በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያን እረኞች ‘ልባችሁን አስፉ’!

ክርስቲያን እረኞች ‘ልባችሁን አስፉ’!

ክርስቲያን እረኞች ‘ልባችሁን አስፉ’!

“እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፣ የሚያሳጣኝም የለም።” ዳዊት እንዲህ በማለት በአምላኩ ላይ ፍጹም ትምክህት እንዳለው ገልጿል። ይሖዋ “በጽድቅ መንገድ” በመምራት በመንፈሳዊ አነጋገር ወደ “ለመለመ መስክ” እና ወደ “ዕረፍት ውኃ ዘንድ” ወስዶታል። ዳዊት በተቃዋሚዎች ተከብቦ በነበረበት ጊዜ ድጋፍና ማበረታቻ በማግኘቱ ይሖዋን “አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም” ብሎ ለመናገር ተገፋፍቷል። ዳዊት እንዲህ የመሰለ ታላቅ እረኛ በማግኘቱ “በእግዚአብሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ” በማለት ቁርጥ አቋም ይዟል።​—⁠መዝሙር 23:​1-6

በተጨማሪም የአምላክ አንድያ ልጅ የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤ የቀመሰ ሲሆን በምድር ላይ በኖረበት ጊዜም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረው ግንኙነት ይህን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። በዚህም የተነሳ ቅዱሳን ጽሑፎች “መልካም እረኛ፣” “ትልቅ እረኛ” እና ‘የእረኞች አለቃ’ በማለት ይገልጹታል።​—⁠ዮሐንስ 10:​11፤ ዕብራውያን 13:​20፤ 1 ጴጥሮስ 5:​2-4

ይሖዋ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ለእነሱ ፍቅር ላላቸው ሰዎች እንደ እረኛ ሆነው መጠበቃቸውን አላቆሙም። እነሱ የሚያከናውኑት የእረኝነት ሥራ በተወሰነ መጠን በጉባኤ ውስጥ ባሉት የበታች እረኞች ፍቅራዊ ዝግጅት ውስጥ ተገልጿል። ጳውሎስ እንደነዚህ ላሉት የበታች እረኞች ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት [“የበላይ ተመልካቾች፣” NW ] አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።”​—⁠ሥራ 20:​28

ይሖዋ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ከተዉልን አርአያ ጋር በሚጣጣም መንገድ ለመንጋው እረኝነት ማድረግ ቀላል ኃላፊነት አይደለም። ሆኖም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን እጅግ አስፈላጊ ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የተጠመቁትን ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮችን አስብ! እነዚህ አዳዲስ ሰዎች ለዓመታት በማገልገል የሚገኘው መንፈሳዊ ተሞክሮ የላቸውም። በተጨማሪም ገና ልጆች ስለሆኑት ወይም በአሥራዎቹ ዕድሜ ስለሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች አስብ። ከወላጆቻቸው ብቻ ሳይሆን በጉባኤ ካሉት የበታች እረኞችም ትኩረት ማግኘት ይሻሉ።

እርግጥ ነው፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን የእኩዮችን ተጽእኖ ጨምሮ ከውጭ ለሚሰነዘሩ ተጽእኖዎች የተጋለጠ ነው። ከልክ በላይ ለራስ ምኞት የማደርን የዓለም ጎዳና እንዲከተሉ የሚደርስባቸውን ጠንካራ ግፊት ለመቋቋም ሁሉም መታገል አለባቸው። በአንዳንድ አገሮች የመንግሥቱ አስፋፊዎች ለሚያዳርሱት መልእክት የሚያገኙት ምላሽ አነስተኛ በመሆኑ የተነሳ ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። በርካታ አስፋፊዎች ከባድ የጤና እክሎች አሉባቸው። ሌሎች ደግሞ ያለባቸው ገንዘብ ነክ ችግር መንግሥቱን ለማስቀደም ያላቸውን ውስጣዊ ግፊት ሊያሟጥጥባቸው ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ በእውነት ውስጥ ለረዥም ጊዜ የቆዩትን ጨምሮ ሁላችንም አፍቃሪ የሆኑ እረኞች የሚሰጡት እርዳታ ያስፈልገናል፤ እንዲሁም ማግኘት አለብን።

ትክክለኛ የውስጥ ግፊት

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ‘ልባችሁን አስፉ’ ተብለው ተመክረው ነበር! (2 ቆሮንቶስ 6:​11-13) ክርስቲያን ሽማግሌዎች የእረኝነት ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ይህን ምክር መከተላቸው አስፈላጊ ነው። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? እንዲሁም ከመካከላቸው ብዙዎቹ እረኛ የመሆን ተስፋ ያላቸው የጉባኤ አገልጋዮችስ ምን ማድረግ ይችላሉ?

ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለመንጋው በረከት ሆነው መገኘት ከፈለጉ ከግዴታ ስሜት የበለጠ ነገር ለሥራ ሊያነሳሳቸው ይገባል። እንዲህ ተብለው ተመክረዋል:- “በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፣ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት።” (1 ጴጥሮስ 5:​2፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ስለዚህ ውጤታማ እረኝነት ሌሎችን ለማገልገል በውዴታና በበጎ ፈቃደኝነት መነሳሳትን ያካትታል። (ዮሐንስ 21:​15-17) ይህም በጎቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማወቅና ምላሽ ለመስጠት ፈጣን መሆን ማለት ነው። ሌሎችን በሚይዙበት ጊዜ የአምላክ መንፈስ ፍሬዎች ተብለው የሚታወቁትን መልካም ክርስቲያናዊ ባሕርያት ማሳየት ማለት ነው።​—⁠ገላትያ 5:​22, 23

አንዳንድ ጊዜ እረኝነት ወንድሞችን ቤታቸው ሄዶ መጠየቅን ያካትታል። a ይሁን እንጂ ‘ልባቸውን የሚያሰፉ’ እረኞች ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ያቀርባሉ። ይህም፣ አልፎ አልፎ የእረኝነት ጉብኝት ከማድረግ የበለጠ ነገር ያከናውናሉ ማለት ነው። ማንኛውንም አጋጣሚ በመጠቀም በመንጋው ላሉት ለሌሎችም እረኝነት ያደርጋሉ።

እረኞች እንዲሆኑ ሌሎችን ማሠልጠን

በየትኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኝ ማንኛውም ወንድም “ኤጲስ ቆጶስነትን [“የበላይ ተመልካችነትን፣” NW ] ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል።” (1 ጢሞቴዎስ 3:​1) በርካታ የጉባኤ አገልጋዮች ተጨማሪ መብቶች ላይ ለመድረስ ያላቸውን ፈቃደኝነት አሳይተዋል። በመሆኑም ሽማግሌዎች እነዚህ ፈቃደኝነት ያሳዩ ወንድሞች ‘ለበላይ ተመልካችነት በሚያደርጉት መጣጣር’ ለዚህ ትልቅ መብት እንዲበቁ በደስታ ይረዷቸዋል። ይህም ውጤታማ እረኞች እንዲሆኑ ያሰለጥኗቸዋል ማለት ነው።

የአምላክን ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች በጥብቅ በመከተላቸው የይሖዋ ክርስቲያን ጉባኤ በ⁠ሕዝቅኤል 34:​2-6 ላይ እንደተገለጸው ባሉት ሐሰተኛ እረኞች ተጽእኖ አልተዳከመም። እነዚህ በይሖዋ ዓይን የተናቁ ናቸው፤ ደግሞም መናቅ ይገባቸዋል። መንጋውን ከመመገብ ይልቅ ራሳቸውን መግበዋል። የደከመውን አላጸኑም፣ የታመመውን አላከሙም፣ የተሰበረውን አልጠገኑም እንዲሁም የባዘነውን ወይም የጠፋውን አልመለሱም። እንደ እረኞች ሳይሆን በአመዛኙ እንደ ተኩላዎች በመሆን በጎቹን ጨቁነዋል። ችላ የተባሉት በጎች የሚንከባከባቸው አጥተው ያለ ዓላማ በመቅበዝበዝ ተበታትነው ነበር።​—⁠ኤርምያስ 23:​1, 2፤ ናሆም 3:​18፤ ማቴዎስ 9:​36

ከእነዚህ ታማኝ ያልሆኑ እረኞች በተለየ መልኩ ክርስቲያን እረኞች የይሖዋን ምሳሌ ይከተላሉ። በጎቹን በመንፈሳዊ ወደ “ለመለመ መስክ” እና ወደ “እረፍት ውኃ ዘንድ” ለመምራት እርዳታ ያበረክታሉ። በጎቹ የይሖዋን ቃል በሚገባ እንዲረዱና በግል ሕይወታቸው በሥራ እንዲያውሉት በመርዳት “በጽድቅ መንገድ” ለመምራት ይጥራሉ። ‘የማስተማር ብቃቱ’ ስላላቸው ይህን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማከናወን ይችላሉ።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 3:​2

ሽማግሌዎች የማስተማር ሥራቸውን በአብዛኛው የሚያከናውኑት በጉባኤ ስብሰባዎች ወቅት ከመድረክ በሚሰጡት ትምህርት ነው። ይሁን እንጂ ሽማግሌዎች በግለሰብ ደረጃም ያስተምራሉ። እርግጥ ነው፣ አንዳንዶች በነፍስ ወከፍ በማስተማር ረገድ የተሻለ ችሎታ ያላቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ ንግግር በመስጠት ረገድ የበለጠ ተሰጥኦ አላቸው። ሆኖም አንድ ሰው በአንዱ ዓይነት የማስተማር ዘርፍ ያለው ችሎታ አነስተኛ መሆኑ የግድ አስተማሪ የመሆን ብቃቱን እንዲያጣ አያደርገውም። ሽማግሌዎች እረኝነትን ጨምሮ ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ያስተምራሉ። አንዳንድ የእረኝነት ጉብኝት መደበኛ በሆነ መንገድ ለምሳሌ ያህል በፕሮግራም በሚደረግ ጥየቃ ሊከናወን ይችላል። ይሁን እንጂ ይበልጥ መደበኛ ባልሆነ መንገድም ሰፊ እረኝነት ሊደረግ ይችላል። ይህም ቢሆን ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል።

ሁልጊዜ እረኞችና አስተማሪዎች ናቸው

አንድ ሐኪም ሥራውን ማከናወን እንዲችል እውቀትና ልምድ ማካበት ያስፈልገዋል። ይሁን እንጂ ደግነት፣ ርኅራሄ፣ አሳቢነትና ልባዊ ትኩረት ሲያሳይ ታካሚዎቹ ለሥራው አድናቆት ይኖራቸዋል። እነዚህ ባሕርያት የስብዕናው ክፍል ሊሆኑ ይገባል። በተመሳሳይ እንደዚህ ዓይነቶቹ ባሕርያት የአንድ ጥሩ አስተማሪና እረኛ ስብዕና ክፍል ማለትም በየዕለቱ የሚያሳየው የማንነቱ ክፍል ሊሆኑ ይገባል። አንድ እውነተኛ አስተማሪ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ በአጠገቡ ያሉትን ሰዎች ለማስተማር የተዘጋጀ ይሆናል። ምሳሌ 15:​23 [NW ] “በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ ቃል ምንኛ መልካም ነው!” ይላል። ‘ትክክለኛው ጊዜ’ መድረክ ላይ ሆኖ ንግግር ሲሰጥ፣ ከቤት ወደ ቤት ሲሰብክ አሊያም መንግሥት አዳራሽ ውስጥ ወይም በስልክ ከሌሎች ጋር ሲነጋገር ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይም አንድ ጥሩ እረኛ የእረኝነት ጉብኝት በሚያደርግበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ አሳቢነት የሚንጸባረቅባቸውን መልካም ባሕርያት ለማሳየት ይጥራል። ‘ልቡን አስፍቶ’ በትክክለኛው ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ በመስጠት ለበጎቹ እረኝነት ለማድረግ የሚያስችለውን እያንዳንዱን አጋጣሚ ይጠቀማል። እንዲህ ማድረጉ በበጎቹ ዘንድ ተወዳጅ ያደርገዋል።​—⁠ማርቆስ 10:​43

በአሁኑ ጊዜ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ቮልፍጋንግ አንድ የጉባኤ አገልጋይና ባለቤቱ ለቤተሰቡ ያደረጉለትን ማኅበራዊ ጥየቃ ያስታውሳል። እንዲህ ይላል:- “ልጆቻችን ትኩረት በማግኘታቸውና አስደሳች ጊዜ በማሳለፋችን በጣም ተደስተው ነበር። እስካሁን ድረስ እያስታወሱ ያወራሉ።” አዎን፣ ይህ የጉባኤ አገልጋይ ለእነሱ ያለውን አሳቢነት አሳይቷል፤ ‘ልቡን አስፍቶ’ ነበር።

‘አንድ ሰው ልቡን ማስፋት’ የሚችልበት ሌላው አጋጣሚ የታመሙትን በመጠየቅ፣ አጠር ያለ የማበረታቻ ቃል ጽፎ በመላክ ወይም ስልክ ደውሎ በማነጋገር ነው። እንደምታስቡላቸው እንዲያውቁ የሚያደርግ ማንኛውም ድርጊት ሊሆን ይችላል! አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እርዳታ ስጡ። መናገር ሲፈልጉ በጥሞና አዳምጧቸው። በጉባኤያችሁም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ስለተደረጉ ገንቢና አስደሳች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ተናገሩ። ይሖዋን ለሚወድዱ ሰዎች በተዘጋጀው ታላቅ የወደፊት ተስፋ ላይ እንዲያተኩሩ እርዷቸው።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:​16-18

ከእረኝነት ጉብኝት በተጨማሪ

እረኝነት የሚደረግበትን ዓላማ ካስታወስን፣ ወንድሞች ቤት ሄዶ መደበኛ የሆነ እረኝነት ማድረጉ አስፈላጊ ቢሆንም እንኳ ይህ እረኝነት ከሚጠይቃቸው ተግባሮች መካከል አንዱ ክፍል ብቻ መሆኑ ግልጽ ነው። አንድ አፍቃሪ እረኛ በማንኛውም ሁኔታ ወይም በማንኛውም ጊዜ በቀላሉ የሚቀረብ በመሆን ‘ልቡን ያሰፋል።’ ከወንድሞቹ ጋር ያዳበረው ሞቅ ያለ ዝምድና አፍቃሪ የሆነው ወንድማቸው ማለትም ክርስቲያን እረኛው በክፉ ጊዜ እንደሚደርስላቸው ስለሚያስገነዝባቸው የሚያስፈራቸው ነገር አይኖርም።​—⁠መዝሙር 23:​4

አዎን፣ ክርስቲያን እረኞች የሆናችሁ ሁሉ ‘ልባችሁን አስፉ።’ ለወንድሞቻችሁ ልባዊ ፍቅር አሳዩአቸው፤ አበረታቷቸው፣ አነቃቋቸው፣ በሚቻላችሁ መንገድ ሁሉ በመንፈሳዊ ገንቧቸው። በእምነት ጸንተው እንዲቆሙ እርዷቸው። (ቆላስይስ 1:​23) በጎቹ ‘ልባቸውን የሚያሰፉ’ ክርስቲያን እረኞች በማግኘታቸው ምንም የሚጎድላቸው ነገር አይኖርም። እንደ ዳዊት እነሱም በይሖዋ ቤት ለዘላለም ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ያደርጋሉ። (መዝሙር 23:​1, 6) አንድ አፍቃሪ እረኛ ከዚህ የተሻለ ምን ነገር ሊመኝ ይችላል?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የእረኝነት ጉብኝት ስለማድረግ የሚረዱ ሐሳቦችን ከመስከረም 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 20-3 እና ከመጋቢት 15, 1996 ገጽ 24-7 ላይ ማግኘት ይቻላል።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ክርስቲያን እረኞች

• በውዴታና በበጎ ፈቃድ አገልግሉ

• መንጋውን መግቡ እንዲሁም ተንከባከቡ

• ሌሎች እረኞች ለመሆን ብቃቱን እንዲያሟሉ እርዷቸው

• የታመሙትን ጠይቁ፣ እንክብካቤም አድርጉላቸው

• በማንኛውም ጊዜ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ንቁ ናቸው

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመስክ አገልግሎትም ሆነ በስብሰባዎች ወይም በማኅበራዊ ግንኙነቶች ወቅት ሽማግሌዎች ምንጊዜም እረኞች ናቸው