ልታየው በማትችለው ነገር ታምናለህን?
ልታየው በማትችለው ነገር ታምናለህን?
አንድ ሰው ‘ካላየሁ አላምንም’ ብሎ ሲናገር ቃል በቃል አንድን ነገር እስካላየሁ ድረስ አላምንም ማለቱ አይደለም። ሁላችንም ልናያቸው በማንችላቸው ነገሮች እንደምናምን የታወቀ ነው።
ለምሳሌ ያህል መግነጢሳዊ መስክ መኖሩን ለማረጋገጥ በትምህርት ቤት አንድ ሙከራ አድርገህ ይሆናል። ሙከራው እንደሚከተለው ሊሆን ይችላል:- በአንድ ወረቀት ላይ የብረት ፍቅፋቂዎችን በትን። ከዚያም ወረቀቱን ከማግኔቱ በላይ ያዘው። ወረቀቱን ስታንቀሳቅሰው አንድ የሆነ ምትሃታዊ ኃይል ያለ ይመስል የብረት ፍቅፋቂዎቹ ወደ መግነጢሱ ዋልታዎች በመሰብሰብ የመግነጢሳዊ መስኩን ቅርጽ ይይዛሉ። ይህን ሙከራ ብታደርግ መግነጢሳዊ መስኩን
ልታየው ትችላለህ? አትችልም፤ ሆኖም መግነጢሳዊ መስኩ በብረት ፍቅፋቂዎቹ ላይ የሚያስከትለው ለውጥ በግልጽ የሚታይ በመሆኑ መግነጢሳዊ ኃይል መኖሩን እንድታምን ያደርግሃል።ሌሎች ልናያቸው የማንችላቸው ነገሮችንም ያላንዳች ማንገራገር አምነን እንቀበላለን። አንድ ውብ ስዕል ስንመለከት ወይም አንድ ግሩም ቅርፅ አይተን ስናደንቅ የሰዓሊውን ወይም ቅርፁን ያወጣውን ሰው ሕልውና እንደማንጠራጠር የታወቀ ነው። እንግዲያው ስለ አንድ ፏፏቴ ስናስብ ወይም ፀሐይ ስትጠልቅ የምትፈጥረውን ማራኪ እይታ በትኩረት ስንመለከት ቢያንስ ቢያንስ እነዚህን ነገሮች የሠራ አንድ ታላቅ አርቲስት መኖር አለበት ብለን ለማሰብ አንገፋፋምን?
አንዳንዶች የማያምኑበት ምክንያት
የሚያስገርመው ነገር አንዳንድ ሰዎች በአምላክ ላይ የነበራቸውን እምነት ያጡት በቤተ ክርስቲያን በተማሩት ትምህርት ሳቢያ ነው። አምላክ ክፉዎችን በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ያቃጥላል ተብሎ የተነገረው አንድ የኖርዌይ ተወላጅ ሁኔታ ይህን የሚያሳይ ነው። ሰውየው አምላክ ሰዎችን በዚህ መንገድ ያሠቃያል የሚለውን አባባል አእምሮው ሊቀበልለት ስላልቻለ አምላክ የለም ባይ ሆነ።
ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ በአንድ የይሖዋ ምሥክር እርዳታ መጽሐፍ ቅዱስን ለመመርመር ተስማማ። መጽሐፍ ቅዱስ ክፉዎች በእሳታማ ሲኦል ይሠቃያሉ ብሎ እንደማያስተምር ሲገነዘብ በጣም ተገረመ። መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን ከእንቅልፍ ጋር ያመሳስለዋል። ወደ መቃብር ስንወርድ ምንም ዓይነት ሥቃይ የማይሰማን ከመሆኑም በላይ አንዳችም የሚታወቀን ነገር አይኖርም። (መክብብ 9:5, 10) በተጨማሪም ይህ ሰው አምላክ ፈጽሞ የማይታረሙ ክፉዎች ብሎ የሚፈርድባቸው ሰዎች ለዘላለም በመቃብር እንደሚቀሩ ተገነዘበ። (ማቴዎስ 12:31, 32) የቀሩት ሙታን ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይዘው አምላክ በወሰነው ጊዜ ከሞት ይነሳሉ። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ 17:3) ይህ አገላለጽ ምክንያታዊ ነበር። “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር ይስማማል። (1 ዮሐንስ 4:8) ይህ ልበ ቅን ሰው የአምላክን ቃል ማጥናቱን በመቀጠሉ ከጊዜ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተገለጸው አምላክ ፍቅር ሊያድርበት ችሏል።
ሌሎች ደግሞ መከራና ግፍ በመስፋፋቱ ምክንያት አፍቃሪ ፈጣሪ አለ የሚለው ሐቅ አይዋጥላቸውም። በአንድ ወቅት እጁን ወደ ሰማይ ዘርግቶ “እዚህ ምድር ላይ ምግባረ ብልሹነትና ክፋት ተስፋፍቶ እያለ በላይ በሰማይ ሁሉን ቻይና እጅግ ለጋስ የሆነ አምላክ እንዴት ሊኖር ይችላል?” ሲል ከጠየቀው ስዊድናዊ ሰው ጋር ይስማማሉ። ይህም ሰው ይህን ጥያቄ የሚመልስለት ሊያገኝ ባለመቻሉ አምላክ የለም ባይ ሆኖ ነበር። ከጊዜ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። የአምላክ ቃል አምላክ ክፋትን የፈቀደው ለምንድን ነው? ለሚለው ረጅም a
ዘመን ያስቆጠረ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ እንደሚሰጥ ተገነዘበ።ይህ ልበ ቅን የሆነ ሰው ክፋት መኖሩ በራሱ አምላክ ስላለመኖሩ ማስረጃ ሊሆን እንደማይችል ተረዳ። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- አንድ ሰው ሥጋ ለመቁረጥ የሚያገለግል ቢላ ሊሠራ ይችላል። ሆኖም አንድ ሌላ ሰው ቢላውን ገዝቶ ሥጋ ለመቁረጥ ሳይሆን ነፍስ ለማጥፋት ሊጠቀምበት ይችላል። ቢላው አላግባብ ጥቅም ላይ መዋሉ ቢላውን የሠራውን ሰው ሕልውና ውድቅ ሊያደርገው አይችልም። በተመሳሳይም ምድር መጀመሪያ ላይ ከታለመላት ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ጥቅም ላይ አለመዋሏ ፈጣሪ የላትም ሊያሰኝ አይችልም።
መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ሥራ ፍጹም እንደሆነ ይናገራል። “ፍትሕ የማያጓድል፣ ጻድቅና ትክክለኛ ነው።” (ዘዳግም 32:4 NW ) አምላክ ለሰው ልጅ መልካም ስጦታዎች የሰጠ ቢሆንም ከስጦታዎቹ መካከል አንዳንዶቹ አግባብ ባልሆነ መንገድ ጥቅም ላይ በመዋላቸው ይህ ነው የማይባል መከራ አስከትለዋል። (ያዕቆብ 1:17) ይሁን እንጂ አምላክ መከራን ያስወግዳል። ከዚያ በኋላ “ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ፣ . . . በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:11, 29
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ስዊድናዊ ሰው የሌሎች መሰል ሰዎችን መከራ ሲመለከት ልቡ በጥልቅ ተነክቷል። ለሌሎች ጥልቅ አሳቢነት ማሳየቱ ራሱ የአምላክን ሕልውና የሚያረጋግጥ ነው። እንዴት?
አብዛኞቹ ሰዎች በአምላክ የማያምኑ ከሆነ ያላቸው አማራጭ በአዝጋሚ ለውጥ ማመን ነው። የአዝጋሚ ለውጥ አማኞች “ከአካባቢያዊ ሁኔታ ጋር ይበልጥ መጣጣም የቻሉ በሕይወት ይቀጥላሉ” ማለትም ሰዎችና እንስሳት በየወገናቸው በሕይወት ለመቀጠል ትግል ያደርጋሉ ብለው ያስተምራሉ። ራሱን ከአካባቢያዊው ሁኔታ ጋር ማጣጣም የቻለ በሕይወት ይቀጥላል፣ ደካማው ግን ይሞታል። ተፈጥሯዊው ሂደት ይህ ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ደካማው ለጠንካራው ቦታ ለመልቀቅ መሞቱ “ተፈጥሯዊ” ከሆነ እንደ ስዊድናዊው ሰው ያሉ አንዳንድ ጠንካራ ሰዎች የሌሎች ሰዎችን መከራ ሲመለከቱ ለምን ልባቸው በጥልቅ ይነካል?
አምላክን ማወቅ
አምላክ ሰብዓዊ ቅርፅ ስለሌለው ልናየው አንችልም። ሆኖም አምላክ እንድናውቀው ይፈልጋል። ከእሱ ጋር መተዋወቅ የምንችልበት አንዱ መንገድ ዕፁብ ድንቅ የሆኑትን ሥራዎቹን ማለትም የፍጥረት “ሥዕሎቹን” እና “ቅርፃ ቅርፆቹን” በማጥናት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ 1:20 ላይ እንዲህ ይላል:- “[የአምላክ] የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያል።” አዎን፣ አንድን ሥዕል ወይም ቅርፅ ማጥናትህ የአርቲስቱን ባሕርይ ይበልጥ እንድትገነዘብ ሊረዳህ እንደሚችል ሁሉ በአምላክ ዕፁብ ድንቅ ሥራዎች ላይ ማሰላሰልህም ከባሕርይው ጋር ይበልጥ እንድትተዋወቅ ሊረዳህ ይችላል።
እርግጥ ነው፣ የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች እንዲሁ በመመልከት ብቻ በሕይወት ውስጥ ለሚገጥሙን በጣም የሚረብሹ ጥያቄዎች ሁሉ መልስ ማግኘት አንችልም። ሆኖም የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በመመርመር ለእንዲህ ዓይነቶቹ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንችላለን። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ሁለት ሰዎች አምላክ አለ፣ በእኛ ላይ የሚደርሰውም ነገር ያሳስበዋል የሚል መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ የቻሉት መጽሐፍ ቅዱስን አእምሯቸውን ክፍት አድርገው በማንበባቸው ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አምላክ ክፋትን የፈቀደበትን ምክንያት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት እባክህ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ አለ? (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ 10ኛ ምዕራፍ ተመልከት።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
J. Hester and P. Scowen (AZ State Univ.), NASA