በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስደት በአንጾኪያ እድገት እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል

ስደት በአንጾኪያ እድገት እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል

ስደት በአንጾኪያ እድገት እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል

እስጢፋኖስ ሰማዕት ከሆነ በኋላ የስደት ማዕበል ሲቀሰቀስ ብዙዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከኢየሩሳሌም ሸሹ። በስደት ከኖሩባቸው ቦታዎች መካከል አንዷ ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን በ550 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የሶርያዋ አንጾኪያ ነበረች። (ሥራ 11:​19) ይህን ተከትሎ የተከሰቱት ሁኔታዎች ነገሮች በመላው የክርስትና ታሪክ ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ምን እንደተከናወነ ለመረዳት በቅድሚያ ስለ አንጾኪያ አንዳንድ ጉዳዮችን ማወቅ አስፈላጊ ነው።

አንጾኪያ በስፋት፣ በብልጽግና እንዲሁም ባላት ጠቀሜታ በሮም ግዛት ከሚገኙ ከተማዎች ጋር ስትወዳደር ከሮም እና ከእስክንድርያ በስተቀር ሁሉንም ትበልጣለች። ይህች ትልቋ የሶርያ ከተማ የሜድትራኒያንን ሰሜን ምሥራቅ ዳርቻ በበላይነት ትቆጣጠር ነበር። አንጾኪያ (በአሁኗ ቱርክ ውስጥ አንታኪያ ትባላለች።) የተቆረቆረችው ለመርከብ ጉዞ ምቹ በሆነው ኦሮንተስ ወንዝ ዳርቻ ሲሆን ይህ ወንዝ 32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የሴሌውቅያ ፒዬራ የባሕር ወደብ ጋር ያገናኛታል። በሮምና በጤግሮስ ኤፍራጥስ ሸለቆ መካከል ያለውን ዋና የንግድ እንቅስቃሴ ትቆጣጠራለች። የንግድ መናኸሪያ በመሆኗ በሮም ግዛት ሥር ከሚገኙት አገሮች ሁሉ ጋር የንግድ ግንኙነት የምታደርግ ሲሆን ለዚሁ ዓላማ የሚመላለሱ የተለያዩ ሰዎች በሮም ግዛት ሥር በየትኛውም ቦታ የሚደረገውን ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ የሚገልጹ ዜናዎችን ያመጣሉ።

በአንጾኪያ ሄለናዊ ሃይማኖትና ፍልስፍና ተስፋፍቶ ነበር። ሆኖም ታሪክ ጸሐፊው ግላንቨል ዳውኒ እንዲህ ብለዋል:- “ኢየሱስ በኖረበት ዘመን የጥንት ሃይማኖታዊ ኑፋቄዎችና ፍልስፍናዎች የተናጠል እምነት ወደ መሆን አዘንብለው ነበር። ሰዎች ሃይማኖታዊ እርካታን የግል ችግሮቻቸውን ለመፍታትና ምኞቶቻቸውን ለማሳካት ተጠቅመውበታል።” (ኤ ሒስትሪ ኦቭ አንቲዮክ ኢን ሲሪያ ) የአይሁድ እምነት በአንድ አምላክ ስለ ማመን፣ ስለ በዓል አከባበርና ስለ ሥነ ምግባር የሚሰጣቸው ትምህርቶች ብዙዎችን አርክቶ ነበር።

ከተማይቱ በ300 ከዘአበ ከተቆረቆረችበት ጊዜ አንስቶ ብዛት ያላቸው የአይሁድ ሰፋሪዎች በአንጾኪያ ይኖሩ ነበር። ብዛታቸው ከ20, 000 እስከ 60, 000 ይደርሳል ተብሎ የሚገመት ሲሆን ይህ ደግሞ ከጠቅላላው ሕዝብ 10 ከመቶ የሚያክል ነው። ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ እንደተናገረው የሴሌውቅያ ሥርወ መንግሥት ለአይሁዳውያን ሙሉ የዜግነት መብት እየሰጠ በከተማይቱ እንዲሰፍሩ አበረታቷል። በዚያን ጊዜ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጹሑፎች ወደ ግሪክኛ ተተርጉመው ነበር። ይህ ደግሞ ደጋፊዎችም እንደ አይሁዳውያን መሲሁን እንዲጠብቁ አነሳስቷቸዋል። በዚህ ምክንያት ብዙ ግሪካውያን ወደ ይሁዲነት ተለውጠዋል። ይህ ሁሉ ተዳምሮ አንጾኪያ ክርስቲያን ደቀ መዛሙርትን ለማፍራት የሚያስችል ምቹ መስክ አድርጓታል።

ለአሕዛብ መመሥከር

ከኢየሩሳሌም በስደት የተበተኑት አብዛኞቹ የኢየሱስ ተከታዮች እምነታቸውን የሚያካፍሉት ለአይሁዳውያን ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ ከቆጵሮስና ከቀሬና ወደ አንጾኪያ የመጡ አንዳንድ ደቀ መዛሙርት “ለግሪክ ሰዎች ተናገሩ።” (ሥራ 11:​20) በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት አንስቶ ግሪክኛ ተናጋሪ ለሆኑ አይሁድና ወደ ይሁዲነት ለተለወጡ ሰዎች መስበክ የተለመደ ቢሆንም በአንጾኪያ የታየው ይህ ስብከት ግን እንግዳ ይመስል ነበር። የሚሰብኩት ለአይሁዳውያን ብቻ አልነበረም። እርግጥ ነው፣ ከአሕዛብ ወገን የሆነው ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። ሆኖም ሐዋርያው ጴጥሮስ ለአሕዛብ ወይም ለሌሎች ብሔራት ሕዝቦች መስበክ ተገቢ መሆኑን እንዲያምን ከይሖዋ የተላከ ራእይ ማየት አስፈልጎት ነበር።​—⁠ሥራ 10:​1-48

እጅግ ብዙ ቁጥር ያለውን የአይሁድ ማኅበረሰብ ለረጅም ዓመታት ባስተናገደችው ከተማ ውስጥ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል እምብዛም ጥላቻ ስለማይታይ ምሥክርነቱ አይሁድ ላልሆኑ ሰዎችም ይሰጥ ነበር። እነሱም ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። በአንጾኪያ ምቹ ሁኔታ መኖሩ ይህን የመሰለ እድገት እንዲገኝ ያስቻለ ሲሆን በዚህ ምክንያት ‘እጅግ ብዙ ሰዎች አምነዋል።’ (ሥራ 11:​21) እንዲሁም አረማዊ አማልክትን ሲያመልኩ ቆይተው ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ወገኖቻቸው ለመመስከር ዝግጁ ሆነዋል።

በኢየሩሳሌም የሚገኘው ጉባኤ በአንጾኪያ እድገት እንደተገኘ ሲሰማ ሁኔታውን ለማጣራት በርናባስን ወደዚያ ላከ። ይህ ምርጫ ጥበብና ፍቅር የታከለበት ነበር። አይሁድ ላልሆኑ መስበክ እንደ ጀመሩት አንዳንዶች እሱም ቆጵሮሳዊ ነበር። በርናባስ በአንጾኪያ በሚገኙ አሕዛብ ዘንድ እንደ ባይተዋር አልታየም። ከዚህ ይልቅ በቅርብ ካለች መንደር የመጣ ያህል ተሰምቷቸው መሆን አለበት። a ለሚሠራው ሥራም ቢሆን ከእነሱ የተለየ አመለካከት አልነበረውም። “እርሱም መጥቶ የእግዚአብሔርን ጸጋ ባየ ጊዜ ደስ አለው፣ ሁሉንም በልባቸው ፈቃድ በጌታ ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው።” በዚህ ምክንያት “ብዙ ሕዝብም ወደ ጌታ ተጨመሩ።”​—⁠ሥራ 11:​22-24

ታሪክ ጸሐፊው ዳውኒ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል:- “የአንጾኪያው ተልዕኮ የተሳካ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ ሚስዮናውያኑ በኢየሩሳሌም እንደነበረው ያለ የአክራሪ አይሁዳውያን ፍራቻ አልነበረባቸውም፤ በተጨማሪም ከተማይቱ የሶርያ መዲና በመሆኗ የምትተዳደረው በወታደራዊ አዛዥ ነበር። ስለሆነም የይሁዳ ገዥዎች (ቢያንስ በዚያን ጊዜ) አይሁዳውያን አክራሪዎችን መግታት ስላልቻሉ በኢየሩሳሌም እንደሚታየው ያለ ሕዝባዊ ዓመፅ ስላልገጠማት አንጾኪያ በእጅጉ ሕዝባዊ ሥርዓት የሰፈነባት ሆናለች።”

በርናባስ እንደዚህ ባለ አመቺ ሁኔታዎች ሥር ብዙ የሚያከናውነው ሥራ እንዳለውና ረዳት እንደሚያስፈልገው ሲገነዘብ ወዳጁ ሳውል ትዝ ሳይለው አልቀረም። ሳውልን ወይም ጳውሎስን ያሰበው ለምን ነበር? ጳውሎስ ከ12ቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ ባይሆንም እንኳን የአሕዛብ ሐዋርያ ተደርጎ በመሾሙ ይመስላል። (ሥራ 9:​15, 27፤ ሮሜ 1:​5፤ ራእይ 21:​14) በዚህ ምክንያት ጳውሎስ የአሕዛብ ከተማ በሆነችው በአንጾኪያ ምሥራቹን ለማወጅ መጠራቱ ተስማሚ ነበር። (ገላትያ 1:​16) ስለዚህ በርናባስ ወደ ጠርሴስ ሄዶ ሳውልን ካገኘው በኋላ ወደ አንጾኪያ ይዞት ተመለሰ።​—⁠ሥራ 11:​25, 26፤ ከገጽ 26-7 ያለውን ሣጥን ተመልከት።

በመለኮታዊ አመራር ክርስቲያን ተባሉ

በርናባስና ሳውል አንድ ዓመት ሙሉ “ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፣ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ [“በመለኮታዊ አመራር፣” NW ] ክርስቲያን ተባሉ።” አይሁዳውያን ኢየሱስ መሲህ ወይም ክርስቶስ መሆኑን ስላልተቀበሉ ተከታዮቹን ክርስቲያኖች (በግሪክኛ) ወይም መሲሃውያን (በዕብራይስጥ) ብለው ሰይመዋቸዋል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም። የኢየሱስን ተከታዮች ክርስቲያኖች ብለው በመጥራት ክርስቶስን በተዘዋዋሪ መቀበል አልፈለጉም። አንዳንዶች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በቀልድ ወይም በፌዝ ክርስቲያኖች የሚል ቅጽል ስም አውጥተውላቸዋል ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያን የሚለውን ስያሜ ያገኙት ከአምላክ መሆኑን ይናገራል።​—⁠ሥራ 11:​26

በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በአብዛኛው “ተባሉ” ተብሎ የተተረጎመውና ክርስቲያን ከሚለው አዲስ ስም ጋር ተያይዞ የገባው ግስ ሁልጊዜ የሚዛመደው ከሰብዓዊ ፍጡር በላይ ከሆነ ነገር፣ ከመለኮት ወይም ከመለኮታዊ ኃይል ጋር ነው። ስለሆነም ሃይማኖታዊ ምሁራን “በመለኮት ኃይል መናገር፣” “መለኮታዊ ሐሳብ፣” ወይም “መለኮታዊ ትእዛዝ ወይም ማሳሰቢያ መስጠት፣ ሰማይ ሆኖ ማስተማር” ብለው ተርጉመውታል። የኢየሱስ ተከታዮች ክርስቲያኖች ተብለው የተጠሩት “በመለኮታዊ አመራር” ስለሆነ ይሖዋ ሳውልና በርናባስ ስያሜውን እንዲሰጡ መርቷቸዋል ብሎ መናገር ይቻላል።

ደቀ መዛሙርት በአዲሱ ስያሜ መጠራት ቀጠሉ። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በግልጽ የሚለያቸውን ስም ስላገኙ ከአይሁድ እምነት እንደተገነጠለ አንድ ቡድን ተደርገው አይታዩም። በ58 እዘአ ገደማ የሮም መንግሥት ባለሥልጣናት የክርስቲያኖችን ማንነት በደንብ ለይተው ነበር። (ሥራ 26:​28) ታሪክ ጸሐፊው ታሲተስ እንዳስቀመጠው በ64 እዘአ ሮም ውስጥ ተራው ሕዝብ እንኳን ሳይቀር ክርስቲያን የሚለውን ስም ያውቅ ነበር።

ይሖዋ በታማኝ አገልጋዮቹ ይጠቀማል

በአንጾኪያ ምሥራቹ ጥሩ እድገት አድርጓል። በይሖዋ በረከትና የኢየሱስ ተከታዮች ምሥራቹን ያለማሰለስ ለመስበክ ባደረጉት ቁርጥ ውሳኔ ምክንያት አንጾኪያ ለመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስትና ማዕከል ሆናለች። ምሥራቹን እስከ ምድር ዳርቻ ለማዳረስ አምላክ በዚያ የሚገኘውን ጉባኤ እንደ መነሻ ተጠቅሞበታል። ለምሳሌ ያህል አንጾኪያ ሐዋርያው ጳውሎስ ላደረጋቸው ፈር ቀዳጅ ሚስዮናዊ ጉዞዎቹ መነሻ ነበረች።

በተመሳሳይ በእኛ ዘመን ተቃውሞ ሲያጋጥም የታየው ቅንዓትና ቆራጥነት ብዙ ሰዎች ምሥራቹን እንዲሰሙና አድናቆታቸውን እንዲገልጹ በማድረጉ ለእውነተኛው ክርስትና መስፋፋት አስተዋጽዖ አበርክቷል። b አንተም ከንጹሕ አምልኮ ጎን ስለቆምህ ተቃውሞ ቢያጋጥምህ ይሖዋ ይህን የፈቀደበት ምክንያት ሊኖረው እንደሚችል አትዘንጋ። እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት የመስማትና ከእሱ ጎን የመሰለፍ አጋጣሚ ሊሰጣቸው ይገባል። አንድ ሰው ትክክለኛውን የእውነት እውቀት እንዲያገኝ ለመርዳት ከአንተ የሚፈለገው ይሖዋን በታማኝነት ማገልገልህን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ብቻ ሊሆን ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ጥርት ባለ ቀን የቆጵሮስ ደሴት በአንጾኪያ ደቡብ ምዕራብ ከሚገኘው የቃስየስ ተራራ ላይ ትታያለች።

b የነሐሴ 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 9⁠ን፤ መስከረም 1999 ንቁ! ገጽ 15-16⁠ን፤ የ1999 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ገጽ 250-2ን ተመልከት።

[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሳውል “ደብዛው ጠፍቶ የነበረባቸው ዓመታት ”

ሳውል በ45 እዘአ ገደማ ወደ አንጾኪያ ከመሄዱ በፊት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ስለ እሱ ለመጨረሻ ጊዜ የተጠቀሰው በኢየሩሳሌም እሱን ለመግደል የተጠነሰሰውን ሴራ ለማክሸፍ ክርስቲያን ወንድሞቹ ወደ ጠርሴስ በላኩት ጊዜ ነበር። (ሥራ 9:​28-30፤ 11:​25) ሆኖም ይህ የሆነው ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በ36 እዘአ ገደማ ነው። ሳውል ደብዛው ጠፋ በሚባልባቸው በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ምን ሲሠራ ነበር?

ሳውል ከኢየሩሳሌም ወደ ሶርያ ከዚያም ወደ ኪልቅያ በሄደ ጊዜ በይሁዳ የሚገኙት ጉባኤዎች “ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፣ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል” ሲባል ሰሙ። (ገላትያ 1:​21-23) ይህ ሪፖርት የሚያመለክተው ከበርናባስ ጋር በአንጾኪያ ያደረገውን የአገልግሎት እንቅስቃሴ ይሆናል። ሆኖም ሳውል ከዚያም በፊት ቢሆን ሥራ እንዳልፈታ አያጠራጥርም። በ49 እዘአ በሶርያና በኪልቅያ ብዙ ጉባኤዎች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል አንዱ በአንጾኪያ የሚገኝ ሲሆን አንዳንዶች የተቀሩት ጉባኤዎች ሳውል ደብዛው ጠፋ ተብሎ በሚታሰብባቸው ዓመታት ያደረገው እንቅስቃሴ ውጤት ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ያስባሉ።​—⁠ሥራ 11:​26፤ 15:​23, 41

አንዳንድ ሃይማኖታዊ ምሁራን በሳውል ሕይወት ውስጥ ተፈታታኝ ችግሮች የገጠሙት በእነዚህ ዓመታት ነው የሚል እምነት አላቸው። ‘የክርስቶስ አገልጋይ’ ሆኖ ሚስዮናዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ መከራ የተፈራረቀበትን ጊዜ ይኸኛው ነው ብሎ መጠቆም ያስቸግራል። (2 ቆሮንቶስ 11:​23-27) አይሁድ ሳውልን አምስት ጊዜ 39 ግርፋት የገረፉት መቼ ነው? ሦስት ጊዜ በዱላ የተደበደበው የት ነው? ‘ብዙ ጊዜ’ ለእስር የተዳረገው የት ነው? በሮም በእስር እንዲቆይ የተደረገው ከጊዜ በኋላ ነበር። ፊልጵስዩስ ሳለ ተደብድቦ ወደ ወኅኒ እንደተጣለ የሚገልጽ አንድ ዘገባ አለን። ሆኖም ሌሎቹስ? (ሥራ 16:​22, 23) አንድ ጸሐፊ ሳውል በዚህ ጊዜ ውስጥ “ተበትነው ባሉ አይሁዳውያን ምኩራብ ውስጥ ስለ ክርስቶስ ይመሰክር የነበረ ሲሆን ይህም ከሃይማኖት መሪዎችና ከመንግሥት ባለሥልጣናት ስደት ሳያስከትልበት አልቀረም” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።

ሳውል አራት ጊዜ የመርከብ አደጋ ቢያጋጥመውም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በዝርዝር የሰፈረው አንዱ ብቻ ነው። ይኸኛውም ቢሆን ያጋጠመው የተፈራረቀበትን መከራ በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በዝርዝር ከጻፈላቸው በኋላ ነበር። (ሥራ 27:​27-44) ስለዚህ ሌሎች ሦስት አደጋዎች የደረሱበት ስለ እሱ ምንም በማይታወቅባቸው የጉዞ ዓመታት ውስጥ ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ አንዱ ወይም ሁሉም የተከናወኑት ሳውል “ደብዛው ጠፍቶ በነበረባቸው ዓመታት” ውስጥ ሳይሆን አይቀርም!

በዚህ ጊዜ ውስጥ የተከናወነ የሚመስለው ሌላው ድርጊት በ⁠2 ቆሮንቶስ 12:​2-5 ላይ ይገኛል። ሳውል እንዲህ ሲል ተናግሯል:- ‘ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፣ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። ወደ ገነት ተነጠቀ፣ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።’ እዚህ ላይ ሳውል ስለ ራሱ እየተናገረ ያለ ይመስላል። ይህን የጻፈው በ55 እዘአ ገደማ ስለሆነ ከ14 ዓመት በፊት መባሉ ወደ 41 እዘአ ይኸውም “ደብዛው ጠፍቶ ነበር ወደ ተባለባቸው ዓመታት” ያደርሰናል።

ይህ ራእይ ለሳውል የተለየ ማስተዋል እንዳስገኘለት አያጠራጥርም። ዓላማው “የአሕዛብ ሐዋርያ” እንዲሆን እሱን ለማዘጋጀት ይሆን? (ሮሜ 11:​13) ራእዩ በአስተሳሰቡ፣ በጻፋቸውና በተናገራቸው ነገሮች ላይ ለውጥ አስከትሎ ይሆን? ሳውል ወደ ክርስትና በተለወጠበትና ወደ አንጾኪያ በተጠራበት ጊዜ መካከል ያሉት ዓመታት ወደፊት ለሚሸከመው ኃላፊነት ለማሰልጠንና እንዲጎለምስ ለማድረግ የዋሉ ዓመታት ይሆኑ? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ ምንም ይሁን ምን በርናባስ በአንጾኪያ ለሚያደርገው የስብከት ሥራ እንዲመጣ ሳውልን ሲጋብዘው ለመብቱ የጓጓው ሳውል ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችል ብቃት እንደነበረው እርግጠኛ መሆን እንችላለን።​—⁠ሥራ 11:​19-26

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሶርያ

ኦሮንተስ

አንጾኪያ

ሴሌውቅያ

ቆጵሮስ

የሜድትራኒያን ባሕር

ኢየሩሳሌም

[ምንጭ]

Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከላይ:- የዛሬይቷ አንጾኪያ

መካከል:- ሴሌውቅያ ከደቡብ አንጻር ስትታይ

ከታች:- የሴሌውቅያ የወደብ ግንብ