በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የይሖዋ ምሥክሮች ማንኛውንም የደም ተዋጽኦ ለሕክምና ይወስዳሉን?

ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መሠረታዊ መልስ የይሖዋ ምሥክሮች ደም አይወስዱም የሚል ነው። ደምን በተመለከተ የተሰጠው የአምላክ ሕግ ተለዋዋጭ ከሆኑ አመለካከቶች ጋር እንዲስማማ ተብሎ ማሻሻያ ሊደረግበት የሚችል እንዳልሆነ እናምናለን። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ደምን ወደ አራት ዋና ዋና ክፍሎችና እነዚህንም ክፍልፋዮች እንደገና መለያየት በመቻሉ አዳዲስ ጥያቄዎች ተከስተዋል። አንድ ክርስቲያን እነዚህን ለመውሰድ ወይም ላለመውሰድ ከመወሰኑ በፊት ሊገኙ ከሚችሉት የሕክምና ጥቅሞችና ጉዳቶች ባሻገር መመልከት ይኖርበታል። ሊያሳስበው የሚገባው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚልና ውሳኔው ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ባለው ዝምድና ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖ መሆን ይኖርበታል።

ዋነኛው አወዛጋቢ ጉዳይ ምን እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት መረዳት እንድትችል አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ ታሪካዊና ሕክምና ነክ ማስረጃዎችን ተመልከት።

ይሖዋ አምላክ የሁላችንም አባት ለሆነው ለኖኅ ደም እንደ አንድ ልዩ ነገር ተደርጎ መታየት እንዳለበት ነግሮታል። (ዘፍጥረት 9:​3, 4) ከጊዜ በኋላ ለእስራኤላውያን የተሰጠው የአምላክ ሕግ ደም ቅዱስ መሆኑን አሳይቷል:- “ከእስራኤልም ልጆች ወይም በመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው ደም ቢበላ፣ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ።” አንድ እስራኤላዊ የአምላክን ሕግ በመጣስ ሌሎችን ሊበክል ስለሚችል አምላክ “ያንንም ሰው ከሕዝቡ ለይቼ አጠፋዋለሁ” ሲል አክሎ ተናግሯል። (ዘሌዋውያን 17:​10) በኋላም ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በኢየሩሳሌም ባደረጉት ስብሰባ ላይ ‘ከደም መራቅ’ እንዳለብን ደንግገዋል። ይህን ትእዛዝ ማክበር ከጾታ ብልግና እና ከጣዖት አምልኮ የመራቅን ያህል አስፈላጊ ነው።​—⁠ሥራ 15:​28, 29

‘መራቅ’ የሚለው ቃል በዚያን ጊዜ ለነበሩት ምን ትርጉም ነበረው? ክርስቲያኖች ትኩስም ሆነ የረጋ ደም እንዲሁም ደሙ ያልፈሰሰ የእንስሳ ሥጋ አይበሉም ነበር ማለት ነው። በተጨማሪም እንደ ደም ቋሊማ የመሳሰሉ ደም የተጨመረባቸውን ምግቦች አይበሉም ነበር። ከእነዚህ በየትኛውም መንገድ ደም መውሰድ የአምላክን ሕግ ያስጥስ ነበር።​—⁠1 ሳሙኤል 14:​32, 33

ተርቱሊያን (ሁለተኛውና ሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ) ካዘጋጃቸው ጽሑፎች መረዳት እንደምንችለው በጥንት ዘመን የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች ደም መብላትን በተመለከተ ምንም የሚረብሻቸው ነገር አልነበረም። ተርቱሊያን ክርስቲያኖች ደም ይበላሉ ተብሎ ለተሰነዘረባቸው የሐሰት ክስ መልስ ሲሰጥ ደም በመጎንጨት ስምምነታቸውን ያጸድቁ ስለነበሩ ጎሳዎች ጠቅሷል። በተጨማሪም “በስፖርት መዘውተሪያ ቦታዎች ትዕይንት በሚቀርብበት ጊዜ [አንዳንዶች] ለሚጥል በሽታ መድኃኒት እንዲሆናቸው . . . የወንጀለኛውን ትኩስ ደም ተስገብግበው ይልፉ እንደነበር” ጠቅሷል።

እነዚህ ልማዶች (ምንም እንኳ አንዳንድ ሮማውያን ከጤና አንፃር ቢወስዷቸውም) ለክርስቲያኖች ተገቢ አልነበሩም። ተርቱሊያን “በምግባችን ውስጥ የእንስሳት ደም እንኳ አንጨምርም ነበር” ሲል ጽፏል። ሮማውያን የእውነተኛ ክርስቲያኖችን የአቋም ጽናት ለመፈተን ደም የተቀላቀለበት ምግብ ያቀርቡላቸው ነበር። ተርቱሊያን በማከል እንዲህ ብሏል:- “እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፣ [ክርስቲያኖች] የእንስሳት ደም እንደሚያንገሸግሻቸው አሳምራችሁ እያወቃችሁ የሰው ደም ለመጠጣት ይስገበገባሉ ብላችሁ ማሰባችሁ ምን ማለታችሁ ነው?”

በዛሬው ጊዜ አንድ ሐኪም ደም እንዲወስዱ ሐሳብ ቢያቀርብላቸው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ያወጣው ሕግ ጥያቄ ላይ እንደሚወድቅ የሚያውቁት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። የይሖዋ ምሥክሮች በእርግጥ በሕይወት መኖር የሚፈልጉ ቢሆንም ደምን በተመለከተ ይሖዋ ያወጣውን ሕግ ለማክበር ቆርጠናል። በዘመናችን ካለው ሕክምና አንፃር ሲታይ ይህ ምን ማለት ነው?

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሙሉ ደም መስጠት የተለመደ እየሆነ በመጣበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ድርጊት ከአምላክ ሕግ ጋር እንደሚቃረን ተገነዘቡ። አሁንም ቢሆን ያለን እምነት ይኸው ነው። ይሁን እንጂ ሕክምና ከጊዜ ወደ ጊዜ ይለዋወጣል። በዛሬው ጊዜ በአብዛኛው የሚሰጠው ሙሉ ደም ሳይሆን ከደም ዋና ዋና ክፍሎች አንዱ ነው:- (1) ቀይ የደም ሕዋስ፤ (2) ነጭ የደም ሕዋስ፤ (3) አርጊ ሕዋስ ደም (platelets)፤ (4) ፕላዝማ (እዥ) ፈሳሹ ክፍል። በታካሚው ሁኔታ ላይ ተመርኩዘው ሐኪሞች ቀይ የደም ሕዋስ፣ ነጭ የደም ሕዋስ፣ አርጊ ሕዋስ ደም ወይም ፕላዝማ ሊያዝዙ ይችላሉ። እነዚህን ዋና ዋና ክፍሎች መርጦ የመስጠቱ አሠራር አንዲትን አሃድ (unit) ደም ለበርካታ ታካሚዎች ከፋፍሎ ለመስጠት ያስችላል። የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉ ደምም ሆነ ከአራቱ ዋና ዋና ክፍሎች ውስጥ አንዱን መውሰድ የአምላክን ሕግ እንደሚያስጥስ ያምናሉ። ይህን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አቋም መከተላቸው እንደ ሄፐታይተስና ኤድስ ያሉትን ጨምሮ በደም ሊተላለፉ ከሚችሉ በርካታ በሽታዎች ጠብቋቸዋል።

ደም ከዋና ዋናዎቹም ክፍሎች በላይ ሊከፋፈል ስለሚችል ከዋና ዋናዎቹ ክፍሎች የሚገኙትን ክፍልፋዮች በተመለከተ ጥያቄዎች ይነሳሉ። እነዚህ ክፍልፋዮች ጥቅም ላይ የሚውሉት እንዴት ነው? አንድ ክርስቲያን ክፍልፋዮቹን በተመለከተ ውሳኔ ሲያደርግ መመዘን የሚኖርበት ነገር ምንድን ነው?

ደም ውስብስብ ነው። ሌላው ቀርቶ 90 በመቶ ውኃ የሆነው ፕላዝማ እንኳ ሚኒራሎችንና ስኳርን ጨምሮ በርካታ ሆርሞኖችን፣ ኢካርቦናማ ጨውን (inorganic salt)፣ ኤንዛይሞችንና ንጥረ ምግቦችም ይዟል። በተጨማሪም ፕላዝማ እንደ አልቡሚን፣ ደም እንዲረጋ የሚያስችሉ ንጥረ ነገሮችንና በሽታ ተከላካይ ፀረ እንግዳ አካላትን የመሳሰሉ ፕሮቲኖችን ይዟል። ባለሙያዎች በርካታ የፕላዝማ ፕሮቲኖችን ለይተው በማውጣት ጥቅም ላይ ያውሏቸዋል። ለምሳሌ ያህል ደም እንዲረጋ የሚያስችለው ፋክተር 8 በቀላሉ ደም ለሚፈስሳቸው ለሄሞፊሊያ በሽተኞች ይሰጣል። ወይም አንድ ሰው ለአንድ ዓይነት በሽታ የተጋለጠ ከሆነ ሐኪሞች መድህን (immunity) ካላቸው ሰዎች የደም ፕላዝማ ውስጥ ጋማ ግሎቡሊን ተወስዶ በመርፌ እንዲሰጠው ሊያዝዙ ይችላሉ። ሌሎች የፕላዝማ ፕሮቲኖችም ለሕክምና ተብለው ሊታዘዙ ይችላሉ። ሆኖም ከላይ የተጠቀሰው ነጥብ ደቃቅ ክፍልፋዮችን ለማግኘት አንድ ዋና የደም ክፍል (ፕላዝማ) ምን ያህል ሊከፋፈል እንደሚችል ያሳያል። a

የደም ፕላዝማ ብዙ ክፍልፋዮች ሊወጣው እንደሚችል ሁሉ ሌሎቹን ዋና ዋና ክፍሎችም (ቀይ የደም ሕዋስ፣ ነጭ የደም ሕዋስ፣ አርጊ ሕዋስ ደም) ወደ ተለያዩ አነስተኛ ክፍሎች መለያየት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ ነጭ የደም ሕዋስ አንዳንድ በቫይረስ የሚተላለፉ ልክፈቶችንና የካንሰር በሽታዎችን ለማከም ሊያገለግሉ ለሚችሉ ኢንተርፌሮን እና ኢንተርሉኪን ለተባሉት መድኃኒቶች ምንጭ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ከአርጊ ሕዋስ ደም፣ ቁስል እንዲሽር የሚያስችል ንጥረ ነገር ለማውጣት ይቻላል። በተጨማሪም (ቢያንስ መጀመሪያ ላይ) ከደም ክፍሎች የተወሰዱ ንጥረ ነገሮችን የሚያካትቱ መድኃኒቶች በመዘጋጀት ላይ ናቸው። እንዲህ ዓይነቶቹ ሕክምናዎች የደምን ዋና ዋና ክፍሎች በደም ሥር እንደመውሰድ ተደርገው አይታዩም። በአብዛኛው የሚከናወነው ከዋና ዋና ክፍሎች ላይ የተወሰኑ ክፍሎችን ወይም ክፍልፋዮችን በመውሰድ ነው። ክርስቲያኖች ለሕክምና ብለው እነዚህን ክፍልፋዮች መውሰድ ይኖርባቸዋልን? እንደዚያ ብለን መናገር አንችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ዝርዝር መመሪያ ስለማይሰጥ እያንዳንዱ ክርስቲያን በአምላክ ፊት ማስተዋል የተሞላበት የራሱን ውሳኔ ማድረግ አለበት።

አንዳንዶች ከደም የተገኘ ማንኛውም ነገር (ሌላው ቀርቶ ጊዜያዊ ሃላፊ መድህን (passive immunity) የሚሰጡ ክፍልፋዮችን ጨምሮ) ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም። ‘ከደም ራቁ’ የሚለውን የአምላክ ትእዛዝ የሚረዱት በዚህ መልኩ ነው። በተጨማሪም አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ከአንድ እንስሳ የወጣ ደም ‘በምድር ላይ መፍሰስ’ ያለበት መሆኑን እንደሚያጠቃልል ይገነዘባሉ። (ዘዳግም 12:​22-24) ይህ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሚኖረው እንዴት ነው? ጋማ ግሎቡሊንን፣ የደም ተዋጽኦ ያላቸው ደም አርጊ ንጥረ ነገሮችንና ሌሎችንም ለማግኘት ሙሉው ደም ወደ አነስተኛ ክፍልፋይ መለወጥ ይኖርበታል። በመሆኑም አንዳንድ ክርስቲያኖች ሙሉ ደም ወይም አራቱን ዋና ዋና ክፍሎች ለመውሰድ ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ሁሉ እንደዚህ ዓይነት የደም ውጤቶችንም አይወስዱም። እንዲህ ዓይነቱ ማስተዋል የተሞላበት ከልብ የመነጨ አቋማቸው ሊከበርላቸው ይገባል።

ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ ከዚህ የተለየ አቋም ይወስዳሉ። እነሱም ቢሆኑ ሙሉ ደም፣ ቀይ የደም ሕዋስ፣ ነጭ የደም ሕዋስ፣ አርጊ ሕዋሰ ደም ወይም ፕላዝማ ለመውሰድ ፈቃደኞች አይደሉም። ይሁን እንጂ አንድ ሐኪም ከዋና ዋናዎቹ የደም ክፍሎች በተወሰደ ክፍልፋይ ቢያክማቸው ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። እዚህም ላይ ቢሆን ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። አንድ ክርስቲያን ጋማ ግሎቡሊን ለመወጋት ፈቃደኛ ሊሆን ቢችልም ከቀይ ወይም ከነጭ የደም ሕዋስ የተወሰደ ነገር የያዘ መርፌ ለመወጋት ግን ሊስማማ ወይም ላይስማማ ይችላል። በጥቅሉ ሲታይ ግን አንዳንድ ክርስቲያኖች የደም ክፍልፋዮችን መውሰድ እችላለሁ ብለው እንዲደመድሙ የሚያደርጋቸው ምን ሊሆን ይችላል?

የሰኔ 1, 1990 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው “የአንባብያን ጥያቄዎች” በአንዲት እርጉዝ ሴት ደም ውስጥ ያሉ የፕላዝማ ፕሮቲኖች (ክፍልፋዮች) ራሱን የቻለ የደም ዝውውር ወዳለው ሽል እንደሚገቡ ጠቅሷል። በመሆኑም አንዲት እናት ለልጅዋ ጠቃሚ የሆነ መድህን በመስጠት ኢሚውኖግሎቡሊን ታስተላልፋለች። ከዚህ በተናጥል የሽሉ ቀይ የደም ሕዋሳት የተለመደውን በሕይወት የመቆያ ዘመናቸውን ሲያጠናቅቁ በውስጣቸው ባለው ኦክሲጅን ተሸካሚ በሆነው ክፍል ላይ ለውጥ ይካሄዳል። አንዳንዱ ወደ ቢሊሩቢን ተቀይሮ የእንግዴ ልጁን አልፎ ወደ እናትየው ይገባና ከሰውነቷ ከሚወጣው ቆሻሻ ጋር አብሮ ይወገዳል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ተፈጥሯዊ በሆነው በዚህ መንገድ የደም ክፍልፋዮች ወደ ሌላ ሰው ማለፍ እስከቻሉ ድረስ ከደም ፕላዝማ ወይም ሕዋሳት የተገኘ የደም ክፍልፋይ መውሰድ እንደሚቻል ይወስኑ ይሆናል።

የሰዎች አመለካከትና የሚወስዱት ማስተዋል የተሞላበት ውሳኔ ሊለያይ መቻሉ ጉዳዩ ክብደት የሌለው ተራ ነገር ነው ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት አይቻልም። እንዲያውም አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ሆኖም አንድ ግልጽ የሆነ መሠረታዊ ሐቅ አለ። ከላይ የቀረበው ጽሑፍ የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉውን ደምም ሆነ ዋና ዋናዎቹን የደም ክፍሎች እንደማይወስዱ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደም፣ ከዝሙትም እንዲርቁ’ ያዝዛቸዋል። (ሥራ 15:​28, 29) ከዚህ በላይ ግን የየትኛውንም ዋና ዋና የደም ክፍል ክፍልፋዮች በተመለከተ እያንዳንዱ ክርስቲያን በጥንቃቄና በጸሎት ካሰበበት በኋላ ማስተዋል በተሞላበት መንገድ የራሱን ውሳኔ ማድረግ አለበት።

ብዙ ሰዎች ቶሎ ፋታ የሚሰጥ መስሎ ከታያቸው የትኛውንም የሕክምና ዓይነት ሌላው ቀርቶ በጤና ላይ አደጋ እንደሚያስከትል የሚታወቅን፣ የደም ተዋፆዎችን እንደመጠቀም ያለ ሕክምና ከመቀበል ወደኋላ አይሉም። አንድ ቅን ክርስቲያን ከጤና አኳያ በተጨማሪ ሌሎች ነጥቦችንም የሚያካትት ሰፋ ያለና ይበልጥ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ለመያዝ ይጥራል። የይሖዋ ምሥክሮች ጥራት ያለው የሕክምና እርዳታ ለመስጠት የሚደረጉትን ጥረቶች ያደንቃሉ። እንዲሁም የትኛውም የሕክምና ዓይነት ያለውን ጠቃሚና ጎጂ ጎን ያመዛዝናሉ። ይሁን እንጂ ከደም የተገኙ የሕክምና ውጤቶችን በተመለከተ አምላክ የሚናገረውን ነገር እና ከሕይወት ሰጪያችን ጋር ያላቸውን የግል ዝምድና በጥንቃቄ ያመዛዝናሉ።​—⁠መዝሙር 36:​9

አንድ ክርስቲያን መዝሙራዊው እንዲህ ሲል የጻፈው ዓይነት ትምክህት ማዳበሩ እንዴት ያለ በረከት ነው:- “እግዚአብሔር አምላክ ምሕረትንና እውነትን ስለ ወደደ፣ ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም። . . . አምላክ ሆይ፣ በአንተ የታመነ ሰው ምስጉን ነው”!​—⁠መዝሙር 84:​11, 12

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የሰኔ 15, 1978 (እንግሊዝኛ) እና የጥቅምት 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡትን “የአንባብያን ጥያቄዎች” ተመልከት። መድኃኒት አምራች ድርጅቶች ከደም ያልተወሰዱና ከዚህ ቀደም ይሠራባቸው በነበሩ ከአንዳንድ የደም ክፍልፋዮች ምትክ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ሰው ሠራሽ ምርቶችን ቀምመዋል።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለአንድ ሐኪም ሊቀርቡ የሚችሉ አንዳንድ ጥያቄዎች

የደም ተዋጽዖ እንድትወስድ ሊያደርግህ የሚችል ቀዶ ሕክምና ወይም ሌላ ዓይነት ሕክምና ቢያጋጥምህ እንዲህ ብለህ ጠይቅ:-

የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን በማንኛውም ሁኔታ ሥር ብገኝ ደም (ሙሉ ደም፣ ቀይ የደም ሕዋስ፣ ነጭ የደም ሕዋስ፣ አርጊ ሕዋሰ ደም ወይም የደም ፕላዝማ) መውሰድ እንደማልፈልግ ሕክምና የሚያደርጉልኝ ባለሙያዎች በሙሉ ያውቃሉን?

ከደም ፕላዝማ፣ ከቀይ ወይም ከነጭ የደም ሕዋስ ወይም ከአርጊ ሕዋስ ደም የተዘጋጀ መድኃኒት የሚታዘዝልህ ከሆነ እንዲህ ብለህ ጠይቅ:-

መድኃኒቱ የተዘጋጀው ከአራቱ የደም ዋና ዋና ክፍሎች በአንዱ ነውን? ከሆነ ከምን እንደተሠራ ሊያስረዱኝ ይችላሉን?

በዚህ መንገድ ከተዘጋጀው መድኃኒት ውስጥ ምን ያህሉ ነው የሚሰጠኝ? በምንስ መንገድ?

ሕሊናዬ ፈቅዶልኝ ይህን የደም ክፍልፋይ ብወስድ ምን ዓይነት ችግር ሊያስከትልብኝ ይችላል?

ይህን የደም ክፍልፋይ ለመውሰድ ሕሊናዬ ባይፈቅድልኝ ሌላ ምን ዓይነት ሕክምና ልወስድ እችላለሁ?

ተጨማሪ ጊዜ ወስጄ ይህን ጉዳይ ካሰብኩበት በኋላ ውሳኔዬን መቼ ላሳውቅዎት እችላለሁ?