በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምሥራቹን በጉጉት አውጁ

ምሥራቹን በጉጉት አውጁ

ምሥራቹን በጉጉት አውጁ

“በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ።”​—⁠ሮሜ 12:​11

1, 2. ክርስቲያኖች የምሥራቹ ሰባኪ እንደመሆናቸው መጠን ምን ዓይነት አመለካከት ለመያዝ ይጥራሉ?

 አንድ ወጣት አዲስ ሥራ በማግኘቱ በጣም ተደስቷል። ሥራ በጀመረበት በመጀመሪያው ዕለት አሠሪው የሚሰጠውን መመሪያ በጉጉት ይጠባበቃል። ምን ሥራ ይሰጠኝ ይሆን እያለ ያስባል፤ ሥራውንም በቁም ነገር ይመለከተዋል። በተቻለው መጠን ጥሩ አድርጎ ለመሥራት ይጓጓል።

2 በተመሳሳይም እኛ ክርስቲያኖች ራሳችንን እንደ ጀማሪ ሠራተኞች አድርገን ልንመለከት እንችላለን። ከፊታችን ለዘላለም የመኖር ተስፋ የተዘረጋልን እንደመሆኑ መጠን ለይሖዋ መሥራት ገና መጀመራችን ነው ሊባል ይችላል። ፈጣሪያችን ወደፊት የዘላለም ሕይወት ስናገኝ የምንሠራቸው በርካታ ሥራዎች እንዳዘጋጀልን የተረጋገጠ ነው። ሆኖም በመጀመሪያ የተሰጠን ተልእኮ የእርሱን መንግሥት ምሥራች ማወጅ ነው። (1 ተሰሎንቄ 2:​4) አምላክ ለሰጠን ለዚህ ሥራ ያለን አመለካከት ምንድን ነው? እንደ ወጣቱ ልጅ ባለን ችሎታ ሁሉ፣ በቅንዓትና በደስታ አዎን፣ በጉጉት ለመሥራት እንፈልጋለን!

3. የምሥራቹ አገልጋይ በመሆን ረገድ ስኬታማ ለመሆን ምን ነገር ይጠይቃል?

3 እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለውን አዎንታዊ አመለካከት ጠብቆ መኖር ቀላል አይደለም። ከአገልግሎታችን በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ኃላፊነቶች ያሉብን ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ አካላዊና ስሜታዊ ኃይላችንን የሚያሟጥጡ ሊሆኑ ይችላሉ። አብዛኛውን ጊዜ አገልግሎታችንን ችላ ሳንል እነዚህን ኃላፊነቶች መወጣት እንችላለን። ሆኖም ይህ የማያቋርጥ ትግል ማድረግ ሊጠይቅብን ይችላል። (ማርቆስ 8:​34) ኢየሱስ የተሳካልን ክርስቲያኖች ለመሆን በብርቱ መጋደል እንዳለብን ጎላ አድርጎ ገልጿል።​—⁠ሉቃስ 13:​24

4. በየዕለቱ የሚያጋጥሙ ጭንቀቶች በመንፈሳዊ አመለካከታችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉት እንዴት ነው?

4 የምንሠራቸው ሥራዎች በጣም ከመብዛታቸው የተነሳ አልፎ አልፎ ጭንቀት ወይም ውጥረት ሊሰማን ይችላል። ‘የኑሮ ሐሳቦች’ ለቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ያለንን ቅንዓትና አድናቆት ሊያቀዘቅዙብን ይችላሉ። (ሉቃስ 21:​34, 35፤ ማርቆስ 4:​18, 19) ፍጽምና የጎደለን እንደመሆናችን መጠን ‘የቀድሞ ፍቅራችንን’ ልንተው እንችላለን። (ራእይ 2:​1-4) ለይሖዋ የምናቀርባቸው አንዳንዶቹ የአገልግሎት ዘርፎች ልማዳዊ ሊሆኑብን ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ለአገልግሎት ያለንን ቅንዓት ጠብቀን ማቆየት እንድንችል ማበረታቻ የሚሰጠን እንዴት ነው?

በልባችን ውስጥ እንዳለ “የሚነድድ እሳት”

5, 6. ሐዋርያው ጳውሎስ የመስበክ መብቱን የተመለከተው እንዴት ነበር?

5 ይሖዋ በአደራ የሰጠን አገልግሎት በጣም ውድ በመሆኑ ፈጽሞ እንደ ተራ ነገር ልንመለከተው አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ ታላቅ መብት እንደሆነ አድርጎ በመቁጠሩ ራሱን ለዚህ መብት ብቁ እንዳልሆነ አድርጎ ተመልክቷል። እንዲህ አለ:- “ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስን ባለ ጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ፣ ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘላለም የተሰወረው የምሥጢር ሥርዓት ምን እንደ ሆነ ለሁሉ እገልጥ ዘንድ ይህ ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ለማንስ ለኔ ተሰጠ።”​—⁠ኤፌሶን 3:​8, 9

6 ጳውሎስ ለአገልግሎቱ የነበረው አዎንታዊ አመለካከት ለእኛ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ወንጌልን ልሰብክ ተዘጋጅቼአለሁ [“እጓጓለሁ፣” NW ]” በማለት ተናግሯል። በምሥራቹ አያፍርም ነበር። (ሮሜ 1:​15, 16) ለአገልግሎቱ ትክክለኛ አመለካከት የነበረው ሲሆን አገልግሎቱንም ለመፈጸም ይጓጓ ነበር።

7. ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለ ምን ነገር አስጠንቅቋቸዋል?

7 ሐዋርያው ጳውሎስ ቅንዓት የተሞላበት አመለካከት መያዝ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘቡ በሮም የነበሩትን ክርስቲያኖች “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ” በማለት አጥብቆ መክሯቸዋል። (ሮሜ 12:​11) “መለገም” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛው ቃል “ዳተኛ፣ ሰነፍ” መሆን የሚል ትርጉም ያዘለ ነው። በአገልግሎታችን የምንለግም ባንሆን እንኳ ሁላችንም በመንፈሳዊ ዳተኞች እየሆንን እንዳለን የሚጠቁሙ ምልክቶችን አስቀድመን ለማወቅና እነዚህ ምልክቶች እንዳሉብን ከታወቀንም በአመለካከታችን ላይ ተገቢውን ማስተካከያ ለማድረግ ንቁ መሆን ይኖርብናል።​—⁠ምሳሌ 22:​3

8. (ሀ) በኤርምያስ ልብ ውስጥ “እንደሚነድድ እሳት” የሆነው ነገር ምንድን ነው? ለምንስ? (ለ) ከኤርምያስ ተሞክሮ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

8 የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲያድርብን የአምላክ መንፈስም ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ነቢዩ ኤርምያስ በአንድ ወቅት የተስፋ መቁረጥ ስሜት አድሮበት ነበር። በዚህም የተነሳ የነቢይነት ሥራውን ማቆም እንዳለበት ተሰማው። እንዲያውም “የእግዚአብሔርን ስም አላነሣም፣ ከእንግዲህ ወዲህም በስሙ አልናገርም” በማለት ተናግሮ ነበር። ኤርምያስ እንዲህ ብሎ መናገሩ ከባድ መንፈሳዊ ድክመት እንደነበረበት የሚያሳይ ነው? በጭራሽ። እንዲያውም ኤርምያስ በመንፈሳዊ የነበረው ጥንካሬ፣ ለይሖዋ የነበረው ፍቅርና ለእውነት የነበረው ቅንዓት ትንቢት መናገሩን እንዲቀጥል ኃይል ሰጥቶታል። “[የይሖዋ ቃል] በአጥንቶቼ ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት ያለ በልቤ ሆነብኝ፤ ደከምሁ፣ መሸከምም አልቻልሁም” በማለት ተናግሯል። (ኤርምያስ 20:​9) ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አልፎ አልፎ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ቢያጋጥማቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ይሁን እንጂ ለእርዳታ ሲጸልዩ ይሖዋ ልባቸውን ያነብና ቃሉ ልክ እንደ ኤርምያስ በልባቸው ውስጥ ካለ ቅዱስ መንፈሱን በነፃ ይሰጣቸዋል።​—⁠ሉቃስ 11:​9-13፤ ሥራ 15:​8

“የመንፈስን እሳት አታጥፉ ”

9. የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እንዳናገኝ እንቅፋት ሊሆንብን የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

9 ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖችን “የመንፈስን እሳት አታጥፉ” በማለት አጥብቆ መክሯቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:​19 NW ) አዎን፣ ከአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚቃረን ድርጊትና አመለካከት የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እንዳናገኝ እንቅፋት ሊፈጥርብን ይችላል። (ኤፌሶን 4:​30) ዛሬ ክርስቲያኖች ምሥራቹን የመስበክ ሥራ ተሰጥቷቸዋል። ይህን መብት በታላቅ አክብሮት እንይዘዋለን። አምላክን የማያውቁ ሰዎች የምናከናውነውን የስብከት ሥራ ቢያጣጥሉ ምንም አያስደንቀንም። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ሆን ብሎ አገልግሎቱን ችላ ሲል ቀስቃሽ የሆነው የአምላክ መንፈስ እሳት እንዲያጠፋ ሊያደርግ ይችላል።

10. (ሀ) ባልንጀራችን ያለው አመለካከት በእኛ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) በ⁠2 ቆሮንቶስ 2:​17 ላይ ስለ አገልግሎታችን ምን ከፍ ያለ አመለካከት ተገልጿል?

10 ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ያሉ አንዳንድ ሰዎች አገልግሎታችን ጽሑፍ ማሰራጨት ብቻ እንደሆነ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ ከቤት ወደ ቤት የምንሄደው የመዋጮ ገንዘብ ለመሰብሰብ እንደሆነ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ሊደመድሙ ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉት አሉታዊ አስተያየቶች በአመለካከታችን ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ከፈቀድንላቸው በአገልግሎት ያለን ውጤታማነት እንዲቀንስ ሊያደርጉብን ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉት አስተሳሰቦች በእኛ ላይ ተጽእኖ እንዲያሳድሩ ከመፍቀድ ይልቅ ይሖዋና ኢየሱስ ለአገልግሎታችን ያላቸውን አመለካከት ይዘን ለመመላለስ ጥረት እናድርግ። ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን” ብሎ ሲናገር ይህንን ከፍ ያለ አመለካከት መግለጹ ነበር።​—⁠2 ቆሮንቶስ 2:​17

11. የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በስደት ጊዜ እንኳን ሳይቀር ቀናተኞች ሆነው እንዲቀጥሉ ያስቻላቸው ምንድን ነው? ምሳሌነታቸው እንዴት ሊነካን ይገባል?

11 ኢየሱስ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኢየሩሳሌም በነበሩ ደቀ መዛሙርቱ ላይ ስደት ደረሰ። መስበካቸውን እንዲያቆሙ ትእዛዝና ዛቻ ደረሳቸው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፣ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ” በማለት ይናገራል። (ሥራ 4:​17, 21, 31) ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖች ሊኖራቸው የሚገባውን አዎንታዊ አመለካከት ገልጿል። ጳውሎስ እንዲህ አለ:- “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፣ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል።”​—⁠2 ጢሞቴዎስ 1:​7, 8

ለጎረቤታችን ያለብን ዕዳ ምንድን ነው?

12. ምሥራቹን የምንሰብክበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?

12 ለአገልግሎታችን ተገቢ የሆነ አመለካከት መያዝ ከፈለግን ትክክለኛ የውስጥ ግፊት ሊኖረን ይገባል። የምንሰብከው ለምንድን ነው? የምንሰብክበት ዋነኛ ምክንያት መዝሙራዊው በተናገራቸው ቃላት ተገልጿል:- “ቅዱሳንህም ይባርኩሃል። የመንግሥትህን ክብር ይናገራሉ፣ ኃይልህንም ይነጋገራሉ፣ ለሰው ልጆች ኃይልህን የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቁ ዘንድ።” (መዝሙር 145:​10-12) አዎን፣ የምንሰብከው ይሖዋን በሕዝብ ፊት ለማወደስና በሁሉም ሰው ፊት ስሙን ለመቀደስ ነው። የሚያዳምጡን ሰዎች ጥቂት በሚሆኑበት ጊዜ እንኳ የመዳንን መልእክት በታማኝነት ማወጃችን ለይሖዋ ክብር ያመጣለታል።

13. ለሌሎች የመዳንን ተስፋ እንድንነግር የሚገፋፋን ምንድን ነው?

13 በተጨማሪም ለሰዎች ባለን ፍቅርና ከደም ባለ ዕዳነት ለመራቅ ስንል እንሰብካለን። (ሕዝቅኤል 33:​8፤ ማርቆስ 6:​34) ጳውሎስ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ስላሉ ሰዎች በተናገረው ቃል ውስጥ ከዚህ ጋር የሚዛመድ ሐሳብ ሰንዝሯል:- “ለግሪክ ሰዎችና ላልተማሩም፣ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ዕዳ አለብኝ።” (ሮሜ 1:​14) የአምላክ ፈቃድ ‘ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ’ ስለሆነ ጳውሎስ ምሥራቹን ለሰዎች የማወጅ ዕዳ እንዳለበት ሆኖ ተሰምቶታል። (1 ጢሞቴዎስ 2:​4) ዛሬም ቢሆን ለጎረቤታችን ተመሳሳይ የሆነ ፍቅር ያለን ከመሆኑም በላይ ለእነርሱ ግዴታ አለብን። ይሖዋ ለሰው ዘር ያለው ፍቅር ለእነርሱ እንዲሞት ልጁን ወደ ምድር እንዲልክ ገፋፍቶታል። (ዮሐንስ 3:​16) ይህ ትልቅ መሥዋዕት ነው። እኛም ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ተጠቅመን በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ የተመሠረተውን የመዳንን ምሥራች ለሌሎች በመናገር የይሖዋን ፍቅር መኮረጃችንን እናሳያለን።

14. መጽሐፍ ቅዱስ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ያለውን ዓለም የሚገልጸው እንዴት ነው?

14 የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች ሰዎችን የክርስቲያን ወንድማማች ማኅበር አባላት ሊሆኑ እንደሚችሉ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ምሥራቹን በድፍረት መስበክ ያለብን ቢሆንም ከሰዎች ጋር ጠብ እንገጥማለን ማለት አይደለም። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በጥቅሉ ዓለምን በተመለከተ ሲናገር ጠንከር ያሉ ቃላት ይጠቀማል። ጳውሎስ “የዚህ ዓለም ጥበብ” እና ‘ዓለማዊ ምኞት’ ብሎ ሲናገር “ዓለም” የሚለውን ቃል የተጠቀመው አሉታዊ በሆነ መንገድ ነው። (1 ቆሮንቶስ 3:​19፤ ቲቶ 2:​12) በተጨማሪም ጳውሎስ የኤፌሶን ክርስቲያኖች “በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ” ይመላለሱ በነበረበት ወቅት በመንፈሳዊ “ሙታን” እንደነበሩ አስታውሷቸዋል። (ኤፌሶን 2:​1-3) እነዚህ አነጋገሮችና ከእነዚህ ጋር የሚመሳሰሉ ሌሎች መግለጫዎች ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምም በሞላው በክፉው [ተይዟል]” ብሎ ከተናገረው ሐሳብ ጋር የሚስማሙ ናቸው።​—⁠1 ዮሐንስ 5:​19

15. ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ያሉ ግለሰቦችን በተመለከተ ማድረግ የሌለብን ምንድን ነው? ለምንስ?

15 ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉት አነጋገሮች ከአምላክ ርቆ የሚገኘውን ጠቅላላውን ዓለም በጥቅሉ ለማመልከት እንጂ እያንዳንዱን ግለሰብ በተናጠል ለማመልከት ተብሎ የተነገሩ እንዳልሆኑ ማስታወስ ይገባል። ክርስቲያኖች ማንኛውም ግለሰብ ለስብከቱ ሥራ ስለሚሰጠው ምላሽ አስቀድመው በጭፍን ግምታዊ ሐሳብ አይሰጡም። አንድን ሰው ፍየል እንደሆነ አድርጎ ለመናገር የሚያስችል ምንም ዓይነት መሠረት የላቸውም። ኢየሱስ ‘በጎችን ከፍየሎች’ ለመለየት በሚመጣበት ጊዜ የግለሰቡ ዕጣ ምን እንደሚሆን የመናገር መብት አልተሰጠንም። (ማቴዎስ 25:​31-46) የተሾመው ፈራጅ ኢየሱስ እንጂ እኛ አይደለንም። ከዚህም በላይ በጣም አስጸያፊ በሚባል አኗኗር ይመላለሱ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንኳን ሳይቀሩ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ተቀብለውና ተለውጠው በመጨረሻ ንጹሕ አኗኗር ያላቸው ክርስቲያኖች መሆን እንደቻሉ የሚያሳዩ ተሞክሮዎች አሉ። እንደዚህ ከመሰሉ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት የምንዳዳ ባንሆንም እንኳ አጋጣሚ በፈቀደልን መጠን የመንግሥቱን ተስፋዎች ለእነርሱ ከመናገር ወደኋላ አንልም። ቅዱሳን ጽሑፎች ገና አማኝ ከመሆናቸው በፊት “ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ” ስለነበራቸው አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች ውሎ አድሮ አማኞች ሆነዋል። (ሥራ 13:​48 NW ) ምሥክርነቱን እስካልሰጠን ምናልባትም ደጋግመን እስካላነጋገርን ድረስ ትክክለኛ ዝንባሌ ያለውን ሰው ለይተን ማወቅ አንችልም። ይህንን በአእምሯችን በመያዝ ከመካከላቸው አንዳንዶቹ የሕይወትን መልእክት ሊቀበሉ እንደሚችሉ ተስፋ በማድረግ የመዳንን መልእክት ገና ያልተቀበሉ ሰዎችን “በየዋህነት” እና “በጥልቅ አክብሮት” እንይዛቸዋለን።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 2:​25፤ 1 ጴጥሮስ 3:​15 NW

16. ‘የማስተማር ጥበብን’ ማዳበር የምንፈልግበት አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?

16 የማስተማር ችሎታችንን ማዳበራችን ምሥራቹን በከፍተኛ ጉጉት እንድንሰብክ ያደርገናል። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- አንድ ጨዋታ ወይም ስፖርት ምንም ያህል አስደሳች ቢሆን ጨዋታውን ለማያውቅ ሰው አስደሳች ላይሆን ይችላል። ጥሩ አድርጎ መጫወት ለሚችል ሰው ግን በጣም አስደሳች ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይም “የማስተማር ጥበብ” ያዳበሩ ክርስቲያኖች በአገልግሎት የሚያገኙት ደስታ ይጨምራል። (2 ጢሞቴዎስ 4:​2፤ ቲቶ 1:​9 NW ) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ” ሲል መክሮታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:​15) የማስተማር ችሎታችንን ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

17. ለመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ‘ጉጉት ማዳበር’ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ያለው እውቀት ለአገልግሎታችን ጠቃሚ የሚሆነው እንዴት ነው?

17 አንደኛው መንገድ ተጨማሪ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ላልተበረዘው የቃል ወተት ጉጉት አዳብሩ” በማለት ይመክረናል። (1 ጴጥሮስ 2:​2 NW ) ጤነኛ የሆነ አንድ ሕፃን በተፈጥሮው ወተት ለማግኘት ይጓጓል። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ለመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ‘ጉጉት ማዳበር’ ሊያስፈልገው ይችላል። ይህንንም ጥሩ የጥናትና የንባብ ልማድ በማዳበር ሊያደርግ ይችላል። (ምሳሌ 2:​1-6) የተዋጣልን የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ለመሆን ከፈለግን ጥረት ማድረግና ራሳችንን መገሰጽ ይኖርብናል። ሆኖም የምናደርገው ጥረት መልሶ ይክሰናል። የአምላክን ቃል በመመርመራችን የምናገኘው ደስታ በአምላክ መንፈስ እንድንቃጠልና የተማርናቸውን ነገሮች ለሌሎች ለማካፈል እንድንጓጓ ያደርገናል።

18. ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የእውነትን ቃል በትክክል እንድንጠቀም ሊያስታጥቁን የሚችሉት እንዴት ነው?

18 ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም የአምላክን ቃል ጥሩ አድርገን እንድንጠቀምበት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክቱልናል። የሕዝብ ስብሰባዎች በሚካሄዱበትና ሌሎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይቶች በሚደረጉበት ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሲነበቡ የራሳችንን መጽሐፍ ቅዱስ አውጥተን መከታተል ይኖርብናል። ስለ ስብከት ሥራችን በቀጥታ የሚናገሩ ክፍሎችን ጨምሮ በስብሰባ ላይ የሚቀርቡ ክፍሎችን ትኩረት ሰጥተን መከታተላችን ጥበብ ነው። ምናልባት ሐሳባችን ወደ ሌላ እንዲሄድ በመፍቀድ ሠርቶ ማሳያዎች የሚሰጡትን ጥቅም ፈጽሞ አቅልለን አንመልከት። በዚህ ጊዜም ቢሆን ራስን መገሠጽና በትኩረት መከታተል አስፈላጊ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:​16) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እምነታችንን ይገነቡልናል፣ ለአምላክ ቃል ጉጉት እንድናዳብር ይረዱናል እንዲሁም ምሥራቹን በጉጉት እንድናውጅ ያሠለጥኑናል።

ይሖዋ በሚሰጠው ድጋፍ መታመን እንችላለን

19. በስብከቱ ሥራ አዘውትሮ መካፈል ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

19 ‘በመንፈስ የሚቃጠሉ’ እና ምሥራቹን ለማወጅ የሚጓጉ ክርስቲያኖች በአገልግሎት አዘውትረው ለመካፈል ይጣጣራሉ። (ኤፌሶን 5:​15, 16) እርግጥ ነው፣ ሁላችንም ያለንበት ሁኔታ የሚለያይ በመሆኑ በዚህ ሕይወት አድን በሆነ ሥራ ላይ ሁላችንም እኩል ሰዓት ማሳለፍ አንችልም። (ገላትያ 6:​4, 5) ሆኖም በስብከቱ ሥራ ላይ ከምናውለው አጠቃላይ ሰዓት ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ተስፋችንን ደጋግመን ለሌሎች ሰዎች መናገሩ ሊሆን ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 4:​1, 2) በስብከቱ ሥራ ይበልጥ በተካፈልን መጠን የሥራውን አስፈላጊነት የዚያኑ ያህል እያደነቅን እንሄዳለን። (ሮሜ 10:​14, 15) የሚያዝኑና የሚተክዙ እንዲሁም ተስፋ የቆረጡ ልበ ቅን ሰዎችን ደጋግመን ስናነጋግር የርኅራኄ ስሜታችንና የሌላውን ችግር እንደ ራስ ችግር አድርጎ የመመልከት ባሕርያችን ያድጋል።​—⁠ሕዝቅኤል 9:​4፤ ሮሜ 8:​22

20, 21. (ሀ) አሁንም ልንሠራው የሚገባ ምን ሥራ አለ? (ለ) ይሖዋ ጥረታችንን የሚባርክልን እንዴት ነው?

20 ይሖዋ ምሥራቹን በአደራ ሰጥቶናል። ይህ የእርሱ “የሥራ ባልደረቦች [NW ]” በመሆን የተቀበልነው የመጀመሪያው ተልእኮ ነው። (1 ቆሮንቶስ 3:​6-9) ይህን አምላክ የሰጠንን ኃላፊነት በሙሉ ነፍሳችንና አቅማችን በፈቀደልን መጠን ለመፈጸም እንጓጓለን። (ማርቆስ 12:​30፤ ሮሜ 12:​1) በዓለም ዙሪያ ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው እውነትን የተራቡ በርካታ ሰዎች አሁንም አሉ። የሚሠራ በርካታ ሥራ አለ። ይሁን እንጂ አገልግሎታችንን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ጥረት ስናደርግ ይሖዋ በሚሰጠው ድጋፍ ላይ መታመን እንችላለን።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 4:​5

21 ይሖዋ መንፈሱን ይሰጠናል እንዲሁም ‘የመንፈስ ሰይፍ’ በሆነው በቃሉ ያስታጥቀናል። እርሱ በሚሰጠን እርዳታ ‘የመናገር ነፃነት ተሰምቶን የምሥራቹን ምሥጢር ለማሳወቅ’ አፋችንን መክፈት እንችላለን። (ኤፌሶን 6:​17-20) ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች “ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣም” በማለት የጻፈው መልእክት በእኛም ላይ እንዲሠራ እንመኛለን። (1 ተሰሎንቄ 1:​5) አዎን፣ ምሥራቹን በጉጉት እናውጅ!

አጭር ክለሳ

• የኑሮ ጭንቀቶች ለአገልግሎቱ በሚኖረን ቅንዓት ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ?

• ምሥራቹን ለመስበክ ያለን ፍላጎት በልባችን ውስጥ “እንደሚነድድ እሳት” ሊሆን የሚችለው በምን መንገድ ነው?

• ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ የትኛውን አሉታዊ አመለካከት ማስወገድ ይኖርብናል?

• እምነታችንን የማይጋሩ ሰዎችን በጥቅሉ እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?

• ለስብከቱ ሥራ ያለንን ቅንዓት መጠበቅ እንድንችል ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች ጳውሎስና ኤርምያስ ያሳዩትን ቅንዓት ይኮርጃሉ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአምላክና ለጎረቤት ያለን ፍቅር በከፍተኛ ጉጉት እንድናገለግል ያነሳሳናል