“ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ”
“ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ”
“መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ።”—ማቴዎስ 23:8
1.ልንመረምረው የሚገባን ጉዳይ የትኛው ነው?
“ይበልጥ መከበር ያለበት ማን ነው፣ ሚስዮናዊ ወይስ ቤቴላዊ?” ስትል በሩቅ ምሥራቅ በሚገኝ አንድ አገር የምትኖር አንዲት ክርስቲያን ሴት ከአውስትራሊያ የሄደችውን ሚስዮናዊ በቅንነት ጠየቀቻት። ከሌላ አገር መጥቶ ከሚያገለግል ሚስዮናዊና በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ከሚሠራ የአገሩ ተወላጅ የሆነ አገልጋይ መካከል ይበልጥ መከበር ያለበት ማንኛው እንደሆነ ለማወቅ ፈልጋ ነበር። ለመደብ ልዩነት ትልቅ ቦታ የሚሰጥን ባሕል የሚያንጸባርቀው ይህ ቅንነት የተሞላበት ጥያቄ ሚስዮናዊቷን በጣም አስገረማት። ይሁን እንጂ ብዙዎች ማን ይበልጣል የሚለውን ጥያቄ የሚያነሱት ሰዎች በሥልጣንና በኃይል ረገድ ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለማወቅ በመጓጓት ነው።
2.የአምልኮ አጋሮቻችንን እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?
2 እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ አዲስ አይደለም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንኳ ከሁሉ የሚበልጠው ማን ነው በማለት በየጊዜው ይከራከሩ ነበር። (ማቴዎስ 20:20-24፤ ማርቆስ 9:33-37፤ ሉቃስ 22:24-27) እነርሱም ቢሆኑ ለመደብ ልዩነት ትልቅ ቦታ ይሰጥ ከነበረው ባሕል ማለትም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው የአይሁድ እምነት የመጡ ናቸው። ኢየሱስ ይህን ኅብረተሰብ በአእምሮው በመያዝ ደቀ መዛሙርቱን “መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ” ሲል መክሯቸዋል። (ማቴዎስ 23:8) “ረቢ” (“መምህር” ማለት ነው) እንደሚለው ያለ ሃይማኖታዊ መጠሪያ “መጠሪያውን ያገኙት ሰዎች እንዲኩራሩና የበላይነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ሲሆን ይህን መጠሪያ ያላገኙት ደግሞ የቅናትና የበታችነት ስሜት ያድርባቸዋል። መላ መንፈሱና አዝማሚያው ‘በክርስቶስ ላይ ከተንጸባረቀው የተለየ ሁኔታ’ ጋር የሚጋጭ ነው” ሲሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት አልበርት ባርንዝ ገልጸዋል። አዎን፣ ክርስቲያኖች “ሽማግሌ” የሚለውን ቃል እንደ ማዕረግ ስም አድርገው በመጠቀም በመካከላቸው የሚገኙትን የበላይ ተመልካቾች “ሽማግሌ እገሌ” ብለው ከመጥራት ይቆጠባሉ። (ኢዮብ 32:21, 22) በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ታማኝ አምላኪዎቹን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ታማኝ ተከታዮቹን እንደሚያከብሩ ሁሉ ሽማግሌዎችም ከኢየሱስ ምክር መንፈስ ጋር በሚስማማ መንገድ በመመላለስ ሌሎች የጉባኤ አባላትን ያከብራሉ።
የይሖዋና የኢየሱስ ምሳሌነት
3.ይሖዋ መንፈሳዊ ፍጥረታቱን ያከበረው እንዴት ነው?
3 ይሖዋ “ልዑል” አምላክ ቢሆንም ከመጀመሪያ አንስቶ ፍጥረታቱ በሥራው ላይ ድርሻ እንዲኖራቸው በማድረግ አክብሯቸዋል። (መዝሙር 83:18) የመጀመሪያውን ሰው በፈጠረ ጊዜ አንድያ ልጁ “ዋና ሠራተኛ” ሆኖ በፕሮጄክቱ ውስጥ እንዲካፈል አድርጓል። (ምሳሌ 8:27-30፤ ዘፍጥረት 1:26) ሌላው ቀርቶ ይሖዋ ክፉውን ንጉሥ አክዓብን ለማጥፋት ወስኖ በነበረ ጊዜ ሰማያዊ መላእክቱ ይህን ንጉሥ ማጥፋት በሚቻልበት መንገድ ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ ጋብዟቸው ነበር።—1 ነገሥት 22:19-23
4, 5. ይሖዋ ሰብዓዊ ፍጥረታቱን ያከበረው እንዴት ነው?
4 ይሖዋ የሁሉ የበላይ የሆነ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ነው። (ዘዳግም 3:24) ሰዎችን ማማከር አያስፈልገውም። ሆኖም ያሉበትን ሁኔታ ለመመልከት ራሱን ዝቅ ያደርጋል ሊባል ይቻላል። አንድ መዝሙራዊ እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ማን ነው? በላይ የሚኖር፤ በሰማይና በምድር የተዋረዱትን የሚያይ፤ . . . ችግረኛን ከመሬት የሚያነሣ።”—መዝሙር 113:5-8
5 ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ በፊት የአብርሃምን ጥያቄዎች በመስማት የፍትሕ ስሜቱን አርክቶለታል። (ዘፍጥረት 18:23-33) ምንም እንኳ ይሖዋ የአብርሃምን ጥያቄዎች ውጤት ቀድሞውኑ ያውቅ የነበረ ቢሆንም አብርሃምን በትዕግሥት ከመስማቱም በላይ ሐሳቡን ተቀብሎታል።
6.ዕንባቆም ጥያቄ ባቀረበ ጊዜ ይሖዋ አክብሮት ማሳየቱ ምን ውጤት አስገኝቷል?
6 በተጨማሪም ይሖዋ “አቤቱ፣ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው?” በማለት ዕንባቆም ያቀረበውን ጥያቄም ሰምቶታል። ይሖዋ ጥያቄውን በሥልጣኑ ላይ እንደተነሣ ግድድር አድርጎ ተመልክቶት ነበርን? በፍጹም፣ ዕንባቆም ያቀረበውን ጥያቄ አግባብነት እንዳለው አድርጎ በመመልከት ፍርድ ለማስፈጸም ከለዳውያንን ለማስነሳት ያለውን ዓላማ ገለጸለት። ‘ይህ አስቀድሞ የተነገረ ፍርድ በእርግጥ እንደሚመጣ’ ለነቢዩ አረጋገጠለት። (ዕንባቆም 1:1, 2, 5, 6, 13, 14፤ 2:2, 3) ይሖዋ፣ ዕንባቆም ያሳሰበውን ነገር በቁም ነገር በመመልከትና መልስ በመስጠት ነቢዩን አክብሮታል። በመሆኑም በጭንቀት ተውጦ የነበረው ነቢይ አዳኙ በሆነው አምላክ ሙሉ በሙሉ በመተማመን በሐሴትና በደስታ ተሞላ። ይህ በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ላይ ያለንን ትምክህት በሚያጠነክረው በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የዕንባቆም መጽሐፍ ውስጥ ተንጸባርቋል።—ዕንባቆም 3:18, 19
7.ጴጥሮስ በ33 እዘአ በተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ የነበረው ሚና ትልቅ ትርጉም ያለው ለምንድን ነው?
7 ለሌሎች አክብሮት በማሳየት ረገድ ሌላው ግሩም ምሳሌ የሚሆነን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ . . . በአባቴ ፊት እክደዋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:32, 33) ይሁን እንጂ ለጠላቶቹ በተሰጠበት ምሽት ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ ጥለውት ከመሄዳቸውም በተጨማሪ ሐዋርያው ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ ክዶታል። (ማቴዎስ 26:34, 35, 69-75) ኢየሱስ ከውጫዊው ገጽታ አልፎ በመሄድ የጴጥሮስን ውስጣዊ ስሜት ማለትም ከልቡ ንስሐ መግባቱን ተመልክቷል። (ሉቃስ 22:61, 62) ይህ በሆነ በ51 ቀናት ውስጥ ክርስቶስ በጰንጠቆስጤ ዕለት 120 ደቀ መዛሙርቱን እንዲወክልና ‘ከመንግሥቱ መክፈቻዎች’ የመጀመሪያውን እንዲጠቀም በማድረግ ንስሐ የገባውን ሐዋርያ አክብሮታል። (ማቴዎስ 16:19፤ ሥራ 2:14-40) ጴጥሮስ ‘ተመልሶ ወንድሞቹን ማጽናት’ የሚችልበት ዕድል ተሰጥቶታል።—ሉቃስ 22:31-33
ለቤተሰብ አባላት አክብሮት ማሳየት
8, 9. አንድ ባል ለሚስቱ አክብሮት በማሳየት ረገድ ይሖዋንና ኢየሱስን መምሰል የሚችለው እንዴት ነው?
8 ባሎችና ወላጆች አምላክ የሰጣቸውን ሥልጣን በሚጠቀሙበት ጊዜ ይሖዋንና ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል ይኖርባቸዋል። ጴጥሮስ “እናንተ ባሎች ሆይ፣ . . . ለተሰባሪ ዕቃ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ሚስቶቻችሁን በክብር በመያዝ ከእነርሱ ጋር በእውቀት አብራችሁ ኑሩ” ሲል አጥብቆ መክሯል። (1 ጴጥሮስ 3:7 NW ) በቀላሉ ሊሰበር የሚችል የሸክላ ዕቃ ይዛችኋል እንበል። ከእንጨት ዕቃ ይበልጥ በቀላሉ ሊሰበር የሚችል በመሆኑ የበለጠ ጥንቃቄ አታደርጉለትምን? አንድ ባልም የይሖዋን ምሳሌ በመኮረጅ የቤተሰብ ጉዳዮችን በሚወስንበት ጊዜ የሚስቱን አስተያየት በመስማት እንዲህ ያለ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይችላል። ይሖዋ ጊዜ ወስዶ ከአብርሃም ጋር እንደተነጋገረ አስታውስ። አንድ ባል ፍጽምና የሚጎድለው በመሆኑ የአንድን ጉዳይ ሙሉ ገጽታ ሳይመለከት ሊቀር ይችላል። በመሆኑም ሚስቱ የምትሰጠውን አስተያየት ከልብ በማጤን አክብሮት ቢያሳያት ጥበብ አይሆንም?
9 ለወንድ ሥልጣን ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ባሕሎች ሥር በሰደዱባቸው አገሮች አንድ ባል ሚስቱ ውስጣዊ ስሜቷን ለመግለጽ አንድ ትልቅ ጋሬጣ ማለፍ ሊጠይቅባት እንደሚችል ማስታወስ ይኖርበታል። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የወደፊት ሙሽራው ክፍል አባላት የሆኑትን ደቀ መዛሙርቱን የያዘበትን መንገድ ኮርጅ። የሚፈልጉትን ነገር ገና ሳይናገሩ እንኳ ሥጋዊና መንፈሳዊ አቅማቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ተንከባክቧቸዋል። (ማርቆስ 6:31፤ ዮሐንስ 16:12, 13፤ ኤፌሶን 5:28-30) በተጨማሪም ሚስትህ ለአንተና ለቤተሰብህ ምን እያደረገች እንዳለች ቆም ብለህ በማጤን አድናቆትህን በቃልና በተግባር ግለጽ። ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ የሚገባቸውን ሰዎች አድንቀዋል፣ አመስግነዋል እንዲሁም ባርከዋል። (1 ነገሥት 3:10–14፤ ኢዮብ 42:12-15፤ ማርቆስ 12:41-44፤ ዮሐንስ 12:3-8) በሩቅ ምሥራቅ የምትኖር አንዲት ክርስቲያን ሴት ባሏ የይሖዋ ምሥክር ከሆነ በኋላ እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “ቀደም ሲል ባለቤቴ ሁሉን ነገር ያሸክመኝና ሦስትና አራት እርምጃ ቀድሞኝ ከፊት ከፊቴ ይሄድ ነበር። አሁን ግን ከረጢቶቹን ይይዝልኛል፣ በቤት ውስጥ የማከናውናቸውንም ነገሮች ያደንቃል!” ልባዊ አድናቆትን በቃል መግለጽ ባለቤትህ ዋጋማ እንደሆነች እንዲሰማት በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።—ምሳሌ 31:28
10, 11. ወላጆች ይሖዋ ከዓመፀኛው የእስራኤል ሕዝብ ጋር በነበረው ግንኙነት ከተወው ግሩም ምሳሌ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?
10 ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት በተለይ ደግሞ ተግሳጽ መስጠት በሚያስፈልግበት ጊዜ የአምላክን ምሳሌ መኮረጅ ይኖርባቸዋል። ይሖዋ ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱ ‘እስራኤልንና ይሁዳን ቢያስጠነቅቅም’ “አንገታቸውን አደነደኑ።” (2 ነገሥት 17:13-15) እንዲያውም እስራኤላውያን “በቃላቸው ሸነገሉት፤ [የ1980 ትርጉም ] በአንደበታቸውም ዋሹበት።” ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ድርጊት እንደሚፈጽሙ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። እስራኤላውያን ‘አምላክን ከመፈተናቸውም’ በተጨማሪ ስሜቱን በመጉዳት አሳዝነውታል። ሆኖም ይሖዋ “መሐሪ ነው፣ ኃጢአታቸውንም ይቅር አላቸው፣ አላጠፋቸውምም።”—መዝሙር 78:36-41
11 እንዲያውም ይሖዋ እስራኤላውያንን እስከ መማፀን ደርሶ ነበር:- “ኑና እንዋቀስ [“እርቅ እንፍጠር፣” NW ] . . . ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች።” (ኢሳይያስ 1:18) ይሖዋ ምንም የሠራው ስህተት የለም፤ ያም ሆኖ ግን ዓመፀኛው ብሔር ወደ እሱ መጥቶ እርቅ እንዲፈጥር ግብዣ አቅርቧል። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ሊኮርጁት የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም አመለካከት ነው! አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በጉዳዩ ላይ እነሱ የሚሰጡትን ሐሳብ በመስማት አክብሮት አሳዩአቸው፣ እንዲሁም ለውጥ ማድረግ ያለባቸው ለምን እንደሆነ በግልጽ አስረዷቸው።
12. (ሀ) ልጆቻችንን ከይሖዋ ይበልጥ ከማክበር መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ልጆቻችንን በምንገሥጽበት ጊዜ ክብራቸውን መጠበቅ እንድንችል ምን ማድረግ ይኖርብናል?
12 እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ልጆች ጠንከር ያለ ምክር ሊሰጣቸው ይገባል። ወላጆች ‘ከይሖዋ ይልቅ ልጆቹን ያከበረውን’ ዔሊን መምሰል እንደማይፈልጉ የታወቀ ነው። (1 ሳሙኤል 2:29) ያም ሆኖ ግን ልጆች ከሚሰጣቸው እርማት በስተጀርባ ያለውን ፍቅራዊ ዓላማ መረዳት አለባቸው። ወላጆቻቸው እንደሚወዷቸው መገንዘብ መቻል አለባቸው። ጳውሎስ አባቶችን “ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው” ሲል አጥብቆ መክሯል። (ኤፌሶን 6:4) እዚህ ላይ ግልጽ ለማድረግ የተፈለገው ነገር የአባትነት ሥልጣን የተሰጠ ቢሆንም እንኳ አባትየው ከልክ በላይ ኃይለኛ ሆኖ ልጆቹን ከማስቆጣት በመታቀብ የልጆቹን ክብር መጠበቅ እንዳለበት ነው። አዎን፣ ወላጆች የልጆችን ክብር ግምት ውስጥ ለማስገባት ጊዜና ጥረት እንደሚጠይቅባቸው የታወቀ ነው። ሆኖም ይህን በማድረግ የሚገኘው ፍሬ መሥዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባው ነው።
13. መጽሐፍ ቅዱስ በቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ አረጋውያንን በተመለከተ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
13 ለቤተሰብ አባላት አክብሮት ማሳየት ሚስትንና ልጆችን ከፍ አድርጎ በመመልከት ብቻ የሚወሰን አይደለም። አንድ የጃፓናውያን ምሳሌ “ስታረጅ ልጆችህን ታዘዝ” ይላል። ይህ ምሳሌ አረጋውያን ወላጆች የወላጅነት ሥልጣናቸው ከሚፈቅድላቸው አልፈው መሄድ እንደሌለባቸውና የጎለመሱት ልጆቻቸው የሚሰጡትን ሐሳብ ልብ ማለት እንዳለባቸው የሚጠቁም ነው። ምንም እንኳ ወላጆች ለልጆቻቸው ጆሯቸውን በመስጠት አክብሮት ማሳየታቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው ቢሆንም ልጆች በዕድሜ ለገፉት የቤተሰባቸው አባሎች አክብሮት የጎደለው አመለካከት ሊያሳዩ አይገባም። ምሳሌ 23:22 “እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት” ይላል። ንጉሥ ሰሎሞን ከዚህ ምሳሌ ጋር በሚስማማ መንገድ የኖረ ሲሆን እናቱ አንድ ልመና ለማቅረብ ባነጋገረችው ጊዜ አክብሮት አሳይቷታል። ሰሎሞን ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ ካስቀመጣት በኋላ አረጋዊት እናቱ ቤርሳቤህ ልትነግረው የፈለገችውን ጉዳይ አዳምጧል።—1 ነገሥት 2:19, 20
14. አረጋውያን የሆኑ የጉባኤ አባሎችን ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?
14 በትልቁ መንፈሳዊ ቤተሰባችን ውስጥ አረጋውያን ለሆኑ የጉባኤ አባላት አክብሮት በማሳየት ረገድ ‘ቀዳሚ’ መሆን የምንችልበት ጥሩ አጋጣሚ አለን። (ሮሜ 12:10 የ1980 ትርጉም ) እነዚህ አረጋውያን ቀደም ባሉት ጊዜያት ያከናውኑት የነበረውን ያህል መሥራት አይችሉ ይሆናል። ይህ ደግሞ ያበሳጫቸው ይሆናል። (መክብብ 12:1-7) አቅመ ደካማ ለሆኑ ሰዎች እንክብካቤ በሚደረግበት ቦታ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ አንዲት አረጋዊት ቅቡዕ ምሥክር በአንድ ወቅት “ሞቼ ወደ ሥራ የምመለስበት ቀን ናፍቆኛል” ሲሉ የተሰማቸውን ብስጭት ገልጸዋል። ለእነዚህ አረጋውያን የሚገባቸውን ዕውቅና መስጠታችንና አክብሮት ማሳየታችን ሊረዳቸው ይችላል። እስራኤላውያን “በሽበታሙ ፊት ተነሣ፣ ሽማግሌውንም አክብር” የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 19:32) በዕድሜ የገፉ ሰዎች እንደሚፈለጉና ከፍ ያለ ግምት እንደሚሰጣቸው እንዲሰማቸው በማድረግ አሳቢነት አሳይ። ‘መነሣት’ የሚለው ቃል ቁጭ ብሎ ለዓመታት ያከናወኑትን ነገር ሲተርኩ መስማትን የሚጨምር ሊሆን ይችላል። ይህ አረጋውያንን የሚያስከብራቸው ከመሆኑም በላይ የራሳችንንም መንፈሳዊ ሕይወት ያበለጽግልናል።
‘አክብሮት በማሳየት ረገድ ቀዳሚ ሁኑ’
15. ሽማግሌዎች ለጉባኤ አባላት አክብሮት ለማሳየት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
15 ሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ ሲተዉላቸው የጉባኤ አባላት እድገት እያደረጉ ይሄዳሉ። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) አሳቢ የሆኑ ሽማግሌዎች ሥራ የሚበዛባቸው ቢሆንም እንኳ ቅድሚያውን ወስደው ችግር ያለባቸውንም ሆነ የሌለባቸውን ልጆች፣ የቤተሰብ ራሶች፣ ነጠላ እናቶች፣ የቤት እመቤቶችና አረጋውያን ቀርበው ያነጋግራሉ። ሽማግሌዎቹ የጉባኤው አባላት የሚናገሩትን ያዳምጣሉ እንዲሁም እያደረጉት ላሉት ነገር ያመሰግኗቸዋል። አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ላደረጉት ነገር የአድናቆት ቃላት የሚሰነዝር ሁኔታዎችን በትኩረት የሚከታተል ሽማግሌ ምድራዊ ፍጥረታቱን የሚያደንቀውን ይሖዋን እየመሰለ ነው።
16. ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ካሉት ከሌሎች አባላት የተለየ ክብር ሊሰጣቸው እንደሚገባ አድርገን መመልከት የማይኖርብን ለምንድን ነው?
16 ሽማግሌዎች ይሖዋን በመምሰል የሚከተለውን የጳውሎስ ምክር ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ:- “ወንድማማቾች እንደመሆናችሁ መጠን እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ለመከባበርም ተሽቀዳደሙ።” (ሮሜ 12:10 የ1980 ትርጉም ) ለመደብ ልዩነት ትልቅ ቦታ በሚሰጥባቸው አገሮች ለሚኖሩ ሽማግሌዎች ይህ ከባድ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል በሩቅ ምሥራቅ በሚገኝ አንድ አገር ውስጥ “ወንድም” የሚለውን ቃል የሚወክሉ ሁለት ቃላት አሉ። አንደኛው ከፍ ተደርገው የሚታዩ ሰዎችን ለማመልከት የሚሠራበት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ተራ የሆኑ ሰዎችን ለማመልከት የሚሠራበት ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የጉባኤ አባላት የጉባኤ ሽማግሌዎችንና በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ሲጠሩ አክብሮታዊውን መጠሪያ ይጠቀሙ የነበረ ሲሆን ሌሎችን ሲጠሩ ደግሞ ተራውን መጠሪያ ይጠቀሙ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለተከታዮቹ “እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ” ሲል በተናገረው መሠረት በሁሉም ጊዜያት ተራውን መጠሪያ እንዲጠቀሙ ማበረታቻ ተሰጣቸው። (ማቴዎስ 23:8) በሌሎች አገሮች እንዲህ ያለ ግልጽ ልዩነት የማይታይ ሊሆን ቢችልም እንኳ ሁላችንም የመደብ ልዩነት የመፍጠር ሰብዓዊ ዝንባሌ መኖሩን መገንዘብ ይኖርብናል።—ያዕቆብ 2:4
17. (ሀ) ሽማግሌዎች የሚቀረቡ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ከጉባኤ አባላት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ይሖዋን ሊመስሉ የሚችሉት በምን መንገዶች ነው?
17 እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ አንዳንድ ሽማግሌዎችን “እጥፍ ክብር” እንደሚገባቸው አድርገን እንድንይዛቸው ያበረታታን ቢሆንም እነርሱም ወንድሞቻችን ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 5:17) ‘የመናገር ነፃነት ተሰምቶን ወደ ጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ የጸጋ ዙፋን’ መቅረብ ከቻልን ይሖዋን የሚኮርጁትን ሽማግሌዎች መቅረብ መቻል አይኖርብንምን? (ዕብራውያን 4:16፤ ኤፌሶን 5:1) የበላይ ተመልካቾች ሌሎች ምክር ለማግኘት ወይም ሐሳብ ለመስጠት ምን ያህል አዘውትረው ወደ እነሱ እንደሚመጡ ቆም ብለው በማሰብ ምን ያህል የሚቀረቡ ሰዎች እንደሆኑ ራሳቸውን መገምገም ይችላሉ። ይሖዋ ሌሎች በፕሮጄክቱ ውስጥ እንዲካፈሉ ከሚያደርግበት መንገድ ትምህርት ለመቅሰም ጥረት አድርግ። ይሖዋ ኃላፊነት በመስጠት ሌሎችን ያከብራል። አንድ ምሥክር የሰጠው ሐሳብ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ቢመስል እንኳ ሽማግሌዎቹ ምሥክሩ ያሳየውን አሳቢነት ማድነቅ ይኖርባቸዋል። ይሖዋ የአብርሃምን የምርመራ ጥያቄዎችና ዕንባቆም ተጨንቆ ያሰማውን ጩኸት በምን መንገድ እንደያዘ አስታውሱ።
18. ሽማግሌዎች እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በማቅናት ረገድ ይሖዋን ሊመስሉ የሚችሉት እንዴት ነው?
18 አንዳንድ ክርስቲያኖች ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። (ገላትያ 6:1) ያም ሆኖ ግን በይሖዋ ፊት ዋጋማ በመሆናቸው በአክብሮት ሊያዙ ይገባቸዋል። “አንድ ምክር የሚሰጥ ሰው በአክብሮት ሲይዘኝ ወደ እሱ ለመቅረብ ነፃነት ይሰማኛል” ሲል አንድ ምሥክር ተናግሯል። አብዛኞቹ ሰዎች በአክብሮት በሚያዙበት ጊዜ ለሚሰጣቸው ምክር ጥሩ ምላሽ ያሳያሉ። ተጨማሪ ጊዜ ሊወስድ ቢችልም ስህተት የፈጸሙ ሰዎች የሚናገሩትን በትዕግሥት ማዳመጡ የሚያስፈልጋቸውን ማንኛውንም ምክር እንዲቀበሉ ሁኔታውን ሊያቀልላቸው ይችላል። ይሖዋ ለእስራኤላውያን በመራራት በተደጋጋሚ ጊዜያት እነርሱን ለማሳመን እንዴት ጥረት እንዳደረገ አስታውስ። (2 ዜና መዋዕል 36:15፤ ቲቶ 3:1, 2) ችግራቸውን በመረዳትና በርኅራኄ ስሜት የሚሰጥ ምክር እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ልብ ይነካል።—ምሳሌ 17:17፤ ፊልጵስዩስ 2:2, 3፤ 1 ጴጥሮስ 3:8
19. የክርስቲያኖች ዓይነት እምነት የሌላቸውን ሰዎች መመልከት ያለብን እንዴት ነው?
19 ለሌሎች የምናሳየው አክብሮት ወደፊት መንፈሳዊ ወንድሞቻችን ሊሆኑ የሚችሉትንም ሰዎች የሚያቅፍ ነው። እነዚህ ሰዎች አሁን መልእክታችንን በመቀበል ረገድ ዝግተኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ቢሆን ግን በትዕግሥት ልንይዛቸውና ሰብዓዊ ክብራቸውን ልንጠብቅላቸው ይገባል። ይሖዋ “ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ” ይፈልጋል። (2 ጴጥሮስ 3:9) እኛም ይህን የይሖዋን አመለካከት መያዝ አይኖርብንም? ሰዎችን በጠቅላላ በሚመለከት ዘወትር ወዳጃዊ መንፈስ ለማሳየት በመጣር ምሥክርነት መስጠት የሚቻልበትን መንገድ ልንጠርግ እንችላለን። እርግጥ መንፈሳዊ አደጋ ሊያስከትል ከሚችል ዓይነት ባልንጀርነት እንርቃለን። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ሆኖም የእኛ ዓይነት እምነት የሌላቸውን ሰዎች ባለመናቅ “ቸርነት” እናሳያቸዋለን።—ሥራ 27:3
20. ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ የተዉልን ምሳሌ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
20 አዎን፣ ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ እያንዳንዳችንን አክብሮት እንደሚገባን አድርገው ይመለከቱናል። እኛም ዘወትር እነሱ የሚያደርጉትን በማስታወስ እርስ በርስ ለመከባበር ቀዳሚ እንሁን። በተጨማሪም “ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ” የሚሉትን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃላት ዘወትር እናስታውስ።—ማቴዎስ 23:8
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የአምልኮ አጋሮችህን መመልከት ያለብህ እንዴት ነው?
• ይሖዋና ኢየሱስ የተዉት ምሳሌ ሌሎችን እንድታከብር የሚገፋፋህ እንዴት ነው?
• ባሎችና ወላጆች ሌሎችን ማክበር የሚችሉት እንዴት ነው?
• ሽማግሌዎች ክርስቲያን ባልደረቦቻቸውን እንደ ወንድሞቻቸው አድርገው መመልከታቸው ምን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአድናቆት ቃላት በመሰንዘር ለሚስትህ ያለህን አክብሮት ግለጽ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጆቻችሁን በማዳመጥ አክብሮት አሳዩአቸው
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጉባኤ አባላትን በአክብሮት ያዟቸው