በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትንሣኤ ተስፋ መፈጸሙ የማይቀር ነው!

የትንሣኤ ተስፋ መፈጸሙ የማይቀር ነው!

የትንሣኤ ተስፋ መፈጸሙ የማይቀር ነው!

“ሙታን ይነሡ ዘንድ . . . በእግዚአብሔር ዘንድ [ተስፋ] አለኝ።”​—⁠ሥራ 24:​15

1. በትንሣኤ ተስፋ ማድረግ የምንችለው ለምንድን ነው?

 ይሖዋ በትንሣኤ ተስፋ እንድናደርግ የሚያስችሉ አጥጋቢ ምክንያቶች ሰጥቶናል። ሙታን ተነስተው እንደገና በሕይወት እንደሚኖሩ ቃል ገብቶልናል። ስለሆነም በሞት ላንቀላፉት ያለው ዓላማ መፈጸሙ የማይቀር ነው። (ኢሳይያስ 55:​11፤ ሉቃስ 18:​27) እንዲያውም አምላክ ሙታንን ለማስነሣት ኃይል እንዳለው አሳይቷል።

2. የትንሣኤ ተስፋ ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው?

2 አምላክ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ሙታንን ለማስነሣት ባደረገው ዝግጅት ላይ እምነት ማሳደራችን በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜ ሊያጽናናን ይችላል። በተጨማሪም የትንሣኤ ተስፋ መፈጸሙ የማይቀር መሆኑ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ቢሆን በሰማያዊ አባታችን ፊት ጽኑ አቋም ይዘን እንድንመላለስ ሊረዳን ይችላል። ወደ ሕይወት ስለ ተመለሱ ሰዎች የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በምንመረምርበት ጊዜ በትንሣኤ ላይ ያለን ተስፋ መጠናከሩ አይቀርም። እነዚህ ሁሉ ተአምራት ሊከናወኑ የቻሉት ሉዓላዊ ጌታ በሆነው በይሖዋ ኃይል ነው።

ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ

3. በሰራፕታ የምትኖር የአንዲት መበለት ልጅ በሞተበት ጊዜ ኤልያስ ምን የማድረግ ኃይል ተሰጥቶት ነበር?

3 ሐዋርያው ጳውሎስ ከክርስትና ዘመን በፊት የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ስላሳዩት እምነት ባቀረበው ስሜት ቀስቃሽ ትረካ ላይ “ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 11:​35፤ 12:​1) ከእነዚህ ሴቶች አንዷ የከነዓን ከተማ በሆነችው በሰራፕታ የምትኖር ድኻ መበለት ነበረች። የአምላክ ነቢይ የሆነውን ኤልያስን በእንግድነት በመቀበሏ የእሷንና የልጅዋን ሕይወት ሊያጠፋ ይችል በነበረው የረሃብ ወቅት የነበራት ዱቄትና ዘይት በተአምራዊ ሁኔታ ሊበረክትላት ችሏል። ከጊዜ በኋላ የሴትዮዋ ልጅ ሲሞት ኤልያስ አልጋ ላይ አስተኝቶት ከጸለየና ሦስት ጊዜ ከተዘረጋበት በኋላ “አቤቱ አምላኬ ሆይ፣ የዚህ ብላቴና ነፍስ ወደ እርሱ ትመለስ ዘንድ እለምንሃለሁ” ሲል ምልጃ አቀረበ። አምላክ የልጁ ነፍስ ወይም ሕይወት እንዲመለስለት አድርጓል። (1 ነገሥት 17:​8-24) ይህች መበለት ውድ ልጅዋ ዳግም ሕያው በሆነበት በዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመዝግቦ በሚገኘው ትንሣኤ አማካኝነት እምነቷ ሲካስ የተሰማትን ደስታ ገምት!

4. ኤልሳዕ በሱነም ያከናወነው ተአምር ምንድን ነው?

4 ሙታንዋን በትንሣኤ የተቀበለች ሌላዋ ሴት ደግሞ በሱነም ከተማ ትኖር የነበረችው ናት። የአንድ አረጋዊ ሚስት የሆነችው ይህች ሴት ለነቢዩ ኤልሳዕና ለሎሌው ደግነት አሳየቻቸው። ይህን በማድረጓም ወንድ ልጅ በማግኘት ተክሳለች። ሆኖም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ነቢዩን ወደ ቤቷ አስጠራችው፤ እዚያ ሲደርስ ልጁን ሞቶ አገኘው። ኤልሳዕ ከጸለየና አንዳንድ ነገር ካደረገለት በኋላ “[ቀስ በቀስ] የሕፃኑ ገላ ሞቀ።” “ልጁም ሰባት ጊዜ ካስነጠሰው በኋላ ዐይኖቹን ከፈተ። [የ1980 ትርጉም ]” ይህ ትንሣኤ እናትየውንም ሆነ ልጅዋን በጣም እንዳስደሰታቸው ምንም አያጠራጥርም። (2 ነገሥት 4:​8-37፤ 8:​1-6) ይሁን እንጂ ያለመሞትን አጋጣሚ በሚከፍትላቸው ‘በሚበልጠው ትንሣኤ’ አማካኝነት በምድር ላይ ለመኖር ሲነሡ ምንኛ የላቀ ደስታ ይሰማቸው ይሆን! ይህ አፍቃሪ ለሆነው የትንሣኤ አምላክ ለይሖዋ ምስጋና እንድናቀርብ በእጅጉ ይገፋፋናል!​—⁠ዕብራውያን 11:​35

5. ኤልሳዕ ከሞተ በኋላም ተአምር የፈጸመው እንዴት ነው?

5 ኤልሳዕ ከሞተና ከተቀበረ በኋላ እንኳ አምላክ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት አጥንቱ ኃይል እንዲኖረው አድርጓል። እንዲህ እናነባለን:- “ሰዎችም [የተወሰኑ እስራኤላውያን] አንድ ሰው ሲቀብሩ [ሞዓባውያን] አደጋ ጣዮችን አዩ፣ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዬው ድኖ በእግሩ ቆመ።” (2 ነገሥት 13:​20, 21) ይህ ሰው ምን ያህል ተደንቆና ተደስቶ ይሆን! ከማይታጠፈው የይሖዋ አምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ የምናፈቅራቸው ሰዎች ከሞት ሲነሡ የምናገኘውን ደስታ ገምት!

የአምላክ ልጅ ሙታንን አስነስቷል

6. ኢየሱስ በናይን ከተማ አቅራቢያ ያከናወነው ተአምር ምን ነበር? ይህስ እኛን ሊነካን የሚችለው እንዴት ነው?

6 የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙታን ትንሣኤ ሲያገኙ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይዘው ሊነሡ እንደሚችሉ እንድናምን የሚያደርጉ አጥጋቢ ምክንያቶች ሰጥቶናል። በናይን ከተማ አቅራቢያ የተከሰተ አንድ ገጠመኝ እንዲህ ዓይነቱ ተአምር አምላክ በሚሰጠው ኃይል አማካኝነት ሊከናወን እንደሚችል እንድንገነዘብ ይረዳናል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ የአንድ ወጣት አስከሬን ተሸክመው ወደ ቀብር የሚሄዱ ለቀስተኞችን ከከተማ ውጪ አገኘ። ወጣቱ የአንዲት መበለት ብቸኛ ልጅ ነበር። ኢየሱስ “አታልቅሽ” አላት። ከዚያም ቃሬዛውን ነካና “አንተ ጎበዝ፣ እልሃለሁ፣ ተነሣ” አለው። በዚህ ጊዜ ቀና ብሎ ተቀመጠ፤ መናገርም ጀመረ። (ሉቃስ 7:​11-15) ይህ ተአምር የትንሣኤ ተስፋ መፈጸሙ እንደማይቀር ያለንን ጽኑ እምነት እንደሚያጠናክርልን የታወቀ ነው።

7. ከኢያኢሮስ ሴት ልጅ ጋር በተያያዘ የተከናወነው ነገር ምንድን ነው?

7 በቅፍርናሆም የሚገኝ የአንድ ምኩራብ አለቃ ከሆነው ከኢያኢሮስ ጋር በተያያዘ የተፈጸመውን ሁኔታም ተመልከት። ለሞት ተቃርባ የነበረችውን የሚወዳትን የ12 ዓመት ሴት ልጁን መጥቶ እንዲያድናት ኢየሱስን ለመነው። ብዙም ሳይቆይ ልጅትዋ መሞቷን ሰሙ። ኢየሱስ በሐዘን የተደቆሰውን ኢያኢሮስን እምነት እንዲያሳይ በማበረታታት ሰዎች ተሰብስበው ያለቅሱ ወደነበረበት ወደ ኢያኢሮስ ቤት አብሮት ሄደ። ኢየሱስ “ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” ሲላቸው ሳቁበት። በእርግጥም ልጅቷ ሞታለች፤ ሆኖም ኢየሱስ ሰዎች ከከባድ እንቅልፍ ሊቀሰቀሱ እንደሚችሉ ሁሉ ወደ ሕይወት ሊመለሱ እንደሚችሉም ማሳየት ፈልጎ ነበር። የልጅቷን እጅ ይዞ “አንቺ ብላቴና፣ ተነሺ” አላት። ልጅቷ ወዲያውኑ ተነስታ ቆመች፤ ‘ወላጆችዋም እጅግ ተገረሙ።’ (ማርቆስ 5:​35-43፤ ሉቃስ 8:​49-56) የቤተሰብ አባላት በሞት የተለዩአቸው የሚያፈቅሯቸው ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ከሞት ተነስተው በሕይወት ሲኖሩ ‘እንደሚገረሙ’ ምንም አያጠራጥርም።

8. ኢየሱስ በአልዓዛር መቃብር ያከናወነው ነገር ምንድን ነው?

8 ኢየሱስ ወደ አልዓዛር መቃብር ሄዶ መቃብሩ ላይ የነበረውን ድንጋይ እንዲያነሱ ባደረገበት ጊዜ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀናት ሆኖት ነበር። ኢየሱስ በዚያ የነበሩ ሰዎች አምላክ በሚሰጠው ኃይል እንደሚመካ እንዲያውቁ ሲል በሕዝብ ፊት ከጸለየ በኋላ ድምፁን ከፍ አድርጎ “አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና” አለ። አልዓዛርም ከመቃብር ወጣ! እጅና እግሩ በመግነዝ እንደተገነዘ፣ ፊቱም በጨርቅ እንደተሸፈነ ነበር። ኢየሱስ “ፍቱትና ይሂድ ተዉት” አላቸው። የአልዓዛርን እህቶች ማርያምንና ማርታን ለማጽናናት በቦታው ተገኝተው የነበሩ ብዙዎች ይህን ተአምር በማየታቸው በኢየሱስ አመኑ። (ዮሐንስ 11:​1-45) ይህ ዘገባ የምታፈቅራቸው ሰዎች አምላክ በሚያዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ ከሞት ሊነሡ እንደሚችሉ ተስፋ አይሰጥህምን?

9. አሁን ኢየሱስ ሙታንን ማስነሣት ይችላል ብለን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

9 አጥማቂው ዮሐንስ ታስሮ በነበረበት ጊዜ ኢየሱስ “ዕውሮች ያያሉ . . . ሙታንም ይነሣሉ” የሚል የሚያበረታታ መልእክት ልኮለት ነበር። (ማቴዎስ 11:​4-6) ኢየሱስ በምድር በነበረበት ወቅት ሙታንን ስላስነሣ በአምላክ የተሾመ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር በሆነበት ጊዜ ደግሞ ሙታንን ማስነሳት እንደሚችል ምንም አያጠራጥርም። ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት” በመሆኑ በቅርቡ ‘በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን ሰምተው እንደሚወጡ’ ማወቁ ምንኛ ያጽናናል!​—⁠ዮሐንስ 5:​28, 29፤ 11:​25

ተስፋችንን የሚያጠናክሩ ሌሎች ትንሣኤዎች

10. ሐዋርያት እንዳከናወኗቸው ከተገለጹት ትንሣኤዎች የመጀመሪያውን እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?

10 ኢየሱስ ሐዋርያቱን የመንግሥቱ ሰባኪዎች አድርጎ ሲልካቸው “ሙታንን አስነሡ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:​5-8) እርግጥ ነው፣ ይህን ለማድረግ በአምላክ ኃይል መታመን ነበረባቸው። በ36 እዘአ በኢዮጴ ትኖር የነበረች አምላካዊ ፍርሃት ያላት ዶርቃ (ጣቢታ) የተባለች ሴት በሞት አንቀላፋች። ዶርቃ ችግረኛ ለሆኑ መበለቶች ልብስ መስፋትን ጨምሮ በምታከናውናቸው መልካም ተግባሮች ትታወቅ የነበረ በመሆኑ መበለቶቹ በእሷ ሞት ምክንያት ጥልቅ ሐዘን ተሰማቸው። ደቀ መዛሙርቱ አስከሬኗን ለቀብር ካዘጋጁ በኋላ መጥቶ እንዲያጽናናቸው ሳይሆን አይቀርም ለሐዋርያው ጴጥሮስ መልእክት ላኩበት። (ሥራ 9:​32-38) ጴጥሮስ በሰገነቱ ላይ ካለው ክፍል ሁሉንም አስወጥቶ ከጸለየ በኋላ “ጣቢታ ሆይ፣ ተነሺ” አላት። ዓይንዋን ገልጣ ተቀመጠች፤ ጴጥሮስም እጁን ሰጥቶ አስነሣት። ሐዋርያት ካከናወኗቸው ትንሣኤዎች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ ተመዝግቦ የሚገኘው ይህ ትንሣኤ ብዙዎችን አማኞች አድርጓል። (ሥራ 9:​39-42) እኛም በትንሣኤ ተስፋ እንድናደርግ ተጨማሪ ምክንያት ይሆነናል።

11. መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የመጨረሻው ትንሣኤ የትኛው ነው?

11 መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የመጨረሻው ትንሣኤ በጢሮአዳ የተከናወነው ነው። ጳውሎስ በሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው እዚያ ባደረገው ቆይታ ንግግሩን እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አራዘመ። አውጤኪስ የሚባል አንድ ወጣት በድካም በመሸነፉና ምናልባትም ክፍሉ ውስጥ የበሩት በርካታ ፋኖሶች በሚፈጥሩት ሙቀት እና በስብሰባው ቦታ በነበረው የተጨናነቀ ሁኔታ የተነሳ እንቅልፍ ስለጣለው ከሦስተኛው ፎቅ መስኮት ወደቀ። ሲያነሱት እንዲሁ ሕሊናውን ስቶ ሳይሆን “ሞቶ” ነበር። ጳውሎስ አውጤኪስ ላይ ወድቆ አቀፈውና ከበውት የነበሩትን ሰዎች “ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ” አላቸው። ጳውሎስ የልጁ ሕይወት እንደተመለሰለት መናገሩ ነበር። በቦታው የነበሩት ሰዎች “እጅግም ተጽናኑ።” (ሥራ 20:​7-12) በዛሬው ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች በፊት አብረዋቸው በአምላክ አገልግሎት ይሳተፉ የነበሩ ሰዎች የትንሣኤ ተስፋ እንደሚፈጸምላቸው በማወቃቸው ታላቅ ማጽናኛ ያገኛሉ።

ትንሣኤ​—⁠ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ተስፋ

12. ጳውሎስ በሮማዊው ገዥ በፊልክስ ፊት በቀረበበት ጊዜ ምን ጽኑ እምነት እንዳለው ገልጿል?

12 ጳውሎስ ሮማዊው ገዥ ፊልክስ በተገኘበት ለፍርድ በቀረበበት ወቅት እንዲህ ሲል መሥክሯል:- “በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ፣ . . . ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።” (ሥራ 24:​14, 15) እንደ “ሕጉ” ያሉት የአምላክ ቃል ክፍሎች ስለ ሙታን መነሣት የሚጠቅሱት እንዴት ነው?

13. አምላክ የመጀመሪያውን ትንቢት ሲናገር የትንሣኤን ተስፋ በተዘዋዋሪ ጠቅሷል ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?

13 አምላክ በኤደን የመጀመሪያውን ትንቢት ሲናገር ትንሣኤን በተዘዋዋሪ መንገድ ጠቅሷል። አምላክ ‘በቀደመው እባብ’ በሰይጣን ዲያብሎስ ላይ ፍርድ ሲያስተላልፍ እንዲህ ብሏል:- “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።” (ራእይ 12:​9፤ ዘፍጥረት 3:​14, 15) የሴቲቱን ዘር ሰኮና መቀጥቀጥ ኢየሱስ ክርስቶስን መግደል ማለት ነው። ይህ ከተፈጸመ በኋላ ዘሩ የእባቡን ጭንቅላት መቀጥቀጥ ያለበት ከሆነ ክርስቶስ ከሞት መነሣት አለበት ማለት ነው።

14. ይሖዋ ‘የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ ያልሆነው’ እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ሙታን እንዲነሡ ግን ሙሴ ደግሞ በቍጥቋጦው ዘንድ ጌታን የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ በማለቱ አስታወቀ፤ ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፣ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።” (ሉቃስ 20:​27, 37, 38፤ ዘጸአት 3:​6) አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ሞተዋል። ይሁን እንጂ አምላክ እነሱን ለማስነሳት ያለው ዓላማ መፈጸሙ የማይቀር ከመሆኑ የተነሳ በእሱ ዘንድ ሕያው የሆኑ ያህል ነው።

15. አብርሃም በትንሣኤ እንዲያምን የሚያስችል ምክንያት የነበረው ለምንድን ነው?

15 አብርሃምና ሚስቱ ሣራ በጣም አርጅተውና ልጅ በመውለድ ችሎታቸው ረገድ ሙት በነበሩበት ጊዜ አምላክ በተአምራዊ መንገድ የመውለድ ችሎታቸውን ስለመለሰላቸው አብርሃም በትንሣኤ ተስፋ የሚያደርግበት ምክንያት ነበረው። ይህ ከትንሣኤ የማይተናነስ ነበር። (ዘፍጥረት 18:​9-11፤ 21:​1-3፤ ዕብራውያን 11:​11, 12) አብርሃም ልጁ ይስሐቅ 25 ዓመት ገደማ ሲሆነው አምላክ መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርበው አዘዘው። ይሁን እንጂ አብርሃም ይስሐቅን ሊያርደው ሲል የይሖዋ መልአክ ከለከለው። አብርሃም “እግዚአብሔር [ይስሐቅን] ከሙታን እንኳ ሊያነሣው እንዲቻለው አስቦአልና፣ ከዚያም ደግሞ በምሳሌ አገኘው።”​—⁠ዕብራውያን 11:​17-19፤ ዘፍጥረት 22:​1-18

16. አብርሃም በሞት አንቀላፍቶ ምን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል?

16 አብርሃም ተስፋ በተሰጠበት ዘር ማለትም በመሲሑ አገዛዝ ሥር በሚከናወነው ትንሣኤ ተስፋ አድርጓል። የአምላክ ልጅ ሰው ከመሆኑ በፊት የአብርሃምን እምነት ተመልክቶ ነበር። ከዚህ የተነሳ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በመጣ ጊዜ አይሁዳውያንን “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ” ሲል ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 8:​56-58፤ ምሳሌ 8:​30, 31) በአሁኑ ጊዜ አብርሃም በአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ሥር በምድር ላይ ለመኖር የሚነሳበትን ጊዜ እየተጠባበቀ በሞት አንቀላፍቶ ይገኛል።​—⁠ዕብራውያን 11:​8-10, 13

በሕጉና በመዝሙራት ውስጥ የሚገኝ ማስረጃ

17. ‘በሕጉ ላይ የተገለጹት ነገሮች’ የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚያመለክቱት እንዴት ነው?

17 ጳውሎስ በትንሣኤ ላይ የነበረው ተስፋ ‘በሕጉ ከተገለጸው ነገር’ ጋር የሚስማማ ነበር። አምላክ እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “የእናንተን መከር በኩራት ነዶ ወደ ካህኑ አምጡ። እርሱም [በኒሳን 16] ነዶውን በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምርላችሁ ይወዝውዘው።” (ዘሌዋውያን 23:​9-14) ጳውሎስ ይህን ሕግ በአእምሮው ይዞ ሳይሆን አይቀርም “ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል” ሲል ጽፏል። ኢየሱስ “በኩራት” ሆኖ ከሞት የተነሣው ኒሳን 16, 33 እዘአ ነው። ከዚያም በሥልጣኑ በሚገኝበት ወቅት ‘በሁለተኛ ደረጃ’ ትንሣኤ የሚያገኙ ሌሎችም የሚኖሩ ሲሆን እነዚህም በመንፈስ የተቀቡ ተከታዮቹ ናቸው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​20-23፤ 2 ቆሮንቶስ 1:​21፤ 1 ዮሐንስ 2:​20, 27

18. ጴጥሮስ የኢየሱስ ትንሣኤ በመዝሙራት ላይ አስቀድሞ እንደተነገረ የገለጸው እንዴት ነው?

18 መዝሙራትም ትንሣኤን የሚደግፍ ሐሳብ ይዘዋል። በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ መዝሙር 16:​8-11ን ጠቅሶ እንዲህ ብሏል:- “ዳዊት ስለ [ክርስቶስ] እንዲህ ይላልና:- ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፣ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፣ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፣ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፣ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም።” ጴጥሮስ አክሎ እንዲህ ብሏል:- “[ዳዊት] ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፣ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው።”​—⁠ሥራ 2:​25-32

19, 20. ጴጥሮስ ከ⁠መዝሙር 118:​22 ጠቅሶ የተናገረው መቼ ነው? ይህስ ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

19 ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ጴጥሮስ ሳንሄድሪን ፊት በቀረበ ጊዜ በድጋሚ ከመዝሙራት ጠቅሶ ተናግሯል። ሐዋርያው አንድን አንካሳ ለማኝ እንዴት ሊያድን እንደቻለ ሲጠየቅ እንዲህ ብሏል:- “እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደኅና ሆኖ በፊታችሁ እንደ ቆመ፣ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን። እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ [ኢየሱስ] ነው። መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።”​—⁠ሥራ 4:​10-12

20 እዚህ ላይ ጴጥሮስ ከ⁠መዝሙር 118:​22 ጠቅሶ የተናገረ ሲሆን ሐሳቡ በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ላይ ተፈጻሚ እንደሆነ ተናግሯል። አይሁዳውያን በሃይማኖታዊ መሪዎቻቸው ገፋፊነት ኢየሱስን ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል። (ዮሐንስ 19:​14-18፤ ሥራ 3:​14, 15) ‘ግንበኞቹ ድንጋዩን መናቃቸው’ የክርስቶስን ሞት ያስከተለ ቢሆንም እንኳ ‘ድንጋዩ የማዕዘን ራስ መሆኑ’ ክርስቶስ ተነስቶ በሰማይ መንፈሳዊ ክብር መላበሱን ያመለክታል። መዝሙራዊው እንደተነበየው ‘ይህ የሆነው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።’ (መዝሙር 118:​23) ‘ድንጋዩን’ የማዕዘን ራስ ማድረግ ክርስቶስን ንጉሥ አድርጎ በመሾም ከፍ ከፍ ማድረግን የሚጨምር ነው።​—⁠ኤፌሶን 1:​19, 20

በትንሣኤ ተስፋ መጽናናት

21, 22. ኢዮብ 14:​13-15 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው መሠረት ኢዮብ የገለጸው ተስፋ ምንድን ነው? ይህ በዛሬው ጊዜ ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ሊያጽናናቸው የሚችለው እንዴት ነው?

21 ከሞት የተነሣ ሰው አይተን ባናውቅም እንኳ የትንሣኤን መኖር የሚያረጋግጡልን አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ዘገባዎችን ተመልክተናል። ከዚህ የተነሳ ጻድቁ ሰው ኢዮብ የገለጸው ተስፋ ሊኖረን ይችላል። በሥቃይ ላይ በነበረበት ወቅት እንዲህ ሲል ተማጽኗል:- “በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! . . . ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ! በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? . . . በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፤ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር።” (ኢዮብ 14:​13-15) አምላክ ኢዮብን ከሞት ለማስነሣት በእጅጉ በመጓጓት ‘የእጁን ሥራ ይመኛል።’ ይህ ትልቅ ተስፋ ያሳድርብናል!

22 እንደ ኢዮብ ሁሉ ለአምላክ ያደረ አንድ የቤተሰብ አባል በጠና ሊታመም፣ አልፎ ተርፎም ጠላት በሆነው ሞት ሊሸነፍ ይችላል። ኢየሱስ በአልዓዛር ሞት እንዳለቀሰ ሁሉ ሐዘንተኛውም ያለቅስ ይሆናል። (ዮሐንስ 11:​35) ሆኖም አምላክ በአእምሮው የያዛቸውን ሰዎች እንደሚጠራቸውና እነሱም እንደሚመልሱለት ማወቁ ምንኛ ያጽናናል! ሳይታመሙና ጉዳት ሳያገኛቸው በጥሩ ጤንነት ከረጅም ጉዞ የተመለሱ ያህል ይሆናል።

23. አንዳንዶች በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያላቸውን እምነት የገለጹት እንዴት ነው?

23 በአንዲት ታማኝ አረጋዊት ክርስቲያን ሞት ምክንያት ወንድሞች እንዲህ ብለው ጽፈዋል:- “በእናትሽ ሞት ምክንያት የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን ልንገልጽልሽ እንወዳለን። ሰውነታቸውና ኃይላቸው ታድሶ እንደገና የምንገናኝበት ጊዜ ሩቅ አይደለም!” ልጃቸውን በሞት ያጡ ወላጆች እንዲህ ብለዋል:- “ጄሰን ከሞት የሚነሣበትን ጊዜ በታላቅ ጉጉት እንጠባበቃለን! ተነስቶ ዙሪያውን ሲመለከት ለረጅም ጊዜ በጉጉት ሲጠባበቀው የነበረውን ገነት ያያል። . . . እሱን የምናፈቅረው ሰዎችም በዚያ እንድንገኝ ከፍተኛ ማበረታቻ ሆኖናል!” አዎን፣ የትንሣኤ ተስፋ መፈጸሙ የማይቀር በመሆኑ ምንኛ አመስጋኝ መሆን ይኖርብናል!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• አምላክ ሙታንን ለማስነሣት ባደረገው ዝግጅት ላይ እምነት ማሳደራችን እንዴት ሊጠቅመን ይችላል?

• በትንሣኤ ተስፋ እንድናደርግ የሚያስችሉን ቅዱስ ጽሑፉ ላይ የሰፈሩ የትኞቹ ክንውኖች ናቸው?

• ትንሣኤ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ተስፋ ነው ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?

• ሙታንን በተመለከተ ምን የሚያጽናና ተስፋ ሊኖረን ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤልያስ ከይሖዋ ባገኘው ኃይል የአንዲት መበለት ልጅ ዳግመኛ ነፍስ እንዲዘራ አድርጓል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የኢያኢሮስን ልጅ ከሞት ሲያስነሣ ወላጆቿ እጅግ ተገርመው ነበር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ ከሞት መነሣቱን በድፍረት መሥክሯል