በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመንግሥቱን የእውነት ዘሮች መዝራት

የመንግሥቱን የእውነት ዘሮች መዝራት

የመንግሥቱን የእውነት ዘሮች መዝራት

“በማለዳ ዘርህን ዝራ፣ በማታም እጅህን አትተው።”​—⁠መክብብ 11:​6

1. በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች ዘር እየዘሩ ያሉት በምን ሁኔታ ነው?

 ግብርና በጥንቱ የዕብራውያን ኅብረተሰብ ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። ሰብዓዊ ሕይወቱን ሙሉ በተስፋይቱ ምድር ያሳለፈው ኢየሱስ ምሳሌዎቹን ከግብርና ሥራዎች ጋር አያይዞ የተናገረው በዚህ የተነሳ ነው። ለምሳሌ ያህል የአምላክን መንግሥት ምሥራች ስብከት ዘር ከመዝራት ጋር አመሳስሎታል። (ማቴዎስ 13:​1-9, 18-23፤ ሉቃስ 8:​5-15) የምንኖረው በግብርና በሚተዳደር ኅብረተሰብ ውስጥ ሆነም አልሆነ እስከ ዘመናችን ክርስቲያኖች ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች ሁሉ የላቀው ሥራ መንፈሳዊውን ዘር የመዝራቱ ሥራ ነው።

2. የስብከት ሥራችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ይህን ሥራ ለማከናወን ምን እየተደረገ ነው?

2 በዚህ የፍጻሜ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በመዝራቱ ሥራ መካፈል ታላቅ መብት ነው። ሮሜ 10:​14, 15 “ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ?” በማለት የዚህን ሥራ አስፈላጊነት ጥሩ አድርጎ ገልጿል። አዎንታዊ አመለካከት በመያዝ ይህን አምላክ የሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም ወደፊት መግፋት የአሁኑን ያክል አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ የለም። በዚህም የተነሳ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን በ340 ቋንቋዎች በማተሙና በማሰራጨቱ ተግባር ላይ ሙሉ በሙሉ ተጠምደዋል። እነዚህን ጽሑፎች ለማዘጋጀት በዋናው መሥሪያ ቤትና በተለያዩ አገሮች በሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ከ18, 000 የሚበልጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች አስፈልገዋል። እንዲሁም እነዚህን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በዓለም ዙሪያ በማሠራጨቱ ተግባር ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጉ ምሥክሮች ይካፈላሉ።

3. በሚዘራው የመንግሥቱ የእውነት ዘር አማካኝነት ምን በመከናወን ላይ ይገኛል?

3 ይህ ትጋት የተሞላበት ሥራ ምን ፍሬ አስገኝቷል? በክርስትና የመጀመሪያ ዓመታት እንደታየው ሁሉ ዛሬም በርካታ ሰዎች እውነትን እየተቀበሉ ናቸው። (ሥራ 2:​41, 46, 47) ይሁን እንጂ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ከመጠመቃቸውም ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይህ ታላቅ ምሥክርነት ለይሖዋ ስም ቅድስና እና እውነተኛው አምላክ እርሱ ብቻ መሆኑ እንዲረጋገጥ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑ ነው። (ማቴዎስ 6:​9) በተጨማሪም ከአምላክ ቃል የሚገኘው እውቀት የብዙ ሰዎችን ሕይወት እያሻሻለ ከመሆኑም በላይ ወደ መዳን ሊመራቸው ይችላል።​—⁠ሥራ 13:​47

4. ሐዋርያት ይሰብኩላቸው ለነበሩት ሰዎች ምን ያህል ያስቡ ነበር?

4 ሐዋርያት ምሥራቹ ሕይወት ሰጭ መሆኑን በሚገባ ተገንዝበው ስለነበር ይሰብኩላቸው ለነበሩት ሰዎች የጠለቀ ስሜት ነበራቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ ከጻፈው ቃላት ይህንን መገንዘብ ይቻላል:- “እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፣ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።” (1 ተሰሎንቄ 2:​8) እንዲህ ያለውን ልባዊ አሳቢነት ለሰዎች በማሳየት ጳውሎስና ሌሎች ሐዋርያት በዚህ ሕይወት አድን በሆነው ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ የሚካፈሉትን የኢየሱስንና የሰማያዊ መላእክትን ምሳሌ ኮርጀዋል። እነዚህ በሰማይ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች የመንግሥቱን እውነት በመዝራቱ ሥራ የሚጫወቱትን ትልቅ ሚና በመመርመር እኛም ድርሻችንን እንድንወጣ የእነርሱ ምሳሌነት እንዴት ሊያበረታታን እንደሚችል እንመልከት።

ኢየሱስ​—⁠የመንግሥቱ እውነት ዘሪ

5. ኢየሱስ ምድር በነበረበት ወቅት በዋነኛነት የተጠመደው በየትኛው ሥራ ነበር?

5 ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ በጊዜው የነበሩ ሰዎችን በቁሳዊ ሊጠቅም የሚችል ብዙ ነገር ለማድረግ የሚያስችል ኃይል ነበረው። ለምሳሌ ያህል፣ በጊዜው የነበሩትን የተሳሳቱ የሕክምና አስተሳሰቦች ማስወገድ ወይም በሌላ የሳይንስ መስክ የሰዎችን የእውቀት አድማስ ማስፋት ይችል ነበር። ሆኖም፣ ገና አገልግሎቱን ሲጀምር ተልእኮው ምሥራቹን መስበክ እንደሆነ ግልጽ አድርጓል። (ሉቃስ 4:​17-21) እንዲሁም በአገልግሎቱ መገባደጃ አካባቢ “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:​37) ስለዚህ የመንግሥቱን እውነት ዘር በመዝራቱ ሥራ ራሱን አስጠመደ። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ከማስተማር ሌላ የተሻለ ትምህርት ሊሰጣቸው አይችልም ነበር።​—⁠ሮሜ 11:​33-36

6, 7. (ሀ) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ምን አስደናቂ ቃል ገባ? ይህንንስ እየፈጸመ ያለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ለስብከቱ ሥራ ያለው አመለካከት አንተን በግልህ የሚነካህ እንዴት ነው?

6 ኢየሱስ ራሱን የመንግሥቱ እውነት ዘሪ እንደሆነ አድርጎ ገልጿል። (ዮሐንስ 4:​35-38) ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የምሥራቹን ዘር ዘርቷል። በተሰቀለበት እንጨት ላይ ሊሞት እያጣጣረ በነበረበት ጊዜ እንኳን ሳይቀር ወደፊት ስለሚመጣው ምድራዊ ገነት የሚናገረውን ምሥራች አውጆአል። (ሉቃስ 23:​43) ከዚህም በላይ የምሥራቹ ስብከት ሥራ እንዲካሄድ የነበረው ጥልቅ ፍላጎት በመከራ እንጨት ላይ በሞተበት ጊዜ አልተዳፈነም። ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ሐዋርያቱ የመንግሥቱን እውነት ዘር መዝራታቸውን እንዲቀጥሉና ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ አዘዛቸው። ከዚያም ኢየሱስ አንድ አስደናቂ ተስፋ ሰጠ። “እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት ተናገረ።​—⁠ማቴዎስ 28:​19, 20

7 ኢየሱስ እንዲህ ብሎ በመናገር “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ” ምሥራቹን የመስበኩን ሥራ እንደሚደግፍ፣ እንደሚመራና እንደሚጠብቅ ቃል ገብቷል። ኢየሱስ እኛ እስካለንበት ጊዜ ድረስ የወንጌላዊነቱን ሥራ በትኩረት ሲከታተል ቆይቷል። የመንግሥቱን እውነት የመዝራቱን ሥራ በበላይነት የሚቆጣጠረው መሪያችን እርሱ ነው። (ማቴዎስ 23:​10) የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እንደመሆኑ መጠን በዓለም ዙሪያ ለሚከናወነው ለዚህ ሥራ በይሖዋ ዘንድ ተጠያቂ ነው።​—⁠ኤፌሶን 1:​22, 23፤ ቆላስይስ 1:​18

መላእክት አስደሳች ዜና ያውጃሉ

8, 9. (ሀ) መላእክት የሰዎችን ጉዳይ በትኩረት እንደሚከታተሉ ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) በመላእክት ፊት በመድረክ ላይ እንደሚታዩ ተዋንያን የሆንነው በምን መንገድ ነው?

8 ይሖዋ ምድርን በፈጠረ ጊዜ መላእክት ‘በአንድነት እየዘመሩ እልል ብለዋል።’ (ኢዮብ 38:​4-7) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ሰማያዊ ፍጥረታት የሰው ልጆችን ጉዳይ በንቃት ሲከታተሉ ቆይተዋል። ይሖዋ መለኮታዊ ቃል ለሰዎች ለማስተላለፍ በእነርሱ ተጠቅሟል። (መዝሙር 103:​20) ይህ ደግሞ በተለይ በጊዜያችን ምሥራቹን ከማሰራጨቱ ሥራ ጋር በተያያዘ እውነት ሆኖ ተገኝቷል። ሐዋርያው ዮሐንስ በተገለጠለት ራእይ ላይ “በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው . . . መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር” ተመልክቷል። “በታላቅ ድምፅም:- የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት . . . አለ።”​—⁠ራእይ 14:​6, 7

9 መጽሐፍ ቅዱስ መላእክትን “መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት” እንደሆኑ አድርጎ ይገልጻቸዋል። (ዕብራውያን 1:​14) መላእክት የተሰጣቸውን ሥራ በጉጉት ሲያከናውኑ እኛንም ሆነ ሥራችንን የመመልከት አጋጣሚ ያገኛሉ። በግልጥ በሚታይ የቲያትር መድረክ ላይ እንዳለን ሆነን ሥራችንን ስናከናውን ከሰማይ ይመለከቱናል። (1 ቆሮንቶስ 4:​9) የመንግሥቱን እውነት የመዝራቱን ሥራ የምናከናውነው ብቻችንን አለመሆኑን ማወቃችን በቁም ነገር እንድናስብበት የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ እጅግ የሚያስደስት ነው!

የተሰጠንን ድርሻ በጉጉት እንፈጽማለን

10. መክብብ 11:​6 ላይ የሚገኘው ምክር በምናከናውነው የወንጌላዊነት ሥራ ላይ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

10 ኢየሱስና መላእክቱ ሥራችንን በትኩረት የሚከታተሉት ለምንድን ነው? ኢየሱስ “እላችኋለሁ፣ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል” ብሎ በተናገረ ጊዜ አንዱን ምክንያት ገልጿል። (ሉቃስ 15:​10) እኛም ልክ እንደ እነርሱ ለሰዎች ከልብ እናስባለን። በመሆኑም የመንግሥቱን የእውነት ዘር በሁሉም ቦታ ለማሰራጨት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። መክብብ 11:​6 ላይ የሚገኙት ቃላት እኛ በምናከናውነው ሥራም ላይ ተግባራዊ ሊሆኑ ይችላሉ። እዚያ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይመክረናል:- “ወይም ይህ ወይም ያ ማናቸው እንዲበቅል ወይም ሁለቱ መልካም እንዲሆኑ አታውቅምና በማለዳ ዘርህን ዝራ፣ በማታም እጅህን አትተው።” እርግጥ ነው፣ በመቶ ወይም በሺህ ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል መልእክታችንን የሚቀበለው አንድ ሰው ብቻ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ “አንድ ኃጢአተኛ” እንኳን የመዳንን መልእክት በሚቀበልበት ጊዜ እንደ መላእክት እኛም ደስ ይለናል።

11. በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በመጠቀም ምን ያህል ውጤታማ መሆን ይቻላል?

11 የምሥራቹ ስብከት ሥራ በርካታ ነገሮችን ያጠቃልላል። ለዚህ ሥራ ጠቃሚ እርዳታ ከሚያበረክቱት ነገሮች መካከል አንዱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ናቸው። በአንዳንድ መንገዶች እነዚህ ጽሑፎች በየቦታው ከሚዘሩ ዘሮች ጋር ይመሳሰላሉ። የት ቦታ እንደሚበቅሉ አናውቅም። አንዳንድ ጊዜ አንድ ጽሑፍ አንባቢ የሚያገኘው የተለያዩ ሰዎች እጅ ከገባ በኋላ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስና መላእክት ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እንዲጠቀሙ ለማድረግ ነገሮችን በመምራት በአንዳንድ ወቅቶች ይህ ሁኔታ እንዲከሰት ሊያደርጉ ይችላሉ። ይሖዋ በሰው እጅ የገቡ ጽሑፎችን ተጠቅሞ ያልተጠበቁና አስደናቂ የሆኑ ውጤቶች እንዲገኙ የሚያደርግበትን መንገድ የሚያሳዩ አንዳንድ ተሞክሮዎችን ተመልከት።

የእውነተኛው አምላክ ሥራ

12. አንድ ቤተሰብ ይሖዋን እንዲያውቅ አንድ የቆየ መጽሔት እንደ መሣሪያ ሆኖ ያገለገለው እንዴት ነው?

12 በ1953 ሮበርት፣ ላይላ እና ልጆቻቸው ይኖሩበት የነበረውን አንድ ትልቅ ከተማ ለቅቀው ፔንሲልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ገጠር በመሄድ በአንድ ያረጀ የገበሬ ቤት ውስጥ መኖር ጀመሩ። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ሮበርት ከአንድ ደረጃ ሥር መታጠቢያ ቤት ለመሥራት ይወስናል። በርካታ ሳንቃዎችን ነቃቅሎ ካስወገደ በኋላ ከግድግዳው ጀርባ አይጦች የሰበሰቧቸውን ቁርጥራጭ ወረቀቶች፣ የኦቾሎኒ ገለባዎችና ሌሎች ግብስባሾችን ያገኛል። በእነዚህ መካከል ወርቃማው ዘመን (እንግሊዝኛ) የተባለ መጽሔት አንድ ቅጂ አገኘ። ሮበርት በተለይ ልጆችን ስለ ማሳደግ የሚናገረው ርዕስ ትኩረቱን ሳበው። መጽሔቱ በሚሰጠው ግልጽና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያ በጣም በመነካቱ የተነሳ “የወርቃማው ዘመን ሃይማኖት” አባል መሆን እንዳለባቸው ለላይላ ይነግራታል። ጥቂት ሳምንታት ካለፉ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታቸው መጡ። ይሁን እንጂ ሮበርት ቤተሰቡ ወርቃማው ዘመን ሃይማኖት” ሌላ እንደማይፈልግ ነገራቸው። ምሥክሮቹም ወርቃማው ዘመን አሁን ንቁ! በተባለ ሌላ ርዕስ መተካቱን ገለጹላቸው። ሮበርትና ላይላ ከምሥክሮቹ ጋር አዘውትረው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩና ከጊዜ በኋላ ተጠመቁ። እነርሱም በተራቸው የእውነትን ዘር በልጆቻቸው ልብ ውስጥ በመዝራት የተትረፈረፈ በረከት አጭደዋል። ዛሬ የሮበርትንና የላይላን ሰባት ልጆች ጨምሮ ከ20 የሚበልጡ የዚህ ቤተሰብ አባላት የተጠመቁ የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች ሆነዋል።

13. በፖርቶ ሪኮ የሚገኙ አንድ ባልና ሚስት ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደረገው ነገር ምንድን ነው?

13 ከዛሬ 40 ዓመት በፊት ዊልያም እና አዳ የተባሉ በፖርቶ ሪኮ የሚኖሩ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስ የማጥናት ፍላጎት አልነበራቸውም። የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸውን በሚያንኳኩበት ጊዜ ባልና ሚስቱ እቤት እንደሌሉ ያስመስላሉ። አንድ ቀን ዊልያም ቤት ውስጥ ለሚጠግነው ነገር ዕቃ ፍለጋ ያገለገሉ ብረታ ብረቶች ወደሚሸጡበት ቦታ ይሄዳል። ወደ ቤት በመመለስ ላይ እንዳለ ወደ አረንጓዴነት የሚያደላ ቢጫ ቀለም ያለው አንድ መጽሐፍ በአንድ ትልቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ ወድቆ ያገኛል። ይህ መጽሐፍ የይሖዋ ምሥክሮች በ1940 ያሳተሙት ሃይማኖት (እንግሊዝኛ) የተባለ መጽሐፍ ነበር። ዊልያም መጽሐፉን ወደ ቤት ከወሰደ በኋላ በሐሰተኛና በእውነተኛ ሃይማኖት መካከል ስላለው ልዩነት የሚናገረውን ክፍል ሲያነብ በጣም ተደሰተ። በቀጣዩ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሲመጡ ዊልያም እና አዳ መልእክታቸውን በደስታ ተቀበሉና አብረዋቸው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። ከጥቂት ወራት በኋላ በ1958 ተደርጎ በነበረው መለኮታዊ ፈቃድ በተባለው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ተጠመቁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከ50 የሚበልጡ ሰዎች የክርስቲያን ወንድማማች ማኅበራችን ክፍል እንዲሆኑ ረድተዋል።

14. በአንድ ተሞክሮ ላይ እንደታየው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችን ምን የማድረግ ኃይል አላቸው?

14 የ11 ዓመቱ ካርል በጣም ተንኮለኛና አስቸጋሪ ልጅ ነበር። የጀርመን ሜቶዲስት ሰባኪ የነበረው አባቱ መጥፎ ሰዎች ከሞቱ በኋላ በሲኦል ይቃጠላሉ ብሎ አስተምሮታል። በዚህም የተነሳ ካርል ሲኦል በጣም ያስፈራው ነበር። አንድ ቀን በ1917 ካርል በመንገድ ላይ ሲሄድ አንድ የስብሰባ ጥሪ ወረቀት መሬት ወድቆ ያገኛል። ወረቀቱን ሲያነብ ወዲያውኑ ዓይኑ “ሲኦል ምንድን ነው?” በሚለው ጥያቄ ላይ ያርፋል። ወረቀቱ ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው የሚታወቁት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሲኦልን በተመለከተ ያዘጋጁት የሕዝብ ንግግር መጋበዣ ነው። ካርል በርከት ላሉ ጊዜያት በተከታታይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲያደርግ ቆይቶ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ተጠመቀና እርሱም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አባል ሆነ። በ1925 በዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት እንዲሠራ ግብዣ ቀረበለት። አሁንም እዚያው በማገልገል ላይ ይገኛል። ይህ ሰው ከስምንት አሥርተ ዓመታት የሚበልጥ ጊዜ በክርስትና ሕይወት ሊያሳልፍ የቻለው መንገድ ላይ ወድቃ ባገኛት ወረቀት ነው።

15. ይሖዋ አስፈላጊ ሆኖ በሚያገኘው ጊዜ ምን ሊያደርግ ይችላል?

15 እርግጥ ነው፣ በእነዚህ ተሞክሮዎች ውስጥ የመላእክት እጅ ስለ መኖር አለመኖሩ፣ ካለም ደግሞ እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ማወቅ ከሰው አቅም በላይ ነው። ሆኖም ኢየሱስና መላእክት በስብከቱ ሥራ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱና ይሖዋም አስፈላጊ ሆኖ በሚያገኝበት ጊዜ ነገሮችን ሊመራ እንደሚችል ፈጽሞ መጠራጠር አይኖርብንም። እነዚህና እነዚህን የመሰሉ ሌሎች በርካታ ተሞክሮዎች ጽሑፎቻችን በሰው እጅ ከገቡ በኋላ ጥሩ ውጤት ሊያስገኙ እንደሚችሉ ያሳያሉ።

ውድ ሃብት በአደራ ተሰጥቶናል

16. ሁለተኛ ቆሮንቶስ 4:​7 ላይ ከሚገኙት ቃላት ምን ልንማር አንችላለን?

16 ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በሸክላ ዕቃ ውስጥ ስላለ ውድ ሃብት’ ተናግሯል። ይህ ውድ ሃብት አምላክ የሰጠን የስብከት ተልእኮ ሲሆን የሸክላ ዕቃው ደግሞ ይሖዋ ይህን ውድ ሃብት በአደራ የሰጣቸው ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ፍጽምና የጎደላቸውና የአቅም ገደብ ያለባቸው በመሆኑ እንዲህ ያለውን ተልዕኮ ሊቀበሉ የቻሉት ‘በራሳቸው አቅም ሳይሆን ከአምላክ ባገኙት ከወትሮው የበለጠ ኃይል’ እንደሆነ ጳውሎስ በመቀጠል ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 4:​7 NW ) አዎን፣ የተሰጠንን ሥራ ወደ ፍጻሜው ለማድረስ የሚያስችለንን ኃይል እንድናገኝ በይሖዋ ላይ ልንደገፍ እንችላለን።

17. የመንግሥቱን እውነት ዘር በምንዘራበት ጊዜ ምን ሊገጥመን ይችላል? ሆኖም አዎንታዊ አመለካከት እንደያዝን መቀጠል የሚኖርብን ለምንድን ነው?

17 ብዙውን ጊዜ መሥዋዕት መክፈል ይኖርብናል። አንዳንዶቹ የአገልግሎት ክልሎች አስቸጋሪ ወይም ምቹ ያልሆኑ ናቸው። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ከመጠን በላይ ግድ የለሾች ሌላው ቀርቶ ተቃዋሚዎች ናቸው። በነዚህ ቦታዎች ከፍተኛ ጥረት ተደርጎም አመርቂ ውጤት አልተገኘ ይሆናል። ሆኖም የብዙዎቹ ሕይወት አደጋ ላይ ከመሆኑ አንጻር ስናየው በምናደርገው ጥረት አንቆጭም። የምትዘራው ዘር ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ደስታ ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ሊያደርጋቸው እንደሚችል አስታውስ። “በሄዱ ጊዜ፣ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ” የሚሉት በ⁠መዝሙር 126:​6 ላይ የሚገኙት ቃላት በተደጋጋሚ እውነት ሆነው ተገኝተዋል።

18. ለአገልግሎታችን የማያቋርጥ ትኩረት መስጠት የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ ያለብንስ ለምንድን ነው?

18 ባገኘነው አመቺ አጋጣሚ ሁሉ የመንግሥቱን የእውነት ዘር በልግስና እንዝራ። ዘሩን የምንተክለውና የምናጠጣው እኛ ብንሆንም እንኳ የሚያሳድገው ይሖዋ መሆኑን ፈጽሞ አንዘንጋ። (1 ቆሮንቶስ 3:​6, 7) ሆኖም ኢየሱስና መላእክት በሥራው ውስጥ ያላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ሁሉ እኛም አገልግሎታችንን ሙሉ በሙሉ እንድንፈጽም ይሖዋ ይጠብቅብናል። (2 ጢሞቴዎስ 4:​5) እንግዲያው ለትምህርታችን፣ ለአመለካከታችንና በአገልግሎቱ ለምናሳየው ጉጉት የማያቋርጥ ትኩረት እንስጥ። ለምን? ጳውሎስ “ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ” በማለት መልሱን ይሰጠናል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​16

ምን ተማርን?

• ዘር የመዝራት ሥራችን በምን መንገዶች ጥሩ ፍሬ በማስገኘት ላይ ይገኛል?

• ኢየሱስ ክርስቶስና መላእክት ዛሬ እየተከናወነ ባለው የወንጌላዊነት ሥራ የሚካፈሉት እንዴት ነው?

• የመንግሥቱን እውነት በመዝራት ረገድ ለጋሶች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

• በአገልግሎታችን ግድየለሽና ተቃዋሚ ሰዎች ሲያጋጥሙን እንድንጸና ሊያነሳሳን የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥንቷ እስራኤል እንደነበሩት ገበሬዎች በዛሬ ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች የመንግሥቱን እውነት ዘር በልግስና ይዘራሉ

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ብዙ ዓይነት ጽሑፎችን በ340 ቋንቋዎች እያዘጋጁ ያሰራጫሉ