መልካም ሥራዎች አምላክን ያስከብራሉ
መልካም ሥራዎች አምላክን ያስከብራሉ
አምላክን የሚወዱ ሁሉ ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ብርሃን ለማንጸባረቅ ይጥራሉ። እንዲህ በማድረግም ኢየሱስ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ይፈጽማሉ። (ማቴዎስ 5:16) የምንናገረው ነገርና የምናሳየው ትክክለኛ ምግባር አምላክን ሊያስከብር ይችላል።
የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖርና ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት በመጣጣር አምላክን ለማስደሰት ይሞክራሉ። ይህንን የሚያደርጉት ሕዝባዊ አገልግሎታቸው ሕጋዊ እውቅና ባላገኘባቸው አገሮች ውስጥ ጭምር ነው። ከእነዚህ አገሮች መካከል በአንደኛው ዋና ከተማ ምሥክሮቹ ከ6, 000 እስከ 9, 000 የሚያክሉ ሰዎች የተገኙባቸው ዓመታዊ የአውራጃ ስብሰባዎች አድርገው ነበር። እነዚህን ስብሰባዎች ለማድረግ በአንድ የኤግዚብሽን ማዕከል የሚገኙትን አዳራሾች ተከራይተው ነበር። ቀደም ባሉት ዓመታት እንዳደረጉት ሁሉ በ1999ም ስብሰባው ከመካሄዱ በፊት በመቶ የሚቆጠሩ ምሥክሮች ቦታዎቹን ለማጽዳት፣ የድምፅ መሣሪያዎቹን ለመትከልና በሺህ የሚቆጠሩ ወንበሮችን ለመደርደር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።
ሆኖም ይህ ሁሉ ዝግጅት ሳይስተዋል አላለፈም። የአስተዳደር ቢሮው ሠራተኞች ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ ሲደረግ ይመለከቱ ነበር። በተጨማሪም ስብሰባው 15, 666 የደረሰ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር የነበረው ቢሆንም ሁሉ ነገር የተሳካና ምሥክሮቹም በጣም ሥርዓታማ መሆናቸውን መመልከት ከመቻላቸውም በላይ ከስብሰባው በኋላ አዳራሹ በሚገባ ፀድቶ በማየታቸው ተደንቀው ነበር።
አስተዳደሩ ለዚህ ሁሉ ያለውን አድናቆት የገለጸው የሕንፃውን አዳራሽ ለመከራየት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መካከል ምሥክሮቹን በአንደኛ ደረጃ በማስቀመጥ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ሕንፃውን ለመከራየት ቢፈልጉ የመጀመሪያውን አጋጣሚ የሚያገኙት እነርሱ ይሆናሉ። ሆኖም አስተዳደሩ ከዚህም በላይ አድርጓል። ሐምሌ 15, 1999 ለአውራጃ ስብሰባው አስተባባሪ ኮሚቴ የአድናቆት ሽልማት ሰጥቷል። ሽልማቱ “የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ” የሚል ጽሑፍ ተቀርጾበታል። መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ በታገደበት አገር ይህ ፈጽሞ ያልተጠበቀ ሁኔታ ነበር።
በዓለም ዙሪያ በ2000/2001 በሚደረጉት “የአምላክ ቃል አድራጊዎች” የሚል ጭብጥ ባላቸው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል። እርስዎም በስብሰባው ላይ በመገኘት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈውን ከልብ የሚያደርጉ ሰዎች አምላክን የሚያስከብሩ መልካም ሥራዎች በመሥራት የተጠመዱት እንዴት እንደሆነ ራስዎ መመልከት ይችላሉ።