በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍጹም የሆነ ሕይወት ሕልም አይደለም!

ፍጹም የሆነ ሕይወት ሕልም አይደለም!

ፍጹም የሆነ ሕይወት ሕልም አይደለም!

ፍጹም የሆነ ዓለም ለአንተ ምን ትርጉም አለው? ወንጀል፣ አደገኛ ዕፅ፣ ረሃብ፣ ድህነት ወይም የፍትሕ መጓደል የሌለበትን ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ለአንድ አፍታ አስብ። ሁሉም ስሜታዊም ሆነ አካላዊ ጤና ያገኛል። ሞትም ጭምር ስለሚወገድ ሃዘን አይኖርም። እንዲህ ባለ ዓለም ውስጥ ለመኖር መጓጓቱ ምክንያታዊ ነውን?

ብዙ ሰዎች ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም እንኳ የሰው ልጅ አእምሮ ወይም ያካበተው እውቀት ሁሉም ሰው ሰላምና ደስታ አግኝቶ የሚኖርበት ፍጹም የሆነ ዓለም ያመጣል ብለው አያምኑም። በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ልጅ ነገሮችን ለማሻሻልና ጉድለቶችን ለማስተካከል እንደሚፈልግ የሚካድ አይደለም። እርግጥ ነው፣ እንዲሁ የማይሆን ሕልም ማለም ቤት አልባ ለሆኑና ለድሆች የሚፈይድላቸው ወይም ከሥቃያቸው እፎይታ ለማግኘት ለሚጓጉ ለአካል ጉዳተኞችና ለታመሙ ሰዎች የሚያስገኝላቸው እርካታ የለም። ባጭሩ ፍጹም የሆነ ዓለም በሰዎች የፈጠራ ችሎታ አይመጣም። ይሁን እንጂ ጊዜያችን ችግርና ጭቆና የሞላበት ቢሆንም እንኳ ፍጹም ብለህ ልትጠራው የምትችለው ዓለም በቅርቡ እንደሚመጣ ለማመን የሚያበቃ ጠንካራ ማስረጃ አለ።

ፍጹም ስለሆነ ሕይወት በምታስብበት ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ወደ አእምሮህ መምጣቱ አይቀርም። ፍጹም ሆኖ በምድር ላይ የኖረው ኢየሱስ ብቻ አይደለም። በአምላክ መልክ የተፈጠሩት አዳምና ሔዋንም በገነት ውስጥ ፍጹም ሕይወት ነበራቸው። ይሁን እንጂ በሰማያዊ አባታቸው ላይ በማመጻቸው ምክንያት ይህን ግሩም ሕይወት አጡ። (ዘፍጥረት 3:​1-6) ሆኖም ፈጣሪ ለዘላለም የመኖር ምኞት በሰው ልጆች ውስጥ አሳድሯል። መክብብ 3:​11 ይህን ሲያረጋግጥ “[አምላክ] ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው” በማለት ይናገራል።

አለፍጽምናና ኃጢአት የሰውን ልጅ “ከንቱ” ሕይወት እንዲኖርና ‘የጥፋት ባሪያ’ እንዲሆን ያደረገው ቢሆንም ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውን የሚከተለውን የሚያጽናና ቃል ልብ በል:- “የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና። ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፣ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።” (ሮሜ 8:​19-21) አምላክ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና ለመመለስ ያደረገው ዝግጅት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት እውን እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል።​—⁠ዮሐንስ 3:​16፤ 17:​3

ከዚህ ግሩም የወደፊት ተስፋ በተጨማሪ ሁላችንም በመንፈሳዊ እድገት የማድረግ አቅም ያለን ሲሆን በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሳይቀር እድገታችን ግልጥ ሆኖ እንዲታይ ማድረግ እንችላለን።

ምክንያታዊ ለመሆን ጣር

ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም መሆንን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አድርጎ ከመመልከቱ የተነሳ በፊቱ ተሰብስበው ያዳምጡ የነበሩትን በርካታ ሰዎች “የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 5:​48) ኢየሱስ በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ስንኖር እንከን የሌለብን ሆነን እንድንመላለስ ይጠብቅብናል ማለት ነው? በጭራሽ። እርግጥ ነው፣ የልግስናን፣ የደግነትንና ለሰዎች ፍቅር የማሳየትን ባሕርያት ለማዳበር መጣጣር ያለብን ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር ሳናደርግ እንቀራለን። እንዲያውም ከኢየሱስ ሐዋርያት መካከል አንዱ “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም” በማለት ጽፏል።​—⁠1 ዮሐንስ 1:​9, 10

ያም ሆነ ይህ ጽንፈኝነትን አስወግደን ራሳችንን በምንመለከትበትና ሌሎችን በምንይዝበት መንገድ ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንችላለን። ሚዛናዊና ምክንያታዊ ባሕርይ መላበስ የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው መመሪያ የተሻለ ምክር ከየት ማግኘት ይቻላል? እንደ ደስታና ልከኝነት የመሰሉ ባሕርያትን ማዳበር በሥራ ቦታ አብረውን ከሚሠሩ ሰዎች፣ ከትዳር ጓደኛችን እንዲሁም ከወላጆቻችን ወይም ከልጆቻችን ጋር ተስማምተን እንድንኖር ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፣ ደስ ይበላችሁ። ገርነታችሁ [“ምክንያታዊነታችሁ፣” NW ] ለሰው ሁሉ ይታወቅ” በማለት ለክርስቲያኖች ምክር ለግሷል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​4, 5

ምክንያታዊ መሆን የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

ከሌሎች በምትጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆንህና ጉዳትና ችግር ሊያስከትልብህ የሚችለውን ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይን ማስወገድህ ራስህንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ይጠቅማል። አቅምን በትክክል ማወቅ ማለት ልታደርግ ስለምትፈልገው ነገር እውነታን መቀበልና ምክንያታዊ መሆን ማለት ነው። አምላክ የፈጠረን በምድር ላይ እንድንኖርና እኛንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን የሚጠቅም ትርጉም ያለው ሥራ በመሥራት እርካታ እንድናገኝ ነው።​—⁠ዘፍጥረት 2:​7-9

ከራስህ ብዙ የምትጠብቅ ሰው ከሆንክ ለምን ወደ ይሖዋ አትጸልይም? የአምላክን ሞገስ ማግኘትህ ከፍተኛ እፎይታ ያመጣልሃል። ይሖዋ አፈጣጠራችንንና ፍጹም አለመሆናችንን ያውቃል፤ በመሆኑም ግትር ወይም ከእኛ አቅም በላይ የሚጠብቅ አምላክ አይደለም። መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤ ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፣ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ።” (መዝሙር 103:​13, 14) አምላክ ሰዎችን እንዲህ በመሰለ የምሕረት መንገድ የሚይዝ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል! አቅማችን ውስን መሆኑን ቢያውቅም እንደ ተወደዱ ልጆች በፊቱ ውድ ሆነን ልንታይ እንችላለን።

ፍጽምና የመጠበቅን ባሕርይ ይዞ ከመኖር ይልቅ መንፈሳዊ ማስተዋልንና ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበሩ ምንኛ ጥበብ ነው! ከዚህም በላይ ይሖዋ በእርሱ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሰውን ዘር ወደ ፍጽምና ደረጃ ለማድረስ ያወጣውን ዓላማ እንዳይፈጸም ሊያግደው የሚችል ኃይል እንደሌለ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ይሁን እንጂ ሰብዓዊ ፍጽምና ሲባል ምን ማለት ነው?

ፍጹም የሆነ ሕይወት ፍጽምናን ከመጠበቅ ባሕርይ የተሻለ ነው

ፍጹም መሆን ፍጽምናን ከመጠበቅ ባሕርይ የተለየ ነው። በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በሚተዳደረው ገነት ውስጥ እንዲኖሩ መብት የሚሰጣቸው ሰዎች ከሌሎች ብዙ የሚጠብቁና ራሳቸውን የሚያመጻድቁ እንደማይሆኑ የተረጋገጠ ነው። ከታላቁ መከራ በሕይወት ለመዳን የሚያስችለው አንደኛው ብቃት ሐዋርያው ዮሐንስ በመዘገበው መሠረት በዓለም ዙሪያ የሚገኙት እጅግ ብዙ ሰዎች “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው” በማለት እንደገለጹት ለቤዛው መሥዋዕት ልባዊ አድናቆት ማሳየት ነው። (ራእይ 7:​9, 10, 14) ከፊታችን እየቀረበ ካለው ታላቅ መከራ በሕይወት የሚተርፉ ሁሉ ለእነርሱና በእርሱ ላይ እምነት ለሚያሳዩ ሁሉ ለሞተው ለክርስቶስ አመስጋኝነታቸውን ይገልጻሉ። በፍቅር ላይ ተመሥርቶ ያቀረበው መሥዋዕት ከአለፍጽምናቸውና ከድክመታቸው ለዘለቄታው ያላቅቃቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 3:​16፤ ሮሜ 8:​21, 22

ፍጹም የሆነ ሕይወት ምን ይመስል ይሆን? ከፉክክርና ከራስ ወዳድነት ምኞት ነፃ በሆነ መንገድ ሰዎች የሚያሳዩት ፍቅርና ደግነት ጭንቀትንና ለራስ ጥሩ ግምት የማጣትን ባሕርይ በማስወገድ ሕይወትን ይበልጥ አስደሳች ያደርገዋል። ፍጹም የሆነ ሕይወት አሰልቺ አይሆንም። የአምላክ ቃል ስለ ገነት ዝርዝር ማብራሪያ የሚሰጥ ባይሆንም ምን ዓይነት ሕይወት ልንጠብቅ እንደምንችል ግን ይገልጻል:- “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፣ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና። . . . በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም።”​—⁠ኢሳይያስ 65:​21-23

በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ምን ዓይነት መዝናኛ፣ የገበያ ሥፍራ፣ ቴክኖሎጂ ወይም መጓጓዣ ይኖር ይሆን እያሉ ከማሰብ ይልቅ የሚከተሉት ቃላት ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ በዓይነ ሕሊናህ ልትመለከት ትችላለህ:- “ተኩላና ጠቦት በአንድነት ይሰማራሉ፣ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል፣ የእባብም መብል ትቢያ ይሆናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ አይጐዱም፣ አያጠፉምም፣ ይላል እግዚአብሔር።” (ኢሳይያስ 65:​25) ፍጹም የሆነ ሕይወት በአሁኑ ጊዜ ካለው ሕይወት ምንኛ የተለየ ነው! በዚያ ጊዜ የመኖር መብት ከሚሰጣቸው ሰዎች መካከል አንዱ የምትሆን ከሆነ አፍቃሪው ሰማያዊ አባትህ ለአንተም ሆነ ለቤተሰብህ እንደሚያስብ እርግጠኛ እንድትሆን የሚያበቃ ምክንያት ይኖርሃል። “በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፣ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።”​—⁠መዝሙር 37:​4

ፍጹም የሆነ ሕይወት ሕልም አይደለም። ይሖዋ ለሰው ዘሮች ያወጣው ፍቅራዊ ዓላማ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ያገኛል። አንተም ሆንክ ቤተሰብህ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ፍጽምና ከሚላበሱትና ለዘላለም ከሚኖሩት ሰዎች መካከል ልትሆኑ ትችላላችሁ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ትንቢት ይናገራል።​—⁠መዝሙር 37:​29

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍጽምና የመጠበቅን ወይም ጥቃቅኗን ነገር ሁሉ አክብዶ የመመልከትን ባሕርይ በማስወገድ ለራሳችንና ለሌሎች ሰዎች ባለን አመለካከት ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንችላለን

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዓይነ ሕሊናህ ሰላምና ጽድቅ በሰፈነበት ገነት ውስጥ እንዳለህ አድርገህ ለመመልከት ለምን አትሞክርም?