ሲኒኮች ተጽእኖ አሳድረውብህ ያውቃሉ?
ሲኒኮች ተጽእኖ አሳድረውብህ ያውቃሉ?
“ሲኒክ የሆነ ሰው መጥፎው እንጂ ጥሩ የሆነው የሰው ባሕርይ ፈጽሞ አይታየውም። ሲኒክ የሰው ጉጉት ነው፤ በጨለማ ውስጥ ሁልጊዜ ንቁ፣ ለብርሃን እውር፣ ጥሩውን አደን ትቶ ትንንሽ ነፍሳትን የሚለቃቅም ነው።” ይህንን የተናገሩት የ19ኛው መቶ ዘመን አሜሪካዊ ቄስ ሄንሪ ዋርድ ቢቸር ናቸው። ይህ አባባል የዘመናችንን ሲኒኮች በትክክል ይገልጻል በማለት ብዙዎች ያስቡ ይሆናል። ሆኖም በጥንቷ ግሪክ ይሠራበት የነበረው “ሲኒክ” የሚለው ቃል እንዲህ ያለ ዝንባሌ ያለውን ሰው ብቻ አያመለክትም። ላለፉት ብዙ መቶ ዘመናት ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸውን ፈላስፎች ለማመልከት ሲሠራበት ቆይቷል።
የሲኒኮች ፍልስፍና እንዴት ሊዳብር ቻለ? የሚያስተምሩትስ ምንድን ነው? የሲኒክ ዓይነት ባሕርይ ማሳየት ለአንድ ክርስቲያን ተገቢ ነውን?
የቀድሞዎቹ ሲኒኮች—አመጣጣቸውና እምነታቸው
ጥንታዊቷ ግሪክ በውይይትና በክርክር ትታመስ ነበር። ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት በነበሩት ብዙ መቶ ዓመታት እንደ ሶቅራጥስ፣ ኘላቶና አርስቶትል ያሉ ሰዎች ታዋቂ ያደረጓቸውን ፍልስፍናዎች ለውይይት አቅርበው ነበር። ትምህርቶቻቸው በሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ከማሳደራቸውም በላይ እንዲህ ያሉት አስተሳሰቦች እስከ ዛሬ በምዕራባውያን ባህል ውስጥ ይገኛሉ።
ሶቅራጥስ (470-399 ከዘአበ) ቁሳዊ ነገሮችን ወይም ሥጋዊ ተድላን ማሳደድ ዘላቂ ደስታ አያስገኝም በማለት ይከራከር ነበር። እውነተኛ ደስታ የሚገኘው በጎነትን በመፈለግ ላይ ብቻ የተወሰነ ሕይወት በመምራት ነው ብሎ ተከራክሯል። ሶቅራጥስ በጎነትን የመጨረሻው ጥሩ ምግባር አድርጎ ይመለከተው ስለነበር እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ሲል ከቁሳዊ ነገሮች የሚገኘውን ቅንጦትና ለዚህ የሚደረገውን ከንቱ ሩጫ ወደ ጎን ትቷል። ምክንያቱም ይህ የትኩረት አቅጣጫውን ሊያስተው እንደሚችል ተሰምቶት ስለነበር ነው። ቀላልና በቁጠባ ላይ የተመሠረተ ሕይወት በመምራት ልከኝነትንና የራስን ጥቅም የመሠዋትን መንፈስ እንደሚደግፍ አሳይቷል።
ሶቅራጥስ አንድ ዓይነት የማስተማሪያ ዘዴ ያዳበረ ሲሆን ይህም ሶቅራጥሳዊ ዘዴ በመባል ይታወቃል። አብዛኞቹ ፈላስፎች አንድ ሐሳብ ካስተዋወቁ በኋላ ለዚህ ሐሳባቸው ድጋፍ የሚሆኑ የመከራከሪያ ነጥቦች ሲያቀርቡ ሶቅራጥስ ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር አድርጓል። ሌሎች ፈላስፎች ያቀረቧቸውን ፅንሰ ሐሳቦች ካዳመጠ በኋላ ጉድለቶቻቸውን ለማጋለጥ ይሞክር ነበር። እንዲህ ያለው የማስተማሪያ ዘዴ ሌሎችን በነቀፌታና በንቀት የመመልከትን ዝንባሌ አበረታቷል።
ከሶቅራጥስ ተከታዮች መካከል አንቲስቲኒስ (ከ445-365 ከዘአበ አካባቢ) የተባለ ፈላስፋ ይገኝበት ነበር። እሱና ሌሎች የተወሰኑ ሰዎች ከሶቅራጥስ መሠረታዊ ትምህርት አልፈው በመሄድ በጎነት ብቸኛው ጥሩ ነገር ነው ማለት ጀመሩ። ለእነርሱ ተድላን ማሳደድ የትኩረት አቅጣጫን የሚያስት ብቻ ሳይሆን ክፋትም ነበር። የከረረ ፀረ-ማኅበራዊ አቋም በመያዝ ለሰዎች ያላቸውን ከፍተኛ ንቀት አሳይተዋል። ስለዚህ ሲኒኮች በመባል መታወቅ ጀመሩ። ሲኒክ የሚለው መጠሪያ ጠብራራነታቸውንና ትዕቢታቸውን ከሚያመለክተው (ኪኒኮስ ) የግሪክኛ ቃል የመጣ ሊሆን ይችላል። ትርጉሙም “የውሻ ዓይነት ባሕርይ ያለው” ማለት ነው። a
በአኗኗራቸው ላይ ያሳደረው ተጽእኖ
ፍቅረ ንዋይንና ከልክ በላይ ለራስ ፍላጎት መገዛትን መቃወም የመሳሰሉት የሲኒክ ፍልስፍና ገጽታዎች በራሳቸው ጥሩ እንደሆኑ ተደርገው ቢታዩም ሲኒኮች ወደ ሌላኛው ጽንፍ ሄደው ነበር። ይህንንም በጣም ታዋቂ ሲኒክ ከነበረው ዳያጀኒዝ የተባለ ፈላስፋ ሕይወት በግልጽ ማየት ይቻላል።
ዳያጀኒዝ ጥቁር ባሕር ላይ በምትገኘው ሲኖፒ በተባለች ከተማ በ412 ከዘአበ ተወለደ። ከአባቱ ጋር በመሆን ወደ አቴንስ በመዛወሩ ከሲኒኮች ትምህርት ጋር ለመተዋወቅ ቻለ። አንቲስትኒስ ዳያጀኒዝን ያስተማረው ሲሆን በውጤቱም ዳያጀኒዝ በሲኒክ ፍልስፍና ሙሉ በሙሉ ተዋጠ። ሶቅራጥስ ቀለል ያለ ሕይወት የመራ ሲሆን አንቲስትኒስ ደግሞ ምቾት የለሽ ሕይወት መርቷል። ዳያጀኒዝ ግን ሕይወቱን ሙሉ ባሕታዊ በመሆን አሳልፏል። ዳያጀኒዝ ከቁሳዊ ነገሮች የሚገኘውን ምቾት እንደማይፈልግ ጎላ አድርጎ ለማሳየት ሲል ለአጭር ጊዜ በውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ውስጥ እንደኖረ ይታመናል!
ዳያጀኒዝ ከሁሉ የላቀውን ጥሩ ምግባር ለማከናወን በማሰብ በጎ ሰው ፍለጋ በቀን የተለኮሰ ፋኖስ ይዞ አቴንስ ውስጥ ይዞር እንደነበር ይነገራል! እንደዚህ ያለው አድራጎት የሌሎችን ትኩረት በመሳቡ የዳያጀኒዝም ሆነ የሌሎቹ ሲኒኮች ማስተማሪያ ዘዴ ለመሆን ችሏል። በአንድ ወቅት ታላቁ እስክንድር በጣም የሚፈልገው ምን እንደሆነ ዳያጀኒዝን ሲጠይቀው የፀሐይዋን ብርሃን እንዳትከልለኝ ከፊቴ ገለል ብቻ እንድትልልኝ እፈልጋለሁ እንዳለው ይነገራል!
ዳያጀኒዝና ሌሎቹ ሲኒኮች እድሜ ልካቸውን ለማኞች ነበሩ። የሰው ልጅ ለሚያደርጋቸው የተለመዱ ሰብዓዊ ግንኙነቶች ጊዜ ያልነበራቸው ከመሆኑም በላይ ሕዝባዊ ግዴታዎች በእነርሱ ዘንድ ተቀባይነት አልነበሯቸውም። ሶቅራጥሳዊው የማስተማሪያ ዘዴ ተጽእኖ ስላሳደረባቸው ሊሆን ይችላል፣ ለሌሎች ሰዎች ምንም አክብሮት የሌላቸው ነበሩ። ስለዚህ ዳያጀኒዝ በአቁሳይ አሽሙሩ የታወቀ ሆነ። ሲኒኮች በቡድን ደረጃ “የውሻ ዓይነት ባሕርይ ያላቸው” የሚለውን ስም ያትርፉ እንጂ ዳያጀኒዝ ራሱ ውሻው የሚል ቅጽል ስም ወጥቶለት ነበር። ዳያጀኒዝ በ90 ዓመቱ መዳረሻ ላይ ማለትም በ320 ከዘአበ ሲሞት መቃብሩ ላይ የውሻ ቅርጽ ያለው የእብነ በረድ ሃውልት ቆሞለት ነበር።
ከሲኒክ የፍልስፍና ዘርፎች መካከል አንዳንዶቹ ወደ ሌሎች የምሁራን ቡድኖች ውስጥ ሰርገው መግባት ችለው ነበር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ዳያጀኒዝና የኋለኞቹ ተከታዮቹ ካሳዩት ለየት ያለ ባሕርይ ጋር በተያያዘ የሲኒኮች ፍልስፍና ተቀባይነት እያጣ ሄደ። ቀስ በቀስም ከነአካቴው ጠፋ።
የዛሬዎቹን ሲኒኮች ባሕርይ ማንጸባረቅ ይገባሃልን?
ዚ ኦክስፎርድ ኢንግሊሽ ዲክሽነሪ ዘመናዊውን ሲኒክ “ዘለፋ የሚቀናው ወይም ስህተት ፈላጊ የሆነ ሰው። . . . በሰዎች ሐሳብና ተግባር ቅንነት ወይም ጥሩነት ላይ እምነት እንደሌለው የሚያሳይና ይህንንም በማንኳሰስና በአሽሙር የመግለጽ ልማድ ያለው፤ ጉድለት የሚለቃቅምና ሌሎችን የሚያጣጥል ሰው” በማለት ይገልጸዋል። እነዚህ ባሕርያት በዙሪያችን ባለው ዓለም ውስጥ በግልጽ የሚታዩ ቢሆንም ከክርስቲያናዊ ባሕርይ ጋር ፈጽሞ አይስማሙም። የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ተመልከት።
“እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፣ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። ሁልጊዜም አይቀሥፍም፣ ለዘላለምም አይቈጣም።” (መዝሙር 103:8, 9) ክርስቲያኖች “እግዚአብሔርን የምትከተሉ [“የምትመስሉ፣” NW ] ሁኑ” ተብለው ተመክረዋል። (ኤፌሶን 5:1) ሁሉን የሚችለው አምላክ ‘ከመዝለፍ ወይም ስህተት ከመፈላለግ’ ይልቅ ምሕረትና ፍቅራዊ ደግነት ማሳየትን ከመረጠ በእርግጥም ክርስቲያኖች እንደዚሁ ለማድረግ መጣር ይኖርባቸዋል።
ትክክለኛው የይሖዋ ነጸብራቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ፍለጋውን እንድንከተል ምሳሌ ትቶልናል።’ (1 ጴጥሮስ 2:21፤ ዕብራውያን 1:3) አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስ የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ከማጋለጡም በላይ የዚህ ዓለም ሥራዎች ክፉ እንደሆኑ ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:7) ያም ሆኖ ግን ቅን ሰዎችን ያሞግስ ነበር። ለምሳሌ፣ ናትናኤልን አስመልክቶ “ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 1:48) ኢየሱስ ተዓምር በሚሠራበት ወቅት አንዳንድ ጊዜ ትኩረቱን በተቀባዩ እምነት ላይ አድርጎ መሆን አለበት። (ማቴዎስ 9:22) በተጨማሪም አንዳንዶች አንዲት ሴት አድናቆቷን ለመግለጽ ያቀረበችው ስጦታ አላግባብ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት እንደሆነ አድርገው ቢያስቡም ኢየሱስ ግን እንዲህ ለማድረግ የተነሳሳችበትን ውስጣዊ ዓላማ አልተጠራጠረም። ከዚህ ይልቅ “ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል” በማለት ተናግሮአል። (ማቴዎስ 26:6-13) ኢየሱስ ተከታዮቹን ‘እስከ መጨረሻው በመውደድ’ እምነት እንደሚጥልባቸውና እንደሚያፈቅራቸው አሳይቷል።—ዮሐንስ 13:1
ኢየሱስ ፍጹም እንደመሆኑ መጠን ፍጽምና ከሌላቸው ማቴዎስ 11:29, 30
ሰዎች በቀላሉ ስህተት ማግኘት ይችል ነበር። ሆኖም ሌሎችን በጥርጣሬ ከመመልከትና ስህተት ከመፈላለግ ይልቅ ሰዎችን ለማሳረፍ ጥረት ያደርግ ነበር።—“[ፍቅር] ሁሉን ያምናል።” (1 ቆሮንቶስ 13:7) ይህ መግለጫ የሌሎችን ውስጣዊ ግፊትና ተግባር ከሚጠራጠረው የሲኒክ ባህርይ ፍጹም ተቃራኒ ነው። እርግጥ በዓለም ውስጥ ስውር ዓላማ ያላቸው ብዙ ሰዎች ስላሉ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። (ምሳሌ 14:15) የሆነ ሆኖ ፍቅር ከልክ በላይ ተጠራጣሪ ስላልሆነ ለማመን ዝግጁ ነው።
አምላክ አገልጋዮቹን ከመውደዱና ከማመኑም በላይ እነርሱ ከሚያውቁት የበለጠ የአቅማቸውን ውስንነት ይገነዘባል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሕዝቡን ፈጽሞ በጥርጣሬ ዓይን አይመለከትም። ሊሠሩት ከሚችሉት የበለጠ አይጠብቅባቸውም። (መዝሙር 103:13, 14) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ሰዎች ያሏቸውን ጥሩ ጥሩ ነገሮች ይመለከታል። ስለዚህም በእነርሱ ላይ እምነት እንዳለው በሚያሳይ መንገድ ፍጹማን ላልሆኑት ታማኝ አገልጋዮቹ መብትና ሥልጣን ይሰጣቸዋል።—1 ነገሥት 14:13፤ መዝሙር 82:6
“እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኩላሊትንም እፈትናለሁ።” (ኤርምያስ 17:10) ይሖዋ የሰውን ልብ በትክክል ማንበብ ይችላል። እኛ ግን አንችልም። ስለዚህ ሌሎች አንድ ነገር ለማድረግ ስለተነሳሱበት ዓላማ በምንናገርበት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል።
የጥርጣሬ መንፈስ በውስጣችን ሥር እንዲሰድና በመጨረሻም አስተሳሰባችንን እንዲቆጣጠር ከፈቀድንለት በራሳችንና በመሰል አማኞች መካከል መከፋፈል ሊፈጥርና የክርስቲያን ጉባኤውን ሰላም ሊያናጋ ይችላል። ስለዚህ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ሐቁን ቢገነዘብም አዎንታዊ አመለካከት የነበረውን የኢየሱስን ምሳሌ እንከተል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ እምነት የሚጣልበት ጓደኛ ሆኗቸዋል።—ዮሐንስ 15:11-15
“ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።” (ሉቃስ 6:31) ይህንን የኢየሱስ ክርስቶስ ምክር በብዙ መንገዶች ተግባር ላይ ማዋል ይቻላል። ለምሳሌ፣ ሁላችንም ብንሆን ሌሎች በደግነትና በአክብሮት እንዲያነጋግሩን እንፈልጋለን። እንግዲያው እኛም ሌሎችን ደግነትና አክብሮት ባለው መንገድ ልናነጋግራቸው ይገባል። ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹ የሚያስተምሯቸውን የሐሰት ትምህርቶች በድፍረት ቢያጋልጥም አነጋገሩ ንቀት የተሞላበት አልነበረም።—ማቴዎስ 23:13-36
ሲኒካዊ አስተሳሰብን ለመዋጋት የሚያስችሉ መንገዶች
ያልጠበቅነው ነገር ደርሶብን አዝነን ከነበረ ሲኒካዊ አስተሳሰብ በቀላሉ ተጽእኖ እንዲያሳድርብን ልንፈቅድ እንችላለን። ይሖዋ ፍጹማን ካልሆኑት ሕዝቦቹ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት እምነት እንደሚጥልባቸው ከተገነዘብን እንዲህ ያለውን ዝንባሌ መዋጋት እንችላለን። ይህን ማወቃችን ሌሎች አምላኪዎች ትክክል የሆነውን ለማድረግ የሚጥሩ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች መሆናቸውን አምነን እንድንቀበል ሊረዳን ይችላል።
አንዳንዶች በሕይወታቸው ውስጥ ያጋጠሟቸው አሳዛኝ ሁኔታዎች ሰዎችን እንዳያምኑ ያደርጋቸው ይሆናል። እውነት ነው፣ እምነታችንን ፍጹማን ባልሆኑ የሰው ልጆች ላይ ሙሉ በሙሉ መጣል አይገባንም። (መዝሙር 146:3, 4) ይሁን እንጂ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ብዙዎች ለሌሎች የብርታት ምንጭ ለመሆን ልባዊ ፍላጎት አላቸው። የራሳቸውን ቤተሰቦች ላጡ ሁሉ እናቶች፣ አባቶች፣ እህቶች፣ ወንድሞችና ልጆች የሆኑትን በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አስብ። (ማርቆስ 10:30) በጭንቀት ጊዜ እውነተኛ ጓደኞች ሆነው ስለተገኙት በርካታ ወንድሞች አስብ። b—ምሳሌ 18:24
ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ስላለ ተከታዮቹን ለይቶ የሚያሳውቃቸው ነገር ሲኒካዊ አስተሳሰብ ሳይሆን ወንድማዊ ፍቅር ነው። (ዮሐንስ 13:35) ስለዚህ ለሌሎች ፍቅር እናሳይ እንዲሁም ክርስቲያን ባልደረቦቻችን ባሏቸው ጥሩ ጥሩ ባሕርያት ላይ የምናተኩር እንሁን። እንዲህ ማድረጋችን ሲኒክ የሆነ ሰው የሚያሳያቸውን ባሕርያት ከማንጸባረቅ ይጠብቀናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በሌላም በኩል ሲኒክ የሚለው ስም አንቲስቲኒስ ያስተምርበት ከነበረው ኪኖሳሬስ ከሚባለው በአቴንስ የሚገኝ የስፖርት ማዕከል መጠሪያ የመጣ ሊሆን ይችላል።
b “ክርስቲያን ጉባኤ—የብርታት ምንጭ” በሚል ርዕስ የወጣውን የግንቦት 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ተመልከት።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳያጀኒዝ—በጣም የታወቀው ሲኒክ
[ምንጭ]
ታላላቅ ወንዶችና ታዋቂ ሴቶች ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ