ይቅር ባዮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
ይቅር ባዮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
“ሳይንቲስቶች ይቅር ባይነት በስሜታዊ (ምናልባትም በአካላዊ) ጤንነት ላይ ጥሩ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ፍንጭ መስጠት የጀመረ ጥናት በማካሄድ ላይ ናቸው” ሲል በካናዳ የሚታተመው ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። ሆኖም በዩ ኤስ ኤ፣ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የስታንፎርድ ፎርጊቭነስ ፕሮጀክት የቡድን መሪ የሆኑት ተመራማሪው ካርል ቶርኢሴን “ይቅር ባይነት ምን ማለት እንደሆነና እንዴት ማሳየት እንደሚቻል የሚያውቁት ሰዎች ቁጥር በጣም ጥቂት” ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ከልብ ይቅር ማለት የክርስትና እምነት ዐቢይ ገጽታ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ዘ ቶሮንቶ ስታር ላይ የወጣው ዘገባ ይቅር ባይነትን “በደል እንደተፈጸመብህ መገንዘብ፣ በዚህ ምክንያት የተፈጠረብህን ቅያሜ ሁሉ ማውጣትና በመጨረሻም የበደለህን ሰው በርኅራኄ እንዲያውም በፍቅር መያዝ” ማለት እንደሆነ ገልጾታል። ይቅር ባይነት የተፈጸመን በደል ቸል ከማለት፣ እንዲሁ ከማለፍ፣ ከመርሳት ወይም በደልን ከማስተባበል የተለየ እንደሆነ መታየት አለበት። እንዲሁም ራስን ችግር ውስጥ መልሶ ማስገባት ማለትም አይደለም። ዘገባው ከልብ ይቅር ለማለት የሚያስችለው ቁልፍ “ቁጣንና መጥፎ ስሜቶችን ማስወገድ ነው” ሲል ተናግሯል።
ተመራማሪዎች ይቅር ባይነት ስለሚያስገኛቸው አካላዊ ጥቅሞች ተጨማሪ ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ “የውጥረት፣ የስጋትና የመንፈስ ጭንቀት መቀነስን” ጨምሮ ሥነ ልቦናዊ ጥቅሞች እንዳሉት ተናግረዋል።
ይቅር ባይ መሆን የሚያስፈልግበት ዋነኛ ምክንያት ኤፌሶን 4:32 ላይ ተገልጿል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ [“በነፃ፣” NW ] ይቅር እንዳላችሁ [“በነፃ፣” NW ] ይቅር ተባባሉ።” ይቅር ባይነትን በተመለከተም ሆነ በሌሎች ባሕርያት ረገድ አምላክን እንድንመስል ማበረታቻ ተሰጥቶናል።—ኤፌሶን 5:1፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል መሠረት እያለ ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ አለመሆን ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ሊጎዳብን ይችላል። ይሖዋ እርስ በርሳችን ይቅር እንድንባባል ይጠብቅብናል። ከዚያም እርሱ ይቅር እንዲለን ልንጠይቀው እንችላለን።—ማቴዎስ 6:14፤ ማርቆስ 11:25፤ 1 ዮሐንስ 4:11