በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍጽምና የመጠበቅን ባሕርይ መዋጋት ያለብን ለምንድን ነው?

ፍጽምና የመጠበቅን ባሕርይ መዋጋት ያለብን ለምንድን ነው?

ፍጽምና የመጠበቅን ባሕርይ መዋጋት ያለብን ለምንድን ነው?

ሥራህ ሁሉ ልቅም ያለና ምንም ዓይነት እንከን የማይገኝበት እንዲሆን ትፈልጋለህ? እንዲህ ያለው ፍላጎት አንተንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን በብዙ መንገድ ሊጠቅም እንደሚችል የታወቀ ነው። በሌላ በኩል ግን አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱ ፍላጎታቸው ከልክ ያልፍና ፍጽምና የሚጠብቁ ይሆናሉ። ይህ ምን ማለት ነው?

ፍጽምና መጠበቅ ተብሎ የተተረጎመው “ፐርፌክሽኒዝም” የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል አንዱ ፍቺ “ፍጽምና የጎደለውን ነገር ሁሉ ተቀባይነት እንደሌለው አድርጎ ማሰብ” የሚል ነው። እንዲህ ያለ ባሕርይ ያላቸው ሰዎች አጋጥመውህ ሊሆን እንደሚችል የተረጋገጠ ነው። ከሌሎች ሰዎች የሚጠብቁት ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ብዙ ችግር ሲፈጥርና እርካታ ማጣትንና ተስፋ መቁረጥን ሲያስከትል ልትመለከት ትችላለህ። ሚዛናዊ አመለካከት ያላቸው ብዙ ሰዎች በማንኛውም የኑሮ ዘርፍ የተጋነነና ከልክ ያለፈ ነገር በመሻት ከሌሎች ፍጽምናን መጠበቅ የሚወደድ ነገር እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። ይህ ሊዋጉት የሚገባ ባሕርይ ነው። ይሁን እንጂ ወደ ራሳችን አመለካከት ወይም ዝንባሌ ስንመጣ ችግሩ ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ እንዳለብን መገንዘቡ አስቸጋሪ ሊሆንብን የሚችል መሆኑ ነው። ስለሆነም ይህን ባሕርይ መዋጋት ቀላል አይደለም።

ኔልሰን ትልቅ ኃላፊነት ያለውና መፍትሔ የሚሹ በርካታ ችግሮች የሚቀርቡለት ሰው ነው። የሥራውን ውጤት የሚያሳዩ አኃዛዊ መረጃዎችን ነጋ ጠባ መመርመር ደስ ይለዋል። ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ደግሞ ለምርታማነት ነው። ፍጽምና መጠበቅ ብዙውን ጊዜ ፉክክር በበዛበት በሥራው ዓለም ስኬታማ ለመሆን አስፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ምንም እንኳ አንዳንዶች የኔልሰንን ውጤታማነት የሚያደንቁ ቢሆኑም ፍጽምና የመጠበቅ ባሕሪው እንደ ራስ ምታትና ውጥረት የመሳሰሉ አካላዊ ችግሮች አስከትሎበታል። አንተም የኔልሰን ዓይነት ችግር እንዳለብህ ሆኖ ይሰማሃልን?

ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ ወጣቶችንም ጭምር ያጠቃል። በሪዮ ዴ ጄኔሮ የምትኖረው ሪታ ከልጅነት ዕድሜዋ ጀምሮ ትምህርት ትወድ ነበር። ለደረጃ የምትጨነቅ መስላ ለመታየት ባትፈልግም ከፍተኛ ውጤት ካላመጣች በጣም ትበሳጭ ነበር። ሪታ እንዲህ ትላለች:- “ከልጅነቴ ጀምሮ ዘወትር ነገሮችን አከናውን የነበረው ውጥረትና ጥድፊያ በሞላበት መንገድ ሆኖ ሳለ ሰፊ ጊዜ ካላቸው ሰዎች ጋር ራሴን አወዳድር ነበር። ሁልጊዜ መሠራት ያለባቸው ነገሮች ስለማይጠፉ እረፍት ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ እንዳለኝ ሆኖ አይሰማኝም ነበር።”

ማሪያ ልጅ በነበረችበት ጊዜ የሌሎቹን ልጆች ያህል ጥሩ አድርጋ መሣል ሳትችል ስትቀር ታለቅስ ነበር። ከዚህም በላይ በሙዚቃው ዓለም የተዋጣላት የኪነ ጥበብ ሰው ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ታደርግ የነበረ ሲሆን በጨዋታና በዘፈን ችሎታ ከመደሰት ይልቅ ብዙውን ጊዜ በውጥረትና በጭንቀት ትዋጥ ነበር። ቶኒያ የተባለች ሌላ ብራዚላዊት ወጣት ጠንቃቃ ለመሆንና ከፉክክር መንፈስ ለመራቅ ትጥር የነበረ ቢሆንም እንኳ በትምህርት ቤትም ሆነ በቤት ውስጥ ለራሷ ከፍተኛ መስፈርቶች ታወጣ እንደነበር ሳትሸሽግ ተናግራለች። የምታከናውነው ሥራ ፍጹም እስካልሆነ ድረስ ሰዎች ሊወዷት እንደማይችሉ ሆኖ ይሰማት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ቶኒያ አንዳንድ ጊዜ ከሌሎች ብዙ ትጠብቅ የነበረ በመሆኑ ብስጭትና ሃዘን ላይ ትወድቅ ነበር።

ጥሩ ብቃት፣ ትጋትና በራስ የመርካት ስሜት አስፈላጊ ነገሮች ቢሆኑም እንኳ ሊደረስባቸው የማይችሉ ግቦችን ማውጣት አይሳካልኝ ይሆናል የሚለውን ስጋት ጨምሮ ሌሎች አሉታዊ የሆኑ ስሜቶች ሊያስከትል ይችላል። ወላጆች ወይም ሌሎች ሰዎች ልጆች በትምህርት ወይም በስፖርት ሊደርሱባቸው የማይችሏቸውን ፍጹም የሆነ ብቃትን የሚጠይቁ መስፈርቶች ሊያወጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል የሪካርዶ እናት ልጅዋ ሐኪም እንዲሆን እንዲሁም ፒያኖ መጫወትና በርካታ ቋንቋዎች መናገር እንዲችል በመመኘት ከልጅዋ ብዙ ነገር ትጠብቅ ነበር። እንዲህ ዓይነቱ ባሕርይ ከልኩ ሲያልፍ ሊያስከትል የሚችለውን ችግርና ብስጭት መገመት ትችላለህ?

ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ መወገድ ያለበት ለምንድን ነው?

ምንም እንከን የማይወጣለትና ጥራቱን የጠበቀ ሥራ ማከናወን እጅግ ተፈላጊ ነው። በዚህም የተነሳ ሰዎች በሥራው ዓለም ውስጥ ሳይወዱ በግድ ፉክክር ውስጥ ይገባሉ። ሌሎች ደግሞ መተዳደሪያቸውን ላለማጣት ሲሉ ባለ በሌለ ኃይላቸው ይሠራሉ። አንዳንድ ሠራተኞች አዲስ ሪኮርድ ለማስመዝገብ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ከሚከፍል ሯጭ ጋር ይመሳሰላሉ። ከባድ ፉክክር በሚገጥመው ጊዜ ብቃቱን ለማሻሻልና ብሎም ድል ለመቀዳጀት ሲል ከቀድሞው የበለጠ ልምምድ ማድረግ እንዳለበት ሊሰማውና ምናልባትም አበረታች መድኃኒቶችን ለመጠቀም ሊያስብ ይችላል። ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ ሰዎች ጤናማ በሆነ መንገድ የተዋጣላቸው ለመሆን እንዲጣጣሩ ከማድረግ ይልቅ “አይሳካልኝ ይሆናል በሚል ስጋት ተገፋፍተው እንዲሠሩ” ወይም “ከሁሉ ልቆ ለመገኘት በሚያነሳሳ ምኞት እንዲነዱ” ያደርጋቸዋል።​—⁠ዘ ፊሊንግ ጉድ ሃንድቡክ

እርግጥ ነው፣ አንዳንዶች በሥነ ጥበብ ወይም በስፖርት የሚያደርጉት ተሳትፎ ሁልጊዜ ሊሻሻል እንደሚችል ሆኖ ይሰማቸዋል። ሆኖም ዶክተር ሮበርት ኤስ ኤሊየት እንደሚሉት ከሆነ “ፍጽምናን የመጠበቅ ባሕርይ ፈጽሞ ሊሆን የማይችልን ነገር ከመጠባበቅ ተለይቶ የሚታይ አይደለም።” አክለውም “የጥፋተኝነት ስሜት፣ ድክመትን ለመሸፈን የሚደረግ ጥረትና መሣቂያ እሆናለሁ የሚለው ፍርሃት ውጤት ነው” ብለዋል። በእርግጥም ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው:- “የሰውን ድካምና የብልሃት ሥራውን ሁሉ ተመለከትሁ፣ በባልንጀራውም ዘንድ ቅንዓት እንዲያስነሣ አየሁ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።”​—⁠መክብብ 4:​4

ፍጽምና የመጠበቅ ባሕርይ እንዳለብህ ሆኖ ከተሰማህ ምን ልታደርግ ትችላለህ? አንድ ነገር ለማከናወን ከፍተኛ ጥረት ብታደርግም የዚያኑ ያህል ውጤት ሳታገኝ በመቅረትህ ትበሳጫለህ? ከሌሎች ብዙ ነገር የመጠበቅንና ከመጠን በላይ ጥብቅ የመሆንን ባሕርይ ማስወገድ ትፈልጋለህ? ፍጹም መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ፍጽምናን የመጠበቅ ባሕርይ ሳይኖርብህ ችሎታህን ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም አትጓጓም? ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ከአምላክ ያገኙትን ችሎታ ተጠቅመው ሌሎችን የሚጠቅሙ ነገሮችን መፍጠር ከቻሉ የሰው ልጅ ፍጹም በሚሆንበትና በመለኮታዊ አመራር ሥር በሚሆንበት ጊዜ ምን ሊሠራ እንደሚችል አስብ!

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች ወይም ሌሎች ሰዎች ፍጽምና ሊጠብቁ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ ከልጆች አቅም በላይ ነው