በሮቢንሰን ክሩሶ ደሴት የተከናወነ የነፍስ አድን ሥራ
በሮቢንሰን ክሩሶ ደሴት የተከናወነ የነፍስ አድን ሥራ
ሮቢንሰን ክሩሶ ከቺሊ የባሕር ዳርቻ 640 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በፓስፊክ ውቅያኖስ ከሚገኙትና ሁዋን ፈርናንዴስ ተብለው ከሚጠሩት ሦስት ደሴቶች አንዷ ናት። a ይህች 93 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት ደሴት ስሟን ያገኘችው በ18ኛው መቶ ዘመን ዳንየል ዲፎ የተባለ እንግሊዛዊ ደራሲ ከጻፈው ሮቢንሰን ክሩሶ ከተባለ የታወቀ ልብ ወለድ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ በዚህች ደሴት ላይ ብቻውን አራት ዓመት ገደማ የኖረ አሌክሳንደር ሴልከርክ የተባለ ስኮትላንዳዊ ሰው ባሳለፈው አስገራሚ ገጠመኝ ላይ የተመሠረተ ይመስላል።
በደሴቲቷ ላይ በተተከለ አንድ ከእንጨት የተሠራ ምልክት ላይ የተጻፈው ጽሑፍ በከፊል እንዲህ ይላል:- “ስኮትላንዳዊው መርከበኛ አሌክሳንደር ሴልከርክ ከገለልተኝነት ሕይወቱ የሚያላቅቀው ነፍስ አድን ጀልባ ለማግኘት በጭንቀት መንፈስ ተውጦ ቀን በቀን በዚህ ቦታ ላይ እየቆመ ዓይኑን ወዲያና ወዲህ በማንከራተት ከአራት ዓመት በላይ አሳልፏል።” በመጨረሻ ሴልከርክ የነፍስ አድን እርዳታ አግኝቶ ወደ ትውልድ አገሩ ቢወሰድም በራሱ አነስተኛ ገነት ውስጥ ሲኖር ከቆየ በኋላ ዳግመኛ የተመለሰበት ዓለም እርካታ ሊሰጠው አልቻለም። ከጊዜ በኋላ “ምነው፣ እዚያችው ውዷ ደሴቴ ላይ በቀረሁ ኖሮ!” ሲል ቅሬታውን እንደገለጸ ይነገርለታል።
ጊዜያት እያለፉ ሲሄዱ ደሴቲቷ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ “የእምነት ወንጀል” የፈጸሙ አንዳንድ ሰዎች የሚታጎሩባት ወንጀለኞች የሚቀጡባት ቦታ ሆነች። ሴልከርክ በአንድ ወቅት ከተመለከታት ገነት መሰል ደሴት ይህ ምንኛ የተለየ ነው! ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ የደሴቲቱ ነዋሪዎች በብዙ የዓለም ክፍሎች የማይታይ ሰላምና ጸጥታ የሰፈነበት ሕይወት ይመራሉ። የብዙዎቹ ደሴቶች ዓይነተኛ ባሕል የሆነው ዘና ያለ አኗኗር ከማንኛውም ሰው ጋር በቀላሉ ውይይት ለመክፈት የሚያስችል ሁኔታ ይፈጥራል።
ሮቢንሰን ክሩሶ 500 ገደማ የሚሆኑ ነዋሪዎች ያሏት ቢሆንም በዓመት ውስጥ
በአብዛኞቹ ወራት በደሴቲቷ ውስጥ የሚኖሩት 400 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው። ለዚህ አንዱ ምክንያት አንዳንድ እናቶችና ልጆቻቸው ትምህርት ቤቶች ክፍት በሚሆኑባቸው ጊዜያት ወደ ዋናው የቺሊ መሬት የሚሻገሩ መሆኑ ነው። ከተቀሩት የቤተሰባቸው አባሎች ጋር ሆነው ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ወደ ደሴቲቱ የሚመለሱት ትምህርት ቤቶች በሚዘጉባቸው ጊዜያት ብቻ ነው።ሮቢንሰን ክሩሶ ከውብ የአትክልት ሥፍራ ጋር የሚመሳሰል ገጽታ የተላበሰች ብትሆንም አንዳንድ የደሴቲቷ ነዋሪዎች መንፈሳዊ ባዶነት የሚሰማቸው በመሆኑ ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ በመንፈሳዊ ነፍሳቸውን የሚታደጋቸው እንደሚያስፈልጋቸው ሆኖ ተሰምቷቸዋል።
መንፈሳዊ የነፍስ አድን ሥራ
እንዲህ ዓይነቱ መንፈሳዊ የነፍስ አድን ሥራ መከናወን የጀመረው በ1979 ገደማ ነው። በቺሊ ሳንቲያጎ ውስጥ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ታጠና የነበረች አንዲት ሴት ወደዚህች ደሴት በመዛወሯ የተማረችውን ለሌሎች ማስተማር ጀመረች። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለሰብዓዊ ጉዳዮች ወደዚህች ደሴት የሄደ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ በዚህች ሴት እርዳታ በመንፈሳዊ እድገት በማድረግ ላይ
ያሉ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሲያገኝ በጣም ተገረመ። ከሦስት ወራት በኋላ ሽማግሌው ወደ ደሴቲቷ ተመልሶ ሲሄድ በገለልተኛ ሥፍራ የምትገኘው ይህች የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪና ሁለት ተማሪዎቿ ለጥምቀት ዝግጁ ሆነው ስለነበር የጥምቀት ሥርዓቱን አከናወነላቸው። ከጊዜ በኋላ ከእነዚህ አዳዲስ ተጠማቂ ክርስቲያኖች አንዷ አገባችና ከባሏ ጋር ሆና በመንፈሳዊ የሌሎችን ነፍስ ለመታደግ ጥረት ማድረጓን ቀጠለች። ባሏ ቅድሚያውን በመውሰድ እስከ አሁንም ድረስ በደሴቲቷ የሚገኘው ይህ አነስተኛ ቡድን የሚጠቀምበትን መጠነኛ የመንግሥት አዳራሽ ሠራ። ውሎ አድሮ በኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ሳቢያ ሮቢንሰን ክሩሶን ለቅቀው በማዕከላዊ ቺሊ ወደሚገኝ ጉባኤ የተዛወሩ ሲሆን በዚያም በንቃት ይሖዋን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል።ሌሎችንም ከሐሰት ሃይማኖት መታደግ በመቻሉ በደሴቲቱ ላይ የሚገኘው ይህ አነስተኛ ቡድን ቀስ በቀስ እያደገ መሄዱን ቀጠለ። ይሁን እንጂ ተማሪዎች የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ዋናው የቺሊ መሬት መሻገር ስላለባቸው የቡድኑ ቁጥር ይቀንስና ሁለት የተጠመቁ እህቶችና አንዲት ልጃገረድ ብቻ ይቀራሉ። በዕረፍት ጊዜያት አንዳንድ እናቶች ወደ ደሴቲቱ ስለሚመለሱ ቡድኑ በቁጥር ያድጋል። ይህም ዓመቱን ሙሉ ብቻቸውን በደሴቲቷ የሚቆዩት ሦስቱ ክርስቲያኖች እንዲነቃቁ ይረዳቸዋል። እነዚህ እህቶች ትጋት በተሞላበት መንገድ በመሥራታቸው የይሖዋ ምሥክሮች በሮቢንሰን ክሩሶ ውስጥ በስፋት ሊታወቁ ችለዋል። እርግጥ፣ አንዳንድ የደሴቲቷ ነዋሪዎች ሥራቸውን የተቃወሙ ከመሆኑም በላይ ሌሎች የመንግሥቱን መልእክት እንዳይቀበሉ ለመገፋፋት ሞክረዋል። ሆኖም ቅን በሆኑ ልቦች ላይ የተተከሉ የመጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ዘሮች ማደጋቸውን ቀጥለዋል።
የነፍስ አድን እርዳታ ያገኙትን ማጠናከር
በዓመት አንድ ጊዜ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ደሴቲቱን ይጎበኛል። በጣም ሩቅ በሆነ ደሴት ላይ የሚኖሩ በጣት የሚቆጠሩ ምሥክሮችን መጎብኘት ምን ይመስላል? አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች በሮቢንሰን ክሩሶ ያደረገውን የመጀመሪያ ጉብኝት እንዲህ ሲል ገልጾታል:-
“ይህ ጉዞ በጉጉት ስጠብቀው የነበረ ነው። ጉዞውን የጀመርነው ከጠዋቱ 1:00 ሰዓት ከቫልፐሬዞ ተነስተን ወደ ሳንቲያጎ ሴሪዮስ አውሮፕላን ማረፊያ በመጓዝ ነበር። እዚያ እንደደረስን ሰባት ሰዎች በምትይዝ አነስተኛ አውሮፕላን ተሳፈርን። ሁለት ሰዓት ከ45 ደቂቃ ከበረርን በኋላ ከደመናው በላይ ከፍ ብሎ የሚታይ አንድ የተራራ ጫፍ በርቀት ተመለከትን። እየቀረብን ስንሄድ ደሴቲቱን ተመለከትን። በውቅያኖሱ
መካከል የምትታይ ማራኪ አለታማ መሬት ናት። በባሕር ላይ እንደጠፋ መርከብ በውቅያኖሱ ላይ የምትንሳፈፍ ትመስላለች።“መሬት ካረፍን በኋላ በአንዲት ጀልባ ተሳፍረን ወደ መንደሩ ሄድን። በየቦታው የሚታዩት ከባሕሩ በላይ ያፈጠጡ በርካታ ትልልቅ አለቶች በሁዋን ፈርናንዴስ ለሚኖሩ ባለ ፀጉር አቆስጣዎች ማረፊያ ሆነው የሚያገለግሉ አነስተኛ ደሴቶች ሠርተዋል። ባለ ፀጉር አቆስጣዎች ቁጥራቸው በእጅጉ እየተመናመነ በመምጣቱ ጥበቃ የሚደረግላቸው ዝርያዎች ሆነዋል። በድንገት በጀልባዋ አጠገብ አንድ ነገር ውልብ አለና ተመልሶ ባሕሩ ውስጥ ገባ። ከወፍ ክንፍ ጋር የሚመሳሰሉ ድርብ ክንፎች ያሉት በራሪ ዓሣ ነበር። ከውኃ ውስጥ እየዘለለ በመውጣት ሦስት አፅቄዎችን መያዝ የሚያስደስተው ይመስላል። እርግጥ፣ አንዳንድ ጊዜ ይህ አዳኝ ራሱ በሌላ ይታደናል። ከዘለለ በኋላ ተመልሶ ውኃው ላይ ሲያርፍ እሱን ለመዋጥ ተዘጋጅተው የሚጠብቁትን የሌሎች አዳኞች ትኩረት ሊስብ ይችላል።
“በመጨረሻ ወደ ሳን ሁዋን ቦቲስታ (ቅዱስ መጥምቁ ዮሐንስ) መንደር ደረስን። እዛም እንግዶቻቸውን ለመጠበቅ ብለው አለዚያም ዛሬ ደግሞ ማን መጥቶ ይሆን በሚል እንዲሁ የማየት ፍላጎት አድሮባቸው ወደቡ አካባቢ የቆሙ በርካታ የደሴቲቱ ነዋሪዎች ነበሩ። በአካባቢው ያለው ውብ እይታ ልባችንን ሰረቀው። ኤል ዩንኬ (መስፍ) ተብሎ የሚጠራው ትልቅ ግርማ የተላበሰ ወጣ ገባ ተራራ ደማቅ አረንጓዴ ምንጣፍ የተነጠፈበት ይመስላል። ከበስተጀርባው ደግሞ ጠርዝ ጠርዙ እጅብ ባሉ ነጭ ደመናዎች ያሸበረቀ ጥርት ያለ ሰማያዊ ሰማይ ይታይ ነበር።
“በርከት ያሉ ክርስቲያን እህቶችና ልጆቻቸው ወደቡ ላይ ቆመው ሲጠብቁን ተመለከትን። የዕረፍት ጊዜ ስለነበር የቡድኑ ቁጥር ከወትሮው ጨምሯል። ሞቅ ያለ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ለሳምንት ያህል ቤታችን ብለን ወደምንጠራት አንዲት ማራኪ ጎጆ ወሰዱን።
“በጣም ልዩ ሳምንት ነበር። ይህ ሳምንት በፍጥነት እንደሚያልፍ ስለተገነዘብን ጊዜያችንን በሚገባ መጠቀም ፈለግን። በዚያው ዕለት ምሳ እንደበላን ከጥቂት ጊዜ በኋላ መንፈሳዊ እህታችንና የአምላክ መንፈሳዊ ገነት አባል ለመሆን ተዘጋጅታ ወደነበረች አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ሄድን። በጣም የፈነደቀች ቢሆንም እንኳ ትንሽ ፍርሃት ይነበብባታል። ለረጅም ጊዜ ስትጠባበቀው የቆየችው የጥምቀት ግቧ ዳር የሚደርስበት ጊዜ ተቃርቧል። የምሥራቹ አስፋፊ የመሆን ብቃት እንድታገኝ አስፈላጊ በሆኑ አንዳንድ ሐሳቦች ላይ ተወያየን። በቀጣዩ ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በስብከቱ ሥራ ተካፈለች። በሦስተኛው ቀን ለጥምቀት ዝግጁ በሚያደርጉ ብቃቶች ላይ መወያየት ጀመርን። ሳምንቱ ከመገባደዱ በፊት ተጠመቀች።
“በሳምንቱ ውስጥ በተካሄዱት ስብሰባዎች ላይ ጥሩ የተሰብሳቢዎች ቁጥር የነበረ ሲሆን ከፍተኛው የተሰብሳቢዎች ቁጥር 14 ደርሶ ነበር። በየቀኑ የመስክ አገልግሎት፣ ተመላልሶ መጠየቆች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የእረኝነት ጉብኝት ማድረግ የሚቻልበት ጥሩ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። ዓመቱን ሙሉ እንቅስቃሴያቸውን በራሳቸው ለሚያከናውኑት እህቶች ይህ እንዴት ያለ ማበረታቻ ነው!”
በደሴቲቱ ላይ የሚኖሩት ወንዶች ሰብዓዊ ሥራቸው ብዙ ጊዜና ጉልበት የሚጠይቅባቸው ስለሆነ ሊሆን ይችላል፣ ለእውነት ምላሽ ለመስጠት ይቸገራሉ። በደሴቲቱ ላይ ያለው ዋናው ሥራ ሎብስተሮችን ማጥመድ ሲሆን ይህ ደግሞ ከፍተኛ መሥዋዕትነት የሚጠይቅ ሥራ ነው። መሠረተ ቢስ ጥላቻም ብዙዎች አዎንታዊ ምላሽ እንዳይሰጡ በማድረግ ረገድ የበኩሉን ሚና ይጫወታል። ሆኖም ወደፊት ተጨማሪ የደሴቲቷ ነዋሪዎች ወንዶችም ሆኑ ሴቶች አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ ተስፋ ይደረጋል።
እስከ አሁን ድረስ በዚህች ደሴት ላይ አሥር ሰዎች እውነትንና የይሖዋ አምላክን ዓላማዎች በማወቅ ከአደገኛ ሁኔታ ሊድኑ ችለዋል። አንዳንዶቹ በተለያዩ ምክንያቶች ደሴቲቱን ለቅቀዋል። ሆኖም ደሴቲቱን ለቀቁም አልለቀቁ በመንፈሳዊ የዳኑበት ሁኔታ አሌክሳንደር ሴልከርክ ከዳነበት ሁኔታ እጅግ የላቀ ትርጉም እንዳለው ተረጋግጧል። በአሁኑ ጊዜ የትም ይኑሩ የት በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ መመላለስ ችለዋል። በአሁኑ ጊዜ በዚህች ደሴት ላይ የሚገኙት እህቶችና ልጆቻቸው የአትክልት ሥፍራን ገጽታ በተላበሰ አካባቢ የሚኖሩ ቢሆንም ወደፊት ከዚህ በበለጠ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ወደ እውነተኛ ገነትነት በምትለወጠው ምድር ላይ የመኖር ተስፋ አላቸው።
ነፍስ የማዳኑ ሥራ ቀጥሏል
ከመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ሲታይ በሮቢንሰን ክሩሶ የሚገኘው የዚህ አነስተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን አባላት ከተቀሩት መንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው በጣም ርቀው የሚኖሩ ናቸው። ሆኖም እንደ ስኮትላንዳዊው ሰው እንደ ሴልከርክ እንደተተዉ ሆኖ አይሰማቸውም። ያለማቋረጥ በሚደርሷቸው ቲኦክራሲያዊ ጽሑፎች፣ በቺሊ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ በዓመት ሦስት ጊዜ በሚልክላቸው የትልልቅ ስብሰባዎች ፕሮግራሞች የተቀዱባቸው የቪዲዮ ካሴቶችና በዓመት አንድ ጊዜ በወረዳ የበላይ ተመልካች በሚደረግላቸው ጉብኝት አማካኝነት ከይሖዋ ድርጅት ጋር ያልተቋረጠ የቅርብ ግንኙነት ያደርጋሉ። በመሆኑም ‘የዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር’ ንቁ አካል ሆነው ይቀጥላሉ።—1 ጴጥሮስ 5:9
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ደሴቷ ማስ ኣ ቲዬራ የሚል ይፋዊ ስም ተሰጥቷታል።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ቺሊ
ሳንቲያጎ
ሮቢንሰን ክሩሶ ደሴት
ፓስፊክ ውቅያኖስ
ሳን ሁዋን ቦቲስታ
ኤል ዩንኬ
ሳንታ ክላራ ደሴት
[ሥዕል]
አንድ ሰው ወደ ደሴቲቱ እየተቃረበ ሲመጣ በውቅያኖሱ መካከል በጣም ማራኪ የሆነ ዓለታማ መሬት ይመለከታል
[ምንጭ]
የቺሊ ካርታ:- Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.
[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤል ዩንኬ (መስፍ) ተብሎ የሚጠራው ትልቅ ግርማ የተላበሰ ወጣ ገባ ተራራ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሳን ሁዋን ቦቲስታ (ቅዱስ መጥምቁ ዮሐንስ) መንደር
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለተለያዩ አቆስጣዎች ማረፊያ ሆነው የሚያገለግሉ ትናንሽ ደሴቶች
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሳንቲያጎ ቺሊ በአነስተኛ አውሮፕላን ተጓዝን
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣ ገባ የሆነው የሮቢንሰን ክሩሶ ደሴት የባሕር ዳርቻ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በደሴቲቱ ላይ የሚገኘው መለስተኛ የመንግሥት አዳራሽ