አፍቃሪ የሆነውን አምላክ ማወቅ
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
አፍቃሪ የሆነውን አምላክ ማወቅ
አንቶኒዮ የተባለው ብራዚላዊ ወጣት ገና በ16 ዓመቱ የሕይወት ትርጉም እንቆቅልሽ ሆኖበት ነበር። ይሰማው ከነበረው የከንቱነት ስሜት የተነሳ የአደገኛ ዕፆችና የመጠጥ ሱሰኛ ሆነ። ከዚህም በኋላ በተደጋጋሚ ራሱን ለመግደል ያስብ ነበር። እናቱ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት የነገረችውን ነገር ያስታወሰው በዚህ ወቅት ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) ይሁን እንጂ ይህ አፍቃሪ አምላክ የት ነበር?
አንቶኒዮ ከሱሱ ለመላቀቅ ስለፈለገ እርዳታ አገኛለሁ በማለት ወደ አንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ሄደ። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ቢያደርግም ገና ያልተመለሱለት ብዙ ጥያቄዎች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ “እውነትን ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” በማለት የተናገራቸው ቃላት ትርጉም ግራ ያጋባው ነበር። (ዮሐንስ 8:32) ኢየሱስ ታገኛላችሁ ያለው አርነት ምን ዓይነት ነበር? ለጥያቄዎቹ ምንም ዓይነት የሚያረካ መልስ ስላላገኘ ቀስ በቀስ ከቤተ ክርስቲያኑ በመራቅ ወደ ቀድሞው ልማዱ ተመለሰ። እንዲያውም ሱሱ እየባሰበት ሄደ።
በዚህ ጊዜ ማሪያ የተባለችው ሚስቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ማጥናቷን ባይቃወምም እንኳ “የአሜሪካን ኢምፔርያሊዝም ለማስፋፋት የሚያገለግል የአሜሪካውያን ሃይማኖት ነው” በማለት ምሥክሮቹን ይንቃቸው ነበር።
ማሪያ ተስፋ ባለመቁረጥ ሊስቡት ይችላሉ ብላ ያሰበቻቸውን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት እትሞች ቤት ውስጥ ሊታይ በሚችል ቦታ ታስቀምጥለት ነበር። አንቶኒዮም ማንበብ ስለሚወድ አልፎ አልፎ ሚስቱ በማትኖርበት ጊዜ መጽሔቶቹን ያገላብጣቸው ነበር። በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቹ መልስ አገኘ። አንቶኒዮ “ከዚህም በተጨማሪ ሚስቴና ሌሎቹ ምሥክሮች የሚያሳዩኝን ፍቅርና ደግነት ማስተዋል ጀመርኩ” በማለት ያስታውሳል።
በ1992 አጋማሽ ላይ አንቶኒዮ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማ። ይሁን እንጂ አደገኛ ዕፅ መውሰዱንና ከልክ በላይ መጠጣቱን ቀጥሎ ነበር። አንድ ቀን ምሽት እሱና ጓደኛው የዱርዬዎች መናኸሪያ ከሆነ አንድ መንደር ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ፖሊሶች አስቆሟቸው። አንቶኒዮ ኮኬይን ይዞ ስላገኙት ይደበድቡት ጀመር። ከዚያም አንደኛው ፖሊስ መሬት ላይ ጣለውና የመሣሪያውን አፈሙዝ ደገነበት። ወዲያው ሌላኛው ፖሊስ “ጨርሰው!” በማለት ጮኸ።
አንቶኒዮ ጭቃው ላይ እንደተኛ ያሳለፈውን ሕይወት መለስ ብሎ ለማስታወስ ሞከረ። በዚህ ጊዜ ግን ወደ አእምሮው የመጡለት ጥሩ ነገሮች ቢኖሩ ቤተሰቡና ይሖዋ ብቻ ናቸው። ስለዚህ ይሖዋ እንዲረዳው አጭር ጸሎት አቀረበ። ወዲያው ፖሊሱ ያለ ምንም በቂ ምክንያት ጥሎት ሄደ። አንቶኒዮ ይሖዋ እንደጠበቀው ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ።
ከዚያም አንቶኒዮ በአዲስ መንፈስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ጀመረ። ቀስ በቀስ ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ ለውጥ አደረገ። (ኤፌሶን 4:22-24) ራስን የመግዛት ባሕርይ በማዳበር ከአደገኛ ዕፅ ሱሰኝነት ለመላቀቅ ጥረት ማድረግ ጀመረ። ያም ሆኖ የሕክምና እርዳታ ማግኘት አስፈልጎት ነበር። በተኃድሶ ክሊኒኩ ባሳለፋቸው የሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ጨምሮ የተወሰኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማንበብ ችሎ ነበር። አንቶኒዮ ከእነዚህ መጽሐፎች የተማረውን ነገር ለሌሎች ሕመምተኞችም አካፍሏል።
አንቶኒዮ ከክሊኒኩ ከወጣ በኋላ ከምሥክሮቹ ጋር ጥናቱን ቀጠለ። በዛሬው ጊዜ አንቶኒዮ፣ ማሪያ፣ ሁለቱ ሴቶች ልጆቻቸውና የአንቶኒዮ እናት አንድነት ያለው ደስተኛ ቤተሰብ በመሆን ይሖዋን ያገለግላሉ። አንቶኒዮ “‘እግዚአብሔር ፍቅር ነው’ የሚሉትን ቃላት ትክክለኛ ትርጉም አሁን ተረድቻለሁ” በማለት ይናገራል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሪዮ ዲ ጄኔሮ መስበክ