞት ስለማይኖር የማትሞት ነፍስ አለች ካልን ትንሣኤ አያስፈልግም።

እንዲሁም ኢየሱስ ሰዎችን ከሞት በማስነሳት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ የሚያስተምረውን ትምህርት በተግባር አሳይቷል። ለአራት ቀናት ሞቶ የነበረውን የአልዓዛርን ሁኔታ በምሳሌነት ተመልከት። ኢየሱስ ከሞት ሲያስነሳው አልዓዛር ከመቃብር የወጣው እስትንፋስ ያለው ሕያው ሰው ሆኖ ነው። አልዓዛር ከሞት ሲነሳ ከሰማያዊው ደስታ ሾልካ መጥታ ወደ ሰውነቱ የገባች ምንም ዓይነት የማትሞት ነፍስ አልነበረችም። ሁኔታው እንዲህ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት በማስነሳቱ ጥሩ ነገር አድርጎለታል ሊባል አይችልም!​—⁠ዮሐንስ 11:​39, 43, 44

ታዲያ ነፍስ አትሞትም የሚለው ንድፈ ሐሳብ ምንጩ ከየት ነው? ዘ ዌስትሚንስተር ዲክሽነሪ ኦቭ ክርስቺያን ቲኦሎጂ የተባለው መጽሐፍ ይህ ሐሳብ “መጽሐፍ ቅዱስ ከሚገልጸው ይልቅ ይበልጥ ከግሪክ ፍልስፍና የመነጨ” መሆኑን ይናገራል። ዘ ጁውሽ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ነፍስ ሥጋ ከጠፋ በኋላ በሕይወት ትኖራለች የሚለው እምነት በተራ እምነት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በፍልስፍና ወይም በሃይማኖታዊ ግምት ላይ የተመሠረተ ነው። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በየትኛውም ስፍራ አልተገለጸም።”

አብዛኛውን ጊዜ አንድ ውሸት ወደ ሌላ ውሸት ይመራል፤ ይህ ደግሞ የማትሞት ነፍስ አለች በሚለው ትምህርት ረገድ እውነት መሆኑ ታይቷል። ይህ ትምህርት በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ዘላለማዊ ስቃይ አለ ለሚለው አረማዊ አስተሳሰብ መንገድ ከፍቷል። b ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት” እንጂ ዘላለማዊ ስቃይ አለመሆኑን በግልጽ ይናገራል። (ሮሜ 6:​23) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ።” በተመሳሳይ ዱዌይ የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ባሕር . . . እንዲሁም ሞትና ሲኦል ሙታናቸውን ሰጡ” ይላል። አዎን፣ በቀላል ቋንቋ በሲኦል ያሉ ሰዎች ሞተዋል፤ ኢየሱስ እንደተናገረው ‘አንቀላፍተዋል።’​—⁠ራእይ 20:​13

ሲኦል ውስጥ ዘላለማዊ ቅጣት አለ የሚለው ትምህርት ሰዎችን ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ያደርጋቸዋል ብለህ ከልብ ታምናለህን? ይህ የማይመስል ነገር ነው። ፍትሕ ወዳድና አፍቃሪ በሆኑ ሰዎች አእምሮ ይህ ዘግናኝ የሆነ ሐሳብ ነው! በአንጻሩ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ ፍቅር መሆኑን’ እንዲሁም በእንስሳት ላይ እንኳ ሳይቀር የሚፈጸም ጭካኔ በእሱ ዘንድ በጣም የተጠላ መሆኑን ያስተምራል።​—⁠1 ዮሐንስ 4:​8፤ ምሳሌ 12:​10፤ ኤርምያስ 7:​31፤ ዮናስ 4:​11

በዛሬው ጊዜ “ሥዕሉን” ማበላሸት

ዛሬም የአምላክንና የክርስትና እምነትን ገጽታ የማበላሸቱ ጉዳይ ቀጥሏል። አንድ የሃይማኖት ፕሮፌሰር እሳቸው አባል በሆኑበት የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚካሄደውን ውዝግብ በቅርቡ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል:- “በቅዱስ ጽሑፉና በቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ እንዲሁም በባዕድና ሰው ሠራሽ በሆኑ አስተሳሰቦች መካከል የሚካሄድ ውዝግብ፤ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ ሥልጣን ባላት ታማኝነትና በሌላ ወገን ደግሞ የክርስትና እምነት ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር በመስማማቱና በዚያም መሠረት ለውጥ በማድረጉ መካከል የሚካሄድ ውዝግብ። አከራካሪው ጉዳይ:- የቤተ ክርስቲያንን አካሄድ መምራት ያለበት ማን ነው? . . . ቅዱስ ጽሑፉ ወይስ በዘመኑ ተስፋፍቶ የሚገኘው አስተሳሰብ? የሚል ነው።”

የሚያሳዝነው ነገር “በዘመኑ ተስፋፍቶ የሚገኘው አስተሳሰብ” አሁንም የበላይነቱን ይዞ መገኘቱ ነው። ለምሳሌ ያህል በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ተራማጅና አዳዲስ አስተሳሰቦችን የሚያስተናግዱ ሆነው ለመታየት ስለሚፈልጉ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አቋማቸውን መለወጣቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው። በመጀመሪያው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው በተለይ በሥነ ምግባር ጉዳዮች ላይ ቤተ ክርስቲያን በጣም ልል ሆናለች። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ዝሙት፣ ምንዝርና ግብረ ሰዶም በአምላክ ዓይን ከባድ ኃጢአት መሆናቸውንና እንዲህ ዓይነት ኃጢአት የሚፈጽሙ ሰዎች ‘የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ’ በግልጽ ይናገራል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:​9, 10፤ ማቴዎስ 5:​27-32፤ ሮሜ 1:​26, 27

ሐዋርያው ጳውሎስ ከላይ የተጠቀሱትን ቃላት በጻፈበት ጊዜ በዙሪያው የነበረው የግሪኮ-ሮማ ዓለም በልዩ ልዩ ዓይነት ርኩሰቶች ተጥለቅልቆ ነበር። ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ማሰብ ይችል ነበር:- ‘አምላክ ከባድ የጾታ ብልግና በመፈጸማቸው ምክንያት ሰዶምና ገሞራን አመድ እንዳደረጋቸው የታወቀ ነው፤ ይህ ግን የተፈጸመው ከዛሬ 2, 000 ዓመት በፊት ነው! በዚህ በሥልጣኔ ባደገ ዘመን ውስጥ ተግባራዊ እንደማይሆን ምንም ጥርጥር የለውም።’ ይሁን እንጂ ጳውሎስ ሰበብ ለማቅረብ አልሞከረም፤ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመበረዝ እምቢተኛ ሆኗል።​—⁠ገላትያ 5:​19-23

የመጀመሪያውን “ሥዕል” ፈልግ

ኢየሱስ በወቅቱ ከነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ጋር ሲነጋገር ‘የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት ስለሚያስተምሩ’ አምልኮታቸው ከንቱ መሆኑን ጠቅሷል። (ማቴዎስ 15:​9) እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በክርስቶስ ትምህርት ላይ እንዳደረጉትና አሁንም እያደረጉ እንዳሉት ሁሉ በሙሴ በኩል በተሰጣቸው የይሖዋ ሕግ ላይ ተመሳሳይ ነገር ፈጽመዋል። በመለኮታዊ እውነት ላይ የሰዎችን ወግ “ቀለም” ረጭተዋል። ሆኖም ኢየሱስ ቅን ልቦና ላላቸው ሰዎች ጥቅም ሲል ማንኛውንም ዓይነት ውሸት ጠራርጎ አስወግዷል። (ማርቆስ 7:​7-13) ተወዳጅነት አገኘም አላገኘ ኢየሱስ እውነትን ተናግሯል። ምንጊዜም የአምላክን ቃል ባለሥልጣን አድርጎ ይጠቅስ ነበር።​—⁠ዮሐንስ 17:​17

ኢየሱስ ከአብዛኞቹ ክርስቲያን ነን ባዮች ምንኛ የተለየ ነበር! በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ተንብዮ ነበር:- “ለወሬ በመጎምጀት እነርሱ ራሳቸው የሚወድዱትን ነገር የሚነግሩአቸውን አስተማሪዎች ይሰበስባሉ። እውነትን መስማት ትተው ተረትን መስማት ይወድዳሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 4:​3, 4 የ1980 ትርጉም ) እነዚህ ‘ተረቶች’ (ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹን ተመልክተናቸዋል) በመንፈሳዊ ሁኔታ አፍራሽ ሲሆኑ በአንጻሩ ደግሞ የአምላክ ቃል እውነት ይገነባል እንዲሁም ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራል። የይሖዋ ምሥክሮች እንድትመረምረው የሚያበረታቱህ ይህን እውነት ነው።​—⁠ዮሐንስ 4:​24፤ 8:​32፤ 17:​3

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ኢየሱስ ስለ ስንዴና እንክርዳድ እንዲሁም ስለ ሰፊውና ጠባቡ መንገድ በተናገረው ምሳሌ ላይ እንደገለጸው (ማቴዎስ 7:​13, 14) በዘመናት ሂደት እውነተኛውን የክርስትና እምነት በተግባር ማዋላቸውን የሚቀጥሉት አናሳ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ብቻ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ ራሳቸውንና ትምህርቶቻቸውን ትክክለኛው የክርስትና እምነት ገጽታ አድርገው በሚያቀርቡት አረም መሰል ብዙሃን ይዋጣሉ። ይህ ርዕስ የሚያተኩረው በዚህ ገጽታ ላይ ነው።

b “ሲኦል” የሚለው ቃል ሺኦል ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል እና ሔድስ ከሚለው የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ሲሆን ሁለቱም “መቃብር” የሚል ትርጉም አላቸው። በመሆኑም የኪንግ ጀምስ ቨርሽን ተርጓሚዎች ሺኦልን 31 ጊዜ “ሲኦል” ብለው ቢተረጉሙም 31 ጊዜ ደግሞ “መቃብር” እንዲሁም 3 ጊዜ “ጉድጓድ” ብለው መተርጎማቸው እነዚህ ቃላት በመሠረቱ ተመሳሳይ ነገር የሚያመለክቱ መሆናቸውን ያሳያል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ክርስቲያን የሚለው ስም አመጣጥ

ከኢየሱስ ሞት በኋላ ቢያንስ ለአሥር ዓመት ያህል ተከታዮቹ የነበሩበት ቡድን “መንገድ” ተብሎ ይጠራ ነበር። (ሥራ 9:2፤ 19:9, 23፤ 22:4) ለምን? ምክንያቱም አኗኗራቸው “መንገድና እውነት ሕይወትም” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት ዙሪያ የተገነባ ስለነበር ነው። (ዮሐንስ 14:6) ከዚያም ከ44 እዘአ በኋላ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሶርያ አንጾኪያ “በመለኮታዊ አመራር ክርስቲያን ተባሉ።” (ሥራ 11:26 NW) ይህ ስም በሕዝብ ባለሥልጣናት ዘንድ እንኳ ሳይቀር ወዲያውኑ ተቀባይነት አገኘ። (ሥራ 26:28) አዲሱ ስም የክርስቶስን ፈለግ መከተሉን የቀጠለውን ክርስቲያናዊ አኗኗር አልቀየረውም።—1 ጴጥሮስ 2:21

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች ለሕዝብ በሚሰጡት አገልግሎት አማካኝነት ሰዎችን የአምላክ ቃል ወደሆነው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ይመራሉ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከበስተግራ ሦስተኛው:- United Nation/Photo by Saw Lwin