በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትንሣኤ ተስፋ ኃይል አለው

የትንሣኤ ተስፋ ኃይል አለው

የትንሣኤ ተስፋ ኃይል አለው

‘[ኢየሱስ ክርስቶስን] እና የትንሣኤውን ኃይል ለማወቅ ስል ሁሉን ተጎዳሁ።’​—⁠ፊልጵስዩስ 3:​8-10

1, 2. (ሀ) ከዓመታት በፊት አንድ ቄስ ትንሣኤን የገለጹት ምን ብለው ነው? (ለ) ትንሣኤ የሚከናወነው በምን መንገድ ይሆናል?

 በ1890ዎቹ መጀመሪያ በዩ ኤስ ኤ፣ ኒው ዮርክ፣ ብሩክሊን ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አንድ ቄስ ስላቀረቡት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ስብከት ዘግበው ነበር። ቄሱ በሰጡት ስብከት ላይ ትንሣኤ በእሳትም ሆነ በአደጋ፣ አውሬ በልቶትም ሆነ ማዳበሪያ ሆኖ የጠፋን የሰው አካል አጥንቶችና ሥጋ ባጠቃላይ እንደገና ማሰባሰብንና ሕይወት መስጠትን እንደሚያጠቃልል ተናግረዋል። ሰባኪው የ24 ሰዓት ርዝመት ባለው አንድ ቀን በቢልዮን በሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎች እጆች፣ ክንዶች፣ እግሮች፣ ጣቶች፣ አጥንቶች፣ ጅማቶችና ቆዳ ሰማዩን እንደሚያጨልሙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። እነዚህ የአካል ክፍሎች የዚያኑ አካል ሌሎች ክፍሎች ለማግኘት ፍለጋ ያደርጋሉ። ከዚያም በእነዚህ ከሞት በተነሡ አካሎች ውስጥ ለማደር ነፍሶች ከሰማይና ከሲኦል ይመጣሉ።

2 ትንሣኤ የሚከናወነው የመጀመሪያዎቹን አተሞች እንደገና በማደራጀት ነው ማለት የማይመስል ነገር ከመሆኑም በላይ የሰው ነፍስ ሟች ነው። (መክብብ 9:​5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:​4) የትንሣኤ አምላክ የሆነው ይሖዋ የሰው አካል መጀመሪያ የተገነባበትን ቁስ አካል እንደገና መገጣጠም አያስፈልገውም። ከሞት ለተነሡ ሰዎች አዲስ አካል ሊሰጣቸው ይችላል። ይሖዋ ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሙታን ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይዘው እንዲነሡ የማድረግ ኃይል ሰጥቶታል። (ዮሐንስ 5:​26) ከዚህ የተነሳ ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል” ብሏል። (ዮሐንስ 11:​25, 26) እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ነው! ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነን ፈተናዎችን በጽናት እንድናሳልፍና ሞትን እንኳ ሳይቀር እንድንጋፈጥ ብርታት ይሰጠናል።

3. ጳውሎስ ትንሣኤን በተመለከተ የመከላከያ ሐሳብ ማቅረብ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

3 ትንሣኤ ግሪካዊው ፈላስፋ ፕላቶ ከነበረው አመለካከት ማለትም ሰው የማይሞት ነፍስ አለው ከሚለው ትምህርት ጋር አይጣጣምም። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴና አርዮስፋጎስ ታዋቂ ለነበሩ ግሪካውያን ኢየሱስን በተዘዋዋሪ ጠቅሶ አምላክ ከሞት እንዳስነሣው ሲናገር የተከሰተው ነገር ምንድን ነው? “የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኩሌቶቹ አፌዙበት” ሲል ዘገባው ይናገራል። (ሥራ 17:​29-34) ከሞት የተነሣውን ኢየሱስ ክርስቶስን የተመለከቱ ብዙዎች ገና በሕይወት የነበሩ ሲሆን ቢፌዝባቸውም እንኳ ስለ ትንሣኤው መሥክረዋል። ሆኖም በቆሮንቶስ ጉባኤ ይሰበሰቡ የነበሩ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ትንሣኤውን ክደዋል። በዚህ ምክንያት ጳውሎስ በ⁠1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ላይ ይህን ክርስቲያናዊ ትምህርት በተመለከተ ጠንካራ የመከላከያ ሐሳብ አቅርቧል። ያቀረባቸውን የመከራከሪያ ሐሳቦች በጥልቀት ማጥናታችን የትንሣኤ ተስፋ መፈጸሙ እንደማይቀርና ኃይል ያለው መሆኑን ያረጋግጥልናል።

የኢየሱስን ትንሣኤ የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ

4. የኢየሱስን ትንሣኤ በተመለከተ ጳውሎስ ምን የዓይን ምሥክርነት ማስረጃ አቅርቧል?

4 ጳውሎስ የመከላከያ ሐሳቡን ምን ብሎ እንደጀመረ አስተውል። (1 ቆሮንቶስ 15:​1-11) የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አማኞች የሆኑት አላንዳች ዓላማ ካልሆነ በስተቀር ደኅንነት የሚያስገኘውን ምሥራች አጥብቀው መያዛቸው አይቀርም። ክርስቶስ ለኃጢአታችን ሲል ሞቶ ከተቀበረ በኋላ ተነሥቷል። እንዲያውም ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለኬፋ (ጴጥሮስ)፣ “በኋላም ለአሥራ ሁለቱ” ታይቷል። (ዮሐንስ 20:​19-23) ‘ሂዱና ደቀ መዛሙርት አድርጉ’ ብሎ ባዘዛቸው ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፣ 500 የሚያክሉ ሰዎች አይተውታል። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ታማኝ ሐዋርያቱ በሙሉ እንዳዩት ሁሉ ያዕቆብም አይቶታል። (ሥራ 1:​6-11) ኢየሱስ በደማስቆ አቅራቢያ ‘እንደ ጭንጋፍ ለሆነው’ ለሳውል ታይቷል። ይህም ሳውል ለመንፈሳዊ ሕይወት ትንሣኤ ያገኘ ያህል ነበር። (ሥራ 9:​1-9) የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጳውሎስ የሰበከላቸውን ምሥራች በመቀበላቸው አማኞች ሊሆኑ ችለዋል።

5. በ⁠1 ቆሮንቶስ 15:​12-19 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው መሠረት ጳውሎስ ያቀረበው የመከላከያ ሐሳብ ምንድን ነው?

5 የጳውሎስን የመከራከሪያ ሐሳብ በጥሞና አጢን። (1 ቆሮንቶስ 15:​12-19) የዓይን ምሥክሮች ክርስቶስ ከሞት መነሣቱን ከሰበኩ እንዴት ትንሣኤ የለም ሊባል ይቻላል? ኢየሱስ ከሞት ካልተነሣ ስብከታችንም ሆነ እምነታችን ከንቱ ነው፤ እንዲሁም ክርስቶስን ከሞት አስነስቶታል በማለታችን በአምላክ ላይ የምንመሠክር ሐሰተኞች ነን ማለት ነው። ሙታን የማይነሡ ከሆነ ‘እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችን አለን፤’ በክርስቶስ ያንቀላፉትም ጠፍተዋል ማለት ነው። ከዚህም በላይ “በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።”

6. (ሀ) ጳውሎስ የኢየሱስ ትንሣኤ እርግጠኛ መሆኑን ሲገልጽ ምን ብሏል? (ለ) “የመጨረሻው ጠላት” ምንድን ነው? የሚሻረውስ እንዴት ነው?

6 ጳውሎስ የኢየሱስ ትንሣኤ የተረጋገጠ መሆኑን ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:​20-28) ክርስቶስ በሞት ላንቀላፉት “በኩራት” እስከሆነ ድረስ ሌሎችም ከሞት ይነሣሉ። ሰው የነበረው አዳም ባለመታዘዙ ምክንያት ሞት እንደመጣ ሁሉ ትንሣኤ የሚገኘውም ሰው በሆነው በኢየሱስ በኩል ነው። የክርስቶስ የሆኑት በመገኘቱ ወቅት ይነሣሉ። ክርስቶስ የአምላክን ሉዓላዊነት የሚገዳደርን ‘አለቅነት ሁሉና ሥልጣን ሁሉ ኃይልም የሚሽር’ ሲሆን ይሖዋ ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግለት ድረስ ንጉሥ ሆኖ ይገዛል። ሌላው ቀርቶ ከአዳም የተወረሰው “የኋለኛው ጠላት” ሞት የኢየሱስ መሥዋዕት በሚያስገኘው ጥቅም አማካኝነት ይሻራል። ከዚያም ክርስቶስ መንግሥቱን ለአምላኩና ለአባቱ አሳልፎ በመስጠት “እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ . . . ሁሉን ላስገዛለት” ራሱን ያስገዛል።

ስለ ሙታን መጠመቅ?

7. “ስለ ሙታን የሚጠመቁት” እነማን ናቸው? ይህስ ለእነሱ ምን ማለት ይሆናል?

7 የትንሣኤ ተቃዋሚዎች “ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:​29) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በግለሰብ ደረጃ ተምረውና አምነው መጠመቅ ያለባቸው በመሆኑ ጳውሎስ ሕያዋን ለሙታን ሲሉ መጠመቅ አለባቸው ማለቱ አልነበረም። (ማቴዎስ 28:​19, 20፤ ሥራ 2:​41) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ስለ ሙታን የሚጠመቁት’ ወደ ሞት እና ትንሣኤ በሚመራው የሕይወት ጎዳና ውስጥ በመግባት ነው። ይህ ዓይነቱ ጥምቀት የሚጀምረው የአምላክ መንፈስ በውስጣቸው የሰማያዊ ሕይወት ተስፋ በሚያሳድርባቸው ጊዜ ሲሆን የሚያበቃው ደግሞ በሰማይ የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት ለማግኘት ከሞት በሚነሡበት ጊዜ ነው።​—⁠ሮሜ 6:​3-5፤ 8:​16, 17፤ 1 ቆሮንቶስ 6:​14

8. ክርስቲያኖች ሰይጣንና አገልጋዮቹ ቢገድሏቸው እንኳ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይችላሉ?

8 የጳውሎስ ቃላት እንደሚያሳዩት የትንሣኤ ተስፋ ክርስቲያኖች የመንግሥቱን ስብከት ሥራ ለማከናወን ሲሉ በየዕለቱ የሚያጋጥማቸውን አደጋና ሞት እንዲጋፈጡ ያስችላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:​30, 31) ይሖዋ፣ በሰይጣን እና በአገልጋዮቹ እጅ እንዲገደሉ ከፈቀደ ከሞት ሊያስነሣቸው እንደሚችል ያውቃሉ። ዘላለማዊ ጥፋት በሚያመለክተው በገሃነም ነፍሳቸውን ወይም ሕይወታቸውን ማጥፋት የሚችለው አምላክ ብቻ ነው።​—⁠ሉቃስ 12:​5

ንቁ የመሆን አስፈላጊነት

9. የትንሣኤ ተስፋ በሕይወታችን ውስጥ ብርታት የሚሰጥ ኃይል እንዲሆን ከተፈለገ ማስወገድ ያለብን ነገር ምንድን ነው?

9 የትንሣኤ ተስፋ ጳውሎስን አበረታቶታል። ጳውሎስ በኤፌሶን በነበረበት ወቅት ጠላቶቹ ከአራዊት ጋር እንዲታገል ወደ ትርዒት ማሳያ ሜዳ ሳያስገቡት አይቀርም። (1 ቆሮንቶስ 15:​32) ይህ ነገር ቃል በቃል ተፈጽሞ ከነበረ አምላክ ዳንኤልን ከአንበሳ አፍ እንዳዳነው ሁሉ እሱንም አድኖታል ማለት ነው። (ዳንኤል 6:​16-22፤ ዕብራውያን 11:​32, 33) ጳውሎስ በትንሣኤ ተስፋ ያደርግ ስለነበር በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት ከሃዲ አይሁዳውያን የያዙት ዓይነት አመለካከት አልተከተለም። በዚያ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን “ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ” ብለዋል። (ኢሳይያስ 22:​13) የትንሣኤ ተስፋ እንደ ጳውሎስ ሁሉ በእኛም ሕይወት ውስጥ አበረታች የሆነ ኃይል እንዲኖረው ከተፈለገ እንዲህ ዓይነት ጤናማ ያልሆነ መንፈስ ካላቸው ሰዎች መራቅ አለብን። ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።” (1 ቆሮንቶስ 15:​33) እርግጥ ነው፣ ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በተለያዩ የሕይወት ዘርፎች ላይ ሊሠራ ይችላል።

10. በትንሣኤ ላይ ያለን ተስፋ ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

10 ጳውሎስ ትንሣኤን የሚጠራጠሩ ሰዎችን እንዲህ ብሏቸዋል:- “በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 15:​34) በዚህ ‘የፍጻሜ ዘመን፣’ ስለ አምላክ እና ስለ ክርስቶስ ካለን ትክክለኛ እውቀት ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ አለብን። (ዳንኤል 12:​4፤ ዮሐንስ 17:​3) የትንሣኤ ተስፋችንን ሕያው አድርጎ የሚያቆይልን ይህ ነው።

ከሞት የሚነሡት ምን ዓይነት አካል ይዘው ነው?

11. ጳውሎስ የቅቡዓን ክርስቲያኖችን ትንሣኤ በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?

11 በመቀጠል ጳውሎስ ለተወሰኑ ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 15:​35-41) ምናልባት አንድ ሰው በትንሣኤ ላይ ጥርጣሬ ለመዝራት በሚያደርገው ጥረት “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ?” ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። ጳውሎስ አፈር ላይ የተዘራ ዘር ወደ ቡቃያነት በሚለወጥበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንደሚሞት ገልጿል። በተመሳሳይም በመንፈስ የተወለደ ሰው መሞት አለበት። አንድ ተክል ከአንድ ዘር አዲስ አካል ይዞ እንደሚወጣ ሁሉ በትንሣኤ የሚነሣው የአንድ ቅቡዕ ክርስቲያን አካልም ከሰብዓዊ አካል የተለየ ነው። ከመሞቱ በፊት የነበረው ዓይነት ሰው ቢሆንም በሰማይ ለመኖር የሚያስችል መንፈሳዊ አካል ያለው አዲስ ፍጥረት ሆኖ ይነሣል። በምድር ለመኖር ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች ደግሞ ሰብዓዊ አካል ለብሰው እንደሚነሡ ግልጽ ነው።

12. “ሰማያዊ አካል” እና “ምድራዊ አካል” የሚሉት መግለጫዎች ምን ያመለክታሉ?

12 ጳውሎስ እንደተናገረው የሰው ሥጋ ከእንስሳት ሥጋ ይለያል። የእንስሳ ሥጋ እንኳ እንደየወገኑ የተለያየ ነው። (ዘፍጥረት 1:​20-25) “ሰማያዊ አካል” ያለው መንፈሳዊ ፍጡር ሥጋ ከሆነ “ምድራዊ አካል” በክብር ይለያል። በተጨማሪም ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ያላቸው ክብር ይለያያል። ይሁን እንጂ ከሞት የተነሡ ቅቡዓን እጅግ የላቀ ክብር ይኖራቸዋል።

13. በ⁠1 ቆሮንቶስ 15:​42-44 መሠረት የሚዘራውና የሚነሣው ምንድን ነው?

13 ጳውሎስ ልዩነቶች እንዳሉ ከጠቀሰ በኋላ “የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው” ሲል አክሎ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:​42-44) እንዲህ ብሏል:- “በመበስበስ ይዘራል፣ ባለመበስበስ ይነሣል።” እዚህ ላይ ጳውሎስ ስለ ቅቡዓኑ በቡድን ደረጃ መናገሩ ሊሆን ይችላል። በሚሞቱበት ጊዜ በመበስበስ የተዘራው ከኃጢአት ነፃ ሆኖ ባለመበስበስ ይነሣል። ምንም እንኳ በዓለም የተናቁ ቢሆኑም ለሰማያዊ ሕይወት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋር በክብር ይገለጣሉ። (ሥራ 5:​41፤ ቆላስይስ 3:​4) ሲሞቱ “ሥጋዊ አካል” ይዘራል፤ ከዚያም “መንፈሳዊ አካል” ይነሣል። ይህ በመንፈስ በተወለዱ ክርስቲያኖች ላይ ሊፈጸም እስከቻለ ድረስ ሌሎች ደግሞ በምድር ላይ ለመኖር ሊነሡ እንደሚችሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

14. ጳውሎስ ክርስቶስን ከአዳም ጋር ያነጻጸረው እንዴት ነው?

14 በመቀጠል ጳውሎስ ክርስቶስን ከአዳም ጋር አነጻጽሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:​45-49) ፊተኛው ሰው አዳም “ሕያው ነፍስ ሆነ።” (ዘፍጥረት 2:​7) “ኋለኛው አዳም” ማለትም ኢየሱስ ‘ሕይወት የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።’ በመጀመሪያ ደረጃ ሕይወቱን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ የሰጠው ለቅቡዓን ተከታዮቹ ነው። (ማርቆስ 10:​45) ሰው እያሉ ‘የመሬታዊውን መልክ የለበሱ’ ሲሆን ከሞት በሚነሡበት ጊዜ ግን እንደ ኋለኛው አዳም ይሆናሉ። እርግጥ ነው፣ የኢየሱስ መሥዋዕት በምድር ላይ ከሞት የሚነሡትን ጨምሮ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ጥቅም ያስገኛል።​—⁠1 ዮሐንስ 2:​1, 2

15. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሥጋ ለብሰው የማይነሡት ለምንድን ነው? በኢየሱስ መገኘት ወቅትስ ከሞት የሚነሡት በምን ሁኔታ ነው?

15 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሞቱ በኋላ የሚነሡት በሥጋ አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 15:​50-53) ሥጋና ደም የሆነ የሚበሰብስ አካል ያለ መበስበስን ባሕርይ እና ሰማያዊውን መንግሥት ሊወርስ አይችልም። አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለረጅም ጊዜ በሞት አንቀላፍተው መጠበቅ አያስፈልጋቸውም። በኢየሱስ መገኘት ወቅት ምድራዊ ሕይወታቸውን በታማኝነት ሲያጠናቅቁ ‘በድንገት በቅጽበተ ዓይን ይለወጣሉ።’ ያለመበስበስ ባሕርይ እና ክብር ተላብሰው ወዲያውኑ መንፈሳዊ ሕይወት ይዘው ይነሣሉ። በመጨረሻ የክርስቶስ ሰማያዊ ‘ሙሽራ’ ቁጥር 144, 000 ይሞላል።​—⁠ራእይ 14:​1፤ 19:​7-9፤ 21:​9፤ 1 ተሰሎንቄ 4:​15-17

ሞትን ድል መንሣት!

16. ጳውሎስና ጥንት የነበሩ ነቢያት በተናገሩት መሠረት ኃጢአተኛ ከሆነው አዳም የተወረሰው ሞት ምን ይሆናል?

16 ጳውሎስ ሞት ለዘላለም እንደሚዋጥ በድል አድራጊነት ስሜት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:​54-57) የሚበሰብሰውና ሟች የሆነው ያለመበስበስንና ያለመሞትን ባሕርይ ሲለብስ “ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ፍጻሜውን ያገኛል። “ሞት ሆይ፣ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፣ ድል መንሣትህ የት አለ?” (ኢሳይያስ 25:​8፤ ሆሴዕ 13:​14) ለሞት የሚያደርሰው መውጊያ ኃጢአት ሲሆን የኃጢአት ኃይል ደግሞ በኃጢአተኞች ላይ ሞት የሚፈርድባቸው ሕግ ነው። ሆኖም ከኃጢአተኛው አዳም የተወረሰው ሞት ድል አድራጊነት በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ አማካኝነት ያከትማል።​—⁠ሮሜ 5:​12፤ 6:​23

17. የ⁠1 ቆሮንቶስ 15:​58 ቃላት በዛሬው ጊዜ የሚሠሩት እንዴት ነው?

17 ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ስለዚህ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፣ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።” (1 ቆሮንቶስ 15:​58) በዛሬው ጊዜ ያሉ ቅቡዓን ቀሪዎችም ሆኑ የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ቢሞቱ እንኳ እነዚህ ቃላት በእነሱ ላይ ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል። (ዮሐንስ 10:​16) ትንሣኤ ስለሚጠብቃቸው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን የሚያከናውኑት ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ሥራ ከንቱ አይሆንም። የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ‘ሞት ሆይ፣ ድል መንሣትህ የት አለ?’ ብለን በደስታ የምንናገርበትን ጊዜ እየተጠባበቅን በጌታ ሥራ የተጠመድን እንሁን።

ፍጻሜውን ያገኘ የትንሣኤ ተስፋ!

18. ጳውሎስ በትንሣኤ ላይ የነበረው ተስፋ ምን ያህል ጠንካራ ነው?

18 በ1ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት የትንሣኤ ተስፋ በሕይወቱ ውስጥ ኃይል እንደነበረው በግልጽ ያሳያሉ። ኢየሱስ ከሞት እንደተነሣና ሌሎችም ከሰው ልጆች የጋራ መቃብር እንደሚወጡ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር። ይህን የመሰለ ጽኑ እምነት አለህን? ጳውሎስ ለራስ ብቻ በማሰብ የሚገኙ ጥቅሞችን ‘እንደ ጉድፍ የቆጠረ’ ሲሆን ‘ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኃይል ለማወቅ’ ሲልም ‘ሁሉን ነገር አጥቷል።’ ሐዋርያው ‘የመጀመሪያውን ትንሣኤ’ እንደሚያገኝ ተስፋ በማድረግ የክርስቶስ ዓይነት ሞት ለመሞት ፈቃደኛ ሆኗል። ይህ 144, 000ዎቹ የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች የሚያገኙት ትንሣኤ ሲሆን ‘ፊተኛው ትንሣኤ’ ተብሎም ተጠርቷል። ቅቡዓን ከሞት የሚነሡት በሰማይ መንፈሳዊ ሕይወት ለማግኘት ሲሆን ‘የቀሩት ሙታን’ ግን ምድር ላይ ለመኖር ይነሣሉ።​—⁠ፊልጵስዩስ 3:​8-11፤ ራእይ 7:​4፤ 20:​5, 6

19, 20. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግበው የሚገኙ በምድር ላይ ለመኖር ከሞት የሚነሡ ግለሰቦች እነማን ናቸው? (ለ) በጉጉት የምትጠባበቀው የማንን ትንሣኤ ነው?

19 እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ለሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የትንሣኤ ተስፋ አስደሳች እውነታ ሆኖላቸዋል። (ሮሜ 8:​18፤ 1 ተሰሎንቄ 4:​15-18፤ ራእይ 2:​10) ‘ታላቁን መከራ’ በሕይወት የሚያልፉ ሰዎች ‘ባሕር በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሲሰጡና’ የትንሣኤ ተስፋ ምድር ላይ ሲፈጸም ይመለከታሉ። (ራእይ 7:​9, 13, 14፤ 20:​13) በምድር ላይ ለመኖር ከሞት ከሚነሡት ሰዎች መካከል ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆችን በሞት ያጣው ኢዮብ ይገኝበታል። እነሱን ሲቀበል የሚሰማውን ደስታ ገምት! እነሱም ሌሎች ሰባት ወንድሞችና ሦስት የሚያማምሩ እህቶች በማግኘታቸው ምንኛ ይደሰታሉ!​—⁠ኢዮብ 1:​1, 2, 18, 19፤ 42:​12-15

20 አዎን፣ አብርሃምና ሣራ፣ ይስሐቅና ርብቃ እንዲሁም “ነቢያትን” ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሰዎች በምድር ላይ ለመኖር በሚነሡበት ጊዜ እንዴት ያለ በረከት ይሆናል! (ሉቃስ 13:​28) ከእነዚህ ነቢያት አንዱ በመሲሑ አገዛዝ ሥር ከሞት እንደሚነሣ ቃል የተገባለት ዳንኤል ነው። ዳንኤል ለ2, 500 ዓመታት ያህል መቃብር ውስጥ ያረፈ ቢሆንም በቅርቡ በትንሣኤ ኃይል አማካኝነት “በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች” ከሚሆኑት አንዱ ሆኖ ‘በዕጣ ክፍሉ ይቆማል።’ (ዳንኤል 12:​13፤ መዝሙር 45:​16) በድሮ ዘመን የኖሩትን ታማኝ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ጠላት በሆነው ሞት የተወሰዱብህ አባትህ፣ እናትህ፣ ልጅህ ወይም ሌሎች የምታፈቅራቸው ሰዎች ሲመለሱ መቀበሉ ምንኛ አስደሳች ይሆናል!

21. ለሌሎች መልካም ነገሮች በማድረግ ረገድ መዘግየት የሌለብን ለምንድን ነው?

21 አንዳንድ ወዳጆቻችንና የምናፈቅራቸው ሰዎች አምላክን ለዓመታት ያገለገሉና በእድሜ የገፉ ሊሆኑ ይችላሉ። እርጅና የሕይወትን ውጣ ውረዶች ሊያከብድባቸው ይችላል። በአሁኑ ጊዜ የቻልነውን ማንኛውንም ዓይነት እርዳታ መስጠታችን ጥሩ ፍቅራዊ መግለጫ ነው! እንዲህ ካደረግን ሞት ሰለባ አድርጎ ቢወስዳቸው እንኳ በሆነ መንገድ ሳንረዳቸው በመቅረታችን የሚሰማን ጸጸት አይኖርም። (መክብብ 9:​11፤ 12:​1-7፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​3, 8) እድሜያቸውም ሆነ ያሉበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ለሌሎች የምናደርጋቸውን መልካም ነገሮች ይሖዋ እንደማይረሳ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ።”​—⁠ገላትያ 6:​10፤ ዕብራውያን 6:​10

22. የትንሣኤ ተስፋ ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ ምን ለማድረግ መወሰን አለብን?

22 ይሖዋ “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:​3, 4) ቃሉ ከፍተኛ ኃይል ባለው የትንሣኤ ተስፋ የሚያጽናናን ከመሆኑም በላይ ሌሎችን በዚህ ተስፋ ማጽናናት እንድንችል ይረዳናል። ሙታን ምድር ላይ ለመኖር ከሞት ተነስተው የዚህን ተስፋ ፍጻሜ እስክንመለከት ድረስ በትንሣኤ እምነት እንደነበረው እንደ ጳውሎስ እንሁን። በተለይ አምላክ እሱን ከሞት ለማስነሣት ባለው ኃይል ላይ የነበረው ተስፋ የተፈጸመለትን ኢየሱስን የምንመስል እንሁን። በቅርቡ በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ድምፅ ሰምተው ይወጣሉ። ይህ መጽናኛና ደስታ የሚያስገኝልን እንዲሆን ምኞታችን ነው። ከሁሉም በላይ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ሞት ድል እንዲነሣ ላስቻለው ለይሖዋ አመስጋኞች እንሁን!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ጳውሎስ የኢየሱስን ትንሣኤ በተመለከተ ምን የዓይን ምሥክርነት ማስረጃ ሰጥቷል?

• “የኋለኛው ጠላት” ምንድን ነው? የሚሻረውስ እንዴት ነው?

• በቅቡዓን ክርስቲያኖች ረገድ የሚዘራውና የሚነሣው ምንድን ነው?

• መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግበው ከሚገኙት ምድር ላይ ለመኖር ከሞት የሚነሡ ሰዎች መካከል እነማንን ለማግኘት ትጓጓለህ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐዋርያው ጳውሎስ ትንሣኤን በተመለከተ ጠንካራ የመከላከያ ሐሳብ አቅርቧል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢዮብ፣ የቤተሰቡ እና የሌሎች በርካታ ሰዎች ትንሣኤ ወደር የለሽ ደስታ ያስገኛል!